መንግሥት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ 11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ለመገንባት አቅዶ በ2008 ዓ.ም ሥራቸው ተጀመረ። በግንባታው ሂደትም የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ ታይተዋል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በ2009 ዓ.ም ባደረገው ምርመራ በዩኒቨርሲቲዎቹ ግንባታ ሂደት በርከት ያሉ የኦዲት ግኝቶችን እና ህጸጾችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ምክር ቤቱም ባለፈው ዓመት የቀረበለት የኦዲት ግኝት እንዲስተካከል ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። የኦዲት ግኝቱን ማስተካካያ ከምን ደርሰ ሲል ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቧል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ማብራሪያ ሰጥቷል።
ምክር ቤቱ ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከል የ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በእቅድ መመራት ሲገባው ይህ አለመሆኑ በኦዲቱ ተረጋግጧል። የኦዲቱ ግኝት እንደሚያመለክተው ግንባታዎች በምዕራፍ ተከፋ ፍለው መቼ እንደሚሰሩ አልተቀመጠም። ለካሳና ለግንባታው የሚወጣው ወጪ መቼ እንደሚጠናቀቅም አልታቀደም። የቤተ መጻሕፍት፣ የቤተ ሙከራና የግንባታ ዕቃዎች በእቅድ ተመርቶ ባለመገዛቱ በመማር ማስተማሩ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም ተናብቦ የመስራት ችግር ታይቷል። ስለምን በእቅድ አልተመራችሁም? ከሌሎች ጋር ለምን በቅንጅት መስራት አልተቻለም ሲሉ አንስተዋል። ግኝቱ ስለመስተካከሉም እንዲብራራላቸው ጠይ ቀዋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የግዥ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ደስታ ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ ዕቅድ ቢወጣም በዕቅዱ መሰረት መሄድ አልተቻለም። ለዚህ ዋናው ምክንያት የሚመደበው በጀት ዝቅተኛ መሆን ነው። ለ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በዕቅድ የተያዘው 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ቢሆንም የተፈቀደው 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ነው። ስራውና በጀቱ ባለመጣጠሙ የእቅድ አፈጻጸሙ መጣጣም አልቻለም። ከዚህ በተጨማሪም የግዥ ኤጀንሲ ዕቃዎችን በወቅቱ ገዝቶ አለማቅረብ ለዕቅዱ መፋለስ ሌላው ምክንያት ነው። በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተጠቃሽ ለእቅዱ መፋለስ ሰበብ መሆኑን አብራርተዋል።
ከፍተኛ የግዥ ባለሙያው እንዳብራሩት፤ የዚህ ሁሉ አካሄድ መፋለስ በመስከረም ወር ተማሪዎችን ለመቀበል የተያዘውን ዕቅድ ወደ ታህሳስ አራዝሞታል። አስፈላጊ የሆኑ የምግብና የማደሪያ ቤት ቁሳቁስ ቢሟሉም የቤተ ሙከራ ዕቃዎችን ግን ማሟላት አልተቻለም። በሌላ በኩል፤ ዕቃዎቹን ለመግዛት 450 ሚሊዮን ብር ቢያስፈልግም አጠቃላይ የተፈቀደው ከ200 ሚሊዮን ብር ያልበለጠ መሆኑ ለችግሩ መንስዔ መሆኑን አብራርተዋል። ተማሪዎቹም በአጎራባች ዩኒቨርሲቲዎች የቤተ ሙከራዎች ልምምድ እያደረጉ ናቸው። እኛም በአቅማችን መግዛት የምንችላቸውን ለማሟላት በግዥ ሂደት ላይ ነን ሲሉ አብራርተዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋርም በትብብርና በውይይት ተሰርቷል። ችግሮችም ተቃልለዋል። ሆኖም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች የኃይል አቅርቦት 509 ሚሊዮን ብር ክፍያ ብንፈጽምም በውሉ መሰረት አገልግሎት ሊያቀርብልን አልቻለም ብለዋል።
ምክር ቤቱ በተጨማሪም ለ11 ዩኒቨርሲቲዎች ዲዛይን 9 ሚሊዮን ብር በእቅድ ቢያዝም ኤም ኤች ኢንጅነሪንግ ለተባለ ድርጅት 12 ሚሊዮን 494 ሺህ 751 ሺህ ተከፍሏል። ለዲዛይን ማጣጣምና ቁጥጥር ለሚሰሩ ሰባት አማካሪዎች በዕቅድ 28 ሚሊዮን 600 ሺህ ተይዞ ሳለ 117 ሚሊዮን 668 ሺህ 636 ብር፤ ማለትም ከ89 ሚሊዮን ብር በላይ በብልጫ ውል ተፈጽሟል። የኦዲት ግኝቱም በጥናት ላይ ተመስርቶ አለመሰራቱን ያረጋግጣል። ይህ እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ እንዲብራራለት ጠይቋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ ዲዛይን ለሚሰራው ድርጅት የተያዘው 9 ሚሊዮን ብር ተገማች ዋጋ ነበር። ሆኖም ድርጅቱ ያቀረበው ዋጋ ከሶስት እጥፍ በላይ ነበር። ሆኖም ውይይት በማድረግ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስራት ተስማምቷል። ዝርዝር ዲዛይን በመስራት ለሚያጣጥሙና ለሚቆጣጠሩ ድርጅቶች በጨረታ ተወዳድረው በአንድ ዓመት 28 ሚሊዮን ብር፤ በሶስቱ የግንባታ ምዕራፍ በአምስት ዓመት 117 ሚሊዮን ብር ለመክፍል ነው የስምምነት ውል የተደረገው፤ ይህ በጨረታ በመሆኑ የገበያ ዋጋ ነው። ከዚህ በላይ ግን የመቆጣጠር አቅማቸው ደካማ መሆን እንደሚያሳስባቸው አመላክተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ሌላው በኦዲት ግኝቱ ላይ ተመስርተው የሰነዘሯቸው ጥያቄዎች፤ ለተነሽዎች በህግና በመመሪያ አለመፈጸም ዋና ጉዳይ ነው። በዚህም፤ የካሳ ክፍያው በበቂ ጥናት ላይ አልተመሰረተም። ለደምቢ ዶሎ፣ ለወራቤ፣ ለራያ፣ ለመቅደላ አምባ እና ለቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ካሳ 100 ሚሊዮን ብር በእቅድ ከተያዘው በላይ 215 ሚሊዮን 71 ሺህ 377 ብር ተከፍሏል።
ለራያ ዩኒቨርሲቲ ከ35 ተከፋዮች የመንግሥት ሰራተኞች ናችሁ፤ የዚህ ወረዳ ነዋሪዎች አይደላችሁም በሚሉና በሌሎች ምክንያቶች ክልሉ አጥንቶ ካጸደቀው 7 ሚሊዮን 347 ሺህ 757 ብር 4 ሚሊዮን 49 ሺህ 779 ተቀንሶ መከፈሉ ቅሬታ መነሳቱ። የካሳ ክፍያው ለባለይዞታዎች በግል የባንክ ደብተራቸው መግባት ሲገባው ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን መመሪያ በመጣስ ለ468 ባለ ይዞታዎች በክልሎች የተለያዩ ተቋማት በኩል 79 ሚሊዮን 925 ሺህ 769 ገቢ ተደርጓል። ገንዘቡ እስከ ህዳር 2009 ዓ.ም አልተወራረደም ሲሉ አባላቱ ጥያቄ አዘል አስተያየት አንስተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለባለመብቶች የተደረገው ክፍያ ሰነድ የተሰረዘና የተደለዘ እንደሆነ በኦዲቱ ተገኝቷል። የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ችግሮቹ ለምን እንደተፈጠሩና የተደረጉ ማስተካካያዎችን እንዲያብራሩ ጠይቀዋል።
የ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ጽሕፈት ቤት የምህንድስና ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ሺፋ፤ የሚሰረዙና የሚደለዙ የካሳ ክፍያዎች ሰነዶች በክልሎች የቀረቡ ናቸው። ክልሎች የሚያቀርቧቸው መረጃዎች ትክክል ባለመሆናቸው ስራዎች የሚከናወኑት ሶስትና አራት ጊዜ እየተመለሱ ነው፤ ከዚህም በላይ ባለይዞታዎች ካሳ ከተከፈላቸው በኋላ እንደገና ክፈሉን ብለው ይመጣሉ። ቦታውንም የመልቀቅ ችግር አለ። እነዚህ ሁሉ ለግንባታዎች መጓተት ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
አቶ ሰለሞን በበኩላቸው ክልሎች የባለ ይዞታዎችን ካሳ አጥንተው ሲልኩ ክፍያ ይፈጸ ማል። የሚልኩትም ተቆራርጦ በመሆኑ ለክፍያ አስቸጋሪ ነው። የሚቆራረጠውም ስራው እንዳይ ጓተት በሚል ነው። ክፍያውም ከባንክ ደብተራቸው ውጭ በተለያዩ ተቋማት እንዲገባ መደረጉ እውነት መሆኑን አምነዋል።
ዶክተር ሳሙኤል በበኩላ ቸው፤ የካሳ ክፍያ ትልቅ ችግር ነው። መነሻውም ከክልሎች እስከ ወረዳ ድረስ ካሳን አጣርቶ የማቅረብ ችግር መኖሩ ነው። መሬቱን በነፃ የሚያቀርቡ እንዳሉ ሁሉ በጣም የተጋነነ ካሳ የሚጠይቁም አሉ። ለምሳሌ፤ ለደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የተጠየቀው ካሳ 142 ሚሊዮን ብር ነው። በአጠቃላይ ለ11 ዩኒቨርሲቲዎች የተያዘው የካሳ መጠን ይህንን ያህል አይሆንም። በመሆኑም፤ በ200 ሄክታር መሬት ለመገንባት የተያዘው እቅድ ተከልሶ በ100 ሄክታር ላይ መገንባት ተጀምሯል። ክልሎችና ዩኒቨርሲቲው የሚገነባባቸው አካባቢዎች ቦታ አዘጋጅተናል ዩኒቨርሲቲ ይገንባልን ብለው መንግሥት ወስኖ ወደ ግንባታ ሲገባ ከፍተኛ የመሬትና የአፈፃፀም ችግር እየገጠመው መሆኑን ገልጸዋል።
ለ11 ዩኒቨርሲቲዎች ለእያንዳንዳቸው 20 ሚሊዮን ብር ካሳ ቢያዝም በገቡት ቃል መሰረት አንድም ብር ያልከፈሉ ቢኖሩም፤ ከተያዘው እቅድ እስከ ሰባት እጥፍ ያስከፈሉ ደግሞ አሉ። ክፍያው ከተከፈለ በኋላ ለባለይዞታዎች በወቅቱ ባለመድረሱ መንግሥትን ከህዝብ ጋር ሲያጋጨው መቆየቱንም ተናግረዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ የ428 ካሳ ተከፋይ አርሶ አደሮችን በተመለከተ፤ የትግራይ ክልል የአርሶ አደሮቹ ህይወታቸው ጉዳት ላይ እንዳይወድቅና ቀጣይ ቋሚ ህይወታቸው ማረጋገጥ ስላለብኝ በሚል በቀረበው ጥያቄ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በደደቢት ቁጠባ እንዲገባለት ተደርጓል። የተወሰነው በቋሚነት መንግሥት እንዲያቋቁመው ሲይዘው ቀሪውን እራሳቸው እንዲቆጣጠሩት ተደርጓል። ይህ በክልሉ ጥያቄ የተፈጸመው ነው። የተወሰነውም በከፍተኛ አመራሩ ታይቶ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ከፍርድ ቤት ውርስ፤ ለአቅመአዳም ያልደረሱ ወራሾች ካሳው ወደ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ገቢ መደረጉና ችግሩ ሲፈታ ወራሾች እንዲወስዱ ይደረጋል። አሰራሩ ግን ከመመሪያችን ውጭ ነው ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ከዚህ በተጨማሪ ለዩኒቨር ሲቲዎቹ የሚያስፈልጉ 825 ዕጩ መምህራንን ለማሰልጠን እቅድ ቢያዝም የተሳካው ግን 623 ብቻ ነው። በዚህም በዩኒቨርሲቲዎቹ የመምህር ችግር እንደሚያጋጥም ኦዲቱ ማረጋገጡን ገልጸዋል። ይህንና ሌሎች በኦዲት የተለዩ ግድፈቶችን ለማስተካካል ስለተወሰዱ እርምጃዎች የሚኒስቴሩ yላፊዎች እንዲያብራሩ ጠይቀዋል።
ዶክተር ሳሙኤል በሰጡት ምላሽ፤ የሰብዓዊ ልማት ለማደራጀት ከፍተኛ ውጤት ያላቸውን 10 ሺህ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች ፈተና ፈትነን በመመዘኛው ያለፉትን አንድ ሺህ ተመራቂዎች በሁለተኛ ዲግሪ ለማሰልጠን ወደ ስራ ገብተናል። ሆኖም ከተመለመሉትም ውስጥ በስልጠናው የቀጠሉት 623 ብቻ ናቸው። ይህም በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም በአብዛኛው የሰው ኃይል ፍላጎት የሚያሟላ ነው። ቀሪውን ደግሞ ከገበያ ለመቅጠር እቅድ መያዙን አንስተዋል።
ከዚያ ውጭ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ሰራዎች ተሰርተዋል። የኤሌክትሪክ ችግርና የቤተ ሙከራ ግብአቶችን ለማሟላት ስራዎች እየተከናወኑ ነው። ካሳ ተከፍሎባቸው ያልተለቀቁ ቦታዎችን ለማስለቀቅና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታትም ይሰራል። ሆኖም፤ የበጀትና የአቅራቢ ችግር እየፈተነን በመሆኑም ምክር ቤቱ ትልቅ ድጋፍ እንዲያደርግልን እንፈልጋለን ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ጠይቀዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየትም፤ ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ የማቀድና ከሚመለከታቸውም ጋርም ተቀናጅቶ የመስራት ውስንነት እንዳለበት፤ እንዲሁም የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አለመደረጉን ገልፀው፤ የግለሰቦች የካሣ ክፍያ በወጣው መመሪያ መሠረት በየግል አካውንታቸው ገቢ ሊደረግ ይገባዋል ብለዋል። የግንባታ ፕሮጀክቶችን በተመለከተም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በተገቢ መጠን ውይይት መደረግ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ 11 ዩኒቨርሲቲዎችን ለመገንባት ሲያስብ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በተገቢው መጠን አለመለየቱን፤ ከፌዴራልና ከክልል አካላት ጋር ከፍተኛ የቅንጅት ችግር መኖሩን፤ ከግብዓት ጋር በተያያዘ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ግቢ ሜዳ ላይ ተጥለው ሣር እየበቀለባቸው ያሉ ግብዓቶች እስካሁንም በመኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የካሣ ክፍያዎች በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ሊፈፀም እና ክፍያዎቹ ለባለመብቶቹ መድረሱን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሐመድ የሱፍ በበኩላቸው፤ በኦዲት ግኝቱ የታዩትን ችግሮች በእቅድ መፍታትና ማረም እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ችግ ሮቹ በሌሎች ተመሳሳይ ግንባታዎች እንዳይደገሙ ሚኒስቴሩ በትኩረት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ