መላኩ ኤሮሴ
የሰው ልጆች ህመማቸውን ለሀኪሞቻቸው የማስረዳት አቅም ታድለዋል። ታማሚዎች ማስረዳት ባይችሉ እንኳ ዘመድ ወዳጆቻቸው አስረድተውላቸው ለህመማቸው መፍትሄ እንዲገኝ ጥረት ያደርጋሉ። ዕጽዋት ግን ይህን አልታደሉም። «ደቦ ኢንጂነሪንግ» የተሰኘ አገር በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያ ይህን የዕጽዋት ችግር የሚያቃልል መተግበሪያ አበልጽጓል። በሞባይል፣ በዴስክቶፕ ኮምፒዩተር እና በድረገጽ ላይ ተጭኖ አገልግሎት የሚሰጠው ይህ መተግበሪያ ፎቶ በማንሳት ብቻ የዕጽዋት በሽታዎችን መለየት ይችላል፤ መወሰድ ያለባቸውን መፍትሄዎችንም ያመላክታል።
ሰፋፊ እርሻ ያላቸው ኢንቨስተሮች አፕሊኬሽኑን ከዴስክቶፕ ወይም ከድረ ገጽ ላይ ከድሮን ጋር በማገኛኘት ማሳቸውን የመቆጣጠር ዕድል የሚሰጥ ሲሆን መተግበሪያው የሚከሰቱ በሽታዎችን ቀድሞ የመተንበይ አቅም አለው። በመሆኑም በሽታዎች ሳይከሰቱ ይተነብያል። በትንበያው ላይ በመመርኮዝ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግም አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡
መተግበሪያውን ያበለጸገው በጅማ የሚገኘው «ደቦ ኢንጂነሪንግ» ኩባንያ በጥቅምት 2010 ዓ.ም ጀርሚያ ባይሳ እና ቦኤዝ ብርሃኑ በተባሉ ሁለት ወጣት ኢንጂነሮች የተቋቋመ የተቀናጀ የምህንድስና ዘርፍ የግል ኩባንያ ነው። ሁለቱም ኢንጂነሮች የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተመረቁበት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
ጀርሚያ ባይሳ በቢ.ኤስ.ሲ በኮምፒተር ሳይንስ እና በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዎችን የያዘ ሲሆን በኮምፒዩተር ኔት ወርኪንግ ሁለተኛ ዲግሪውን ሰርቷል። እንዲሁም በፕሮጀክት ማኔጅመንት እና ፋይናንስ ሁለተኛ ዲግሪውን በመማር ላይ ይገኛል። ቦኤዝ ብርሃኑ በኤሌክትሪክና በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘ ሲሆን፣ በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡
የደቦ ኢንጂነርንግ መስራችን ሥራ አስኪያጅ ጀርሚያ ባይሳ ከቦኤዝ ብርሃኑ ጋር የተዋወቀበትን ወቅት እንዲህ በማለት ያስረዳል፤ «ተወልደን ያደግነው በተለያዩ አካባቢዎች ነው። እኔ አምቦ ነው ተወልጄ ያደግኩት። ቦኤዝ ደግሞ የከሚሴ ልጅ ነው። ጂማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም የተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ተማሪዎች ነበርን። የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ በነበርንበት ወቅት ትውውቃችን በዓይን ብቻ ነበር። የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታችንንም እዚያ መማር ጀመርን። ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች በጋራ ሆነው የማህበረሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲሰሩ የሚያመቻች ፕሮጀክት አለው። ፕሮጀክቱ ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የተውጣጡ ተማሪዎችን አንድ ላይ ሰብስቦ የማህበረሰቡን ችግሮች ፈቺ ጥናቶችን እንዲያካሂዱ ያበረታታ ነበር። ከቦኤዝ ጋር የተገናኘነው በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት ነው» ይላል፡፡
ሁለቱም የኅብረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ ቴክኖሎጂዎችን የማበልጸግ ፍላጎት እንዳላቸው ሀሳብ ተለዋወጡ። ሁለቱም የሚማሩበት የትምህርት ክፍል የተለያየ ቢሆንም እየተገናኙ ሀሳብ መለዋወጣቸውን ቀጠሉ። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ደቦ ኢንጂነርንግ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አቋቋሙ። ኩባንያው ሁለቱም በየትምህርት መስካቸው ያላቸውን እውቀት እና ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በጋራ የኅብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ የተነሱ መሆናቸውን ለማሳየትም የኩባንያውን ስም ደቦ ብለው እንደሰየሙት ጀርሚያ ያስረዳል፡፡
ደቦ ኢንጂነርንግ በትምህርት፣ በጤና፣ በትራንስ ፖርት እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች ሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተልጀንስን) ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ የመስራት እቅድ እንዳለው ያብራረው ጀርሚያ፤ ግብርና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነገራቸው ስለሆነ ለግብርና ቅድሚያ መስጠትን እንደመረጡ ይናገራል። በመሆኑም በመጀመሪያም የግብርና ችግር የሚፈታ ቴክኖሎጂ ማበልጸግን እንደመረጡ ይናገራል።
በ2012 ዓ.ም የሰሩት መተግበሪያ ዕጽዋትን ፎቶ በማንሳት በበሽታ መያዛቸውንና አለመያዛቸውን የሚጠቁም፤ መፍትሄዎችንም የሚያመላክት ሲሆን በጅማ አካባቢ በቡና ተክል ላይ የሚስተዋሉ እና አርሶ አደሮችን የሚፈታተኑ በሽታዎችን ለመለየትና መፍትሄ ለመስጠት የሚውል መሆኑን ያብራራል፡፡
ቡና የሀገሪቱ ትልቁ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መሆኑን እና እነሱም ያሉበት ጅማ አካባቢ በቡና ምርት የምትታወቅ በመሆኗ በቡና ተክል ላይ ትኩረት አደረጉ። በቡና ምርት ሂደት ውስጥ ትልቅ ተግዳሮት የሆነው የቡና በሽታ መሆኑን ከዕጽዋት ተመራማሪዎች ያገኙት መረጃ እና ከአርሶ አደሮች ባገኙት መረጃዎች በመመርኮዝ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የቡና ቅጠሎችን ናሙና በመሰብሰብ ምን ያህል እንደተጠቃ፣ የተከሰተውን የበሽታ ዓይነት፣ ቡናውን ምን ያህል እንዳጠቃ፣ መፍትሄው ምን እንደሆነ ያመላክታል ብሏል።
በዚህም ከተለያዩ በጅማ አካባቢ ከሚገኙ የቡና ማሳዎች መረጃ (ዳታ) በማሰባሰብ የተጠቁ ቅጠሎችን ምስል በመሰብሰብ ከዚያም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስን) በመጠቀም የሰሩት በሞባይልና በዴስክቶፕ ላይ መተግበሪያውን በመጫን ሰዎች እንዲጠቀሙ ለማስቻል መተግበሪያውን የማበልጸግ ሥራ እንደጀመሩ ያስታውሳል።
የደቦ ኢንጂነርንግ ተባባሪ መስራች ቦኤዝ ብርሃኑ በበኩሉ እንደሚለው፤ የተጠቁትን ቡናዎች የመለየት ሥራ በትላልቅ የቡና ማሳዎች የድሮን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጭምር የሚከናወን ሲሆን መተግበሪያው ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም መረጃና ምስልን በማቀነባበርና በመተንተን ዕጽዋትን ያጠቁትን በሽታዎች ከለየ በኋላ ለማሳው ባለቤቶች መውሰድ ያለባቸውን መፍትሄዎችን ለአርሶ አደሮች የሚጠቁም ነው።
በሽታውን በመለየትና መፍትሄ በመጠቆም ሂደት ብቻቸውን እንዳላከናወኑት የሚያብራራው ቦኤዝ፤ ከዕጽዋት ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እንደሰሩ ይናገራል። መምህር ጀርሚያና ቦኤዝ እንደሚሉት በጅማና አካባቢዋ የሚገኙ የቡና አምራች ገበሬዎች በዚህ መተግበሪያ ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ አገልግሎቱ በበይነ መረብ ወይም በተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ አማካኝነት በአንድ ጊዜ ወይም በየወሩ በሚደረግ ክፍያ የሚጫን ነው። በአሁኑ ወቅት ለሚያውቋቸው አርሶ አደሮች በነፃ ሰጥተው እየተጠቀሙበት ነው። መተግበሪያው ያለኢንተርኔት ግንኙነት የሚሰራ ሲሆን ለጊዜው በአራት ቋንቋዎች እንዲሰራ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
መምህር ቦኤዝ እንደሚለው መተግበሪያው በአራት ቋንቋች ይሰራል። በእንግሊዝኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛ እና በትግርኛ ነው የተሰራው። ሶማሊኛን ለመጨመር ሂደት ላይ ነው። ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ቋንቋች ውስጥም የተወሰኑትን ለመጠቀም እና አጠቃቀሙን የበለጠ ቀላል ለማድረግም የመጠቀሚያ ቋንቋዎቹን ቁጥር ከፍ የማድረግ፣ መፃፍና ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ደግሞ በድምፅ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት ዕቅድ ይዘዋል።
ማንበብና መረዳት ለማይችሉ ሰዎች ደግሞ በድምፅ የሚያዙትን ነገር የሚሰራ ነው። በ«ቮይስ አሲስታንስ» የሚያዙት ነገር ተረድቶ እንዲሰራ ማድረግ ነው። ለምሳሌ አንድ ገበሬ ማሳው ላይ ሄዶ የሞባይል መተግበሪያውን ከፍቶ ፎቶ አንሳ ሲለው እንዲያነሳለት። ቅጠሉ ጤናማ ነው አይደለም ብሎ ሲጠይቅ መልስ የሚሰጥ ጭምር ነው።» በማለት አብራርቷል።
አሁን ዝግጁ የሆነው መተግበሪያ የጅማ አካባቢ ዳታዎችን በመጠቀም ያዘጋጁት እንደሆነ ያብራራው ቦኤዝ በቀጣይ የይርጋ ጨፌ፣ የሐረር እና የሌሎችንም አካባቢዎች መረጃ በመውሰድ መተግበሪያውን ሙሉ ለማድረግ አስበዋል። መተግበሪያው ሙሉ ከሆነ በኋላ በጎግል ፕሌይ ላይ በማስቀመጥ አርሶ አደሮቹ አፕልኬሽኑን አውርደው እንዲጠቀሙ እንደሚያደርጉ ተናግሯል።
መተግበሪያው እስካሁን ድረስ ፎቶ ብቻ በመጠቀም መረጃዎችን መሰብሰብ በሚችል ሁኔታ የተዘጋጀ ሲሆን አሁን ደግሞ መተግበሪያው ቪዲዮዎችን ጭምር በመጠቀም መረጃ ከሰበሰበ በኋላ እንዲተነትን ለማድረግ እየሰሩ ነው። ቪዲዮ ከበሽታዎች ባሻገር ተባይ እንደሚለይ ቦኤዝ አስረድቷል።
መምህር ጀርሚያ እንደሚለው መተግበሪያው በመጀመሪያ ለአርሶ አደሮች ሲያቀርቡ አላመኑም ነበር። ስለ ሞባይል ስልክ ካላቸው አነስተኛ እውቀት የተነሳ በስልክ እንዴት የዕጽዋት በሽታ መለየት ይቻላል በሚል አርሶ አደሮች ለማመን ከብዷቸው ነበር። የዕጽዋት በሽታ ተመራማሪዎች ጭምር እኛ በላቦራቶሪ ውስጥ ያልቻልነውን እናንተ እንዴት በፎቶ ልትለዩ ትችላላችሁ በሚል ሲከራከሩ ነበር። በመሆኑም ስለመተግበሪያው በአግባቡ ማስረዳት ይፈልግ ነበር።
ከብዙ ማስረዳት በኋላ በጅማ ከተማ አንድ የተማረ አርሶ ተጠቀመው መተግበሪያውም እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አስተያየት ከሰጡና ብዙኃን መገናኛዎች ስለመተግበሪያው፤ ፕሮግራም ከሰሩ በኋላ ብዙ ሰዎች እያመኑ መጥተዋል። የምርምር ማዕከላትም አብሮ ለመስራት ሀሳብ እያቀረቡ ነው። አሁን ብዙዎች እያመኑበት መጥተዋል፡፡
ደቦ ኢንጂነርንግ በሰራቸው የቴክኖሎጂ ሥራዎች የተለያዩ ሽልማቶችንም አሸንፏል። ካገኙዋቸው ሽልማቶችና እና እውቅናዎች የተወሰኑትን ዘርዝሯል። እ.አ.አ በ2019 በዲጂታል ኢኖቬሽን ወይም በቢዝነስ በዲጂታል ኢኖቬሽን ዘርፍ ግሪን ኢኖቬሽን እና አግሪ-ቴክ ሰላም የተሰኘ ሽልማት አግኝቷል። እንዲሁም በ2020 ሜስት አፍሪካ በተሰኘ ውድድር በማሸነፍ እውቅናና ሽልማት አሸንፏል። በተጨማሪም በ2020 ምርጥ ዲጂታል ግኝት በሚል ዓለም አቀፍ ሽልማት እና በተለያዩ የአፍሪካ ደረጃ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ ስሟን ከፍ አድርጓል።
ደቦ ኢንጂነሪንግ በአፍሪካ የፈጠራ ሳምንት 2020 (እ.ኤ.አ.) በአገሪቱ የመጨረሻ ተወዳዳሪ ከሆኑት መካከል አንዱ ነበር። በሞሮጋን ምርምር ኢንስቲትዩት በተዘጋጀው በአፍሪካ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) ወርክሾፕ ላይ በቡና እና በቆሎ በሽታዎች ምርመራ ዙሪያ ከሚገኙት ውስጥ ደቦ ኢንጂነርንግ ምርጥ የቴክኖሎጂ ባለቤት ተብሏል፡፡
የፈጠራው ባለቤቶች እንደሚሉት፤ ሥራቸው አልጋ በአልጋ አልነበረም። የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል። አሁንም የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠማቸው ነው። ከነዚህ ተግዳሮቶች መካከል አብረዋቸው የሚሰሩ ሰዎች ክፊያ መጠየቅ፣ በሌላ በኩል የፋይናንስ አቅማቸው አነስተኛ ስለሆነ መክፈል አይችሉም። በዚህም ምክንያት ከሰዎች ጋር አብረው ለመስራት ተቸግረዋል። ይህም ሥራቸው ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው። ከዚያ ባሻገር ማይክሮ ሶፍት ኩባንያ በስጦታ የሰጣቸው ግዙፍ የመተግበሪያ ማበልጸጊያ ኮምፒዩተር ሥራ የሚያቆምበት ጊዜው እየደረሰ ነው። ከአራት ወር በኋላ ኮምፒዩተሩ ከጥቅም ውጪ ይሆናል። በኮምፒዩተሩ ላይ የተለያዩ የማህበረሰብ ችግሮችን የሚቀርፉ መተግበሪያዎችን እያበለጸጉ ነበር።
ኮምፒዩተሩ አገልግሎት የሚያቆም ከሆነ እነዚያ መተግበሪያዎችም ጭምር ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ የሚሉት የፈጠራው ባለቤቶች፤ ከጥቅም ውጪ የሚሆኑ ከሆነ መተግበሪያዎቹን ዳግም ወደ ሥራ ማስገባትም አይቻልም። እንደገና እንደ አዲስ መስራትን ይፈልጋል። ይህ የሚሆን ከሆነ ብዙ እውቀት፣ ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ በከንቱ ይባክናል። በመሆኑም አቅም ያለው ኮምፒዩተር መግዛት ይፈልጋሉ። ለዚህም መንግሥት እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የፋይናንስና የመሠረተ ልማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በግብርና ላይ እየሰሩ ካለው ሥራ ጎን ለጎን የወባ ትንኝ የሚለይ መተግበሪያ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት የፈጠራው ባለቤቶች፤ ደቦ ኢንጂነሪንግ በተለያዩ ዘርፎች ካሉ ሰዎች ጋር በመሆን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በማስገባት ራሳቸውን እና ሕዝቡን የመጥቀም ህልም እንዳላቸው ይናገራሉ። ትልቁ ህልማቸውም በቀጣይ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ባለቤት መሆን ነው፡፡
የፈጠራ ባለቤቶቹ የሰሩት ቴክኖሎጂ የዕጽዋት በሽታን መለያና መፍትሄ አመላካች ነው፤
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013