ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መሰረት የሚሆነውን ዘርፍ ዘንግታው ቆይታለች፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ትኩረት ያልተሰጣቸውና ወዳድቀው የሚገኙ የተፈጥሮ ማዕድናት ሞልተዋል፡፡ በዘርፉ የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል ካለመኖሩም ጋር ተያይዞ ውድ የሆኑ ማዕድናት ለማህበረሰቡ አልተዋወቁም፤ በአግባቡም ጥቅም ላይ አልዋሉም፡፡ አሁን አሁን ግን መንግሥት ዘርፉን ለማልማት ከመቼውም በተሻለ ቁርጠኛ አቋም ይዞ መስራት ጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጋማሽ እና የ2011 በጀት ዓመት የመንፈቅ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያስረዳው የውጭ ምንዛሪ ግኝትም ሆነ የሌሎች ተግባራት አፈጻጸም ከሚፈለገው አንጻር አነስተኛ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት በኩባንያዎች በኩል ከማዕድናት ይገኛል ተብሎ የታሰበው ልዩ ልዩ ገቢ 727 ነጥብ 881 ብር ሲሆን 502 ነጥብ 86 ብር ተሰብስቧል፡፡ ይህም የእቅዱ 69 ነጥብ አንድ በመቶ ነው፡፡
በ2008 ዓ.ም 304፣ በ2009 ዓ.ም 231፣ በ210 ዓ.ም 133 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመዝገቡን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተመሳሳይ ባለፉት ሶስት ዓመታት በፌዴራል ደረጃ ከማዕድን 351 ነጥብ 49 ሚሊዮን ብር ታቅዶ 113 ነጥብ 57 ሚሊዮን ብር (32 ነጥብ 3 በመቶ) መከናወኑን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ከፔትሮሊየም ደግሞ 1ነጥብ 52 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እና 1 ነጥብ 113 ሚሊዮን ዶላር (73 ነጥብ ሁለት በመቶ) ተፈጽሟዋል፡ በክልል ደረጃ ከማዕድን 148 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ታቅዶ 81 ነጥብ 56 ሚሊዮን ብር (54 ነጥብ 8 በመቶ)፤ ከጂ ኦሳይንስ አገልግሎቶች ብር 4‚450‚060 ታቅዶ ብር 487‚883 ነጥብ 046 ብር ወይም የእቅዱን 11 በመቶ መሰብሰቡን የሪፖርት ሰነዱ ያመለክታል፡፡
በማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገረመው ነጋሣ እንደሚሉት በዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት እና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተገኙት ገቢዎች ሁለት አይነት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ማዕድናትን ወደ ውጪ በመላክ የሚገኝ የውጪ ምንዛሪ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአገር ውስጥ ከሚሰጥ የማዕድናት ፈቃድ፣ ከእድሳት፣ እና ኩባንያዎች ውል ሲገቡ እና ሲፈራረሙ የሚገኙ የሥልጠና ገቢዎች ናቸው፡፡ ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ባለፉት ስድስት ወራት ከማዕድናት ታቅዶ የነበረው የውጪ ምንዛሪ 528 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነበር፡፡ አፈጻጸሙ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ወደ 30 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ ካለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው ወርቅ ስለሆነ ነው፡፡ ወርቅ የሚመረተውም አንደኛው በኩባንያዎች በዘመናዊ መንገድ እና ሁለተኛው ደግሞ በባህላዊ መንገድ ነው፡፡ በኩባንያዎች ይመረት የነበረው በሜድሮክ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በማህበረሰቡ ከተነሱ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ምርቱ ቆሟል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በባህላዊ ማዕድናት ዘርፍ የሚገኘው በጣም ዝቅተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ ነው፡፡ አሁን በአገሪቱ ከሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ እሱም ቢሆን ለኮንትሮባንድ ተጋላጭ ሆኗል፡፡ የሚመረተው ወርቅ በህጋዊ አሰራር ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባበት ሁኔታ ባለመኖሩ የሚገኘው የውጪ ምንዛሪ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ እነዚህና መሰል ምክንያቶች ተደራርበው የውጪ ምንዛሪ ግኝቱን ዝቅተኛ እንዳደረጉትም ዳይሬክተሩ ተናረዋል፡፡ በእኛ አገር የውጪ ምንዛሪ ሲነሳ ተጠቃሹ ወርቅ ነው ያሉት አቶ ገረመው፤ 95 በመቶ የውጪ ምንዛሪ የሚገኘው ከዚሁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአንድ ምርት ላይ ብቻ ማተኮር የራሱ የሆነ ችግር አለው፡፡ ሌሎች የማዕድናት ምርቶችንም ማምረት እና ለውጪ ገበያ ማቅረብ ነበረብን በሚል አሰራራችንን ገምግመናል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ሌሎች እንደ ኦፓል፣ሣፋየር፣ ኢመራልድ ያሉ ውድ ውድ ማዕድናትም በአገራችን በሰፊው ይመረታሉ፡፡ በእነዚህ ላይ የሚስተዋለው ትልቁ ችግር እሴትን የሚጨምር አሰራር አለመከተል ነው፡፡ የሚላከው ጥሬ ማዕድን ስለሆነ የሚገኘው የውጪ ምንዛሪ በጣም ዝቅተኛና እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ ማዕድናትን እሴት ጨምረን የምንልክበት መንገድ እንዲፈጠር በካናዳ መንግሥት በሚታገዝ አንድ ፕሮጀክት 15 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ በጋራ እየሰራን እንገኛለን ያሉት ዳይሬክተሩ እነዚህን ጌጣጌጦች በምን አግባብ እሴት ጨምረን ወደ ውጪ ገበያ እንልካለን የሚለውን ፓኬጅ ቀርጸን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች ጌጣጌጦቹን እዚሁ አገር ቤት ውስጥም በቱሪዝም በኩል በውጪ ምንዛሪ መሸጥ እንዲቻል እየተሰራ በመሆኑ በፓኬጁ ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሚላኩ ጥሬ ማዕድናት ከሚደርሱብን ጉዳቶች መካከል አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጪ ምንዛሪ እያጣች መሆኑ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻልበትን መንገድ ማሳጣቱ ይጠቀሳል ያሉት አቶ ገረመው፣ በቻይና እና በሕንድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ አገራት የሚላኩ ጥሬ ማዕድናትን አሣምረው እሴት የሚጨምሩ ጌጣጌጦች በማምረት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ቁጥር እና የሚሸጡበት የዶላር ዋጋ ቀላል አለመሆኑን አነጻጽረው አንስተዋል፡፡
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ሚኒስቴር ዶክተር ሣሙኤል ኡርካቶ እንደገለፁት ዘርፉ ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ከሚያስገቡ ዋና ዋና መስሪያ ቤቶች አንዱ ነው፡፡ የከበሩ ማዕድናትን በተለይም ወርቅን በቀጥታ ለአለም ገበያ በማቅረብ የሚገኝ ነው ምንዛሪው፡፡ በአገሪቱ ስድስት ክልሎች ወርቅን በባህላዊ መንገድ የሚያመርቱ በርካታ ማህበራት ይገኛሉ፡፡ በዘመናዊ መንገድ ወርቅ በማምረት የተሰማሩት ግን ሜድሮክ እና ኢዛና የተባሉ ሁለት ኩባንያዎች ናቸው፡፡
በየጊዜው እየቀነሰ ለመምጣቱ ዋናው ምክንያት የመጀመሪያው በስድስቱ (ኦሮሚያ፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ፣ ትግራይ፣ጋምቤላ) ክልሎች በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማምረት የተሰማሩ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሰዎችን አለማገዛቸው እንደሆነ ተናረዋል፡፡ የሚያመርቱትን ምርት ከገበያ ጋር ከማገናኘት ያለፈ እገዛ እንዳልተደረገላቸውና እነዚህን ሰዎች ወደ መደበኛ ቢዝነስ ማሸጋገር፣ ማበረታታት፣ በቴክኖሎጂ ማገዝ እና ሌሎችም አስፈላጊ ሁኔታዎችን ማሟላት ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እንደሚጠበቅም ገልፀዋል፡፡ የሚጠበቀውን ያህል ምርት ለማግኘት አምራቾቹን ማገዝ ግዴታ መሆኑን አንስተው፤ ይሄ በደንብ ባለመሰራቱ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች በራሳቸው ፍላጎት ላይ ተመስርተው፣ የራሳቸውን ጉልበት ተጠቅመው የሚያመርቱትን ነው ለአለም ገበያ እያቀረብን የምንገኘው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ጥራት ያለው የማዕድናት መገኛ ጂኦሎጂካል ሠርቬይ መረጃ መሰብሰብ እና ማደራጀትም እጥረት መኖሩን ጠቁመው የሃያ አምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ሳሙኤል እንዳሉት፤ ሁለተኛው ጉዳይ የኩባንያዎች ድርሻ ነው፡፡ በዚች አገር ላለፉት ሃያ ዓመታት በዘመናዊ መንገድ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች ሁለት ብቻ ነበሩ፡፡ ሜድሮክ ሰፋ ያለውን የወርቅ ገበያ ድርሻ ይዟል፡፡ አሁን በማምረት ላይ አይደለም፡፡ ከዚህ ኩባንያ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙት ችግሮች አሉ የሚሉት ዶክተር ሳሙኤል ላለፉት ሃያ ዓመታት ፈቃድ ወስዶ መስራቱን ለቀጣይ አስር ዓመታት ፈቃድ በሚያድስበት ወቅት መታየት የነበረባቸው ጉዳዮች ባለመታየታቸው የተፈጠረ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በኩል ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር እየተመካከረና በመግባባት ሲሰራ ነበር ወይ የሚለው መጣራት ስለሚኖርበት በህዝቡ ጥያቄ መሰረት በፍተሻ ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ የረዥም ዓመታት የምርቱ ሂደት ከሕዝቡ ጋር የነበረው ቁርኝት ምን ይመስላል፣ የአካባቢ ጥበቃ ሥራው እንዴት ነበር፣ ከጤና አንጻር ምን ጉዳት ተከስቶ ነበር የሚሉ ጉዳዮችን ለማወቅ ሳይንሳዊ ጥናት እየተካሄደ መሆኑንና ሶስት ሺህ ቤተሰቦች ናሙና ተወስዶ የዚህ ኩባንያ ሥራ በትክክል ጉዳት ማድረስ አለማድረሱ ተለይቶ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ ጥር አጋማሽ የመጀመሪያው ጥናት እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም፤ አገሪቱ ወርቅ ማምረት ትፈልጋለች፡፡ ነገር ግን ህዝብን እንዲጠቅም እንጂ በሚጎዳ መልክ በፍጹም ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡ ሌላው ወርቅ አምራች ኩባንያ ኢዛና ነው፡፡ በግብዓት ችግር በሙሉ አቅም ካለማምረት አልፎ ቆሞ እንደነበረ አንስተው አሁን ላይ ብድር አግኝቶ ችግሩ በማቃለል ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የወርቅ አምራች ክልሎች የተከሰተው የጸጥታ ችግር በዚህ ስድስት ወር ውስጥ በወርቅ ምርት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡ ምርቱ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዳይደርስ አድርጓል፡፡ ለኮንትሮባንድ ሰለባ ሆኗል፡፡ ወደ ህጋዊ ገበያው አለመምጣቱ እንጂ በህገ ወጥ ገበያው ምርቱ አለ፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ አምራቾች ፈቃዳቸውን ለመመለስ ይዳረጉ ነበር ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሰፊ እርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ሚንስትሩ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጀምሮ ማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ ከግብርናው ባልተናነሰ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ እንዲሆን መልማት አለበት የሚል አቋም ተይዟል ብለዋል፡፡
ዘርፉን በአግባቡ አለማልማታችን እንጂ የውጪ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ ማስገኘት የሚችል አቅም እንዳለና በዚህ የተነሳም አሁን ያለው ተቋም ችግሩ በጥናት ተለይቶ ዘርፉን ማልማት በሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች፣ ብቁ የሰው ኃይል እንዲደራጅ እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሰረት ለአስር ዓመት የተንከባለለ የማዕድን ፖሊሲ ረቂቅ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የነዳጅ ፖሊሲ ረቂቅ ተዘጋጅቷል፡፡ በ1976 ዓ.ም በ26 አንቀጾች የተዘጋጀው የኢትዮጵያ መዳብ ሥራዎች አዋጅ ተሻሽሎ 76 አንቀጾች አካቶ፣ አዳዲስ የፔትሮሊየም ሐሳቦች ይዞ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡ አያይዘውም፤ የሥነ ምድር መረጃ ጥራቱም ሽፋኑም አስፈላጊ ነው ያሉት ዶክተር ሳሙኤል የማዕድን አለኝታ ቦታ ብቻ ሣይሆን በመጠን ጭምር ቢደራጅ አልሚ ኢንቨስተሩ ከየትኛውም አለም አስልቶ መምጣት ይችላል፡፡ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ አሁንም መስራት አልቻልንም፡፡ በዚህ ረገድ የተሰሩ አዋጆችን መከለስና በዘርፉ የዳበረ ልምድና እውቀት ያላቸውን ምሁራን በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ ማዕድንና ነዳጅ መስሪያ ቤት በባህሪው አለም አቀፍ ኩባንያዎችን የመሳብ ኃይል አለው፡፡ አለም አቀፍ ቢዝነስን የማራመድ ሚና በአገሪቱ ይጫዎታል፡፡ በመሆኑም ሜድሮክን ጨምሮ አሁን 60 ትላልቅና አለም አቀፍ ኩባንያዎች በምርት ላይ ይገኛሉ፡፡ 76 ኩባንያዎች በተለያዩ የማዕድን ዘርፎች ፍለጋ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ አምስት አለም አቀፍ ኩባንያዎች በነጋጅ ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ አደረጃጀት ውስጥ የፕሮሞሽን ጉዳይም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በፍጥነት ያደጉ አገራት ተሞክሮ እንደሚያሣየው በማዕድን ልማት ላይ ተገቢውን ሥራ መስራት መቻላቸው ለኢንዱስትሪው ዕድገት እና ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቶላቸዋል፡፡
በአገራችን የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ለማንቀሳቀስም ከፍተኛ የሆነ ከውጪ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን እየተጠቀምን እንገኛለን፡፡ ይሄን በአገር ውስጥ መተካት ይገባናል፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ የአገሪቱን የማዕድን ሃብት ሙሉ በሙሉ ኦዲት አድርገን መጨረስ አለብን፡፡ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ቀድሞ እያሳወቀ የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች በዚያ ላይ ተመስርተው በማቀድ ተመጋጋቢ ሆነው እንዲሄዱ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ምንድን ነው ያለን? ለየትኛው ኢንዱስትሪ ነው የሚሆነው? በምን ያህል መጠን? የሚሉትን በተጨባጭ መለየት ላይ እንደሚሰሩም ሚኒስትሩ ተናረዋል፡፡ የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች፣ የወጡ ማሻሻያዎች እና አዳዲስ ረቂቅ ሕጎች መቼ ወደ ሥራ ይገባሉ በሚል ጠይቀናቸው በዋናነት ለውይይት የቀረቡት ለተቋሙ ሰራተኞች ነው፡፡
ባለቤቶቹ በደንብ እንዲያዩት ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ይቀርባሉ፡፡ የማዕድን ጉዳይ ውጤቱ በጊዜ ሂደት የሚታይ በመሆኑ ለረዥም ጊዜ ማገልገል የሚችሉ የሕግ ማዕቀፎች እና የፖሊሲ ማዕቀፎች መሆን እንዲችሉ በየደረጃው ይመከርበታል፤ በመቶ ቀን ዕቅዳችን ውስጥ እናጠቃልላለን ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ሙሀመድ ሁሴን