ወደ አልማዝ ኮረብታዎች

ኑሮ ምን መልክ አለው ካሉ፤ ሸጋም ቢሆን መልከ ጥፉ መዥጎርጎሩ አይቀርም። የሕይወት መልኳን ፍለጋ ተራራው አናት ላይ የወጡም፤ ተንሸራቶ ከመውደቅ ቡድኑ፣ ማጅራትን ብሎ ቁልቁል ወደመጡበት ከሚሸኘው ከሞት ጡጫ አያመልጡም። ደግሞ አንዳንዶችም አሉ፤ በሕይወት ኮረብታዎች ላይ ለከፍታም ለዝቅታም የቅርብ ሆነው የሚኖሩ። ከፍታን ታየ ዝቅታ ራሳቸውን ሆነው ከመኖር ወደኋላ አይሉም። ከመጣ ከሄደው ጋር ዋዥቀው፣ ከከፋው ላይ ከፍተው ከደግነት፣ ከፍቅርና ከመልካምነት አይጎድሉም። እንዲህ ዓይነቶቹ፤ ከምንወዳቸው በላይ ወደን፣ ከምናደንቃቸው በላይ እንድናደንቃቸው ይጋብዙናል። እነርሱም ልክ እንደ አልማዝ ያሉ እንቁዎች ናቸው።

በተለይ ቀርበው ለአፍታ እንኳ የተመለከቱት ዓይኖቿ የእናትነትን የብርሃን ጸዳል በልብ ላይ ያሳርፋሉ። በአካል የሚያውቋትም የማያውቋትም ሁሉም “ማሚ” ብለው የሚጠሯት ሲሏት ስለሰሙ ብቻ አይደለም። እርሷም፤ ይህንንም ያንንም “ልጄ… ልጆቼ” ማለትን የምታዘወትረው ለምታውቀውም ለማታውቀውም ጭምር ነው። የኢትዮጵያ እናቶች መልክና ማንነት ሁሉ ተሰብስቦ የተሰጣት ትመስላለች። እጅግ ሲበዛ ሆደ ቡቡ ናት። የእናትነት ርህራሄዋ መጠን የለውም። ምንም ለራሷ የሚሆን ሳይኖራት ስለሌላው ከመጨነቅ አልፋ፣ አንድ ጎርሳ ሁለተኛውን ለማጉረስ እጅ የምትዘረጋ የእናትነት ልክ ናት። በትወናው ዓለም ያሉ፣ የተወኑትን ሕይወት ከካሜራ በስተጀርባ ሲኖሩት ከተመለትን፤ በእርግጥም አንደኛዋ አርቲስት አልማዝ ኃይሌ ናት። ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች “ማሚ” ብለው ስሟን ጠርተው አይጠግቡም። በተለይ በተለምዶ የ90ዎቹ፤ የማስታወቂያና ሌሎች ሥራዎቿንም፣ ዛሬ ላይ በየማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ የጊዜ ትዝታዎቻቸውን የሚኮመኩሙባቸው ሲሆኑ እንመለከታለን።

ውልደትና እድገቷ በቀድሞው የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ነው። መስከረም 1 ቀን 1938 ዓ.ም፤ ከአባቷ አቶ ኃይሌ ኡርጋ እና ከእናቷ ወይዘሮ የሺ ሰይፉ ተወለደች። የአሰበ ተፈሪ አድባር መርቆ ማንነቷን ያለመለመው በደግነትና ኩሩ ኢትዮጵያዊነት ነው። በዚያው የትውልድ ቀዬዋ ደግሞ ወደ ተማሪ ቤት አቀናች። በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ውስጥ ከተማሪው መሀል ቁጭ ብላ ስትቆጥር የነበረው ፊደላትን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ንጽሁ ኢትዮጵያዊነትንም ጭምር ነበር። ልጅነቷ የሰጣት ዕውቀትን ብቻ ሳይሆን የተከሸነ ማንነትንም ጭምር ነው። እስከመጨረሻው ድረስ ለእልፎች የእናትነት ጥግ መስላ ስትታይበት የነበረውን ማንነት የተጎናጸፈችው ገና ያኔ ከልጅነቷ ነበር።

በልጅነት ውስጥ ብዙ አልፋ፣ ወጣትነቷንም ይዛ አዲስ አበባ ስትገባ በአጋጣሚ ነበር። በወቅቱ ሐረር ከተማ ላይ ትዳር መሥርታ አንድ ልጅም ነበራት። በ1958 ዓ.ም አንድ ልጇን ይዛ አዲስ አበባ በመጣችበት አጋጣሚ የተመለከተችው የብሔራዊ ቲያትር የውድድርና ቅጥር ማስታወቂያ ነበር፤ ሌላኛዋን አልማዝን ወልዶ በጥበብ መታቀፊያ የተቀበላት። ማስታወቂያ አንብባ ለውድድር የገባችው አልማዝ እዚያው ሳትወጣ ቀረች። ታህሳስ 8 ቀን 1958 ዓ.ም ነበር፤ በብሔራዊ ቲያትር ለመቀጠር የቻለችው። በዚህ የጥበብ ቤት ውስጥ ለ35 ዓመታት ስትቆይ፣ ያልሆነችውና ያልሠራችው፣ ያልገባችበትና ያልዳሰሰችው ነገር የለም። ሁለገብነቷ በሙያዋ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ጋር ባላት ግንኙነትና ድንቅ ስብዕናዋም ጭምር ነው።

በብሔራዊ ቲያትር መድረክ ላይ ከታየችባቸው ነገሮች አንደኛው በውዝዋዜ ነው። በተለይ አብዛኛውን ጊዜ ለብሳ በምንመለከታት የሓበሻ ቀሚስ አምራና ተውባ ስትውረገረግ መንፈስን የምታድስ ነበረች። ወጋ ነቀል እያደረገች ከሁሉም የባኅል ውዝዋዜ ጋር እርሷን መመልከት የሚናፍቅም ጭምር ነበር። ሰውነቷ ለውዝዋዜ፣ ድምጽዋም ለመስረቅረቅ የተሰጠ ነበርና በድምጻዊነት የሠራችባቸው ዓመታትም ቀላል አይደሉም። በእነዚህ ችሎታዎቿ ላይ ብዙዎች የምናውቅላት ትወና ታክሎበት፣ ለቲያትር ቤቱ እስትንፋስ ነበረች። ከመድረክ በስተጀርባ ደግሞ ልክ እንደቤቱ እማወራ ስትንጎዳጎድ ማየት የሁሌም ነው። ሙያን አድሏታልና በሜካፕ አርቲስትነት ፉንጋውን ስታቆነጅ፣ ቆንጆውንም መልከጥፉ አድርጋ መሥራቱን ትችለበታለች። የገጸ ባህሪያቱን አካላዊ ገጽታ ለማምጣት እጆቿ የተለዩ ናቸው። የተቀደዱትን ሰፍታ፣ አልባሳቱን በወግ በቄንጥ አሰናድታ፣ መድረኩን በቀለማት እያስጌጠች፣ ምን አለ፤ ምንስ የለም…እያለች ልክ እንደቤቷ የምትጨነቅ እንደነበረች አብረዋት የሠሩ ሁሉ ይመሠክሩላታል።

ሁለገብነቷ በሁሉም ነገሮች ውስጥ መሆኑን ስንመለከት እንገረምባታለን። በደግነትና መልካም ስብዕናዋ ውስጥ የትኛዎቹ ቀሯት የምትባል ነች። በኪነ ጥበብ ሙያዋ ስታገለግል የማትደርስበት፣ ደርሳም በእጆቿ የማትነካካቸውና የማትዳስሳቸው ነገሮች የሉም። ለቲያትር መድረኮች ከትወና አንስቶ እስከ ጥቃቅን ጉዳዮች ድረስ ወርዳ በኃላፊነት የተሰጣት ያህል ሁሉንም ስትከውን ትታያለች። በፊልም የቴሌቪዥን ድራማዎች ውስጥም ገጸ ባህሪያቱን ከመጫወት ባለፈ፣ ለማድረግ የምትችላቸውን ምንም ዓይነት ነገሮችን ተመልክታ አታልፍም። በምትሠራቸው የማስታወቂያ ሥራዎቿ ከማስታወቂያነት ያለፈ እውነት መኖሩም ሆነ ያለ እንዲመስለን ማድረጓ የተለየች ያደርጋታል። ኪነ ጥበባዊና ሙያዊ ከሆኑ ነገሮቿ ውጪም እንዲሁ ሁለገብ ናት። በማኅበራዊ ሕይወቷ ከትልቅ ትንሹ፣ ከልጅና አዋቂው ጋር ሁሉ ያላት መስተጋብር በፍቅርና በክብር፣ በእናትነትና ኢትዮጵያዊነት የታጀበ ነው። ውስጧ ብቻ ሳይሆን አንደበቷም ሕብር በሆነ በኢትዮጵያዊነት ነው። አማርኛን ጨምሮ ኦሮሚኛና ሶማሊኛ ቋንቋዎችንም ትናገራለች። ከውጭ ደግሞ እንግሊዝኛና አረብኛ ቋንቋዎችንም አንደበቷ ይናገራል።

አልማዝ ኃይሌና የጉማ ቲያትር፣ በ1991 ዓ.ም የሚያዚያና የግንቦት ወራት ሰኔና ሰኞ የገጠሙበት ይመስላሉ። በሁለቱ ተከታታይ ወራት፣ ሁለት ከባድ የሕይወት መድፎች ልቧ ላይ አርፈዋል። በዚያን ሰሞን በብሔራዊ ቲያትር ቤት ውስጥ “ጉማ” የተሰኘ ቲያትር የሚታይበት ነበር። ቲያትሩ አልማዝ በተዋናይነት የምትሳተፍበት ነበርና በልምምድና በእይታ ጊዜ መድረኮች ባተሌ የነበረችበት ነው። ለሕዝብ ከሚቀርብባቸው ቀናት አንዱ በደረሰበት ወቅት ግን፤ ሚያዚያ 30/1991ዓ.ም በሀዘን ልቧን የሰበረውን መርዶ ሰማች። መርዶው ለአልማዝ ብቻ ሳይሆን ለጉማ ቲያትር አባላትም ጭምር ነበር። የእናትነትን ልብና ማንነት ያወረሷትን እናቷን አትጣ ቲያትሩን ትቀጥላለች ብሎ ማሰብ ለሁሉም ዘበት ነበር። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሲገጥሟት ከነበሩ ነገሮች ሁሉ ሙያዋን ስታስቀድም ለኖረችው አልማዝም፤ ከየትኛውም በላይ የተፈተነችበት ሆነ። በቲያትር ቤቱ ፈቃድና በብዙዎች ግፊት የእናቷን ሀዘን አውጥታ እንድትመጣ ቢደረግም፤ የምትወደው ሙያና የምታከብረው ሕዝብ በልጦ ታያት። የማይቻለውን ችላና ሀዘኗን በሆዷ ዋጥ አድርጋ፣ ቲያትሩን እየጠበቀ ላለው ታዳሚ ለማሳየት ወሰነች። ከውስጣዊ ስሜቷ ጋር እየታገለች የመድረክ ትወናዋን በብቃት ከወነችው። እንስፍስፍነቷንና የደረሰባትን ሀዘን ለሚያውቅ፣ አግራሞትን የሚያጭር ከመሆኑም፤ ምን ያህል ለሙያዋ ሟችና በምንም የማትደራደርበት መሆኑን የሚያሳይ ነበር። ትልቅ ብቃት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ማንነት፣ ሩህሩህ ብቻ ሳይሆን ቆራጥ ልብ እንዳላትም የሚያሳይ ነበር።

መጥፎው ታሪክ ግን ገና ወር ሳይሞላ ራሱን ደገመ። አሁንም “ጉማ” የተሰኘውን ቲያትር ለሕዝብ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ናቸው። ግንቦት 23 ቀን 1991 ዓ.ም ግን ሁለተኛው ዱብዳ ወረደ። በእናቷ ሀዘን የተሰበረው ልቧ ሳይሽር ሌላኛው ደገማት። በእናት ፍቅር ተንከባክባ የምታሳድገውን የልጅ ልጇን በሞት ተነጠቀች። አልማዝ ልቧ በሀዘን ሙሽሽ! እንዳለም፤ በሦስተኛው ዕለት ግንቦት 25 ቀን መድረክ ላይ ለመውጣት ወደ ቲያትር ቤቱ መጣች። እንደምን ያለውና መቻልና ልዩ ስብዕናን ሰጣት…ለብዙዎች ከአድናቆት ያለፈ ትንግርት ነበር።

ለዚህ ሙያዊ ገድሏ የብሔራዊ ቲያትር ቤትም የአልማዝን ታላቅነት የሚያጎላ የምስጋና ደብዳቤ ጽፎላታል። ሰኔ 22 ቀን 1991 ዓ.ም ከብሔራዊ ቲያትር ለአልማዝ የተጻፈው ደብዳቤም ቀጣዩን ይመስላል… “ሚያዝያ 30 ቀን 1991 ዓ.ም “ጉማ” የተሰኘው ቴአትር ለሕዝብ በሚቀርብበት ጊዜ የእናትዎን ማረፍ ሰምተው ትርኢቱ ከሚስተጓጎል ሀዘኔን በውስጤ ችዬ ቴአትሩን እሰራለሁ ብለው በመወሰን አንዳችም ነገር ሳይጓደል በብቃት እንደተወጡት፣ ከዚህም በተጨማሪ በእንክብካቤ ያሳድጉት የነበረው የልጅዎት ልጅ በሕጻንነት እድሜው ከዚህ ዓለም በሞት በተለየ በሶስተኛው ቀን ግንቦት 25 ቀን 1991 ዓ.ም “ጉማ” ቴአትር ለሕዝብ በሚቀርብበት ጊዜ ከመራር ሀዘንዎት ላይ ተነስተው ቴአትሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ማድረግዎን ከጉማ ቴአትር ዋና አዘጋጅ ሰኔ 14 ቀን 1991 ዓ.ም ሪፖርት ተደርጓል። በመሆኑም በሁለቱም ቀናቶች የእናትዎንና የልጅ ልጅዎን ሀዘን በመቻል ያከናወኑት ተግባር አርአያነቱ እጅግ የላቀ በመሆኑ የተሰማንን አድናቆትና ምስጋና እየገለጽን ቸሩ አምላክ ለእርስዎና ለቤተሰብዎ መጽናናትን እንዲሰጣችሁ ከልብ እንመኛለን።”

አልማዝ ኃይሌ ለብሔራዊ ቲያትር የተለየ ቦታ እንዳላት ሁሉ፣ ቲያትር ቤቱም ለርሷ ያለው አክብሮትና አድናቆትም እንዲሁ ነው። ይህን ያመጣላት አንጋፋነቷ ብቻም አይደለም። በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆና፣ ከሕመሟ ጋር እየታገለች እንኳን ቤቱን ለማቅናት ደከመኝ ሰለቸኝ አትልም። ቅዳሜ፣ የበዓል፣ የእረፍት ቀናት ብሎ ነገር አታውቅም። በዚያ ላይ ሰዓት አክባሪነቷ፤ የሓበሻ ቀጠሮን የማታውቅ፣ በጊዜ ደረስኩ ያለውን ቀድማው የምትገኝ ነበረች። በጡረታ ብትገለል እንኳ የቤቱ ጠረን ካለችበት ያወዳታል። የብሔራዊ ቲያትር ቤትን ደጅ ሳትረግጥ ውላ አታድርም። ለዚያ ቲያትር ቤት የእውነትም እናት ነበረች። ሁሉም “ማሚ” በሚሏት ስም ውስጥ አንዳችም የውሸት ድምጸት የለበትም። ለርሷ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት የሚገልጹበት ነው።

የ65ኛ ዓመት የልደት በዓሉን በብሔራዊ ቲያትር በደመቀ ሁኔታ ተከብሮላት ነበር። በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በነበራት ቆይታ ላይ “ሰዎች እንወድሻለን እናከብርሻለን ይላሉ። እኔ ደግሞ ምን ሠርቼ እላለሁ። ምክንያቱም ሙያውን ያዝኩኝ እንጂ ያን ያህል ሠርቻለሁ ብዬ አላስብም” ስትል ለጋዜጠኛው ትመልስለታለች። ከአልማዝ ላይ የሚነበበው ትህትና ብቻ ሳይሆን፤ የምትመኘው ከሠራችው በላይ ስለነበረም ነው። በሙያዋ በሀገር ውስጥና በተለያዩ ዓለማት እየዞረች፣ ጥበብን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ከፍ ብታደርግም ገና የጠገበችና የረካች አትመስልም ነበር።

በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሠራችባቸው 40 ዓመታት፤ ብዙዎች ከምናውቀው በላይ ለፍታበታለች። እጅግ ፈታኝ በሆኑ የሕይወት ውጣውረዶች ውስጥ ሆና ሙያዋን መርጣ አስቀድማለች። አብዛኛዎቻችን ልናደርገው በማንችልበት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆና እንኳን ከሙያዋ የሚበልጥባት እንደሌለ ያሳየችባቸው ነገሮች በቂ ናቸው። አንዲት ማስታወቂያ አንብባ ለድፍን 42 ዓመታት የከረመችው አልማዝ፤ በ40 ብር የወር ደሞዝ ተቀጥራ በ150 ብር ጡረታ ወጣች።

በጡረታ ተገላ 150 ብሯን ይዛ ከቤቷ እንደገባች፣ በዚያው ሰሞን የአልማዝን ኮረብታዎች ማለምለም የጀመረ የሚመስል የተስፋ ዝናብ ማካፋት ጀመረ። ዝነኛ የሚያደርጋትን መንገድ የከፈተውን “ሳራ” የተሰኘውን የመጀመሪያ ፊልሟን ሠራች። ከዚህ በኋላ ግን ልምላሜው የእውነትም መሰለ። ከፊልሞች ባሻገር፤ የቴሌቪዥን ድራማዎችና ማስታወቂያዎችም ወዳለችበት ኮረብታ ተከታትለው መምጣት ቀጠሉ።

አልማዝ ኃይሌ፣ ማሚ የሁሉ እናት፣ የጥንት የጠዋትዋ የጥበብ ፈርጥ ስንት እንደ ወርቅ አብረቅርቃ ስታበቃ፣ ከውዝወዜ እስከ ቲያትር መድረኮች ደማምቃ ስታከትም፣ በማስታወቂያ፣ በድራማና በፊልም ክብር፣ ፍቅርና ዝና ሸማምታ በስተመጨረሻ፤ መንደሯ ውስጥ ባለ የጉልት ገበያ ውስጥ ተቀምጣ ጎመንና ካሮት ስትቸረችር ስንመለከት ምንድነው የሚሰማን? ለፊልም አሊያም ለድራም ቀረጻ ካልሆነ በስተቀር፤ እርሷን በእውን እንዲህ ሆና መመልከት እንዴት? ዓይን ቢመለከት ልብ እንዴት እሺ ብሎ ያምናል…እርግጥ ነው በመሥራት ውስጥ ክብር እንጂ ነውር የለውም። ግን እንደ አልማዝ በከፍታው ለነበረ፣ እንደ አልማዝ ዕድሜው ለገፋ፣ በአንድ ወቅት የሆቴል ባለቤት ለነበረች…ከኮረብታነት ያለፈ የድንጋይ ተራራ ነው። እርሷን እንደ እናት መልክ ስንል፤ የአብዛኛዎቹን የኢትዮጵያ እናቶችን ስቃይና ችግር በማየቷም ነው።

በስተመጨረሻ ዕጣፈንታዋ ኮረብታው ላይ ጉሊት ተቀምጣ መቸርቸር ቢሆንም፤ ደግነቷ ግን ጥሎ አልጣላትም። ባታጠባም እናትነቷ ልጅ አልባ አላደረጋትም። ሁኔታዋን ተመልክተው ያዘኑ ብዙዎች ነበሩ። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ “ማሚ” የሚሏት ሁሉ ለሽንገላ አለመሆኑን ያሳየ ተግባር በደግነት ተገለጠ። ሁሉም የቻለውን ተረባርቦ ደረሰላት። አለንልሽ እያለ፤ እጆቿን ይዞ ቀና አደረጋት።

የአልማዝ የሕይወት ኮረብታዎች አስቸጋሪና ፈተና የበዛባቸው ነበሩ። አንድም በሕመም ለብዙ ጊዜያት ተሰቃይታለች። በዚህም በዚያም ብላ በሕክምና ስትታገል ብትቆይም ለማለፍ ያልተቻላት ዕለት ግን መጣ። መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም አረፈች። በወራትና በቀናት ጥግግት፣ እንዲሁም በወራቱ ድግግሞሽ ውስጥ ተመሳሳይ የሆነ የክስተት ድግግሞሽ ቢኖርም፤ እንደ አልማዝ ይከብዳል። ከዚህም በተለየ ደግሞ፤ ውልደትና ሞቷም በአንዷ መስከረም ላይ ነው። መስከረም 1 ቀን ከእናቷ ማህፀን ወጥታ፣ በመስከረም 16 ቀን ከቅድስት ሥላሴ ካቴደራል አፈር ገባች። በምሥራቅ የወጣች ፀሐይ፣ በምዕራብ መጥለቋ ግን መቼም የማይሻር የተፈጥሮ ሕግ ነው።

አልማዝ ከመሞቷ ሁለት ወራት ቀደም ብሎ፤ ከኮሜዲያን እሸቱ ጋር ቆይታ አድርጋም ነበር። አብሯት የሠራ በመሆኑም ማንነቷን በደንብ ያውቅ ነበርና በርካታ ጉዳዮቿንም አንስተዋል። በዝግጅቱ መሃል እንዲህ ስትል እናደምጣታለን፤ “ከመሞቴ በፊት የምለምናችሁ፤ እባካችሁ! እባካችሁ ልጆቼ! የሀገር ፍቅርና የቤተሰብ ፍቅር ይኖራችሁ። የናንተን ሠላምና የናንተን አንድነት አይቼ ልሙት…እባካችሁ! እርስ በርስ አትጫረሱ…እባካችሁን ተዋደዱ!…” እያለች ሲቃና ሳግ ተናንቋት፣ ከዓይኖቿ የእንባ ዥረት እያወረደች ነበር ምርር! ባለ ለቅሶ መማጸኗ። እርሷ እንዲህ ናት፤ ማስመሰልና አድር ባይነት የለባትም። ለመወደድ ብላ የምታደርገው፣ ለክብሯ ስትል የምተወው ምንም ነገር የለም። “ማሚ” በሚሏት ስም ውስጥ እናትነቷ ለወለደቻቸው አራት ልጆቿ ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገሯ ልጆች በሙሉ መሆኑን ሁሌም በንግግሮቿ ውስጥ ይንጸባረቃል። ከሞቷ በኋላ ኮሜዲያን እሸቱ ስለ እናትነትና ደግነቷ ባወሳበት ንግግር ውስጥ “ገና ጀማሪ ተቃጣሪ ነበርኩና ደሞዝህ ትንሽ ነው አይበቃህም፤ እያለች ከምሳ እቃዋ ታጎርሰኝ ነበር” ይላል። አልማዝ ማለት፤ በጎበዝ ሰዓሊ ተመስላ የተሳለች፣ የመላው ኢትዮጵያ እናቶችን መልክ የያዘች ምስል ናት። ፈጣሪ ለሰውነት ማሳያ አድርጎ የፈጠራትም ጭምር ነበረች።

በዚያው ቃለመጠይቅ ላይ፤ ደግሞ እንዲህም ስትል ተናገረች “ከሞትኩ በኋላ ሰው አበባ ቢደረድርልኝ ዋጋ የለውም። ችጋር እየጋጠህ በስምህ ብቻ አርቲስት… አልሚ እንደዚህ ነበረች…እሷ እኮ እንዲህ…ያናድደኛል!” በእርግጥም የአበባው ልምላሜ በሕይወት ነው። በቁም ቁም ነገር አበቦች ቀርቶ ኮረብታዎቹም ይለመልማሉ።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You