የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአገሪቱ የእግር ኳስ ደረጃ ነጸብራቅ ነው። በአገሪቱ የእግር ኳስ ጉዞ ላይ ዋናውን ድርሻ መያዙ ይነሳል። ለእግር ኳሱ መውደቅም ሆነ መነሳት ትልቅ ሚና አለው። አገሪቱ በእግር ኳሱ ለሚኖራት ተራማጅ ውጤት ዋልታና ማገር ተደርጎ የሚነሳው ይህ ውድድር፤ የስፖርታዊ ጨዋነት መጉደል በሚል በሽታ ከተጠቃ ሰነባብቷል::
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ችግሩ ፈር ለቋል። ችግሩ በክልል እና በመዲናዋ ስታዲየሞች በመዛመት እግር ኳሱን መልክ አሳጥቶታል። እግር ኳሱን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድሮችን መጀመር ተከትሎ «በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ትኩረት አድርጌ ሠርቻለሁ» በሚል መግለጫና ሪፖርት ቢደጋግምም ያለውና የተባለው በተግባር አልታየም፡ ፡ ወደ ሜዳ ሲገባ የሚደረገውና የሚታየው ሁሉ ተሠራ የተባለው ከዲስኩር ያለፈ አለመሆኑን የሚያመላክት ሆነ። የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ለአገሪቱ የእግር ኳስ ጉዞ እንቅፋት ሆኗል፡፡ «ችግሩ አይጸዳም፤ ጸድቶም አያውቅም» የሚሉ ድምፆችም ጎልተው በመደመጥ፤ በኅብረተሰቡ ዘንድ የቆየውን አብሮ የመኖር እሴት የሚያጠፋ፣ አለፍ ሲልም ለንብረትና ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የእግር ኳስ ሜዳዎች የጠብ መናገሻ ለመሆናቸው ከሚነሱ በርካታ ምክንያቶች የደጋፊዎች ሥነ ምግባር መጓደል እንደሆነ ይጠቀሳል።«መጠጥ ጠጥቶ ስታዲየም መግባት» የደጋፊዎች ሥነ ምግባር ፈር ለመልቀቁ ዋነኛ ሰበብ ተደርጎም እንደሚወሰድ ይነሳል።
ከስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ጀርባ የመጠጥ ጉዳይ አብሮ ለመነሳቱ አዲስ አበባ ስታዲየምን እንደ ማሳያ መጥቀስ ተገቢ ነው። በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ መኖሩን ከሚያሳብቁ ትዕይንቶች መካከል በስታዲየም ዙሪያ ያለው ሸብረብ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል። የሸብረቡን ገጽታ የሚያጎሉት ደግሞ በዙሪያው የሚገኙት መጠጥ ቤቶች ናቸው። እነዚህ ቤቶች በተለያዩ ቡድኖች ማልያዎች ባሸበረቁና በቡድን በቡድን ሆነው የቢራ ጠርሙሶች በከበቡ ሰዎች የተጨናነቁ ሆነው ይታያሉ።
ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አዛውንት፤ ለመጠጥ ቤት ያልደረሱ ወይም ከእድሜአቸው ጋር በተያያዘ መጠጥ እንዳይሸጥላቸው በህግ እገዳ የተጣለባቸው ታዳጊዎች ክብ ሠርተው በመጠጣት ከጨዋታው መጀመር በፊት የሚደረግ የደጋፊዎች ሁካታ አላፊ አግዳሚው በስታዲየም ጨዋታ ስለመኖሩ በሚገባ ያስገነዝባሉ። የክለቡን ማንነት በሚያሳብቅ መልኩ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ደጋፊዎች በዚህ ትዕይንት ውስጥ ሆነው መመልከት አዲስ አይደለም። እነዚህ ደጋፊዎች በማወቅ፣ ባለማወቅ፣ በታሪክ አጋጣሚ የሚደግፉት ቡድን የሚጫወትበት ሰዓት ከመድረሱ በፊት በመጠጥ የመድመቅና የመነቃቃቱ ትዕይንት ይከናወናል። ከጨዋታው በፊት ያለው ሁነት በዚህ መልክ ተቃኝቶ ወደ ስታዲየም አብሮ ይገባል። ቆይታውም ከስፖርታዊ ክንውን ወደራቀ፣ ጨዋነት ወደጎደለው አንባጓሮ ሊያቀና እንደሚችል መገመት አያዳግትም። በሜዳ ላይ ያለው እግር ኳስ ይዘነጋል፤ ተረብና ስድብ ይጎላል፤ ጨዋታው ተረስቶ የመጠጥ ቅኔው ወደ ዱላ ከፍ ይላል። አንድ ሁለትዘንግቶ የድብድብ መነሻ የሆኑ የቃላት ዱላዎችን ወደ መወርወር ይሻገራል። በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ የሚንጸባረቀው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እንደዚህ ዓይነት ስለመሆኑ ሀቅ ነው።
ለእዚህ እውነታ ለማሳየት የአዲስ አበባን ስታዲየም ገጽታ እንደ መነሻ ወሰድን እንጂ ችግሩ በሌሎች የክልል ስታዲሞችም ይስተዋላል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ደጋፊዎች መጠጥ ጠጥተው ወደ ስታዲየም የመግባት ባህል መጎልበቱ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መልክ ማጣት ዋነኛው ምክንያት እስከመሆን ደርሷል። ለእዚህም ደግሞ ሰበቡ ስፖርት ስሜትን በመያዙ እንደሆነ ይነገራል። እግር ኳስ በሁለት ተቃራኒ ቡድኖች ውስጥ የሚገኙ 22 ተጫዋቾች ፍልሚያ ሲሆን፤ የእነዚህ ተጫዋቾች የሜዳ ላይ ፍልሚያ አንዳች ዓይነት ስሜት የሚፈጥርና ሰንጎ የሚይዝ እንደሆነ ይታመናል። በተጫዋቾች መካከል የሚደረገው እንቅስቃሴ ተሻጋሪ ስሜትን መፍጠሩ አድማሳዊ ስሜት የሚያሰርጽ ያስብለዋል።
አንድ ቡድን የሚያደርገው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ እንቅስቃሴ ተመልካችን እንደ ሁኔታው ይነዳል። ይሁንና መጠጥ ጠጥቶ የሚገባ ተመልካች ባለበት ግን ከጨዋታው ባሻገር ተመልካቹ የሚነዝረው የስፖርታዊ ክህሎቱ ትዕይንት ሳይሆን አእምሮው ውስጥ የሚላወሰው የመጠጥ ሙቀትና ያልታሰበበት የስሜት መገለጫ ቃል/ቃላት መሆኑ እርግጥ ነው። ታዲያ፤ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር አንዱ መነሻ ይህ አይነቱ ተግባር በመሆኑ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ መጠጥ ጠጥቶ ወደስታዲየም መግባት የሚከለክል ህግ ማውጣት ይገባዋል ሲሉ የሚጎተጉቱ በርካቶች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ችግሩን ቢያውቁትም መፍትሄ ለመፈለግ እንደማይሹ በትችት ይነሳል። ለእዚህ ደግሞ በዋነኛነት የሀገሪቱ እግር ኳስ መሰረቱን የገነባው በቢራ ካምፓኒዎች ድጋፍና አለሁ ባይነት መሆኑ በምክንያትነት ይጠቀሳል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋልያዎቹ የሚደገፈው በቢራ፤ ክለቦች የሚመሰረቱት፤ በቢራ ስፖንሰር የሚሆኑት በቢራ፤ የክለብ ድጋፍም በቢራ፤ በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ የስፖርት ፕሮግራሞች ሳይቀር ስፖንሰር የሚደረጉት በቢራ ካምፓኒዎች መሆኑ ከዚህ ሀቅ ጋር ለመጋፈጥ እንዳይቻል፤ ሚዲያው ሳይቀር የድርሻውን እንዳይወጣ አድርጎታል። የችግሩም ደረጃ እንደቀላል ተጠቅሶ እንዲታለፍ እንጂ፤ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ለመነሳት እንዳይችል በጥቅም ሸምቀቆ ተለጉሞ ዓመታትን እንዲጓዝ ተፈርዶበታል። የችግሩ ደረጃ እግር ኳሱን እየጎዳ መሆኑን ለመታዘብ ቢቻልም መፍትሄ ለማበጀት የተሄደ ርቀት አለ ለማለት አያስደፍርም።
ደጋፊም ወደስታዲየም ጠጥቶ እንዳይገባ የሚከለክል የህግ አጥር እንዳይበጅለት ይህ የእግር ኳስ ጥገኝነት ገትቶታል የሚሉም አሉ። በርግጥ፤ ከቢራ ካምፓኒዎች ጋር መሥራቱ በአንድ በኩል እግር ኳሱን ለማሳደግ ድጋፍ ያደረጋል። በሌላ በኩል፤ ሕፃናትና ወጣቶች የአልኮል ሰለባዎች እንዲሆኑ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እይታዩ ነው። የማስታወቂያ አቀራረቦች በሀገሪቱ ከተደነገገው የማስታወቂያ ህግ ያፈነገጠ ነው። ስፖርቱን በስፖንሰር ለመደገፍ ብሎ ትውልድ በመግደል የሚገኝ ጥቅም ባለመኖሩ የሚመለከተው አካል ከማስታወቂያው ከሚገኘው ገቢ ይልቅ የሀገር ተረካቢ ልጆች ያስፈልጋሉ፤ የ እግር ኳሱ የበላይ አስተዳዳሪ የሆነው የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ክፍለ አህጉራዊ የልማት ቢሮ ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ አስመርቋል።
የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የእግር ኳስ አስተዳዳሪው አካል በማህበሩ አባል አገራት በኩል የእግር ኳስ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በአዲስ አበባ የተከፈተው 10ኛው የፊፋ ክፍለ አህጉራዊ የልማት ቢሮ ፊፋ ከሦስት ዓመት በፊት እግር ኳስ በመላው ዓለም እንዲያድግ የጀመረው የእግር ኳስ ልማት ሥራ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሮው በአዲስ አበባ እንዲከፈት ላደረገው አስተዋጽኦና ትብብር ትልቅ ምስጋና የሚቸረው መሆኑን ጠቅሰው፤ የአፍሪካ አገራት ላለፉት ሁለት ዓመታት የቀረጿቸው ፕሮጀክቶች ለአህጉሪቷ የእግር ኳስ እድገትና ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው፤ ፊፋም ለፕሮጀክቶቹ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው የክፍለ አህጉራዊው ቢሮ መከፈት ፊፋ ከምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ዳንኤል ዘነበ ዳንኤል ዘነበ አገራት ጋር በቅርበት ለመሥራት ያስችለዋል ብለዋል። የቢሮው መከፈት ፊፋ ከአባል አገራቱ ጋር በቅርበት ለመገናኘት እንደሚያግዘውና ለኢትዮጵያ፣ ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራትና ለአፍሪካ አጠቃላይ እግር ኳስ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የሚለው ሊያሳስበው ይገባል። በእርግጥ የቢራ ስም ከተሸከሙ ክለቦች ፍላጎት ጀርባ የምርት ተጠቃሚና የምርታቸው አፍቃሪ ለማበርከት ማለማቸው ክፉ ሀሳብ እንዳልሆነ እሙን ነው። ብሄራዊ ቡድንንም ሆነ፣ የሊግ ውድድሮችን ስፖንሰር በማድረግ የምርት አገልግሎትን ማስተዋወቁ እንደኃጢያት የሚቆጠር አይደለም።
ትልቁ ጉዳይ ግን የቢራ ስም የተሸከሙ ቡድኖች ደጋፊዎችም ሆኑ በቢራ የሚደገፍ ቡድን ደጋፊዎች እግር ኳስና መጠጥ ጠጥቶ መደገፍን ነጥሎ ማየት እስኪያዳግታቸው ቁርኝት ሲፈጥሩ አደጋው አስከፊ ይሆናል ለማለት ነው። እግር ኳሱም ስፖርታዊ ወዙን ያጣል።
በአሁኑ ወቅት በተለየ መልኩ በሸገር ደርቢ የፉክክር መንፈስ ላይ እንዳለውና በክልል ስታዲየሞችም እንደሚንጸባረቀው አይነት ሁኔታ በእግር ኳሱ መሰረት ላይ የቢራ ካምፓኒዎች መቆማቸው የፕሪሚየር ሊጉን የስፖርታዊ ጨዋነት ህልውናን ፈተና ውስጥ እንዲገባ ከማድረግ ስለሚሻገር ይሄንን ሀይ የሚል ህግ ተግባራዊ ማድረጉ አማራጭ የለውም። ይሁን እንጂ፤ «ለምን ሲባል?» የሚል ጥያቄ ከተለያዩ አቅጣጫዎች መነሳታቸው አይቀሬ ነው። ስፖርት መዝናኛ ነው፤ ስታዲየም ደግሞ ዘና የሚያስበለው ስሜት መፍጠሪያ ስፍራ። ታዲያ ጠጥቶ መዝናናቱ ኃጢያቱ ምኑ ላይ ይሆን? በሚል ይሄንን ሀሳብ የሚሞግቱ በሌላ ፅንፍ ይከራከራሉ።
በሠለጠኑት አገሮችም የሚፈጸመው ይሄው መሆኑን በመጥቀስ ሀሳቡን መሞገታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ጠንካራ የክለብ ጨዋታ ለመመልከት ወደ ስታዲየም ሲዘልቁ ፣ በስታዲየሙ ግቢ ውስጥ ካሉ ምግብ ቤቶች በፕላስቲክ ብርጭቆ የተሞሉና የአልኮል መጠናቸው ከ4 ነጥብ 5 እስከ ስድስት በመቶ የሆኑ ቢራዎችን ተጎንጭተው፣ ካስፈለገም ተጨማሪ ቢራ ገዝተው በመግባት ጨዋታ ይኮመኩማሉ፡፡ እንዲያውም ለስታዲየሙ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገቡት በእዚያው ስታዲየም ዙሪያ የሚገኙ ልዩ ልዩ የንግድ ቤቶች መሆናቸው ይነሳል፡፡እነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ከመዝናኛ ቦታዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው:: በእንግሊዝ፣ በጀርመን… እና በመሳሰሉት አገራት ይህ አይነቱ ልምድ ያለና የኖረ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
በሀገራችንም ተመሳሳይ ልምድ ተግባራዊ ማድረጉ እንደክፋት መወሰድ እንደሌለበትም ይሞግታሉ። በዚህ የሀሳብ ማዕበል ውስጥ ያሉ ወገኖች ግን መገንዘብ የሚገባቸው፤ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የጣሊያን ሴሪ አ፣ የጀርመን ቡንደንስ ሊጋም ሆነ የሌሎች ሊጎች ደጋፊዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ጠንካራ ሥርዓት የፈጠሩ ናቸው። ጠንካራ መሰረት ያለው ደጋፊ ማህበራት ናቸው፤ ማን የትኛው ወንበር ላይ እንደተቀመጠ/ እንደሚቀመጥ ሳይቀር ይታወቃል። ቢያጠፋም ተለይቶ የሚቀጣበት መንገድ አላቸው። የሊጋቸው ደረጃ በራሱ የደጋፊዎቻቸውንም ሥነምግባር ደረጃ ይወስናል። ይህ አመክንዮ የሌሎች ተሞክሮ እንደ መሟገቻ የሚያስኬድ አይደለም ተብሎ ይነሳ ይሆናል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የተቃኘ እንዳልሆነ እውነታውን የሚታወቅ ነውና፤ ይህ ግን አያስኬድም።
ስለዚህ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ የሚገኙትን መጠጥ ቤቶች በህግ ማዕቀፍ መጎብኘቱና በሥርዓት እንዲመሩ ማድረጉ ለችግሩ መቀረፍ የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይችላል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። በእርግጥ ከሁለት ዓመት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሀሳቡን በማጠንጠንና በማፅደቅ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ያሉ ምግብ ቤቶች በስታዲየሙ አካባቢ የአልኮል መጠጥ በመሸጥ ለሚነሱ ሁከትና ረብሻዎች ሁሉ እሳት ለኳሽ እንደሆኑ በመግለጽ፣ ዘወትር ከቀኑ 11፡00 ሰዓት በኋላ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ እንዳይፈጽሙ የሚከለክል ሕግ መረቀቁንና ለማፅደቅም በሂደት ላይ እንደነበረ ይታወቃል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ለሚታየው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ይሄ አይነቱ እርምጃ መውሰዱ ዋነኛው ባይሆንም አይነተኛ መፍትሄ ነውና፤ ማዘጋጃ ቤቱ የጀመረውን እንቅስቃሴ ከዳር ማድረስ ይገባዋል። በሌላ ወገን፤ የችግሩ ነጸብራቅ በመዲናዋ ብቻም ሳይሆን በክልል ጨዋታዎች ወቅት በግልጽ ይንጸባረቃል። እዚያም ቢሆን ይሄን መንገድ በአርዓያነት ወስዶ ወደተግባር መሻገር ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ መወሰንና ርምጃ ነውሰድ ችግሩን በአንድ ወገን ለማስቀረት ያግዛል።
ቀዳዳውንም መድፈን ያስችላል። ግን በዚህ ብቻ መወሰን «ግማሽ ተላጭቶ ግማሽ አጎፍሮ» ይሆናል። ምክንያቱም ረብሻንና ሁካታን የሚፈልግ፣ ግብረ ገብ የጎደለው ሰው እኮ ከስታዲየም ዙሪያ በቅርብ ርቀት ከሚገኙ መዝናኛ ቤቶች ጥግብ ብሎ ጠጥቶ ወደስታዲየሙ በመግባት ለመረበሽ ከልካይ አይኖረውም የሚል ሙግት መነሳቱ አይቀርም። በመሆኑም ወደ ስታዲየም የሚገቡ ደጋፊዎች መጠጥ ጠጥተው እንዳይገቡ የሚያስችል፤ ያ ባይሆን እንኳን ሰክረው ወይም ሞቅ ብሏቸው እንዳይገቡ የሚያግድ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት መተግበር ተገቢ ይሆናል።
በደጋፊዎች የትኬት አቆራረጥና የፍተሻ ሥርዓት ላይም ቁጥጥርና ክትትል ማካሄዱ ተገቢ ይሆናል። በተለይ ደግሞ የፍተሻ ሥርዓቱን ማስተካከል ችግሩን በበሩ ላይ ስለሚያስቀር የትንፋሽ መመርመሪያ መሳሪያ በስታዲየሙ መግቢያ በሮች ላይ ያስፈልጋል። ምናልባት ይህ ሀሳብ የቅንጦት ነው ካልተባለ፤ ከትራፊክ ፖሊስ ልምድ ወስደን ካንቦሎጆ ሲገባ የአልኮል መጠን በትንፋሽ ተፈትሾ ቢገባ መልካም ነው።
ምክንያቱም ጠጥቶና ሰክሮ ወደውስጥ መግባት ከመኪና ለበለጠ ግጭትና አደጋ ስለሚያጋልጥ በጎ በጎውን መኮረጅ ለእዚህ ጊዜ ይጠቅማል በሚል ሀሳብ የሚያሻግሩ አሉ። በዘላቂነት ደግሞ አጥፊውን፤ ረብሻ የሚያስነሳውን ለመለየት የሚያስችል ካሜራ መግጠምና መጠቀም ሊታሰብበት የሚገባ ነው። በሌላ ወገን፤ ከተቻለ በእግር ኳሱ ውስጥ የቢራ ፋብሪካዎችን ተጽእኖ ከራስ ላይ ማራገፍ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። እስቲ ከዚህ እውነታ ጋር የአንዳንድ አገሮችን ተሞክሮ እናንሳ።
በስፖርት ውድድሮች የአልኮል መጠጦች ስፖንሰር እንዳያደርጉ የሚከለክል ሕግ ካላቸው አገራት መካከል ብራዚል ትጠቀሳለች፡፡ የኳስ ከዋክብት መፍለቂያ የሆነችው ብራዚል በስታዲየሞችና በእግር ኳስ ግጥሚያዎች ወቅት የአልኮል ማስታወቂያዎችን ማስነገርና በአካባቢ መሸጥ የተከለከለ መሆኑን እ.ኤ.አ. ከ2003 ጀምሮ የሕግ ክልከላ ተቀምጦበታል፡፡ የኛም አገር ከዚህ አይነቱ አካሄድ ቁርጠኝነት በመማር ከቢራ ካምፓኒዎች ተጽእኖ ራሱን በማላቀቅ የተሳከረውን እግር ኳስ ሊታደገው ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
ዳንኤል ዘነበ