በቀድሞው አጠራር በሸዋ ከፍለሀገር ጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ሞጨ ገበሬ ማህበር ልዩ ስሙ ቆርጨ በሚባል መንደር 1964 ዓ.ም ነው የተወለዱት። ከመምህር አባታቸውና ከቤት እመቤት እናታቸው የተወለዱት እኚሁ የእምነት አባት በጥሩ ሥነምግባር ታንፀውና መንፈሳዊውንም ሆነ ዘመናዊን ትምህርት በእኩል መንገድ አውቀው እንዲያድጉ ተደርገው ነው የተቀረፁት።
ዕድሜያቸው ለትምህርት አንደደረሰ በቤታቸው አቅራቢያ በሚገኘው ናድነ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረዋል። ይሁንና መለስተኛም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ ወላጅ አባታቸው በሚያስተምሩበት ጉመር በተባለው ትምህርት ቤት ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በእግራቸው እየተጓዙ 7ኛ እኛ 8ኛ ክፍልን ተማሩ።
በትምህርታቸው ጎበዝና ታታሪ የሆኑት እኚሁ ሰው ታዲያ ከልጅነታቸው ጀምሮ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ከፍተኛ ፍቅርና ፍላጎት አድሮባቸው በማደጋቸውና አገልጋይ የመሆን መሻታቸው በማየሉ ከወላጅ አባታቸውና በቅርብ ከሚገኙ ካህናት ጋር በመማከር አዲስ አበባ በሚገኘው ንዑስ ዘርዓ ክህነት የተባለ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ውስጥ ገቡ። እስከ 12ኛ ክፍል በዚያው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተምረው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ከፍተኛ ውጤት ቢያመጡም አገልጋይ የመሆን ህልማቸውን ለማሳካት ሲሉ በቀጥታ ጉለሌ በሚገኘው ከፍተኛ ዘርዓ ክህነት የካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ገቡ።
ለሦስት ዓመታት ፍልስፍና፤ በንባበ መለኮት ትምህርት ደግሞ አራት ዓመት ተምረው በዲግሪ መርሃ ግብር ከፍተኛ ማዕረግ በማግኘት በ25 ዓመታቸው የክህነት ማዕረግ ተቀበሉ። በቀጥታ በጉራጌ አካባቢ ሀጣጥ ሉርድ ማርያም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው ተላኩ። አራት ዓመት ካገለገሉ በኋላ በገዳሙና አካባቢ ያደረጉትን አስተዋፅኦ በማየት ወደ ሮም ተልከው የቤተክርስቲያን ቀኖና አጥንተው እስከ ዶክትሬት ማዕረግ ደርሰው ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
ከዚያ በኋላ በእንድብር ሀገረ ስብከት የጳጳሱ እንደራሴና የሀገረ ስብከቱ ፅሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ ሆነው በርካታ የልማት ሥራዎችን በማስፋፋት ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል። አስር ዓመት ካገለገሉ በኋላ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የሃዋርያዊ ሥራዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊና የጠቅላይ ፅሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የቤተክርስቲያኗ ዋና ፀሐፊ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
አፋቸውን ከፈቱበት ከጉራጊኛ ቋንቋ በተጨማሪ አማርኛ፣ እንግሊዝኛና ጣሊያንኛን አቀላጥፈው የሚናገሩትና ላቲን ብሎም ግዕዝንም ማንበብና መረዳት የሚችሉት ዶክተር አባ ተሾመ ፍቅሬ የዛሬው የፋሲካ ዋዜማ ልዩ የዘመን እንግዳችን ናቸው። ከእንግዳችን ጋር በሃይማኖታዊ ገዳዮችና በሰላም እሴቶች እንዲሁም በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ውይይት እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡– ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት ሊገቡ የቻሉበትን አጋጣሚ ምን እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- እኔ እንግዲህ አንደአጋጣሚ ሆኖ ቤተሰቦቼም ሆኑ የአደኩበት ማህበረሰብ ለሃይማኖቱ የተለየ ቦታ የሚሰጥ ከመሆኑ የተነሳ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የተለየ ክብርና ፍቅር ኖሮኝ ነው ያደኩት። ቤተሰቦቼም ለሃይማኖት ትልቅ ዋጋ የሚሰጡ በመሆኑ ከልጅነቴ ጀምሮ አገልጋይ የመሆኑ መሻት ነበረኝ። ለቤተክርስቲያናችን ቅርብም ስለነበርን ጠዋት ጠዋት ከትምህርት ቤት በፊት ለማገልገል እንሄዳለን።
እቤታችን በየዕለቱ የሚመጡ የሃይማኖት አባቶችንም እያየሁኝ ማደጌም አሁን ላለሁበት ደረጃ ትልቅ መሠረት የጣለልኝ ይመስለኛል። በዋናነት ግን አባ ፍራንሷ ማርቆስ የተባሉ አባት ለእኔም ሆነ ለዚያ አካባቢ ማህበረሰብ አርዓያ ሆነው ያለፉ ሰው ናቸው። አገልጋይ የመሆን መሻቴን ይበልጥ እንዲጎለብት ያደረጉትም እሳቸው ናቸው ብዬ አምናለሁ።
እኚህ ሰው የእምነት ሥራን ብቻ አልነበረም ይሰሩ የነበሩት፤ የታመመን ይጎበኛሉ፤ ወጣቶችን ሰብስበው ያስተምራሉ፤ ያላቸውን ሁሉ በመስጠት የተቸገረን ይረዳሉ። ለአካባቢው ሕዝብ የእውቀት ብልጭታን የፈነጠቁ ትልቅ ሰው ነበሩ። በራሳቸው አቅም ብቻ 14 የሚሆኑ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አስፋፍተዋል። ወጣትና ሴት ወጣቶችን እኩል የትምህርት ዕድል እየሰጡ አሳድገዋል። ሁሉም የሚያከብራቸው፣ ለሁሉም እንደአባት የሚያገለግሉ፤ ሰዎች ሲያለቅሱ አብረው የሚያለቅሱ፣ የሁሉ ችግር ችግራቸው አድርገው የሚያዩና ሕፃናትን የሚንከባከቡ አባት ነበሩ።
የሚገርምሽ መኖሪያቸው እኛ ከምንኖርበት አካባቢ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው እንድብር ከተማ ቢሆንም ያንን ሁሉ መንገድ በእግር እየተጓዙ ነበር ሕዝቡን ያገለግሉ የነበሩት። ታዲያ እሳቸው መጡ ከተባለ የሰፈር ሕፃናት ተሰብስቦ ነው የሚቀበላቸው። እሳቸውም ከረሜላና የተለዬ ነገሮችን በመስጠት ለእኛ ያላቸውን ፍቅር በተግባር ያሳዩን ነበር። እኚህ ታላቅ አባት ክርስቲያኑም ሆነ እስላሙን በፍቅር የሚወዱ አባት ስለነበሩ ለብዙዎቻችን አርዓያ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ሁሉም ወጣት እሳቸውን መሆን ይመኝ ነበር።
እንደነገርኩሽ እኔ ደግሞ ከልጅነቴ ጀምሮ የመንፈሳዊ አገልግሎት ጥሪ ስለነበረኝ እንደእሳቸው ለመሆን ዕለት ዕለት እተጋ ነበር። ለነገሩ እኚህን ሰው አይተሽ አለማድነቅ አይቻልሽም። እኔ ደግሞ በልዩ መንፈስ ከእሳቸው ጋር ቅርበት ስለነበረኝ ሁልጊዜ እንደእርሶ መሆን እፈልጋለሁ እላቸው ነበር። ይሄ ነገር በውስጤ በጣም እያደገ ስለመጣ ለአባቴም ቄስ መሆን እንደምፈልግ ነግሬዋለሁ።
9ኛ ክፍል ስደርስ በአካባቢያችን ያሉ ካህን አማክረን አዲስ አበባ ንዑስ ዘርዓ ክህነት የተባለ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ውስጥ ገባሁ። ይህ ትምህርት ቤት የክህነት አገልግሎት የሚፈልጉ ወጣቶችን አይቶ ከቀለም ትምህርታቸው ባሻገር የሞራል ሥነምግባር፣ የክህነት አገልግሎት ጥሪ እንድናውቅ አድርጎናል።
በነገራችን ላይ 12ኛ ክፍልም እንደዚሁ በጣም ጥሩ ውጤት ባመጣም ስሜቴም፣ ጥረቴም፣ ፍላጎቴም ማገልገል ስለነበር በቀጥታ ጉለሌ በሚገኘው ከፍተኛ ዘርዓ ክህነት የካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ገባሁና ለሰባት ዓመት ትምህርቴን ተከታትዬ ተመርቄ ወጣሁ። በእዚህ የሥልጠና ጊዜ ውስጥ ምንም እንኳን ልጆች ብንሆንም ልናውቀው የሚገባን ሁሉ በተግባር እንድናውቅ ተደርገናል። በጣም ከማስታውሰውና በሕይወቴ መሠረት ጥለውልኛል ከምላቸው ነገሮች አንዱ የቋንቋ ሥልጠና ነው።
ስናጠፋ የሚቀጡን ዱላ አይደለም፤ አንድ የመፅሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ ወስደን በእንግሊዝኛ እንድናጠና ነው የሚያደርጉን። ይህ ዛሬም ድረስ ለሕይወቴ መሠረት ጥሎልኛል። የንስሃና የተሰበረ ልብ እንዲኖረኝ አድርጎኛል። ሳጠፋ ሰውን ፈርቼ ሳይሆን እግዚአብሔርን ፈርቼ ንስሃ ብገባ እሱ መሃሪ እንደሆነ እንድረዳ አድርጎኛል። ሁለተኛው የአንድ አገልጋይ ዋና ሥራው ደሃን መርዳት የተጎዳ ልብን መጠገን መሆኑን በተግባር እየፈፀምኩኝ እንድገነዘብ ረድቶኛል። በአጠቃላይ ሥልጠናው ዛሬም በሕይወቴ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
አዲስ ዘመን፡– ነገ የትንሳኤ በዓል ነው። በልጅነትዎ የትንሳኤ በዓልን በምን መልኩ ነው ነበር የሚያከብሩት? የሚስታውሱት የተለየ ገጠመኝ ካለም ያጫውቱን?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- አስቀድሜ እንደነገርኩሽ የእኔ የሕይወት ቁርኝት ከቤተሰብና ከቤተክርስቲያን ጋር ነው። የእኔም ሆነ የአካባቢው ሕፃናት ውሎ ከቤተክርስቲያን ጋር ነው። ፋሲካ ሲመጣ ከምንም በላይ የሚታወሰን የፀሎተ ሐሙስ ትዝታ ነው። ትልልቅ አባቶችና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ቁጭ ብለው እኛ እግራቸውን በማጠብ ቡራኬ የምናገኝበት ትልቁ ቀን ነው። 12 ውስጥ ለመግባት ዓመቱን ሙሉ ነው የምንፀልየው። ምክንያቱም ዓመቱን ሙሉ በቋሚነት ያገለገለ፤ ያልቀረ፤ በሥነምግባሩ ጥሩ የሆነ ተብሎ ነው የሚመረጥ የነበረው። ሌላው ደግሞ እንደማንኛውም የካቶሊክ ቤተእምነት ተከታይ ፋሲካ ሲመጣ ሁሌም ትልቅ ስፍራ የምሰጠው ንስሃ መግባት ነው። የካቶሊካውያን መገለጫ በዓመት አንዴ ንስሃ መግባትና መቁረብ ነው።
ይህንን ስል ንስሃ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚከናወነው እያልኩ አይደለም፤ ሃጢያት ሁልጊዜም ስለምንሰራ ንስሃ ያስፈልገናል። ግን በፋሲካ ጊዜ ደግሞ በተለየ መንገድ ነበር የሚከናወነው። ሌላው የስግደት ፕሮግራም በጣም የሚወደድና የምናፍቀው ነው። በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የመስቀል መንገድ የሚባል ጠዋት ጠዋት የሚደረግ ፀሎትና ልዩ መዝሙሮች አሉ። እነዚያ ፕሮግራሞች ዛሬም ድረስ በህሊናዬ ቀርተዋል።
ልጆች ሆነን ሌሊት የሚደረገው ቅዳሴ ጋቢ ለብሰን ከቤተሰቦቻችን ጋር ረጅም ርቀት እየሄድን ስናገለግል የነበረው ሁኔታ በልጅነት አዕምሮዬ ተቀርፆ ኖሯል። ከዚህም ባሻገር እንደማንኛውም ማህበረሰብ በፋሲካ ሌሊት የሌሊቱ ቅዳሴ ካለቀ በኋላ ቤታችን ሄደን የፋሲካን የሌሊት እራት የምንቋደስበት እና ማታ ቤተክርስቲያን ከመሄዳችን በፊት እናታችን ዶሮ ስትሰራ ቁጭ ብለን ከሴቶቹ እኩል እናይ የነበረውን ሁኔታ ሳስብ ዛሬም ድረስ በዓሉን የተለየ አድርጌ እንዳስብ ያደርገኛል።
የትንሳኤ በዓል ትልቁ ቁምነገር ከጨለማ በኋላ ብርሃን መኖሩን፣ ከሞትና ከውድቀት በኋላ መነሳት መኖሩን የሚያመላክት ተምሳሌታዊ የሆነ በዓል በመሆኑ ለየት ያደርገዋል። በክርስትና እምነት ትንሳኤ ትልቅ ትርጉም አለው። የሰው ልጅ በሕይወቱ ተስፋን ባይሰንቅ፤ ሩቅ አሻግሮ ባይመለከት፣ ነገን ባያስብ ኖሮ ሁሉም ነገር ጨለማ ይሆንበት ነበር።
ተስፋ መቁረጥ በሕይወት ውስጥ ትልቅ ፈተና ነው። የ40 ቀን ፆሙም ዋና ዓላማ ከምግብ መከልከል ሳይሆን ስጋን መቅጣትና በንስሃ መመለስ ነው። ምክንያቱም ፈጣሪ ከእኛ የሚፈልገው ተግባራዊ ፆም ነው። በትክክልም የክርስቶስን ፆም ፆመን የክርስቶስን ህማማትን፣ ስቃይን እያስታወስን መኖር ነው የሚገባን። መንፈሳዊ ሕይወት በዚያ ልክ በመስዋእትነት የተሞላ መሆን አለበት። እግዚአብሔር ያስተማረን የመስዋእትነት፣ የውድቀት ሕይወት ነው፣ የትህትና ሕይወት ነው።
በነገራችን ላይ በክርስትና እምነት ክብር በጉልበት አይገኝም። ክርስቶስ ክብሩን ጥሎ፣ ወርዶ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ፣ ተገርፎ፣ ተሰቃይቶ፣ ተገድሎ ከሞት የተነሳ አምላክ ነው። ስለዚህ እኛ የሕይወታችን አቅጣጫ መሆን የሚገባው ዝቅ በማለትና ራሳችንን በማዋረድ የክርስቶስን ትንሳኤ መነሳት ነው። ክርስቶስ ‹‹የእኔ ወታደሮች ከዚህ አይደሉም፤ ከሰማይ ናቸው ብሎ›› እንደተናገረው ሰማያዊውን ክብር ለማግኘት በሕይወት የተገለጠ የቅድስና ሕይወት መኖር ነው የሚገባን።
ደግሞም እሱ ሰው ሆኖ በበረት መወለዱ፣ በአህያ መሄዱ፣ በመስቀል መሞቱ ለእኛ ሲል መሆኑን ማስታወስ ይገባናል። ክርስቶስ ከሞት የተነሳው ትንሳኤን ብቻ ሊያሳየን አይደለም። ነገር ግን ትንሳኤ የሚገኘው በመዋረድና በመውረድ ጉዞ ውስጥ እንደሆነ ሊያስተምረን እንጂ። ሰው ግን ዝቅ ማለት ይቸግረዋል፤ መዋረድን መቀበል አይፈልግም። የፈጣሪ ባህሪ ግን ዝቅ ማለትንና ትህትና መላበስ ነው። በነገራችን ላይ መዋረድ ማለት መሬት መውደቅ ማለት ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስቀደም ማለት ነው።
አሁን ላይ በአገራችን ያለው ሁኔታ ጨለማ የበዛበት ጊዜ እንደመሆኑ የክርስቶስን ህማማትና ስቃይ በተለይም ጌታ ሞቶ አለመቅረቱንና በትንሳኤው ሞትን ድል ማድረጉን አሸናፊነቱን በማሰብ በመዋረድ ውስጥ ለአገራችን ትንሳኤ እንዲሆን በብርቱ መፀለይ ይገባናል። እሱ ሆኖ እንዳሳየን በትህትና እና በፍቅር እንመላለስ። እግዚአብሔር ምን ያክል እንደወደደንና ለእኛ ሲል አንድ ልጁን አሳልፎ በመስቀል ላይ እንዲሞት የፈቀደው እሱ በደል ስላለበት አይደለም፤ የእኛን ሃጢያት ይሸከም ዘንድ እንጂ።
በእኛ ስጋ ውስጥ ገብቶ፤ የእኛን ደካማነት ተሸክሞ፤ ቁስላችንን ዳሶና ፈውሶ፤ ዳግም ጨለማ በእኛ ላይ እንዳያንሰራራ፣ ክፋት በእኛ ላይ ቤቱን እንዳይሰራ እግዚአብሔር ለእኛ ሲል ልጁን ሰጠን። ይህም እግዚአብሔር ምን ያህል እንደወደደኝ አይቼ እኔስ ለወንድሜ ምንድን ነው የማደርገው? ብለን ራሳችንን አንድንጠይቅ ያስገድደናል።
እኛ ለሰዎች ፍቅር መስጠት መሠረታዊ ግዴታችን ነው። ምንአልባት ይህንን ማድረግ መስዋትነት ይጠይቃል። ክርስቶስ ለፍቅር ብሎ ነው የተሰዋው። እኛ በፍቅር መንገድ ብንጓዝ፤ መስዋትነት ቢያስከፍለንም እንኳን፤ ክብር ቢያሳጣን ለእውነት ከቆምን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን አይቀርም። በመሆኑም በትንሳኤ ጊዜ በእርግጥም የፆምነው ፆም ትርጉም የሚኖረው በትክክልም የክርስቶስ ፍቅር ከተረዳንና በዚያ ፍቅር ለመኖር ቁርጥ ፍቃድ አድርገን በዚያ ሕይወት መመላለስ ስንችል ነው። የትንሳኤን ፀጋ ተቀብለናል፤ ተሻግረናል የምንለው በሕይወታችን የተገለጠ ለውጥ ሲኖር ነው።
ጨለማ ውስጥ እየኖርን መሻገር አንችልም። ስለዚህ ለመሻገር ፣ ለመነሳትና ለመሄድ የምንሻ ከሆነ በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር ይጠበቅብናል። እርግጥ ነው ፋሲካ በየዓመቱ የምናከብረው በመሆኑ አንድ አንድ ክርስቲያኖችን ባህላዊ ሁኔታ ውስጥ ሊያስገባን ይችላል። ግን ጥልቅ ምስጢሩ ለእያንዳንዳችን የመለወጫ ዘመን ፣ የብርሃን ዘመን ነው ካልን፤ ‹‹ክርስቶስ ትንሳኤ ሙታን›› ብለን የምንዘምረው መዝሙር በትክክልም የእኛን መነሳትን የሚያረጋግጥልን፤ ከወደቀው፣ ከተበላሸው ማንነታችን፤ ከጨመለቀው እኛነታችን፣ ያንን ሁሉ ቡትቷችንን አራግፈን በክርስቶስ ብርሃን የምንመላለስ ሰዎች ለመሆን መጣር አለብን።
አዲስ ዘመን፡– እርሶም ሆነ አብዛኞቻችን ካደግንበትና ከተቀረፅንበት እሴት አንፃር አሁን ላይ ያለው ወጣት ላይ የሚስተዋለው የአስተሳሰብ ዝቅጠት ከምን የመነጨ ነው ይላሉ? አሳሳቢነቱስ ምንያህል ነው?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡– እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ እንደማህበረሰብ ሁሉም ለልጁ መልካም እሴትን ለማውረስ የሚተጋ ነው። እኔ እንደጉራጌ ማህበረሰብ አባቴ ብዬ የምጠራው የወለደኝን አባቴን ብቻ አይደለም። በአካባቢዬ ያሳደጉኝን ሁሉ እንደአባት አከብራቸዋለሁ፣ እታዘዛቸዋለሁ። እነሱም የሚመለከቱኝ አባቴ አለ፤ የለም ብለው ሳይሆን ኃላፊነት እንዳለበት እንደገዛ ልጃቸው ነው። መንገድ ስስት ይመልሱኛል፣ ወደ ቀናው መስመር እንድመለስ ይገስፁኛል። ልጅ ሆነን የሰው ማሳ ገብተን እሸት ስንቆርጥ የሚቆጡንና የሚገስፁን ልክ እንደወለዱት ልጅ ነው። እኛም ሁሉንም ታላላቆቻችንን እየፈራን፣ እያከበርን እየታዘዝን ነው የኖርነው።
በዚያ ማህበረሰብ እርቅ ትልቅ ቦታ አለው። እኔ በሕይወት ታሪኬ ሰው ሰውን ገደለ ሲባል የሰማሁት ሁለትና ሦስት በላይ አይሆንም። የግድያና የሌብነት ወንጀልን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ነው። ‹‹ሰው ክቡር ነው›› ብሎ የሚያስብ ማህበረሰብ ውስጥ ነው ያደኩት። በዚያ ሂደት ውስጥ ትልቁ የተማርኩት ነገር ታላላቆችን ማክበርና ሁሉንም ሰው በእኩል መንገድ መውደድ ነው።
እኔን ያሳደገችኝ የወለደችኝ እናቴ ብቻ አይደለችም፤ ጎረቤቶቻችንም ጭምር እንጂ። በዚህ ምክንያት ሁላችንም የእዛ እሴት ተገዢዎች ሆነን ነው ያደግነው። ስህተት ስንሰራ አባቴ አየኝ ሳይሆን ጎረቤት አየኝ ብለን ነው የምንጨነቀው። ምክንያቱም የአባቴን ስም በመጥፎ ማስጠራት ስለማልፈልግ ነው። ለዚህም ነው ለማህበራዊ ግንኙነታችን ትልቅ ስፍራ የምንሰጠውና የምንጠነቀቀው።
ሌላ ምሳሌ ልንገርሽ፤ እኔ ባደኩበት ማህበረሰብ የትኛው ወጣት ማንም ሰው ሲልከው ‹‹አባቴ አይደለህም፤ አልታዘዝህም›› አይልም። የእኔ አባቴ ደመወዝ ተቀብሎ ሲመጣ ቤታችን ለመጡት ሁሉ ገንዘቡን በመስጠት ነበር የሚጨርሰው። እናቴም ከከተማ ያሉ ዘመዶቻችን የሚልኩላትን እንደ ጨው ዘይትና የመሳሰሉትን የምግብ ቁሳቁሶች ለሁሉም ታካፍላለች። በእኛ ማህበረሰብ ለብቻዬ ልብላና ልደር፤ ለብቻዬ ልበልፅግ የሚባል ነገር የለም። እኔም ያለንን ተካፍለን መኖር የተማርኩት ካሳደገኝ ማህበረሰብ ነው።
እኔ እንደሚገባኝ ይሄ መተባበር አብሮነቱ ነው ዛሬ ድረስ በፍቅር ያቆየን። በእርግጥ አሁን አሁን ከተሜነቱ እያደገና እየተስፋፋ ሲመጣ፣ ባህሉ እየተቀየረ ሲሄድ፤ ከዓለም ጋር ያለን ግንኙነት ሲጠናከር የወጣቶቻችን አመለካከት እየተቀየረ መጥቷል። ጥቂት የማይባለው ትውልድ ባህሉን እየተወ፣ ዘመናዊነት እየያዘ ሲሄድ የቆየው እሴታችን እየተሸረሸረ መምጣቱን ማስተዋል ይቻላል።
ለአንድ ማህበረሰብ ባህል ትልቅ ሀብት ነው። አንድን ሰው ሰው የሚያደርገው በባህል ያገኘው ማንነቱ ነው። በእምነት የምናገኘው እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ ማህበራዊ ሕይወት ትልቅ ስፍራ አለው። ይህንን ማህበራዊ እሴት ዛሬ ምን ላይ ነው ያለው? ብለን ብንጠይቅ አብሮነቱ፤ መተጋገዙ ፣ መፈራራቱ መከባበሩ እየቀነሰ እንደመጣ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ መሆኑ እንደእምነት አባት ያስጨንቀናል።
ወጣቶቻችን ይህንን እሴት ማስተማር ከታሪካችሁ መራቅ የለባችሁም ብለን መመለስ ይጠበቅብናል። በቤተክርስቲያናችን ትልቁ ሥራ ወጣትን መስመር አስይዞ ማሳደግ ነው። ነገር ግን የዛሬ ወጣት ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ትውልድ ነው። መሪው ቴክኖሎጂ ነው የሆነው። ሽማግሌ ወይም የእምነት አባት ከሚመራው ቴክኖሎጂን ያስበልጣል። ይህንን ስል ግን ሁሉም እያልኩ አይደለም። ነገር ግን አብዛኛው ወጣት በዚያ ሰንሰለት ውስጥ የገባ ነው።
የማንክደው ነገር ቴክኖሎጂ ጥሩ ነገር ነው። ግን ደግሞ ልጆቻችን በጎ ስብዕና ተላብሰው መልካም ማንነት ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግ የቱ የበለጠ ይጠቅማቸዋል ብለን መመርመር ይገባናል። እንደእኔ እምነት ቴክኖሎጂ የልጆቻችንን ስብእና እንዲቀርፅልን መፍቀድ የለብንም።
በተለይም ወላጆች የልጆቻቸውን ማህበራዊ እሴት ለመገንባት በስልክና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ መመርኮዝ አይገባቸውም። ወላጆች አትኩረው ሰጥተው ልጆቹ የሚገባቸውን ሰብአዊ ክብር ማግኘት የሚያስችላቸውን እሴቶች ከቴክኖሎጂ በራቀ መንገድ ሊያሳዩዋቸው ይገባል። ትልቁ ኃላፊነት ቤተሰብ ላይ ቢሆንም የእምነትም ሆነ የትምህርት ተቋማትም ኃላፊነት አለባቸው። መንግሥትም በተመሳሳይ መንገድ ኃላፊነት አለበት።
በመሆኑም ወጣቶች በሥነምግባር ታንፀው እንዲወጡ ሁላችንም የየበኩላችንን መወጣት አለብን። እኛ ትምህርት ቤት የምንገነባው ‹‹አንድና አንድ ሲደመር ሁለት ነው›› የሚለውን ሳይንስ ለማስተማር አይደለም። ይልቁንም እግዚአብሔርን የሚፈራ ትውልድ ለመቅረፅ ነው። ይሄ ደግሞ ለሙስሊሙም፣ ለወንጌላውያንም፤ ለኦርቶዶክሱም፤ ለካቶሊክም ለሁሉም ሰው ሆኖ ለተፈጠረ ሰው እንደሰው ሊያገኘው የሚገባ መሠረታዊ እሴት የምንገነባበት ነው። ስለዚህ ሰውን ማክበር፣ ፈጣሪን መፍራትና ማክበር፣ የተቸገረን መርዳት የመሳሰሉት መሠረታዊ እሴቶች በአንድ ሰው ህሊና ውስጥ ገብተው የዚህን ሰው ተክለሰብ እና መገንባት የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
በዚህ መርህ መሰረት ቤተክርስቲያችን ከእምነት ተቋሞቻችን ባሻገር በማህበረዊ አገልግሎት በምንሰጣቸው በርካታ ፕሮጀክቶቻችን ላይ እንሰራለን። እግዚአብሔር ይመስገን በእኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ መቶ በመቶ ሁሉም ጥሩ ናቸው ባይባልም እንኳን አብዛኞቹ ዛሬ ተመልሰው እኛኑ ሲያመሰግኑን ስመለከት ያስደስተኛል። አብዛኞቹ መልካም የሚባልና ከፍተኛ ደረጃ ደርሰውልናል። በርካቶቹ ‹‹እናንተ ያሳደጋችሁት እሴት ሰው አድርጎ ቀርፆናል፤ ማንነታችንን እንድናውቅ አድርጎናል›› ብለው ምስክርነት በአደባባይ የሚሰጡን ሰዎች አሉ።
እንደአገር ግን ወጣቱን በትክክለኛ መስመር እንዲጓዝ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ሥራ ይጠብቀናል። ግን ሁሉም በእኩል ደረጃ፣ በእሴትና በሞራል ወጣቶቻችንን መገንባት ተገቢነት አለው ብሎ አምኖ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ሊሰሩ ይገባል። እንዳልኩሽ ግን አሁንም ቢሆን እግዚአብሔርን የሚፈራ እና ሰውን የሚያከብር ትውልድ ከመፍጠር አኳያ ብዙ ይቀረናል።
ፈጣሪ የሰጠንን ሕግ ወደተግባር የመለወጡ ሂደት ገና በደንብ አልሰራንበትም። ብዙ ንፋሶች አሉ፣ ብዙ መቋቋም የማንችላቸው እንደወጣት አይደለም ጎልማሶች እንኳን የምንፈተንባቸው ትልልቅ ንፋሶች አሉ። በውጭም ሆነ በውስጥ ልንቆጣጠራቸው የሚገዳደሩን ፈተናዎች አሉ። ይህንን ፈተና ማሸነፍ የምንችለው ደግሞ በእምነት ፀንተን ስንቆይ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ቀደም የነበረው ታላላቆችና የሃይማኖት አባቶችን የማክበር ባህል ሊጠፋ የቻለው የሃይማኖት አባቱም ሆነ ትልልቅ ሰው የሚባለው አርዓያ መሆን ባለመቻሉ ነው የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- እንግዲህ ሁሉንም በአንድ ላይ መጠቅለል አልችልም። ምክንያቱም ሁሉም እንደዚያ ነው ማለት አይቻልም። ብዙ ንፋስ አለ፤ ብዙ ጫና አለ። የእምነት አባቶችን የሚገዳደር ፈተና አለ። በዚህ ረገድ ፖለቲካው ራሱ አንድ ጫና ነው። ኢኮኖሚውም ሌላ ጫና ነው። ሥልጣኔውና ዘመናዊነቱም የራሱ የሆነ ጫና አለው።
እነዚህን ጫናዎች በትክክል ተጋፍጦ፤ በንፋሱ ፊት ለፊት ቆሞ ‹‹እኔ የእምነት አባት ነኝ ፤ አላማዬም ሃይማኖትን ማስተማር ነው፤ ፖለቲካው የእኔ ሥራ አይደለም፣ የኢኮኖሚው ጉዳይ የእኔ ሥራ አይደለም›› ማለት መቻልን ይጠይቃል። እኔ በእምነት በመታነፅ፣ መልካም እረኛ በመሆን ትክክለኛውን እሴትን ማስተማር አለብኝ የሚለው ነገር የእያንዳንዱ የእምነት አባት ውሳኔን የሚጠይቅ ነገር ነው።
እርግጥ ነው እንደሰው ሁላችንም ወድቀናል፣ ተፈትነናል። ከዚህ አንፃር አንቺ ያነሳሽው ጉዳይ ውሸትነት አለው ማለት አልችልም። ግን አጠቃልዩ የእምነት አባቶች ሁሉ በዚህ ፈተና ውስጥ የገቡ ናቸው ብዬ መናገር አልችልም። እኔ በየትኛውም መንገድ ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ አላውቅም፣ ልገባም አልፈልግም፤ ቤተክርስቲያኔም አትፈቅድልኝም፤ በፖለቲካ ጉዳይ ላይ የቤተክርስቲያንን አስተሳሰብ ላሰርፅ አልችልም። ግን ደግሞ በአገሪቱ የሚከናወነውን ነገር ሁሉ እንዳላየ ማለፍ አንችልም። ምክንያቱም ፖለቲካ ማህበራዊውንም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወትን የሚነካ ነው። የሰዎችን የእርስ በእርስ መስተጋብር የሚነካ ነው።
እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠውን ክብርና መብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠበቅ ብንችል ለፖለቲካው ቤተክርስቲያን ግብዓት ትሰጣለች። ለዚህም ቤተክርስቲያን አጠንክራ ትሰራለች። እንዳልኩሽ ግን ከፖለቲካ ራሷን ማራቅ ይገባታል። ሩቅ ሆና ግን ሁንም ነገር እየታዘበች ወይም እየተመለከተች ክፉውን ‹‹ክፉ›› የምትል፤ መልካሙንም ‹‹መልካም›› የምትል ቤተክርስቲያን መሆን ይጠበቅባታል። ስለዚህ ራሳችንን በቦታችን ካስቀመጥን፣ በትክክል ማስተማር የሚገባንን፣ መሆን የሚገባንን ከሆንን ይህንን የሚባለውን ወጀብ በጥንቃቄ ልናልፈው እንችላለን።
አብዛኛው ምዕመን አሁንም እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ አገልጋዮችንም የሚያከብርና የሚታዘዝ ነው። ስለዚህ ይህ እሴት እኛው እንዳበላሸነው በአደባባይ ቢነገርም ሁሉም የእምነት አባት ግን በዚያ መንፈስ እየተመላለሰ ነው ብለን መደምደም አንችልም። የሚፀልይ ፣ የደከመውን የሚያበረታታ፤ ያዘነውን የሚያፅናና፤ የተሰበረውን የሚጠግን በርካታ የእምነት አባት አለ። እኛ የማናያቸውና አደባባይ ላይ የማይጮሁ ጥቂት የማይባሉ የእምነት አባቶች ዛሬም አሉ። በእነሱ ፀሎት ነው ይህቺ ቤተክርስቲያንም ሆነ አገሪቱ ያለችው። በየገዳሙ ጥሬ በልተው እየዋሉ፤ እያደሩ የሚፀልዩ አሉ።
ይሁንና በአደባባይ የሚታዩ የጥቂቶቹን ብቻ በመያዝ ነው ሌላው ተደምሮ የሚኮንነው። ‹‹አንድ ሚሊዮን ባለበት የሚጮኸው የወደቀው ዛፍ ነው›› እንደሚባው ከብዙ መልካም ነገር ውስጥ በጣም ጥቂት የሆነው አገልጋይ ውድቀት ይታያል። ስለዚህ ሁሉን የእምነት አባት በዚያ ጥላ ውስጥ ባንጨፈልቃቸው ጥሩ ነው።
በቅንነት የሚያገለግሉ፣ ለማህበረሰብ ቅድሚያ የሚሰጡ ለሕይወት ዋጋ የሚከፍሉ አባቶች እንዳሉ በእርግጠኝነት መናገር እችላሁ። ይህም ሆኖ ግን ችግር የለም ማለት አይደለም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ኅብረተሰቡን ከወዲህ ወዲህ የሚያንከራትተውና የሚተራምሰው ንፋስ ሁላችንም ጋር የሚነፍስ በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡– አሁን አሁን በእምነት ተቋማትም በፖለቲካና በብሔር የመከፋፈሉ፣ የመቃቃሩ ነገር ጎልቶ መታየቱ የምን ምንጭ ነው ይላሉ?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- ይሄ ጉዳይ በእምነት ተቋማት መታየቱ በእርግጥ የሚያሳዝን ነገር ነው። መሠረታዊ መርሆአችን የእግዚአብሔር ሕግጋት መሆን ነበር የሚገባው። ምክንያቱም ሁላችንንም የፈጠረን እሱ ነው። ሰውን፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ እንስሳትንም ሆነ እፅዋትን የፈጠረው እሱ ነው። በተለይም ደግሞ ሁሉንም ሰው በአምሳሉ የፈጠረው በመሆኑ በመካከላችን መከፋፈል ሊኖር አይገባም ነበር።
የፈጠረው አንተ የዚህ እና የዚያ ወገን ነህ ብሎ አይደለም። እኩል ክብር፣ እኩል ግዴታ ሰጥቶ በፍትህ እንድንመላለስ ነው ያስተማረን። ሁላችንም ግንኙነታችን የጠነከረ እንዲሆን፤ ከእያንዳንዱ የሰው ልጅ ጋር ህብረት እንዲኖረው አድርጎ ነው የፈጠረን። ለዚህም ነው ቅዱስ ቃሉ ‹‹እግዚአብሔር አባትን በፍፁም ነፍስህ፣ በፍፁም ሕይወትህ፣ በፍፁም ሃሳብህ ውደድ፤ ሰውን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› ብሎ የሚያዘን። ሰው ሲል ደግሞ ከእናቴ የተወለደ ወንድሜ ማለት አይደለም። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሁሉንም ፍጥረት ማለት ነው።
ስለዚህ መሠረታዊ መርሆአችን ሊሆን የሚገባው በቅዱስ ቃሉ የተቀመጠው ትዕዛዝና ሕግ ነው። ግን አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ ከባድ ንፋሶች የሰውን አዕምሮ የሚሰርቁ በመሆናቸው በቤተ እምነትም የገቡበት ሁኔታ ይታያል። ከእነዚህ ንፋሶች መካከል የፖለቲካው ንፋስ አንዱ ነው። ፅንፈኝነት እና ወገንተኝነትም ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው። ነገር ግን የሃይማኖት ተቋማት በምንም መንገድ ፅንፈኝነትና ወገንተኝነት ሊሰብኩ አይችሉም። መነሻም ሆነ መድረሻቸው ፈጣሪ ነው።
ደግሞም ሁሉም ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ነው ካልን ወንድማማቾችና እህትማማቾች ነን ማለት እንደሆነ መዘንጋት አይገባንም። በመሆኑም ወንድማችንን ልንከባከበው፣ ልጠብቀው እንጂ ላሳድደው፣ አንተ የእኔ ወገን አይደለህም ብዬ ላስጨንቀው ሥልጣን አልተሰጠኝም። የእግዚአብሔር ቃል እኮ የገዛ ወንድማችንን እንድንገድል ቀርቶ ክፉ እንድንናገር አይፈቅድልንም። ወገንተኛ የምንሆን ከሆነ ይህንን የፈጣሪ ሕግ ጣስን ማለት ነው። ይህንን ትዕዛዝ ጥሰን ሃይማኖተኛ ልንሆን አንችልም። ሃይማኖተኛ እግዚአብሔርን ይወዳል፤ ይፈራል። እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጡር ይወዳል፤ ይጠብቀዋል፤ ይንከባከበዋልም።
እኔ የመጣሁበት ማህበረሰብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንስሳትን እንኳን መግደል ሃጢያት ብሎ ነው ያሳደገኝ። ድንገት ዶሮ እንኳን መትቼ ቢጎዳብኝ ሳለቅስ ነበር የምውለው። ስለዚህ እግዚአብሔር ያከበረውን የሰው ልጅ ለምን እገድላለሁ? ለምንስ አሳድደዋለሁ?። ሰውን የሚያዋርድና የሚገድል ሃይማኖተኛ አይደለም። እኛ የጥል ግድግዳ አፍርሶ አንድ አድርጎ ያቆመንን አምላክ የምናመልክ ከሆነ እንዴት ከገዛ ወንድማችን ጋር እንጋደላለን? እንባላለን?። ጌታ ኢየሱስ እንደሚነግረን አይሁዳዊ፣ ግሪካዊ፣ ወንድ፣ ሴት ባሪያና ነፃ የሚባል ነገር በመካከላችን ሊኖር አይገባም።
ምክንያቱም በክርስቶስ ሁላችንም አንድ ሆነናል። የእምነት ተቋማት ከዚህ ውጪ ሌላ ነገር የላቸውም። ፖለቲካ ቢከፋፍለን ፣ ብሔርተኛ ቢከፋፍለን እንኳን የእምነት ተቋማት ሊሰበስቡ ነው እንጂ የሚገባው ሊበትኑ አይደለም። ክርስቶስ የመጣው እኮ የተበተኑትን የእስራኤል በጎች ሊሰበስብ ነው። አንድ የእምነት ተቋም ደግሞ የተበተኑትን፣ የሚጋጩትን ሰብስቦ ፣ አስታርቆ፣ አንድ አድርጎ አንድነትን ሊሰብክ ነው የሚገባው። እኛ በንፋሱ ከተገፋንማ ሥራችን ምን ሊሆን ነው?።
አዲስ ዘመን፡– ይህ ከሆነ ታዲያ በሁሉም ሥፍራ ስር ሰዶ ያለው የልዩነትና የመከፋፈል በሽታ ፈውሱ ከወዴት ይገኛል ብለው ያምናሉ?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- አንድ የእምነት አባት በጎጠኝነት፣ በብሔርተኝነት፣ በፅንፈኝነት በፖለቲካ ውስጥ ገብቶ የሚሰራ ከሆነ ሥራውን ትቶ ቢሄድ ነው የሚሻለው፤ ቦታው አይደለምና። እንደ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጣም በጥልቅ የምናምነው የእምነት ተቋም የእምነት ቤት ብቻ መሆኑን ነው። ይህንን መርህ ይዞ የሚመራ አገልጋይ ነው የሚያስፈልገውም። ህብረት የሚፈጥር፣ የሚያስታርቅ አባት እንጂ የሚለያይ አባት ሊኖር አይገባም። እኔ በብሔሬ ጉራጌ ነኝ፤ ግን ያሳደገኝ ማህበረሰብም ሆነ ቤተክርስቲያን ያስተማረችኝ ሰው ሁሉ እኩል መሆኑን ነው። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሁሉ ወገንህ ነው ተብዬ ነው የተቀረፅኩት።
አይደለም በተመሳሳይ የእምነት ተቋም ውስጥ በሙስሊም መስኪድ ፊት ለፊት ብናልፍ ወንድሞቻችን ሙስሊሞች የሚያመልኩበት የተከበረ ቦታ ተብዬ ነው ያደኩት። የኦርቶዶክስም ሆነ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነው ተብሎ ነው የተነገረኝ። ሰዎች በፍቅር ተሰባስበው እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ቅዱስ ስፍራ እንደሆነ ነው ያሳወቁኝ።
በሁሉም እምነት ‹‹ወንድምህን ወይም ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› የሚል ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ይህም ማለት ወንድሜ የእኔን ቋንቋ የሚናገር የእኔ ሃይማኖት ያለው መሆን አለበት ማለት አይደለም። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሁሉ ወንድሜም፣ እህቴም ነው።
ካቶሊካዊነት በዚህ ነው የሚገለፀው፤ ለምዕመኖቻችንም ይህንን ነው የምናስተምረው፤ በዚህ መንፈስ ነው የምናሰለጥነው። ሌላ ቦታ ስሄድ መሸማቀቅ የለብኝም። አንቺ ካቶሊክ ስላልሆንሽ እዚህ ስትመጪ መሸማቀቅ የለብሽም። እግዚአብሔር ያከበረሽ፤ የእግዚአብሔር ክቡር ፍጡር ነሽ። የእምነት አባቶች ይህንን መርሆ ከጣልን ቦታችንን ልንለቅ ነው የሚገባው ብዬ አምናላሁ።
በሁለት ቢላ ከምንበላ፣ በሁለት እግር ከምንቆምና ታሪካችንን ከምናበላሽ፣ ለሌላውም መሰናከል ከምንሆን ለምን አንደኛችንን እዚያው ብሔርተኛ ሆነን ብሔራችንን አናደራጅም?። ወይም ፖለቲካ ውስጥ ገብተን የፈለግነው አስተሳሰብ አናራምድም?። የእምነት አባት የእምነት አባት ነው። ፖለቲከኛ ወይም ብሔርተኛ አይደለም። ካርዲናል ጳውሎስ አድዋ የሚባሉት የእኛ ቤተክርስቲያን የቀድሞው ጳጳስ ይህንኑ ነው በግልፅ የሚናገሩት።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ምሳሌ ልጥቀስልሽ፤ በደርግ ጊዜ እንደሚታወቀው በተለይም ለቤተ እምነቶችም ሆነ ለአማኞች ከባድ ሁኔታ ነበር። ብዙ የእምነት አባቶች ካድሬ እንዲሆኑ ግፊት ይደረግባቸው ነበር። ጥቂት የማይባሉትም ታስረዋል፤ ተገድለዋል። ቅድም የጠቀስኩልሽ የቤተክርስቲያናችን ጳጳስ የሸንጎ አባል እንዲሆኑ ካድሬዎች ይወተውቷቸውና ያስጨንቋቸው ነበር። እሳቸው ግን ‹‹ቤተክርስቲያን ፖለቲካ ፖለቲካ ከሸተተች፤ ፖለቲካ እጣን እጣን ከሸተተ ዋጋ የለውም፤ እባካችሁ ተውኝ፤ እኔ እጣን እጣን ልሽተት የእጣን ሰው ነኝ፤ እናንተ ፖለቲካ ፖለቲካችሁን ሽተቱ›› በማለት ነበር የመለሱላቸው።
በእኔ እምነትም በዚህ ድፍረት ነው ቤተክርስቲያን መቆም ያለባት። በዚህ ድፍረት ስትቆም ደግሞ ቅድም እንዳልኩት ሩቅ ቆማ ክፉውን ‹‹ክፉ›› ብላ በጎውን ‹‹በጎ›› በማለት የበኩሏን አስተዋፅኦ ማበርከት ትችላለች። ምክንያቱም የሞራል ኃላፊነት አለባት። የሰው መብት እንዳይረገጥ፣ ክፉ እንዳይደረግ፣ ሥልጣን ያለአግባብ እንዳይጠቀሙ፣ የአገር ኢኮኖሚ እንዳይበዘበዙ፣ ሙስና እንዳይፈፀም ቤተክርስቲያን ‹‹ተዉ›› የማለት የመገሰፅ ኃላፊነት አለባት። ሩቅ ሆና መንገድ ማስተካከል ይገባታል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ የእምነት ተቋማት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ማለት ይቻላል?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- እንዳልሽው የአገራችን ፖለቲካ እንዳይበላሽ የእምነት አባቶች ትልቅ ኃላፊነት ነበረብን። አንድ የተሰበረብን፣ ያጣነውና ያበላሸነው ጉዳይ ይህ ነው። ኢትዮጵያችን ዛሬ ለደረሰችበት ነገር ፖለቲካው ከባድ ቢሆንም፤ መስዋትነት ቢያከፍለንም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባን አምናለሁ። ሕዝቡንም ሆነ ፖለቲከኛውን ‹‹በዘርና በጎጥ ከምንከፋፍል በህብረት ብንኖር ይሻለናል፤ ሁላችንንም
እግዚአብሔር ክቡር አድርጎ ነው የፈጠረን›› ማለት መቻል ነበረብን። እርግጥ ነው ቋንቋ ማደጉ ጥሩ ነው፣ ብሄረሰቦች ራሳቸውን ማጠናከራቸው፣ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉ መልካም ነው። ነገር ግን እርስበርስ እንድንባላ፤ እንድንጠላላ፤ እንድንጠላለፍ በሚያደርገን ደረጃ ግን መድረስ አልነበረብንም። ሁላችንም ክቡር ሆነን ነው የተፈጠርነው። ክብራችንን ጠብቀን ልንኖር የምንችልበት የፖለቲካ ሥርዓት ያስፈልገናል፡ በዚህ መንፈስ ብቻ ነው የእምነት አባቶች ኃላፊነታችንን ልንወጣ የሚገባን።
አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ የእምነት አባት ህሊናው ከፈቀደለትና ፖለቲካ ውስጥ፣ ብሔርተኝነት ውስጥ ከገባ መስቀሉን ትቶ ያንን የፖለቲካ ሥራ ቢያከናውን ነው የምመርጠው። ‹‹እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን›› እንደሚለው ቅዱስ ቃሉ ግሪካዊ ፣ አይሁዳዊ፣ ወንድና ሴት ብለን ልንከፋፈል አይገባንም። የጥል ግድግዳን አፍርሶ ድልድይ የሰበረው የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መዘንጋት የለብንም።
አዲስ ዘመን፡– በዕየለቱ የሞትና የግጭት ዜናዎች እየተለመዱ መምጣታቸው በማህበራዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው ጫና ምንድን ነው? በቅርቡ እርስዎም አጣዬ በግጭት ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ሄደው ሲጎበኙ ያስተዋሉትን ነገር እግረመንገድዎትን ያጋሩን?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- ያነሳሽው የአጣዬ ጉዳይ አንድ ምሳሌ ነው። እኛ እንደካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለይም ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ሰው ሰራሽም ይሁን የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ቀድሞ በመድረስ የበኩላችንን ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል። ካልኩሽ የፈጣሪ መርህ በመነሳት ‹‹እዛ ጋር ካቶሊካውያን አሉ፤ እዚህ ጋር ደግሞ የእኔ ብሔረሰብ አባላት አሉ›› ሳትል ሁሉንም በእኩል ዓይን እየረዳች ነው ያለችው። ቤተክርስቲያናችን የሰው ልጅ ተጎድቷል፣ ክብሩን አጥቷል፤ ተጎሳቁሏል በማለት ለሁሉም የምትደርስ ቤተክርስቲያን ነች። በትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኮንሶ፣ በኦሮምያና በሱማሌ ክልል በነበረው ግጭት፣ በጉጂና በጌድዮ መካከል በተከሰተው አደጋ ሁሉ ደርሰን የተጎዱትን አይተናል፤ ድጋፍ አድርገናል። እነዚህ ሰዎች ንፁኃን ዜጎች ናቸው።
ክቡር የእግዚአብሔር ፍጡሮች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ያለሃጢያታቸው ምንአልባትም በግለሰቦች የሥልጣን ሽኩቻ ወይም የፖለቲካ ሥርዓትን እናስተካክላለን በሚሉ ወገኖች ቁጭ ብሎ በመወያየት ፈንታ የሕዝባችን እና የአገራችን ጥቅም እናስቀድም በማለት ፈንታ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደማቸው የብዙኃን ዜጎቻችን ክቡር ሕይወት አልፏል። አንድም ዜጋ ክብሩ ሳይጠበቅለት አይደለም መሞት ዳቦ ሳይበላ መዋል የለበትም። ምክንያቱም እያንዳንዱ ዜጋ ክቡሩ፣ መብቱ ተጠብቆለት ግዴታውን አንዲወጣ ተደርጎ፣ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሰላማዊ ኑሮ የመኖር መብት አለው።
ዳቦ መብላት ያቃተው ማህበረሰብ በገጀራና በጥይት መግደል ወንጀልም ሃጢያትም ነው። ይህች አገር በዚህ መልኩ ደም ሊፈስባት አይገባም ነበር። ደም የፈሰሰባትን ምድር የማስታረቅ ሥርዓት ውስጥ ገብተን፤ ይቅር ተባብለን ማህበራዊ መግባባታችን የበለጠ የምናስቀጥልበት ሥርዓት መገንባት ሲገባን በዚህ ደረጃ እርስበርስ መጎዳዳታችን ለእኔ እንደሃይማኖት አባት ልብ የሚሰብር ነው። ምንአልባት ፖለቲካውን በበላይነት የሚመሩ አካላት በዚህ መልኩ የሚሄዱት ለአገር ጥቅም አስበው ነው ብለን እናምናለን። ለኢኮኖሚ ጥቅም አስበው ነው ብለን እናምናለን።
ግን የተኬደበት ርቀት ግን የሰበሰበን ሳይሆን የለያየን ገመድ ነው። በእያንዳንዳችን በግድግዳችን ውስጥ አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር እንዳይገናኝ ሆኖ ከሚገባው በላይ የተኬደበት ነው። አንዳንድ ጊዜ ‹‹ባህልንና ማንነትን እጠብቃለሁ›› በሚል እሳቤ ሰውን ከሰው የሚለያይ ግድግዳ እናበጃለን። ይህ ሁኔታ በመላው ዓለም ያለ ነገር ነው። ለምሳሌ አሜሪካ በዶናልድ ትራምፕ ጊዜ አሜሪካዊ ያልሆኑ ሰዎች እንዳይገቡ ግድግዳ አዘጋጅታ ነበር። ይህም የራሴን ባህል እጠብቃለሁ በሚል እሳቤ ግድግዳ እንዲፈጠር አድርጓል።
ያ የማንነትና የብሔር ግድግዳ የግንባችን እስረኛ እና ታጣሪ አልፎ ተርፎም ባሪያ አድርጎናል። ከዚያ ባሻገር ዓይናችን ከፍ ባለ ቦታ የተስፋን አድማስ እንዳናይ አድርጎናል። በዚያች ግንብ ውስጥ ስንታጠር ተስፋችን ሁሉ ይገድበዋል። ሩቅ እንዳንመለከት ያደርገናል። ስለዚህ ፖለቲካ ሩቅ እንድንመለከት ሊያደርገን ይገባል። የጥል ግድግዳን ልንገነባ ሳይሆን ወደ አንድነት ልንመጣ ነው የሚገባን። የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዩናይትድ ስቴት ብሎ የዓለም ሕዝብ ወደ አንድ በመጣበት ዘመን እኛ ልዩነታችንን አስፍተን የብቸኝነት ኑሮን መርጠናል።
ለዚህ ደግሞ የመጣንበት የፖለቲካ ሂደት ዋነኛው ተጠያቂ ሲሆን የማህበረሰቡን ሥነልቦና መስተጋብር ያላማከለ ፖለቲካዊ ጥቅምን ብቻ ለማግኘት የተደረገ ነው። ስለዚህ ይህንን የማረም ሂደት ውስጥ ነው መገባት ያለበት። በዚህ ሂደት ውስጥ እንግዲህ የምናያቸው ልብ የሚሰብሩ፣ የሚያስለቅሱን ነገሮች እንደእምነት አባት ተንበርክከን የፈጣሪን ምህረት መጠየቅ ይገባናል። አንድም ሰው መፈናቀል የለበትም፣ አንድም ሰው መሞት የለበትም።
ስለዚህ ይህንን የሚያደርጉ ወገኖች በፖለቲካ ሥልጣን ላይም ያሉ፣ ተፎካካሪም ይሁኑ መብት እናስከብራለን ብለው የሚቆሙ ቡድኖችም ይሁኑ በሰው ሕይወት ላይ ሊደራደሩ አይገባም። የሰውን ሕይወት ጥያቄ ውስጥ በማያስገባ መልኩ፣ በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየትና መግባባት ይገባል። ፅንፈኝነት፣ ብሔርተኝነት እና የእኔ ወገንተኝነት ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ነው አገር የሚያፈርሰው።
ይህንን ንፋስ መስበር አለብን። እንደሃይማኖት ተቋም አንደኛ በፀሎት፣ ሁለተኛ ሕዝባችንን በማስተማር አሁን ይህንን የማረም ሂደት ውስጥ ነው መግባት ያለበት። የፖለቲካውን ንፋስ ሳይሆን የፈጣሪን ንፋስ ነው ማስቀደም ያለብን። ምእመኖቻችንንም በዚህ መንገድ ነው ማነፅ ያለብን። ጊዜ ይፈጅ ይሆናል ግን ሰውን በሰውነቱ ካከበርን አይፈናቀልም የሚል እምነት አለኝ። እያዳንዳችን የወንድማችንና የእህታችን ባልንጀራዎች እንጂ ባላንጣዎች አይደሉም።
አቤል ቃየል ወንድሙን መግደሉ ሳያንስ እኔ ‹‹የወንድሜ ጠባቂ አይደለሁም›› ነው ያለው። አሁን ያለው ያ የአቤል ትምቢት ነው። እኔ ግን የወንድሜ ጠባቂ እንድሆን ነው ቅዱስ ቃሉ የሚያስተምረኝ። የወደቀውን ሰው ማንሳት የቆሰለውን ማከም ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። በፖለቲካው መስመር ያሉ ሰዎች ሰውን እንደሰውነቱ ሊያዩ እንጂ በብሔር ማንነቱ ወይም በሃይማኖት ማንነቱ መከበር የሚገባው አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– ሕግ የማስከበር ሂደቱ ላይ የሚያነሱት ክፍተት ካለ ቢገልፁልን?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- ሕግ የማስከበር ሥራ አሁን ላይ ብዙ ትርጉም እየተሰጠው ነው ያለው። ሕግ ማስከበር ማለት ሥርዓት ማስፈን ማለት ነው። ሥርዓት እንዲያስይዙልን ድምፃችንን የሰጠናቸው ሰዎች ሕግ ሲጣስ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው። እኔ ሕግን ከጣስኩ፣ ከእኔ መብት አልፌ የሌላውን መብት ከነካሁ ሕግ በእኔ ላይ መስራት መቻል አለበት። መንግሥት የተቋቋመው ሕግን እንዲያስፈፅም ነው።
በአገሪቱ ሕግ ወንጀለኞችን መቅጣት መቻል አለበት። የከፋ ነገር ሲመጣ ለምሳሌ ዜጎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርጉ ነገሮች ካሉ ፈጥኖ እርምጃ መውሰድ ከአንድ መንግሥት የሚጠበቅ ግዴታ ነው። የግለሰቦችንም ሆነ የቡድኖች መብት የሚገፉትን ሰዎች በሕጉ መሠረት በጥፋታቸው ልክ መቅጣት መቻል አለበት።
እንግዲህ በነበርንበት ሂደት ለዘመናት ብዙ ሰው ታስሯል። ብዙ ሰው ተፈርዶበታል፤ በፍትህም፤ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድም። አሁን ያለው መንግሥት በዚህ ረገድ አቅሙ መጠናከር አለበት። ሁሉም ጋር ችግር አለ። በሰሜኑም፤ በደቡቡም፤ በምሥራቁም በምዕራቡም ብዙ ፍላጎት ያለው ቡድን አለ። ሕግ ማስከበር ስንል የዜጎችን ነፃነት የሚነኩና የሚፃረሩ ነገሮች እንዳይከሰቱ ማድረግ መቻል አለበት። የፍርድ ሂደቱ ሥርዓት ባለው መንገድ መሄድ እንዳለበት ይታመናል።
ከዚያ ባለፈ በትክክል መሣሪያ መጠቀም በሚያስፈልግበት ቦታ ላይ በተለይ የአገር ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ በሚገባበት ወቅት መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። አሁንም ቢሆን ግን የመንግሥት የመጨረሻ ግቡ መሆን የሚገባው የፖለቲካ ስልጣኑን ማራዘም ሳይሆን የዜጎች ነፃነትና ህልውናን ለማስከበር ነው። ህዝቡ እየጮኸ ያለው መብቴ አልተከበረልኝም፤ ነፃነቴ ተጣሰ፤ ተፈናቀልኩኝ፤ ተገደልኩኝ፤ ቤቴ ተቃጠለ፤ ንብረቴ ወደመ፤ መንግሥት ሊጠብቀኝ ሲገባ ብሎ ነው።
ድምፃችን የሰጠነው መንግሥት ሊጠብቀን ሊንከባከበን መንገድ ሊያበጅና ሥርዓት ሊያሲይዝ ይገባዋል። ይሄ በእርግጥም የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ትልቁ የመንግሥት ውድቀት እያንዳንዱ ዜጋ የመንቀሳቀስ ሕግ ማስከበር ሲያቅተው ነው። በእርግጥ መንግሥት በሁሉ ቦታ ወታደር ሊያሰማራ አይችልም። ሁሉም ጋር ፌደራል ፖሊስ ሊኖር አይችልም። በመሆኑም እያንዳንዱ ማህበረሰብ፣ የሀገር ሽማግሌ፤ የሃይማኖት አባት ሕግ እንዳይበላሽ ዜጎች በመከባበር እንዲኖሩ ማድረግ መቻል አለብን።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ አንፃር መጪው ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ አኳያ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- እንግዲህ ምርጫ አንድ የፖለቲካ ሥርዓት ነው። አንድ አገር ውስጥ ያሉ ዜጎች እኩል መብት አላቸው ካልን፣ እኩል ግዴታም አለባቸው። ግዴታ ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ መብት አለ። ግዴታው ሕጎችን ፣ ሥርዓትን የማክበር ነው። እነዚህ ሥርዓቶች ለእኔ ጥቅም የተሰሩ ናቸው ብሎ ሕዝቡ ማመንና መቀበል አለበት።
ይሄ የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ በእውነትና በትክክለኛው መንገድ የሚያስተዳድሩ መሪዎችን የምንመለምልበት ሥርዓት ነው። የእኔ ወገን ስለሆነ ሳይሆን የእኔ ሃይማኖት ተከታይ ስለሆነ ሳይሆን ክቡር የሆነ ሰው በሰለጠነ መንገድ የሚያስተዳድር፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ከሆነ፣ ሁሉንም ዜጎች በእኩል መንገድ የሚያይ፤ ለሁሉም መስዋትነት የሚከፍል፤ ለእያንዳንዱ የሚገባውን ክብር የሚሰጥ የምንመርጥበት ሥርዓት ነው።
የእያንዳንዱ ዜጋ መብትና ግዴታው እንዲጠበቅለት ከፈለገ ያመነበትን ፓርቲ ወጥቶ መምረጥ መቻል አለበት። ስንመርጥ ፍትህ ለሚሰጠን እንጂ በወገንተኝነት አይደለም መምረጥ ያለብን። ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ነው ካልን የሚመረጠውም አካል ፍትሃዊና ታማኝ መሆን አለበት። ምርጫው በእርግጠኝነት የሰዎችን ስሜት ያከማከለ፣ የፖለቲካ ቀመር ውስጥ ያልገባ በትክክልም የሰዎች ድምፅ የሚከበርበት እንዲሆን ቤተክርስቲያናችን ታሳስባለች፤ ትመኛለች።
በሌሎች አገራት የምንመኘው ኮሮጆ የማይሰረቅበት፣ ያልተመረጠው ከተመረጠው ጋር ተጨባብጦና ተመራርቆ ወደ ቤቱ የሚሄድበትና አጋዥ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው የምንፈልገው። ከዚህ የሚያፈነግጥ ካለ ደግሞ የመንግሥት ሕግ አለ። ሁላችንም በሥርዓት መኖርና ለሕግ መገዛት አለብን። ሁላችንም እኩል መብት እንዳለን ሁሉ እኩል ግዴታ እንዳለን አውቀን የሁላችንም ጥቅም የሚከበርበትን ሁኔታ ማመቻት አለብን። ምርጫውን ተገቢ፣ ትክክለኛ፣ ፍትሃዊ ካደረግን እያንዳንዳችን ለዚህ አስተዋፅኦ ማድረግ ይገባናል።
መንግሥትም በገባው ቃል መሠረት በተጨባጭ ምርጫው ፍትሃዊ ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማድረግ መቻል አለበት። ሌሎችም ተመሳሳይ ኃላፊነት አለባቸው። ያኮረፉ ቡድኖች አሉ፤ ከምርጫ የወጡም አሉ። እነዚህ አካላትም ወደ ጉልበት መሄድ አያዋጣቸውም። ጥያቄዎቻቸውን በሰለጠነ መንገድ የሚያቀርቡ፤ የሚያዳምጡ መሆን አለባቸው። አብሮ በጋራ የሚያስተዳደር መንግሥት ሊመጣ ይገባል። ሁላችንም ጦሩን ትተን ቁጭ ብለን ችግሮቻችን በውይይት ለመፍታት መጣር አለብን።
ለዘመናት በድህነት ማቀናል፣ ጦር ተማዘናል አሁን ግን የተሻለች አገር መፍጠር አለብን ብለን መነሳት አለብን። አገራችን መሰቃየት ይበቃታል። ወደ መልካም ሁኔታ መሸጋገር ይገባታል። በፖለቲካ ሽኩቻ ለግል ጥቅም ተብሎ ሕዝብን ሰላም ማሳጣት ተገቢ አይደለም ብዬ ነው የማምነው። በዚህ መንፈስ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ ሁሉንም ያማከለ ከሆነ የዚህች አገር ትንሳኤ መምጣቱ አይቀርም። የእያንዳንዱ ዜጋ መብቱ ተከብሮለት የሚኖርባት አገር መፍጠር መቻል አለብን። ይህ እንዲሆን ደግሞ የእኛ የእምነት አባቶች ፀሎት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻ አገሪቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ አኳያ እንደሃይማኖት አባት ሊያስተላልፉት የሚገባው መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥዎትና ውይይታችንን እናብቃ?
ዶ/ር አባ ተሾመ፡- እንግዲህ ፋሲካ ስንል መሻገር ማለት ነው። 40 ቀን ፆመን ስጋና ወተት የምንበላበትና የምንጠጣት ጊዜ ደረሰ ብለን ጮቤ የምንረግጥበት ጊዜ አይደለም። ንስሃ ገብተን፣ የበደልነውን ወንድማችንን ጎንበስ ብለን፣ ይቅርታ ጠይቀን፣ እግዚአብሔር አምላካችን ይቅር እንዲለን የምንማፀንበትና በአዲስ ልብ በንፁህ ልብ ዘረኝነትን አስወግደን፤ ሁሉም ወንድሜ ነው የሚል ልዕልና ላይ መድረስ መቻል አለብን። ክርስቶስ ሲሞትልን የጥል ግድግዳን አፍርሶልናል።
በመሆኑም ትንሳኤን በትክክል ካከበርን በዚህ ሥርዓት ውስጥ ማለፍ አለብን። ስለሆነም የበደልን፣ የገደልን፣ ያጠፋን፣ ያፈናቀልን ሰዎች ወደ ህሊናችን ልንመለስና ይቅርታ ልንጠይቅ እንዲሁም ከስህተት መንገድ ልንመለስ ይገባል። ሁላችንም በንስሃ፣ ለፍቅር ለለውጥ መነሳት መቻል አለብን። ክርስቶስ የበሰበሰ ስጋ ይዞ አይደለም የተነሳው፣ የከበረ ስጋን ይዞ እንጂ። ስለዚህ ትንሳኤን ነገን የሚያይ ተስፋ ይዘን በፍቅና በአብሮነት ለመኖር መዘጋጀት አለብን።
ምክንያቱም ይህች አገር እውነተኛ ትንሳኤ ያስፈልጋታል። በዚህ የትንሳኤ ወር የምንሰራው የምንፀልየው ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያን እውነተኛ አማኞች የሚያደርገን ተግባር መሆን መቻል አለበት። የበሰበሰውን መጣል አለብን። ወደፊት እንመልከትና ይህችን አገር የመልካም የቅድስና አገር እናድርጋት የሚል መልዕክት ነው ያለኝ። በዚህ አጋጣሚ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች አንኳን ለዚህ የተቀደሰ የትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶ/ር አባ ተሾመ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝ ያ 23/2013