ለመኖር ከሚያስፈልጉን መሰረታዊ ነገሮች ዋነኛው ውሃ ነው፤ ውሃ በጣም በርካሹ የሚገኝ ነው፤ በአንጻሩ በቀጥታ ለህይወታችን የማይውሉት እንደ አልማዝ ያሉት የከበሩ ማእድናት ዋጋ ደግሞ በጣም ውድ ነው::
ዋናው እውቀትና ራስን ማወቅ ቢሆንም፣ ዋጋ ሲሰጥ የሚስተዋለው ግን ከአስኳላ ለገዛነው /ለተቀበልነው/ የምስክር ወረቀት ነው:: ለዚህም ነው ታላቁ ፈላስፋ አርስቶትል አስፈላጊ ነገሮች በሙሉ በቀላሉ የሚታዩ እና ርካሽ ናቸው:: ሰው ለአፋላጊዎቹ ሳይሆን በህይወቱ ላይ በቀጥታ አንዳች ነገር ለማይጨምሩት (ያን ያህል አስፈላጊ ላልሆኑት) ጉዳዮች ከባድ ዋጋ ይከፍላል ያለው::
ደስታ በቀላሉ ይገኛል፤ ለዚያውም የማንንም አስተዋጽኦ ሳይፈልግ፣ ከራስህ ከውስጥ የሚፈልቅ ነው:: አንድ በህይወቱ ደስተኛ ያልሆነ ታወሰኝ፤ አውቀዋለሁ:: ሲነጋ ነጋልኝ ሳይሆን ነጋብኝ የሚል ፤ ሕይወትን በእጅጉ የሚያማርር፤ ቁጡ ፤ ከሰዎች ጋር ባለው ተግባቦትም ቀና ያልሆነ…ከራሱ ጋር የተጣላ የሚባለው አይነት::
ታዲያ እንደ ወትሮው ስራ ሊሄድ ማለዳ ከቤቱ ይወጣል፤ ከቤት ሲወጣ ደስተኛ አልነበረም፤ የሚያማርረው ነበረው:: ወደ መስሪያ ቤቱ የሚወስደውን ትራንስፖርት በመያዝ ጉዞ ይጀምራል:: በጉዞው ላይ ችግር ተፈጠረ:: የተሳፈረበት መኪና ከሹፌሩ ቁጥጥር ውጪ ሆና በሚያስፋራ ፍጥነት መጓዝ ትጀምራለች፤ ይህ ግለሰብ እንደዚያ ሲያማርረው የነበረውን ህይወቱን በአደጋ ጊዜ ለማትረፍ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ውስጥ ገባ:: መስታወት በመስበር በመስኮት ዘሎ ይወጣል :: ቀላል ጉዳትም ያጋጥመውና ለተወሰነ ጊዜ ሆስፒታል ለመተኛት ይገደዳል:: ይህ አጋጣሚ ጉዳት ብቻ አድርሶበት አላለፈም:: ያመርረውን የነበረውን ህይወቱን ዋና ጉዳዩ አርጎ እንዲመለከት ማስተዋልን ሰጥቶት አለፈ ::
ይህ ሰው ከዚያች ቀን ጀምሮ ሕይወቱ ይቀየራል፤ ለእያንዳንዱ ቀን ዋጋ መስጠትም ጀመረ::“ይህ ቀን የእኔ ነው” በማለት በክፉ ልማድ የተተበተበውን ህይወቱን ሶስት መቶ ስላሳ ዲግሪ አቅጣጫ በመቀር መኖር ውስጥ ገባ:: ሞኝ በራሱ ብልጥ በሌላው ይማራል እንዲሉ ወዳጄ! ተጎድተህ ከስረህ ከምትማር ከዚህ ሰው ህይወት ተማር፤
እያንዳንዱን አዲስ ቀን መጠባበቅ እና ከፈጣሪ እንደተላከ አዲስ ስጦታ መቀበል በህይወት ውስጥ ደስታን ከሚችሩ ነገሮች አንዱ እና የመጀመሪያው እርምጃ ነው:: ግለሰቦች እና ቤተሰቦች ወደዚህች ምድር ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ:: ህዝቦች እና መንግስታት ይነሳሉ፤ ይወድቃሉ፤ ዓለም ባለችበት ስለሆነች ምንም የሚለወጥ ነገር የለም:: ለማትለወጠው አለም አንተ ራስህን ለምን ታጣለህ፤ ባሻዬ! ባለህ ተደሰት!
ቶማስ ካርላይል የተባለ ደራሲ “ታሪክ ማለት በጊዜ ተውኔት ላይ የሚተመን ፀሐይን ለመብራትነት፣ ዘላለምን ደግሞ ለታሪክ መነሻነት በመጠቀም የሚሰራ ታላቅ ድራማ ነው” ብሎታል:: በዚህ አባባል ለድራማው የሚያስፈልጉት አልባሳት እና ቁሳቁስ ቢቀያየሩም፣ ተዋንያኑ እና የተውኔቱ ጽሑፍ (ምድር) እጅግ አንድነት አላቸው:: ስለዚህ ቡድንም ሀሳብም ይመጣል ፤ይሄዳል፤አገር ግን ትቀጥላለች:: ስለዚህም መጥቶ ለሚጠፋው ቡድንና ሀሳብ አድረህ አገርህን ከማፍረስ ታቀብ:: በጥቂቷ እድሜህ መልካም በመስራት ተደስተህ ማለፍን የመሰለ ነገር የለም::
ያም መጣ ያ ለበጎም ይሆን ለክፉ ወጣቶችን ይፈልጋል፤ ሁሉም ወጣቶችን በሙሉ ሀይላቸው እና ጎልበታቸው በግንባር ቀደምትነት ሲጠቀሙ እንመለከታለን:: ጠቢቡ ሰለሞን ከብዙ የንግስናና የህይወት ጉዞ በኋላ የወጣትነት ዘመኑን መሰረት በማድረግ ወጣቶችን መክሯል:: ወጣቶች ‹‹ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በጋለ ስሜት እና ሀይል በምትፈጽሙበት በዚህ በማለዳ እድሜያችሁ “የጨለማ ቀን” ማለትም እርጅና ሳይመጣ ዋጋ እና ትኩረት ለሚሰጠው ጉዳይ አትኩሮት በመስጠት ጊዜያቸውን ለደስታ እና ለበጎ ስራና ለአገር ጥቅም እንዲያውሉት አስገንዝቧል::
ባሻዬ! በወጣትነት ዘመን ደስታ በቀላሉ ይገኛል፤ ለዚህ ደስታ ዋጋ በመስጠት በልኩ መጠቀም አስፈላጊም ተገቢም ነው፤ይህ ካልሆነ ጠቢቡ ሰለሞን እንዳለው በማለዳ ያጠፋነው በስተኋላ ጉድ እና ችግር ይዞብን ይመጣል፤ ጉድ እና ጅራት ከወደ ኋላ ነው እንደሚባለው:: እንደዚህ ካለ አደጋ ለመዳን የመስሪያ የመሰሪያም ጊዜ አሁን ነው ::
በወጣነት ዘመናቸው ያፈሩትን ሀብት ለኋላ ዘመናቸው ጭምር እንዲሆን አርገው ባለመጠቀማቸው ሳቢያ በጉልምስና ዘመናቸው በእጅጉ የሚቆጩ ሞልተዋል:: ይህን የተመለከተው ማህበረሰባችንም ገንዘብ በሰላሳ ልብ በስልሳ እያለ ይገልጻል:: አስቀድሞ ልብ መግዛት ይጠቅማል፤ ነገሮች ካለፉ በኋላ ትርፉ ቁጭት ነው:: አባባሉ ወጣቶች አሻግረው እንደሚለከቱ ያስገነዝባል:: ይህ እንዳይሆን በወጣትነህ የምታፈራውን ሀብት ለጉልምስናም ለእርጅናም ዘመን እንዲደርስ አርገህ በአግባቡ ተጠቀምበት:: ይህን ማድረግ ከቻልክ ገንዘብን ብቻ ሳይሆን ልብንም በወጣትነት እድሜህ ታገኛለህ::
ወዳጄ! የወጣትነት ዘመንህ የሰጠህን እምቅ አቅም ማለትም ጉልበት እና ኃይል ማንንም ሳታጠፋ፣ ሳትገል፣ ሳታዋርድ … ከእኩይ ስራ ተላቀህ በመልካምነት በመኖር፣ ደካሞችን በማገዝ ደስታ በማግኘትም ለቀጣይ ዘመንህ ስንቅ መያዝ ትችላልህ::
“ልጅነት እና ወጣትነት” የተባሉ የዕድሜ ደረጃዎች አንደኛው የጉብዝና መጀመሪያ ሲሆን ሌላኛው የጉብዝና ወቅት ነው:: እነዚህ የዕድሜ ደረጃዎች ረብ በሌላቸው ነገሮች መጥፋት የለባቸውም:: ምክንያቱም ለረዥሙ የሕይወት መንገድ ስንቅ የሚያዘው በእነዚህ ወቅቶች ነውና::
ማንኛውም ግለሰብ ደስተኛ የጎልማሳነት እና የእርጅና ዘመን ባለቤት ለመሆን ቀድሞ ከልጅነት ጀምሮ ብሎም በወጣትነት ዘመኑ መስራት ያለበትን ሁሉ በአግባቡ መስራት ይኖርበታል:: ያኔ የኋለኛው ዘመኑ ከችግር እና ከአህምሮ ክስ የጸዳ ይሆናል::
ሰው በህይወት ዘመኑ ያለፈባቸውን ልምምዶች፣ ያከናወናቸውን ስራዎችና ያገኘውን ትምህርት በዕድሜው መጨረሻ በሚያከናውነው ተግባር ወይም በሚጽፈው ታሪክ አእምሮውን የሚያሳርፍ ደስታ መፍጠር ይኖርበታል:: በዕድሜው ማለዳ መልካምነትን ሰንቆ ለኩይ ዓላማ ሳይሆን ለመልካም መትጋት ይኖርበታል:: ህይወት አጭር ናት፤ በመሆኑም ለመልካም ነገር አብር ፤ ትጋ!
የልቤ ደርሶ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2013