ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ፣ ባለስልጣናት አልያም የተወሰኑ የፖለቲካ ፣ የአይዶሎጂና የኢኮኖሚ ቡድኖች ሚስጥራዊ ዕቅድ ውጤት የሆነ ሁነት ወይም ክስተት የሴራ ኀልዮት Conspiracy Theory ሲል ይበይነዋል።የእንግሊዘኛው መዝገበ ቃላት ሜሪያም ዌቢስተር ።( A theory that explains an event or situation as the result of a secret plan by usually powerful people or groups .) የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ .ም ባሰናዳው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ፤ አድማን፦ ሴራ ዱለታ ፤ ሲል በአጭሩ ይተረጉመዋል ፡፡
ሆኖም በባለስልጣናት ፣ በመንግሥት ሆን ብሎ ጉዳት ለማድረስ በሚስጥር የሚፈፀም ደባም የሴራ ኀልዮት (ወሬ) ነው ሲሉ ድርሳናት ትርጉሙን ሰፋ ያደርጉታል ።ታዋቂው የፖለቲካ ሊቅ ማይክል ባርኩን በበኩሉ ኀልዮቱ አፅናፈ ዓለም universe በአፈተት በአቦሰጥ ሳይሆን በንድፍ design ትመራለች በሚለው ተረክ ላይ የተዋቀረ ነው ሲል ይሞግታል ።እንደ ባርኩን ትንተና የሴራ ኀልዮት ሶስት መገለጫዎች አሉት ።የመጀመሪያው ምንም ነገር በአጋጣሚ አይሆንም ።ሁለተኛው ደግሞ ምንም ነገር ላይ ላዩን እንደምናየው ፣ እንደመሰለን አይደልም ፡ ሶስተኛው ደግሞ ሁሉም ነገር እርስ በርሱ የተያያዘ ነው ብሎ ያምናል።ሌላው የኀልዮቱ ባህሪ ይላል ባርኩን ውሸት መሆኑን በመረጃ ለማስተባበል ፈታኝ መሆኑ ነው ።የኀልዮቱ መነሻ የመሪዎች ግድያ ሲሆን ዘመኑም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አንስቶ መሆኑን ድርሳናት ያትታሉ ፡፡
ከእያንዳንዱ ክስተት ጀርባ ሴራ ደባ አለ በማለት በዜጎች በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን የሚቀፈቅፍ ኀልዮት ነው ።በታላቁ መፅሐፍ “ በእግዜአብሔር እናምናለን ።“ እና
“ አይኖቹ በምድር ሁሉ ያያሉ ።“ ከሚለው ቅዱስ ቃል ላይ ተመስርቶ በአሜሪካ የአንድ ዶላር ላይ ፈጠሪ ሁሉን እንደሚያይ ፤ አሜሪካ በቅጥሩ በጥበቃው ስር እንደሆነች የሚወክለውን ምስል ( the all seeing eye ) ሳይቀር በአሜሪካ መስራች አባቶች የተሸረበ ሴራ ተደርጎ መቆጠሩ ኀልዮቱ ምን ያህል ጥርጣሬን ለመዝራት ምን ያህል ምቹ እንደሆነ ያሳያል ።
አንዳንድ የስነ ልቦና ሊቃውንት ኀልዮቱ በማኪያቬሊያዊ ፅንሰ ሀሳብ በዜጋውና በሕዝብ መካከል ፍርሀትን በመንዛት ላይ ያተኮረ መሆኑን ይተነትናሉ ፡፡በዓለማችን በሴራ ኀልዮት አብነትነት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል የአሜሪካዊ 35ኛ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ላይ የሀገሪቱ የስለላ ድርጅት ( ሲ አይ ኤ ) እጁ አለበት ።እ አ አ በ1971 አፓሎ የተሰኘች የአሜሪካ መንኮራኩር ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ ማረፏን የሚክደው እንዲሁም በተለምዶ በ9/11 አልቃይዳ በዓለም የንግድ ድርጅት ህንፃዎች ፣ በፔንታጎንና በመንገደኞች አውሮፕላን ከ3ሺህ በላይ አሜሪካውያንና የውጭ ዜጎች ባለቁበት የሽብር ጥቃት አሁንም ሲ አይ ኤ ተሳትፎበታል።ኤች አይ ቪ / ኤድስን አሜሪካ ነች ጥቁሮችንና ሌሎች ለመጨረስ በቤተ ሙከራ የፈጠረችው እና የእንግሊዟን ልዕልት ዲያና ፈረንሳይ ፓሪስ በመኪና አደጋ የሞተችው በሀገሪቱ የስለላ ድርጅት ኤም አይ 6 እና ንጉሳዊ ቤተሰቡ ሴራ ነው የሚሉ ይገኙበታል ፡፡
ወደሀገራችን ስንመጣ ደግሞ የሴራ ኀልዮትን ባህሪያት ሙሉ በሙሉ ባያሟሉም ህልቁ መሳፍርት ከሆኑ አሉባልታዎች ፣ በሬ ወለደዎች ለአብነት ያህል ሰሞነኛ የሆኑትን ላነሳሳ ።ማንነትንና ኃይማኖትን ኢላማ አድርገው የሚፈጸሙ የንጹሐን ጭፍጨፋዎች በክልልና በፌዴራል መንግሥት እንደሚደገፍ የሚናፈሰው አሉባልታ ይገኝበታል ። ይህ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር ፤ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ልዩነትን ለመጎንቆል የሚደረግ ደባ አካል ነው ።
ሌላው የኮቪድ 19 ክትባትን በውሸት የማጠልሸቱ ሴራም ሕዝብ በመንግሥት አገልግሎት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው የማድረግ የተቀናበረ ዘመቻው አካል ነው ። የሰኔ 15ቱ “ መፈንቅለ መንግሥት “ ሙከራ ፣ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የኢታ ማዦሩ ግድያ በፌዴራል መንግሥት የተቀነባበረ ነው ።ለውጡ በኦነግ ተጠልፏል …! ? ጌታቸው አሰፋ በሌላ ሰው ፓስ ፓርትና ማንነቱን ደብቆ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይሁንታ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ውጭ ሀገር ተልኳል ።ኦሮሚያ ብልጽግና አማራን ለማዳከም እያሴረ ነው ።በኦሮሞ ልሒቃን ተረኝነት እየታዬ ነው እና ሌሎች የሀበሻ ሴራዎች ማህበራዊ አልፎ ተርፎም አንዳንድ መደበኛ ሚዲያዎችን እየተቆጣጠሩት ፤ የቡና ፣ የድራፍት ማጣጫ ከሆኑ ዋል አደር ብለዋል ።እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ነገር በመንግሥትም ሆነ በፓርቲ መዋቅር የሚነሱ ቅሬታዎች ሁሉ መሠረት የሌላቸው አሉባልታዎች ናቸው ማለት አይደለም።
የሴራ ኀልዮት ባህሪያት፦
ሀ . ጥርጣሬን ማንበር፤
እነዚህን እና ሌሎችን የሴራ ኀልዮቶች የሚያመሳስላቸው ሕዝብ በመንግሥቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ፣ እምነቱን እንዲያጣ በተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሚሸረቡ መሆናቸው ነው ።ለውጡ ከባተ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው የሚነዙ አሉባልታዎችን እዚህ ላይ ያጤኑአል ፡፡
ለ . የሌለ ምስል መከሰት፤
የሴራ ኀልዮት የማይገናኙ ሁነቶችን ነጥቦችን በማገናኘት በማገጣጠም ትርጉም መስጠት ፣ ምስል መከሰት መለያ ባህሪው ነው ።ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በህወሓት በበላይነት ተይዘው የነበሩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የብሔር ተዋፅኦን መሰረት ባደረገ መልኩ በመከላከያና በደህንነቱ አንዳንድ ቦታዎችን መያዙን ተከትሎ “ ተረኝነት “ ሰፍኗል ብሎ የሌለን ምስልን ለመከሰት የተሄደበትን እርቀት እዚህ ላይ ያስተውሏል ።በነገራችን ላይ እዚህ ላይ የቡድን መብትን የሚያስቀድመው እና በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ሥርዓት እስካለ ድረስ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያለው በቅደም ተከተል የስልጣን ፣ የሀብት ተጠቃሚ መሆኑን መቀበል pragmatist መሆን የግድ ይላል ።ይሄን የምለው ትክክል ነው እያልሁ ሳይሁን የመጫወቻ ሕጉን ከግምት በማስገባት ነው ፡፡
ሐ . ተአማኒነት ፣ ተቀባይነት፤
አሜሪካውያኑ የሴራ ኀልዮት አጥኚዎችና የፖለቲካ ሳይንስ ሊቃውንት ጆሴፍ ኡዚነስኪ እና ባልንጀራው ከ5 ዓመታት በፊት በሀገረ አሜሪካ ባካሄዱት ጥናት የሴራ ኀልዮት ጾታ ፣ ሀይማኖት ፣ ዘር ፣ ዕድሜ ሳይለይ ተቀባይነት ታማኝነት ቢኖረውም በወጣቶች ግን ይበልጥ ተቀባይነት እንዳለው አረጋግጠዋል ።ከተፈጥሮ አደጋዎች ፣ እንደ 9/11 ያሉ ሰው ሰራሽ ጥቃቶች ፣ የሥራ አጥነት ፣ ተስፋ መቁረጥና ድብርት ወጣቱን የኀልዮቱ ሰለባ እንዳደረገው ጥናቱ አክሎ ጠቁሟል ።የሀገራችን ወጣቶች የኀልዮቱ ሰለባ የሆኑበት ምክንያት ከዚህ ብዙ የሚለይ አይደለም ።ስለዚህ ወጣቱ ሕልም ፣ ተስፋ ፣ ሥራ እንዲኖረው በማድረግ ከሴራ ኀልዮት ምርኮኝነት ነፃ ማውጣት ከማስቻሉ ባሻገር የጥቂቶች ክፉ አጀንዳ አስፈፃሚ ከመሆን መታደግ ይቻላል ።በአንድ ጠጠር ..ይሉት ይሄን አይደል !?
መ . የቡድን ማንነት፤
አንድ የህብረተሰብ ክፍልን ማለትም ነጭ ፣ ጥቁር፣ አይሁድ ፣ ኢስላም ኢላማ ያደረጉ የሴራ ኀልዮቶችን መንዛት ሌላው መለያው ነው ።ኤች አይ ቪ / ኤድስ ጥቁሮችን ለመጨረስ በቤተ ሙከራ የተፈጠረ በሽታ ነው ።አይሁዶች ሚዲያውን በሞላ ተቆጣጥረዋል የሚሉ የሴራ ትርክቶች በአብነት ይጠቀሳሉ ።ወደሀገራችን ስንመጣ ደግሞ በመካከላችን ጥላቻን ፣ መጠራጠርን ለመንዛት በመሳሪያነት እያገለገለ መሆኑን ያጤኑአል ፡፡
ሰ . ፖለቲካዊ ርዮተ ዓለሞች (አይዶሎጂ)፤
ሕዝበኝነት፣ ሶሻሊዚም ፣ካፒታሊዝም፣ ቀኝ ዘመም ሆነ ግራ ዘመም አይዶሎጂዎች የየራሳቸው የሴራ የደባ ኀልዮት ትርክቶች አሏቸው ።ሕዝበኞች ሉዓላዊነትን ካፒታሊዝምን አውሮፓ ሕብረትን ኔቶን ስደተኝነትን የሚያጠለሹ ፣ የሚያሰየጥኑ ተረኮችን ሲነዙ ።ግራ ዘመሞች በበኩላቸው ሚዲያውንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በባለጠጋዎች ጭፍራነት የሚወነጅሉ የሴራ ኀልዮቶችን ያነብራሉ ።የተቀሩትን አይዶሎጂዎች አሰላለፍ በዚህ አግባብ መለየት ይቻላል ፡፡
ረ . የትምህርት ደረጃ፤
መማር የሴራ ኀልዮት ምርኮኝነትን ሊቀንስ ይችላል የሚል አጠቃላይ ዕምነት ቢኖርም የእነ ኡዚነስኪ ጥናት የደረሱበት መደምደሚያ ግን ለየቅል ነው ።የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ 5 አሜሪካውያን አንዱ ለኀልዮት ልባቸውን፣ ጆሮአቸውንና ቀልባቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው ይላል ።ወደ ሀገራችን ስንመጣ የተደረገ ጥናት ባይኖርም ሁለትና ከዚያ በላይ ዲግሪ ያላቸው አንዳንድ ጓደኞቼ በሴራ ፖለቲካ ተጠልፈው በጉንጭ አልፋ ጭቅጭቅ ልቤን ሲያወልቁኝ ስለሚውሉ የጥናቱን ግኝት እጋራና በአመክንዮ ፣ በተጠየቅ ፣ በጥልቅ እሳቤ መሟገት ካልተቻለ የተነበበው የተሰማው ሁሉ እንደ እስፖንጅ ከተመጠጠ ታዲያ መማር ምኑ ላይ ነው !? አበው እመው ተምሮ እማይፅፈ ጾሞ የማያከፍል እንደሚሉት ።በእነዚህ ባህሪያት ማጥለያነት የትኛው የሴራ ኀልዮት ትርክት እንደሆነ ለመለየት እና አበክሮ ጥንቃቄ ለማድረግ ከውዥንብር ከመደናገር ለመውጣት ይቻላል፡፡
እንደ መላ
የሴራ ኀልዮቶችን ማለትም የሴራ ወሬዎችን እውነትነት እና ሀሰትነት ፈትኖ ማጣራት ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ሚዲያና መንግሥት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ።በዘመነ ማህበራዊ ሚዲያ በጥቂት ደቂቃዎች ሀገር የሚያዳርሱ የሴራ የደባ ዋና ዋና ወሬዎችን እግር በእግር እየተከታተሉ በተጨባጭና ሀቀኛ መረጃዎችን ፉርሽ ማድረግ ማክሸፍ ካልተቻለ ሊፈጠረ የሚችለውን ሀገራዊ አደጋ እያየነው ነው ።ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንዲሉ ።ሀገር ፣ ወገን በበሬ ወለደ ወሬ ሴራ እንዳይፈታ አበክሮ በቅንጅትና በርብርብ ሊሰራ ይገባል ።የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የክልል ፕሬስ ሴክሬታሪት መደበኛ ሚዲያዎች ከእነ ማህበራዊ ገጾቻቸው መረጃን በጥራት በፍጥነት በሰፊ ተደራሽነት 24/7 ማሰራጨት ይጠበቅባቸዋል ።አሰራራቸውን አደረጃጀታቸውን እና ብቃታቸውን ከዚህ አንጻር ቆም ብለው መፈተሽ ሰልፋቸውን ማሳመር ይጠበቅባቸዋል ፡፡
ልሒቃን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተከታዮቻቸው በመጨረሻም መላ ሕዝብ አሉባልታ የሴራ የደባ ወሬ ሲሰሙ በተቻለ መጠን ማጣራት በተለያዩ ምንጮች ማገናዘብ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ።ስውር አጀንዳ ያላቸው ኃይላት መጠቀሚያ እንዳያደርጓቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል ። ይሁንና የሴራ ኀልዮቱን ተዋንያን በቀላሉ መለየት አዳጋች ነው ። ምክንያቱም ኀልዮቱ የተዋቀረበት መሠረት በውል የማይታወቅና ሚስጥራዊ መሆኑ ነው ።የእያንዳንዱ ሴራ ስውር አላማ ሕዝብን ፣ ስልጣንን ፣ ኢኮኖሚውን መልሶ ከመቆጣጠር የቡድን ፍላጎት የሚመነጭ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችና ተቋማት የሚሳተፉበት በመሆኑ ለመቆጣጠር ለማክሸፍ የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ያደርገዋል ፡፡
ይሁንና እነዚህ ኀልዮቶች የዳበሩ የዴሞክራሲ ተቋማትና ሚዲያዎች ባሉባቸው ምዕራባውያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እንደኛ ካሉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸሩ ያን ያህል ተፅዕኖ የማያሳድሩ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ ።በአንጻሩ የዳበሩ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በተለይ ጠንካራ ሚዲያዎች ባልደረጁባቸው ሀገራት የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከፍ ያለ መሆኑን እነዚሁ ጥናቶች ያረጋግጣሉ ።ሀገራችንን እንደ አብነት ብናነሳ ከሶስት ዓመት በፊት ለውጡ የነበረው ተቀባይነት እና ዛሬ ያለው ተቀባይነት ሲነጻጸር በተመሳሳይ ደረጃ ላይ አይገኝም ።
ደጋፊን መራጭን ላለማጣትም ሆነ ለማስደሰት ሲባል የተፈፀሙ ፖለቲካው ስህተቶች የራሳቸው ድርሻ ቢኖራቸውም እንደ በሬ ወለደ አይነት ነጭ ውሸቶችን አልቧልታዎችን የሴራ ኀልዮቶችን ያህል ተፅዕኖ እንደሌላቸው ለመግለፅ የሕዝብ አስተያየት ጥናት እስኪያደርግ መጠበቅ አያስፈልግም ።የተቀናጀ የደባ የሴራ ፖለቲካ ለውጡንም የሀገራችንን መጻኢ ዕድልም አደጋ ላይ እንደጣለው ከልብ ልብ ማለት ያስፈልጋል ።መንግሥት ሚዲያዎች ሀገር ወዳድ ዜጎች የችግሩን አደገኝነት የሚመጥን የተቀናጀና የተናበበ ሥራ መስረት ይጠበቅባቸዋል ።
በተለይ መንግሥትና ሚዲያው አሉባልታው ወደ ሴራ ደባ ኀልዮት ፖለቲካ ከማደጉና በሕዝብ ዘንድ መደናገርን ፣መጠራጠርንና ውዥንብርን ከመፍጠሩ በፊት የሆነውን ከስር ከስር ለሕዝብ ማሳወቅ ይገባል ።ቀደም ሲል እንዳሳሰብሁት አሰራርን አደረጃጀትን ከዚህ አንጻር መቃኘት መከለስ ያስፈልጋል።የመንግሥት አሰራር ከዚህ ይበልጥ ግልፅ ፣ አሳታፊና ተጠያቂ ሊሆን ይገባል ፡፡
ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ነውና ብሂሉ ሀገራዊ ለውጡ በበሬ ወለደ ውሸት እንዳይፈታ በትጋት መስራት ይገዳል ።በሀገራችን የመጣው ለውጥ የሴራና የደባ የመጠላለፍ ፖለቲካ ጥላ እንዳጠላበት እና ከፊቱ አደጋ እንደተደቀነበት ምልክቶችን እያየን ነው ።ይሄን ለውጥ ዳር ለማድረስ ያጠላበትን ጥላ የመግፈፍ የዜግነት ድርሻችንን የመወጣት ኃላፊነት ተጥሎብናል ።
ይሄን ተማፅኖ የማቀርበው ይሄን ለውጥ ከእነ ውስንነቶቹ ከማሳካት ዳር ከማድረስ በቀር አማራጭም አቋራጫም አለን ብዬ ስለማላምን ነው ።በታሪካችን ከአንዴም ሁለት ሶስቴ ይሄን መሰል አጋጣሚዎችን አባክነናል ።አሁን ግን ለማባከን የሚያቀናጣ ሌላ ዕድል እጃችን ላይ የለም ።ይሄን ታሪካዊ መታጠፊያ በእንዝህላልነት ማባከን በአግባቡ አለመጠቀም ልንገምተው ወደ ማንችል መቀመቅ ተያይዞ ለመውረድ የመወሰን ያህል ሆኖ ይሰማኛል ።የፊታችን ግንቦት 28 ቀን የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኃላፊነትን መወጣት ታሪካዊ አጋጣሚው ሳይባክን ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ አንዱ ማሳያ ነው ።
ሀገራችን ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቅ !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2013