
የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ተጀምሮ ባለፉት ዘጠኝ ቀናት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሆሳዕና ከተማ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የ2017 የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል፤ ዛሬ በአቢዮ ኤርሳሞ ሁለገብ ስታዲየም ይጠናቀቃል።
ከቀትር በኋላ በሚኖረው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት በርካታ መርሐ ግብሮች የሚካሄዱ ሲሆን፤ የተለያዩ የፍፃሜ ውድድሮችም ይጠበቃሉ።
ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በተለያዩ ፉክክሮች በርካታ የፍጻሜ ውድድሮች በሁለቱም ፆታዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። በዚህም መሠረት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የቤት ውስጥ የፍጻሜ ውድድሮች አሸናፊዎቹን ለመለየት ተችሏል። ባለ 12 እና ባለ 18 ጉርጓድ ገበጣ በሁለቱም ፆታዎች ፍፃሜ ሲያገኝ፣ በባለ 12 ጉድጓድ የገበጣ ጨዋታ በወንዶች፤ አማራ ክልል፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ከ1ኛ-3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አሸናፊዎች ሆነዋል። በሴቶች ደግሞ፤ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አማራ እና ኦሮሚያ ባለድል ናቸው።
በሌላኛው ምድብ፤ ባለ 18 ጉርጓድ ገበጣ በወንዶች አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ከ1-3 ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በሴቶች የፍጻሜ ውድድር፤ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አማራ እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አሸናፊዎች ሲሆኑ፤ በሁለቱም ምድብና ፆታዎች እንደየደረጃቸው የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
በአቢዮ ኤርሳሞ ሁለገብ ስታዲየም ብርቱ ፉክክር በታየበት በሌላኛው የፍጻሜ ውድድር፤ በሁለቱም ፆታና በተለያዩ ምድቦች የተደረገው የትግል ስፖርት ውድድር ፍፃሜ አግኝቷል። በሁለት ምድቦች በተካሄደው በወንዶች ፍጻሜ ከ48-52 ኪሎ ግራም፤ አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ እና አማራ ያሸነፉ ሲሆኑ፤ ከ68-72 ኪሎግራም በነበረው ፉክክር ደግሞ፤ አማራ፣ ኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ከ1-3 ባለው ደረጃ አጠናቀዋል። በአራት ምድቦች ሲካሄድ የቆየው የሴቶች የትግል ውድድርም በዚሁ ዕለት ፍጻሜውን አግኝቷል።
በቀስት የፍጻሜ ውድድር በወንዶች አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት አሸናፊዎች ሆነዋል። በሴቶች ደግሞ ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ እና ደቡብ ኢትዮጵያ የሜዳሊያ ደረጃውን ይዘው አጠናቀዋል።
ትናንት ረፋድ ላይ በተደረገው የወንዶች የገና ጨዋታ የግማሽ ፍጻሜ ውድድር፣ ኦሮሚያ አዲስ አበባን 2ለ1 የረታ ሲሆን፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ አማራ ክልልን 3ለ2 ማሸነፍ ችሏል። በዚህም መሠረት ዛሬ በፍፃሜው ጨዋታ ኦሮሚያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሲጫወቱ አማራና አዲስ አበባ ለደረጃ ይፋለማሉ።
በሁለቱ ቀናት ውስጥ በርካታ የፍጻሜ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን፤ የፈረስ ጉግስና ሸርጥ፣ ድብልቅ ቀስት፣ ቡብ እና ሻህ የባሕል ስፖርቶችን ጨምሮ ደማቅ በሆኑ የፍጻሜ ውድድሮች ተጠናቋል።
ለአዲስ ዘመን አስተያየት የሰጡት ኢንስትራክተር ተስፋዬ ወልደ ሚካኤል፤ ውድድሩ ደማቅና አስደሳች በሆነ የባሕል ውድድርና ፌስቲቫል መንፈስ ፍጻሜው ላይ መድረሱን ተናግረዋል። “በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ካሳተፏቸው ተወዳዳሪዎች አንጻር ዘንድሮ በቁጥር የላቀ ነበር። ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ እየተመለከትነው ያለው ስፖርታዊ ጨዋነትም ለውጦቹን በተግባር ያሳየ ነው” በማለት፤ በዛሬው የፍጻሜ ውድድሮችና መርሐ ግብሮች ውስጥም፤ እስካሁን ከታየው የበለጠ ኢትዮጵያዊ ፍቅር፣ አንድነትና ስፖርታዊ ወንድማማችነቶች የምናይ ይሆናል የሚል ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ውድድርና ፌስቲቫሉ መክፈቻውን ካደረገበት ዕለት አንስቶ፣ ከዋነኛ መርሐ ግብሮች ጎን ለጎን፣ ልዩ ልዩ ባሕላዊ ትርዒቶች በስታዲየምና በጎዳናዎች ላይ ሲካሄዱ ቆይተዋል። እነኚሁ ደማቅ ዝግጅቶችም ከሰሞኑ በተለይ ከሦስት ቀናት ወዲህ፤ አመሻሹን እየተካሄዱ ያሉ የጎዳና ላይ የባሕል ትርዒቶች የከተማዋን ድባብ የለወጡ ሆነዋል። በዚሁ ትርዒት አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ፣ ለሁሉም ክልሎች የባሕል ትርዒቶቻቸውን የሚያቀርቡበትን የየራሳቸው ቀናት የተመደቡላቸው ሲሆን፤ ሁሉም ባማረ መልኩ አጠናቀዋል። ዛሬ ከመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ በኋላም፤ በተመሳሳይ መልኩ ሁሉም በአንድነት ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዛሬው ዕለት በአቢዮ ኤርሳሞ የመታሰቢያ ስታዲየም በሚካሄደው የመዝጊያ መርሐ ግብሮች አንድ የፍጻሜ ውድድር አንዱ በጉጉት የሚጠበቀው የወንዶች የትግል ስፖርት ሲሆን፣ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ይሆናል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም