ማነቆ ነው።ኢትዮጵያ ላለማደጓና ያላትን ከፍተኛ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባበቡ ላለመጠቀሟ አንዱ ምክንያት ስንፍና መሆኑም ይነገራል። ለመሆኑ ከግለሰብ እስከ ሀገር መገለጫችን ከሆነው ስንፍና ለመውጣት ምን ማድረግ ይጠበቃል ስንል የማህበራዊ ሳይንስ አመራርና ባለሙያ የሆኑትን አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ስንፍና ለግለሰብ አሳሪ ልምድ ለአገርና ለህዝብ ደግሞ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነው።ስንፍና ማለት ምንም ለማድረግ ባለመፈለግ ውስጥ ብዙ ለማሰብና ለማግኘት የሚደረግ የተግባር ድህነት ነው።ስንፍና ምኞተ ብዙ ድርጊተ ደሃ መሆን ማለት ነው።ስንፍና በሃይማኖታዊ ዕይታው ሃጢያት እንደማለት ነው።
ስንፍና እጅንና እግርን አሳስሮ የሌለው እንደሚመጣ በማሳመን ጉጉት የሚያከስር በሽታ ነው።ወይም እግርና እጅን በመንጠቅ አፍ ብቻ ወይም ወሬ-መር ለሆነ ህይወት ይዳርገናል።ስንፍና ተግባርና ድርጊት ጠል የሆነ በሽታ ሲሆን የሚያመውም የተግባራዊ ድርጊት ትዕዛዝ ማስፈጸሚያ አስተሳሰባዊ ክፍላችንን ነው።ስንፍና እንደ ግለሰብ መታከት፣ መሰልቸትና ጉጉት ማጣት መገለጫዎቹ ሲሆን እንደሀገር ብልሹ አሰራር፣ ሙስናና ብክነት ደግሞ ፍሬዎቹ ናቸው።
የስንፍና መንስኤዎች
1. አለአግባብ እርዳታን መፈለግና ጥገኛ መሆን፡- ካለበቂ ምክንያት የሚደረግ ማንኛውም እርዳታ ግለሰብንም ሆነ ህዝብን ለተለያዩ ስንፍና የሚዳርግ ነው።እጅግ በጣም አስፈላጊ ሆነው ካልተገኙ የቤተሰብ እርዳታ፣ የምግብ እርዳታ፣ የማዳበሪያ እርዳታ ወዘተ ከፍተኛ የስንፍና ማዳበሪያዎች ናቸው።እርዳታ ከልመና በኋላ የሚገኝ መልስ ሲሆን ልመና ደግሞ ስራ ሆኖ ስንፍናን በማስተማር የሰውን ልጅ ለህሊና ባርነት የሚዳርግ ይሆናል።
2. የአደገኛ እጽ ሱሰኝነትና ጥገኝነት፡- የአደገኛ እጽ ሱሰኝነትና ጥገኝነት ስንፍናን ባህሪ የማድረግ አስተዋጽኦ አለው።አደገኛ እጽ አካልን የማድከምና የማዛል ባህሪ ስላለው፣ እንቅልፍን ስለሚነጥቅ ወይም ሥርዓቱን ስለሚያዛባ እንዲሁም ለመጠቀም ጊዜ ስለሚፈልግ ወይም ስለሚሻማ እና መጥፎ ባህሪዎችን የመውለድ አስተዋጽኦ ስለአለው ተደምሮ ስልቹ፣ ግዴለሽ፣ ወሬኛ፣ ተገዥ በማድረግ ለስንፍና ይዳርጋል።ስለዚህ አደገኛ እጽ ሱሰኝነት አዕምሮንና አካልን በማላሸቅ ለተግባር ያለንን ተነሳሽነት በመንጠቅ ለስንፍና ይዳርገናል።
3. ለስራ ያለን የተሳሳተ ግንዛቤ፡- ራስን መመገብ ብቻ አዕምሮን ስንፍና የሚያስተምር የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። ለምሳሌ ስለስራ ባለን የተዛባ ግንዛቤ ብዙዎቻችን ስራ የገንዘብ ምንጭ ብቻ ይመስለናል።ስለዚህም ስራ እንንቃለን፣ እንመርጣለን ወይም እናናንቃለን።እውነታው ግን ስራ ስንሰራ ከገንዘብ ባለፈ ጤና፣ እድሜ፣ ክብር፣ ዝና፣ እድገትንና መሰል ነገሮችን ያስገኝልናል።
4. ተግዳሮትን፣ ውድቀትንና ትችትን መፍራት፡- ተግዳሮትን፣ ውድቀትንና ትችትን መፍራት በድምሩ ፍርሃት ስንፍናን ይወልዳል።የሚፈራ ሰው አይሞክርም፣ ለውጥ ያስጨንቀዋል፣ ሰዎችን ይፈራቸዋል። በመሆኑም ምንም ነገርን ከመሞከር ይልቅ ነገሮችን ባሉበት ለመቀበልና ለማማረር እድል ይፈጥራል።
5. የጊዜን ዋጋ መረዳት አለመቻል፡- የግዜን ዋጋ በአግባበቡ መረዳት ያልቻለ ለበኋላ፤ ለነገ ለሌላ ጊዜ በሚሉ ምክንያቶች ያለስራ ይቀመጣል። እንዲህ አይነት ሰው ነገ ሌላ የራሱ ጉዳይ እንዳለው ስለማይረዳ በስንፍና ውስጥ ሆኖ ጉዳዮችንና ስራዎችን ራሱ ከመስራት ወይንም ከመሞከር ይልቅ በራሱ ላይ በመደራረብ አንድም ለመተው አልያም የሌሎችን እርዳታ ለመጠየቅ ይገደዳል።
የስንፍና ጉዳቶች
ስንፍና ውርደትን፣ በሽታን፣ ኪሳራን፣ ጥገኝነትን፣ ብክነትን እና ድህነትን ስቦ የማምጣት ሃይል ያለው ሲሆን ሰዎችን ስራ ፈት በማድረግ፡-
1. ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል። በዚህም ከአካላዊ ወይም ለመጠን አልባ ውፍረት መዳረግ፣ ለድንዛዜ መጋለጥና ለልብ ህመም፣ የደም ግፊት፣ ስኳርና ተያያዥ የበሽታ አይነቶች እንዲጠቁ ያደርጋል።
2. ድሃ ያደርጋል። ይህም ለተመጽዋችነት፣ ለማኝነት ወይም እንደሀገር የእኔ ቢጤ ለምንላቸው መብዛት ይዳርጋል።በውስጡም ሰብአዊ ክብርን፣ ዝናን፣ ተመስጋኝነትን፣ ተወዳጅነትን በመንጠቅ ለጥገኝነትና ተለጣፊነት ይዳርጋል።
3. አስተሳሰብን እንዳያድግና እንዳይሻሻል በማድረግ ለአስተሳሰብ ድንዛዜና መዛግ ይዳርጋል። ሰነፍ ቁጭ ብሎ ሌሎች የሚሰሩትን መተቸት፣ አቃቂር ማውጣት፣ ማጣጣል ወይም ማናናቅ በመዳረግ አስተሳሰቡ እንዳይሰራ፣ የድርሻውን እንዳይወጣ ወዘተ በማድረግ ለድንዛዜና ይዳርጋል።
4. አቋራጭ መንገድ እንድንከተል ያደርገናል።በዚህም ትክክለኛውን መንገድ ከመከተል ይልቅ አጭር፣ ደንብና መርህን መጣስ አማራጭ መንገድ ስለምናደርግ በውጤቱ ለሌብነት፣ ለሙስና፣ ለቡልሹ አሰራር፣ ለንብረት ውድመትና መባከን ይዳርጋል።
መፍትሔዎቹ
1. በራስ መጨከን፡- ራስን ማቅበጥ፣ ራስን ማማረጥ፣ ራስን ማሳረጥ፣ ራስን ማዳከም ወዘተ ለስንፍና አሳልፎ ይሰጣቸዋል።ከተመቸን፣ ከምንናፍቀው፣ ከሚያዝናናን፣ ከለመድነው፣ ወዘተ ላይ አዎ ወይም አይሆንም ከሚሉት ምርጫዎች አንዱን መርጦ በጽናት ራስን ለመምራት መዘጋጀት።
2. መረጃን መምረጥ፡- ወደ ውስጣችን የምናስገባው ወይም አዕምሮአችንን የምንመግበውን እያንዳንዱ መረጃ መምረጥ መቻል።ምክንያቱም የስህተት ትምህርትና የውሸት መረጃ ስንፍናን ስለሚወልድ ለራሳችን የእውነት እውቀትን መመገብ።
3. ድጋፍና ማበረታቻን መሻት፡- ካለንበት ችግር ለመውጣት ለጀመርነው፣ ለምንሞክረው ወይም እየጣርን ላለንበት ነገር ከእርዳታ ይልቅ ድጋፍና ማበረታቻ ለመቀበል መዘጋጀት።
4. ለራስ የሚሰጥን ዋጋ ከፍ ማድረግ፡- ራስን ማነቃቃት ወይም ማበረታታት፣ ማድረግና መስራት እችላለሁ በሚል እሳቤ ለራስ ተስፋ መስጠት፣ አቅምን መፍጠርና ለራስ የሚሰጥን ዋጋ ከፍ ማድረግ፤
5. መስጠትን መልመድ፡- ከመቀበል ይልቅ መስጠትን መልመድ ከስንፍና ለመውጣት ይረዳል
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2013