ጨዋታ ቀያሪው አሊ ኤክስፕረስ

ነገር በሶስት ይጸናል እንዲሉ፤ ትናንት የተከበረውን የዓለም የሸማቾች ቀን በማስመልከት ሶስተኛውንና የመጨረሻውን ከሸማቾች ጋር የተገናኘውን መጣጥፍ ይዤ መጥቻለሁ። ለዛውም በሀገራችን የችርቻሮ ንግድ ፈር ቀዳጅና ጨዋታ ቀያሪ ስለሆነው አሊ ኤክስፕረስ። የውጭ ምንዛሬ በገበያ መወሰኑና የችርቻሮ ንግዱ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መደረጉ ይዞት የመጣ ትሩፋት አካል ነው ማለት ይቻላል። አሊ ኤክስፕረስ በቅርቡ በብር ክፍያ መቀበል እንደሚጀምር አስታወቀ። ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ተቋም የሆነው አሊ ኤክስፕረስ እንደገለፀው ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የበርካታ ሀገራትን ገንዘብ ጥቅም ላይ ያውላል። ከእነዚህ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፤ ግብፅ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል።

የክፍያ መፈፀሚያ ገንዘቦችን ማስፋፋት ያስፈለገው ለአፍሪካ ተጠቃሚዎች በስፋት ተደራሽ ለመሆን በማሰብ እንደሆነ የጠቀሰው አሊ ኤክስፕረስ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የክሬዲት ካርዶችና የውጭ_ምንዛሬ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለማስቀረት እንደሆነ አስረድቷል። የአፍሪካ ሀገራትን ገንዘብ በግብይቱ ውስጥ ጥቅም ላይ ማዋሉ በዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርአት የተነሳ ለአፍሪካዊያን ትልቅ ማነቆ የሆነውን ችግር ለመቅረፍ ማቀዱንም አስታውቋል። በዚህም አዳዲስ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን እንደሚያገኝ ተስፋ ሰንቋል። ለዚህ እንዲረዳው በተጠቀሱት አገራት ከሚገኙ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ጥምረት መፍጠሩን ገልጿል።

የአሊባባ ግሩፕ (AliExpress) በኢትዮጵያ የኢኮሜርስ ገበያ ለመጀመር የሚያስችል ሥራ መጀመሩን በዚያ ሰሞን ይፋ ማድረጉ አይረሳም። የቻይናው አሊባባ ግሩፕ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማህበር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን እንቅስቃሴ ነው የጀመረው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ይሽሩን አለማየሁ የአሊባባን አሊ ኤክስፕረስ በኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩ ዓለም አቀፋዊ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባቱን ብቻ ሳይሆን ለዲጂታል ፈጠራ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተሰሩ ሥራዎችን ማሳያ ነው ብለዋል። ይህ ጅማሮ ለአሊ ኤክስፕረስ አዲስ ምዕራፍ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን ሸማቾች እና ነጋዴዎች በአዲሱ የዓለም ገበያ ምርትና አገልግሎትን ለመገበያየት እና ኢትዮጵያን ወደ ዓለማቀፍ ንግድ ማስገባት ያስቻለ ነው ብለዋል።

አሊባባ የሚያቀርባቸውን ዲጂታል መሳሪያዎች እና መድረኮችን በመጠቀም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ተዋናይ ለመሆን ያላትን አቅም እና ዝግጁነት ማሳየት እንደሚገባም ተገልጿል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢኮሜርስ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አያሌው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሊባባ ግሩፕ በኢትዮጵያ የሚጀምረውን የኢኮሜርስ ሥራ ለማሳለጥ የሚያስችል የኢኮሜርስ ሎጂስቲክስ አገልግሎትን የሚሰጥ ሀብ ዝግጁ ማድረጉን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን የኢኮሜርስ ሎጂስቲክስ አገልግሎትን የሚሰጥ ሀብ ማዘጋጀቱ አሊባባ ግሩፕ በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር እንዲችል ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተነስቷል።

በዚያ ሰሞን በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በተካሄደው የ አሊ ኤክስፕረስ የኢትዮጵያ ገበያ ለመጀመር የሚፈጀው ይፋ ማድረግያ ዝግጅት ላይ የድርጅቱን ፕላትፎርም ያስተዋወቁት በአፍሪካ ገበያ የአሊ ኤክስፕረስ ቢዝነስ ዳይሬክተር ጄፍሪ ጂያንግ አሊ ኤክስፕረስ በኢኮሜርስ ያለውን ዓለምአቀፍ ልምድ በመጠቀም የኢትዮጵያውያን ሸማቾችን እና የንግድ ቦታዎችን በአንድ ቁልፍ ስትራቴጂያዊ እንቅስቃሴ በማስተሳሰር እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማህበር ፕሬዚዳንት ፍቅር አንዳርጋቸው ማህበሩ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እንቅስቃሴ ውጤታማነት ለማገዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን ገልጸው እንደ አሊባባ ያሉ የኢኮሜርስ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ገበያ መቀላቀላቸው የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና

እንደሚኖረውም ተናግረዋል። ማህበሩ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት ቻይና በሚገኘው የአሊባባ ግሩፕ በመገኘት ልምድ በመቅስም ይህ የግንኙነት መስመር እንዲጀመር የድርሻውን መወጣቱ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢሼሎን ግሩፕ ከአሊ ኤክስፕረስ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ገበያ ሊሰሩ ነው። ኩባንያዎቹ ለዚሁ ሥራ አንዲሆን በአዲስ አበባ ጌቱ ኮሜርሻል ህንጻ ላይ ምርት ማሳያ ቦታ ከፍተዋል። ኢሼሎን ግሩፕ የኢትዮጵያዊያን እና ካናዳዊያን ድርጅት ሲሆን በኢኮሜርስ፣ መጋዘን፣ ሎጅስቲክስ፣ ግብርና እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ የሚሠራ ኩባንያ ነው። ኢሼሎን ግሩፕ ከአሊ ኤክስፕረስ በፈጠሩት ጥምረት በኢትዮጵያ የኦንላይን ግብይት የበለጠ ተደራሽ፣ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ ማድረግ ያስችላቸዋል። በዚህ አጋርነት፣ ኢሼሎን ግሩፕ በኢትዮጵያ ያለውን ልምድና ስም በመጠቀም የሀገሪቱን የኢ-ኮሜርስ እድገትን ለማፋጠን ይሠራል። የሁለቱ ኩባንያዎች ትብብር አዲስ አበባ ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበትና ደንበኞችም በአካል ሄደው የሚያዩት የምርት ማሳያ ክፍል ማቋቋምን ያካትታል ተብሏል።

ይህም ደንበኞችን፤ ምርቶችን መፈተሽ እና በቦታው ላይ ድጋፍ የሚያገኙበት አዲስ ሁኔታን ስለሚፈጥር በባህላዊ እና የዲጂታል ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት ያጠባል ተብሎ ተነግሮለታል። ኢሼሎን ግሩፕ ከአሊ ኤክስፕረስ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያን ገበያ ሥራ መጀመራቸው ከውጪ ሀገር እቃ የሚያስመጡ ነጋዴዎች ውጪ ሀገር መጓዝ ሳይጠበቅባቸው በኦንላይን የሚያዙትን እቃ አዲስ አበባ በተከፈተው ማሳያ ቦታ አይተው ትዕዛዝ መስጠት ያስችላቸዋል። የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት

ሙያውን በጠበቀ፣ በታማኝነት እና በብቃት ለማበርታት ቁርጠኛ ነን። ከአሊ ኤክስፕረስ ጋር ያለን አጋርነት ከዚህ ራዕይ ጋር የተጣጣመ ነው፣ ለኢትዮጵያዊያን ሥራ ፈጣሪዎች ብዙ እድሎችን እና ለተጠቃሚዎች የበለጠ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል”ሲሉ የኢሼሎን ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚካኤል ማሞ ተናግረዋል። ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደል ብሂሉስ። ስለአሊባባ ግሩፕ መስራች ጃክ ማ ትንሽ ልላችሁ ወደድሁ።

ለመሆኑ ጃክ ማን ነው ? ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ በebs ቴሌቪዥን የTeckTalk አዘጋጅ ” ግርምተ ሳይቴክ ” በተሰኘው ድንቅ መፅሐፉ ” ዓለምን የቀየሩ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን 20 ምርጦች ” በሚል ንዑስ ርዕስ እንዲህ ያስነብበናል።” … ‘ አሊ ባባ ‘ የተሰኘው ግዙፍ የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ከድሀ ቤተሰብ በመስከረም 1964 ዓ ም ተወለደ ። በትውልድ ስሙ ማን ዩን በፕሮፌሽናል የስም አጠራሩ ጃክ ማ በመባል ይታወቃል። በበርካታ የሕይወት ፈተና ያለፈው ጃክ ማ እንኳን ግዙፍ የሆነ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለቤት እንደሚሆን ሊያስብ ቀርቶ በሒሳብ ትምህርት ደካማ እንዲሁም እስከጉልምስናው ኮምፒዩተር ባለበት ድርሽ ብሎ አያውቅም። በወጣትነቱ በቱሪስት አስጎብኝነት ተሰማርቶ የነበረው ጃክ ማ በሕይወቱ በርካታ ውድቀቶችን አስተናግዷል።

የኮሌጅ መግቢያ ፈተናን ሶስት ጊዜ ወድቆ በአራተኛው ነበር የተሳካለት። ኮሌጅ ገብቶ የተማረውም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ነበር። ከጨረሰ በኋላ ለ30 የተለያዩ መስሪያ ቤቶች አመልክቶ ሳይሳካለት ቀረ። በአንድ “KFC” በሚባል ምግብን በርካሽ የሚሸጥ ምግብ ቤት በአነስተኛ ደመወዝ ለመቀጠር ከ24 ሥራ ፈላጊዎች ጋር አመልክቶ ሁሉም ሲቀጠሩ እሱ ብቻ ሳይሳካለት ቀረ። ለፖሊስነት ለመቀጠር ተወዳድሮም ወድቋል። “ተስፋ መቁረጥ ትልቅ ውድቀት ነው።” የሚለው ጃክ በዚህ ሁሉ ፈተና እና ውድቀት ቢያልፍም እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ከብዙ ልፋትና ውጣ ውረድ በኋላ ተሳክቶለት በወር 12 ዶላር እየተከፈለው በእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርነት ተቀጠረ።

በዚህ ከባድ ፈተና በማለፍ ላይ ሳለነው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1994 ዓ.ም ስለኢንተርኔት የሰማው። ከአንድ ዓመት በኋላ በተፈጠረለት መልካም አጋጣሚ ወደ አሜሪካ አቀና። በዚያም ስለኢንተርኔት አጠቃቀም መሰረታዊ ግንዛቤ እንዳገኘ ስለሀገሩ ቻይና ለማወቅ ጉጉት አድሮበት መረጃ ሲያስስ እንደሌሎች ሀገራት የደለበ መረጃ ማግኘት አለመቻሉ ቁጭት ፈጠረበት። በዚህ በመነሳሳት ከጓደኛው ጋር ስለ እናት ሀገሩ የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጥ ድረ ገፅ ፈጠረ።

በጥቂት ሰዓታት የአብረን እንሥራ ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው ጎረፉለት። በዚህ ጊዜ ነበር ጃክ የኢንተርኔትን ኃይል የተረዳው። ከባለቤቱ እና ከጓደኛው ጋር 20ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወረት በማሰባሰብ በሚያዚያ 1995 ዓ ም ” ቻይና የሎ ፔጅን / chaina yellow page ” አቋቋመ ። በሶስት ዓመቱ 800ሺህ ዶላር አተረፈ። 1999 ዓ ም ከ18 የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የዛሬውን ” አሊ ባባ ” መሰረተ ። በጥቂት ወራት ውስጥም ከባለሀብቶች 25 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አሰባሰበ ። በ2005 ዓ ም ያሁ /ya­hoo / አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ ከአሊባባ የ40 በመቶ ድርሻን ገዛ ። ነጮች የተቀረው ታሪክ ነው ቢሉም የጃክ ጉዳይ ከታሪክ በላይ ስለሆነ እንቀጥል ።

በ2006 ዓ.ም አሊ ባባ በታዋቂው የኒዮርክ የአክሲዎን ሽያጭ / New York Stock Exchange / ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ሲቀርብ ነጮች Initial Public Offering / IPO / ይሉታል ። 25 ቢሊዮን ዶላር የተተመነለትን ሽርክና በመሰብሰብ ከአንጋፋ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተርታ ተሰለፈ ። በ2008 ዓ.ም የ463 ቢሊዮን ዶላር ግብይት አከናወነ ። የቅርብ ጊዜ ተመኑም ከግማሽ ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገመታል ። ዛሬ ተአምረኛው ጃክ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሀብት ባለፀጋ ነው።

በዓለማችን በቁጥር አንድነት በሚታወቀው የአሜሪካው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለመከታተል 10 ጊዜ አመልክቶ ውድቅ እንዳልተደረገበት በኋላ ላይ በክብር ጥሪ ተደርጎለት የክብር ተናጋሪ ለመሆን በቅቷል ። ታዋቂውና ተነባቢው የTIME መፅሔት በ2009 ዓ ም ከዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አንዱ አድርጎ መርጦታል። “ስለአላደርግህልኝ ነገር አመሰግናለሁ ” የሚለውን የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወግ ማስታወስ የዚህ ጊዜ ነው።ስለአሊባባ መስራች ይሄን ያህል ካወጋን ለዛሬ ይበቃናል።ይሁንና የመጣጥፉ ዘፍጥረት የሸማች ጉዳይ ነውና በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ሀሳብ እንለዋወጥ። ሀሳቡን ያቀበለኝ የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስቴር ነውና እነሆ ምስጋናዬ ይድረሰው።

ሸማች ማለት ማን እንደሆነ ያውቃሉ? “ሸማች” ማለት ለማምረት ሥራ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን ዋጋውን ራሱ ወይም ሌላ ሰው የሚከፍልለት ሆኖ ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው ነው። በሕግ አወጣጥ “ሰው” የሚለው ቃል የተፈጥሮ ሰው እና በሕግ የሰውነት ሥልጣን የተሠጠው አካልን አጠቃሎ የሚይዝ ቃል ነው። በሀገራችን ሕግ መሠረት ሸማች ተደርጎ የሚቆጠረው የተፈጥሮ ሰው ብቻ ነው። በዚህ ትርጉም መሠረት ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ጨምሮ በሕግ የሰውነት ሥልጣን የተሠጣቸው ተቋማት በሙሉ በአዋጅ ቁጥር 813 መሠረት በዚህ ሕግ ፊት እንደ ሸማች አይቆጠሩም ማለት ነው።

በመሆኑም ፡-

  • በሕግ የሰውነት ሥልጣን የተሠጣቸው ተቋማት፣
  • ለማምረት ሥራ ወይም መልሶ ለመሸጥ የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው፣ እንዲሁም
  • የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎትን ያለ ክፍያ በነፃ የተቀበለ ሰው ሸማች ተደርጎ አይቆጠርም።

 

የሸማች መብቶች፦በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 መሠረት ማንኛውም ሸማች የሚከተሉት መብቶች አሉት፦

  1. ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራትና ዓይነት በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት (14.1)፣
  2. ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት (14/2)፣
  3. የዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ ያለመገደድ (14/3)፣
  4. በማንኛውም ነጋዴ በትህትናና በአክብሮት የመስተናገድ እና በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራት እና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ (14/4)፣
  5. የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በመግዛቱ ወይም በመጠቀሙ ምክንያት ለደረሰበት ጉዳት የንግድ ዕቃዎቹን ወይም አገልግሎቶቹን ከማቅረብ ጋር ተያይዞ በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ ሻጭነት፣ በችርቻሮ ሻጭነት ወይም በሌላ በማንኛውም ሁኔታ በአቅርቦቱ የተሳተፉ ሰዎችን በተናጠል ወይም በአንድነት ካሳ እንዲከፍሉት ወይም ከዚህ ጋር ተያያዥ መብቶችን የመጠየቅ (14/5)፣
  6. ስለ ንግድ ዕቃው የተሠጡ የበለጠ የሚጠቅሙ ዋስትናዎች ወይም የሕግ ወይም የውል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፡-

 

6.1. የገዛው የንግድ ዕቃ ጉድለት ያለበት እንደሆነ ዕቃውን ከገዛበት ቀን ጀምሮ በአስራ አምስት (15) ቀን ውስጥ የንግድ ዕቃው እንዲለወጥለት ወይም ዋጋው እንዲመለስለት (20/2/ሐ)፣

6.2. የገዛው አገልግሎት ጉድለት ያለበት ከሆነ አገልግሎቱን ከገዛበት ቀን ጀምሮ በአስራ አምስት (15) ቀን ውስጥ አገልግሎቱ በድጋሚ ያለክፍያ እንዲሠጠው ወይም የአገልግሎት ክፍያው እንዲመለስለት ሻጩን የመጠየቅ (20/2/ለ)፣

6.3. ሸማቹ ጉድለት ያለበትን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመጠቀሙ ወይም ሻጩ ከላይ በተራ ቁጥር 6 የተገለፁትን ሁለት ነጥቦች በተመለከተ የቀረበለትን ጥያቄ ባለማሟላቱ ለደረሰበት ጉዳት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ካሳ እንዲከፈለው መጠየቅ መብት አለው።

  1. ለገዛው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ደረሰኝ የማግኘት መብት አለው (17/1)።

 

የነጋዴ ግዴታዎች፦

  1. የንግድ ዕቃዎቹንና የአገልግሎቶቹን ታክስና ሌሎች ሕጋዊ ክፍያዎችን ያካተተ የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ በግልፅ በሚታይ ቦታ የማመልከት ወይም በንግድ ዕቃዎቹ ላይ መለጠፍ (አንቀፅ 15)፤
  2. በሚሸጣቸው የንግድ ዕቃዎች ላይ መግለጫ የመለጠፍ ወይም በተለየ ወረቀት ላይ ጽፎ ለሸማቹ መስጠት (አንቀፅ 16)፤
  3. መግለጫው የዕቃውን ስም፣ የተሠራበትን ሀገር፣ ክብደቱን፣ ብዛቱን፣ ጥራቱን፣ ይዘቱን፣ አጠቃቀሙን፣ የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜ …ወዘተ ያካትታል፤ (አንቀፅ 16/2 ሀ-ኀ)

 

ለነጋዴ የተከለከሉ ድርጊቶች (አንቀጽ 22)፦

  • የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ስላላቸው ጥራት ወይም መጠን ወይም ብዛት ወይም ተቀባይነት ወይም ምንጭ ወይም ባህርይ ወይም ውሁድ ወይም ጥቅም የተሳሳተ መረጃ መስጠት (22/1)፤
  • የንግድ ዕቃዎች ስለአዲስነታቸው ወይም ስለሞዴላቸው ወይም አገልግሎታቸው የቀነሰ ወይም የተለወጡ ወይም እንደገና የተሠሩ ወይም በአምራቹ እንዲሰበሰቡ የተባሉ ወይም ያገለገሉ ስለመሆናቸው በትክክል አለመግለጽ (22/2)፤
  • የሌላውን ነጋዴ የንግድ ዕቃዎች በአሳሳች ሁኔታ መግለፅ (22/3)፤
  • የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን በማስታወቂያ እንደተነገረላቸው አለመሸጥ ወይም ማስታወቂያው የመጠን ውሱንነት መኖሩን ካልገለፀ በስተቀር ሸማቾች በሚፈልጉት መጠን ልክ አለመሸጥ (22/4)፤
  • ስለዋጋ ቅናሽ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መረጃ ማስተላለፍ (22/5)
  • የሸማቹን መብት የሚጠብቅ ባልሆነ ምክንያት የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን አልሸጥም ማለት (22/12)፤
  • የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በንግድ መደብሩ ውስጥ ከተለጠፈው ዋጋ አስበልጦ መሸጥ (22/14)፤
  • ከሽያጭ ጋር በተያያዘ የተገባ የዋስትና ግዴታን አለመወጣት (22/7)፤
  • የንግድ ዕቃ የሚያስፈልገው ጥገና ወይም የሚተኩ ክፍሎች እንደማያስፈልጉት አድርጎ ማቅረብ (22/8)
  • የንግድ ዕቃዎች የተሠሩበትን ሀገር አሳስቶ መግለጽ (22/15)፤
  • በሸማቾች መካከል ተገቢ ያልሆነ አድልዎ መፈጸም (22/16)፤
  • ማንኛውንም አገልግሎት የመስጠት ሥራን በንግድ ሥራው ከሚታወቀው ደረጃ በታች ወይም ባልተሟላ ሁኔታ መስጠት (922/9)፤
  • በግብይት ወቅት ማንኛውንም የማጭበርበር ወይም የማደናገር ተግባር መፈፀም (22/11)፤
  • ደረጃ የሚያስፈልጋቸውን የንግድ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ያለደረጃ ማህተም ለሽያጭ ማቅረብ (22/13)፤
  • አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ለመሸጥ ሸማቹ ያልፈለገውን ሌላ የንግድ ዕቃ አብሮ እንዲገዛ ማስገደድ (22/17)፤
  • ሕገ ወጥ በሆነ ማንኛውም የመለኪያ መሣሪያ መጠቀም (22/18)፤
  • ለሰው ጤናና ደህንነት አደገኛ የሆነ፣ ምንጩ ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃው የወረደ፣ ወይም የተመረዘ፣ አገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ ወይም ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቁ የንግድ ዕቃዎችን ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ (22/10)፤
  • አንድ ሸማች አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመግዛቱ ወይም የገንዘብ መዋጮ በማድረጉ እና በሸማቹ አሻሻጭነት ከእሱ ቀጥሎ ሌሎች ሸማቾች የንግድ ዕቃውን ወይም አገልግሎቱን የሚገዙ ወይም የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ከሆነ ወይም በሽያጭ ስልቱ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ በሸማቾቹ ቁጥር ልክ ተጨማሪ የገንዘብ ወይም የዓይነት ጥቅም እንደሚያገኝ የሚገልጽ ፒራሚዳዊ የሽያጭ ስልት ተግባራዊ ማድረግ(22/6)፤
  • ከላይ ከተጠቀሱት መብቶች ውስጥ ያልተከበረ ካለ ግብይቱን በፈጸሙበት አካባቢ ለሚገኝ ንግድ ቢሮ ወይም ለፖሊስ በማቅረብ በሕግ ምላሽ እንዲሰጥዎ ያድርጉ።
  • በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ በተፈጸመ ግብይት በሸማቹ ላይ ለደረሰ ጉዳት የካሳ ጥያቄ በፍትህ ሚኒስቴር የንግድ ውድድና የሸማቾች ጥበቃ ዳኝነት ችሎት ማቅረብ ይቻላል።

 

ሸማቾች በግብይት ወቅት ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች እና መውሰድ ያለባቸው እርምጃዎች፦

የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ከመግዛትዎ በፊት፣ በሚገዙበት ወቅት እና ከገዙ በኋላ ማድረግ የሚገባዎት ጥንቃቄ

ከመግዛትዎ በፊት

  • ስለሚገዙት እቃ ወይም አገልግሎት በቂና ትክክለኛ መረጃ ያላቸውን መሆኑን ማረጋገጥ፣
  • በተጋነኑ ማስታወቂያዎች ተገፋፍቶ ለውሳኔ ያለመቸኮል፤
  • ተጨማሪ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣
  • በማንኛውም ሁኔታ የሚገለጹ የዋጋ ቅናሽ ማስታወቂያዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ፤
  • በንግድ ቤቶች ስለ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚለጠፉ የዋጋ ዝርዝሮች ታክስ እና ሌሎች ሕጋዊ ክፍዎችን ያካተተ ያላካተተ መሆኑን ማረጋገጥ፤

 

በሚገዙበት ወቅት

  • ከክፍያ በፊት የገዙት የንግድ ዕቃ የዋስትና ወረቀት እና ውል ካለ የውሉን ኮፒ /የርስዎን ድርሻ/ መቀበልዎን፣
  • በመጨረሻም ተገቢውን ክፍያ በመፈጸም ደረሰኞችን ወይም መግለጫዎችን ወይም ሌሎች ማስረጃዎችን መቀበልዎን አይዘንጉ።

 

ከገዙ በኋላ

  • ስለፈጸሙት ግዢ የሚያስረዱ ደረሰኞችን ወይም መግለጫዎችን ወይም ሌሎች ማስረጃዎችን በአግባቡ ማስቀመጥ፣
  • የንግድ ዕቃው ወይም የአገልግሎት አጠቃቀም ማንዋል፣ የጥገናና ሌሎች የዋስትና ሰነዶችን በጥንቃቄ ማስቀመጥ፣
  • የገዙት የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጉድለት ያገኙበት እንደሆነ ግዢ ከፈጸሙበት ቀን ጀምሮ በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ የንግድ ዕቃውን ወደገዙበት የንግድ ድርጅት ወይም ነጋዴ ጋር በመሄድ የንግድ ዕቃው አገልግሎት እንዲለወጥ ወይም ዋጋውን እንዲመለስ መጠየቅ፣

 

ሻሎም። አሜን።

 

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You