አቶ ኦርዲ በድሪ የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ናቸው፡፡ የአሁኑን ኃላፊነት የተረከቡት ከሁለት ወር በፊት ነው፡፡ በፔዳጎጂካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፤ በሁለተኛ ዲግሪም ተመርቀዋል፡፡ በሥራ ዓለም በትምህርት ቢሮ፤ በመምህራን ኮሌጅ፤ በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤትና በባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በኃላፊነት አገልግለዋል፡ ወቅታዊ በሆኑት የሐረሪ ክልል ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሐረሪ ክልል ሕገ መንግሥት በክልሉ ለሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች እውቅና አለመስጠቱ እንደ ክፍተት ይነሳበታል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለዎት ?
አቶ ኦርዲ ፡- ከሕገ መንግሥቱ ጋር በተያያዘ አሁን በቀረበው መልኩ የተነሳ ጥያቄ የለም፡፡ የሐረሪ ክልል የሐረሪ ብቻ ነው የሚል ሕገ መንግሥቱ ላይ አልተቀመጠም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሐረሪም የኦሮሞ ሕዝብም ያላቸውን ድርሻ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ሕገ መንግሥቱን አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ጥያቄዎቹ አሁን በተነሳው መልኩ አይደለም የሚቀርቡት፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ የፍትሐዊነት ጥያቄዎች አሉ፡፡ ጥያቄውን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበት የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው፡፡ ሕግና ሥርዓቱን ተከትሎ የሚሻሻልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ዞሮ ዞሮ በክልሉ ላይ የሐረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሐብሊ)ም ሆነ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በሕዝብ የተመረጡ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ማንኛውም ሀገራዊም ክልላዊም ፓርቲ በሐረሪ ክልል ላይ ተወዳድሮ ማሸነፍ ያለማሸነፍ ጉዳይ ነው እንጂ ክልሉን ሁልጊዜ ማስተዳደር ያለበት ሐብሊ ወይንም ኦዴፓ ብቻ ነው የሚል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሐረሪ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 5 ላይ የሐረሪ ሕዝብ የክልሉ የሥልጣን ባለቤት ነው ይላል፤ ይህ ትክክል ነው አይደል?
አቶ ኦርዲ ፡- ትክክል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ በክልላችሁ የሚገኙት እስከ 22 በመቶ የሚሆኑት የአማራ ብሔረሰብ እንዲሁም የሌሎችን ፖለቲካዊ መብት አይገደብም፤ ኦዴፓ ምንም እንኳን ከሐብሊ ጋር ‹‹ሀምሳ/ሀምሳ/ ዜሮ›› በሚለው ድልድል የሥልጣን ተጋሪ ነው ቢባልም ህገ መንግሥታዊ እውቅና አለማግኘቱ ክፍተት አይደለም?
አቶ ኦርዲ ፡- ይሄ ክልል በዋነኛነት በከተማው ውስጥ ያለው የሐረሪ ሕብረተስብ እና በገጠሩም አካባቢ ያለው የኦሮሞ ብሔረሰብ በጋራ ያቋቋሙት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሥልጣኑ ባለቤት የሐረሪ ሕዝብ ነው የሚለው ክልሉ በዋናነት ሲቋቋም የሐረሪን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ስለሆነ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ጥያቄ ካለ ሕዝቡ ውሳኔ የሚሰጥበት የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው፡፡ በዚህ መልኩ ታይቶ ሕብረተሰቡ ተወያይቶ በሚመለከታቸው አካላት ሂደቱን ጠብቆ የሚሻሻልበት ሥርዓት ሊኖር ይችላል፡፡
ሃምሳ ሃምሳ ዜሮ የሚለው የሥልጣን ክፍፍል ነው፡፡ እሱም ከሕገ መንግሥቱ ጋር ምንም አይገናኝም፡፡ ነገ የአማራ ፓርቲ ካሸነፈ ሥልጣን ሊይዝ ይችላል የሚለውን ነገር መያዝ አለብን፡፡ መቶው ነገ ዜሮ ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ ሃምሳ ሃምሳ የሆነበት ትልቁ ምክንያት ሐብሊና ኦዴፓ በሕዝብ ምርጫ ስላሸነፉ እንጂ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ሥልጣን የሚይዙትም እነሱው ናቸው፡፡ አሁን ግን ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችንም ማካተት አለብን ብለን ወሰነናል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በምን ደረጃ ነው የወሰናችሁት?
አቶ ኦርዲ ፡- በሐብሊ ደረጃ ነው የወሰነው፡፡ አራት የሚሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች መድበናል፡፡ በቢሮ ኃላፊ፣ በፕሬዚዳንት አማካሪነት፣ የተመደቡ አሉ፡፡ ሐረሪ ብሔራዊ ሊግም ውስጥ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም አሉ፡፡ ሀገራዊ አንድነቱን ለማጠናከር ከጽንፈኛ ብሄርተኝነት መውጣት ስላለብንና ጽንፈኛ ብሔርተኛነት ለክልላችንም ለህዝባችንም አደጋ ስለሆነ ወደ አካታችነት ገብተናል፡፡ ብዙ የምንጋራቸው ነገሮች አሉ፤ እነዛ ነገሮች ቀላል አይደሉም፡፡
እስከ አሁን የነበረው አመለካካት እኔ ብቻ የሚል ነው፡፡ እኔ ብቻ የሚለውና ሌላውን የማግለል ነገር ለማንም አይበጅም፡፡ ከሕብረተሰቡ ጋር ተነጋግሮ ማሳመን ያስፈልጋል፡፡ አብረን ነው የምናድገው የጋራ ሀገራችን ነው፤ሁሉም መሳተፍ አለበት የሚለውን ለማምጣት በሂደት የሚስተካከል ጉዳይ ይኖራል፡፡ ይህን ሊያሳዩ የሚችሉ ጅምር ሥራዎች ባለፉት ሁለት ወራት እያካሄድን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በምክር ቤት ደረጃ ሃምሳ በመቶ የሐብሊ ፣ ሃምሳ በመቶ ደግሞ የኦዴፓ ተወካዮች ቢኖሩም፤ በኃላፊነት ደረጃስ የፍትሃዊነት ክፍተት አለ ይባላል ?
አቶ ኦርዲ ፡- በሥልጣን ክፍፍል ደረጃ ስንመጣ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ እዛ ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይሄ በሂደት የሚስተካከል ይሆናል፡፡ ጉዳዩ በሁለቱ ፓርቲዎች የጋራ ስምምነት እንጂ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦች አያያዝ እንዴት ነው ? ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ይጠቀማሉ ? አንዳንዶች ጫና ተደርጎብናል፤ ሙሉ መብት የለንም እየተገፋን ነው ሲሉ ይደመጣል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው ?
አቶ ኦርዲ ፡- ጥያቄው ይነሳል፡፡ ሁሉንም ያቀፈ አካሄድ መከተል እንዳለብን ለመግለጽ የተለያዩ የሕዝብ መድረኮችን ስናካሂድ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ተገለልን የሚሉ አካላት ድምጽ ይሰማል፡፡ ሥርዓቱ ሁሉንም አቃፊ መሆን አለበት የሚል ጥያቄም ይቀርባል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በተመለከተ ለውጡ ከተጀመረ በኋላ የበለጠ ፍትሐዊ ለመሆን እየሞከርን ነው፡፡ በተለይም ከስልጣን ክፍፍል አኳያ በእኛ ክልል ያሉ ሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች በኃላፊነት ደረጃ እንዲመደቡ መደረጋቸውንም ቀደም ሲል ገልጫለሁ፡፡ አሁንም በቂ ነው ባይባልም ተስፋ እንዳለው የሚያመላክቱ ጅምር ሥራዎች አሉ፡፡
በፖለቲካው ሐብሊና ኦዴፓ ናቸው በክልሉ ተመርጠው ውክልና ያላቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን በክልሉ ውስጥ ያሉ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የሥልጣን ክፍፍል ላይ ድርሻ እንዲኖራቸው ተወስኖ የተጀመረ ነገር አለ፡፡ ከዛ ውጪም በኢንቨስትመንትም በሌሎችም አገልግሎት አሰጣጦች ረገድ ጥያቄአቸውን ለመመለስ ቅድመ ዝግጅት አድርገናል፡፡ የተወሰኑ መሻሻሎች አሉ፡፡ ለቀጣይ ሁሉን አካታች የሆነ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለ ሆኖ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምናስተካክላቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እየሄዱ ነው ? የመንግሥት መዋቅር በክልሉ ተሽመድምዷል የሚል መረጃ አለ፤ ይሄን እንዴት ያዩታል ?
አቶ ኦርዲ ፡- እንደገለጽከው በተለይም ሀገራዊ ለውጥ ከተጀመረ በኋላ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይታያሉ፡፡ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ ክፍተት አለ፡፡ በመንግሥት ተቋማት አካባቢም በሥራ ገበታ ያለመገኘት ሁኔታ፣ ለሕብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ያለመስጠትና አንዳንድ ችግሮችም እንዳሉ ይነሳል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ሥራ ገብተናል፤ የምናስተካክለው ጉዳይ ይሆናል፡፡ በተለይ ችግሩ ያለው ገጠር አካባቢ ነው፡፡ ሕብረተሰቡ እሮሮ የሚያነሳባቸው የገጠር ወረዳዎች አሉ፡፡ ከሕብረተሰቡ ጋር በመወያየት በሂደት የምንፈታው ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ሥርዓተ አልበኝነትን ለመከላከል፤ መንግሥታዊ ሥራዎች እንዲቀጥሉ ለማድረግ፤ እየተደራጁ የመንግሥት ሥራ አናሠራም የሚሉትን ለመከላከል ምን እርምጃ ወሰዳችሁ ?
አቶ ኦርዲ ፡- አዳዲስ አመራሮችን መድበናል፡፡ በተለይም ከሕዝቡ እሮሮ ጋር በተያያዘ ብልሹነት ያሉባቸውን ወረዳዎችና ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን በተመለከተ ከሁለቱ ፓርቲዎች ጋር ስምምነት ላይ ደርሰን አዲስ የአመራር ሽግሽግ አድርገናል፡፡ ለውጡ ገና ሂደት ላይ ነው፡፡ በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት እየተሰጠ አይደለም፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የጸጥታ ችግርም ስላለ ከሚመለከታቸው ፌደራል ተቋማት ጋር በተለይ ከፌዴራል ፖሊስና ከመከላከያ ጋር በመሆን የጋራ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ በሚገባበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በክልሉ የፍትሕ ጉዳይ በሥርዓቱ እየተከበረ አይደለም ይባላል፡፡ በተለይ ፖሊስ ስራውን በአግባቡ እንደማይሰራ ይነሳል፤ ትክክል ነው ?
አቶ ኦርዲ ፡- በፖሊስ በኩል ያለውን ችግርና የፍትህ እጦትን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ ትክክለኛ ነው፡፡ ለእዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ብለን ያስቀመጥነው ፖሊሱን ወደ ተሀድሶ ሥልጠና ማስገባት ነው፡፡ ፖሊሱን ሪፎርም ማድረግ አለብን ብለን ተስማምተን ሙሉ በሙሉ የአመራር ሽግሽግ አድርገናል፡፡ ለስልጠናና ለተሀድሶ ደግሞ ከፌደራል ፖሊስ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ለዚህ የሚያስፈልገውን ወደ አስር ሚሊዮን ብር በጀት ከክልሉ መንግሥት ተመድቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፖሊስ ሕዝቡንና ሕገ መንግሥቱን ብቻ እንዲያገለግል ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎችን አጠናቀናል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- የሐረር ከተማ በቆሻሻ አወጋገድና በውሃ እጥረት እንደምትፈተን ይታወቃል፤ ችግሩ አልተፈታም?
አቶ ኦርዲ ፡- የቆሻሻ አወጋገድን በተመለከተ የሕግ የበላይነትን ካለማክበርና ከካሳ ክፍያ ጥያቄ ጋር የሚየያዙ ችግሮች ነበሩ፡፡ ባለፉት አስራ አምስት ቀናት ሕግና ስርአቱን ተከትለው የቀረቡ የካሳ ጥያቄዎችን ስለፈታን በአሁኑ ወቅት አስቸግረውን የነበሩት አብዛኞቹ ቆሻሻዎች ተነስተዋል፡፡ አሁን ችግሩ እንደሌለ ላረጋግጥልህ እወዳለሁ፡፡ ውሀን በተመለከተ የክልላችን የረዥም ጊዜ ችግር እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይሄ ችግር እየተፈታ ነው፡፡ ወደ ከተማው በሦስቱም አቅጣጫዎች የሚመጡት የውሃ መስመሮች እየሰሩ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- እርስዎ ይህን ቢሉም ከኤረር ይመጣ የነበረው ውኃ እየተቆራረጠ በሥርዓቱ እንደማይደርስ ነዋሪው ይናገራል፤ መረጃው ትክክል አይደለም ?
አቶ ኦርዲ ፡- የኤረር ውኃ በአሁኑ ጊዜ እዛ አካባቢ ካለው ሕብረተሰብ ጋር ተነጋግረን አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ በእርግጥ የውኃ እጥረት ስላለ አቅርቦቱ በሁሉም አካባቢዎች በሚፈለገው ደረጃ አይደለም፡፡ ሕብረተሰቡ ባነሳቸው ችግሮች ተዘግቶ የነበረው ውኃ ግን አሁን ተከፍቷል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ዘላቂ መፍትሄው ምንድነው ይላሉ ?
አቶ ኦርዲ ፡- በአካባቢው የሚቀርቡትን የንጹህ ውኃ ጥያቄዎች ጥናት አድርጎ አግባብነት ባለው ሁኔታ ማስተናገድ የመጀመሪያው መፍትሔ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሕግና ሥርዓትን ሳይከተሉ በሥርዓተ አልበኝነት የሚነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ማድረጉ ይቀጥላል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በቅርቡ በቀላድ አምባና 01 ቀበሌ ወጣቶች መካከል በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙም ተነግሯል፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ፖሊስ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ነው የመጣው ይላሉ፤ ቅሬታውን እንዴት ያዩታል ?
አቶ ኦርዲ ፡- በ01 አካባቢና በቀላድ አምባ ወጣቶች መካከል በተፈጠረው የሰፈር ግጭት መጣራትና መስተካከል ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ የተሳሳተ መረጃ ተሰራጭቷል፡፡ የሞተ ሰው የለም፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ቀደም ሲል በተፈጠረ ግጭት ጉዳት ደርሶበት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እያዋጡ እንዲያሳክሙት ተብሎ የነበረ ወጣት የለም ?
አቶ ኦርዲ ፡- እሱ ሌላ ነው፡፡ ገንደ ፌሮ ሰፈር ይበላል፡፡ አንደኛው አንደኛውን ወግቶት ህይወቱ ያለፈበት ክስተት ነበር፡፡ በግለሰቦች መካከል የነበረ ግጭት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ሆኖም ቀረ በቡድን በሚነሱ ግጭቶች የሰው ህይወት ያልፋል ይባላል፡፡ ይሄን ለማስወገድ እየሠራችሁት ያለው ሥራ ምንድነው?
አቶ ኦርዲ ፡- እየሠራነው ያለው ነገር ሕብረተሰቡን ማወያየት ነው፡፡ በተለይም በየወረዳው የሰላም አምባሳደሮችን አሰልጥነናል፡፡ ሐረር የምትታወቅበት በሰላም በአብሮነትና በመቻቻል እሴት ነው ፡፡ የሰላም ኮንፈረንሶችን በየወረዳው በማካሄድ ላይ እንገኛለን፡፡ ባለፈው ሳምንት የሰላም አምባሳደሮች ከገጠርም ከከተማም ተውጣጥተው ሕብረተሰቡን የማረጋጋትና ሰላምን የመስበክ ሥራ ሠርተዋል፤እየሠሩም ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪ በሚዲያ ከፍተኛ ሽፋን ተሠጥቶት ስለ ሰላም ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ የሃይማኖት አባቶችም ሰላሙን የማረጋገጡን ሥራ እያገዙን ነው፡፡ በዋናነት ግን የጸጥታ ኃይሉን የማጠናከር ሥራ ነው መሠራት ያለበት፡፡ ፖሊሱን ወደ መስመር ማስገባት ፖሊሱን ለሕገ መንግሥቱና ለሕዝቡ ብቻ እንዲቆም ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻ ሆኖ እንዲያገለግል የማድረግ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገልን ያለው ፌደራል ፖሊስና መከላከያ ነው፡፡ ይህ አካል ለሀረር ብቻ ሳይሆን የምሥራቁን አካባቢ የጸጥታ ችግሮች በተመለከተ ስለሚሠራ የተሻለ ሰላም እንደሚገኝ ተስፋ አለኝ፡፡ የጸጥታ ሁኔታውን ለማረጋገጥ መረጃዎችን ተንተርሰው ፓትሮል የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ ሙሉ ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡ በተለይ የተቋም ጥበቃና ማታ ላይ የሚደረግ ፓትሮል በሚፈለገው ደረጃ አይደለም፡፡ እሱን በቀጣይ የምናስተካክለው አንድ ጉዳይ አድርገን ነው የወሰድነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የክልላችሁ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ቢሮ መኪና መስታወት በወጣቶች ተሰባብሯል፡፡ በመንግሥት ንብረት ላይ ጉዳት የማድረስ፤ ዜጎችን የመዳፈር፤ ቢሮ ገብቶ የመረበሽ፤ ንብረቶችን አምጡ የማለት ሁኔታዎች አሁንም አሉ፡፡ ይህ ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ ምን እየተደረገ ነው ያለው ?
አቶ ኦርዲ ፡- አሁን የቀረበው ነገር ትክክለኛ መረጃ ነው፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመንጋ ሄዶ የቢሮ ኃላፊዎችን የማስገደድ ፤ ትክክለኛ ውሳኔ ሳይሰጥበት ነገሮችን ለማስፈጸም መሞከር ፤ የሕግ የባላይነትን የመሸርሸር ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ አንድ የመንግሥት መኪናም ተሰብሯል፡፡ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ቢሮ መኪና ተሰባብሯል ኃላፊውም ላይ የደረሰ ጉዳት አለ፡፡ በቀጣይ ሕግና ደንቡን ተከትሎ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ ይወሰዳል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ሥርዓተ አልበኝነት ለመከሰቱ ምክንያቶቹ ምንድናቸው ብለው ያምናሉ? ከጀርባ እጆች አሉበት የሚልም ነገር ይደመጣልና፤ የደረሳችሁበት ጉዳይ አለ ?
አቶ ኦርዲ ፡- የማን እጅ አለበት እንዳለበት ተጣርቶ በሕግ የሚደረስበት ጉዳይ ይሆናል፡፡ እስከ አሁን ያሉት ጥርጣሬዎች ትክክለኛ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ እያንዳንዱ ጉዳይ በሕግ የተያዘ መሆኑን ላረጋግጥልህ እወዳለሁ፡፡ ወንጀል ሠርተው የተደበቁም አሉ፡፡ ይሄንን ያስተባበረ፣ ያቀናበረ ተልእኮ የሰጠና እጁን ያስገባ አካል ካለ ተጣርቶ ለሕግ ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- አዲስ አመራር ከመጣ ወዲህ ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከሙስና ጋር በተያያዘ የወሰደው እርምጃ አለ ?
አቶ ኦርዲ ፡- የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በዚህ ጉዳይ የማጣራት ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተለይም ከጸረ ሙስና ኮሚሽንና ከፍትሕ ቢሮ ጋር በጋራ ጉዳዩን አጣርተው ለሕግ እንዲያቀርቡ እየተሠራ ነው፡፡ እስከአሁን ወደ እርምጃ የተገባበት ሁኔታ የለም፡፡ ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎችና መረጃዎች በማቀናበር የማጣራት ሥራው እየተሠራ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ቀደም ባለው አመራር ዘመን የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት ነበር የሚሉ አሉ፤ እውነት ነው ?
አቶ ኦርዲ ፡- የፌዴራል መንግሥት በበፊቱ አመራር ላይ ጣልቃ ይገባ ነበር የሚባለው ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ሁሉም ክልል በሕገ መንግሥቱ መሰረት የራሱ የሆነ ስልጣን አለው፡፡ የሚያገለግለው ለመረጠው ሕዝብ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ስለነበረ ሥራ ይሠራ የነበረው የፌዴራል መንግሥትን ጣልቃ ገብነት ስለመኖሩ የሰማሁት ነገር የለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ሥልጣን የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይ ከሆነ እንጂ፤ በፌዴራል መንግሥት ከሚደረግ ድጋፍ ውጪ ጣልቃ ገብነት ስለመኖሩ አላውቅም፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት በምን ደረጃ ነው የሚገለጸው?
አቶ ኦርዲ ፡- ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለን ግንኙነትና ትብብር መልካም ነው፡፡ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የጋራ የአሠራር ሥርዓት አለን፡፡ በተለይም አሁን በዋናነት በጸጥታ ጉዳይ በጋራ እየሰራን ነው፡፡ ይህን በተመለከተ በጋራ እቅድ አዘጋጅተናል፡፡ በዚህ የጋራ እቅድ ሌሎችም የፌደራል ተቋማት እገዛ እያደረጉልን ስለሆነ የአካባቢውን ሰላም የምናረጋግጥበት ሁኔታ እየተመቻቻ ይገኛል፡፡ ከዚያ ውጭ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በተመለከተ ከኦሮሚያ ጋር የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ በሐረሪና በኦሮሚያ ክልል ያለው የኢኮኖሚና ባሕላዊ ትስስሩ ከፍተኛ ነው፡፡ ይሄንን በቀጣይ ግዜያት አጠናክረን እንሄድበታለን፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ ያጋጠሟችሁን ስኬቶችና ተግዳሮቶች ቢያነሱልን ?
አቶ ኦርዲ ፡- የሐረሪ ክልል መንግሥት በሐረሪ ብሔራዊ ሊግና በኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ በጥምረት የሚተዳደር ክልል እንደመሆኑ፤ ከለውጡ በኋላ በሁለቱ ፓርቲዎች አዳዲስ አመራሮች እንዲመደቡ ተደርጓል፡፡ በሕዝቡ በኩል የሚነሱ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ስምምነት ተደርሶ ወደ ሥራ ገብተናል፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ ጋር በተያያዘ ጥሩ ነገር አድርጌ የማነሳው ሐረሪ ላይ እስከአሁን ይህ ነው የሚባል የብሔር ግጭት አልተከሰተም፡፡ ሰው አልሞተም፤ አልተፈናቀለም ማለት ይቻላል፡፡ ይሄ ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በአመለካካት ደረጃ የሚገለጹ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዛን ማስተካከል አንድ ጉዳይ ሆኖ ይህ ነው የሚባል ግጭት አልተከሰተም፡፡ ሕዝቡ ሰላም ፈላጊ ስለሆነና የቀድሞ እሴቶቻችን ስላሉ ነው፡፡ አብሮነትና መቻቻሉ ነው እዚህ ያደረሰን፡፡ ሕዝቡ ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ችግር እንኳን ቢከሰት ሊከላከል የሚችል ጠንካራ የጸጥታ አካል ሳይኖረን ሕዝቡ በራሱ ነው ሰላሙን የጠበቀው፡፡ ይሄ ጥሩ ነገር ነው ብዬ አስቀምጠዋለሁ፡፡
ክልሉ በሁለት ፓርቲዎች እንደመተዳደሩ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት የክልሉን አጠቃላይ ሁኔታ ይወስነዋል፡፡ ጥሩው ነገር በሁለቱም መካከል መተማመንና አብሮ ተግባብቶ መሥራት አለ፡፡ በፊት የመጠራጠር፤ ያለመወያየት አብሮ መሥራት ላይ ችግሮች ይታዩ ነበር፤ ዛሬ ተቀርፈዋል፡፡ በሁለቱም ክልሎች ከለውጡ ጋር አብረው ሊራመዱ የሚችሉ አመራሮች ተመድበው በጋራ ነው እየመራን ያለነው፡፡
ያልተሻገርናቸው ችግሮች አሉ፡፡ ትልቁ ችግር የሕግ የበላይነትን ማስከበር ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የጸጥታ አካል በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የጸጥታ አካሉን ወደ መስመር ለማስገባት የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ቅድም ከተነሱትን በርካታ ችግሮች ከቆሻሻ መከማቸት፤ ከውሀ እጥረት፤ ከጎዳና ንግድና፤ግብር ካለመክፈል፤ ከዚህም አልፎ የደረቅ ወንጀሎችን ችግር የምንፈታበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ስለዚህም ትልቁ ሥራችን ብለን የምናስቀምጠው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ሕዝቡን የማስተማር ፤የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን የማጠናከር፤ የሰላም፣ የአብሮነትና የፍቅር እሴቶቻችንን የማጠናከር ሥራዎችን የምንሠራባቸው ይሆናል፡፡ በአንጻራዊነት ያለፉት ሁለት ሳምንታት ጥሩ የሚባሉ ሁኔታዎች አሉ፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ለሠጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን !
አቶ ኦርዲ ፡- እኔም አመሰግናለሁ !
ወንድወሰን መኮንን