ያኔ በወርሃ የካቲት አብዮቱ ሣይፈነዳ፣ ጭቁኑ ሲመዘበር በበዝባዦች ሲጎዳ እየተባለ ብዙ ተደስኩሯል። ከወርሃ የካቲት አንስቶም ክንዶቻችን ዝለዋል፤ ልሣኖቻችንም እረፍት አጥተዋል – በመፈክር ዓይነትና ብዛት። ያኔ ምን ያልተባለ፣ ያልተዜመ አለ?
“ያለሴቶች ተሣትፎ አብዮት ግቡን አይመታም!” ለዓመታት ክንዶቻችን እስኪዝሉ መፈክሮች አሠምተናል። “ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው!” ጉሮሮአችን እስኪደርቅ ብዙ ጮኸናል። እንዲህም ብለናል – “በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጾታዊ ጥቃቶች ይቁሙ” ብለን አደባባይ ወጥተናል። ግራ እጆቻችንን እያወናጨፍን እሪ ብለናል፤ ዘምረናል። አቡጀዲ ጨርቆች ተወጥረውና በቀለማት ተዥጎርጉረው ከአደባባይ ወጥተን እየተቀባበልን ጭምር ድምጻችንን ከፍ አድርገን ለዓመታት ጮኸናል – በጩኸትና በመፈክር ብቻ ችግሮቹ ይቃለሉ ይመስል።
ዛሬም ድረስ ብዙ የሚነገርለት “ሴቶች የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል ናቸው” አባባል እውነታነት ባያጠራጥርም መሠረታዊ ከሚባሉት ችግሮቻቸው ምን ያህሎቹ ተፋቱ? ምን ያህሎቹስ ሕይወታቸው ተለወጠ? ለመሆኑ ምን ያህሎቹስ ከአስከፊ ኑሯቸው ሣይላቀቁ በአጣብቂኝ ሥቃይና መከራ ውስጥ አሁንም እንዳሉ አሉ? ሥር የሰደዱ እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ምን ጥረቶች ተደረጉ? የሚሉት ጥያቄዎች ሲነሱ አነጋጋሪና ምላሻቸውም የዚያኑ ያህል የራቁ መሆናቸውን ግን ልብ እንበል።
የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሥፍራዎች ይህን መሠል ርዕሰ ጉዳዮችን አስመልክቶ በማስታወሻዎቹ ላይ ያሠፈራቸውን ገጠመኞቹን በእንዲህ መልኩ ሰብሰብ አድርጎ አጠናቅሯቸዋል። ኑሮን ለመግፋት ሲሉ ከአውሬ ጋር እየታገሉ እንጨት ለቅመው በመሸጥ ሕይወትን በእንጦጦ ተራራ ላይ እየገፉ ስላሉ እናቶች ለዛሬው በጥቂቱ እንመልከት።
ይህን ጎዳና ብዙዎች አቀበቱን ወጥተው፤ ቁልቁለቱን ወርደው አንዴም አይደል ደግመው ደጋግመው ተመላልሰውበታል። ጥቂት ለማይባሉቱም የሕይወታቸው ስኬት ቁልፍ ምሥጢር ሆኖ ሰንብቷል። ከግል ጥቅምና ዝና ባሻገር በዓለም መድረኮች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሠንደቅ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ መነሻ ሆኖ ረድቷል። ስመ ገናና ሆነውበታል። ራሣቸውንም በመልካም ሁኔታ ማስተዳደር ችለውበታል።
ከእንጦጦ ተራራ አናት ላይ ሆኖ ቁልቁሉን መላ አዲስ አበባን በስፋት መቃኘት፤ ከዚያም እልፍ ሲል ውስጠ ሚስጢሯን መፈተሽ እጅጉን ይቀላል። ሠማይ ጠቀስ ሕንጻዎቿን፣ ዘመናዊ መንደሮቿ በአንድ በኩል ማሰብ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ጣሪያቸው በድንጋይ ድጋፍ የቆሙ አሮጌ ቤቶች፣ የተጎሣቆሉ መንደሮች ገፅታ ፍንትው ብሎ በህሊና ይመጣል። ታዲያ እንጦጦ የከተማዋ ጀርባ ሸፋኝ፣ የነዋሪዎቿም ተስፋ ሆኖ ዛሬም ድረስ ኖሯል። የብዙዎች ባለውለታ ነው – እንጦጦ።
በእንጦጦ የመሠናዶ ጊዜውን ያላሳለፈ፤ ያን ቀዝቃዛ ንጹህ አየር እየማገ ዝግጅቱን ያላጧጧፈ ኢትዮጵያዊ አትሌት አለ ቢሉኝ እንዴት አድርጌ በተጠራጠርኩ። ብዙዎቹ ወጣት አትሌቶች ዘወትር በእንጦጦ ተራራ ላይ ይሮጣሉ፤ ይወድቃሉ፤ እንደገናም ይነሣሉ፤ ለማለዳው ቁር እጃቸውን ሣይሰጡ ላይ ታች ይላሉ። ላብ በመላ አካላቸው ላይ እንደውሃ እየተንቆረቆረ ድካም ልፋታቸው አይጣል ነው።
ከረጅም ጥረትና ዝግጅት፣ ከብርቱ ሥራ በኋላ የድል፣ የሻምፒዮናነት አክሊልን በአናታቸው ደፍተው “እንዲህ ነው እንጂ የአገሬ ጀግና”ን አስዚመው፤ ወገን ፈንድቆ በእልልታ ሲቀበል በሕዝብ መሐል በኩራት ቆሞ የመገኘት ታላቅ – ስኬት የሚመጣው ከዚህ ለጥቆ ነው።
የእነኚህ እግሮች ግን ከእነኚያዎቹ ይለያሉ። በኦሎምፒክ አሊያም በዓለም የሻምፒዮና መድረኮች ሮጠው በወርቅ፣ ብርና ነሐስ ሜዳሊያዎች አይንቆጥቆጡ፤ ጠቀም ያለ የገንዘብ ሽልማቶችን አያግኙ እንጂ ለኑሯቸው መሠረት ሲሉ እነርሱም ሁሌም በእንጦጦ አንግተው፣ ውለው ያመሻሉ። እንጦጦን የማይረግጡበት እለት የለም።
ስንቶች ጎጇቸው እንዳያዘም፣ ቤተሰቡም ሠብሳቢ አጥቶ እንዳይበተን በብዙ ጥረዋል –ደክመዋል። የሌላ እጅ ጠባቂ ላለመሆን ላባቸው በጀርባቸው እየፈሰሰ ለዚያውም ሸክም ተጨምሮበት ክንድ እግሮቻቸው እየዛሉ በየጥሻው ባዝነዋል። ያገኟትንም አሣስረው ወጥተው ወርደዋል፤ ከእንጦጦ ጋር ቁርኝታቸው ለዓመታት ዘልቋል። ከመኖሪያ ቀያቸው – እንጦጦ፤ ከእንጦጦም ያሠባሰቧትን በትከሻቸው ይዘው ገዥ አግኝተው እስኪቀናቸው በመሐል ከተማ ሣይቀር ተዛዙረዋል።
ሕይወት ፈተና ብትሆንባቸውም ከእንጦጦ ተሻርከው፤ ብርታትንና ጥንካሬን ተላብሰው በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በየእለቱ እስከ አርባ ኪሎ ሜትር ረጅሙን መንገድ በእግር ጉዞ ዘልቀዋል። መመላለሱ፣ ላይ ታች ማለቱ የኑሮ እጣ ፋንታ ሆኖባቸዋል።
በሽሮ ሜዳ ወፍ ገና አልተንጫጫም፤ ሌቱም ቢሆን ለንጋት ሥፍራውን ለመልቀቅ አልተሠናዳም። የቤተሠቡ የእለት ጉርሥ የማሠናጃ ወቅት ነው። ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ግን ሥማቸው የተቀየረ ወይዘሮ አዛለች መኖሪያ ቤታቸው በጢስ ተሟሙቃለች።
የቤት ውስጥ ጣጣውም የወደቀው በወይዘሮዋ ትከሻ ላይ ነው። ቀን ላይ የሚቋደሷትን ቆጣጥረው፣ የሚጠጧትን ይዘው፣ የሥራ ትጥቃቸውንም አሠማምረው ለሊቱ አሥር ሰዓት ከመሆኑ በፊት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ሥራ እንዲህ ከውነው ለአድካሚው ቀጣይ እለታዊ ተግባር መንደራቸውን ለኋሊት ትተው ጉዟቸውን ይያያዙታል – ወደ እንጦጦ።
በዚያች መንደር የወይዘሮዋን ሥራ የሚጋሩ፣ በሚያገኟት አነስተኛ ገቢ ቀሪ ሕይወታቸውን የሚገፉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶች አሉ። ሴቶቹ ቀን ከሌት ይለፋሉ፣ ይጥራሉ፤ በየቋጥኙ ለእንጨት ለቀማ ጎንበስ ቀና ይላሉ። ለማገዶ የሚውል እንጨትም ተሸክመው ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ።
የእንጨት ተሸካሚ ሴቶች ሕይወት ጣጣው ብዙ ነው። ድካም ልፋቱም የዚያኑ ያህል ነው። በዚህ ብቻ መቼ አበቃና። ሠው ሰራሹ ችግርም ሌላው ፈተና ነው። ለመከራ ተጋላጭነታቸውም የዚያኑ ያህል የከፋ ነው። የእንጦጦን ጫካ የአንድ ቀን ክሥተት ላወጋችሁ ስወስን ከራሴ ጋር ሙግት ገጥሜያለሁ፤ ብዙ አውጥቼ አውርጄያለሁ።
በሴቶች ላይ የሚደርሰው አካላዊና ሞራላዊ ጉዳቱ የቱን ያህል ዘግናኝ መሆኑን ማኅበረሰቡ በግልጽ ያውቀው ዘንዳ የቅርብ ወዳጆቼ “ግዴለህም ጻፈው” ብለው ስላደፋፈሩኝ ሕሊናዬ እየደማም ቢሆን በሐሳባቸው ተስማማሁ።
ነገሩ እንዲህ ነው። ውሎና አዳሯን በእንጦጦ ያደረገች እመጫት አራስ ልጇን በአንቀልባ ታቅፋ እንጦጦ ጫካ ትወርዳለች። መደበኛ እለታዊ ተግባሯን ለመከወን የእንጨት ማሠሪያ ገመዷን ሸክፋ፣ ሕፃን ልጇን ከዛፍ ጥላ ሥር አስተኝታ ወደሥራዋ ተሠማርታለች።
አድካሚውን የእንጨት ለቀማ ሸካክፋ ስትመለስ ሕጻኑ የለም። ከተጠቀለለበት ጨርቅ በቀር ያገኘችው አንዳች ነገር አልነበረም። ለካንስ በአውሬ ተወሥዶ ኖሯል፡፡ ዕድሜ ልክ ከአዕምሮ የማይጠፋ ልብን የሚሠብር ዘላለማዊ ፀፀት። የእናት አንጀት ስንቱን ችሎ ኖረ ያስብላል።
የኑሮ ውጣ ውረዱ የዚህን ያህል አስቸጋሪ ነው። ሊቋቋሟቸው የሚከብዱ ችግሮችን መጋፈጡ፤ ለተለያዩ ማህበራዊ ጥቃቶች መጋለጡ ብዙዎች ሴቶች የሚጠብቋቸው ዕለታዊ ክስተቶች ናቸው።
በዚህ ዓይነቱ በማያወላዳ የኑሮ ዑደት ውስጥ ሕይወታቸውን እየመሩ ያሉ ስንቶች ይኖሩ ይሆን? እርግጥ ነው በርካቶች አሉ። የማገዶ እንጨት ለቅመው፣ ተሸክመውና ሸጠው ቤተሠብ ከማስተዳደር አልፈው ልጆቻቸውን ኮሌጅ አስገብተው ለወግ ማዕረግ ያበቁም እንዳሉም አንዘንጋ። ከዚህ አድካሚ ሥራ ተላቀው በሌላ የተሻለ ሙያ ዘርፍ በመሠማራት በኑሯቸው ለውጥ ማየትን የጀመሩ ጥቂት የማይባሉ እንዳሉም እንዲሁ። ለዚህ አጋዥ የሆናቸው ደግሞ በጥቅምት ወር 1989 “የቀድሞ እንጨት ተሸካሚ ሴቶች” በሚል የመሠረቱት ማህበር ዋነኛው ነው።
በተሻለ ሥራ የተሻለ የገቢ ምንጭ ፈጥረው የራሣቸውንና የቤተሠቦቻቸውን ሕይወት ለመለወጥ በሽመና፣ በቃጫና በጓሮ አትክልት ልማት ሥራዎች የተሠማሩም አሉ። በቅርቡ እንኳን የእንጦጦ ፓርክ ሲመሠረት በተፈጠረ የሥራ ዕድል ቀዳሚ ተጠቃሚ የሆኑት የማገዶ እንጨት ለቅሞ አዳሪ ሴቶች ናቸው። እነዚህን ከዚያ እጅግ አድካሚ ከሆነ ሥራ አላቅቆ በሌላ አማራጭ የገቢ ማስገኛ ተግባር ላይ የማሣተፍ ዓይነቱ በጎ ተሞክሮ ተጠናክሮ ቢቀጥልስ።
ጋሻው ጫኔ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013