አዲስ አበባ በዓለም ሦስተኛ የዲፕሎማት ከተማ ናት። ይሁን እንጂ ከተማዋ በሚመጥናት መልኩ መልማት አልቻለችም። የነዋሪዎቿንም ሆነ የባለ ሀብቱን የመሬት ጥያቄ ሳትመልስ ቆይታለች። የእምነት ተቋማትም በተመሳሳይ የመስሪያ ቦታ ይጠይቃሉ። በ1987 ዓ.ም የተደነገገው ህገ መንግስት ለኃይማኖት እኩልነት ነፃነት የሰጠ መሆኑ ቢታወቅም የእምነት ተቋማቱ እምነታቸውን የሚያራምዱበት ቦታ በማግኘት በኩል ችግር እንዳጋጠማቸው የሐይማኖት አባቶች ይናገራሉ። ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከገጠማቸው ፈተናም አንዱ የሚቀርበውን የመሬት ጥያቄ ለሁሉም ማሟላት አለመቻላቸው መሆኑን አንስተዋል።
በከተማዋ ውስጥ እየተነሳ ካለው የመሬት ጥያቄ እና ከዚህ ጋር የተያያዘ ጉዳይ በቅርቡ በሸገር የወዳጅነት ፓርክ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚሁ መድረክ ውዝፍ የመሬትና ተያያዥ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙበት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። በመድረኩ የዕምነት ተቋማት መሪዎች፣ ባለሀብቶች ተሳታፊዎች ነበሩ። መድረኩን የመሩት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና በዘርፉ ያለውን ችግር የመፍታት ሂደቱ እጅግ ከባድ ነበር። ለዘመናት ምላሽ ሳያገኙ የቆዩና በአቧራ የተበላሹ ብዛት ያላቸው ሰነዶችን ማገላበጥ ጠይቋል።
ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የመሬት ጥያቄ ቀርቦባቸው ያልተስተናገዱ ወይም በተለያየ ምክንያትም መስጠት አይቻልም ተብሎ ውሳኔ ያላረፈባቸው ይገኙባቸዋል። እነዚህን በጽሞናና በሰከነ መንፈስ ማየትና መመርመርም አስፈላጊ ሆኗል። ለችግሩ መፈጠር ምክንያት የሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎችን መለየትና ማጥራት ተጨማሪ ሥራ ጠይቋል። በልየታ ሥራው እንደተደረሰበት ለሙያዎቹም ሆኑ በአመራርነት ላይ የነበሩት የስነ ምግባርና የብቃት ማነስ ክፍተት እንደነበረባቸው ተደርሶባቸዋል።
ለቀረቡት የመሬት አቅርቦት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል አስቀድሞ ችግር የፈጠሩትን ከመሬት ስርዓቱ ማስወጣትም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በተሰራው የማጣራት ሥራ 422 ባለሙያዎችን ከመሬት ዘርፉ በማስወጣት ወይንም በማስወገድ ለምላሹ ጥሩ መደላድል መፍጠር ተችሏል።
ምክትል ከንቲባዋ በመድረኩ እንደተናገሩት ሰነድ የማጥራትና የልየታ ሥራ ሲሰራ እንደታየውና ባለጉዳዮችን በማነጋገር በተገኘው መረጃ ከቦታ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ቅሬታዎች ሁለት ናቸው። አንዱ መሬት ያለ አግባብ ተይዟል ወይንም ተወርሯል የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ብልሹ አሰራር መስፋፋቱን የሚያሳይ መረጃ ነው የተገኘው።
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በተለያየ መንገድ የተሰበሰበውን መረጃ ይዞ ነው ወደ ሥራ የገባው። ወደ ርምጃ ከመገባቱ በፊት ግን ለአራት ወራት ያህል ጊዜ ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዳይስተናገዱ ተደረገ። በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች በቆርቆሮ የታጠሩ ቦታዎች ባለቤቶቻቸው እንዲለዩና ህጋዊነታቸው እንዲረጋገጥ ጎን ለጎን ተሰርቷል።
በማጥራቱ ሂደት የመሬት ጥያቄ ቀርቦባቸው ያልተስተናገዱና በተለያየ ምክንያት ውሳኔ ያላረፈባቸው ብዙ ሰነዶች ማግኘት ተችሏል። በተጨማሪም ከመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ 10 ሚሊዮን ካሬ በህገወጥ መንገድ የተያዘ መሬት ተገኝቷል። በማጣራት ከተገኘው መካከልም ህጋዊ ሂደትን ተከትሎ ችግር ሳይፈጠር አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ተመልሷል።
‹‹የተመለሰው መሬት በአግባቡ መልማትና በህጋዊ መንገድ ለሚገባቸው ሰዎች መሰጠት አለበት›› ያሉት ምክትል ከንቲባዋ በውይይት መድረኩ ላይ ለተሳተፉት የዕምነት ተቋማት አመራሮች፣ ባለ ሀብቶች እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ ሴቶችን፣ ህፃናትንና አረጋዊያንን ለሚደግፉ ተቋማት ቦታውን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ፍላጎት፣ አቅምና ዝግጅቱ ይኖራቸው እንደሆንም በመጠየቅ በዝርዝር ተወያይተዋል። 138 ሄክታር መሬት በአንድ ጊዜ ውሳኔ ለአገልግሎት እንዲውል መደረጉንም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።
እርሳቸው እንዳሉት ከተማዋ በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማቶች መቀመጫ ከተማ እንደመሆኗ ደረጃዋን የሚመጥኑ ብዙ ነገሮች ይጎሏታል። ትላልቅ የገበያ ማዕከሎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ መኖሪያ ቤቶች ያስፈልጓታል። የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ማድረግም የከተማ አስተዳደሩ ፍላጎት እንደሆነም ተናግረዋል። ለእነዚህ
አገልግሎቶች ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲስተናገዱ መደረጉን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ያሳድጋሉ ተብሎ እምነት ለተጣለባቸው የማኒፋክቸር ዘርፎችም በተመሳሳይ ትኩረት መሰጠቱን፣ ለጊዜው የቅድሚያ መሥፈርት ያላሟሉ ባይስተናገዱም በሂደት ግን ጥያቄያቸው ምላሽ ሊያገኝ እንደሚችል፣ ለሐይማኖት ተቋማትና አረጋዊያን፣ ሴቶችንና ህፃናትን ለሚደግፉ ድርጅቶች መሬት ከሊዝ ነፃ እንዲያገኙ መደረጉን፣ ከነዚህ ውጭ ለተለያየ አገልግሎት ለሚውል ግንባታ በጨረታ መሰጠቱን ተናግረዋል።
ምክትል ከንቲባዋ ያብራሩትን በከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሜልኬሶ ጃግማ በመድረኩ ይህንኑ አፈፃፀም የሚገልፅ ሪፖርት አቅርበዋል። ኃላፊው በሪፖርታቸው በ5/8/13 የከተማ አስተዳደሩ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች የአፍሪካ ሕብረት የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል።
‹‹ጥያቄዎቹን ለመመለስ አመራሩ 24 ሰዓት ያለ እረፍት ሰርቷል›› ያሉት ዶክተር ሜልኬሶ እንደገለጹት የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በሚፈታ አግባብ ለመሥራት ጥያቄ ያቀረቡ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሐይማኖት ተቋምት ምላሽ አግኝተዋል። በተለይም የመሬት ጥያቄዎች ከሐይማኖት ተቋምት ጉባኤ ጋር በመሆን በወጣው መስፈርት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የተፈታ ሲሆን፣ 12 ነጥብ 1 ሄክታር መሬት ተሰጥቷል። በአጠቃላይ በመዲናዋ 54 ተቋማት ተጠቃሚ ሆነዋል።
በከተማዋ ሴቶች፣ ህፃናትና አረጋዊያንን ለሚደግፉ በጎ አድራጎት ድርጅቶችም ከሊዝ ነፃ ሦስት ሄክታር መሬት ተሰጥቷል። ከተማ አስተዳደሩ የከተማውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ለመቅረፍ ማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፋት አለብኝ ብሎ በያዘው አቅጣጫ መሰረት 400 ጥያቄዎች መቅረባቸውንም አስታውሰዋል።
ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር የሚደግፉ፣ ተገቢነትና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው፣ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጡና ከፍተኛ ካፒታል ያላቸው ተለይተው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። ከጤና ቱሪዝም አንፃር የመሬት ጥያቄ ላቀረቡ ስድስት ተቋማት 22 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ተሰጥቷል።
በውሳኔው ከኩታ ገጠም መሬት ጋር ተያይዞ የማስፋፊያ ቦታ የጠየቁ መልስ እንዲያገኙ ተደርጓል። ለአዲስ የመሬት ጥያቄ አቅራቢዎች በቅርቡ በፀደቀው የሊዝ መነሻ ዋጋ 41 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ ሲቀርብ ለነባሮቹ ደግሞ 12 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት በአጠቃላይ 53 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ቀርቧል። ወደ ሥራ ቢገቡ ከተማዋን ያሳድጋሉ ተብሎ የታመነባቸውን 18 ሆቴል ቤትና ሁለገብ የገበያ ማዕከሎች 17 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ተሰጥቷቸዋል። የከተማ አስተዳደሩ በዚህ መልኩ ያከናወናቸውን ተግባራት ነው ከባለድርሻ አካላት ጋር የተወያየባቸው።
138 ሄክታር መሬት በአንድ ጊዜ ውሳኔ ሲሰጥና የኖሩ ችግሮች ሲፈቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ታሪክ የመጀመሪያው እንደሆነ በመድረኩ የተሳተፉት የእምነት ተቋማት ተወካዮች ተናግረዋል። ከአዲቪንቲስት ቤተክርስቲያን የተወከሉት ተሳታፊ እንደተናገሩት ጥያቄያቸው በረጅም ዓመት መልስ ሲያገኝ የመጀመሪያው መሆኑን ነው የገለጹት።
በበጎ አድራጎት ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ አንቺነሽ ተስፋዬ በበኩላቸው ‹‹አፈፃፀሙ ሴቶች ዕድሉ ከተሰጣቸው ከወንዶች የተሻለ እንደሚሰሩ ማሳያ ነው›› ብለዋል። ወይዘሮዋ ሆኖም በዚህ የካቢኔ ውሳኔ ውስጥ እንዲሁም ውሳኔውን አስመልክቶ በቀረበው ሪፖርት በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የሴቶች ተጠቃሚነት አለመታየቱን ገልጸዋል። በቀጣይ ከተማ አስተዳደሩ ይኼን ለማረም የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅበትም አስተያየት ሰጥተዋል።
አንዲት ስማቸውና የተሰማሩበት መስክ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የመድረኩ ተሳታፊ ባለሀብት በሰጡት አስተያየት ምክትል ከንቲባዋ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አበረታች የሆኑ ሥራዎች መስራታቸውን መስክረዋል። የተሰሩ ሥራዎችን ማድነቅ፣ ያልተሰሩትን ደግሞ መንቀፍ ባህል ሊሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። በከተማዋ የግንባታ ዘርፍ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እጅግ ዝቅተኛ ከቀረበው ሪፖርት መረዳታቸውን አንስተውልናል።
ሴት ባለሀብቶችን ዝቅ አድርጎ ማየት፣ ዕውነት ልማት ያለማሉ ብሎ መጠራጠር፣ የሥነ ልቦና ተፅዕኖ የሚያሳድር እንደሆነና ይኼም ሊስተካከል እንደሚገባ አስተያየት ሰጭዋ ሀሳብ ሰጥተዋል። ይኼ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የመመልከት አስተሳሰብ ሊስተካከልና ሊታረም እንደሚገባም አሳስበዋል። ተሞክሮአቸውንም እንዳጫወቱን ሲያለሙና ውጤታማ ሲሆኑ የተመለከቷቸው ቦታውን ለይስሙላ እንዳገኙት እንጂ በትክክል አልምተው ይጠቀማሉ ከሚል እንዳልሆነ አስተያየቶች ተሰንዝሮባቸዋል። ወንድም ሆነ ሴት አልሚ ሊበረታታ ሲገባው ገንዘብ እንዲሰጥ ወይም ሙስና መጠየቁ አግባብ እንዳልሆነና ሊስተካከል እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል።
በሽመና ሥራ የተሰማሩ አቶ ተስፋዬ ቶላ ለሥራ የሚሆን ግንባታ ለማከናወን መሬት ለማግኘት ብዙ ውጣ ወረዶችን ማሳለፋቸውን ይገልጻሉ። አቶ ተስፋዬ እንዳሉት በቦታ ጥበት ለምርት ለማምረቻ የሚጠቀሙባቸውን የሥራ ማሽኖች ያለ ሥራ ለማስቀመጥ ተገደዋል። ይህ ደግሞ በገቢያቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ከተማ አስተዳደሩ የሰጣቸውን መሬት በፍጥነት እንዲገነቡበት ሁኔታዎችን እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።
አቶ ተስፋዬ እግረ መንገዳቸውንም በሸማ ሥራ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ቢደረግ መንግስትም ሀገርም የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይገልጻሉ። በዘርፉ መሰማራት ያለበትም ለሀገር የውጪ ምንዛሪ ማስገኘት የሚችል ባለሀብት መሆን እንዳለበት ያምናሉ። ሆኖም አሁን ላይ በዘርፉ የውጪ ሀገር ባለሀብቶች እንዲሳተፉበት እየተደረገ መሆኑን ታዝበዋል። በዘርፉ የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል ጠንከር ማለት አለበት ይላሉ።
በመድረኩ ከተለያዩ ባለሀብቶች፣ ከዕምነት ተቋማት መሪዎች እንዲሁም ሴቶችን፣ ህፃናትንና አረጋዊያንን በመደገፍ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየሰሩና እየተንቀሳቀሱ ባሉ ባለ ሀብቶች የአቶ ተስፋዬን ሀሳብ የተጋራ ሀሳብ ሲንፀባረቅ አስተውለናል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤም ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በተለይ ከመሬት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የሥራ አመራሮች ሙስና ሊፈፀም እንደሚችል አምነዋል። መፍትሄው ጉቦ አለመስጠት መሆኑን በመረዳት ባለሀብቱም ሆኑ ማንኛውም ተቋማት ከጎናቸው በመቆም በጋራ ትግል እንዲያደርጉም በመጠየቅ በመድረኩ ላይ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
መሬት ውሱንና ወሳኝ ሀብታችን መሆኑን ተገንዝቦ እሴት በመጨመር በአግባቡ አልምቶ መጠቀም ይገባል። መሬትን በህገ ወጥም በህጋዊ መንገድም የያዙ ክፍሎች ሳያለሙ አየር ባየር በመሸጥ ለመክበሪያነት ከሚያውሉት የዜግነት ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2013