የእግር ኳሱ የበላይ አስተዳዳሪ የሆነው የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ክፍለ አህጉራዊ የልማት ቢሮ ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ አስመርቋል።
የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የእግር ኳስ አስተዳዳሪው አካል በማህበሩ አባል አገራት በኩል የእግር ኳስ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በአዲስ አበባ የተከፈተው 10ኛው የፊፋ ክፍለ አህጉራዊ የልማት ቢሮ ፊፋ ከሦስት ዓመት በፊት እግር ኳስ በመላው ዓለም እንዲያድግ የጀመረው የእግር ኳስ ልማት ሥራ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሮው በአዲስ አበባ እንዲከፈት ላደረገው አስተዋጽኦና ትብብር ትልቅ ምስጋና የሚቸረው መሆኑን ጠቅሰው፤ የአፍሪካ አገራት ላለፉት ሁለት ዓመታት የቀረጿቸው ፕሮጀክቶች ለአህጉሪቷ የእግር ኳስ እድገትና ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው፤ ፊፋም ለፕሮጀክቶቹ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው የክፍለ አህጉራዊው ቢሮ መከፈት ፊፋ ከምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ አገራት ጋር በቅርበት ለመሥራት ያስችለዋል ብለዋል።
የቢሮው መከፈት ፊፋ ከአባል አገራቱ ጋር በቅርበት ለመገናኘት እንደሚያግዘውና ለኢትዮጵያ፣ ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራትና ለአፍሪካ አጠቃላይ እግር ኳስ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ሥራውን የጀመረው የፊፋ ክፍለ አህጉራዊ የልማት ቢሮ ከዚህ ቀደም በሴኔጋልና በደቡብ አፍሪካ ከከፈተው ቢሮ ቀጥሎ ሦስተኛ ሲሆን፣ ፊፋ በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ክፍለ አህጉራዊ የልማት ቢሮዎች ቁጥር ወደ 10 እንደሚያደርሰው ታውቋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
በዳንኤል ዘነበ