መቀመጫውን በሀዲያ ዞን በሆሳዕና ከተማ ያደረገው “ዲ ማይንድ” ቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ የሰራው መሳሪያ መኪናን ከኮሮና ቫይረስ በጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል ለማጽዳት የሚያስችል ነው። ሰዎች በእጃቸው ሳይነኩ የመኪናን የውስጥ እና ውጫዊ ክፍል በጸረ ኮሮና ኬሚካል ለማጽዳት የሚያገለግል ነው። መሳሪያው በተለያዩ መነኸሪያዎች እና ተቋማት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
መኪናን በጸረ ተህዋሲ ኬሚካል ከኮሮና ቫይረስ የሚያጸዳው መሳሪያ በ20ዎቹ እድሜ ውስጥ በሚገኝ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ወጣት ዲንሰፋ ሁሴን የተሰራ ነው። ወጣት ዲንሰፋ ከልጅነቱ ጀምሮ ለቴክኖሎጂ ነክ ሥራዎች ልዩ ፍቅር ነበረው። የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ከነበረበት ወቅት ጀምሮ የተለያዩ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን ሰርቷል። በተለይም ዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ የሰራቸው ሥራዎች እራሱን እና ትምህርት ቤቱን ስም ማስጠራት ችሏል።
ጠጣር ማዕድን ከአፈር መለያ፣ ወተት መናጫ፣ ጣውላ ማለስለሻ፣ የከብት መኖ ማቀነባበሪያም እንዲሁም ቆሻሻ ማንሻ መሳሪያዎችን ሰርቷል። ለዚህም ከተለያዩ አካላት የተለያዩ እውቅናዎችና ሽልማቶች ተበርክተውለታል። “ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በምማርበት የካቲት ትምህርት ቤት ውስጥ በሰራሁት ወተት መናጫ፣ ጣውላ ማለስለሻ፣ ጠጠር ማዕድናትን ከአፈር መለያ ቴክኖሎጂ እና በቆሻሻ ማጽጃ ቴክኖሎጂ ምክንያት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እጅ የተቀበልኩት ሽልማት ትልቁ ሽልማት ነው። ለቴክኖሎጂ ሥራዎች ያለኝ ፍቅር ከፍ እንዲል ያደረገም ነው” ይላል።
ከዚያ በኋላ በተለያየ ምክንያት ከቴክኖሎጂ ሥራዎች ርቆ መቆየቱን የሚናገረው ወጣት ዲንሰፋ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለፈጠራ ሥራ ያላቸው ቦታ ትልቅ ስለሆነ ተመልሶ ወደ ፈጠራ ሥራ እንደተመለሰ ይናገራል። “ለረጅም ጊዜ ከቴክኖሎጂ ሥራዎች ርቄ ከቆየሁ በኋላ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ ውስጥ ስለ ፈጠራ እና ስለቴክኖሎጂ የተሰጠው ቦታ ካለፉት ጊዜያት የበለጠ ከፍ ያለ መሆኑን ሳይ ተመልሼ ወደ ፈጠራ ሥራ ገባሁ” ሲል ዳግም ወደ ሥራው እንዲመለስ ምክንያት የሆነውን መነሳሳት ያብራራል።
ከአንድ ዓመት በፊት “ዲ ማይንድ” ቴክኖሎጂ የተሰኘ ኢንተርፕራይዝ አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን መስራት ቀጥሏል። በዋናነት ከግብርና ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሳሪያዎችን ለማምረት እቅድ ይዞ ወደ ሥራው መመለሱን የሚያብራራው ወጣት ዲንሰፋ፤ በመሃል ግን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ከማምረት ጎን ለጎን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቴክኖሎጂዎችን ማምረት መጀመሩን ያብራራል።
መኪና ለማጽዳት የሚያገለግለው ቴክኖሎጂ ሰዎች መኪናን በእጃቸው ሳይነኩ የመኪናውን ውስጠኛ ክፍል ከኮሮና የሚያጸዱበት ነው። መሳሪያው በመኪና ውስጥ ሰዎች በእግራቸው የሚረግጡትን እና በእጃቸው ይነካሉ ተብሎ የሚታሰቡ ቦታዎችን የእጅ ንክኪ ሳይኖረው በኬሚካል ከቫይረሱ ማጽዳት የሚያስችል ነው። ውስጠኛውን ክፍል አጽድቶ ከጨረሰ በኋላ ደግሞ የመኪናውን ውጫዊ ክፍል በኬሚካል በማጽዳት መኪናውን ሙሉ በሙሉ ከኮሮና ቫይረስ ነጻ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ነው።
መኪናን ከኮሮና ቫይረስ ለማጽዳት የሚያገለግለውን መሳሪያ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ድንበር ድረስ የሚገጠምበት መስመር ተመቻችቶ ተገጥሞ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ያብራራል። በተጨማሪም የተለያዩ መናኸሪያዎች ላይ፣ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በሆሳዕና ከተማ ውስጥ በሚገኘው የንግስት እሌኒ ሞሃመድ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ ተገጥሞ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ይናገራል።
የኬሚካል መርጫው በሚይዘው ኬሚካል መጠን የሚለያይ መሆኑን ያብራራው ወጣት ዲንሰፋ ፤ብዙ ኬሚካል መያዝ የሚችሉትን ከፍ ባለ ዋጋ ሲሸጥ፤ ዝቅተኛ ኬሚካል የሚይዙትን ደግሞ በዝቅተኛ ዋጋ ይሸጣል። አንዱን የጸረ ኮሮና መድሃኒት መርጫ ከ35 እስከ 45 ሺህ ብር እየሸጡ እንደሚገኙ የጠቆመው አቶ ዲንሰፋ፤ በርካቶች ገዝተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን ጠቁሟል። 20 ፍሬ ማሽኖችን ሸጧል። ከ20 ፍሬ ውስጥ 10ሩን በ45 ሺህ የሸጠ ሲሆን የተቀረውን 10ሩን ደግሞ በ35 ሺህ ብር መሸጡን ጠቁሟል።
ተቋማቱ ገዝተው መጠቀም ከጀመሩ ከአምስት ወራት በላይ መቆጠሩን የጠቆመው ወጣት ዲንሰፋ፤ እስካሁን ድረስ ያለአንዳች ችግር መሳሪያዎቹ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጿል። መሳሪያዎቹን እየተጠቀሙ ያሉ ተቋማትም መሳሪያው ምቹ እንደሆነ ገልጸውለታል።
ዲንሰፋ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ የዛሬ ዓመት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።ተማሪ በነበረበት ወቅትም ከትምህርቱ ጎን ለጎን ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመደራጀት በጊቢው የሚገነቡ ህንጻዎች ግንባታ ላይ ይሳተፍ ነበር። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በግንባታ ሥራ ላይ መሰማራቱ አሁን ለሚሰራቸው የቴክኖሎጂ ሥራዎች መጀመሪያ የሚሆን ጥሪት እንዲቋጥር እንዳስቻለው ይናገራል።
“በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ ሆኜ ከትምህርቴ ጎን ለጎን ሥራ በመስራት ያጠራቀምኩት 500 ሺህ ብር ገደማ ገንዘብ በቅርቡ መኪናዎችን ከኮሮና ለማጽዳት የሚያስችል መሳሪያ እና የግብርና መሳሪያዎችን ያለ ገንዘብ ችግር እንድሰራ ረድቶኛል። እንደሌሎች ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ችግር ተግዳሮት አልሆነብኝም” ይላል።
በሆሳዕና ከተማ ውስጥ የሚገኘው የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የቴክኒክና ሙያ ድጋፎችን በማድረግ እገዛ እንዳደረገለት የጠቆመው ዲንሰፋ፤ በተለይም ኢንተርፕራይዙ መስራት የፈለጋቸውን የቴክኖሎጂ ሥራዎች ንድፍ በመገምገም፣ በግለሰብ እጅ ላይ የማይገኙ ማሽኖችን ዲንሰፋ በፈለገበት ሰዓት እንዲጠቀም በመፍቀድ እገዛ እያደረገለት መሆኑን ነው ያብራራው። እገዛውም ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የላቀ ሚና መጫወቱን አብራርቷል።
እንደ ወጣት ዲንሰፋ ማብራሪያ ከስሩ ሰራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ ይገኛል። የኮሮና መድሃኒት መርጫ ማሽን በሚሰራበት ወቅት ከ20 በላይ ሰራተኞችን ቀጥሮ ሲያሰራ እንደነበር ጠቁሟል። በአሁኑ ወቅት ከኮሮና መድሃኒት መርጫ ወደ ግብርና ቴክኖሎጂዎች ማምረት ዞሯል። በአሁኑ ወቅት የግብርና ቴክኖሎጂዎች ላይ ከሱ ጋር አብረው የሚሰሩ ሰባት ተቀጣሪ ሰራተኞች አሉ።
ዲ ማይንድ ኢንተርፕራይዝ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ የግብርና መሳሪያዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ያብራራው ዲንሰፋ፤ ከሀገሪቱ ህዝብ ከ80 በመቶ በላይ ህዝብ የተሰማራበት ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን ግብርና ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኝ መሆኑን በማሰብ በግብርና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት መጀመሩን ያብራራል።
በቅርቡ ሶስት የግብርና መሳሪያዎችን መስራቱን ያብራራው ዲንሰፋ፤ ከነዚህ ሁለቱ ማሳን ውሃ ማጠጫ መሳሪያዎች ሲሆኑ አንዱ ደግሞ ጸረ ተባይ መርጫ መሳሪያ መሆኑን ጠቁሟል። አንደኛው 360 ካሬ ሜትር ሊያጠጣ የሚችል ውሃ መርጫ (ሰፕሬየር) ሲሆን ፤ውሃ ማጠጫ ማሽኑ ጎማ ያለው ነው። በጎማው አማካኝነት ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ይቻላል። በአንድ ቦታ ላይ ሆኖ 360 ካሬ ካጠጣ በኋላ ቦታ በመቀየር ሌላ 360 ካሬ ማጠጣት ይቻላል።
ሁለተኛው ደግሞ አንድ ቦታ ላይ በመቀመጥ እስከ 40 ካሬ ማሳ ውሃ ማጠጣት የሚችል ሰፕሬየር ነው። ሶስተኛው ሁለት ጎማ ያለው እና በሰው እጅ መንቀሳቀስ የሚችል ሰባት ሜትር ድረስ ያለውን የአንበጣ መንጋም ሆነ ማጥፊያ ጸረ ተባይም ሆነ ሌሎች ፀረ አረሞችን መርጨት የሚችል መሳሪያ ሰርቷል።
የግብርና መሳሪያዎች የዘርፉን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው። በተለይም ውሃ መርጫ መሳሪያዎቹ ዝናብን ሳይጠብቁ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ማምረት ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ጠቃሜታ አለው።
መሳሪያዎቹ ተሰርተው ካለቁ ገና አራት ወር እንደሆነ ጠቁሟል። ወደ አርሶ አደሩ አልቀረበም። መሳሪያዎቹ በቅርቡ በቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የቴክኖሎጂ ውድድር ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ሲቀርብ የመጀመሪያው ነው። የተለያዩ አካላት አብረው ለመስራት ጥያቄ እያቀረቡ ነው። በርካቶች መሳሪያዎቹን ገዝተው ለመጠቀም ጥያቄ እያቀረቡ ነው። ከነዚህ አካላት ጋር በመሆን ቴክኖሎጂዎቹን በስፋት በማምረት ለአርሶ አደሩ በስፋት ለማቅረብ እቅድ እንዳለው ወጣቱ ይናገራል።
ኢንተርፕራይዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶቹን በሽያጭ ለማቅረብ ማቀዱን የጠቆመው ዲንሰፋ፤ 360 ካሬ ልታጠጣ የምትችለውን ማሽን በ22 ሺህ ለመሸጥ፣ 40 ካሬ የሚያጠጣውን በ250 ብር እንዲሁም አምበጣና የተለያዩ ጸረ ተባዮችን ማጥፊያ መሳሪያ በ17 ሺህ ብር ለመሸጥ ተመን አውጥቷል።
ሥራውን በሚሰራበት ወቅት የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን ያብራራው ዲንሰፋ፤ ዋነኛው እና አንደኛው ችግር የማስተዋወቅ ችግር አለ። ማስተዋወቅ ባለመቻሉ በተለይም በግብርና ዙሪያ የሰራቸው የቴክኖሎጂ ሥራዎች በሚፈልገው ልክ ሊተዋወቁለት አልቻሉም። አብዛኛው ህዝብ በግብርና ሥራ የሚተዳደርበት የሀዲያ ዞን አስተዳደር ቴክኖሎጂዎቹን በማስተዋወቅ አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙ ማበረታታት የሚገባው ቢሆንም የዞኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንዳልሆነ ተናግሯል።
የዞኑ መንግሥት አስፈላጊውን የማስተዋወቅ ሥራ ካልሰራ በራሱ አቅም ብቻ ቴክኖሎጂዎቹን ለአርሶ አደሮች ማስተዋወቅ ከባድ መሆኑን ያብራራው ወጣት ዲንሰፋ፤ በቀጣይ ጊዜያትም የዞኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ማሽኖቹ ወደ አርሶ አደሮች የሚደርሱበትን ሁኔታ ቢያመቻች ፋይዳው የላቀ ነው ብሏል።
ወደ ፊት ግብርናው ላይ ትኩረት አድርጎ የመስራት እቅድ አለው። አብዛኛው አርሶ አደር የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዓመት ሶስቴ የሚያመርትበት እቅድ መፍጠር እቅዱ እንደሆነ ነው ያብራራው። ሥራዎቹን ከሀዲያ ዞን ባሻገር በመላ ሀገሪቱ የማስፋፋት ውጥን እንዳለው ጠቁሟል።እኛም ያሰበው ይሰምር ዘነድ ተመኘን።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2013