አንድ አገር እንደ አገር እንዲቀጥል ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል ሰላም ግንባር ቀደሙን ሚና ይጫወታል። ሰላም ካለ ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መብላት፣ ተምሮ መለወጥ በአጠቃላይ ያሰቡትን ሁሉ ማሳካቱ ብዙ ከባድ አይሆንም። ነገር ግን ሰላም በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ከተናጋ ይህ ሁሉ ነገር እንዳልነበር ከመሆኑም በላይ አገርም ህልውናዋን ጠብቃ ልትቀጥል የምትችልበት ሁኔታ በጣም ጠባብ ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዚያም እየታየና እየተሰማ ያለው ነገር እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ የኖረ የቀደመ የመተሳሳብና አብሮ የመኖር እንዲሁም የመደማመጥ ባህላችንን ያጠፋ፤ እንደ አገርና ህዝብ ወደኋላ እየጎተተን ያለ ስለመሆኑም እየታየ ነው።
ከዚህ ችግር እንድንወጣ “በአንድ ልብ አሳቢ፣ ባንድ ቃል ተናጋሪ” ልንሆን እንደሚገባም ብዙዎች እየመከሩ ይገኛሉ፤ እኛም ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ከፓስተር ጻዲቁ አብዶ ጋር በወቅታዊ የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ዙሪያ ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ እንደ አንድ ሃላፊነት የሚሰማው የሀገር ሽማግሌ ወቅታዊውን አገራዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ፓስተር ጻዲቁ፦ አሁን ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ብሎም አደገኛ ነው። ለምሳሌ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለተኛ ዜና 15 “በዛን ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረም ፤ ከተማ ከከተማ ህዝብም ከህዝብ ጋር ይዋጋል፤ “ ይላል። ይህ የተባለው ደግሞ ህዝብ ከአምላኩ የራቀበት ዘመን ስለነበር ነው። ሆኖም ፊታቸውን ወደአምላካቸው ሲመልሱ ደግሞ ቁጣው መዓቱ በረድ ብሎ በሰላም መኖር እንደቻሉም ይነግረናል። ይህ እንግዲህ አሁን እኛ መካከል ያለውን ነገር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ፤ ከዚህ መንገድም መውጣት በጣም ያስፈልገናል።
እኛ አላገናዘብነው እንደሆን እንጃ እንጂ አሁን እኛ የጀመርነው አካሄድ ሌሎች አገሮችን ያጠፋ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ ህዝቦችን ለስደትና ችግር የዳረገ ነው።
በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን በውስጣችን ብዙ ብሔር ብሔረሰብ ያለን ብዙ ህዝቦች ነን ፤ ስለዚህ ይህንን የመጣብንን ቁጣ ለማብረድ በመጀመሪያ ወደ ፈጣሪ መመለስ፤ ሁለተኛ አንዳችን ለሌላችን ስጋትም፣ ጥፋትም ህመምም ከመሆን መቆጠብ፤ ከዛ ይልቅም ሌላውን የምንፈውስ መድሃኒት ሆነን ማሳየት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለው ግድያና መፈናቀል እንደ አገር ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ እስከምን ድረስ ነው ይላሉ?
ፓስተር ጻዲቁ ፦ አሁን ያለው አዝማሚያ በጣም አደገኛ ነው፤ ወዳልሆነ መንገድም እያመራ ነው ። እነ የመን ሶሪያና ሌሎችም ወዳልሆነ ጥፋት የገቡት ሲጀመር እንደዚህ አድርጓቸው ነበር። በመሆኑም ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ እንዳይሆንብን ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄን ማድረግ ያስፈልጋል።
ብልህ ካልሆንን አስተዋይ ሆነን ነገን በማሰብ ዛሬ ላይ ሰከን ማለት ካልቻልን እንደ አገርና ህዝብ መቀጠላችን አጠያያቂ ነው ። በመሆኑም አገር እንደ አገር እንድትቀጥል፣ ህዝብም እንዳይጠፋ የአገር ሽማግሌዎችን። የሀይማኖት አባቶችን። የኡስታዞችን። የአባገዳዎችን። የሱልጣኖችን ምክር መስማት ትልቁ መፍትሄ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ከዚህ አንጻር በየአካባቢው ያሉ የአገር ሽማግሌዎች ምን ዓይነት ሚናን መወጣት አለባቸው?
ፓስተር ጻዲቁ ፦ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ተሰሚነት እንዲያጡ ለበርካታ ዓመታት ብዙ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ የዛን የስራ ውጤት እያየን ያለን ይመስለኛል። አንዳንድ ጊዜ አባቶቹም ይህንን ብዬ ወይም መክሬ ዘክሬ ልጆቼን ለመመለስ ብፈልግ እንኳን ተሳዳቢው ብዙ በመሆኑ “በዚህ እድሜዬ ለምን እሰደባለሁ” በማለት ችግሮችን አይቶ እንዳላየ ወይ ለፈጣሪያቸው አቤት እያሉ የሚቀመጡበት ሁኔታ ነው ያለው።
እኔ ደግሞ በግሌ እያልኩ ያለሁት እንደ አባት ልጆቻችን የልጅ ልጆቻችን እየኖሩባት ወደፊትም የሚኖሩባት አገር በሰላምና በፍቅር መኖር ሲችሉ ይህ ሊሆን አይገባውም። ምናልባት በእኛ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በኩል የጎደለ ወይም የጠፋ ጥፋት ካለ ነጻ መውጣት አለብን፤ አለበለዚያ ግን ይህ መሆን የለበትም በማለት ያለምንም አድሎ ለሁሉም እኩል በሆነና ለማንም በማይወግን አኳኋን ድርጊቱ አይገባም ማለት መቻል አለብን እላለሁ።
እኛ እድሜያችንም ሀይማኖታችንም እኩይ ተግባርን እያየን እንዳላየን እንድናልፍ ስለማይፈቅድልን በመካከል ቆመን ትክክል ያልሆነ ነገር ሲታይ አይ ይሄ እንደዚህ አይደለም፤ መሆን የለበትም እያልን ማስተማር ጥላቻን በቀልን ምሬትን አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርገው ማንኛውም ዓይነት የግፍ ስራ በኋላ ሁላችንንም ዋጋ ስለሚያስከፍለን ይህ ሁኔታ በፍጹም መሆን የለበትም በማለት መናገር በዚህ ንግግር የሚመጣ ችግር ካለም እንደ አባት ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል።
ነገር ግን “አይ እኔ በዚህ እድሜዬ ለምን ሰዎች ይናገሩኛል “ የሚል ስሜት ውስጥ መግባት አያስፈልግም። አሁን ያለንበት ወይም እያደረግን ያለነው ነገር እንደ አባት የማይጠበቅ ከመሆኑም በላይ ለማንም የሚበጅ አይደለም። ምናልባትም እንደ አገር እኛን የሚያዋርደን ትንሽ የሚያደርገንም ስለሆነ እግዚአብሔርን ከመለመን ጀምሮ አስፈላጊውን ነገር በቃልም በተግባርም ከመናገርና ከማድረግ መቆጠብ የለብንም።
አዲስ ዘመን ፦ በዚህ ዘመን የጠፋውን የአገር ሽማግሌዎች ተደማጭነት ለመመለስ ከማን ምን ይጠበቃል?
ፓስተር ጻዲቁ ፦ በነገራችን ላይ የሀይማኖት አባቶችን ሙሉ በሙሉ የሚሰማ የለም ለማለት አያስደፍርም፤ ነገር ግን አንድን ነገር ለማስተማር ወይም ከዚህ ተግባር እራቁ ለማለት በሚሞከርበት ጊዜ “እርሳቸውማ የመንግስት ደጋፊ ናቸው” ብሎ የመፈረጅ ሁኔታ በሰፊው ይስተዋላል። እዚህ ላይ ችግሩ የሚመስለኝ ከዛሬ ስንት ዓመት በፊት የቀደሙት መንግስታት ያጠፉትን ጥፋት እነሱ ሲመከሩ አልሰማም ብለው የቀጠሉበትን ችግር አሁን ላይ መድገም ከሆነ ይህ በጣም አስቸጋሪ ነው።
የአገር ሽማግሌዎችም ይሁኑ የሀይማኖት አባቶች ሌላው ቢቀር እድሜያቸው ብቻ ብዙ ያሳያቸውና ያስተማራቸው ነገር ስላለ እነሱን መስማቱ ይጠቅም ይሆናል አንጂ አይጎዳም። በተቃራኒው ግን እነሱን አለመስማት በተለይም አሁን ላይ እየታየ ላለው ችግር አጋልጦናልና ። ይህ ፍጹም ሊሆን የማይገባው ወደፊትም የምናፍርበት የምንጸጸትበት ነው።
አንዳንድ ጊዜ እኮ ሰዎች ራሳቸውን በጥላቻ ሲሞሉ የበቀል ስሜት በውስጣቸው ሲያድር የሚፈልጉት ነገር የተሳካ ሳይመስላቸው ሲቀር ከሰው አይደለም ከፈጣሪያቸውም ለመጣላት ይሞክራሉ፤ እንዲያውም ይጣላሉ። እዚይ ላይ አንድ ምሳሌ ባነሳልሽ “ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ነብይ አለ፣ ለመራገም ሲሄድ የሚቀመጥባት አህያ ከሩቁ መልአክ አየች፤ ወዲያውም ተኛች ሰውየው ደግሞ እንድታደርሰው በመፈለግ ይደበድባታል። ነገር ግን አልነሳም አለች ፤ እንዲያውም አንደበት አውጥታ ለምን ትመታኛለህ? አለችው ፤ ሰውየው ግን አልተዋትም በኋላም አህያዋ ከዚህ ቀደም አንተ ለመራገም በሄድክበት ሁሉ በሰላም አድርሼህ የለም ወይ? እንደዚህ አድርጌ አውቃለሁ ወይ? ብላ ጠየቀችው፤ አሁን ግን እኔንም አንተንም አደጋ ውስጥ የሚከት ነገር ከፊቴ እየታየኝ በመሆኑ አልሄድም ትለዋለች፤ ሰውየው የመንግስቴን እኩሌታ እሰጥሃለሁና ጠላቴን እርገምልኝ ያለው ሰው ስላለ የሚያስብ የነበረው እሱን ብቻ ነው፤ በኋላ ቆይቶ ለአህያዋ የታያት ነገር ለእሱም ታየው። ሰይፍ የመዘዘ መላዕክ ከፊቱ ቆሟል። እናም የነብዩን እብደት አህያ አገደችው ይባላል”። እዚህ ላይ ምን ለማለት ፈልጌ መሰለሽ አንዳንድ ሰዎች እንኳን ሽማግሌ እግዚአብሔርም ፊታቸው ቢቆም የማያከብሩ፣ ገፍትሮም ለመሄድ አቅም የሚፈልጉ አሉ ። ይህ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ፣ ከልማቱም ጥፋቱ የሚያመዝን በመሆኑ ሰከን ብሎ ማየት ሁሉንም ከጥፋት ያድናል።
ሰዎች ተባብሮ ከመኖር ይልቅ በሰውነታቸው የተጠሉ ሊመስላቸው አይገባም። ይህንን ከመሰላቸው በቀሉ የከፋ ስለሚሆን እንኳን ሽማግሌ ማንም ሊመልሰው አይችልም። በመሆኑም በተቻለ መጠን ሰዎች መጀመሪያ ከራሳቸው ጋር እንዲታረቁ ማድረግ ፤አባቶችም እውነትን ተናግረው መቀበል ያለባቸውን ሁሉ ለመቀበል ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል።
በመሆኑም አይሰሙኝም ብሎ ዝም ከማለት መናገር ጥሩ ነው። ምክንያቱም እነዚያ ሰዎች የሆነ ቦታ ላይ ሲደርሱ መስማትን ሊጀምሩ ይችላሉና። በዚህ ሰሞን ደግሞ ሰሞነ ህመማት እንደመሆኑ ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር ሲያጥብ ሊያስተምረን የፈለገው ነገር ፍቅር እንደሚያሸንፍ ነው፤ በመሆኑም ክፉውን በመልካም ማሰብ ጥላቻን ማራቅና ፍቅርና ይቅር ባይነትን ማንገስ ደግም ትልቁ አብሮ የመኖራችንና የመደማመጣችን መንገድ ሊሆን ይገባል ።
አዲስ ዘመን ፦ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን አገራዊ ስጋት ለመቀልበስ ምን ይጠበቅባቸዋል ብለው ያምናሉ?
ፓስተር ጻዲቁ፦ ሰሞኑን በቴሌቭዝን የሚያደርጓቸውን ክርክሮች እያዳመጥኩ ነው፤ ነገር ግን ስጋትን ለመቀልበስ ከሚያደርጉት ጥረት ይልቅ እርስ በእርስ ሲሰዳደቡ ነው የታዘብኩት። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለእኛ ምንም ጥቅም የማይሰጥ ነው። ለእኛ ጥቅም የሚሰጠው ወይም ደግሞ ይደግፈኛል ይመርጠኛል ብለው የሚያስቡትን ህዝብ ልብ የሚገዙት ከአንደበታቸው ጨዋ ቃል ሲወጣ እንዲሁም ሊሰሩ ስላሰቡት እቅድ ብቻ ሲያወሩ ነው። በነገራችን ላይ ይህ መሰሉ ችግር የሚንጸባረቀው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በገዢው ፓርቲ ዘንድም ነው።
በመሆኑም ከስድብ የሰዎችን የግል ነገር ከመነካካት ይልቅ አገር አሁን ካጋጠማት ችግር እንዴት ነው መውጣት የምትችለው፤ የትኛውን መንገድ ብንከተል ነው መልካም የሚሆነው የሚለውን ማሰብና ለደጋፊያቸውም ማሰማት ይኖርባቸዋል።
በእኔ እምነት እስከ አሁን ድረስ ስለ ብዝሃነትና ስለ ልዩነት ብዙ ነገሮች ሲነገሩ፣ ሲሰበኩ ቆይተዋል፤ ነገር ግን አንድነትን በተመለከተ የተነገረ ነገር የለም። አሁን ደግሞ ይህንን ነገር እንኳን በወጉ ዳር ሳያደርሱ ሌላ አጀንዳ ላይ መግባት ሳይሆን እኛ ልክ ነው፣ ብዙ ነን፣ የቋንቋም፣ የብሔረም ብዝሃነት አለን፤ ነገር ግን ይህ ማለት አርግማን ሳይሆን መልካም እድል መሆኑን በመገንዘብ ይህንን ብዙ ህዝብ ወደአንድነት ለማምጣት የሚጠቅሙ ሃሳቦችን መሰንዘር፣ በዚያ አማካይነትም ደጋፊና ድምጽ ለማግኘት መጣር ይገባል። ስለዚህ ልዩነትን አንደ መልካም እድል በመጠቀም አንድነታችንን ማጠናከር ላይ ተፎካካሪ ፓርቲ ነን የሚሉት ሁሉ ሊያስቡበት ከፍተኛ የሆነ ስራንም ሊያከናውኑ ይገባል።
አንዳንድ ጊዜ ከዛሬ ስንት ዓመት በፊት የነበረን የፖለቲካ አካሄድ ወደዚህኛው ዘመን አምጥቶ ለማራመድ መሞከር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ፣ ኪሳራው ነው የሚያመዝነው። እንዲያው እንደ ምሳሌ ባነሳልሽ በደርግ ጊዜ ፓርቲዎች ቀኝ ዘመም ግራ ተስፈንጣሪ እንዲሁም መሃል ሰፋሪ በማለት ከከፋፈሉ በኋላ የቀሩትን ደግሞ አምስተኛ ረድፍ በማለት ለያይተው ይጠሯቸው ነበር፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ህብረተሰቡ የቱጋ ሊቆም እንደሚችል መወሰን እስከሚያቅተው ድረስ ያደረሰ ነበር።
በመሆኑም ይህ ልዩነታችን አንዳችን ለአንዳችን ብርሃንና አቅም መሆናችንን የሚያሳይ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል ፤ ፓርቲዎቹም በዚህ ልክ መቃኘት አለባቸው። አልያ ግን እነሱ የሚለኩሱት፣ ለኩሰውም የሚያራግቡት ልዩነትና የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እሩጫ ብዙ ዋጋን የሚያስከፍል ስለመሆኑም መገንዘብ ያስፈልጋል። በመሆኑም የማይጠቅም የሚባል ዘር የለም፤ አንዳችን ለአንዳችን እንጠቅማለን ከዚህ በተቃራኒው በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እሰጣገባ ውስጥ ያለ ጥላቻ ቂም በቀል መጥፎ ነው። ከዚህ ይልቅ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መከባበር፣ አንዳቸው የሌላውን ቁስል ማወቅና መረዳት እንዲሁም ማከም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ወጣቱ ትውልድ ከስሜት ወጥቶ አገር ካለችበት ስጋት ለመውጣት ያለበትን ሃላፊነት እንዴት ይገልጹታል?
ፓስተር ጻዲቁ ፦ እውነቱን ለመናገር ወጣቱ ትውልድ በተለይም በማህበራዊ ድረ ገጾች እንዲሁም በሌሎች አማራጮች ከሚዘራበት መጥፎ ዘር አንጻር ሳየው እንዲያውም ጥፋቱ ትንሽ ነው እግዚአብሔር ይባርካቸው ነው የምለው። ነገር ግን አሁን ላይ ወጣቱን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚዘራው ዘር የሚሰራው ስራ በጣም ከባድ ነው። ምናልባት እኛ በእድሜ ጠና ያልን ሰዎች ብዙ ነገሮችን አይተን ስለመጣን እነዚህን ነገሮች እንደ አመጣጣቸው ለመመለስ አቅሙ ይኖረን ይሆናል። ነገር ግን ወጣቶች እድሜያቸው ገና ከመሆኑም በላይ የሚሰሙትን የሚያዩት እነሱኑ ብቻ ነው። በመሆኑም ወጣቶች ባለፉት አገዛዞችም የነበሩትን ሁኔታዎች በመረዳት በተቻለ መጠን እራስን መግዛት የክፉዎች መጠቀሚያ ላለመሆን ከፍተኛ የሆነ ጥረትን ማድረግ አለባቸው።
በወጣቶች ደም መኖር የሚፈልጉ ሀይላት ስላሉ የሚያምኑትን ማወቅ߹ ያመኑት ነገር ደግሞ ትክክለኛ መሆኑንና ነገ እድሜያቸው ሲገፋና ሲያረጁም የማያፍሩበት መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ሌላው ዛሬ ላይ ሆኜ የምሰራው ወይም የማደርገው ነገርና የምንቀሳቀስበት እያንዳንዱ እርምጃዬ ለራሴም ለአገርም ያለው ፋይዳ ምንድነው ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ትክክለኛ ላልሆነ አላማ ዋጋ መክፈልም አስፈላጊ ስላልሆነ፤ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን በስሜት ሳይሆን በደንብ ተረጋግቶ የዓለምን የአፍሪካንም የአገሪቱንም ታሪክ በቅጡ ተገንዝቦ ትክክል ያልሆነውን በመተው ትክክለኛውን መንገድ በመከተል በተቻለ መጠን ከአመጻና ከሁከት በመራቅ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በተለይም ከፊታችን ያለው አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን እንደ አገር ምን መስራት ይጠበቅብናል?
ፓስተር ጻዲቁ ፦ እንደ አፍሪካም ሆነ እንደ አገራችን በቅድመም ይሁን በድህረ ምርጫ ወቅት ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች እንዳሉ እንገነዘባለን፤ በመሆኑም በተለይም በቅድመ ምርጫው ወቅት ሰዎችን ለጥላቻ ለተለያዩ ቂምና ቁርሾዎች ማመቻቸት ተገቢ ያልሆኑ ቃላትንም መጠቀም አያስፈልግም። ምክንያቱም ትንሽ እሳት ጫካ እንደምታነድ ሁሉ አንደበት እሳት ነውና ብዙ ነገሮችን ይፈጥራል፤ በመሆኑም በምርጫው ላይ ተዋናይ የሆኑ ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄን ማድረግ አለባቸው። ከወዲሁ የአገሪቱን የቆየ አብሮ የመኖር ባህልና የአብሮነት እሴቶች በጠበቀ መልኩ መንቀሳቀስ እንዲሁም የህዝቡን ስነ ልቦና ወዳልተፈለገ መንገድ ለመቀየር መጣርንም ማቆም ይገባቸዋል።
ከምርጫው በኋላም እከሌ አሸናፊ ሆነ ተብሎ ሲገለጽ አይ አይደለም የሚል አካል ካለ በህጉ መሰረት ወደፍርድ ቤት ሄዶ በሰላማዊ መንገድ ሂደቱን የመቃወም መብቱን መጠቀም እንጂ ደጋፊውን አስተባብሮ ወደሁከት ለማምራት መጣር እንደ አገር ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ በዚህም ላይ ሊታሰብበት ይገባል።
ከዚህ ቀደም በመሰል ችግሮች ምክንያት ከበቂ በላይ የሰው አካል አጉድለናል፣ ህይወት አጥፍተናል፣ ንብረት አውድመናል፤ አገሪቱም ከምትሸከመው በላይ ጫና ፈጥረናል፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ስለሆንና” ነገም ሌላ ቀን ነው “ ብለን የምንታገስ በመሆናችን ነው እንጂ ያሳለፍነው ነገር ቀላል ሆኖ አይደለም። አሁን ደግሞ ወደዛ አይነት ሁኔታ ሰዎች ይገባሉ ብዬ አላስብም እንዳይሆንም ደግሞ እንደ አገር ሽማግሌ እንዲሁም የሀይማኖት አባት በምክሩም በጸሎቱም እንተጋለን። የሚሰሙንንም እንመክራለን በተለይም ወጣቶች ለማንም ፍላጎት ሲባል መስዋዕትነት መክፈል ስለማይገባቸው ጉዳዩን በአግባቡ ተከታትለው ከውጤቱ በኋላ እንኳን ችግር ቢነሳ መፈታት ያለበት በህግ ብቻ ነው ብለው አቋም መያዝም ይኖርባቸዋል ።
አዲስ ዘመን፦ በትውልዱ ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት ከምን የመነጨ ነው ይላሉ? ክፍተቱንስ ለመድፈን ምን መሰራት ይኖርበታል?
ፓስተር ጻዲቁ፦ ክፍተቱ ቀደም ብሎ በነበሩ አገዛዞች የተፈጠረ ነው። ለምሳሌ በአብዮቱ ዘመን ሀይማኖት ይቆጠር የነበረው እንደ አደንዛዥ ነገር(ዕጽ) ነው። ሽማግሌዎችና በእድሜ ገፋ ያሉ ሁሉ ተራማጅ አስተሳሰብ የሌላቸው አድሃሪ ይባሉም ነበር፤ ይህንን ተከትሎ ደግሞ እንኳን ሽማግሌ የወለደ አባትንም ያለማክበር መጣ።
መንግስትም ለራሱ አገዛዝ እንዲመቸው ወጣቶቹን ከወላጆቻቸው ለየ፤ ይህ አካሄድ ደግሞ እየቆየ ስር እየሰደደ መጣ። ከዚያ በተጨማሪም የዓለም ስልጣኔ ባልተዘጋጀንበትና አቅማችን ባልዳበረበት ጊዜ ወደ አገር ገባ። ይህንን ተከትሎም መጥፎውም፣ ጥሩውም ነገር ሁሉ ማራገፊያ ሆንን ፤ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ተደማምረው እኛነታችንን አጠፉብን።
አሁን እኔ እንደ ሀይማኖት አባትም እንደ አገር ሽማግሌም የምለምነው ወጣቱን ብቻ ሳይሆን መላውን ነው። ህዝብ ማንኛውንም ነገር ተቀብሎ ከማራገብ እና እኛነታችንን የሚያስተዉ ነገሮች ዝም ብሎ ከመወሰዱ በፊት የነገሩን እውነትነት በጥሞና ማረጋገጥ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ መረዳት አለበት።
አዲስ ዘመን ፦ የቀደመውን ኢትዮጵያዊ የመከባበር የመደማመጥ እሴቶቻችንን አስቀጥሎ ለመሄድ ከአገር ሽማግሌዎች ምን ይጠበቃል?
ፓስተር ጻዲቁ፦ ከዚህ በኋላ የሚጠበቅብን እንግዲህ ሁላችንም ቆም ብለን ለምን እዚህ ደረጃ ደረስን፣ ከዚህ ችግርስ እንዴት እንውጣ፣ ብለን ማሰብ አለብን ። በተለይም በእድሜ ጠና ያሉ አባቶች የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች እድሜያቸው ያስተማራቸው ብዙ ነገር ስላለ እነሱን መስማት ያስፈልጋል። አባቶችም ትውልዱ እኛ የቀመስነውን መከራ መቅመስም በዚያ ውስጥም ማለፍ ስለሌለበት በቁጭት በመነሳት ቆም ብለው አይሰሙኝምን ትተን ቢሰሙም ባይሰሙም መምከር ማስተማር ያስፈልጋል። ይህንን የምልሽ በዚህ ሂደት ውስጥ ጥቂቶችን እንኳን ማትረፍ የሚቻልበት እድል ስላለ ነው።
በመሆኑም ውይይትን ከቤተ እምነት ጀምሮ በማድረግ ከዚህ ከጥፋት መንገድ ብሎም የረሳናቸውን፣ የተውናቸውን የእኛነት መገለጫዎቻችንን የመከባበር፣ የመደማመጥ፣ አንተ ትብስ አንቺ፣ ወዘተ የሚሉ እሴታችንን ለማስቀጠል ዛሬውኑ ስራውን መጀመር ያስፈልጋል።
መንግስትም ለእንደዚህ አይነት አካሄዶች ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልገዋል። አለበለዚያ በዚሁ የጥፋት መንገዳችን ከቀጠልን የሚመራ ህዝብም ሆነ አገር ላይኖረን ይችላልና መጠንቀቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ፓስተር ጻዲቁ ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013