ሕፃናትን ከበይነ መረብ ጥቃት የመከላከል ጅምር

በዓለም ላይ ኢንተርኔት ከሚጠቀሙ ሦስት ሰዎች አንዱ ሕፃን መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። የዚህ ጥናት አካል የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያም ከአራት ሕፃናት አንዱ ኢንተርኔት እንደሚጠቀም ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

እነዚህ ሕፃናት ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 17 እንደሆነና አብዛኞቹ በከተሞች የሚኖሩ መሆናቸውንም በመረጃው ተመላክቷል። ከእነዚህ ሕፃናት ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በይነመረብን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው እንደማያውቁ ተጠቁሟል። 80 በመቶ የሚሆኑት ወላጆችና አሳዳጊዎችም በተመሳሳይ ደኅንነቱ በተጠበቀ የሕፃናት በይነመረብ አጠቃቀም ዙሪያ መረጃ እንደሌላቸው ጥናቱ ይጠቁማል።

ዓለም አቀፉን ደኅንነቱ የተጠበቀ የኢንተርኔት ቀንን በማስመልከት ደኅንነቱ የተጠበቀ የበይነ መረብ አጠቃቀም ለታዳጊዎች በሚል መሪ ቃል ሕፃናትን ከበይነ መረብ ጥቃት ለመከላከል ያለመ ሰነድ ዝግጅትን በይፋ የማስጀመር መርሐ ግብር ተከናውኗል።

በመርሐ ግብሩ ላይ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይሮ ሂክማ ኸይረዲን እንደገለፁት፤ ሕፃናትን ከጥቃት ለመጠበቅ መሠረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ደኅንነቱ የተጠበቀ የበይነመረብ አጠቃቀም ከባቢን መፍጠር ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የታዳጊ ሕፃናት የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ ዘመኑን የሚመጥን ትውልድ ለማብቃት ትልቅ ትኩረት የሰጠችበት ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ሀገራዊ ዓላማ እውን እንዲሆን ታዳጊ ሕፃናት ደኅንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በአወንታዊ መልኩና በእውቀት ላይ የተመሠረተ አጠቃቀም ማስረፅ መቻል እንዳለበት ገልፀዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢ ሕፃናት መብት ተጠብቆ ጤናማ ስብዕና የተሟላ ዜጋ መፍጠርን የመጀመሪያ ርምጃ ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም የሕፃናት ጥበቃ ሥርዓትን ማጎልበት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና በመዘርጋት ሁሉን አቀፍ የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

ሕፃናት በይነ መረብ በሚጠቀሙበት ወቅት ተገቢነት የሌላቸውን ይዘቶች ከመጠቀም አንስቶ ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ እስከመሆን እንደሚደርሱ ገልፀው፤ እነዚህ ችግሮች በትምህርት አቀባበላቸውና በሥነልቦናቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አስረድተዋል።

ዓለም አቀፉን ደኅንነቱ የተጠበቀ የበይነ መረብ አጠቃቀም ቀን ሲከበርም የሁሉንም አካላት ርብርብ ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑን ገልጸዋል። በቅንጅትና በትብብር አዎንታዊና ዘርፈ ብዙ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን መቀነስ ብሎም ማጥፋት የሁላችንም ተግባርና ኃላፊነት መሆኑን አውቀን ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

የቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት አቶ ለማ አስፋው በበኩላቸው ደኅንነቱ የተጠበቀ የሕፃናት የበይነመረብ አጠቃቀም የሁሉንም ድርሻ ወደ አንድ ማምጣትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ ቅንጅት ማምጣት ከልተቻለም የበይነመረብ አጠቃቀም የሚመጣውን ጉዳት ለመቅረፍ እንደሚያስችልም አስረድተዋል።

በይነ መረብን በአግባቡ በመጠቀም በሕፃናት ላይ እያስከተለ ያለውን የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ፣ አላስፈላጊ ይዘት፣ ሥነልቦናዊ ጫና፣ ማኅበራዊ ግንኙነት ላይ ተፅዕኖና ለጥቃት ተጋላጭ መሆን መከላከል እንደሚቻል ገልፀዋል።

ቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ሰባት ሁለተኛ ደረጃና ሠላሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን በበይነ መረብ አጠቃቀም ግንዛቤ ላይ የሚሠራ ፕሮጀክት እንደነበረው ጠቁመዋል። ፕሮጀክቱ ከተማሪዎች ባሻገር የመምህራንን አቅም በተለያዩ ሥልጠናዎች ማጎልበትን እንደሚያካትት አስታውሰዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ በበይነ መረብ አማካኝነት በሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዴት መከላከል ይኖርብናል የሚል ውይይት ተደርጓል። ውይይቱ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከሕፃናት ፓርላማ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት እንዲሁም ከሌሎች የመንግሥት ተቋማትና አጋር ድርጅቶች በተውጣጡ አካላት ተሳትፈውበታል።

በሕፃናት ላይ የሚደርሰውን የበይነ መረብ ጥቃት ሰነድም ይፋ ተደርጎ ከክልል የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ተወካዮች ጋር ርክክብ ተደርጓል ።

ነፃነት ዓለሙ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You