
– የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይትም ወደ ኅዋ ለማምጠቅ ሥራ ጀምራለች
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ሦስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ እየተዘጋጀች መሆኑንና ለዚህም ሻንጋይ ኢንጂነሪንግ ማይክሮ ሳተላይት ከተሰኘው የቻይና ኩባንያ ጋር የውል ስምምነት ተደርጎ ሥራው መጀመሩን የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይትም ወደ ኅዋ ለማምጠቅ እየሠራች መሆኑ ተገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የሳተላይት ልማት የተለያዩ ደረጃዎች አሉት። እነዚህም የተልዕኮ ትንተና፣ የቅድመ ንድፍ ሥራ፣ ጥልቅ የዲዛይን ትንተና እና የሳተላይት ግብዓቶችን በዲዛይን መሠረት የመገጣጠም ናቸው።
ሳተላይት ከመገጣጠም ሥራ በኋላ የመፈተሽ ሥራም በሳተላይት ልማት ሂደት እንደሚካተት ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ የፍተሻ ሥራ ሲካሄድ የምትለማዋ ሳተላይት በኅዋ ከባቢ ውስጥ ከፍተኛ ሙቀትም ቅዝቃዜም ሊያጋጥማት ስለሚችል ይህን መቋቋም እንደምትችል አስቀድሞ ፍተሻ እንደሚካሄድም አስረድተዋል።
ከእነዚህ ሂደቶች በኋላ ሳተላይቷ ወደ ማምጠቂያ ጣቢያ ተጓጉዛ እንድትመጥቅ እንደሚደረግና ከዚህ አንፃር ተቋሙ የመጀመሪያውን ሂደት ማለትም የተልዕኮ ትንተና ሂደትን ማጠናቀቁን ገልፀዋል። ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች ቻይና ሄደው ከኩባንያው ጋር የተልዕኮ ትንተና ሥራዎችን ማጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል።
ሳተላይቷን የመገጣጠምና የመፈተሽ ሥራ በአጠቃላይ ሦስት ወራትን እንደሚፈጅም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች አብረው እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል። ከስምምነቱ ጀምሮ ሳተላይቷን አልምቶ ለማምጠቅ አስራ ስምንት ወራት እንደሚፈጅ ነገር ግን የማምጠቂያ ቀን ገደቡ ሊለያይ እንደሚችልም አያይዘው ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል ወደ ሕዋ ከመጠቁት ሁለት ሳተላይቶች የአሁኗ ከፍተኛ የምስል ጥራት ያላቸው መረጃዎችን መላክ የምትችል መሆኑንም የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የምስል ጥራቱ ከፍተኛ በሆነ መጠን ግልጋሎት ላይ የሚውልባቸው ዘርፎችም በዚሁ መጠን እየበዙ እንደሚመጡ አመልክተዋል።
የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች በዋናነት ተግባራቸው በመሬት ዙሪያ እየዞሩ ምስል በማንሳት ወደ መሬት መላክ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ የምስል መረጃ ደግሞ እየተተነተነ የግብርና፣ ደን፣ ውሃ፣ የተፈጥሮ አደጋዎችንና ሌሎች ሥራዎችን ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንደሚውል ገልፀዋል። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ የምታመጥቃት የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖራት ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይትም ወደ ኅዋ ለማምጠቅ እየሠራች መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ የአዋጭነት ጥናት ተጠናቆ የፋይናንስ ምንጮችን የማፈላለግ ሥራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ኅዋ የምታመጥቃት ሳተላይት ለአምስት ዓመታት እንደምትቆይና ሳተላይቷን ወደ ኅዋ ማምጠቅ የተፈለገው ቀደም ሲል በ2012 ዓ.ም እና በ2013 ዓ.ም ወደኅዋ የመጠቁት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች የአገልግሎት ጊዜያቸውን መጨረሳቸውን ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም