
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከግሉ ዘርፍ 101 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡ባለፉት ዘጠኝ ወራት 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ትርፍ ማግኘቱንም ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የባንኩን የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈፃፀም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የባንኩ ዋና ትኩረት በሆነው የግሉ ዘርፍ 101 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን የ99 ነጥብ 8 በመቶ ያሳካ ሲሆን አፈጻጸሙ ሲታይ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 99 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ብድርና ቦንድ ለመልቀቅ አቅዶ 67.2 ቢሊዮን ብር መልቀቅ መቻሉን የገለፁት አቶ አቤ፣ በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በነበረው አለመረጋጋት ፈታኝ ቢሆንም በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ ስኬት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
የባንኩ አፈፃፀም ከዋና ዋና እቅዶች ጋር ሲታይ፣ አጠቃላይ ተጨማሪ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 124.6 ቢሊዮን ብር ታቅዶ 102.7 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንና ይህም የእቅዱ 82 ነጥብ 4 በመቶ መሆኑን አቶ አቤ ገልፀዋል፡፡
አቶ አቤ እንደገለፁት፣ አጠቃላይ የባንኩ የግል ተቀማጭ ገንዘብ ክምችት 698 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ከአጠቃላይ የገንዘብ ክምችት 97 በመቶ ድርሻ መያዙን ጠቁመዋል፡፡የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችትም የዚህ በጀት ዓመት ሲጀመር ከነበረው 595 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወደ 698 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ማደጉን ገልፀዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማሳደግ በኩልም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከውጪ ንግድ 216 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እና ከውጪ ሃዋላ ሁለት ነጥብ 13 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል፡፡ባንኩ ከሰጣቸው የተለያዩ ብድሮች 36 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በዘጠኝ ወራት ውስጥ የሰበሰበ ሲሆን በዚህም የእቅዱን 54.5 በመቶ መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አቤ ሳኖ ገለፃ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባንኩ ባከናወናቸው ተግባራት 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ትርፍ አግኝቷል፡፡የባንኩ አገልግሎት ተደራሽነት በማስፋት ረገድ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 62 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት ብር 885.9 ሚሊዮን ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ ችሏል፡፡በጀት ዓመቱ ሲጀመር የተቀማጭ ሂሳቦች ብዛት 25 ሚሊዮን ገደማ የነበረ ሲሆን ተጨማሪ አራት ነጥብ 27 ሚሊዮን አዳዲስ የባንክ ሂሳብ በዘጠኝ ወራት ተከፍተው አጠቃላይ የተቀማጭ ደንበኞቹ ሂሳብ ቁጥር ወደ 29 ነጥብ 37 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
ባንኩ በቀጣይ የሀብት ማሰባሰቡን ዋነኛ አቅጣጫ አድርጎ እንደሚሰራ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፣ የተለያዩ ስትራቴጂክ እቅዶችን በመተግበር፤ የተሰበሰበ የብድር ክምችትን መቀነስ፣ የብድር አሰባሰቡን በማጠናከር የተበላሹ ብድሮችን ከደንበኛው ጋር በመነጋገር እንዲሰበሰቡ ለማድረግ ይሰራል፡፡በዓመቱ መጨረሻም የተሻለ የሂሳብ ሚዛን እንዲኖር ከማድረጉም በላይ የባንኩን የካሽ ፍሰት እጅግ የተሻሻለ እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል ብለዋል፡፡
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013