የጉንደት አድባር

በስማኤል ኬዲቭ ፓሻ የመሪነት ዘመን የፈርዖኖቹ ምስር በፈረንጆች አቆጣጠር 1875 በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ደግሞ 1867 ዓ.ም ሲውዘርላንዳዊውን ዋርነር ሙዚንገርንና ዴንማርካዊውን ኮሎኔል ሎሪንግን በአዝማችነት ቀጥራ በአፋሮቹ አውሳ በኩል ተሻግራ ጉንዳ ጉንዲት ላይ በግብጽ ጋባዥነት ለጸብ የተጠራችው ኢትዮጵያ ያበሾቹ መናገሻ የግዜር መቀደሻ የሆነችው አቢሲኒያ ማተበኛ ልጆቿ

“ምረር እንደቅል ምረር እንደቅል፣

አልመር ብሎ ነው ዱባ የሚቀቀል።

ሆ ብዬ እመጣለሁ ሆ ብዬ በድል፣

ጥንትም ያባቴ ነው ጠላትን መግደል።”

እያሉ በመፎከርና በመሸለል የመጣውን ወራሪ ኃይል እንደእህል ነዶ ወቁት። በዚህ የታሪክ ሁነት ለዓለም ስሟን የገለጠችው በኢትዮጵያና ኤርትራ መሃል ድንበር የምትገኘው ጉንደት ጊዮርጊስ “ክብር በግብር” እንዲሉ የቀዬዋን አድባር ካባቱ ሊቀ መምህራን ገብረአምላክ ገብረእግዚና ከእናቱ ወይዘሮ አበባ አስማረ የሕግ ባለሙያውን እንዲሁም በሙዚቃው ዘርፍ ግዙፍ እውቅና ያተረፈውን ዘመድ ገብረአምላክን በ1950 ወለደች። ወላጆቻቸው ጉልቻ አስቀምጠው ምሰሶ አቁመው “ውለዱ ክበዱ” የተባለው ምርቃት ቡራኬው ደርሶ በዘመድ ገብረአምላክ የበኩር ልጅነት ይስመር እንጂ በቤታቸው ኀዘን የተሸከመ ጭጋጋማ አየር ለመንፈስ ከአራት ዓመታት በላይ አልዘለለም። በሞራ (ቻይልድ ካትራክት) ሰበብ እይታቸው እክል ገጥሞት ላይነስውርነት የተዳረጉት ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ ጃንሆይ ወደ ኤርትራ ክፍለሀገር ሲሻገሩ የጉንደት ጊዮርጊስ ነዋሪ ለንጉሡ ያዘጋጀው አቀባበል ለእሳቸው መልካም ገድ ይዞላቸው መጣ። ለክብራቸው ታቦት ወጥቶ ሲዞር ከዕኩዮቻቸው ጋር ድክድክ የሚሉትን እኒህን ሰው አጼ ኃይለሥላሴ ይመለከቷቸውና ባጃቢዎቻቸው አማካኝነት አስቀርበው ወላጆቻቸውን አስጠሯቸው፤ አባታቸውም የደብሩ አስተዳዳሪ በመሆናቸው ለእግዜር እጅ ለንጉስ ደጅ ሩቅ አይደሉምና በልጃቸው እጣ ፋንታ ዙሪያ ከንጉሡ ጋር ሰፊ ውይይት ለማድረግ ቻሉ። “አስኳላ ትምህርት ቁርኝቱ ሳይንስ ጋር ስለሆነ ፈጣሪን እንዳያስጥለው ብዬ ነው ጃንሆይ?” አሉ ሊቀመምህራን ገብረአምላክ ገብረእግዚ ስጋታቸው በግልጽ እየተነበበ። ጃንሆይ ከንግግራቸው ደስ አለመሰኘታቸውን ሲገነዘቡ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ጊዜ ሸሽተው ሀገረ እንግሊዝ ሳሉ አርበኛ ጋዜጠኛና ደራሲ ተመስገን ገብሬ ከላከላቸው ደብዳቤ ኋላም “ሕይወቴ” በሚል ካሳተመው መጽሃፍ ውስጥ ባነሱት ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥርጣሪያቸው እንዲወገድ በመሻት ተዛማጅ ሃሳብ ያለበትን አንቀጽ መዝዘው ያነቡት ዘንድ አቀበሏቸው።

“ቅኔ በጀመርኩበት ዘመኔ ገና ትንሽ የ11 ዓመት ልጅ ብሆን እንኳን እንዴት አድርጎ ማስተማር በሚያውቅበት መንገድ ኑሬ ረዳኝ። ለተማሪው ሁሉ የሰጠው ዋና ምክር እንደሚከተለው ነው። “ቅኔ ልታዘጋጁ ቢሆን የበለጠ የተመቸው ጊዜ ለሊት ማንም ተንቀሳቃሽ ነገር ወይም ድምጽ አምሯችንን ከሃሳቡ ሊያሰናክለው አይችልም። ቅኔ የሚያዘጋጀውን ሰው አምሮውን ካሰበው ለማሰናከል ባጠገቡ አንድ ዝንብ ብትበር ይበቃዋል። ተቀምጦ ቅኔ ከሚያዘጋጅ ይልቅ ተጋድሞ ፊቱን ሸፍኖ ቢያስብ ይሻላል። ብርሃን አእምሮውን ይቀንሰዋል። እኛ አይነስውራን ቅኔ ለማዘጋጀትና በአእምሮ ለማጥናት ዓይን ካላቸው የምንበልጠው ስለዚህ ነው” ብሎ ይመክረን ነበር። ለጋስ በሆነው ማስተማር በሚያውቅበት መንገድ በትጋት ደግሞ አገዘን። ኑሬ ዓይነስውር ነው ግን ለተማሪዎች ሁሉ የሚያስደንቅ ብርሃን ነበር። እኛ ጭቃማ በሆነው በጠባቡ መንገድ መራነው፤ እሱ ግን በተሻለው በእውቀት መንገድ መራን። ሚስት የለውም ግን የሁላችንም አባት ነበር። ወላጆቻችን ገንዘብ ስላልከፈሉት ይርበው ነበር፤ እና ግን ብዙ በሆነ ጊዜ ርሃብን ይረሳው ነበር። በፈቃዱ ነውና የሚያስተምራቸው ብለው አባቶቻችን ገንዘብ መክፈል ሲከለክሉት እሱ እንደወላጆቻችን ጨካኝ አይደለምና ትምህርት አልከለከለንም። እሱ እጅግ አጭር ደግሞም ቀጭን ነው፤ ግን የታላቂቷ ቤተ ቤተክርስቲያን የደብረማርቆስ ጠንካራው ምሰሶ ነበር። ሰውን ሁሉ ለመውደድ ይፈቅዳል፤ ግን ያልታደለ ነውና በሁሉም ዘንድ የተናቀና የተጠላ ዓይነስውር ነበር። ከተማሪዎቹ በቀር ወዳጅ አልነበረውም።”

ጽሁፉን አንብበው እንደጨረሱ ቀና ሲሉ አጼ ኃይለ ሥላሴ በጥያቄ አስተያየት ተቀበሏቸው። “ልጄስ የመሪ ጌታ ኑሬ እድል እንዲገጥመው አልሻም” አሉና ሊቀመምህራን ገብረአምላክ ገብረእግዚ ለጃንሆይ ልጃቸውን ጋሼ ዘመድን መርቀው ሰጧቸው። ለነገሩ ጠጅ ተጥሎ ንጉሥ አባብሎ እንዴት እንቢ ይባላል?

ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ ወደመሃል ሀገር አዲስ አበባ የፈረንጅ ትምህርት ለመማር ከንጉሡ ጋር ሊሄዱ እንደሆነ በጨቅላ አምሯቸው ሲያስቡት አፋቸውን የፈቱበት

“አስኳላ ተማሪ ሽታው ሎሚ ሎሚ”

የሚለው ስንኝ በሕያው የልቦናቸው ጽላት ተሰደረ፤ እኩዮቻቸውም

“ቁመቱ ሰንበሌጥ፣

ለጉንደት ምስለ ጌጥ።

ቃሉ እንደስሉስ፣

አኗኗሩ እንደንጉሥ።”

በማለት ያወድሷቸው እንጂ በዕድላቸው መቅናታቸው አልቀረም። እኔም ማንነታቸውን በመበርበር ታሪካቸውን ለመዘከር ከሕይወት ገጻቸው ክታብ ከዕድሜ ትዝታ ምናብ ሽበታቸውን ያቆነጀውን የዘመን አይሽሬ ሥራቸውን ሃሳብ ሰፈርኩ።

“በሰሜን ቢመጣ ማን ያስገባው ነበር፣

በደቡብ ቢመጣ ማን ያስገባው ነበር፣

በምስራቅ ቢመጣ ማን ያስገባው ነበር፣

በምዕራብ ቢመጣ ማን ያስገባው ነበር፣

በሰማይ መጣ እንጂ በማናቀው ሀገር።”

ሲሉ አርበኞች ያዜሙለት አውሮፕላን ጠቀሜታው በሕዝቡ ልብ ውስጥ ሰርጾ አገልግሎቱ ሲታወቅ

“አውሮፕላን ሲሄድ ይላል ባየር ባየር፣

ያቺ ልጅ ካልመጣች ስሟን ነው መቀየር።”

በሚለው በአበበ ተሰማ ሙዚቃ ተቀየረና ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ ከኤርትራ አዲስ አበባ በንጉሥ አውሮፕላን መጡ። ሰበታ መርሃእውራን ትምህርት ቤት እስኪሰለጥን ድረስ የእግራቸው ጫማ የአዲስ አበባን መሬት እንደሳመ አካል ጉዳተኛ ያልሆኑ የካዛንቺስ ሕጻናት ማሳደጊያን ለወራት እንዲቆዩበት ተቀላቀሉ። “እስከዚያው ድረስ” በሚል እሳቤ አጼ ኃይለሥላሴ ከውጭ ተራዕዶ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የዓይነስውራን መዋለሕጻናት ገነቡና ጋሼ ዘመድን ጨምሮ በርከት ያሉ ዓይነስውር ሕጻናትን አዛወሯቸው፤ ኋላም 1956 ዓ.ም የሰበታ መርሃእውራን ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቆ ለማስተማር ዝግጁ ሲሆን በካዛንቺስ የዓይነስውራን መዋለሕጻናት ከነበሩት ሌላ በየክፍለሀገሩ የሚገኙ ዓይነስውር ታዳጊዎችን በማሰባሰብ ለትምህርት አስገቧቸው። ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ ከቀይ ባሕር የጉርጉሱም ፉጨት ከምጽዋ የተፈጥሮ ውበት ርቀው የሰበታን አየር መላመድ ቢቸግራቸው

“እህህ ይላል ያሰሩት ፈረስ፣

ሳር ባይጥሉለት የልቡ ባይደርስ።

ያውና ይታያል ያገሬ ሰማይ፣

እንዲህ ሆዴ ቆርጦ መጥቻለሁ ወይ።”

እያሉ በዕንባ የታጀበ በብስክስክ የልጅ አንጀት የናፍቆት ዜማ አንጎራጎሩ፤ ይሁን እንጂ በሞግዚቶች ተግሳጽና በጓደኞቻቸው ብርታት አዲስ ማንነት ተላብሰው ለኢትዮጵያ ሙዚቃ አበርክቷቸው እርሾ ማስቀመጥ ጀመሩ። ለስፖርት ያላቸው ፍቅር የሙዚቃ ግዜያቸውን ቢሻማባቸውም ምስጋና ለሰበታ ኦርኬስትራ ይግባውና እድሜያቸውና የክፍል ደረጃቸው እያደገ በሄደ ቁጥር ቀልባቸውን በመሰብሰብ ሙሉ ትኩረታቸውን ሙዚቃው ላይ አደረጉ።

ሰበታ ኦርኬስትራ የአሁን መጠሪያ ስሙን ከማግኘቱ አስቀድሞ የሰበታ «አርሞኒካ ባንድ» ይባል እንደነበር ጋሼ ዘመድ አጫውተውኛል። በርከት ያሉ ያርሞኒካ መሳሪያዎች በመኖራቸው የተነሳ ስያሜው እንደተሰጠው የሚነገርለት ይሄው አርሞኒካ ባንድ አኮርዲዮንና ፒያኖ ተጨምሮበት ያኮርዲዮኑ ሻንጣም እንደድራም እየተመታ ባርሞኒካ መሣሪያ ታጅቦ ሙዚቃው ሲንቆረቆር ደንበኛ ስትሪንግ ኦርኬስትራ ልክ እንደሲንፈኒ ይደመጥ ነበር። ይህም በብስራተ ወንጌል ኋላም (በተዋህዶ ኤክስተርናል ሰርቪስ) የድምጽ ክምችት ለታሪክ ተቀምጧል። በቀዳማዊ የኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት በበላይነት የሚመራው ሰበታ መርሃ እውራን ትምህርት ቤት ከክቡር ዘበኛ፣ ምድር ጦርና ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ጋር ትሥስር በመፍጠር ተማሪዎቹ በሙዚቃው ዘርፍ እምቅ ችሎታቸውን ለዓለም እንዲያሳዩ ጮራ ፈንጥቋል።

በወቅቱ የዛንቢያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ካውንዳ ኢትዮጵያ በመጡበት አጋጣሚ በጃንሆይ ጋባዥነት ሰበታ መርሃ እውራን ትምህርት ቤትን ሲጎበኙ ደስ ተሰኝተው የኢትዮጵያ 4000 ብር በስጦታ መልክ ከማበርከታቸው ባሻገር ጥሩ ተሞክሮ በመሆኑ ቃል ከተግባር የሰመረበትን የንጉሡን ሥራ በልቦናቸው ከተቡት። በጊዜው የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደም ገቢ የተደረገውን የዶክተር ካውንዳን የስጦታ ገንዘብ ከግምጃ ቤት ወጪ አድርገው በክቡር ዘበኛ ደረጃ ልክ ድራም፣ ትራንፔት፣ ሳክስፎን፣ ክላርኔትና ማራካሽ በመግዛት የሰበታ ኦርኬስትራን ቁመና አስተካከሉት። በቀለ ገብረማርያም በሳክስፎን፣ ለባሕል የሙዚቃ መሣሪያዎች አለማየሁ ፋንታ በማስተባበሩ በኩል ደግሞ የምድር ጦሩ ሻለቃ አሽኔ ኃይሌ፣ ኮሎኔል ለማ ደምሰው፣ የዛሬው የኢቢሲ የሙዚቃ ክፍል ኃላፊ ጸጋዬ ደባልቄ፣ ጣሊያናዊው ሲኞር አሜርጎ የሚገኙበት ሲሆን ከንጉሡ በተጨማሪ የሀገሪቱ ሹማምንት እንደዓይናቸው ብሌን ክትትላቸው ተለይቶት አያውቅምና የሰበታ ኦርኬስትራ የሙዚቃ ጉዞ እጅጉን አምሮና ደምቆ በመላው ክፍለሀገር ዝናው ተንሰራፍቶ እየዞሩ አያሌ መድረኮች ላይ ሥራቸውን ማቅረብ ችለዋል።

በእንዲህ መልኩ በሰበታ መርሃ እውራን አዳሪ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል የነበረውን ቆይታ የጨረሱት ጋሼ ዘመድ ገብረ አምላክ ከዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቱ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሙሉጌታ ገድሌ ትምህርት ቤት የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተሾመ ምትኩ፣ ተስፋዬ ኢዶ፣ ታምራት ከበደ፣ ታምራት ፈረንጅ የበቀሉበትን ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤትን ተቀላቀሉ። ጓዛቸውን ጠቅልለው አዲስ አበባ ይግቡ እንጂ ርዕሰ መምህሩ ሚስተር ራምኬል ሀገሩ አሜሪካ እስከሄደበት ድረስ ምግብና ማደሪያ ተመቻችቶላቸው ቅዳሜና እሁድ እየተመላለሱ ለሰበታ ኦርኬስትራ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ከሬንቦ ባንድ አባላት ማለትም ተሾመ አሰግድ፣ አብዱቄ ከፈኒ፣ ንጉሤ ሃይሉ፣ ቁምላቸው አበበ፣ ዶክተር በቀለ ሃይለሥላሴና ዶክተር ሰለሞን ሃይለሥላሴ ጋር በመሆን ያሰለጥኑ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ መከራ ያልለመደውን ትከሻቸውን የሚያጎብጥ የፖለቲካ ጦስ በትምህርት ገበታቸው ዙሪያ አንዣቦ ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ምስቅልቅል ውስጥ ከተተው።

የተማሪዎች አመጽ ጉልበት ሆኖ አጼ ኃይለሥላሴን ከወንበር ያወረደው የደርግ መንግሥት የእድገት በሕብረት ዘመቻ ጥሪ ሲያደርግ። በተማሪዎች መሃል መከፋፈል የወለደው ሽብር ተፈጠረ። ይህም በዓይነስውራን ተማሪዎች ዘንድ ቀላል የማይባል የችግር ጥላውን አጠላባቸው። 1966 ዓ.ም 11ኛ ክፍል የደረሱት እነ ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ “ሀገሪቱ አምናበት ያወጣችውን አዋጅ በመብት ደረጃ ተሳትፈን ኋላ አልተሳተፋችሁም ተብለን ከምንቀር እኛን ታሳቢ ያደረገ ምደባ ይደረግልንና ዘመቻውን እንካፈል?” በማለት ለዘመቻ አስተባባሪዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም አዎንታዊ መልስ አላገኙምና ሙግት ገጠማቸው። “መንግሥት ትምህርት ለሁሉም ብሎ ሙዋለ ነዋዩን አፍስሦ ያስተማረን ከራሳችን አልፈን ሀገር እንድንጠቅም እንጂ ከእጅ ወደአፍ ለሆነ ኑሮማ በልመናስ ይኖር የለም እንዴ? ይልቁንስ ከጥገኝነት አዙሪት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት በመደገፍ ሞራል ሁኑንና በተማርነው ልክ ማኅበረሰባችንንም ሀገራችንንም እናገልግል። ደግሞምኮ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን

የተማርነው ከተረጂነት መንፈስ ለመላቀቅና ሁልጊዜ ለራሳችን ምቾት መደላድል ለመፍጠር መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ግዴታችንንም ለመወጣት ጭምር ነው” አሉ በጠንካራ ተነሳሽነት ተሞልተው። ከስንት ጊዜ ንትርክ በኋላ መሄድ እንደሚችሉ ታምኖበት በኮከበጸባህ ትምህርት ቤት ምድባቸው የደረሳቸውን አርቤጎና ሲዳሞ ክፍለሀገር ከአካል ጉዳተኝነታቸው አንጻር ርቀቱን ተገንዝቦ ዘመቻ አስተባባሪው የሚሹትን ድጋፍ በቅርብ ሆኖ ለመከታተል ያመቸው ዘንድ ደብረሲና መደባቸው። ዘመቻውን የነሱ መቀላቀል ለሌላው ተማሪ ተነሳሽነት ይፈጥራል በሚል እሳቤ የሚዲያ ሽፋን ተሰጠውና የኮከበጽባህ ዓይነስውራን ተማሪዎች እድገት በሕብረቱን በመደገፍ ለዘመቻው እንደተዘጋጁ ተገለጸ። በዚህ መልኩ መንገዳቸው ተሰናድቶ ጉዞ የሚጀምሩበትን ቀን ሲጠባበቁ ያልገመቱት ነገር ተከስቶ በተማሪው ዘንድ ቁርሾ አሲያዘባቸው። ተማሪው ሪቮሊሽነሪና ሪአክሽነሪ በሚል ጎራ ለይቶ ሳንጃ ሲሞሻለቅ የመማሪያ መጽሃፍት በብሬል ያልቀረበላቸው ከሁለተኛ ደረጃ አንስቶ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያሉ አይነስውራን ተማሪዎችም በመማር ማስተማሩ ሂደት የነበራቸው እንቅስቃሴ አደጋ ላይ ወደቀ። በየትራንስፖርቱ፣ በየንግድ ቦታዎች፣ በየመዝናኛ ስፍራውና በየቤተእምነቱ ሳይቀር የሚያገኛቸው ሁሉ “እናንተ የንጉሡ ቅምጥሎች! እናንተ የመንግሥት አፎች! እንጀራችሁን ለማብሰል በወንድሞቻችሁ ደም ትረማመዳላችሁ አይደል?” ይላቸዋል፤ ይህም ውሎ አድሮ ኩርፊያቸውን አንሮት የሚያነብላቸውና የሚቀርጽላቸው ጠፋ። እንደመኢሶን፣ ኢጨአት፣ ወዝሊግ፣ ኢሕአፓ የመሳሰሉት

የአካል ጉዳተኞች የፖለቲካ ተሳትፎ

የፖለቲካ ድርጅቶችስ አካል ጉዳተኞችን ከማሳተፍና ስለአካል ጉዳተኝነት ከመሥራት አንጻር ምን ሚና ነበራቸው? ስል ላነሳሁላቸው ጥያቄ ቅሬታ አዝሎ የሻከረ ስሜታቸውን እያስታመሙ ትዝብታቸውን አካፈሉኝ። “እኛን የሚያካትት የፖለቲካ ማሕቀፍ መዘርጋት ይቅርና በማንፌስቷቸው እንኳን አላሰቡንም፤ ጊዜውም የትጥቅ ትግል ፋሽን የሆነበት ዘመን ስለነበር ሰበብ እንዳንሆንባቸው ያገሉናል እንጂ ጭራሽ አያቀርቡንም” ሲሉ አስረዱኝ ሁኔታው አሁን የሆነ ያህል እያንገሸገሻቸው። ሪአክሽነሪዎች የእድገት በሕብረቱን ዘመቻ ዓላማ በመገንዘብና የመንግሥትን ተልኮ በመቀበል “እንዘምታለን” ብለው ለመዝመት ሲነሱ አብዮት ቀስቃሾች “አንዘምትም” በማለት ክፉኛ ሲነቅፏቸው መንግሥት በነገሩ ጣልቃ ገብቶ ጸቡን በማብረድ በተሳካ ሁኔታ የዘመቻ ስምሪቱን አካሄደ። እነ ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክም ደብረሲና ደርሰው የመምህርነት ሥራቸውን ቢጀምሩም አብዮቱ ላይ በተፈጠረ ቅራኔ ጦርነት ተነስቶ የእድገት በሕብረቱ ዘመቻ ባጭር ተቀጨና ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ተገደዱ።

ከጥቂት ቀናት ግርግር በኋላ 12ኛ ክፍልን ለጨረሱ ተማሪዎች ቋሚ የመምህርነት ቅጥር ተፈቅዶ ዳግም እንዲዘምቱ ቢጠየቁም ሐረር የደረሳቸው ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክና ሌሎች የሬንቦ ባንድ አባላት ወዳጆቻቸው ከቻርለስ ሳተን ጋር የኢትዮጵያ ኦርኬስትራን የመሠረተው ጋሼ ተስፋዬ ለማ “ምድባችሁ ከሐረር በኋላ ገጠር ሊሆንም ይችላልና ለምን እዚህ ቀርታችሁ ከኔ ጋር ሙዚቃ አንሠራም?” የሚል ግብዣ ሲያቀርብላቸው ጊዜ ሙዚቃው አማለላቸውና የተቀበሉትን የማስተማር ጉዞ ያለማመንታት ሰረዙት፤ ይሁን እንጂ መከራ የወለደ ከዕርጥብ ቆዳ የከበደ ችግር ከፊታቸው ተደነቀረና ሕልማቸውን ለመኖር በያዙት የስኬት ጎዳና ላይ የጋሬጣ እሾሁን ነሰነሰበት። በዋናነት የችግሩ ገፈት ቀማሾች ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክና ዶክተር ሰለሞን ኃይለሥላሴ ሲሆኑ ወደቤተሰብ እንዳይሄዱ ወላጆቻቸውን በልጅነታቸው በሞት ተነጥቀዋል። አዲስ አበባም እንዳይኖሩ በአብዮቱ ግርግር የተነሳ ትምህርት ስለተቋረጠ ይሰጣቸው የነበረው የኪስ የሃያ ብር ድጎማው በመቆሙ ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሆነባቸው። “ሪቮሊሽነሪዎች በየትራንስፖርቱ፣ በየንግድ ቦታው፣ በየመዝናኛ ሥፍራውና በየቤተእምነቱ ባገኙን ቁጥር “እናንተ የንጉሡ ቅምጥሎች! እናንተ የመንግሥት አፎች!” እያሉ ያሸማቅቁን እንዲህ ችግር ሊቆላን ኖሯል? እኛ ለራሳችን ለ5 እየተቧደንን ያቀናጀነው ሃያ ብር መቶ ብር ሲመጣ ይሻላል ለምንለው ምግብ ቤት ኮንትራት ከፍለን እንጠቀም ነበር እንጂ እንኳንስ ልንቀብጥ ቁርስ እንኳን በልተን አናውቅም። የምትተርፈንን አንድና ሁለት ብርም ለጫማ ማስጠረጊያ ነው የምናውላት” አሉ ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ ርሃቡና ጥሙ አሁን የሆነ ያህል እየተሰማቸው። የኑሮውስ ሁኔታ ምን ቢሆን ነው በሃያ ብር ልትቋቋሙት የቻላችሁት? ብዬ ጥያቄዬን ሳስከትል ወደኋላ በትዝታ ፈረስ ሽምጥ ጋለቡና የሃሳቤን ዳና ያዙት።

“የምን እንቅፋት ነው እሾህ አይወጋሽ፣

በቅቤ እንጎቻ ነው የሚጋገርልሽ።

ተብሎ የሚዘፈንበት ጊዜ ነበር” አሉ ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ አፋቸው ሞ ልቶ ምራቃቸውን እየዋጡ።

ሕይወት በየፈርጁ

ሕይወት በምን መልኩ ቀጠለ? አልኳቸው ኀዘናቸው ተጋብቶብኝ። “ተሾመ አሰግድ ያሁኑ አሜሪካን ሚሽነሪ ስኩል የቀድሞው ሕይወት ብርሃን ትምህርት ቤት በሙዚቃ መምህርነት ሥራ አግኝቶ ነበር፤ አብዱቄ ከፈኒም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር፤ ሌሎችም እንደዛው። እናም አብዱቄ ከፈኒ ፒያኖውን ተሾመ አሰግድ አኮርዲዮኑን አቀናጅተው ሶስት መቶ የሚጠጉ የዘፈን ሥራዎችን በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ አቀናብረው በማዘጋጀት ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ሸጡና የተገኘውን ገቢ መሸሻ ዘመድ ማምለጫ መንገድ ለሌለን ለኔና ለሰለሞን ክፉ ቀን መውጫ እንዲሆነን ደጎሙን፤ ይህም የድሮ ዓይነስውራን ተማሪዎች ምን ያህል እንደምንዋደድና እንደምንተሳሰብ ምስክር በመሆኑ የዚህ ዘመን ዓይነስውራንም የምትማሩበት ይመስለኛል” አሉ እግረመንገዳቸውን ምክረሃሳብ ጣል እያደረጉ። ጥሎብኝ የጥያቄ አባት ነኝና ሳልዘነጋው የፖለቲካው ትኩሳትስ ከምን ደረሰ? አልኳቸው ሆዴን ቆርጦኝ። “እኛ በጊዜው ሪዎታለማቸውን ሊግቱን ለሚቀርቡን ሁሉ ሁለት ቀይ መስመሮችን አስምረን ነበር” ይላሉ በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ ውዥንብር ሲገልጹ። “የመጀመሪያው ሶሻሊዝምን እንደፈለጉ ይስበኩ ግን “ፈጣሪ የለም” እያሉ በእግዚአብሄር እንዳይመጡብን የሚገስጽ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ እነሱ ያልሠሩትን ሠርተዋልና አጼ ኃይለሥላሴ ያለአግባብ እንዳይሰደቡ ድንበር ማበጀት ግድ ብሎን ነበር” ሲሉ ከማስረዳት በተጨማሪ የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት ለመቀላቀል እንዳልፈቀዱ አያይዘው አጫወቱኝ።

ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ ፈተናን እንደሕይወት ሽግግር በመቁጠር ሁለመናቸውን የሰጡለት ከሙዚቃው ዘርፍ ጋር በጓደኞቻቸው ድጋፍ አማካኝነት የነፍስ ማቆያ ካገኙ በኋላ ልብ ለልብ ተገናኙ። ፋንታሁን አንተአለኸኝ፣ ተፈራ ካሳ አኮርዲዮኑንና አየለ ማሞ ማንዶሊኑን ሸፍነው ከጋሼ ተስፋዬ ጋር ይሠሩ የነበሩት እኒህ እውቅ የሙዚቃ ሰዎች መገናኘት እንዳለ ሁሉ ሲለያዩ ሬንቦ ባንድን የመሠረቱት ሰባቱ ዓይነስውራን ተኳቸውና የሙዚቃ ጥማቸውን ለማርካት አሀዱ አሉ። አብዱቄ ከፈኒ ፒያኖውን፣ ተሾመ አሰግድ አኮርዲዮኑን፣ ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ ቤዝ ጊታሩን፣ ዶክተር ሰለሞን ኃይለሥላሴ ሊድ ጊታሩን፣ ዶክተር በቀለ ኃይለሥላሴ ትራንፔቱን፣ ንጉሤ ኃይሉ ሳክስፎኑንና ቁምላቸው አበበ ድራሙን ሲያሽሞነሙኑት ጋሼ ተስፋዬ በሙዚቃ እምቅ ችሎታቸው ተደንቆ የስመጥር ሰዎችን ሥራ እንዲሠሩ እድል አመቻቸላቸውና ዐሻራቸውን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ማሳረፍ ቻሉ። እንደዋሽንት፣ ክራር በመሳሰሉት በባሕል የሙዚቃ መሣሪያዎች የተካኑት ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክ ትራንፔቱን አንስተው ሳይጥሉ ወደቤዝ ጊታር የነበረውን ሽግግራቸውን ሲያወጉኝ “እንደፋሽኑ እንደጊዜው መሆን አምሮኝ ሳይሆን አይቀርም” ይላሉ ሽበታቸውን ባቆነጀው በመልካም ሥራቸው ፈገግታ ደምቀው። በኢትዮጵያ ኦርኬስትራ ስር እያሉም የጥላሁን ገሰሰን “አልማዝን አይቼ፣ እሁድ ባስር፣ ሳቅ፣ ውቢት፣ ሕይወቴ” እና የጸሃይ እንዳለን “ጸጉሯ ወርዶንና አንተ ነህ” የሚሉትን ለመሥራት በቅተዋል።

ኋላም ገንዘቡም እውቅናውም መጥቶ በሁለት እግራቸው እንደመቆም ሲሉ ከኢትዮጵያ ኦርኬስትራ ወጥተው ነበልባል የተሰኘ ባንድ በማቋቋም በየምሽት ቤቱ መሥራት ጀመሩ። ታዲያ አንድ ቀን በቱሪስት ሆቴል የምሽት ሥራ ላይ ሳሉ በድምጻዊነት እያገለገለ አብሯቸው ላለው ዓይናማ ወዳጃቸው የመሳሪያ ኪራይ እንዲከፍል የሰጡትን ገንዘብ ለተባለው ዓላማ ሳያደርስ ይዞት ይጠፋል። ይህን ጊዜ የተፈጠረባቸውን ያቅም ማነስ ለመሙላት ኮንሰርት አዘጋጅተው ናዝሬት አጼ ገላውዲዎስ ትምህርት ቤት ተገኙ። አዳራሹ ሞልቶ ሰው ባልተረፈ ብለው ቢጠብቁም ይባስ ብሎ ፖስተራቸውም ይቀደድ ጀመር። የማታ ማታ አምስት ሰው ገባና ሳይደናገጡ ሥራቸውን አቅርበው ሲጨርሱ ከታዳሚዎች አንዱ በመድረኩ ዙሪያ አስተያየት መስጠት እንደሚፈልግ ነግሮ የፖስታ ቁጥራቸውን ተለዋውጠው በምስጋና ተለያዩ። በሳምንቱ ፖስታ ደርሷቸው መልዕክቱን ሲያስነብቡት እንዲህ ይል ነበር።

“በወቅቱ የእናንተ ዝግጅት ከጳውሎስ ኞኞ ቲያትር ጋር ከመደረቡም በላይ በጊዜው ሶስተኛው ነበልባል ጦር ተመስርቶ ነበርና ሕዝቡን የምድር ጦር አባላት ስለመሰላችሁት በመድረኩ አለመታደም ብቻ ሳይሆን በየቦታው ፖስተራችሁን ይቀደው ነበር፤ በተረፈ ዝግጅታችሁ እጅግ በጣም ጥሩ ነበር” ይላል። አጋጣሚው መማሪያ ሆኗቸው “ቀስተደመና ሰባት ቀለማት አሉት፤ እኛም ሰባት ዓይነስውራን ነን፤ ስለዚህ እንግሊዝኛውን ቃል በመጠቀም እንለውጠው” ከሚል ስምምነት ላይ ደረሱና ነበልባል ይባል የነበረው ሬንቦ ባንድ ወደሚል ስያሜ ተቀየረ። በሬንቦ ባንድም የተሾመ አሰግድን “ትዝታ” ያበበ ተሰማን፣ የጌታቸው ተሰማን፣ በቀረጥ ምክንያት ለሕዝብ ጆሮ ያልደረሰውን የብዙነሽ በቀለን፣ የጥላሁን ገሰሰን “ስንብት፣ አልተግባባንም፣ እንደከረን ሎሚ” የሚሉትን ሸክላዎች ሠርተዋል። የጥላሁንን “ስንብት” በተመለከተ ያላቸውን ገጠመኝ ሲያጫውቱኝ በወቅቱ የነበረው ግርግር የፈጠረባቸው ድንጋጤ ዛሬም ድረስ የለቀቃቸው አይመስልም። በሰበታ ኦርኬስትራ ሳሉ ለትምህርት ቤት ያዘጋጁት ስንብት ስም አስገኝቷቸው በያመቱ አቃቂ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት እየተጋበዙ በወላጆች ቀን ያቀርቡት ነበር፤ ኋላ ግን ሬንቦ ባንድን መሥርተው የዶክተር በቀለ ኃይለሥላሴ ድርሰት የሆነው ስንብትም ወደፍቅር ዘፈን ተለውጦ ጥላሁን ተጫወተውና ዝናቸው መላ ሀገሪቱን ናኘ።

እንደወትሮው ሁሉ ትምህርት ሲዘጋ አቃቂ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ተጠርተው ሬንቦ ባንድን ሰየሙና

“ወጣቷ ዘንጣፋዬ፣

ደህና ሰንብቺ አበባዬ፣

ፊቴ ታጠበልሽ በንባዬ።

እያለ ተሾመ አሰግድ ሲያዜም የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች “እኛ የምንፈልገው የትምህርት ቤቱን የድሮውን ስንብት እንጂ ይሄን አይደለም” ብለው ሲያስቆሟቸው ተማሪው አምጾ ከድንጋይ ውርወራ ባለፈ ንብረት ማውደም ሲጀምር የጸጥታ ኃይሎች በተኩስ ታግዘው ግርግሩን አስቆሙትና እነ ጋሼ ዘመድ ገብረአምላክን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው። የችግሩ ክብደት በኢሕአፓ አስጠርጥሯቸውም ነበር፤ ኋላ ግን በሙዚቃው አለመግባባት እንደሆነ ሲረዱ ሊፈቱ ችለዋል። ይህን ሁሉ ያየው ሬንቦ ባንድም እነ ጋሼ ዘመድ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡና አብዛኛው የቡድኑ አባላት ከሀገር ሲወጡ ለመፍረስ ተዳረገና የዘመናት የሙዚቃ ጉዞው ተደመደመ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀሉት ጋሼ ዘመድ የሕግ ትምህርት ክፍልን አሜሪካኖች ስላቋቋሙት የግንዛቤ እጥረት ባያጋጥማቸውም ሌሎች ጓደኞቻቸው “ለናንተ አይሆንም አትችሉትም” በሚል የተሳሳተ አመለካከት የተነፈጉትን የትምህርት ዓይነት እንዲያገኙ ብርቱ ጥረት አድርገዋል።

1975 ተመርቀው ከ76 አንስቶ ውሃ ሀብት ሚኒስቴር፣ ውሃ ፈንድና ስታስቲክስ ጽህፈት ቤት በኃላፊነት ደረጃም ጭምር ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ የሠሩባቸው ተቋማት ሲሆኑ “አለመቻላችንን እንጂ ስንችል ደግሞ መቻላችን አይበረታታም” ያሉት ጋሼ ዘመድ የሥራው ዓለም ቆይታቸው ቀላል እንዳልነበር ይገልጻሉ። ባሁኑ ሰዓት የጥብቅና ፍቃድ አውጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

ሐብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You