ድሮ ድሮ … እንዳንልም አልራቀም፤ ዛሬ ዛሬ … እንዳንልም ዛሬ አይደለም። መሀል ላይ ያለው እንዳንል ተገቢው የመሀል ቦታ ላይ አይደለም ያለው። እናስ? ዝም ብለን እንቀጥል።
በእርግጥ ጉዳዩ የቅርብ እሩቅ እንጂ የሩቅ እሩቅ አይደለም። እስከ 1980ዎቹ ድረስ በ”ሕይወት” የነበረና ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሥነልቦናዊ አገልግሎትን ሲሰጥ የቆየ አካታችና ወደፊታዊ ጽንሰ-ሀሳብ ነው – ኢትዮጵያ ትቅደም!!!
ሐረጉ ከጽንሰ-ሀሳብም ባለፈ ፍልስፍና ነው። ከዛም በላይ ደግሞ ለዘመናት የዜጎች መመሪያ፣ የአገር የወደፊት አቅጣጫ መጠቆሚያ፣ የጋራ ርእይ መሰነቂያና የጋራ ግብ መድረሻ፤ እጣ ፈንታ (ዴስቲኔሽን)ም ነው (ወይም ነበረ)።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለምርጫ መቀስቀሻቸው ቁልፍ የምርጫ መሳሪያ አድርገው እንዳ’ዲስ አሜሪካ ትቅደም “America First” እና ታላቋ አሜሪካ “Great America” በማለት ፍራሹን አደሱት እንጂ ፍልስፍናው ቀድሞም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረና የተከበረ እሴት ነው። እሴትነቱ ደግሞ የአገር፤ የአጠቃላይ ህዝቡ ብቻ ሳይሆን የዓለም በተለይም የጥቁር ህዝቦች አለኝታና መከታም ነው (ወይም ነበረ)። ለዚህ ደግሞ ምስክራችን የመላው ጥቁር ህዝቦች ትግልና ውጤቱ፤ እንዲሁም የመታገያው ፍልስፍና ስያሜ “ኢትዮጵያዊ”ነት የሚለው ነው – Ethiopianism!!!
“ኢትዮጵያ ትቅደም” የዜጎች የጋራ ስትራቴጂክ እቅድ፣ አሻግሮ ማያ መነፅር፣ የትውልድ ቅብብሎሽን አመላካች፣ የማንነት መገለጫና ማሰሪያ፤ የጋራ ህልም፣ ስንቅ፣ ኩራትና ማንነት፤ ትውልድ መቅረጫ፣ መሻገሪያ ድልድይም ነው (ወይም ነበረ)።
በፈረንጆቹ ጃንዋሪ 1975 በ120ዎቹ የደርግ አባላት (መንግሥት) በተዘጋጀ ረዘም ያለ ፖሊሲ ሰነድ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ መልክ መገለፁ የሚነገርለት “ኢትዮጵያ ትቅደም” የነገ ታሪክ ዛሬ እንዲፃፍ/የስራ እድል የሚሰጥ፣ ኢትዮጵያን ያስቀደሙ የአያት ቅድም አያቶቻችን ተጋድሎ የሚዘከርበትና ውርሳቸው (“ሌጋሲ”ያቸው) በክብር የሚተላለፍበት፣ በጋራ ለጋራ ጥቅም የመስራት መሰረት የሚጣልበት፣ ከእኔነት እኛነት፣ ከ”ኬኛ” ፖሊቲክስ ይልቅ “የ’ኛ” ሰብእና ፊት መሪ የሚሆንበት ፍልስፍና ነው (ወይም ነበረ)።
“ኢትዮጵያ ትቅደም” ደርጋዊነት ሳይሆን ህብረትና አንድነትን፣ ፍቅርና አብሮነትን፣ ፍትህና እኩልነትን፣ አቃፊና አሰባሳባቢ/ሰብሳቢነትን በአንድ የሚያስተሳስር እትብት፤ ወደ ኋላ ከመቅረትም ሆነ ባሉበት ከመርገጥ ይልቅ ወደ ፊት ማሰብ፣ ማየትና መራመድን የሚሰብክ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ከነጠላነት ይልቅ ህብረትን የሚያጠናክር የማንነት ሐረግ ነው (ወይም ነበረ – “ነበር ባይሰበር” እንዲሉ)።
“ኢትዮጵያ ትቅደም” በእቅፉ ከያዛቸው ጥልቅና መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦች አንዱ “ኢትዮጵያ” ሲሆን በ”ኢትዮጵያ”ም “ኢትዮጵያዊነት” አለ። “ኢትዮጵያዊነት” ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም እንደሚሉት የተለያዩ ኅብረተሰቦች የተዋሀዱበት አካል ክፍል መሆን ነው። ኢትዮጵያዊነት ከጎሰኝነት በላይና ውጭ የሆነ አጠቃላይ ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት የዚህ ውጥንቅጥ መሬት ባለቤትነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት የደጋው ብርድና የቆላው ሙቀት የሚገናኙበት፣ የደጋው ዝናም ከቆላው ወንዝ ጋር የተዛመደበት ኃይል ነው።
ይቀጥላሉ መስፍን፣ ኢትዮጵያዊነት ለሙሴ፣ ለክርስቶስና ለመሀመድ የሚጨሰው ዕጣን በእርገት መጥቆ የሚደባለቅበት እምነት ነው። […] በቄጠማ ጉዝጓዝ ላይ የሚታየው መተሳሰብና መፈቃቀር ነው። ኢትዮጵያዊነት የአስተዋይነት፤ የሚዛናዊነትና የጨዋነት ባህርይ ነው። ኢትዮጵያዊነት ረዢምና ተጽፎ ያላለቀ ታሪክ ነው፤ ብዙ ሰዎችም የተሰውለት ስሜት ነው። ኢትዮጵያዊነት ስቃይና መከራ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ኩራትና ክብርም ነው። ኢትዮጵያዊነት ጭቆናና ጥቃት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት አሻፈረኝና እምቢ ባይነትም ነው። ኢትዮጵያዊነት ጴጥሮሳዊነት ነው። (ኢትዮጵያ ከየት፣ ወዴት?) በሌላ ስራቸው ደግሞ “ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው።”
“ኢትዮጵያ ትቅደም” ሲባል “አገር ይቅደም” ማለት መሆኑ አያጠያይቅም፤ አያስጠይቅምም። አገር ደግሞ ከበደ ሚካኤል እንደሚሉት ከሆነ፣ እንዲህ እንዳሁኑ ማንም እየተነሳ እንደፈለገ የሚያደርገው ጉዳይ አልነበረም። ለከበደ አገር ማለት “በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በልማድ፣ በተስፋ፣ በደስታና በመከራ ተሳስሮ የሚኖር አንድ ወገን የሆነ ህዝብ የሚኖርበት የዓለም ክፍል ነው።
አገር ማለት አያት ቅድመ አያት የተወለዱበት፣ አድገውም በጀግንነት ከውጭ ጠላት እየተከላከሉ ለህዝብና ለመንግሥት የሚጠቅም ሥራ ሰርተው እድሜያቸው ሲደርስም ልጆቻቸውን ተክተው የተቀበሩበት ጉድጓድ ነው።
በመወለድ እትብት በመሞት አካል ከአፈሩ ጋራ ስለሚዋሀድ የአገሩ አፈር ህዝቡ በላዩ የሚኖርበት ማለት ነው።
እግዚአብሄር ከምድርዋ ፍሬ ሕይወት እንዲገኝባት በማድረጉ አገር እያጠባች የምታሳድግ ፍቅርዋ በአጥንት በስጋ ገብቶ የማይደመሰስ የሆነች እናት ማለት ነው።
ከልጅነት ጀምሮ ወንዙን፤ ተራራውን፣ ሜዳውን፤ ቆላውንና ደጋውን በማየት ስለ ማደግ አባቶች በሕይወትና በሞት የሰሩበት ደግ ሥራ በአእምሮ ታትሞ ስለ ቀረ በአገር እስካሉ ሲታይ በስደት ሲሆኑ ሲታሰብ ፍቅርና ናፍቆት የሚያሳድር አገር ነው።
አገር፤ አባት፣ እናት፣ ዘመድ፣ ምግብ፣ ጌጥና ሀብት በመሆኑ ድኽነትና ጥቃት በመጣ ቁጥር እስከ ሞት ድረስ እንዲሰራበት ከአያት ከቅድም አያትና ከአባቶች በጥብቅ የተሰጠ ያደራ ገንዘብ ነው።” (ተረትና ምሳሌ፣ 1ኛ መጽሐፍ)
አገር ማለት ይሄ ሁሉ ከሆነ፤ ኢትዮጵያም አገር ከሆነች፣ ይህም በበኩሉ ኢትዮጵያዊነትን ከቋጠረ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ሲባል የሁላችንም መቅደም ነውና አሁንም፤ “ዛሬም ነገም ኢትዮጵያ ትቅደም!!! መባሉ በትክክል አግባብ ነው (ወይም ነበረ)።
የጋራ ኃላፊነትን የግድ የሚለው “ኢትዮጵያ ትቅደም” ከድህነት መውጫ መንገድን ጠቋሚ፣ የቀዳሚነትን አቅጣጫ አመላካች፣ ግብ ተኮር መሆንን የሚያሳስብ፣ መጋጨትን ሳይሆን አብሮ መስራትና መበልፀግን፤ መግደል፣ መጋደልና መገዳደልን ሳይሆን እጅ ለእጅ ተያይዞ በአንድ መንገድ ወደ አንድ አቅጣጫ መጓዝና መዝለቅን፤ ጭራ ከመሆን ቀንድነትን እንደ መላ የያዘ አገር በቀል እውቀት ነው (ወይም ነበረ)። “ከአይን የራቀ ከልብ ይርቃል” እንዲሉ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ከአይንም ከጆሮም በመራቁ ከልብም እርቋል ባዮች ብዙ ናቸው። ይህ መራቅ መራራቅ ደግሞ እዳው ገብስ ሊሆን አልቻለምና እዳ እያስከፈለን ይገኛል።
“ኢትዮጵያ ትቅደም” ሁሉንም ለሁሉም ተግባር የሚያነሳሳ፣ ሁሉንም ወደ ተግባር የሚያሰማራ፣ ሁሉም ለሁሉም እንዲያስብ የሚያደርግ፤ ሁሉም እኩል ቀዳሚ እንጂ ማንም ወደ ኋላ የማይቀርበት፤ ሁሉም በሁሉም ጉዳይ እኩል አሻራውን እንዲያሳርፍ የሚደረግበት ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናና መርሆ ነው (ወይም ነበረ)።
ትርክቱ እንዲህ እንደዛሬው የመፍረስና አለመፍረስ ጉዳይ ሳይሆን የመቅደምና ያለመቅደም፤ ፊት መሪ የመሆንና አለመሆን ወዘተ ነበር (“ተሰበረ እንጂ መኖሩንስ ነበር” የምንል አሁንም አሁንም አለመርፈዱን እያስታወስን።)
(ከዚሁ ጋር ተያይዞ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይን “ኢትዮጵያ አይትፈርስም የምትፈርሰው መጀመሪያ እኛ ስንፈርስ ነው፡፡“ ያሉት ሌላው “ኢትዮጵያ ትቅደም”ን የማስቀደም አቋም ሲሆን ቴዲ አፍሮ እንዳለው ‘አብሮ አይልም ወይ ሰው?’ እንዳለው ጥያቄው ‘አብሮአቸው የሚል ሰው አለ ወይ?’ የሚለው ነው፡፡)
“ኢትዮጵያ ትቅደም” ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ብቻ አይደለም፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ኢትዮጵያዊ ሰምና ወርቅ ቅኔ ነው፣ ግጥምና ዜማ ነው። እምነት ብቻ ሳይሆን ማተብ ነው፤ መጠሪያ ስም፣ መታወቂያ ስያሜ ነው። ባይሳካም “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ሲባል በውስጠ ዘ እነዚህ ሁሉ ስለ መኖራቸው ዋቢ መጥራት አያስፈልግም። ከሁሉም በላይ “ኢትዮጵያ ትቅደም!!!!” የአብዮቱ ማንቀሳቀሻ ሞተር፤ መፈክር ነው (ነበረ)። “ኢትዮጵያ ትቅደም!!!!” “ከሁሉም በፊት እናት አገር ወይም ሞት!!!” ወዘተ ወዘተ። (ከሁሉም የሚያሳዝነው አብዮት እስከ አሁን ድረስ ከአገሪቱ ሳይጠፋ “ኢትዮጵያ ትቅደም” እንዲጠፋ የተፈረደበት ፍርደ ገምድልነት ነው።)
“ኢትዮጵያ ትቅደም” ጊዜ ነው። ዛሬ “ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን” የሚለውና “አሁን”ን እንደዘለለው የሬዲዮ ፕሮግራም ማጀቢያ ምኞት ብቻ ሳይሆን ተግባርን የሚጋብዝ ጥልቅና ጥቅል ሀሳብ ነው። (የ”ትፈርሳለች/አትፈርስም” የልጆች ጨዋታ የፈጠረው?) ስጋትና ጭንቀት ከወለደው “ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር”ም በእጅጉ ይለያል። ልዩነቱንም ከላይና ቀጥሎ ካሉት ሀሳቦች መረዳት ይቻላል። (ሌላው የዚሁ አባባል ቤተሰብ (ዛሬን መዝለሉ፣ ነገ ትልቅ ለመሆን ዛሬ ላይ መሰራት ያለበት ስለመሆኑ ባይነግረንም) “ትልቅ ነበርን ትልቅ እንሆናለን” የሚለው የፕሮግራም ማጀቢያ (ሲያሻውም መሸጋገሪያ ወይም መግቢያና መውጫ) ይህንን ሀሳባችንን ይጋራል (አይጋራም?) ብለን እዚህ ጠቅሰነዋል። ምንም እንኳን ከጊዜ ቅደም ተከተል አኳያ የተፋለሰ፣ ወሳኝ ለሆነው “አሁን” ተገቢውን ትኩረት ያልሰጠና ተስፋ ያደረገውን “… እንሆናለን” ከወዲሁ ሞራሉን ቢነካውም።)
“ኢትዮጵያ ትቅደም” መተርጎም፣ መፈታት፣ መብራራት፣ መተንተን … ያለበት፤ አላማና ግብ ያለው አገራዊ ራእይ፤ አገራዊ መርሆ፤ አገራዊ ስትራቴጂ፤ አገራዊ የመቅደም (ቀድሞ የመገኘት) ጠሊቅ አስተሳሰብ ነው።
“ኢትዮጵያ ትቅደም” የጥበባት ምሰሶ ነው። በመሆኑም ከ”ሀሁ … ኢትዮጵያ ትቅደም” ጀምሮ እስከ ዋንኞቹ የእውቀት ደንበር እስከሆኑት ትምህርት ቤቶች ድረስ ዘልቆ በመጠሪያነት ሲያገለግል የኖረ
(ቁ.1፣ ቁ.2 “ኢትዮጵያ ትቅደም ትምህርት ቤት” በሚል የሚታወቁት የመዲናዋ እውቅ ት/ቤቶች እምጥ ይግቡ ስምጥ ይህ ፀሐፊ የሚያውቀው ነገር የለም (የ”ትቅደም” ተማሪዎች በትዝታ መልክ ቢያጫውቱን ጥሩ ነው።) በመሆኑም ይመስላል አንዳንድ አረጋውያን ሲናገሩ “እንደሚሰማው በዛ ውስጥ ያለፈው ትውልድ አሁንም በአገሩ ላይ የሚደራደር አይደለም። ሌላው ቀርቶ በክፉም ስትነሳበት እንኳን አይወድም።” ሲሉ የሚሰሙት።)
“ኢትዮጵያ ትቅደም” ከዜማና ግጥም፤ ሰምና ወርቅም በላይ የጋራ ቋንቋ ነው (ወይም ነበረ)። ሁሉም ቅር ሳይለው የሚናገረው፣ ሁሉም በአንድነት የሚዘምረው፤ ሁሉም በኩራት ኢትዮጵያዊነቱን የሚገልፅና የሚፈክርበት፤ ወታደሩ ለዘመቻው (ድሉ)፣ ተማሪው ለትምህርቱ፣ መሪው ለአመራሩ በስትራቴጂነት የሚጠቀምበት ሁነኛ ሥነ-ዘዴው ነው (ወይም ነበረ)።
“ኢትዮጵያ ትቅደም” ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ወዘተ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ያለው፤ “መቅደም” ሲታሰብም ሆነ “ትቅደም” ሲባል እነዚህን ሁሉ መልሶ መሆኑን የሚያስገነዝብ፤ የመሬት ለአራሹና የመሳሰሉትን የ”ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች” (የእነሱ ጥያቄዎች ሳይመለሱ መቅደም ስለማይኖር) ጥያቄዎች በአግባቡ የሚያስተናግድና መልስ ያለው ሆኖ ሳለ ለምን ከአገር በቀል እውቅትነት፣ አገራዊ እሴትነትና ፍልስፍናው ደብር ተወገደ? የሚለው በብዙዎች ብዙ ጊዜ የሚነሳ ጥያቄ ነው።
የዛሬን አያድርገውና “ኢትዮጵያ ትቅደም” በመንግሥት መዋቅር፣ የእለት ተእለት ሥራና ግንኙነት ውስጥ፤ በዲፕሎማሲው መስክና ተግባር፤ በቢዝነሱ ዓለም የጋራ የመግባቢያ መሳሪያ ነው (ወይም ነበረ)። በእያንዳንዷ ደብዳቤ ግርጌ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የጽሑፉም ይሁን የሀሳቡ ማሳረጊያ ነው (ወይም ነበረ)። በእንግሊዝኛ ጽሑፎችም “Ethiopia First!!!”
በወቅቱ “ኢትዮጵያ ትቅደም”ን በየግድግዳው፣ ጋዜጣው፣ በየተማሪ ደብተርና መማሪያ መፃህፍቱ ሁሉ ማጣት ከባድ ብቻ ሳይሆን የሚታሰብ አልነበረም። “ኢትዮጵያ ትቅደም” ሁሉም ጋር አለ፤ በሁሉም ልብ ውስጥ ነው (ወይም ነበረ)። “እናት አገር”ንና ፍልስፍናውንም እንደዚሁ።
ከላይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለምርጫቸው ውጤታማነት “America First”ን አንግበው ከተፍ ከማለታቸው በፊት ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ያለችው አስቀድማ መሆኑን አንስተናል። (ከኦባማ “Yes We Can!!!” በፊት “ይቻላል” እንዳለችው ሁሉ) አስገራሚው ነገር አደጉ የሚባሉቱ ተጨማሪ መቅደምን ሲፈልጉና አገራቸውንና ህዝባቸውን “First” እና “Great” ሲሉና ጽንሰ ሀሳቡን ለውጤታማነት፣ ላሸናፊነት፣ ለብሄራዊ መግባባትና ሀገረ መንግስት ምስረታ ሲጠቀሙበት እኛ ግን … “ኢትዮጵያ ትቅደም”ን እንደ ዋዛ አሽቀንጥረን ጥለን ስቃይ ውስጥ እንገኛለን።
ጥቂቶች እየማሉ ሁሉ እንደሚናገሩት “ኢትዮጵያ ትቅደም” የትምክህት ቋንቋ አይደለም፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የአንድ ወገን የበላይነትን ለመግለፅና የሌላኛውን ወገን የበታችነት ለማሳየት የተፀነሰ ጽንሰ-ሀሳብ አይደለም። “ኢትዮጵያ ትቅደም” የአንዲት ኢትዮጵያ ሉአላዊት አገር መገለጫ፣ የእሷም መረማመጃና መሻገሪያ ድልድይ፤ ያሰበችበትም መድረሻ አቅጣጫ እንጂ ኢትዮጵያውያንን ከፋፍሎ አንተ ትብስ አንተ አትብስ እያለ የሚሸነሽን አተያይ አይደለም። “ኢትዮጵያ ትቅደም” የኢትዮጵያውያን ሁሉ የሆነ፤ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የቆመ፤ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ህልም የሆነ፤ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ርእይ ነው (ወይም ነበረ)። ሊደረስበት እንዳይቻል ቢደረግም ሊደረስበት የሚችል ግብ።
“ኢትዮጵያ ትቅደም” ህዳሴ ሲሆን የመታደስ አስተሳሰብ ውጤት ነው፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ቁጭት የወለደው የቀድሞው ኢትዮጵያዊ ቀደምትነት እና የዛ ቀደምትነት ከማማው ወርዶ መገኘት የፈጠረው ፍልስፍና ሲሆን ቀዳሚ አላማውም በሌሎች የተነጠቅነውን ማንነት የማስመለስ እንጂ ሌሎችን ለመብለጥ ያለመ ምቀኝነት አይደለም።
“ኢትዮጵያ ትቅደም” በርካታ ጉዳዮች በአንድ የተገለፁበት ጽንሰ ሀሳብ ሲሆን ከሁሉም በፊት አንድ የሚያስቀድመው ኃያል ኃይል (ትውልድ) ይፈልጋል። ይህ ኃይል ደግሞ አንድ ሰው ወይም አንድ ቡድን፣ ቀበሌም እንበለው ክልል ሊሆን ከቶም አይቻለውም። በመሆኑም የተባበረ የህዝብ ክንድ፤ ጠንካራ አንድነትን፤ የጋራ የአሰራር እሴት፣ ስልትና የመሳሰሉትን ሁሉ የግድ ይላል። እነዚህም በራሳቸው የግድ የሚሏቸው በርካታ ሰብአዊና አኮኖሚያዊ ጉዳዮች አሉ። ስለዚህ ኢትዮጵያን ለማስቀደም እራስ ቀድሞ መገኘት ይገባል ማለት ነው – በአስተሳሰብ የጋራና ጠንካራ ክንድ የማጎልበት ወዘተ ተግባራት በቅድመ ሁኔታነት ከፊታችን የሚመጡ የመሆናቸው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ።
“ኢትዮጵያ ትቅደም” እንደ “ኢትዮጵያ ትውደም” ምላስና ሰምበር (ወይም የንግግር ክፍሎችን) ብቻ አይደለም የሚፈልገው። “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚፈልገው ከሁሉም በላይ አንድነትን፣ ህብረትን፣ ተፈጥሮ ያደለችውን የጋራ ሀብት በጋራ ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆንን፣ ማህበራዊ ካፒታልን ወዘተ ነው የሚፈልገው – በዋናነት። ወኔን፣ እሱን ተከትሎ የሚመጣውን ጀግንነት፣ አትንኩን ባይነት፤ የጠነከረ እምነት፣ ሥነምግባርና ሞራልን ሁሉ “እፈልጋለሁ” ይላል – ልክ እንደ “ደ’ሞ ላ’ባይ” – “ኢትዮጵያ ትቅደም”። እነዚህ ሁሉ በሌሉበት “ኢትዮጵያ ትቅደም” ከቃል ጩኸትና አዶከበሬ ዜማ የተለየ ሊሆን ስለማይችል “አስቡብኝ” ይላሉ።
ወደ ማጠቃለያው ከመሄዳችን በፊት በአንድ ነገር መስማማት ያለብን ሲሆን፤ እሱም “ኢትዮጵያ ትቅደም” ሲባል የሩጫ እሽቅድድም አለመሆኑን፤ የኢትዮጵያ ቀድሞ መገኘት ማለት የዜጎች ቀድሞ መገኘት መሆኑን፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ሲባል ጉዳዩ ከትውልድም ያለፈ ትውልዶችን ሁሉ (ያለፈው፣ የአሁኑና መጪው) እንደሚያካትት፤ ከስነ-ልቦና ከማህበረ-ፖለቲካዊ እና የመሳሰሉት ጋር ሁሉ ያለው ቁርኝት የዋዛ እንዳልሆነ ልብ ማለት ተገቢ ነው።
“ኢትዮጵያ ትቅደም” በባለቤትነት የያዘው “እኛ”ን ነው፤ “እኛ” ደግሞ በየትኛውም የፖለቲካ (የብሄርም (racial politics) ቢሆን፤ የለየለት ዘረኛ ካልሆነ በስተቀር) መስመር በወርድም ይሁን ቁመት፤ በጥልቀትም ይሁን ርዝመት (ዲያሜንሽን) ያውና አንድ እንጂ ሌላ አይደለም። አሁን ጥያቄው “ታዲያ ለምን …?” የሚለው ነው። “ታዲያ ለምን …?” የ”ኢትዮጵያ ትቅደም” ፎቢያ ከየት መጣ፣ የ”ኢትዮጵያ ትውድም”ስ? የእነዚህ አውዳሚ አስተሳሰብ (ኒሂሊዝም) ምንጩስ ምንድን ነው? ያሳስባል፣ ያነጋግራል፤ ያወያያል።
መውጫችንን የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ “በአገርህ ላይ ክፉ አትይ፣ ክፉ አትስማ ክፉ አትናገር” ይሆን ዘንድ መርጠናልና ኢትዮጵያ ትቅደም!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2013