በአገራችን ሲናገሩ ከሚደመጡና፤ ብዙዎችም ቃላቸውን ሰምተው ከሚተገብሩላቸው ወጣት የሃይማኖት አባቶች አንዱ ናቸው። ከሃይማኖታዊ አስተምህሮም ባሻገር በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይ ወጣቱን ለማስተማር በሚያደርጉት ጥረት ይታወቃሉ፤ በዚህም በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ብቻ ሳይሆን በጋዜጦች ላይ በመፃፍ ሃሳባቸውን ለሌሎች ያካፍላሉ፤ ያስተምራሉ፤ አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ።
እኛም በተለይ በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ የገባንበት ሃገራዊ ምስቅልቅል እና ቀውስ የምን ውጤት ነው፤ ከዚህስ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት ስንል ጥያቄ አነሳንላቸው። እሳቸውም ከሰፊው ልምዳቸውና እውቀታቸው ጨልፈው ጠንከር ያሉ አስተማሪ ቁምነገሮችን አካፈሉን። እናም በዚህ መልኩ አቀረብንላችሁ። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የትውልድ ግንባታ ሲባል ምን ማለት ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡– የትውልድ ግንባታ ሊባል የሚችለው ነገር በሁለንተናዊ አቅጣጫ አንድ ዜጋ ወይም ሰው ሰውነቱን ሊመጥን በሚችል ቁመና እንዲገኝ ማስቻል ነው። ከዚህም አንጻር በሁሉም አቅጣጫ ብለን ስንል በኢኮኖሚ ብቻ ማለታችን አይደለም።በአስተሰሳቡ፣ በኢ ኮኖሚው ከማህበረሰቡ ጋር ባለው መስተጋብር ብለን ልንጠ ቅሳቸው የምንችላቸው ጉዳዮች ናቸው።
አንድ እድገት ወይም አንድ ግንባታ ትክክለኛ ግን ባታ ነው ሊባል የሚችለው ሚዛኑን የጠበቀ እድገትና አካሄድ ሲኖረው ነው።ለምሳሌ እድገትን በሶስት አቅ ጣጫ ልንመለከተው የምንችለው ጉዳይ ነው።ከዚያ ወደ ግንባታው እንሄዳለን። አንድ ነገር ጤነኛ እድገት አደገ ልንል የምንችለው ወደላይ፣ ወደታችና ወደጎን ሚዛኑን ጠብቆ ማደግ ሲችል ነው።ስለዚህ ትክክለኛ የትውልድ ግንባታ ብለን ልናነሳ የምንችለው ነገር ወደላይም፣ ወደጎንም ወደታችም ትክክለኛነቱንና ሚዛናዊነቱን ጠብቆ መገንባት ሲችል ነው፡፡
ለምሳሌ አንዳንድ ሰው ዝም ብሎ በመንፈሳዊ ህይወቱ ብቻ ወደላይ ይገነባል። ማህበራዊ ህይወቱ ላይ በጣም ደካማ ይሆናል።የቆመበት እውቀት ላይ ደካማ ይሆናል።ስለዚህ ጤነኛ እድገትና ግንባታ ልንል የምንችለው በዚያ መልኩ ነው። ስለዚህ ትውልድ በትክክል ተገነባ ልንል የምንችለው በሁሉም አቅጣጫ ሚዛኑን ጠብቆ ማደግ ሲችል ነው። በኢኮኖሚ ያደገ ትውልድ ብቻውን በሞራልና በስነምግባር ማደግ ካልቻለ እንዲሁም በማኅበራዊ መስተጋብርና የጋራ በሚያደርጉት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በእውቀት መገንባት ካልቻለ የሚመጣ ንፋስ ይጥለዋል። ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫ መገንባት አለበት፡፡
ለምሳሌ የአንድን ተክል ጤነኛ እድገቱን የምታይው ስር ይሰዳል፤ ቅርንጫፎች ያወጣል፤ ወደላይ ያድጋል፤ ትውልዱንም እንደዚያ ነው ማየት የሚገባን። ጤነኛ የትውልድ ግንባታ በሁሉ አቅጣጫ ሚዛኑን ጠብቆ ያደገ ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው። በምክንያታዊ አስተሳሰብ የተቀረጸ ትውልድ ሲኖር ነው፤ ልክ እንደኢኮኖሚ ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ደግሞ ማህበራዊ እሴቶቹን ማወቅ መረዳት ሲችል ነው። ኢትዮጵያዊ ማንነቱን በትክክል ተገንዝቦ እሱነቱን፣ የመጣበትን ታሪክ ሳያጣጥል እንዲሁም ሳያፈርስ በነበረው ላይ ገንብቶ የራሱን ነገር ለማስቀጠል ብቃት ያለው ትውልድ መፍጠር ከተቻለ ነው ትክክለኛ የትውልድ ግንባታ ብለን የምንለው። አንድ ትውልድ በአግባቡ ተገነባ ልንል የምንችለው በዚህ አካሄድ ነው፡፡
ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት የምታይው ነገር ትውልዱ በትክክለኛ አቋምና ሚዛናዊነት አለማደጉ ነው አሁን ያለውን ችግር የፈጠረው።ትውልድ በአንድ አክራሪነት በአንድ ትርክት በጣም ያድግና በሌላ በኩል ያለውን እውነታ አያውቀውም።የሚያውቀው እርሱ ሰፈር ያለውን ችግር ብቻ ነው።ሌላው ሰፈር ያለውን ረሃብ አያውቅም።እሱ ሰፈር የጎደለውን መንገድ ብቻ እንጂ ሌላው ሰፈር የሌለውን ጤና ኬላ አያውቅም።ስለዚህ ትውልዱ ወደጎን አልተገነባም።
እንደገና ደግሞ የቆመበት ራሱን የሚገልጥበት፣ ራሱን የሚያብራራበት አገራዊ እውቀት ላይ በጥልቀት አልተመሰረተም።ስለዚህ እንዲሁ በቴክኖሎጂ እንዲሁ በኢኮኖሚ ይዞ መገኘት ብቻ እንደስኬት እየተቆጠረ ስለተነገረው በየትኛውም መንገድ ነው ይዞ ለመገኘት ጥረት የሚያደርገው። ይህ ደግሞ በየትኛውም መንገድ ይዞ ለመገኘት ጥረት የማድረግ ሞራል አይጠይቅም።
መሰላል ለመውጣት አለው ልዩ ብልሃት፤ የላዩን ጨብጦ የታቹን ረግጦ እንደገና ወደላይ መንጠራራት በመባል ብቻ እንዴትም ያድርገው ሰርቆም ይሁን ዘርፎ ይሁን እድገት ወይም ስኬት የተባለው ኢኮኖሚ ብቻ ነው የሚል እሳቤ ነው የተሰጠው።ስለዚህ አንድ ትውልድ በአግባቡ ተገንብቷል ማለት የሚቻለው በሶስቱም አቅጣጫ ሚዛናዊነቱን ጠብቆ ማደግ ሲችል ነው። በነፍሱ፣ ስሜቱን በመግራት፣ ከሰዎች ጋር ባለው ማህበራዊ መስተጋብር እንዲሁም ደግሞ ራሱን በሚገልጥበት እውቀት ሲገነባ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ትውልድን በመገንባት ሂደት ውስጥ ትልቁ ኃላፊነት የማን ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡– በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ የአንዱን ሚና አንዱ አይተካውም።እናት የቱንም ያህል ጥሩ ብትሆንም የአባትን ቦታ አትተካም።ስለዚህ ሁሉም የራሱ የሆነ ቦታ አለው። በትውልድ ግንባታ ውስጥ ይኸኛው አካል ነው ኃላፊነትን መውሰድ ያለበት ሊባል አይችልም። ምክንያቱም በትውልድ ግንባታ ውስጥ የትምህርት ቤት ድርሻ ከፍተኛ ነው፤ ሰዎች ባህሪያቸው ከሚቀረጽባቸው ተቋማት አንዱ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ኃይማኖት ሁለተኛው ነው። ማህበራዊ ህይወት፣ ጓደኝነት፣ ጉርብትና እነዚህን የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ በአንድ የትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ መሰረታዊ ናቸው፤ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰብ ጭምር ነው፡፡
ስለዚህ ለእኔ እንደዚያ በደረጃ እናስቀምጠው ብለን ካልን ለትውልድ ግንባታ በዋነኛነት ቀዳሚ ኃላፊነት የሚወስደው ቤተሰብ ነው። ያልተሰራ ቤተሰብ የተሰራ ትውልድ አይሰራም። ስለዚህ እኛ ቤት ውስጥ የሚነገሩ ትርክቶች ናቸው ለትውልድ ግንባታ የመጀመሪያውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት። በመሆኑም ልጁ ከቤት የተነገ ረውን ይዞ ትምህርት ቤት ይሄዳል፤ ትምህርት ቤት ይዞ የሄደውን ነገር ለጓደኞቹ ያጋራል። ከቤት ወደትምህርት ቤት ይዞ መሄድ ብቻ አይደለም፤ ከትምህርት ቤት ወደቤትም ይዞ ይመለሳል። ስለዚህ በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ በቅድሚያ ቤተሰብ፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ እንደአገር ደግሞ የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በፍጹም ግን አንዱ ሌላውን ሊተካ አይችልም። ሁሉም የየራሱን ሚና መጫወት አለበት ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በአገራችን ታሪክ የትውልዶች ግንባታ ምን ይመስል ነበር?
አገልጋይ ዮናታን፡– በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ ከ30 ዓመት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ትውልድ በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ፣ ለምን ብሎ የሚጠይቅ፣ ኢትዮጵያዊ እሴቱን አክብሮ የሚይዝ፣ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፣ እኔ ከማለት ይልቅ እኛ ማለት የሚቀናው፣ ከራሱ አጥር ክልል ውጭ ወጥቶ ሌላውን ማህበረሰብ የሚያገለግል፣ እዚህ ተወልዶ አድጎ ሌላ ቦታ ደግሞ ሄዶ አግብቶ ወልዶ የሚኖር ነው።በወቅቱ የነበረው ስርዓተ ትምህርትም የነበረው የአገሪቱ ሁኔታም በከፍተኛ ደረጃ በዲሲፕሊን የታነጸ ትውልድ ገንብቶ አልፏል ብዬ አስባለሁ።
በወቅቱ የነበረው የግሎባላይዜሽን እድገትም አሁን ላለው የትውልድና ቀድሞ ለነበረው ትውልድ የበኩሉን ልዩነት አበርክቷል የሚለው ነገር እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። ምክንያቱም ያኔ በነበረው የግሎባላይዜሽኑ የቴክኖሎጂ እንዲሁም የማህበራዊ ትስስር ገጽ አለመኖር ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው የአስተሳሰብ ምንጮቻቸው እዚሁ በአገር ቤት ውስጥ ነው፤ ከራሳችን አገር ታሪክ፣ ትውፊትና ኃይማኖት የተቀዳ ነው።አሁን ላይ ግን አንድ ወጣት ልጅ አንቺ ዘንድ ቁጭ ብሎ አስተሳሰቡን የሚቀዳው ከምዕራባውያን፣ ከአሜሪካንና ከተለያየ ዓለም ነው።ስለዚህ ወደየቤታችን የገቡት ቴክኖሎጂዎች ግሎባላይዜሽን በራሱ የፈጠረው ነገር በትውልድ ቀረጻ ላይ ትልቅ ጫና አምጥቷል።
ቴክኖሎጂው ትምህርት ቤቶቻችንን ቀድሟል። የኃይማኖት ተቋማት በቴክኖሎጂ ተቀድመዋል። መምህሩ የሚያስተምረውን ትምህርት ተማሪው እውነት ይሁን ውሸት የሚለውን ለማረጋገጥ የተለያዩ ድረ ገጾችን ይጎበኛል እንጂ ዝም ብሎ አይቀበለውም። በፊት ግን የሚቀበለው በቅንነት ነው። ስለዚህ በፊት የነበረውንና አሁን ያለውን ትውልድ አነጻጽሬ የቱ ዘንድ ነው የሳትነው ሲባል 50ዎቹና 60ዎቹ እንዲሁም 70ዎቹን ስትመለከቺ ጎረቤት የጎረቤቱን ልጅ የሚቀጣበት ጊዜ ነበር። እሱ ማለት የተገነባው ትውልድ ከቤተሰቡ አልፎ ለሌላ ሰው ቁጣ ስፍራ የነበረው ነው ማለት ነው። የጎረቤትን ልጅ እንደራስ ልጅ አድርጎ የመቁጠርና ልጁም የመቆጠር እሳቤ የነበረበት ጊዜ ነበር።ስለዚህ ስርዓቶች ሲቀየሩ ነው እኛ የሳትነው ብዬ አስባለሁ፡፡
አንዱ ስርዓት ሲመጣ የነበረውን መልካም እሴት አስጠብቆ ከመቀጠል ይልቅ ከዜሮ የመጀመር ባህል ነው በብዛት ያለው። የቀደመውን ሙሉ በሙሉ አፍርሰን ነው የራሳችንን ለመገንባት የምንጣደፈው። ከንጉሱ ስርዓት በኋላ የመጣው የደርግ ስርዓት ነው። የደርግ ስርዓት ሲመጣ የንጉሱን ስርዓት ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ ሊባል በሚችል ደረጃ ነው።ሌላው ቀርቶ ኃይማኖታዊ እሴቶችን በሚሸረሽር ደረጃ ነው የመጣው፡፡
ከዚያ በኋላ ደግሞ የደርግ ስርዓት ከወደቀ በኋላ የመጣው የኢህአዴግም ስርዓት አስተሳሰቡና ውቅሩ፣ የትምህርት ፖሊሲውና ሌሎቹ ግንባታዎች የዓለምን አጠቃላይ እድገት ያማከለና በዓለም እድገት ተጽዕኖ ስር ሊወድቅ የሚችለውን የኢትዮጵያ ትውልድ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ነበር። የተቀረጹ የትምህርት ፖሊሲዎችም ሆኑ ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል። እንደ እኔ አመለካከት የስርዓት ለውጦቹ አንዱ የሌላውን ጅማሬ እያፈረሰ እንጂ ማስቀጠል ባለመቻላቸው ነው ይህን ያህል የትውልድ ግንባታ ላይ ክፍተት መጥቶ አሁን ላለንበት ችግር የዳረግን ብዬ አስባለሁ።
ሌላው ደግሞ በፊት ከነበረው የትውልድ ግንባታ የሳትነው የት ዘንድ ነው ካልሽኝ የኃይማኖት ተቋማት የትኩረት አቅጣጫቸውን መቀየራቸው ለትውልድ ግንባታ ከፍተኛ የችግር መንስዔ ነው ብዬ አስባለሁ። የትኩረት አቅጣጫ ማለት በራሳቸው እቅፍ ውስጥ ያለውን ትክክለኛውን የኃይማኖታቸውን እውነት ከመንገር ይልቅ ሌላውን ወደእነርሱ ለማፍለስ ብቻ በሚደረገው ጥረት የኃይማኖት እውነትን በቁጥር ብቻ የማሰብ ጉዳይ ተይዞ የቤትሽን ሰው ሳትሰሪ የውጪው ነገር ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጋችን የቤቶቻችን ሰዎች ከአጠገባችን ከእጃችን እንዲያመልጡ አድርጓል። በሌላ አስተሳሰብ ተጽዕኖ ስር እንዲወድቁ አድርጓል፤ በተለይ የመንግስት ተቋማትና የኃይማኖት ተቋማት ከስርዓት ለውጥ ጋር በተገናኘ የትኩረት አቅጣጫቸውን መቀየራቸው በትውልድ ሂደት ውስጥ ትልቁ የችግር መንስኤ ሆኗል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ከ1950ዎቹ ጀምሮ በአገሪቱ የነበሩ የራሳቸውን የቆዩ አገራዊ እሴቶች እየተው ወደውጪው ዓለም የማማተራቸው ምስጢር ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?
አገልጋይ ዮናታን፡– በዚህ አጋጣሚ ማንሳት የምፈልገው ነገር ቢኖር ለምሳሌ ይህንን ትውልድ ያስጨነቁና ያጣሉ እንዲሁም ብዙ ደረጃ ላይ እንዲደርስ እያደረጉ ያሉ ጥያቄዎች በ1950ዎቹ፣ 60ዎቹና 70ዎቹ የነበሩ አይደሉም። በፊትም የነበሩ እንጂ አዲስ የመጣ ጥያቄ የለም። የጥያቄ አይነትና መጠን ሊለያይ ይችላል እንጂ በጥያቄነት ደረጃ ስንመለከተው ያልነበረና አዲስ የሆነ ነገር የለም። ታዲያ ምንድን ነው አሁን ላይ እንዲህ አገሪቱን ያስጨነቃት ነገር ብትይኝ የቀድሞው ትውልድ ይህን ጥያቄ የያዘበት አያያዝ ከአሁኑ ትውልድ ይለያል። የቀድሞው ትውልድ የልብ ስፋትና ምክንያታዊነት እንዲሁም አርቆ ማየት ማለት ነው።አሁን ያለው ትውልድ ከማህበራዊ አንጻር የሚያየው በቅርቡ ያለውን ብቻ ነው። ለእኔ ያኔ የነበረው የትውልድ ግንባታ ላይ ጥያቄዎቹን በአግባቡ፣ በቅንነትና በፍቅር መያዝ ነበረበት። መገፋቱ፣ ጭቆናው፣ የፖለቲካው አሻጥሩ ዛሬ አዲስ የመጡ ነገሮች አይደሉም።ነገር ግን እንዳልኩሽ የነበራቸው የአያያዝ ልዩነት ነው፡፡
በትውልድ ግንባታ ውስጥ ትውልዱ ወደውጪ እንዲሳብ ያደረገው ነገር ምንድን ነው ካልሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ የኢንተርኔትና የማህበራዊ ሚዲያ የቴክኖሎጂ መስፋፋት ነው። ምክንያቱም አንድ ልጅ ቁጭ ብሎ ያለቀለትን ኑሮ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያያል። አንድ ሰው መኪና ሲነዳ ያያል፤ እና ያ መኪና እንዴት ሆኖ እንደመጣ አያይም።በጣም ቅንጡ የሆነ ቁሳቁስንና በዚያ ያጌጡ የፊልም ተዋናይ አሊያ አርቲስቶችን፤ ያየነው ህይወት ይናፍቃል።ያንን ህይወት ሲያሳዩት ያለቀለትን እንጂ እንዴት አንደሚሰራ ማለትም ውጤቱን እንጂ መንገዱን አላሳዩትም።ይህ ቁጭ ብሎ የሚያየው ትውልድ የውጤቱ እንጂ የመንገዱ ናፋቂ አይደለም። ስለዚህ ውጤቱ ዘንድ ለመምጣት መንገዱን አይፈልገውም። በምንም መንገድ ይሁን ውጤት ዘንድ ነው መምጣት የሚፈልገው።‹‹ኤ›› ማምጣት ይፈልጋል፤ ማጥናት ግን አይፈልግም። ሀብታም መሆን ይፈልጋል መስራት ግን አይፈልግም። የሚያየው ቅንጡ የሆነ የኑሮ ዘይቤን ስለሆነ።
ማህበራዊ ሚዲያ ትውልድን በመቅረጽ በኩል ያለው ተጽዕኖ በጣም ከፍተኛ ነው።አሜሪካን አገር አብዛኛው ወጣቱ ትውልድ እድሜውን እስኪጨርስ ድረስ በአማካይ 15 ሺህ ፊልሞችን ያያል። ስለዚህ የሚያያቸው ፊልሞች ስለፍቅር ያለውን ትርጓሜ፣ ስለጓደኝነት፣ ስለህይወትና ስለቤተሰብ የሚቀዳው ከቤተሰቡ ሳይሆን ከሚያየው ፊልም ነው። ስለዚህ በትውልድ ግንባታ ሂደት ላይ አሁን ያለው ትውልድ ወደውጪው ዓለም የተሳበበት ምክንያት በአብዛኛው በቴክኖሎጂው አማካኝነት ምዕራባውያን ወደአገራችን መግባት በመቻላቸው ነው።ስለዚህ የእኛ ዝግጅት፣ ግንባታና አስተሳሰብ ይህንን ተቋቁሞ የራሱን ማስቀጠል የሚችልበት ቁመና ላይ አልነበረም።አስተውለሽ ከሆነ ጃፓናውያን የአኗኗር ዘይቤያቸው ከምዕራባውያን ፈጽሞ የተለየ ነው።ቴክኖሎጂው ስለሌለ አይደለም፤ ነገር ግን እንደአገር እንደማህበረሰብ የነበራቸው አደራጃጀትና ቁመና የሚመጣባቸውን የባህል ወረራ እና የአስተሳሰብ ወረራ ሊመክት በሚችል መልኩ የተገነባ ስለነበረ ነው።ስለዚህም ትልቁ ነገር ይህ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ለአንድ ልጅ ሞባይል ገዝተሽ ስትሰጪው ገዝተሽ የሰጠሽው ሞባይል ብቻ አይደለም።ራስህን አጥፋ ብለሽ ሽጉጥ እንደሰጠሽው ቁጠሪ።ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት ሽፋኑ ከ75 እስከ 80 በመቶ ያህል ነው።ሌሎች ኢንተርኔት ያልደረሰባቸው አካባቢዎች አሉ።ከዚህ ከ75 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የኢንተርኔት ሽፋን ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው በዋነኛነት የሚከታተለው ወሲብ ነክ ፊልሞችን ነው።ለምሳሌ አንድ ወቅት ላይ በተደረገ ጥናት ጎግል ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ወሲብ ነክ ቃላትን ከሚጽፉ አገሮች በዓለም አንደኛ ኢትዮጵያ ነች።በእድሜ አማካዩን ማስተዋል ከተፈለገ ደግሞ ከ12 ዓመት እስከ 80 ዓመት የሚደርሱ ሰዎች ናቸው።ይህ የሚያሳየው ቴክኖሎጂው፣ ኢንተርኔቱ፣ ማህበራዊ ሚዲያው ምን ያህል የትውልዱን አስተሳሰብ እየቀረፀ እንዳለ ነው።በጥቅሉ ትውልዱ በዚያ ቁጥጥር ስር ሆኗል ማለት ነው፡፡
ለዚህም ነው አንዱ ስርዓት ወድቆ ሌላው ሲመጣ የቀደመው እየተናደ ሲመጣ አሁን ያለው ትውልድ የተመሰረተበት ምንም አይነት እሴት የሌለው።ምክንያቱም ይኸኛው ትርክቱን ሲጀምር የቀደመውን አጣጥሎ ነው። ስለዚህ ይኸኛው ትውልድ የትኛውን አድንቀሽለት የትኛውን አርዓያ አድርገሽለት ባለው ላይ ታስቀጥይለታለሽ።ለዚህም ነው የቴክኖሎጂው ጉዳይ ይበልጥ ወደውጪ እንዲሳብ ምክንያት የሆነው።
አዲስ ዘመን፡– እንደአገር ምን አትርፈናል ብለው ያስባሉ?
አገልጋይ ዮናታን፡– በትውልድ ግንባታው ላይ ያተረፍነው ነገር እያየነው ነው።ያተረፍነው ጥላቻ፣ ቂም፣ በቀል እንዲሁም ግላዊነትን፣ የሰውን ችግር ለሀብት ማካበቻ ማዋልን እንደድል አድርጎ የሚጠቀም ዜጋ ነው ያፈራነው።ለምሳሌ በቆሎና ስንዴ ደብቆ ሰው ሲርበው ደብቆ ሸጦ መኪና መግዛትና እሱን ደግሞ እንደ ትልቅ ኩራት የሚወስድ ትውልድ ነው።የስራ እድል በመፍጠር ለሌላው ኑሮ ቀኝ እጅ ከመሆን ይልቅ የሌላውን ነገር ነጥቆ የራስን ነገር ለማስቀጠል መፈለግን ነው ያተረፍነው፡፡
በመሰረቱ ባልተገነባ ትውልድ የሚገነባ አገር ሁሉ ይፈርሳል። ለእኔ ከግድቡ እኩል የትውልዱ ግንባታ ያሳስበኛል። ያልተገነባ ትውልድ የተገነባ ድልድይ ያፈርሳል። ለእርሱ ምኑም ነው።አየሽ ትውልዱን ሳትገነቢ ኮንዶሚኒየም ቤት ብትገነቢ መቃሚያ ብሎም መጥፊያ ነው የሚሆነው።
ባለፉት ዓመታት በጣም በርካታ የመሰረተ ልማት በአገሪቱ ተካሂዷል።ነገር ግን ይህ ግንባታ ትውልዱን ሊያስደስተው አልቻለም።ምክንያቱም ያልተሰራ ትውልድ ሁልጊዜ የተሰራ መንገድ መሞቻው ነው የሚሆነው። የተሰራው የትኛውም ልማት መጥፊያው ነው የሚሆነው። ስለዚህ በአንድ አገር ግንባታ ከምንም በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የትውልድ ግንባታና ቀረጻ ነው፡፡
አሁን አሁን በትውልድ ግንባታ ሂደት ላይ አብዛኛውን ትውልድ እየገደልን ነበር። ምክንያቱም የትምህርት ማስረጃ ነው የተባለው ዲግሪ ሲሰጠው እንዴት ነበር።ገበያ ላይ እንደሚቸረቸር ሸቀጥ በአስርና በአስራ አምስት ሺህ ብር እየተገዛ ነው። ይህ ትውልድን እንደመግደል ነው የሚቆጠረው። ስለዚህ ከየትኛውም መሰረተ ልማት ይልቅ የትውልድ ግንባታ ላይ ሊሰራ ይገባል።አገር የሚኖረው ትውልድ ሲኖር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ትውልዱ ለመደማመጥ እልኸኛ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
አገልጋይ ዮናታን፡– መደማመጥ ያቃተን የመጀመሪያው ነገር አንዳችን ሌላውን ስናስተምር ከእኛ ውጭ ሌላውን እንዳይሰማ አድርገን አደንቁረን ነው የምናስተምረው። እኛ ብቻ ነን ፖለቲከኛ፣ ኃይማኖተኛ፣ የዚህች አገር ተቆርቋሪ ብለን የትውልዱን ጆሮ አደንቁረን ነው የምንሰራው። ከእኛ ውጭ ያለውን እውነት አመዛዝኖ እንዳይቀበል የማድረግ እንዲሁም የእኛ የግል ንብረት ወይም ቁስ ይመስል ነው እንዲህ የምናደርገው፡፡
የትኛውም ትውልድ የአገር ባለአደራ ነው እንጂ ባለቤት አይደለም። የአገር ባለቤት የሚባለው የሚቀጥለው ትውልድ ነው። አሁን ያለው ባለአደራ ነው።አሁን በዚህ ዘመን ያለነው ሰዎች ባለአደራ ነን።የዚህች አገር ባለቤት ቀጣዩ ትውልድ ነው። የሚቀጥለው ትውልድ ደግሞ ሲመጣ ባለአደራ ይሆናል። ስለዚህ እኛ መንቀሳቀስ ያለብን እንደባለቤት ሳይሆን እንደባለአደራ ነው።የተረከብናትን አገር እንዴት ነው ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ያለብን ብለን ነው ማሰብ ያለብን እንጂ እንዴት አድርገን ነው ራሳችን በልተን መጨረስ ያለብን ብለን አይደለም ማሰብ ያለብን።
ምክንያቱም አንድ ሰው ባለአደራ ነኝ ብሎ ካሰበ ባለቤቱ ሲመጣ ይጠይቀኛል ብሎ ያስባል።ባለቤት ነኝ ብሎ ካለ ግን እንደፈለገው ያደርገዋል።ዛሬ የቱንም ያህል ገንዘብ ብናገኝና ስልጣን ብንይዝ ባለአደራ እንጂ ባለቤት አይደለንም። ባለቤቱ ቀጣዩ ትውልድ ነው።እነርሱ ደግሞ በተራቸው ባለአደራ ይሆናሉ።በዚህ አግባብ አይደለም እሳቤያችንም አሰራራችንም የተቃኘው።ከዚህ አንጻር ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍና ለጊዜያዊ ስልጣን ሲባል የተፈጠሩ ትርክቶች ገንዘብ ወጥቶባቸው፣ ሰው ተመድቦባቸውና ስትራቴጂ ተነድፎባቸው ሌላው ወገን እንዳይሰማ ነው የተደረገው።
የአማራ ወጣት የኦሮሞን እንዳይሰማ፣ የኦሮሞው የአማራን እንዳይሰማ ሆኖ ነው የተደረገው።አንዱ የሌላው ህመም እንዳይሰማው ተደርጎ ነው የተሰራው። ይህ ደግሞ የአገሪቷ ባለቤት እኛ ነን የሚል እሳቤ ስላለ ነው። በእኔ እምነት የዚህች አገር ባለቤት እኔ አይደለሁም። ምክንያቱም እንደገለጽኩልሽ እኔ ባለአደራ እንጂ ባለቤት አይደለሁም። የዚህች አገር ባለቤት ልጄ ነው። ይሁንና በአንደኛ ደረጃ የምናራምደው ይህን እሳቤ አይደለም።
ሌላው የማንደማመጥበት ምክንያት ምንድን ነው ካልሽኝ ለዚህ ደረጃ ያደረሰን የማንደማመጠው እስካሁን የመጣንበት የታሪክም የፖለቲካም ሆነ የብዙ ነገራችን አመጣጥ አንዱ ሌላውን ቀብሮ በሌላው መቃብር ላይ የራሱን ነገር ለመስራት የመጣበት ሁኔታ ነው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው እያሳነስን ለመተለቅ እንጂ የሰራነው እያተለቅን ለመተለቅ አይደለም የሰራነው። ለምሳሌ አጼ ሚኒልክን ልጅ ኢያሱ የት እንደቀበሯቸው አይታወቅም። ልጅ ኢያሱን አጼ ኃይለስላሴ የት እንደቀበሯቸው አይታወቅም፤ አፄ ኃይለስላሴን ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የት እንደቀበሯቸው አይታወቅም። ይገመታል እንጂ።
ያለፉት አብዛኛቹ ዓመታት አንዱ ሌላውን እየቀበረ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው።ስለዚህ ተበዳይ በዳይ ሆኖ በዳይ ደግሞ ተበዳይ ሆኖ የራሱን ትርክት እያሰናሰለ የመጣበት ሁኔታ ነው። ይህ አንዱ አመጣጣችን ነው ብዬ አስባለሁ። የሌላው መኖር የእኛ መኖር ነው፤ የሌላው ስኬት የእኛ ስኬት ነው በሚል አይደለም የመጣነው። የሌላው መኖር የሚያስጨንቀን ሆነናል፤ አብረነው ትልቅ የምንሆን አይመስለንም። ስለዚህ እሱን አሳብደን ወይም ከአገር አስለቅቀን ካልሆነ በስተቀር አንረጋጋም። እንዲህ አይነት እሣቤ ይዘን በሆነ መልኩ መጥተናል።
በመሰረቱ አሁን አሁን እውነቱን አፍርጠን መነጋገር ያለብን ጊዜ ላይ ደርሰናል ብዬ አስባለሁ።እውነት እንግዳ ተቀባይ ነን ወይ? እውነት ሌላውን አክባሪ ነን ወይ? እያልን ሳንፈራ ፍርጥርጥ ማድረግ አለብን።መደማመጥ ያልቻልነው ሁሉም እየተነሳ የዚህች አገር ዋልታና ማገር እርሱ እንደሆነ፣ መስራቿ እርሱ እንደሆነ እንዲሁም የአገሪቷ መስራች እርሱ እንደሆነ አድርጎ ነው የሚናገረው።
በአገር ግንባታ ሂደት ላይ አንድ አካል ብቻ ባለቤት የሚሆንበት ዘመንም ታሪክም አልነበረም።አገር ስትገነባ ብዙ ትውልድ ዋጋ ከፍሏል።ብዙ ትውልድ መጥቷል፤ ሄዷል። ስለዚህ የሚመጣውና የሚሄደው ትውልድ ራሱን እንደ ባለአደራ እየቆጠረ፤ ቀጣዩን ትውልድ እንደ ባለቤት እያየ እና እያሰበ መሄድ አለመቻሉ ነው መደማመጥ ያቃተን ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ ከዚህ አለመደማመጥ አዙሪት ለመውጣት ምን ማድረግ አለብን?
አገልጋይ ዮናታን፡– ቆም ብለን ማሰብ አለብን።ምን መሰለሽ የአንድ ሹፌር ስኬቱ መሄዱ ብቻ አይደለም፣ መቆሙም ጭምር ነው። ስለዚህ ዝም ብሎ መሄድ ስኬት አይደለም። ቆም ብለን እስካሁን የመጣንባቸው መንገዶች ምን አትርፈውልናል ብለን ማሰብ አለብን።እንደ ታሪክ የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ አለን ብለን እናነሳለን።የ50፣ የ60ና የ70 ዓመት ታሪክ ያላቸው አገሮች በሁሉም አቅጣጫ ይበልጡናል። የእኛ ታሪክ ምንድን ነው ዛሬ ያመጣልን? ታሪካችንን ለመልካም ነገር ካልተጠቀምንበትና ለመጠፋፋታችን ምክንያት የሚሆነን ከሆነ እሱ ታሪክ አይደለም። ታሪክ ታሪክ ነው የሚባለው ከትናንት ተምረሽ ዛሬ ላይ ደምረሽና አሻሽለሽ ወደሚቀጥለው መሄድ ከቻልሽ ብቻ ነው በታሪክነቱ ሊጠቅምሽ የሚችለው።ስለዚህ አሁን ቆም ብለን ማሰብ መቻል አለብን።
ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ሁለተኛ ነው ብዬ የማስበው ለተፈጠሩት ችግሮችና ግራ መጋባቶች ኃላፊነቱን ለዚያኛውም ትውልድ ለጎረቤታችንም ከመስጠት ይልቅ እኛ መውሰድ ያለብን። ከእኔ ጀምሮ በዚህች አገር አለመረጋጋት ላይ እንዲሁም የትውልድ የሞራል ውድቀት ላይ የእኔም አስተዋጽዖ አለ ብለን እንደ አንድ አስተማሪ፣ ገበሬ፣ ቤተሰብ፣ ሐኪም፣ ነጋዴ፣ እንደ ኃይማኖት መሪ ብለን ወደ ሌላ ሰው ከመግፋት ወደ ራሳችንም ማምጣት ይገባናል። ሁሉም የየድርሻውን ቢወስድ ችግሩ ይቀላል።
ሌላው ደግሞ ለሚፈጠሩት ችግሮች እነ እከሌንና ያለፈውን ትውልድ ተጠያቂ ከማድረግ ያለፈውን ነገር ዘግተን ያሉትን ጥያቄዎችና ችግሮች ኃላፊነቱን እኛው መውሰድ አለብን። ኃላፊነቱን የሚወስድ ትውልድ መኖር አለበት። ደርግ በንጉሱ ሲያሳብብ፤ ኢህአዴግ በደርግ ሲያሳብብ፤ አሁን የመጣው ብልጽግና ደግሞ በኢህአዴግ ሲያሳብብ አሁን ያለው አንድ የአማራ ፓርቲ በኦሮሞ ሲያሳብብ፤ ኦሮሞ ላይ ያለ አንድ የኦሮሞ ፓርቲ አማራ ላይ ሲያሳብብ ይህቺ አገር ወደማያባራ ችግር ውስጥ ነው የምትገባው። ስለዚህ ችግሩ የአንዱ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም፤ ለዚህም ኃላፊነቱን እንወስዳለን፤ እንዲሁም አስፈላጊውን ዋጋ እንከፍላለን የሚል የትውልድ አስተሳሰብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– እንደ አንድ የኃይማኖት አስተማሪ አገር፣ ህዝብና ትውልድ ማለት ለእርስዎ ምን ማለት ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡– እንደ አንድ የኃይማኖት አስተማሪ አገር፣ ህዝብና ትውልድ ማለት ሁሉም የክርስትና አስተምሮዬ የቆመበት መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው።ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ሲመጣ እንደ አገር ወደ እስራኤል ነው የመጣው። እንደ ህዝብ ካየሽ ደግሞ ወደ አይሁዶች ነው የመጣው። እንደ ትውልድ ደግሞ ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት እሱ በነበረበት ትውልድ ላይ ነው የመጣ።ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ወደ ምድር የመጣበት ጉዳይ አገር ነው፤ ህዝብ ነው፤ ከዚያ ትውልድ ነው።ትውልድ የለም ማለት ኃይማኖት የለም ማለት ነው።ትውልድ የለም ማለት ህዝብ የለም ማለት ነው፤ ህዝብ ከሌለ የኃይማኖት ትምህርት የለም። ህዝብም ከሌለ አገር የለም።ስለዚህ የትውልድ ድምር ነው ህዝብ የሚፈጥረው።ህዝብ ነው አገርን የሚሰራው። አገር ማለት ጋራ፣ ሸንተረር፣ ወንዝና ሜዳ አይደለም። አገር ማለት ሰው ነው እንጂ በአይን የሚታየው ግዑዙ ነገር አይደለም። በአጠቃላይ አገርም ሰው ነው፤ ህዝብም ሰው ነው፤ ትውልድም ሰው ነው።የእምነትና የክርስትና ትኩረቱ ደግሞ ሰው ነው።ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለሰው ነው። ክርስቶስ የሞተው ለአማራ፣ ለኦሮሞ ወይም በባህሪ ለተሻሉ፤ በኢኮኖሚ ለዳበሩ ልዩነት በመፍጠር አይደለም።ለሰው ልጅ ነው።ለዚያውም 99ኙን ትቶ አንዱን ፍለጋ ነው የሄደው፡፡
ስለዚህ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ አንድ ሰው ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ነው የምታይው።99ኙ እያሉ አንዱን ፍለጋ ሄደ ካለ ቅዱስ መጽሐፍ ያ አንዱ ለ99ኙ ሙላት ነው። አንዱ በመምጣቱ ነው መቶ የሚያደርገው።ስለዚህ በእግዚአብሄር መንግስት እሳቤ በቅዱስ መጽሐፋችን አስተምሮ ትርፍ ሰው የለም።ዝም ብሎ ተራ ሆኖ የመጣ ሰው የለም።እያንዳንዱ ሰው ዋጋ አለው።
ስለዚህ ለእኔ ትውልድም ህዝብም አገርም የእግዚአ ብሔር መንግስት የቅዱስ መጽሐፍ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ናቸው። በዚህ ምድር ክርስቶስ የመጣው ለሰው ነው እኛንም ደግሞ እንድናስተምር ያዘዘን የሰውን ልጆች ነው።ስለዚህ የእግዚአብሔርም የቅዱስ መጽሐፍም የክርስቶስም ዋና ዓላማ ትላልቅ የኃይማኖት አዳራሾችን እንድንገነባና ትልልቅ ካቴድራሎችን እንድንሰራ አይደለም። ሰው እንድንሰራ ነው።የእግዚአብሔር እርካታም ደስታም ማደሪያውም መቅደሱም ሰው ነው። ስለዚህ ሰው ሲሞት ሰው ሲፈርስ ሰው ሲጠፋ የእግዚአብሄር መንግስትና ዓላማ ነው የሚበላሸው።
ስለዚህ ለእኔ ትውልድ፣ ህዝብና አገር ተቀዳሚውና ዋነኛው አምላክ ሰው ሆኖ የሞተበት ጉዳይ ነው።ስለዚህ የትውልድን ጉዳይ ማጣጣል አይቻልም፤ የህዝብንም የአገርንም።
አዲስ ዘመን፡– የኃይማኖት አስተምህርዎች በአገረ መንግስት ሆነ በትውልድ ግንባታ ትርጉም የሚኖራቸው መቼና እንዴት ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡– ይህቺ አገር ስትገነባ የተገነባችው ዝም ብሎ አይደለም።አገሪቱ የተገነባችበት ድርና ማግ አለ።ቀላል አይደለም፤ ረጅም ዓመት ወስዷል።በመሰረቱ እንዳለው ችግርና ጥያቄ ቢሆን ኖሮና እንደ አንዳንድ የውጪ ጠላቶቻችን ናፍቆት ቢሆን ኖሮ እስካሁን ተበትነናል። በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ሁሉ መከራ እና ፍዳ እያየ ያልጠፋነውና እስካሁን መኖር የቻልነው አገሪቷ እንደ አገር የተሰራችበት ድርና ማግ እምነትና ኃይማኖት ስለሆነ ነው።
በጠንካራ የእምነት መሰረት ላይ የተገነባች አገር ነች።አብዛኛው የፖለቲካ እሳቤዎቻችን የፍትሃብሄር፣ የማህበራዊ፣ የሽምግልና፣ የእርቅ መሰረት የሚያደርገው ኃይማኖት ላይ ነው። ሙስሊሙም በእስልምና ክርስቲያኑም በክርስትና ትላልቅ አስተዋጽኦዎችን በአገር ግንባታ ላይ አድርገዋል።ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ማለት ነው።
ከሆነ ጊዜ በኋላ የመጣው ሐሳብ የኃይማኖት ተቋማት ከአንዳንድ መሰረታዊ ከሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሊወጡ ይገባል።በአገር ግንባታ ሂደት ላይ በዝምታ ነው ማየት የሚገባቸውና አይመለከታቸውም የሚል እሳቤ ያላቸው ነገሮች ናቸው የመጡት።ለምሳሌ ስለፖለቲካ እና ስለአንዳንድ ጉዳዮች ብትናገሪ ‹‹አንተ ኃይማኖተኛ አይደለህም እንዴ፤ እዚህ ውስጥ አትግባ›› የሚል ነገር ይደመጣል። እኔ ለዚህ አይነት ነገር ያለኝ የተለየ ሐሳብ ነው።
ለአገርና ለትውልድ ውድቀት በፖለቲካ ውስጥ ያሉ ሰዎች ኃላፊነቱን ብቻቸውን መውሰድ ካልፈቀዱ በአገር ግንባታ ሂደት ላይ የኃይማኖት ተቋማት አይግቡብን ማለት አይችሉም።በቅርብ ጊዜ ሲጠይቁን ነበር፤ አሁን ለተፈጠረው ችግር የኃይማኖት አባቶች ድርሻ ምንድን ነው ይላሉ።የኃይማኖት ተቋማትንና እምነትን በአገር ግንባታ ላይ ገለል አድርገው አገር እንደአገር ስትወድቅ ኃላፊነቱን ኑ በጋራ እንካፈል ማለት ይህ አስቂኝ ነው።ተገቢ አይደለም፡፡
ስለዚህ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መረዳት፤ የተሰራችበትን መዋቅር መረዳት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ስሪት እንደሌላው አገር አይደለም። በዚህች ሀገር ግንባታ ላይ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ የሃይማኖት አባቶች የራሳቸው አስተዋፅኦ አላቸው። ፖለቲካውን ትውልዱን ኢኮኖሚውን ለማጋራት በዋነኛነት የሀይማኖት ተቋማት የራሳቸውን ልጆች በራሳቸው መሰረት ላይ መቃኘት አለባቸው። ልጁ ኪሎ እያታለለ እንዳይሸጥ ኮንትሮባንድ እንዳያስገባ ሰው ከምንም በላይ እምነቱን እንዲያዳምጥ የሞራል ልእልና ያለው ማህበረሰብ ሊፈጥር የሚችለው ሀይማኖት ነው። ቀላል አይደለም ሁኔታው ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገለል ተደርጓል፤ ተገፍቷል፤ ስለዚህ አሁን ሀይማኖቶች በተጠናከረ መልኩ ሀገር ለማዳን መስራት አለባቸው፡፡
በፖሊሲ ቀረፃ በሰርአተ ትምህርት ቀረፃ በብዙ ቀረፃዎች ላይ እነዚህን ያላማከሉ ብዙ ነገሮች ተካሂደዋል። ከሚዲያ ፖሊሲ አንፃር ከብዙ ነገሮች አንፃር። ምክንያቱም በዚህች ሀገር ግንባታ ላይ የሀይማኖት ተቋማት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ከተባለ ስለዚህ ያንን ቦታ በሚመጥን መልኩ አትሊስት የመወሰን ስልጣን እንኳን ባይኖራቸው ሀሳብ የመስጠት እድል እንዲሰጣቸው መደረግ ነበረበት።
ባለፈው ሰላሳ አመት በዚህች ሀገር ግንባታ የሀይማኖት ተቋማት እንደጠላት ነበር ሲቆጠሩ የነበረው፤ ለምሳሌ የባለፈው ሰላሳ አመት የመንግስት አስተሳሰብን ብትመለከቺው ለዚህች ሀገር ከፍተኛ ችግርና ወድቀት መነሻ ኦርቶዶክስን አድርጎ የማቅረብ፤ ከዚያም በፊት የነበረውን አንድን ማህበረሰብ አንድን ብሄርና አንድን ሀይማኖት እንደ ችግር እስከ መቁጠር ደረጃ የደረሱ የፖለቲካ ሰዎች ነበሩ።
በየትኛውም ዘመን በየትኛውም ወቅት የሚኖር ማህበረሰብ የራሱ ችግር የራሱ ጥፋት ነበረው። ግን ደግሞ ከጥፋቱ ይልቅ የገነባው አይበልጥም ወይ የተሰራው አይበልጥም ወይ ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡
እንዲያውም አንድ ወቅት አቦይ ስብሀት ሲናገሩ የነበረውን አይተሽው ከሆነ የዚህች ሀገር ችግር አማራና ኦርቶዶክስ ነው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው። ተገልሏል የምልሽ ለዚህ ነው፤ ተገፍቷል እንደ ጠላት ተቆጥሯል። ሀገር እንዳልገነባ፤ ፊደልን እንዳላበረከተ፤ የተለያዩ ነገሮችን እንዳላደረገ፤ የትምህርት ሂደቶች ላይ በመሰረቱ በሀምሳዎቹ በአርባዎቹ የነበሩ ሰዎች እኮ ትልልቅ ባለስልጣን የሆኑት የቄስ ትምህርት የተማሩ የቤተ ክህነት ተማሪዎች የነበሩ ናቸው።ይህችን ሀገር በከፍተኛ ሁኔታ ያስጠሩ ሰዎች ናቸው።
በደርግ ዘመን ብትመለከቺው ደግሞ ፕሮቴስታንቱን የማሳደድ የአምልኮ ነፃነቱን የመንጠቅ ሁሉ ነገሮች ነበሩ፤ መሰብስብ አይፈቀደም ነበር። የቀብር ቦታ አይፈቀድም ነበር፤ እንደዚሀ እያልሽ በየትኛውም ሀይማኖቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን አስተዋፅኦ ብትመለከቺው ቀላል አይደለም።
ለምሳሌ ካቶሊክን እያት፤ ለብዙ ትምህርት ቤቶች ለብዙ ሆስፒታሎች ለብዙ መሰረተ ልማቶች ትልቅ ዋጋ የከፈለች ናት፤ ታሪኳ የሚናገረው ይኼንን ነው፤ የነበረ ደምቦስኮ የሚባል ትምህርት ቤት የነበሩ የመጀመሪያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በጣም ቀላል ቁጥር አይደሉም፤ የመንግስትን ችግር የቀረፉ ናቸው።
ስለዚህ የሀይማኖት ተቋማት በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ የነበራቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ወደ ማለትና ፖለቲከኞች ሀገሪቱ ልትረጋጋላቸው ሳትችል ስትቀር ኑና ይኼ ፖሊሲ የፈጠረውን የሞራል ውድቀት አግዙን ወደ ማለት መጥተዋል። ይኼ ትክክል አይደለም፤ ሊሆንም አይገባም፤ በተማከለ መልኩ የሀይማኖት ተቋማት አሁንም ባለው የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ አስተዋፅኦ እያደረጉ ሊቀጥሉ የሚገባበት ሂደት ውስጥ እንዲቀጥሉ መንግስት ሁኔታውን ማመቻቸት አለበት እላለሁ።
የሀይማኖት አክራሪነትን በኔ አተያይ እንዴት አየዋለሁ መሰለሽ፤ አንድን መድሃኒት ለበሽተኛው ሊያድነው በሚችለው መንገድ ከመስጠት ከልክ በላይ ሰጥቶ መግደል ማለት ነው። መድሃኒትን በልኩ ብትወስጂው ለፈውስ ምክንያት ይሆናል። መድሀኒትን ከልክ በላይ ቢወሰድ ደግሞ ለጥፋት ምክንያት ይሆናል። ሀይማኖት ሊዳንበት ነው።ትምህርት ከልክ በላይ ከተወሰደ ግን ለጥፋት ምክንያት ይሆናል።
ለምሳሌ በክርስትና ሀይማኖት አስተምሮ መፅሃፍ ቅዱሳችን ጌታ እየሱስ ያስተማረው አንድ ነገር ነው፤ ወዳጅህን አይደለም ጠላትህን ውደድ ነው። ስለዚህ እኔ አንቺን ልጠላ የምችልበት ምክንያት አድርጌ በእግዚአብሄር ፊት ላመካኘው የምችለው ምንም ምክንያት የለም።
የሀይማኖት አክራሪነት በቀጥታ ወደ ጥላቻና ጠላትነት ነው ሰዎችን የሚወስደው። ከእነሱ ውጭ ያለውን ሁሉ እንደ ጠላት እንዲቆጥሩ ነው የሚያደርገው። ስለዚህ ለኔ እንድንድንበት የተሰጠንን መንፈሳዊ መድሃኒት ከልክ በላይ መውሰድ ነው አክራሪነት።
የምናመልከው ጌታ ለኛ ብቻ አይደለም ለወጉት ሁሉ እኮ ነው ይቅርታን የለመነው። በወቅቱ ይገርፉት፣ ይሰድቡት ለነበሩት ሁሉ ነው ይቅርታን የለመነው። የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ነው ያለው። ስለዚህ ከክርስቶስ በላይ አክራሪነት ትርፉ ትዝብት ነው። እሱ እንኳን የህይወት ምንጭ የእውነት ሁሉ ራስ ሆኖ ጠላቶቹን ይወዳል። ከቀራጮች ጋር አብሮ ይበላል፤ ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር፤ ከለምፃሞች ጋር ማህበረሰቡ ካገለላቸው ሰዎች ጋር ይበላል። ሌሎችን ሁሉ ይወዳል። ወደ ራሱ ያስጠጋል፤ በእውነትና በአግባቡ ነው የሚመላለሰው። ስለዚህ የሀይማኖት አክራሪነት እንደዚህ ነው የሚሰማኝ፤ ከእግዚአብሄር በላይ ለእግዚአብሄር እንደማሰብ አይነት ነው።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሠግናለሁ።
አገልጋይ ዮናታን፡– እኔም አመሠግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013