በመሰረቱ ህመም የጋራ ነው፤ የማይታመም የለም። የሰው ሲሆን ይጎላል እንጂ ህይወት ያለውም የሌለውም ፍጡር ይታመማል። በመሆኑም መድሀኒቱን ፍለጋ መባዘኑ የግድ ነው። ከቀናው ይፈወሳል፤ ካልሆነም አዲዎስ!።
ፖለቲካ እኮ ከሁለቱም (ህይወት ያለውም የሌለውም) አይደለም፤ ምኑ ይታመማል? እንዴትስ ይታመማል? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ጥሩ ነው። ጥሩነቱም ለውይይት እድል መስጠቱ ነው።
እርግጥ ነው ፖለቲካ ሀሳብ እንጂ ሁለቱንም አይደለም። ሁለቱንም አይሁን እንጂ ከሁለቱም በላይ ነው። ይህ የበላይነቱም የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣንን ሰጥቶታል። ያስራል፣ ይሾማል፣ ይሸልማል ወዘተ። ይህን ሁሉ ሲያደርግ ወደ ማ(መ)ጠፋፋቱና መ(ማ)ገዳደሉ ካደላ ግን ይህን ጊዜ ታሟል፤ አስታማሚም አጥቷል ማለት ነውና ያሳስባል። አሁን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ፖለቲካ የገጠማቸው ስቃይ ይኼ ነው። ፖለቲካው ታሟል፤ በእሱ ምክንያትም አገሪቷ ታማለች። በሁለቱ ምክንያት ደግሞ ህዝብ እያለቀና እተላለቀ ነው።
ትልቁ የፖለቲካ ህመም ሴራ (conspiracy) ነው የሚሉ አሉ፤ አይደለም ትልቁ የፖለቲካ ህመም ድንቁርና ነው ባዮችም ቁጥራቸው “ሴራ ነው” ከሚሉት የሚተናነስ አይደለም። የበታችነት ስሜት ነው፣ የበላይነት ስሜት ነው፣ ድህነት ነው፣ የውጪ ተፅእኖ (እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ) ነው ወዘተ የሚሉም አሉ። ግን የፖለቲካ ህመም እንደ አገሩ፣ አውዱ፣ ማህበረሰቡ፣ እንደየፖለቲካው መልክ፣ አደረጃጀት … ይለያያል የሚለው ሚዛን ይደፋል። ለዚህ ምሳሌው ደግሞ የአሜሪካ የፖለቲካ ህመምና የሱዳን ወይም የእኛ የፖለቲካ ህመም መለያየቱ ነው።
የህመም ነገር ያው ሁሉም እንደሚያውቀው ሲሆን፤ ከትንሿ እራስ ምታት እስከ መጨረሻው ሞት ድረስ ይዘልቃል። ስቃዩም በዚያው ልክ ሲሆን የመዳን እድሉ የሚወሰነውም በአስታማሚና ታማሚ ጥንቃቄና እንክብካቤ መጠን ነው። (ከፖለቲካ አንፃር) በተለይ የሕግ የበላይነት በሌለባቸው አገራት ፖለቲካው ከመታመሙ በፊት ይታመሳል፤ ታምሶም ያምሳል፤ ያጫርሳል።
የፖለቲካ ህመሙ ይህ ነው፤ የሁለቱንም ጥንቃቄ፣ መተሳሰብና መደጋገፍን ይጠይቃል። ያለ መደጋገፍ፣ ያለ ሕግ የበላይነት፣ ያለ መርህ፣ ስነምግባርና አገራዊና ህዝባዊ ሀላፊነት ፖለቲካ ዋጋ የለውም።
በአሁኑ ወቅት ስለፖለቲካ ብልሹነትም ሆነ ህመሙ ከእኛ በላይ ማሳያም ሆነ ምስክር የለም። በተለይም የሰሞኑ አያያዛችን ፖለቲካው ታሟል ከማለት ይልቅ ፖለቲካው ሰክሯል ወይም አብዶ ጨርቁን ጥሏል ብንል ያስኬደናል።
የፖለቲካው መታመም ያስከተለው ችግር መሀሉን ዳር እስከማድረግ ድረስ እየዘለቀ ነው። ንብረት ከማውደም የተቆጠበ በመምሰል የንፁሀንን ህይወት ያለ ማንም ሀይ ባይ እያጨደ ነው ያለው። እዚህም እዚያም እሳት እየነደደ ሲሆን ለመግለፅ በሚያስቸግር፤ በሚዘገንን ደረጃ የሰው ልጅ ህይወት እየተቀጠፈ ነው፤ እናቶችና ህፃናት ሳይቀሩ የተመመው ፖለቲካ ሰለባዎች ሆነዋል።
በእርግጥ ፖለቲካው እክል የገጠመው፣ የማይድን በሚመስል በሽታ የታመመውና ጉዳት የሚያስከትል ጥፋትን እያስከተለ ያለከው እዚህ ብቻ ሳይሆን የትም ነው። አደጉ፣ በለፀጉ የተባሉት ጋር ሁሉ እንደ ድሮው ወላፈኑ ሳይሆን ራሱ እሳቱ እየነደደ ነው። ለዚህ ደግሞ ቀዳሚዋ አገር አሜሪካ ነች።
ምንም እንኳን ችግሩ ድሮም ያለ ቢሆንም የጥቁር አሜሪካዊው ፍሎይድን በነጭ ፖሊስ መገደል ተከትሎ አሜሪካ ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅና ሁከትን አስተናግዳለች። ሀብትና ንብረት ወድሟል፤ ውድ የሰው ልጅ ህይወት ጠፍቷል። ችግሩን ከወደ ኋላው ብንመለከተው ዝርዝሩም ሆነ አይነቱ ብዙ ነው።
ይህ የቀለም ልዩነት በፈጠረው የበታች / በላይነት ስሜት ምክንያት ቀውሱ እስከ ታችኛው ማህበራዊ መዋቅርና እርከን እስከ ሆነው ት/ቤት ድረስ በመዝለቅ መሳሪያ በታጠቁ ተማሪዎች (እርስ በርስ) የጅምላ ግድያ ሁሉ እስኪፈፀም ድረስ ወንጀሉ ስር ሰድዶ ይገኛል። ይህ አይነቱ ወንጀል ለአሜሪካ መሪዎች በተፈራረቁ ቁጥር ራስ ምታት ሆኖባቸው የቆየ የወንጀል ተግባር ነው። በመሆኑም ሲንከባለል መጥቶ አሁን በባይደን አስተዳደር መፍትሄ አግኝቷል ተብሎ እየተስተጋባ ነው።
ሰሞኑን ይህን የፖለቲካው መታመምና መታወክ ያመጣውን ችግር ከመሰረቱ ይነቅለዋል ተብሎ የታሰበ፤ ለባይደን አስተዳደር የመጀመሪያውና ግሩም ድንቅ የተባለውን ርምጃ አሜሪካ ወስዳለች። መነሻውም ይህን ስር የሰደደ የፖለቲካ ህመም ማከምና መፈወስ የሚቻለው በዚህ አይነቱ ርምጃ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ በመደረሱ ነው። በተለይም የግራ ዘመም ፖለቲከኞችን ሴራ ያከሽፋል፤ የትውልዱን ንቃተ ህሊና ያዳብራል ወዘተ የሚለው ደግሞ ከሁሉም በላይ ቀልብን ስቧል።
የአሜሪካ መንግስት የዚህ አይነቱን የፖለቲካ ህመም መፈወስ ይቻላል ወይም ችግሩን ለመፍታት መሰራት ያለበት ትምህርትና ትውልድ ላይ ነው የሚል መነሻን ይዞ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፤ ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት ወደ ተግባር ሊቀየር የመጨረሻው ምእራፍ ላይ መድረሱ ታውቋል።
ይህ የባይደን አስተዳደር የአሜሪካ ፖለቲካ መታመሙን ተከትሎ የወሰዱት ርምጃ በትምህርት በተለይም በስርአተ ትምህርት ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፤ ውሳኔውም ከኬጂ ጀምሮ እስከላይኛው የትምህርት እርከን ድረስ የጋራ ትምህርት (common course) በመሆን፣ በየክፍል ደረጃው እየተመጠነ እንዲሰጥ አንድ ራሱን የቻለ የትምህርት አይነት ሆኖ መዘጋጀቱ ነው።
ይህ አሜሪካ (የባይደን አስተዳደር ወደ ስልጣን ገና ከመምጣቱ የወሰደውና “ፈጣን ርምጃ” የተባለና የተወደደለት) ውሳኔ በሁሉም ግዛቶች፣ በሁሉም ደረጃ ለሚገኙ ሁሉም ተማሪዎች Critical Race Theory የሚል ኮርስ እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲሰጥ የሚል ሲሆን፤ ለወትሮው ወጪው በግዛቶች ይሸፈን የነበረው ከፍተኛ በጀት በፌዴራል መንግስቱ እንዲሸፈን ተደርጎ ወደ ስራ የመግቢያውን ቀናት እየጠበቀ ይገኛል። (በነገራችን ላይ አሜሪካ ወደ ጠፈር የመውጣት ህልሟን በሩሲያ ስትነጠቅ በመጀመሪያ ደረጃ የወሰደችው ርምጃ ቢኖር ስርአተ ትምህርቷን መፈተሽና ማሻሻል መሆኑ ይታወቃል፤ ስለ ትውልድና ትምህርት በተነሳ ቁጥርም ሁሌም ሳይጠቀስ የማይታለፍ የአገሪቱ ውሳኔና ይኼው ስኬት ነው።)
የአገራትን ምሳሌ በዚሁ ትኩስ መረጃ እናብቃና ወደ ራሳችን፤ ወደ ታመመው ፖለቲካችን እና መፍትሄው እንመለስ።
ምንም ማንገራገር አይቻልም፤ ፖለቲካችን ክፉኛ ታሟል። አቅሉን ሁሉ ስቶ የሚያደርገውን አሳጥቶታል። በአግባቡ የሚይዘው ባለቤት ወይም ባለሙያ አጥቶ ይሁን ወይም ሌላ ጠፍቶ ሊያጠፋን አንድ ሀሙስ ነው የቀረው። ህመሙን ለማዳን፣ መፍትሄ ለመሰንዘርና መፈለግ እንኳን ፋታ አሳጥቶ በሰላም ወጥቶ በሰላም ለመግባት ሁኔታዎች ሁሉ አስጊ ሆነዋል። የፖለቲካው መታመም እዚህ ጥግ ድረስ የሄደ ሲሆን፤ የህመሙ ተፅእኖም እዚህ ጥግ ድረስ መጥቶ ሰዎች ለህይወታቸው ከሚያደርጉት ስጋትና ጥንቃቄ ባሻገር እርስ በእርስ መጠራጠርና አለመተማመን ደረጃ ላይ ሁሉ እንዲደርሱ አድርጓል።
አሁን ጥያቄው ፖለቲካችን ታሟል፤ የህመሙ ተፅእኖም በየቤቱ ገብቶ ህይወት እየቀጠፈ ጦሱም ለትውልዶች ሁሉ እየተረፈ ይገኛል። መፍትሄውን በተመለከተ መደበኛ በሆኑም ባልሆኑም መድረኮች ብዙ የሚባል ሲሆን፤ ከመንግስት አቅም ማነስ፣ ጉልበት መላላት ጀምሮ እስከ ሕገ መንግስቱ መሻሻል ድረስ ይሄዳል። ሆኖም እስካሁን አንዱም ላይ ሳይደረስ ህመሙም፣ ችግሩም፣ ቀውስና መገዳደሉም እንደቀጠለ ይገኛል። አሁንም እንድገመውና መፍትሄው ምንድን ነው? ከአሜሪካስ ምን እንማራለን? እጅግ ያሳስባል፤ ያነጋግራልም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013