ሽምግልና ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አብሮ የኖረ ከባህል ሁሉ ተወዳጅና ተሰሚ የሆነ የአብሮነታችን መገለጫ ነው። ባልና ሚስት መካከል ችግር ሲገባ፣ ልጆች ከወላጆቻቸው አልስማማ ሲሉ፣ ወጣቶች እርስ በእርሳቸው ግጭት ውስጥ ሲገቡ ሰዎች ከማህበረሰቡ ባህልና ወግ ያፈነገጠ ነገር ሲያደርጉና ሌሎችንም እንደ አገርና ህዝብ ወጣ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚፈቱት በባህላዊው መንገድ በሽምግልና ነው።
ይህንን ሽምግልና የሚሰሩ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችም በትንሽ ትልቁ የተወደዱ የተፈሩ እንዲሁም የተከበሩም ናቸው። ያሉት ነገር መሬት ጠብ የማይል ከእነሱ ፍርድ ለማፈንገጥ ማሰብ እንኳን የሚከብድም ሆነው ነው በአገራችን ብዙ ዓመታትን የቆዩት።
ይህ አኩሪ እሴታችን አሁን ላይ አንዳንድ ችግሮች ገጥመውት ይታያል፤ ሽማግሌዎቹንና ሽመግልናውንም በጄ ብሎ የሚቀበል ትውልድም እየጠፋ የመጣም ይመስላል። በተለይም አገር በዚህ መሰሉ ውጥረት ውስጥ ስትሆን ይህ የሽምግልና ሂደት መተኪያ የሌለው የማረጋጊያ መንገድ እንደሆነ ከመንግስት ጀምሮ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። እኛም ይህ የሽምግልና ባህላችን አገራችን ከወጠራት ችግር ለማላቀቅ ያለን ሚና እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መድረክ ሰብሳቢ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት የአእምሮ ሃኪምና መምህር ከሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ እንደ አገር ሽማግሌ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር መስፍን ፦ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ የማየው ድብልቅ በሆነ ስሜት ነው። በአንድ በኩል በአገራችን ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ጥሩ አይደለም። ማንነትና ጎሳን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በየቦታው ይስተዋላሉ። እነዚህ ችግሮች ደግሞ ሰፍተው ህጻናትና ሴቶችንም ጭምር በማፈናቀል፣ በማቁሰል ህይወታቸውን እንዲያጡም እያደረገ ነው ። ይህ ደግሞ በጣም ያሳዝነኛል።
ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት አምበጣው፣ ንፋሱ፣ ጎርፉ እያሰቃየን ነበር፤ ከዚህ ባሻገር ደግሞ ኮቪድ 19 አገራችን ከገባ ዓመት ከአንድ ወር ሆኖታል፤ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ደግሞ በጣም የምንወዳቸውንና የሚያስፈልጉንን በርካታ ዜጎች ተነጥቀናል፤ ህጻናት ከትምህርት ርቀው ቤት እንዲውሉ ሥርዓቱ ሁሉ እንዲዛባ ሆኗል። እነዚህን ሁሉ ነገሮች ደምረን ስናያቸው ደግሞ ያለንበት ሁኔታ እጅግ የሚያሳስብ ነው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተው ጦርነት ከምንም በላይ ያሳዝናል፤ ይህ እንዳይበቃን ደግሞ ከህዳሴው ግድባችን መገንባት ጋር ተያይዞ የምናምናቸው የምንላቸው እንደ ሱዳን ያሉ አገሮች መንግስታት ችግር መፍጠራቸው ይበልጥ ህመማችንን እያባባሰው ነው።
ሌላውን መልካሙን ጎን ስናይ ደግሞ ግድባችን አድጎ 80 በመቶ ላይ ደርሷል ፤ በቀጣይም ሁለተኛው ሙሌት ተካሂዶ ውሃውን በደንብ መያዝ ከቻልንና ሃይል ካመነጨን ወደልማት ፊታችንን ለመመለስ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ይሆንልናል ብዬ አስባለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ለናቁንና ስንራብ ብቻ ስንዴ ለሚወረውሩልን አገሮች በኢኮኖሚ ራሳችንን ስንችል የራሳችንን ስንዴ ስናመርት በሃይል ተምበሽብሸን ለጎረቤቶቻችንም ስንተርፍ በእነሱ ዘንድም ተቀባይነት ይኖረናል።
ሌላው በአገሪቱ ላይ የሚያበረታታኝ ነገር የአገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት መሪዎች ተስፋ ሳይቆርጡ ልጆቻቸውን በመገሰጽ በማስተማር እስከ አሁን የደረሰው መጥፎ ነገር እጅግ መጥፎ እንዳይሆን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።ይህንን ሳይ ደግሞ ይህች አገር እንደምንፈራው ሳይሆን ይህንን ክፉ ጊዜ አልፋ መጻኢ እድሏ የተሻለ ይሆናል የሚል ተስፋም አለኝ።በመሆኑም ከላይም ስሜቶቼ ድብልቅ ናቸው ያልኩት ከዚህ አንጻር ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፦በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለው ግድያና መፈናቀል እንደ አገር ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ እስከ ምን ድረስ ሊሆን ይችላል ይላሉ?
ፕሮፌሰር መስፍን፦ ዋጋው አጅግ በጣም መራር ነው።አገራችን እጅግ ደሃ ነች ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች እዳ አለባት፤ በአሁኑ ወቅት እስከ 10 ሚሊዮን የሚገመት ሰው የእለት ደራሽ እርዳታን የሚፈልግ ነው። ብዙ ሚሊዮኖች ተፈናቅለው በየመጠለያው ነው ያሉት፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ የህጻናትና የእናቶች ጉዳይ እጅግ ያማል፤ ከዚህ ባሻገር ደግሞ አረጋውያን ቀያቸውን ለቀው የሚሄዱበት አቅም የላቸውም፤ በመሆኑም በአገሪቱ በሽታው ረሃቡ ባለበት ወቅት ይህ መሰሉ ችግር መከሰቱ ያለንበት ሁኔታ እጅግ አስደንጋጭና አሳሳቢ በዚሁ ከቀጠለም በጣም መጥፎ ሊሆን ይችላል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚላስ የሚቀመስ የሌለን አገሮች ሆነን ሳለን በተለይም እስከ አሁን ድረስ ሲለግሱን የነበሩ አገሮች አንዳንዶቹ ከጎረቤቶቻችን ጋር በማበር ሌሎቹ ደግሞ በአገራቸው ላይ ኮቪድ 19 በፈጠረባቸው ችግር በጣም በመቸገራቸውና ኢኮኖሚያቸው በመናጋቱ እንደ ድሮው ለጋሽ የሚሆኑበት ሁኔታ ውስን በመሆኑ ችግሮቹ በእኛ ላይ እንዲሰፉ ሆነዋል። በመሆኑም እነዚህን መሰል ችግሮች አሁን የእኛን ሰከን አለማለት ሲደመርባቸው አገራችንን ወደባሰ ቀውስ እንደውም እንደ አገር መቀጠል እንዳትችል ሊያደርጋት ስለሚችል ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አንጻር በየአካባቢው ያሉ የአገር ሽማግሌዎች ሚና ምን ሊሆን ይገባል?
ፕሮፌሰር መስፍን፦ የአገር ሽምግልና ከባህል ከእድገት ጋር የሚመጣ ነገር ነው። ዓለም በሙሉ በየባህሉ ሽምግልና አለው። መንግስታት ከመፈጠራቸው በፊት የነበረ ነገር ቢኖር ሽምግልና ነው።ቤት ውስጥ ያሉ እማወራና አባወራ በእድሜ ትልቅ ስለሆኑ ልጆቻቸውን ይንከባከባሉ፤ የአካባቢው ትልልቅ ሰዎች ካላቸው የህይወት ልምድ ተነስተው ደግሞ የአካባቢውን ወጣቶች ትዳር ንብረት በጠቅላላው ህይወትን በመጠበቅና በመንከባከብ ችግር ሲያጋጥም ደግሞ ወጣቶቻቸውን አስተባበረው እንዲፈታ በማድረጉ ላይ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡
ነገር ግን በእኛ አገር ሽምግልና ብዙ ሺህ ዓመት አብሮን የኖረና ትልቅ ቦታ ያለው ቢሆንም ላለፉት 45 ዓመታት አቅም እንዳይኖረው የሃይማኖት አባትነት ተሰሚነት እንዲያጣ ሆኗል።በዚህ ምክንያት ደግሞ ባለፉት ብዙ ዓመታት ችግሮች ሲኖሩ ሽማግሌዎች ወጥተው ተው ሲሉ ወጣቶች ያልሰሙበት ጊዜ በጣም በርካታ ነው።በፊት ቢሆን ሽማግሌ ተናግሮ፣ የሃይማኖት አባት መስቀሉን (መቁጠሪያውን) አውጥቶ ተው ሲሉ ሁሉም ነገር ሰጥ ይል ነበር። አሁን ይህ እሴታችን እጅግ ተሸርሽሯል።
ይህም ቢሆን ግን እጅግ ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርገን ደግሞ የአገር ሽማግሌዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተሰሚነታቸው ሙሉ በሙሉ አልሞተም፤ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ደግሞ የጋሞ ሽማግሌዎች በአንድ ወቅት ችግር ደርሶ በዚህም ምክንያት ደግሞ ወጣቶቻቸው ለብቀላ በወጡበት ጊዜ ተንበርክከው ሳር ይዘው ሲለምኑ ከድርጊታቸው ታቅበዋል። በሌሎችም አካባቢው የሱማሌ ኡጋዞች ሱልጣኖች የደቡብ ካላዎች ገራዶች የኦሮሚያ አባገዳዎች በተወሰነ ደረጃ ይሰማሉ፤ የአማራ የትግራይ የሀረር ሽማግሌዎችም በተወሰነ ደረጃ የሚሰሙበት ሁኔታ እንዳለ እናውቃለን። በመሆኑም ሽምግልና በአንዳንድ ባህሎች ውስጥ እየሰራ ነው ማለት ይቻላል።
አሁን ትልቁ ስራ ሊሆን የሚገባው እንደ አገር ሽማግሌዎች መድረክም የምናምነው ሽምግልናውን ፖለቲካ ሳይገዛው ለህሊናቸው ተገዢ የሆኑ ሽማግሌዎች የሚበራከቱበት ወጣቶች እነሱን የሚሰሙበት ተቋም እንዲሆን ያስፈልጋል፤ ይህንንም ለማድረግ እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን አገራዊ ስጋት ከመቀልበስ አንጻር ምን ይጠበቅባቸዋል?
ፕሮፌሰር መስፍን ፦ ተፎካካሪዎችም ሆኑ ገዢው ፓርቲ የሚጠበቅባቸው ነገር ተፎካከሩም፣ ተወዳደሩም፣ አሸነፉም በመጨረሻ እናስተዳድረዋለን ብለው የሚያስቡት በህይወት ያለ ህዝብ ያስፈልጋቸዋል። ህዝብ ከሌለ ጠንካራ ኢኮኖሚ አስተዳደራዊ አቅም ያለውን አገር መመስረት በጣም ከባድ ነው ።ከዚህ አንጻር ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቢሆኑ መጀመሪያ ማየት ያለባቸው ህዝባቸውን ነው።
ህዝባቸውን ሲያዩ ደግሞ መጀመሪያ ያስፈልጋል ብለው ወደ አእምሯቸው መምጣት ያለበት ነገር ሰላም ነው። ሰላም ከሌለ መፎካከርም ሆነ መወዳደር አይቻልም፤ አገርም የማንም አትሆንም። በመሆኑም ይህንን ከግምት በማስገባት ሲፎካከሩ በሀሳብ እንጂ በጉልበት መሆን የለበትም። ለአገሬ ምን ባመጣላት ነው የምለውጣት? ተጠቃሚ የማደርጋት? ከዛኛው ፓርቲ እኔ በምን እሻላለሁ? የሚለውን ነገር ማሰብና እነዚህንም ማፋጨት ነው የሚጠቅመው። አሁን በየቴሌቪዥኑ የሚሰራጨውን ፉክክር ስናዳምጥ ግን ብዙውን ነገራቸውን ወደግለሰባዊነት ይወስዱትና አንተ እንዲህ ነህ፣ አንቺ እንደዛ ነሽ፣ ወደመባባል ይሄዳሉ፤ ይህ አይደለም የሚጠቅመው ፤ ይልቁንም ስራ አጥነትን በመቀነስ፣ ሰላምን በማስፈን ፣ አገርን በማሳደግ ፣ ዳርድንበርን ከመጠበቅ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን ከማዳበር፣ የሴቶችን መብት ከመጠበቅ፣ ልጆች መሰረታዊ ነገሮችን ማግኘታቸው ላይ እንዲሁም አረጋውያን በተገቢው መንገድ የሚጦሩበት ሁኔታ በመፍጠሩ በኩል ያላቸውን ፕሮግራም ነው ማቅረብ ያለባቸው።አገራችንን ለማኝ፣ ደሃ ከሚል ስም አውጥተው ካደጉት አገራት ጋር ለማድረስ ምን እናድርግ ፤ ኢትዮጵያን ወደ አንድነቷ መልሰን ጎሳዎች ተከባብረው ቋንቋው ባህሉ አድጎ ያለፈውን ቁርሾ ትቶ ወደፊት ምንም ቁርሾ እንዳይኖር እንዴት አድርገን እንሂድ የሚሉት ሃሳቦች ላይ ቢፋጩ መራጩም ደስ ይለዋል።
አገር በተቻለ መጠን ለሁሉም ዜጋ እኩል መሆን አለበት፤ ትንሽ ጠየም አለ አላለ ረዘመ አጠረ ከደቡብ መጣ ከሰሜን በሚል ሳይሆን ኢትዮጵያዊ እስከሆነ ድረስ አየሯን እኩል እንደሚምገው ሁሉ ሀብቷንም በጋራ ተጠቃሚ መሆን አለበት። ነገር ግን ትልልቅ ብሔረበሶች በሚል በቁጥራቸው አነስ ያሉትን መደፍጠጥ ነውር ነው።እንደውም እነሱ ራሱ የብሔረሰብ ደረጃ ላይ ደርሰው ተከብረው ሁሉም ነገር ተከብሮላቸው ሙሉ ኢትዮጵያዊ ሆነው እንዲዘልቁ እነዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያላቸውን ሃሳብ ማቅረብ መቻል አለባቸው።
አዲስ ዘመን ፦ ወጣቶች ከስሜታዊነት ወጥተው ሀገሪቱን ካለችበት ስጋት ለማውጣት ያለባቸውን ሃላፊነት እንዴት ይገልጹታል?
ፕሮፌሰር መስፍን ፦ ወጣትነት ማለት ትኩስነት ነው። ስሜቶች መጥፎም ይሁኑ ጥሩ በጣም ቅርብ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ፍትህ ከሆነ የሚፈልጉት ወዲያውኑ ካልሆነ ነው የሚሉት።ይህ ደግሞ ከህጻንነታችን ጀምሮ ይዘነው የምንመጣው ባህርይ ነው።
ለምሳሌ አንድ የስድስት ወር ህጻን ምግብ ከፈለገ ፈለገ ነው፤ እናቱ ቆይ ጡጦህን ላሙቅ ትንሽ ጊዜ ስጠኝ ብትለው እንኳን ሊሰማት አይፈልግም፤ አሁኑኑ አቅርቢ ነው የሚለው፤ ነገር ግን ያው ህጻን ልጅ አድጎ የአራት ዓመት ልጅ ሲሆን እናቱን እራበኝ ቢላት ቆይ እንጀራ እየጋገርኩ ነው አውጥቼ እሰጥሃለሁ ስትለው እንደ ስድስት ወር እድሜው አያስቸግርም፤ በትዕግስት ለመጠበቅ ይሞክራል። በመሆኑም እድሜ እየገፋ ሲሄድ መስከኑም አብሮ ይመጣል። ነገር ግን ወጣትነት ስሜታዊነት የሚታይበት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ጀምበር ካልሆነ የምንልበት ጊዜ ነው። በሌሎች ስሜቶች የምንወሰድበትም ወቅት ነው።
ነገር ግን በህጻንነታቸው ኮትኩተን ካሳደግናቸው ተገቢውን ፍቅር ከሰጠናቸው ወጣት በሚሆኑበት ጊዜም አንድን ነገር ከማድረጋቸው በፊት ሁለት ሶስት ጊዜ ያስባሉ። ይህ ደግሞ ሲሆን ተጓደለ የሚሉት ፍትህ እንኳን ሲገጥማቸው ከጉልበት ይልቅ በሃሳብ ወደመታገል ይሄዳሉ። አሁን ግን ያፈራነው ወጣት ቶሎ ስሜታዊ ሆኖ ልክ እንደ ስድስት ወሩ ልጅ የሚፈልገው ነገር ሁሉ ወዲያው ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ የሚል ነው። ይህ ደግሞ የወጣቱ ጥፋት ሳይሆን የእኛ የአሳዳጊዎቹ ነው። ምክንያቱም ወጣቶች እየተከፉ ካደጉ ወደሙሉ ወጣትነት በሚደርሱበት ጊዜ ተበቃይ ነው የሚሆኑት። ለምሳሌ አሁን በመንገድ ከላይ ቤንዚን እየሳቡ ያደጉ ልጆች ህብረተሰቡ እንደሌባ እያያቸው የፈለገ እየሰጣቸው ያልፈለገ እየሰደባቸው አድገው አሁን ባሉበት ሁኔታ 15 ዓመት ቢጨመርላቸው ክፉ ለህብረተሰቡም አደገኛ ተበቃይ ሊሆኑ ይችላሉ።
በመሆኑም አሁን ወጣቶች ሰከን ብለው እንዲያስቡ አገርን ከማጥፋት ወደመታደግ እንዲሄዱ መድረኮችን ማዘጋጀት ስራ መፍጠር ሃይማኖቶች በርትተው መስራት ይገባቸዋል፤ እኛ ሶስት ጊዜ የምንበላ ሰዎች አንዱን እንኳን በመተው በተለይም ህጻናትን ከጎዳና ላይ ለማንሳት መጠቀም አለብን። የተፈናቀሉትን መርዳት አለብን። ከዚህ አንጻር ደግሞ በእጃቸው ሁሉ ነገር ያለ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ከታች ከቀበሌ ከጎጥ ጀምረው ወጣቱ ላይ መስራት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ በተለይም ከፊታችን ያለው ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን እንደ አገር ምን መስራት ይጠበቅብናል?
ፕሮፌሰር መስፍን ፦ ቀደም ብለን ብዙ ስራዎች መስራት አለብን፤ ነገር ግን አሁን ላይ ምን ያህል ሰርተናል የሚለውን ለመመለስ ምናልባት ጥናት ይጠይቅ ይሆናል። ነገር ግን ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ፍቅር መተሳሰብ መኖር አለበት። ይህ ደግሞ በአንድ ክልል ወይም በመዲናዋ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ ሊኖር ይገባል። ይህንን ለማምጣት ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ በጥንካሬ አልሰራንም ። ስለዚህ አሁንም ባለችን ጥቂት ጊዜ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ማህበራዊ አንቂዎች ፣ ከፖለቲካ ውጪ ያሉ የአገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶች ወጥተው ቢያንስ ይህንን ጊዜ በሰላም እንድናልፈው የዴሞክራሲ መሞከሪያ ጊዜም እንዲሆንልን ማድረግ መቻል አለባቸው።
ተመራጮቹም እንደቀደመው ጊዜ ዴሞክራሲን እናመጣለን ብለው የሌላውን አገር ቅድት አድርጎ ህዝቡን ና ተቀበል ሳይሆን ማለት ያለባቸው የአገሪቱን ባህል ወግ ያለውን ቱፊት በሚገባ ጠብቆ የራሱ የሆነ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ እንዲገነባ ማድረግ ነው ያለባቸው።
በመሆኑም በዚህች በቀሪዋ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ባለፉት ጊዜያት በመሰል ችግሮች ያፈሰስነው ደም ብዙ መሆኑን ከዚህ ወዲያ ደም እንዳይፈስ መጠንቀቅ እኛ ከኢትዮጵያዊነታችንም በላይ ሰው መሆናችንን አውቀን ሰው ደግሞ ክቡርነቱን ተረድተን ወደልባችን መመለስ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩልም በዚህ ወቅት ከምንም በላይ ወደፈጣሪያችን የምንቀርብበት የምናስከፋበት ሳይሆን ለጸሎት በፊቱ የምንንበረከክበት ጊዜ መሆኑን አውቀን ፈጣሪን በፍጹም ልቦና መለመን ቢያንስ ምርጫው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ምንም ችግር ሳይገጥም እንዲጠናቀቅ ፖለቲከኞቹም ከፖለቲካ ውጪ ያሉትም አካላት አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን ፦ የቀደመው የመከባበር አገራዊ እሴቶቻችን እንዲቀጥሉ የአገር ሽማግሌዎች ተደማጭነታቸው ከፍ ብሎ አገር ካለችበት መጥፎ ሁኔታ ለማውጣት አቅም እንዲፈጠር ከማን ምን ይጠበቃል?
ፕሮፌሰር መስፍን፦ እዚህ ላይ ፖለቲከኞችም ሆኑ መንግስት ቁርጠኞች መሆን አለባቸው፤ ግን ቁርጠኛ ስንል ምን ማለታችን ነው የሚለውን ለማብራራት አንዳንድ አገሮች ሽምግልናን ህገ መንግስታቸው ውስጥ ሁሉ አስገብተው ይጠቀማሉ፤ ለምን መንግስት በሆነ አጋጣሚ ቢፈርስ በጊዜያዊነት አገርን እንዲመራ ህዝብን እንዲያስተዳድር የሚተካው ሽምግልና ነው።
ለምሳሌ ባለፈው በአፋርና በሶማሌ መካከል ተነስቶ የነበረውን ግጭት ለማብረድ መጀመሪያ ዘለው የገቡት የአገር መከላከያ ሳይሆን የአገር ሽማግሌዎች ናቸው። ሽማግሌዎቹም ያልተስማሙትን አካላት ቁጭ አድርገው ችግራቸውን ጠየቁ፤ ሁላችንም የአዳምና የሄዋን ዘሮች ነን፤ በእኛ መካከል እንዲህ ያለ ነገር ሊፈጠር አይገባም፤ ብለው አሸማግለው የሚካሰው ተክሶ ነገር እንዲበርድ አደረጉ። በተመሳሰይ በሶማሌና በኦሮሚያ መካከልም የተነሳውን ጸብ ያበረዱት እነዚሁ ሽማግሌዎች ናቸው። ስለዚህ ይህንን ተቋም የአገሪቱ መንግስት ሊጠቀምበት በህጉም ውስጥ ተዋህዶ አገርንና ህዝብን ከጥፋት የማዳኛ መንገድ አድርጎ ሊጠቀምበት ይገባል።
በሌላ በኩል ደግሞ በየአካባቢው ያለው የሽምግልና ሂደት ያለፉትን በርካታ ዓመታት ምን ሲሰራ ነው የከረመው? የአካባቢውን ችግር በመፍታት ሂደት ውስጥ ያበረከተው አስተዋጽዖ ምን ይመስላል? የሚለው በደንብ ተጠንቶና ተመርምሮ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ አስገብቶ ልጆች ወጣቶች እንዲማሩበት የዛሬ ወጣቶች ደግሞ እድሜያቸው ሽምግልናው ላይ ሲደርስ አገርን ከጥፋት የሚታደጉበት እንዲሆን ማድረግ ይገባል እላለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር መስፍን፦እኔም አመሰግለሁ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2013