የቁርአን ውድድርና የኢፍጣር መርሐ ግብሮች አብሮነትን ያጎለብታሉ

አዲስ አበባ፤ ሀገር አቀፍ የቁርአን ውድድርና የኢፍጣር መርሐ ግብሮች አብሮነትንና አንድነትን የሚያጎለብቱ መሆናቸውን ተገለጸ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ሀገር አቀፍ የቁርአን ውድድርና የኢፍጣር መርሐ ግብሮች አስመልክተው እንደተናገሩት፤ የቁርአን ውድድርና የኢፍጣር መርሐ ግብሮች አብሮነትን የሚያጎለብቱ እና የጋራ እሴትን ከፍ የሚያደርጉ ናቸው።

ቁርአን የእውቀት እና የሰላም ምንጭ እንደመሆኑ ውድድሩ አብሮነትን፤ አንድነትና፤ መከባበርንና ሰላምን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸው፤ በተጨማሪም ውድድሩ ቁርአን የትውልድ የሕይወት መርሕና መመሪያ እንዲሆንና በክብር ከፍ በማድረግ ትውልድን ለማነጽ ብሎም እምነቱንና ማንነቱን በተገቢው መንገድ ለመግለጽ የሚያስችል ይሆናል ብለዋል።

ውድድር በክልል ደረጃ ሲካሄድ እንደቆየ አውስተው፤ በሁለቱም ፆታዎች ሦስት ሦስት ተወዳዳሪዎች ለመጨረሻው ዙር ውድድር መቅረባቸው ተናግረዋል።

ለውድድሩአሸናፊዎችም እንደየደረጃቸው አንድ የኤሌክትሪክ መኪና፣ 500 ሺህ፤ 300 ሺህ ብር እና የሐጂ ጉዞ ተሸላሚዎች እንደሚሆኑ ጠቁመው፤ በእለቱ ከውድድሩ በተጨማሪም አምስተኛው የታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ፕሮግራም እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

የኢፍጣር መርሐ ግብሩም የጋራ ሀገራዊ እሴትን ከፍ ለማድረግ አብሮነትና አንድነትን ማፅናትን ዓላማው ያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ሁለቱም ፕሮግራሞች በሚካሄዱበት ወቅት ሕዝበ ሙስሊሙ በተቀመጠው ዓላማ መሠረት ተሳታፊ እንዲሆን አስገንዝበዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ፀጥታ ለማስከበር እንደሚሠራ ጠቁመው፤ ከዝግጅቱ ውጪ የሆኑ አላስፈለጊ ክስተቶች እንዳይፈጠሩና ዝግጅቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሕዝበ ሙስሊሙ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት እንዲንቀሳቀስና ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

“ቁርአን የእውቀት እና የሰላም ምንጭ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው ሀገር አቀፍ የቁርአን ውድድርና የኢፍጣር መርሐ ግብሮችም ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You