ብርሃን የመልካም ነገር መገኛ ነው:: በተቃራኒው ጨለማ ደግሞ የክፉ ነገር አብራክ:: በምድር ላይ ያሉ ዓይኖች ሁሉ ብርሃን ይናፍቃሉ..የሁሉም ልቦች ብሩህ ቀንን ይሻሉ:: ምክንያቱም መልካም ነገሮች ሁሉ በነሱ ውስጥ ስለተቀመጠ ነው:: ሕይወት በብርሃን ውስጥ ደስ ትላለች፣ መኖር በተስፋ ውስጥ ያጓጓል:: መልካም ነገር የምንመኝ ብዙዎች ነን ግን መልካም ነገር የት እንደተቀመጠ አናውቅም:: ዝም ብለን የምንፈልግ፣ ዝም ብለን የምንመኝ ነን::
እዚህ ዓለም ላይ ካለ ፍለጋ ካለ ልፋት ዝም ብሎ የሚገኝ መልካም ነገር የለም:: ጥሩ ነገሮች ሁሉ በፍለጋ፣ በብዙ መከራ እንዲገኙ ሆነው የተቀመጡ ናቸው:: የምንፈልገው ነገር የት ቦታ እንደሚገኝ ማወቅ አለብን:: የምንፈልገው ነገር የት ቦታ እንደተቀመጠ ካላወቅን የምንፈልገውን ነገር ማግኘት አንችልም:: ብዙዎቻችን ሕይወትን አልተረዳናትም:: አብዛኞቻችን ጨለማ ውስጥ ተቀምጠን ብርሃን የምንናፍቅ፣ ሳንሰራ መብላትን፣ ሳንለፋ መልካም ሕይወትን የምንሻ ነን:: ለዚህም ነው እስካሁን ድረስ በነጋልን ማለዳ ላይ ጥሩ ነገር ሳንሰራ አመሻሽ ላይ የቆምነው::
ለዚህም ነው የምንፈልገው ነገር አጠገብ ቆመን ሩቅ ቦታ የምንማትረው:: የእስካሁኑን ተዉት..ትናንታችሁ የማይጠቅም ከሆነ ርሱት:: ወደ ነገ..ወደ አዲስ ቀን በሚያሸጋግራችሁ ዛሬ ላይ ናችሁ:: ትናንት ላይ በእውቀት..በአስተሳሰብ የተለያችሁ ብትሆኑ ኖሮ የማትፈልጉት ዛሬ የእናንተ አይሆንም ነበር:: የማትፈልጉት ነገ እንዳይፈጠር በምትፈልጉትና በሚያስፈልጋችሁ ዛሬ ላይ መሆናችሁን ልብ በሉ:: ዛሬአችሁ ያላማረና የማትፈልጉት ከሆነ አሁኑኑ ለመለወጥ ሞክሩ ዛሬ ላይ ደስተኛና የተሳካላችሁ ከሆናችሁ ደግሞ እንኳን ደስ አላችሁ:: ወደ ነገ እየሄድን ነው….ወደ አዲስ ሰማይና ምድር እየቀረብን ነው:: ነጋችሁ ሊወለድ ምጥ ላይ ነው…ነገ የእናንተ ሊሆን ዳዴ ላይ ነው::
ዛሬ የትናንት መልክ እንደሆነ ሁሉ ነገም የዛሬ መልክ ነው:: እኔና እናንተ የቤተሰቦቻችን፣ የጓደኞቻችን ውጤቶች እንደሆንን ሁሉ ነገም የዛሬ ውጤት ነው:: እኛ የሕይወታችን ሰዓሊዎች ነን:: ብሩሹም ቀለሙም በእጃችን ውስጥ ነው:: የፈለግነውን ስዕል ሕይወታችን ላይ መሳል እንችላለን:: ብዙዎቻችን ይሄ አልገባንም ለከሰረ ሕይወታችን ወይ መንግሥትን ወይ ቤተሰቦቻችን አሊያም ደግሞ ሌላ ሦስተኛ ወገንን ተጠያቂ የምናደርግ ነን:: እውነቱ ግን የሕይወታችን አድማቂዎችም አደብዛዦችም እኛ ነን የሚለው ነው:: እርግጥ በዙሪያችን የሚገኙ ሌሎች ሰዎች ለሕይወታችን ብርታትም ውድቀትም የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ:: ይሄ የሚሆነው ግን እኛ ለነሱ በራችንን ስንከፍት ነው:: ይሄ የሚሆነው ግን የሕይወታችንን ቀለምና ብሩሽ ለሌሎች አሳልፈን ስንሰጥ ነው:: ይሄ የሚሆነው ግን ሕይወታችንን አስተሳሰባችንን ለሌሎች አሳልፈን ስንሰጥ ነው::
ባጠቃላይ በእኛ ሕይወት ላይ ሌሎች የበላይ እንዲሆኑ ስንፈቅድ እንደበዝዛለን:: የዛሬ ብርሃናችሁን አጥፍታችሁ የምታበሩት ነጋዊ ብርሃን የለም:: ዛሬን በተስፋ መቁረጥ፣ በከንቱ አሳልፈን ነገን በመልካም የሚያኖር ኃይል የለንም:: እንዳልኳችሁ የምንፈልገውን ቀን የሚፈጥርልን የዛሬው ቀናችን ነው:: በሌላ ቋንቋ ዛሬ የሌለው ነገ አይኖረውም እያልኳችሁ ነው:: ነገ እኮ ከዛሬ ቀጥሎ የሚመጣ ነው:: ነገ እኮ በዛሬ አስተሳሰብ፣ በዛሬ ብርሃን የሚፈጠር እንጂ እንዲያው ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን ተስፋ የምናደርገው ነገር አይደለም:: ዛሬአችን የተሰራው በትናንት አስተሳሰባችን ነው:: የትናንቱ እኛነታችን የዛሬውን ቀናችንን ሰጥቶናል:: ነገ ደግሞ በዛሬ አስተሳሰባችን ይፈጠራል:: በቃ እንደዚህ ነው::
ሌላ ሰዋዊም ሆነ አምላካዊ ቀመር የለም:: ተፈጥሮ በእኛ ቁጥጥር ስር ነው:: በተፈጥሮ ላይ የበላይ ሆነን ነው ወደዚህ ዓለም የመጣነው:: በአስተሳሰባችን መልካሞች ከሆንን የሚያሸንፈን ምንም ነገር የለም:: የውድቀታችን..የተስፋቢስነታችን መነሻም መድረሻም በውስጣችን አዎንታዊ አስተሳሰብ አለመኖር የፈጠረው ነው:: ይሄ ዓለም በአምላክ አስተሳሰብ ተፈጥሯል፤ በእኛ አስተሳሰብ ይቀጥላል:: ብዙ ነገዎች ብዙ ዘላለማት ከፊታችን አሉ:: እልፍ ንጋቶች እልፍ ምሽቶች ይጠብቁናል:: ከትናንትነት ወጥታችሁ የምትፈልጉትን ነገ እንድትሰሩ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁናችሁ ዋጋ አለው::
ሁሉም ነገር በእኛ ቁጥጥር ስር ነው:: በጨለማ እየኖርን የምንፈጥረው ብርሃናማ ነገ የለም:: በቁጭትና በጸጸት እየኖርን አዲስነትን መላበስ አይቻለንም:: አሁኑኑ ተአምራችሁን ፍጠሩ፣ አሁኑኑ ውብ ስዕላችሁን ሳሉ:: አሁኑኑ ከማይጠቅማችሁ ውጡና ወደሚጠቅማችሁ ከነአሁናዊ መንደር አቅኑ:: ተምረው የከሰሩ፣ ኃይልና ጉልበት ይዘው የመከኑ ብዙ ወጣቶች በየከተማው አሉ:: ለምን ሰው እንደሆኑ የማያውቁ፣ ከነመክሊታቸው ከነጸጋቸው በሲጋራና ጫት የደበዘዙ ብዙዎችን አውቃለሁ:: ትናንትን የሚያማርሩ..ዛሬን የሚያኮስሱ በማያውቁት ነገ ላይ የተንጠላጠሉ ነፍሶችም እንዳሉ አውቃለሁ:: ምርጥ አገር በምርጥ አስተሳሰብ ውስጥ ናት:: ድንቅ ማህበረሰብ በድንቅ እይታ ውስጥ ነው:: ማን እንደሆንን ካወቅን፣ ሰውነታችንን ከተገነዘብን ውስጣችን የታመቀ ብዙ ኃይል እንዳለ መረዳት እንችላለን::
የእስካሁኑ ጉዟችን ራሳችንን ባለመገንዘብ የተራመድነው ነው:: ብሩህ ነገ ሊኖረን ግድ ይለናል የአገራችን ብርሃናማ ነገ በእኛ ብርሃናማ ተስፋ የሚፈጠር ነው:: በማሰብ..በማሰላሰል እኛ ከጨለማ እስካልወጣን ድረስ አገራችንም ሆነ ሕዝባችን መልካም ነገን ማየት አይቻለውም:: የእኛ ሰው መሆን፣ የእኛ በዋጋ መኖር ለብዙዎች የተስፋ ምልክት ነውና ራሳችንን ኃላፊነት የሚሰማው ጥሩ ዜጋ አድርገን መፍጠር ይኖርብናል:: ተአምራችንን መፍጠር ካልቻልን ተአምር የሚፈጥርልን ማንም የለም:: የፈጣሪ ዓይኖች እንኳን በልበ ብርሃኖች ላይ ናቸው:: ለራሳችሁ ዋጋ ካልሰጣችሁ መጥቶ ከትቢያ የሚያነሳችሁ የለም:: ዓለማችንን እንደፈለገን አድርገን የምንገነባው እኛ ነን:: የምንፈልገውን ሁሉ መሆን ይቻለናል::
የአሁኑ ነፍስና ስጋችን በትናንትና ማለዳ የተሳለ ነው:: የነገ ነፍስና ሥጋችንም በዛሬ ማለዳችን የሚሳል ነው:: ትናንት ላይ በሆነው ዛሬን እየሆንን ነው:: ዛሬአችን የትናንት እንደሆነ ሁሉ ነገም የዛሬ አብራክ ነው:: ባልተኖረ ዛሬ፣ ተስፋቢስ በሆነ አሁን ላይ ቆመን ታላቅ ነገን መገንባት አንችልም:: ታላቅ ነገ ያለው በታላቅ ዛሬ ውስጥ ነው:: ከሞተ ዛሬ ውስጥ ውጡ:: ከማይረባ አሁን ተለዩ::
ሕይወት አሁን ናት ከአሁን ውጪ የሆነ አንዳች ነገር የለንም:: ለመለወጥም ለመክሰርም ትክክለኛው ጊዜ ላይ ነን:: የፈለግንውን ለመሆን ከሁሉም ምርጡ ቀን ላይ ነን:: ነገ እንዳትሉ ነገ ለእናንተም ለታሪካችሁም ባዳ ነው:: ነገ ምን ዓይነት ቀን ይሆናል ስትሉ አትጨነቁ መጨነቅ ያለባችሁ ለዛሬአችሁ ነው:: ምክንያቱም ቀደም ብዬ እንዳልኳችሁ የነገ ፈጣሪያችሁ እርሱ ነውና:: እየቃማችሁ ከሆነ መቃም ማቆም የምትወስኑበት ጊዜ አሁን ነው:: እያጨሳችሁ ከሆነ፣ እየጠጣችሁ ከሆነ ከሱስ ለመውጣት የዛሬው ቀን ከምንም በላይ ያስፈልጋችኋልል:: ተስፋ ቢስ ከሆናችሁ፣ መልካም ስብዕና ከሌላችሁ የምትፈልጉትን እናንተን ለማግኘት ዛሬ የእናንተ ቀን ነው::
ነገ ላይ ለአገር ወገን ኩራት ለመሆን፣ በኑሯችሁ በትዳራችሁ ኃላፊነት የሚሰማው ለመሆን፣ ከምትፈልጉት የራዕያችሁ ጥግ ለመድረስ ዛሬ የንስሀ ቀናችሁ ነው:: ዛሬ ላይ ጥሩ ሆናችሁ ብቀሉ..ዛሬ ላይ ጥሩ ሆናችሁ ካልበቀላችሁ ነገ ላይ አግድም አደግ የሆነውን እናተን ነው የምታገኙት:: ራሳችሁን ለለውጥ ካዘጋጃችሁ በርካታ የስኬትና የደስታ ዓመታትን መፍጠር ይቻላችኋል:: ወደ ሚደነቅ ነገ እየሄዳችሁ ከሆነ የከሰራችሁበትን ትናንት አታስታውሱት:: በመቆጨት በመብሰልሰል ጀግንነቱን አትንገሩት:: ይልቅ በመርሳት ተበቀሉት፣ ይልቅ በዓለም ላይ ምርጡንና ስኬታማውን እናንተን በመፍጠር አስቀኑት:: ከብልሀት በቀር ከትናንት የምትወስዱት አንዳች ነገር አይኑር::
በአዲሱ የሕይወት ገጻችሁ ላይ አዲስ ታሪክን ለመጻፍ ብዕራችሁን አስሉ:: በማወቅም ባለማወቅም አሁን ላይ ሁላችንም የመረጥንውን ሕይወት እየኖርን ነው:: ከእንግዲህ ባለው ጊዜአችን ግን መርጠን እንጂ ተገደን የምንኖረው ሕይወት መኖር የለበትም:: ፈቅደን ስንኖርና ተገደን ስንኖር ልዩነት አለው:: ልክ የብርሃንና የጨለማ ያክል፣ ልክ የሕይወትና የልደት ያክል ገናና ልዩነት አለው:: ሕይወትን በእኛ ምርጫ ስንኖራት በእኛ የበላይነት፣ በእኛ ፈላጭ ቆራጭነት ነው:: በብዙ ደስታ በብዙ ስኬት ታጅበን ነው:: የፈለግነውን እያገኘን፣ የፈለግነውን እየሆንን በምልዓት ነው::
ሕይወትን ተገደን ስንኖር ግን በተቃራኒው ነው..በእኛ ፍቃድ የሚሆን ምንም የለም:: በሕይወታችን ላይ የሚሆነው ነገር ሁሉ ከእኛ ፍቃድና ይሁንታ ውጪ ይሆናል:: ብዙ ጊዜ የምናማርረውና የእኔ ባልሆነ የምንለው ሕይወት የለም? ያ ሕይወት ከፍቃዳችን ውጪ ተገደን የምንኖረው ስለሆነ ነው:: ሳንፈልገው ተገደን የምንኖረው የሕይወት ዓይነት የለም? ያ ሕይወት በእኛ ፍቃድና ምርጫ ያልሆነ በመሆኑ ነው:: ሕይወት በራስ ምርጫ ስትመራ ደስ ትላለች:: የሕይወት ዋጋው የመኖር ጣዕሙ ያለው ነፃ በሆነ እውነት መኖር ስንችል ነው:: እንዲህ አይነት ህይወት ደግሞ ዝም ብሎ አይገኝም:: መግቢያዬ ላይ እንዳልኳችሁ ጥሩ ነገር የጥሩ አስተሳሰብ ውጤት ነው:: ሁሉም ሰው የአስተሳሰቡን ፍሬ ነው የሚበላው:: በአስተሳሰባችሁ ምርጥ ስትሆኑ ምርጥ ሕይወትን ትመራላችሁ::
በአስተሳሰባችሁ ስትልቁ የላቀ ነገር የእናንተ መሆን ይጀምራል:: በተቃራኒው በአስተሳሰባችን ወደ ኋላ ስንቀር የምንፈልገው ቀርቶ የማንፈልገው ይሆናል:: ሕይወትን ፈቅደን ሳይሆን ተገደን ለመኖር እንገደዳለን:: እኔም ከዚህ እንድትወጡ ነው የምፈልገው….ሕይወትን ካለምርጫ ተገዶ መኖር የሲኦልን ያክል መከራ አለው:: ይሄ እንዳይሆን ማሰብ ጀምሩ:: አሁናችሁ ላይ ግነኑ:: እንደትናንት የምትኖሩት ዛሬ እንዳይኖር:: ከሁሉ በላይ ዋጋ ያላችሁ ሰዎች እንደሆናችሁ እመኑ:: የሰው ልጅ ዋጋ እንዳለው ማሰብ ሲጀምር ኃይሉን ሁሉ ዋጋ ባለው ነገር ላይ ነው የሚያጠፋው::
በነገራችን ላይ ማሰብ ማለት ስለምንበላው ስለምንጠጣው እንዲሁም ደግሞ ስለምንለብሰው ነገር ማሰብ ማለት አይደለም:: ማሰብ ሲመሽ መተኛት ሲነጋ ከአልጋ መነሳት ማለት አይደለም:: ማሰብ እየበሉና እየጠጡ መኖር ማለትም አይደለም:: ብዙዎቻችን ማሰብ ሲባል እንዲህ ይመስለናል:: ማሰብ ማለት ከዚህ አርቆ ማየት ማለት ነው:: ከዛሬ ሸሽቶ፣ ከነገ መጥቆ መመልከት ነው:: እንዲያውም ስለምትበሉትና ስለምትጠቱት አብዝታችሁ የምታስቡ ከሆነ እያሰባችሁ አይደለም ማለት ነው::
ማሰብ በሕይወት ውስጥ ምርጥ የምንሆንበትን ቀመር መፈለግ ነው:: ማሰብ እንዴትና ለምን የሚሉ የሕይወትን መሠረታዊ ጥያቄዎች መመለስ ነው:: ማሰብ ለምን ሰው እንደሆንን..ወደዚህ ዓለም ለምን እንደመጣን ከሁሉም ትልቁን እውነት መፈለግ ፈልጎም ማግኘት ነው:: ማሰብ ራዕይን መኖር ነው፣ ህልምን ምኞትን ማሳካት ነው:: ማሰብ በዓለም ላይ ምርጡን እናተን ማግኘት ነው:: ማሰብ ከትናንት የተሻለን ዛሬ..ከዛሬ የተሻለን ነገ መፍጠር ነው:: ማሰብ እንዴት ለሰው ልጅ ሁሉ አስፈላጊ መሆን እንዳለብን መረዳት ነው:: መግቢያዬ ላይ ዓይኖች ሁሉ ብርሃይ ይናፍቃሉ፣ ልቦች ሁሉ ብሩህ ቀን ይሻሉ ብያችኋለሁ ማሰብ ማለት በዚህ እውነት ውስጥ ራስን ማኖር ሌሎችም እንዲኖሩ መፍቀድ ማለት ነው::
ማሰብ ሚዛናዊ ማንነትን መገንባት፣ በራስ እውነት በራስ ጎዳና ላይ ልክ ሆኖ መቆም ማለት ነው:: ማሰብ ሕይወትን በራስ ምርጫ መምራት ነው:: በልዕልና መኖር ነው:: ማሰብ ስንጀምር መኖር እንጀምራለን:: እውነተኛው መኖር ያለው በማሰብ ውስጥ ነው:: እርግጥ ነው የሚያስቡም የማያስቡም ይኖራሉ…እመኑኝ እውነተኛ ሕይወት በማሰብ ውስጥ ነው:: ብዙዎቻችን ከስኬት ርቀን የምንኖር ነን አንዳንዶች ደግሞ በጥልቅ ማሰብ ውስጥ በስኬት ላይ ስኬትን ደርበው ሕይወትን የሚያጣጥሙ ናቸው:: በብዙ ደስታና በብዙ በረከት ስለሚኖሩ የአንዳንድ ሰዎች ሕይወት በተአምር የተሞላ ይመስለናል:: ግን በሕይወታችን ውስጥ የሆነው ሁሉ በአስተሳሰባችን የተፈጠረ ነው::
ማሰብ ስንጀምር ተአምራቶችን መሳብ እንጀምራለን:: ማሰብ ስንጀምር አስማት በሚመስል ሁኔታ ሁኔታዎች እየተቀየሩ ይመጣሉ..ሕይወትን በደስታ መኖር እንጀምራለን:: በተቃራኒው ማሰብ ስናቆም በሌሎች ተአምራት መደነቅ እንጀምራለን:: በሌሎች ኑሮ፣ በሌሎች ሕይወት መቅናት..ምናለ እሱን..ምናለ እሷን በሆንኩ ስንል መመኘት እንጀምራለን:: በሕይወት ውስጥ ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ ተአምር የለም:: ሁላችንም ማሰብ ከጀመርን ተአምር መፍጠር እንችላለን::
እስካሁን ያስደነቋችሁ ሰዎች፣ በሀብታቸው በዝናቸው በስኬታቸው ያስገረሟችሁ ሁሉ በማሰባቸው የፈጠሩት እንደሆነ ተረዱ:: እናንተም ከመጎምጀትና በሌሎች ከመደነቅ ወጥታችሁ በማሰብ ተአምር ፍጠሩ:: በአገራት መካከል ያሉ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ልዩነቶች በአስማት ወይም በጥንቆላ የተገኙ ሳይሆኑ በማሰብ የተገኙ ናቸው:: እንደዚሁም የእያንዳንዳችን የሕይወት ልዩነትም በአስተሳሰብ የተፈጠሩ ናቸው:: በማሰብ መኖር የላቀ ዋጋ አለው…ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት ብቻ አታስቡ:: ከሁኔታዎች በላይ ገናና ሆናችሁ ቁሙ:: በማሰብ ሕይወትን ማስገደድ ትችላላችሁ::
መቼም ቢሆን እንዲህ እንዳትሉ..ትናንትናዬን ያለፍኩት በብዙ ስህተት ነው፣ ዛሬዬም በብዙ ስህተት የተሞላ ነው..ምንም ዓይነት ብሩህ ነገ አይታየኝም:: ቀጣዩ ቀኔም ጨለማ ነው:: ለመልካም ነገሮች አልተፈጠርኩም..ልክ የሆኑ ነገሮች ሁሉ እኔ ጋ ሲደርሱ ስህተት ይሆናሉ:: የማልጠቅም ሰው ነኝ…እንዲህ ዓይነት አፍራሽ አመለካከቶችን ከውስጣችሁ አስወግዱ:: እንዲህ እያሰባችሁ የምትገነቡት አዲስ ነገ የለም:: ብሩህ ነገ የሚገነባው በብሩህ ዛሬ ነውና:: አበቃሁ ቸር ሰንብቱ::
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2013