
አዲስ አበባ፡- የገዳ ሥርዓት ለመርሳቤት ካዎንት ሕዝብም ባሕሉ እንደሆነና 72ኛውን ባሊ የተረከቡት አባ ገዳ ጉዮ ቦሩ ለእኛም አባ ገዳ ናቸው ሲሉ የኬንያ መርሳቤት ካዎንት ልዑካን ቡድን አስታወቁ።
ባለፈው ሳምንት በቦረና ዞን የባሊ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት በተካሄደበት ወቅት በቦታው የተገኙት የኬንያ መርሳቤት ካዎንቲ ልዑካን ቡድን አባላት እንደገለጹት፤ የገዳ ሥርዓት ለመርሳቤት ካዎንት ሕዝብም ባሕሉ ነው። 72ኛውን ባሊ የተረከቡት አባ ገዳ ጉዮ ቦሩ ለእኛም አባ ገዳ ናቸው።
መርሳቤት ካዎንት አስተዳደር እና ልዑካን ቡድን መርተው የመጡ መሐመድ ዓሊ እንዳሉት፤ እኛ ከቦረና ወንድሞቻቸን ጋር የድንበር እንጂ የባሕል ልዩነት የለንም። ባለፉት ሥርዓቶች በድንበር አካባቢ በሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት ባሕላችንን ማክበር አልቻልንም፣ ዛሬ ግን በተፈጠረልን ምቹ ሁኔታ በ72ኛውን የቦረና ባሊ ርክክብ ላይ በመሳተፋችን ተደስተናል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ዊሊያም ሩቶ አስተዳደር ዘመን ባሕላችንን ለማክበር ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረውልናል ሲሉም ተናግረዋል።
ግንኙነታችን በባሕል ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ጉዳዮችም ነው ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፤ በሁለቱም ሀገሮች መካከል ያለው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን፤ ለመገናኘታችን ምክንያት የሆነውን ባሕላችንን ማጠናከር ይኖርብናል ብለዋል።
አቶ መሐመድ ገልግሎ በበኩላቸው መርሳቤት ካዎንት ከኬንያ ሕንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ ተነስተው ረጅም ኪሎ ሜትር ተጉዘው ያለምንም ችግር በ72ኛውን የቦረና ባሊ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት መታደም መቻላቸውን ገልጸዋል።
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ ያረጋቸው በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያለው እሴት መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ማጣጣም የተቻለው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ዊሊያም ሩቶ ዘመን በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ በመሆኑ ሁለቱንም መንግሥታት አመስግነዋል።
ከመርሳቤት፣ ሞምባሳ፣ ኢስዮሎ፣ ታናናሪቫ እና ናይሮቢ ከተለያዩ ኦሮሚያ ክልል እና አጎራባች ክልል ሕዝቦች ጭምር የርክክብ ሥነ-ሥርዓቱን ለመታደም የመጡትንም ጭምር አንድነት በማጠናከር የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
የአካባቢው ሰላም መጠናከር በሁለቱም ሀገሮች መካከል ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠሩም ባሻገር ከዓባይ ግድብ የሚገኙ ትሩፋቶችን ወደ ኬንያ ለማድረስ መደላድል የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል፡
አቶ ጀማል አብዱ በበኩላቸው ‹‹ኬንያ ሁኜ ስለ ቦረና የሰማሁት እና በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝቼ ያየሁት የተለያየ ነው፤ ከጠበኩት በላይ ፍጹም ሰላማዊ የባሊ ሽግግር በማየቴ ተሰደስቻለሁ፤ የገዳ ሥርዓት እንደተባለውም ሰላም መሆኑን አረጋግጫለሁ፤ ባሕሉ የሁላችንንም አንድነትና ሰላም ስለሚያጠናከር ተባብረን ልንከባከበው ይገባል፤ በክልሉ መንግሥት እየተሠራ ያለው የባሕል ተሐድሶ በክልሉ ብቻ ሳይሆን ድንበርንም ተሻግሮ የተረሳነውን ባሕላችንን እንድናስታውስ አድርጎናል፤ ወደ ኬንያ ስመለስ ለቀጣዩ ባሊ ርክክብ እንዲዘጋጁ ያየሁትን እገልጽላቸዋለሁ›› ብለዋል።
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም