
ታላቋ አህጉር አፍሪካ ብዙ ጊዜ በስፖርት መድረክ ታላላቅ አውራ ውድድሮችን የማዘጋጀት እድል ሲገጥማት አይስተዋልም። ለዚህም ከአቅምና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ጋር ተያይዞ አህጉሪቱ እንደማትችል አድርጎ መቁጠር ዋናው ምክንያት ነው። እኤአ 2010 ላይ ደቡብ አፍሪካ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን በተሳካ ሁኔታ ካስተናገደች ወዲህ ይህ የተሳሳተ አመለካከት በጥቂቱም ቢሆን ተስተካክሏል ማለት ይቻላል። ለዚህም እንደ ሞሮኮ ያሉት አገራት በቅርቡ የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ ካደጉት አገራት ጋር ጨረታ ውስጥ ሲገቡ ለማየት ተችሏል።
ኦሊምፒክ የዓለማችን ትልቁ የስፖርት መድረክ እንደመሆኑ መጠን አፍሪካውያን በተሳትፎ እንጂ በአዘጋጅነት ምን እንደሚመስል ተመልክተውት አያውቁም። አሁን ግን ይህን ታላቅ መድረክ በራሳቸው ምድር ደግሰው ሌሎችን የሚጋብዙበት መንገድ እየተጠረገ የመጣ ይመስላል። ለዚህም ከትናንት በስቲያ ዋናውን የኦሊምፒክ ውድድር ባይሆንም ሴኔጋል ቀጣዩን የወጣቶች ኦሊምፒክ እንድታዘጋጅ መመረጧ ማሳያ ነው። በአርጀንቲና ቦነ ሳይረስ በተካሄደው ሰላሳ ሦስተኛው የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሴኔጋል እኤአ በ2022 የሚካሄደውን አራተኛውን የወጣቶች ኦሊምፒክ ለማዘጋጀት በሙሉ ድምጽ የምርጫ ውጤት በይፋ ተረክባለች።
በዘመናዊው ኦሊምፒክ 122 ዓመታት የውድድር ታሪክ አዘጋጅነትቱ ወደ አፍሪካ አህጉር ሲመጣ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ሴኔጋል ይህንን እድል ያገኘችው ከሌሎች ሶስት የአፍሪካ ሀገራት ማለትም ከቱኒዚያ፡ ናይጄሪያ እና ቦትስዋና የቀረበባትን ከባድ ፉክክር አሸንፋ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በእለቱ የሀገራቸውን ለዚህ ውድድር መመረጥ እና ሀላፊነቱን በአካል ለመቀበል በቦነ ሳይረስ ጉባኤ የተገኙት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ሀገራቸው ለዚህ ውድድር ሲባል አዲስ የተገነባች ከተማን ጨምሮ ለውድድሩ ሶስት ከተሞችን በማዘጋጀት በወጣቶች ብዛት ቀዳሚ የሆነችውን አህጉራቸውን አፍሪካን የሚያኮራ ዝግጅት እንደሚያዘጋጁ ተናግረዋል። ለዚህ ውድድር ሲባልም አዳዲስ ዘመናዊ ባቡሮችና ሃምሳ ሺ ሰው የሚይዝ ስቴድየም ለመገንባት እንደታሰበ ታውቋል።
የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አፍሪካ የኦሊምፒክ ውድድሮችን እንድታዘጋጅ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው ሲሆን ከወራት በፊት ደቡብ ኮሪያ ፒዮንግያንግ ተዘጋጅቶ የነበረውን የክረምት ወራት ኦሊምፒክ አፍሪካ እንድታዘጋጅ ፍላጎት እንደነበረው ይታወሳል። የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባኽ ይህ እድል ለአፍሪካ መሰጠቱ ወደ ፊት ዋናውን የበጋ ወራት ኦሊምፒክ በአፍሪካ ለማዘጋጀት እድል እንደሚፈጥር በመናገር «ጊዜው የአፍሪካ ነው» ብለዋል።
ሦስተኛው የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአርጀንቲና መዲና ቦነ ሳይረስ በታላቅ ድምቀት ከትናንት በስቲያ ተጀምሯል። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ በስታዲየም ውስጥ ሳይሆን ሁሉም ህብረተሰብ ሊመለከተው በሚችል በከተማዋ አደባባይ ላይ ነበር። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ206 ሀገሮች የተውጣጡ አራት ሺ አትሌቶች በሰላሳ ሁለት የስፖርት አይነቶች ለአስራ ሦስት ቀናት ያህል ይፋለማሉ። ኢትዮጵያ በዚህ መድረክ በአትሌቲክስና ብስክሌት ስፖርቶች ተሳታፊ ነች።
ይህ የቦነስ አይረስ የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በኦሊምፒክ የውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወንድና የሴት ተሳታፊ አትሌቶች ቁጥር እኩል የሆነበትና በቶኪዮ 2020 የአዋቂዎች ኦሊምፒክ ላይ ሊካተቱ ይችላሉ የተባሉ እንደ ድብልቅ ጾታን የሚያካትቱ የውድድር አይነቶች የሙከራ ውድድር የሚደረግበት ነው።
የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስምንተኛው ፕሬዚዳንት ጃክ ሮጅ ሃሳብና ውጤት የሆነው እድሜያቸው ከ15-18 ያሉ ወጣቶች ብቻ የሚሳተፍበት የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ እ.ኤ.አ 2010 ሲንጋፖር ላይ የተጀመረ ሲሆን፤ ዋነኛ አላማው በሀገራት መካከል ውድድሮች ገዝፈው ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ሳይሆን ወጣቶችን በስፖርት እንዲሳተፉ ማነሳሳት፣በኦሊምፒክ እሴቶች ላይ የተመሰረተ ኑሮ እንዲኖሩ ማበረታታት እና የኦሊምፒዝም ፍልስፍና አምባሳደር እንዲሆኑ ማድረግ ነው። እነዚህ አምባሳደሮች ተቀራርበው የየሀገራቸውን ባህል፣ትውፊትና እና ወግ የሚከፋፈሉበት ብሎም በልዩነታቸው ውስጥ አንድነታቸው ጎልብቶ በኦሊምፒዝም አተያይ ተቻችለው እና ተከባብረው ይህችን ዓለም የተሻለችና ተፈቃቅረው የሚኖሩባት ሰላማዊ መንደር ማድረግ ነው፡፡ይህንን አላማ አንግቦ ሲንጋፖር ላይ የተጀመረው የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ለሁለተኛ ጊዜ በቻይና ናይንጄ ላይ ተካሂዲ ተራውን ለአርጀንቲናዋ መዲና ቦነስ አይረስ መስጠቱ ይታወቃል።
ሀገራችን ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ሁለቱም ጨዋታዎች ተሳትፋ ጥሩ ውጤት ያገኘችበትና ተስፋ የሚጣልባቸው እንደነ ዮሚፍ ቀጄልቻ ተተኪ አትሌቶችን ለማየት የቻለችበት ሲሆን በዚህ በሶስተኛው የወጣቶች ኦሊምፐክ ጨዋታ ላይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንከር ያለ ዝግጅት አድርጋ ወደ ስፍራው ልዑካኗን ልካለች፡፡
ቦጋለ አበበ