ሀገሬ ሆይ ይማርሽ!
ሀገርምን እንደ ሰው ልጆች ትታመማለች? አዎን ትታመማለች። ዳሩ ማን የማይታመም አለ? የሰው ልጅ በተለያዩ ደዌዎች ተጠቅቶ እያቃሰተ አልጋ ላይ ይውላል። ለምን የሰው ልጅ ብቻ? ተፈጥሮም እንዲሁ ልምላሜዋ ጠውልጎና ወይቦ በክፉ ሕመም ተመትታ ትማቅቃለች። እንስሳትም ሆኑ አራዊቶች በደዌ ዳኛ በጎሬያቸው ቁራኛ ተይዘው እንደ አፈጣጠራቸው ይሰቃያሉ። ሀገርም ከዚህ መሰሉ “በላ” ነጻ ልትሆን አትችልም።
የሀገር ሕመም መንስዔውም ሆነ ሰበቡ ብዙ ነው። መገለጫውም የዜጎቿ ጣርና እህህታ ነው። ልጆቿ በሥጋቸው፣ በነፍሳቸውም ሆነ በስሜታቸው የሚታመሙት እርሷኑ አርግዘውና እርሷኑ ምክንያት አድርገው “አንቺ እኮ ነሽ!” እያሉ በእህህታ ቋንቋቸው እያናገሯት ወይንም እየወቀሷት፤ ሲከፋም እየዶለቱባት ሰበባቸውን ማራገፊያ በማድረግ ጭምር ነው። ስለዚህም ሀገር የምትታመመውና “የሐኪም ያለህ!” እያለች ተራዳዒ የምትማጠነው እኩል ከተፈጥሮና ከልጆቿ ጋር ነው።
ሀገርን በክፉ ደዌ ቀስፈው ለእንባና ለእንቅጥቅጥ የሚዳርጉት ዋንኞቹ ህመሞቿ መከሰቻቸው በርከት ያለ ቢሆንም ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው። የተፈጥሮ ሕመም አንዱ ተጠቃሽ መከራዋ ነው። ተፈጥሮ ፊት ነስታ በድርቅ፣ በቸነፈር፣ በአንበጣና በተምች ክፉ “ቫይረሶች” ስትጠቃ ሀገር ተጠቃች ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ የሀገራችን የሕመም ዓይነቶች የተላመድናቸውና ቤትኛ ያደረግናቸው ዓይነቶች መሆናቸውን ልብ ይሏል።
የውስጥ ፖለቲካዋ ብልሽትና የልጆቿ የእርስ በእርስ መጎሻሸምና “የቡጢ ድብደባ” የሚያርፈውም እንዲሁ በሀገር ፊት ላይ ነው። የውጭ ጠላቶች ሴራና ተንኮልም በግልጽ በሚስተዋል የክብርና የሉዓላዊነት ትንኮሳ፣ በስውር በሚጎነጎን የረቀቀ ሸርና ሴራ አማካይነት ሀገር ታምማ ልታቃስት ትችላለች። ጥቂቱን ነካካን እንጂ የእምዬ ሕመም መነሻና መድረሻው፣ ማረፊያና መገለጫው እጅግ የበረከተና የትዬለሌ የሚባል ዓይነት ነው። ኢትዮጵያ ሆይ ይማርሽ! በማለት በእግዚኦታና በለሆሳስ ለፈውሷ የምንማጠነውም ቀስፈው የያዟት ወቅት ወለድ ዥንጉርጉር ሕመሞቿና የነባር ደዌዎቿ ግርሻዎች ውስጧንና ውጭዋን ቀስፈው ስላስጨነቋት ነው።
ሰሙነ ሕማማት፤
ይህ ሳምንት በአብዛኞቹ የሀገራችን የክርስትና አማንያን ዘንድ እየታሰበ ያለው ሰሙነ ሕማማት እየተባለ ነው። ሰሙነ ሕማማት የሚሸፍነው ከሆሣዕና እሁድ (ሚያዝያ 17) እስከ ቅዳሜ ስዑር (ሚያዝያ 23) ድረስ ያሉትን ሰባት ቀናት ነው። በቅዱስ መጽሐፍ ላይ የተመሠረተው የክርስትና አስተምህሮ ሰሙነ ሕማማትን የሚተርከው በርካታ ክስተቶች እንደተስተናገዱበት በማስታወስ ነው።
በዕለተ ሆሣዕና ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ሲገባ ተከታዮቹ፣ ወዳጆቹና እጅግ ብዙ ሰዎች “በሆት ግባ” እያሉ የተቀበሉት ለምለም እየጎዘጎዙለት፣ የዘንባባ ዝንጣፊ እያውለበለቡለትና አልባሳታቸውም ሳይቀር እያነጠፉለትና እየሰገዱለት “ሆሣዕ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው። ሆሣዕና በአርያም” እያሉ በመጮኽና ደስታቸውን በመግለጽ ነበር።
ከአራት ቀናት በኋላም የጸሎተ ሐሙስ ዕለት በሆታና በዕልልታ፣ በሃሌሉያና በዝማሬ የተቀበለው ያው ሕዝብ “በክብር ያነገሡትን” ያንኑው ኢየሱስን ከፈሪሳዊያን፣ ከሰዱቃዊያንና ከጸሐፍት ዋና ዋና የካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋር በመዶለት በተንኮል አሲዘው ሊገድሉት እንደተማከሩ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ዝርዝሩን እናነባለን። በጥላቻና በግፍ የሰከሩት የአይሁድ መሪዎችና የአካባቢ ገዢዎችም መድኃኒተ ዓለምን በመስቀል ላይ ቸንክረው ሊገድሉት የተማማሉትና የወሰኑት በዚሁ የሰሙነ ሕማማት ሳምንት ውስጥ ነበር።
በእጅጉ የሚያስገርመው ግን በትምህርቱና በሕይወቱ ተማርክው ከተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ መካከል ዋነኛው የሴራው ተዋናይ የአስቆሮቱ ይሁዳ መሆኑ ነበር። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ “መምህር ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ከሳመው” በኋላ እንደነበር ወንጌላዊያኑ ጸሐፍት በሚገባ ተርከውታል። “ጌታዬና አምላኬ” እያለ የኖረው ይሁዳ፣ ከጌታው እጅ የፍቅር ጉርሻ የተቀበለው ይሁዳ፣ በደል ያልተገኘበትን ንፁሁን ጌታ ልክ እንደ መገልገያ ቁስ በሠላሳ ዲናር ሸጦ ለጠላቶቹ አሳልፎ ሲሰጠው ጥቂትም ቢሆን ሰብዓዊ ህሊናው አልገሰጸውም፤ የበደሉ ድርጊትም አልዘገነነውም። ውሎ ሳያድር ግን የግፉን ዋንጫ በራሱ እጅ ተቀብሎ “የትንሳዔውን ድል ሳያይ” በአሰቃቂ ሞት መሰናበቱ የታሪኩ መደምደሚያና አሳፋሪው ክፍል ነው።
የሰሙነ ሕማማት ታሪኮች በአብዛኛው ልብን በሀዘን የሚያኮማትሩና መንፈስን ትካዜ ውስጥ የሚዘፍቁ ዓይነቶች ናቸው። ሣምንቱ በእንባና በኤሎሄ ቢጠናቀቅም የሣምንቱ የመጀመሪያው ቀን እሁድ የትንሣዔው ክብር የገነነበት፣ የምሥራች አዋጁ ከአጥናፍ አጥናፍ የናኘበት ዕለት ነበር። የሰባቱ ቀናት ሰሙነ ሕማማት የዘላለማዊ ሕይወት ዋስትና መስፈንጠሪያ ዕለታት ነበሩ የሚባለውም ስለዚሁ ነው።
የኢትዮጵያ ሰሙነ ሕማማት፤
ያለፉት ሦስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ዐውድ በሰሙነ ሕማማት ቢመሰሉ ተገቢነት ይኖረዋል። ከኢሕአዴግ የሃያ ሰባት ዓመታት የግዞት እስር ነፃ የወጣው ሕዝብ ለውጡንና ለለውጡ እውን መሆን ተቀዳሚ ድርሻ የነበራቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች እንደምን “የዘንባባ ዝንጣፊ እያውለበለበ በሆሳዕና ዝማሬ” እንደተቀበላቸውና እንዳከበራቸው የሚዘነጋ አይደለም። “ሃሌሉያ ዘማሪው ጀማ” በሀገሪቱ ክበብ ውስጥ የነበረው ዜጋ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለማት የተበተኑት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችም የፈነደቁትና “የዝማሬው ተጋሪ ለመሆን የፈቀዱት” እጅግ በሚያስደንቅ ስሜትና መሰጠት ጭምር ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ግን የዕልልታው ድምጽ የሰለለውና የጭብጨባው ግለት ቀንሶ “የኢትዮጵያ ሰሙነ ሕማማት” የተተካው ሳይውል ሳያድር ነበር።
የዘንባባ ዝንጣፊ ተይዞላቸውና “ሆሳዕና እየተዘመረላቸው” ወደ ሀገር የገቡ “ስደተኞች” የተገላቢጦሽ የሰላም ርግብን ገድለው ሰይፋቸውን ለመውልወል ጊዜ አልፈጀባቸውም። “የገዢነት መጎናጸፊያ” ካባ ደርበው በአደባባይና በየሚዲያው “ጌቶች! ነጻ አውጭዎች! የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጠበቆች!” ሲባሉ የኖሩት “ፈላጭ ቆራጭ” አምባገነኖችም እንዲሁ “የሆሳዕናው ዝማሬ” በቅናት ስላደበናቸው ወደመጡበት ዋሻ ለመሸሽና ቀስታቸውን በሀገር ላይ ለማስፈንጠር ጥድፊያቸው አጃኢብ የሚያሰኝ ነበር።
የአስቆሮቱ ይሁዳ የመንፈስ ልጆች የኢትዮጵያ ሰሙነ ሕማማት ቀናትና ወራት እንዲራዘሙ ያላሴሩት ሴራ፣ ያላጠመዱት ወጥመድ አልነበረም። አሸክላቸው ራሳቸውን አጥምዶ ግባ መሬታቸው ባይፈጸም ኖሮ የኢትዮጵያ ትንሣዔ እጅጉን በተራዘመ ነበር። ለነገሩ ሰሙነ ሕማማቱ ዛሬም አልተጠናቀቀም። እንዲያውም ሕመሟ ከቀን ወደ ቀን እየበረታ ለእንባና ለመከራ እንደሚዳርጋት እያስተዋልንም አይደል። የጠላቶች ዓላማ ሀገሪቱን “አኬልዳማ” በማድረግ የሐዘን ማቅ ማልበስ ነበር።
በርግጥም በአንዳንድ ጉዳዮች ተሳክቶላቸዋል ማለትም ይቻላል። ቁጥራቸው በኢምንት የሚሰላው የአስቆሮቱ ይሁዳ ቤተሰቦች ደባና ሸራቸው የሚተገበረው በሀገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ባህር ማዶ ካሉ ታሪካዊ ደመኞቻችን ጋር ኔትወርካቸውን በማስተሳሰር ጭምር ነው። ለዚህም ነው “ኢትዮጵያ ሆይ ይማርሽ!” ብለን የምንጸልይላትና “የትንሣዔሽ ቀናት ሩቅ አይደሉም” ብለን የምናጽናናት።
ኢትዮጵያ በደዌ አልጋ ላይ ለሁልጊዜም እያቃሰተች በጭራሽ የምትኖር ሀገር አይደለችም። በመስቀል ላይ ተቸንክራም በጠላቶቿ ጦር እየተጨቀጨቀች በኤሎሄ ለመቃተት ታሪኳና ውቅሯ አይፈቅዱላትም። ትንሣዔዋ እውን የሚሆነው ሞታ በመነሳት ሳይሆን ኖራ በተግባር በማሳየት ነው። ለውስጥም ሆነ ለውጭ አስቆሮታዊና ይሁዳዊ ጠላቶቿ ያልተገለጸላቸው እውነታ ይህ ነው።
ሰሙነ ጸሎትና ምህላ፤
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባዔ ጥላ ሥር የተሰባሰቡ ሰባት የቤተ እምነት አባቶች (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ 7ኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን) ለየምዕመኖቻቸው የጸሎትና የምህላ አዋጅ በማወጅ “ኢትዮጵያን እየተገዳደረ ላለው ሰሙነ ሕማማት” ፈውስ ሲቃተትና ሲጸለይ መሰንበቱ ይታወሳል። ይሄው ጸሎትና ምህላ በሀገሪቱ በርካታ የቴሌቪዥን ቻናሎች መተላለፉም አይዘነጋም።
የጸሎቱና የምህላው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ሚያዝያ 7 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ የተካሄደው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሣህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር።
በመክፈቻውና በማጠቃለያው መካከል በነበሩት ሰባት ቀናት ውስጥ በየቤተ እምነቱ ሥርዓት መሠረት ምህላውና ጸሎቱ በምዕመናኑ ዘንድ በተሰበረ መንፈስ ተተግብሮ ተከናውኗል። ንስሃ፣ ይቅርታ፣ እርቅ፣ ርህራሄና መታዘዝ፣ ተስፋ፣ እምነትና ፍቅር በሚሉ የእያንዳንዱ ቀን ርዕስ ላይ በብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች አማካይነት የተላለፉት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ ጾሎትና ዝማሬዎች “ለኢትዮጵያ የሰሙነ ሕማማት” መከራዎች ከፍ ያለ የመጽናናት በረከት የፈሰሰባቸው ቀናት ነበሩ።
አባቶች እያነቡ ሲማልዱ፣ እናቶች ተደፍተው በጸሎት ሲቃትቱ፣ ልጆችና ወጣቶች ልባቸው ተሰብሮ በንስሃ ሲታደሱ ፈጣሪ ከመንበሩ ላይ ሆኖ እንደሚያደምጥ ጥርጥር አይገባንም። ከመንፈሳዊ ትምህርቶች ጎን ለጎንም በመሪ አባቶችና በየሃይማኖቱ መምህራን ለሕዝቡ የተሰጡት ምክሮች በቀላሉ የሚታዩ አልነበሩም። በአፍቅሮተ የራስ ብሔርና ቋንቋ የተለከፉ ቡድኖች በራሳቸው ወገኖች ላይ እየፈጸሙት ያለው ግፍና ጭፍጨፋ ብድራቱ ለልጅ ልጆቻቸው እንደሚተላለፍና በራሳቸው ላይ የሚቆልሎትን ዕዳም ዝቀው እንደማይጨርሱት በጥሩ መንፈሳዊ ትምህርቶች መልዕክቱ ተላልፎላቸዋል። “እረፉ!” ተብለው ሲገሰጹ የማይሰሙ ከሆነም የልባቸው ድንዳኔ በአናታቸው ላይ የእሳት ፍም እንደሚከምርባቸው የቅዱስ መጻሕፍት አናቅጽ እየተጠቀሱ ማስጠንቀቂያው እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአስደንጋጭ ፍጥነት እየተስፋፋ መሄዱና ከጸሎትና ምህላው በተጨማሪ ምዕመናን ግዴታቸውን እንዲወጡ ተመክረዋል። ለእርቅ የደነደነው ልብ እንዲለዝብ፣ ወገን በወገን ላይ የመዘዘው ሰይፍ ወደ ሰገባው እንዲመለስ፣ መፈናቀልና የንብረት ጥፋት እንዲገታ አባቶች ማልደዋል። የጥፋት መልእክተኞቹ ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲመለሱም አስገንዝበዋል። ለመጻኢው ሀገራዊ ምርጫም ጸሎት ተደርጓል። የየሃይማኖቱ አባቶች አባታዊ ምክራቸውን የለገሱት በበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ነበር።
ይህን ሀገራዊ የጸሎትና የምህላ መርሃ ግብር ወደ ሕዝቡ ለማድረስ ከፍተኛ ትብብር ላደረጉት የግልና የመንግሥት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በእጅጉ ምሥጋና ይገባቸዋል። የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የተወሰኑ አባላት ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጎን በመቆም ያሳዩት የአጋርነት ተሳትፎም በመልካም አርአያነት የሚያስጠቅስ ተግባር ነው። መሰል መርሃ ግብሮች ለወደፊቱም ተጠናክረው ቢቀጥሉ በየጊዜው የሚያገረሸውን የሀገር ሕመም ለመፈወስ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል። ጸሎትና ምህላን የሚሰማ አምላክ “የኢትዮጵያን ሰሙነ ሕማማት” ያሳጥርልን። አሜን! ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013