አስቴር ኤልያስ
የትኛውም ወገን ተለሳለሰም በአቋሙም ፀና ኢትዮጵያ ከህዝቧ ጋር የደም ትስስር ያህል የጠበቀ ቁርኝት ያለውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛውን ዙር ውሃ ከመሙላት የሚያስጥላት የትኛውም ዛቻም ሆነ ትንኮሳ የለም። ኢትዮጵያ የምታደርገውን የምታውቅ አገር ናት። በምታከናውናቸው ልማቶች ማንም እንዲጎዳ አትሻም። ከእነዚህ ልማቶች አንዱ የሆነው የህዳሴ ግድብም በተፋሰሱ አገሮች የሚያደርሰው የጎላ ጉዳት እንደሌለ ደጋግማ አውስታለች። ይህንንም ጠንቅቀው የሚያውቁት ግብጽና ሱዳን ከትናንት ዛሬ ወደጫፍ የደረሰውና ሊጠናቀቅ ከጫፍ የደረሰው ግድብ ሠላም የነሳቸው ይመስላል። የኢትዮጵያ መልማት የውስጥ እግር እሳት ሆኖ እንደፈጃቸው አይነት ቁጭ ብድግ አድርጓቸዋል። ለምን ይህ ይሆናል? እስከመቼስ ነው ግብጽ በአስገዳጅ ህግ ኢትዮጵያን ጠፍራ ለማሰር የምትናፍቀው? የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትስ በዲፕሎማሲው ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ይኖር ይሆን? የሚሉትንና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ እንዲሁም በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ተደራዳሪ፤ የኢትዮጵያ ኤክስፐርቶች ፓናል ቡድን ሰብሳቢ እንዲሁም በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት ካገለገሉት ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ አድርጎ በሚከተለው መልኩ አጠናቅሮ አቅርቦላችኋል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡– የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከመነሻው ጀምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ሲገጥሙት እንደነበር ይታወቃል፤ ይሁን እንጂ ከዚያ ሁሉ በኋላ አሁን ሁለቱ ተርባይኖች ውሃ በመልቀቅ ማስተንፈሻቸው ስራ ጀምሯል፤ ለመሆኑ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ያለውን የዲፕሎማሲና የውጭ ጫና ሂደት እንዴት ይገልፁታል?
ኢንጂነር ጌድዮን፡– ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በግድቡ ላይ ከተለያዩ አካላት የተለያዩ አስተያየቶችና አቋሞች ሲንጸባረቁ ነበር። የመጀመሪያው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ለሁለቱ አገሮች ግብዣ ተደርጎ ግድቡ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በተመለከተ ለመወያየት ዓለምአቀፍ የኤክስፐርቶች ፓናል ተቋቁሞ ከሶስቱ አገሮች ሁለት ሁለት አባላት ያሉት እና አራት ደግሞ ከጀርመን፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከእንግሊዝ እና ከፈረንሳይ በጥቅሉ አስር ኤክስፐርቶች ለአንድ ዓመት ያህል ስለ ግድቡና ግድቡ ስለሚያደርሰው ተጽዕኖ ሰርተው ሪፖርታቸውን ለሶስቱ መንግስታት አቅርበዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያለው ሁኔታ ሲጤን በሪፖርቱም ላይ የተለያየ አስተያየት ሲሰጥ ነበር። ሶስቱም መንግስታት በሪፖርቱ ላይ የተለያየ አቋም ነበራቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ሆነ በተለያዩ አገራት የዓለምአቀፍ ድርጅቶችም የተለያየ አስተያየት በግድቡ ላይ ሲሰጡ ነበር። እንዲያም ሆኖ በዚሁ በአህጉራችን አፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የመሰሉ ሌሎች ግድቦች ተሰርተዋል። በኃይል ማመንጫነት ይሁን በሌላ መንገድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ግድቦች አሉ። ነገር ግን በግብጽ እና በሱዳን አነሳሽነት ግድቡ በጣም ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው እናም ተጽዕኖም ለማድረግ በሚያመቻቸው መንገድ በጣም ብዙ ስለሰሩ የእኛ ግድብ በዓለም ላይ ካሉ ከሌሎች ግድቦች ሁሉ ይልቅ ውይይት የተካሄደበት እንዲሁም በርካታ ጽሁፍ የተዘጋጀበት አግባብ ባልሆነ መንገድም ተጽዕኖ ለማድረስ ሙከራ የተደረገበት ግድብ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
እንዳልኩሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከህዳሴ የሚበልጡም የሚያንሱም ግድቦች አሉ። ስለዚህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ላይ የመጀመሪያው ግድብ አይደለም። ነገር ግን ግብጽ ግድቡንና የግድቡን ሁኔታ ከጥቅማቸው አኳያ በጣም ከሮ እንዲታይ በማድረጋቸው መሰረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት አስር ዓመታት እንደሚታወቀው ከበድ ያለ የሚዲያ ዘመቻ እንዲሁም ከበድ ያለ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ሲካሄድበት ቆይቷል። ይህ አካሄድ ደግሞ አግባብ ባልሆነ መንገድ የተካሄደ ነው። ይህን ለማስረዳት በኢትዮጵያ በኩል ብዙ ጥረት ተደርጓል።
ለምሳሌ የአስዋን ግድብ ከህዳሴ ግድብ ጋር ሲተያይ የአስዋን ግድብ ከእጥፍ በላይ የሚይዝ የውሃ ይዘት ያለው ትልቅ ግድብ ነው። በሱዳን ውስጥ በራሱ ከአምስት እና ስድስት ግድቦች በላይ መሰራቱ ግልጽ ነው። በሌሎችም አገሮች እንደዚሁ የተለያዩ ግድቦች ተሰርተዋልና ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአባይ ወንዝ ላይ የሃይል ማመንጫ ግድብ በራሷ ተነሳሽነት ራሷ ወጪውን በመሸፈን ለመስራት ባደረገችው ጥረት ብዙ የዲፕሎማሲ እና የሚዲያ ዘመቻ ሲካሄድባት ነበር። ይህም አግባብ ባልሆነ መንገድ ነው ሲካሄድ የነበረው።
ዋናው ግድቡን የሚቃወሙ የግድቡ ምክንያታዊ አሰራር ላይ ዘመቻ የሚያደርጉ አገራት ግድቡ የታችኞቹን አገራት ይጎዳል በሚል ሳይሆን በአመዛኙ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ብድርም ሆነ እርዳታ ሳትፈልግ በመስራቷ ሲሆን፤ ይህ አይነት አካሄድ በራሱ ለአፍሪካ አገሮች ጥሩ ምሳሌ አይሆንም በሚል ነው፤ ሌሎቹም አገሮች ራሳቸውን ችለውና ይህን ምሳሌ ይዘው ራሳቸው ሊሰሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረባቸው የታችኞቹ አገሮች ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ በማይሆን መንገድ የውሃ ጥቅማችንን ይጎዳል በሚል እሳቤ ብዙ ዘመቻ አካሄደዋል።
መነሻው መጀመሪያኑ ኢትዮጵያ ያልተቀበለችው በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገው እኤአ የ1959ኙን ስምምነት ነው። ያንን ኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ባለፉት ሶስት መንግስታት በደብዳቤም ለዓለም አቀፍ ህብረተሰብ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በኩል እንዲሁም በአፍሪካ ህብረትም በኩል ተቃውሞዋን አቅርባለች። ስምምነቱንም እንደማትቀበል የበታች አገሮች በዚያ ስምምነት ላይ ተመስርተው ያደረጉት ስምምነት ለእኛ ወደፊት ለምናደርገው ልማት በምንም አይነት ተቀባይነት እንደማይኖረው በዓለም አቀፉም ህብረተሰብ የታወቀ ነው።
በመሆኑም ይህን ያልተቀበልነውን የውሃ ክፍፍል መሰረት ያደረገ የውሃ ተቃውሞ ነው እየተካሄደ ያለው እንጂ ግድቡ በእኛ ላይ እንዲህ አይነት ተጽዕኖ ያደርሳል ከሚል አኳያ የሚሰነዘር የዲፕሎማሲ ወይም ደግሞ የሚዲያ ዘመቻዎች አሉ። አንደኛ በአቅማችን ስለሰራነው ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ በበታች አገሮች የተደረጉ ስምምነቶችን ስለማትቀበል እና ሶስተኛ ደግሞ በናይል የመጠቀም መብታችንን አሳልፈን ስለማንሰጥ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርላማ ቀርበው ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እደማይጎዳቸው፣ የራሳቸውን ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፤ ይህ ከዲፕሎማሲ አንጻር እንዴት ይታያል?
ኢንጂነር ጌድዮን፡– ከአንድ ሳምንት ቀደም ብለው የሰጡት አስተያየት ወደእውነቱ እየተቃረቡ እየመጡ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ነው። በተለይም ግብጽ በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝና ለእነርሱ ትርጉም ያለው የዓመታዊ ፍሰቱ አስዋን ዘንድ የሚደርሰው ያለመቀየሩ ነው። ነገር ግን በቅርብ ያለው የሮዛሪስ የሱዳን ግድብ ደግሞ የዓመታዊ ፍሰቱ ሳይሆን የቀንና የወር ፍሰቱ የመለዋወጡ ሁኔታ አነስተኛ ግድብ ስለሆነ ዋና የሚሆነው ለሱዳን እሱ ነው ማለት ነው።
በህዳሴ ግድብ አማካኝነት የሚደርሰው ተጽዕኖ በሁለቱ አገሮች ላይ የተለያየ ነው። አሁን ያንን አስተያየት ከሰጡ በኋላ ደግሞ የተቀየረ አስተያየት በሚመስል መልኩ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች እየሄዱ ይገኛሉ። እዚያ ላይ ግብጽ እንደምትጎዳ ሌላ አይነት አስተያየቶች እየሰጡና ገዥ ስምምነት ከሌለ ግድቡ መሞላት የለበትም የሚለውን አቋም እያራመዱ ነው። ስለዚህ አስተያየቶች በየሳምነቱ፣ በየአስራ አምስት ቀኑና በየወሩ ይቀያየራሉ። በኢትዮጵያ በኩል መሆን ያለበት የተያዘውን አቋም በማጽናት መከተል፤ በሚዲያ በሚነገሩ አስተያየቶች ላይ አቋምን የመቀየር አሊያም የማለሳለስ ነገር ሊኖር አይችልም። መሰረታዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ጥቅሞች የሚመሰረቱት በህዝብ ጥቅም ላይና አገሪቱ ባላት ፖሊሲ ላይ ነውና። በእነዚህ በተለያየ ጊዜ በሚነገሩ በሁለቱ አገሮች ባለስልጣኖችና ባለሙያዎቻቸው አሊያም ሌሎች አካላት በሚናገሩት ላይ መሰረት ተደርጎ የአቋምና የፖለሲ ለውጥ አይደረግም። ስለዚህ የተያዘውን የድርድር መንፈስና መርህ ተከትሎ የሚሄድ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ አቋሟን አሁንም አጠናክራ መቀጠሏ እውን ሆኖ ሳለ በግብጽ በኩል ግን አሁን አሁን የአቋም መዋዠቅ አይታይባትም?
ኢንጂነር ጌድዮን፡– አስቀድሜ እንዳልኩት ነው፤ የአቋም መዋዠቆች ይታያሉ። በእያንዳንዱ ወቅት የሚደረጉ መዋዠቆች ደግሞ ከበስተኋላው ምን አለ የሚለውን የውስጥም ፖለቲካ አካባቢን መቃኘት ያስፈልጋልና አንዳንድ ጊዜ በስራ ኃላፊዎች በበታች አገሮች የሚደረጉ የሚዲያ መግለጫዎች መሰረታቸው ምን እንደሆነ ማጥናትም ያስፈልጋል።
የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአገራቸው ፓርላማ ያደረጉት ገለጻ በቴክኒክ ላይ ተመስርቼ ነው ይህን የማደርግላችሁና የውሃ ሙሌቱ ምንም ጉዳት አያደርስም፤ ለሚደርሰውም ጉዳት ተዘጋጅተናል ነው ያሉት። ይህ በእኔ በኩል ጥሩ አቋም ነው። መዘጋጀታቸውም ጥሩ ነው። የግድቡ የውሃ ሙሌት ጉዳት አለማድረሱንም ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ መግለጻቸው ጥሩ ነው። ይህ ደግሞ ወደኋላ ተመልሶ የሚካሄድ ነገር አይደለምና በሚቀጥሉት ውይይቶች ላይ ሊነሳ የሚችል ሐሳብ ነው። በድርድርም ቢሆን ይነሳል።
እንደእርሳቸው ያሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሚያደርጓቸው ገለጻዎች እንደቀላል የሚታዩ አይደሉም። በኤክስፐርት ደረጃ እንደምናደርገው ሳይሆን በከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ ያሉ አካላት የሚናገሯቸው ነገሮች ትርጉም ብሎም መሰረት ያላቸው በመሆናቸው እነዚህ ጉዳዮች በድርድርም በሚደረጉ ውይይቶችም የሚነሱ ነው የሚሆኑት።
ዋናው ነገር መግለጫ የተሰጠው በምን ደረጃ የሚለው ነው። እኚህ የግብጹ ሚኒስትር በአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና በድርደሩም ውስጥ የሚመሩ ሰው ናቸው። ስለዚህ ያንን ባሉበት አፍ ደግሞ ተመልሶ ሌላ ነገር ለመናገር አስቸጋሪ ነው የሚሆንባቸው። በተለይ በአመራር ደረጃ ባሉ አካላት የሚነገሩ ነገሮች በዓለም አቀፍ ልምድም እንደ ፖሊሲና እንደአገር አቋም ነው የሚወሰደው። የአገር መሪዎች የአገር ከፍተኛ ባለስልጣናት በማንኛውም የሚናገሩት ነገር እንደአገር አቋምና እና እንደ አገር ፖሊሲ ነው የሚቆጠረው። ስለዚህ ወደኋላ ተመልሶ ይህንን ለመቃወምና እንደገና ሌላ አቋም ለመውሰድ አስቸጋሪ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ኢትዮጵያ ውሃ ሙሌቱን ለማካሄድ የሚያግዳት ነገር እንደሌለ በተደጋጋሚ ስትገልፅ ነበር፤ ለመሆኑ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በዲፕሎማሲው ላይ ምን አይነት እንድምታ ይኖረዋል?
ኢንጂነር ጌድዮን፡- የግድብ አሰራር በተለይ እንደ ህዳሴ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት የሚመራት እቅድ አለው። እናም የግድቡ ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ነው። ከፍተኛ አመራር የሚሰጥ ቦርድ አለው። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደግሞ በቅርብ የሚከታተለው ነው። ስለዚህ የስራ ሂደቱ እንዲያም ዝም ብሎ የሚቀያየርና ሁኔታዎች በተለዋወጡ ቁጥር ይህን ትልቅ እቅድ በሁኔታዎች ካልተገደደ በስተቀር ፕሮጀክቱ በጣም ትልቅ በመሆኑና በጣም ትልቅ ኮንትራት እንዲሁም በጣም ትልቅ ገንዘብ ኢንቨስት የተደረገበት በተጨማሪም የውጭ አማካሪዎችና የስራ ተቋራጮች ያሉበት እንደመሆኑ የስራ እቅዱ የሚቀያየር አይደለም። ይህ ፕሮጀክት የሚመራውም በተፈረመው ኮንትራት መሰረት ነው።
ስለዚህ የመጀመሪያው ሙሌትም እንደሚታወቀው ጊዜውን ጠብቆ በተያዘለት እቅድ መሰረት ነው የተካሄደው። ከዚያ በኋላ ደግሞ ስራው ቀጥሎ የሁለተኛው ሙሌትም እንዲሁ በተያዘለት እቅድ መሰረት ነው የሚካሄደው። ይህ አንደኛ የግንባታውን ሂደትና የግንባታውን ቅደም ተከተሉን ይዞ ነው የሚሄደው።
ግድቡ ብዙ ክፍሎች ነው ያሉት። ሲቪል ስራዎች፣ የኤሌክትሮሜካኒካል፣ ስራዎች፤ የብረታብረት ስራዎች፣ የኤሌክትሪክ፣ የመንገድ ስራዎች፣ የሰራተኛ ካምፕ፣ የደን ምንጠራ ስራ፣ ከአካባቢ የተነሱ ሰዎችን የማስፈር ስራዎች አሉት። በተለይም የኤሌክትሮሜካኒካልና የኤሌክትሮስቲል ስራዎቹ በጣም ከባድና በአዲስ ኮንትራክተሮች የተያዙ በመሆኑ እያንዳንዱ እቅዱን ጠብቆ ካልሰራ እነዚህ የተለያዩ ስራ ተቋራጮች ተቀናጅተው ካልሄዱ ስራው ስለሚስተጓጎል የዚህን ስራ አሁን አዘግይቼ የሚለው ነገር የሌሎችን ስራዎች የሚያስተጓጉል በመሆኑ እንዲሁ በቀላሉ አንዱን ተግባር ዛሬ አስተላልፎ ሌላውን ተግባር እንዲህ አድርግ የሚባል ተጽዕኖ ሊደረግበት አይችልም። ምክንያቱም ያንን ተከትሎ መሰራት ስላለበት ነው።
ይህ ሁለተኛው ሙሌት የሚደረገው ድርድሩ ውስጥ ያ ጉዳይ ነው። ይህ ስምምነት ያለበት ነው። እኤአ በ2018 እነዚህ ሶስት ሚኒስትሮች ያሉበት ኮሚቴ የውጭ ጉዳይ የውሃና የደህንነት ሚኒስትሮች ያሉበት የሶስቱ አገሮች በወሰነው መሰረት 15 ውሃ አዋቂዎች ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽና ከሱዳን አምስት አምስት ያሉበት ነው። እሱ ተቋቁሞ የሰራው ሰንጠረዥ ነው። ይህም ማለት የአሞላል ሂደት ማለት ነው። ይህም የአሞላል ሂደት በሶስቱ አገሮች ስምምነት የተደረገ ነው።
በመጀመሪያ ዙር 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ እንደሚሞላ፣ ቀጥሎ ደግሞ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ ቀጥሎ ደግሞ 10 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ ቀጥሎ 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ እያለ በአራት ደረጃ ያስቀመጣቸው ጉዳዮች ስምምነት ላይ የተደረሰበት ነው። ይህ በረቂቅ ስምምነቱ በኢትዮጵያ፣ በግብጽም በሱዳንም በድርድሩ ሰነድ ውስጥ አለ። ይህ ማለት እንግዲህ በአዋቂዎቹ ማለትም መንግስት በሰየማቸው በሶስቱ አገሮች መንግስታት በሰየሟቸው የተሰራ የሙሌት ሂደት በረቂቅ ውስጥ ያለ ከመሆኑም በላይ የተስማሙበት ነው። ስለዚህ የሚደረገው ሁለተኛው ሙሌት ሶስቱም አገሮች የሚያውቁት በዚያው ሰነድ ላይ ደግሞ በሐምሌ፣ ነሐሴና ዝናቡ ጥሩ ከሆነ በመስከረም ይቀጥላል የሚል ስምምነት ውስጡ አለ። በመሆኑም ሰንጠረዡ ላይ ውሃ መቼ በምን አግባብ እንደሚሞላ ሶስቱ አገሮች የተስማሙበት ተቀምጧል። ስለዚህ እሱ ከግንባታ እቅዱ ጋር በተጣጣመ መልክ እየሄደ ነው ያለው።
አሁን የሁለቱ አገሮች የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ስምምነት ከሌለ ብለው የሚሉት ምንም ምክንያትና መሰረት የሌለው ነው። ምክንያቱም ቀደም ሲል በእነዚህ ላይ ስምምነት የተደረሰ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ይህንኑ ተከትላ ነው እየሰራች ያለችው። በአሁኑ ሰዓት በሱዳን በኩል 20 ሚሊዮን ህዝብ ይጎዳብኛል የሚል ጩኸት አለ። እሱ ከሆነ ለምንድን ነው 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በሁለተኛው ዙር ውሃ ይሞላል የሚለውን ባለሙያዎቹ የሰሩትን ሰነድ የተቀበልነው። ምክንያቱም እሱ ሰነድ በሚኒስትሮች ደረጃ ተቀባይነት ያገኘና ረቂቅ ስምምነት ውስጥ የገባ ነው። የሚሞላው ቁጥር ሶስቱም አገሮች የተስማሙበት ነው። መቼ እንደሚሞላም ሶስቱም አገሮች የተስማሙበት ጉዳይ ነው።
ስለዚህ አሁን የሚያነሱት ተቃውሞ በሁለተኛው ሙሌት ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ነው። እናም እንዳልኩት በግንባታ እቅዱ መሰረት ቅድም እንደተጠቀሰው ሁለቱ የበታች ማስተንፈሻ ቱቦዎች በራቸው ሙሉ በሙሉ ስለተሰራ በራቸው ተከፍቶ አሁን ውሃው ከባህር በላይ ካለበት እና 165 ሜትር ላይ ካለው ቁመት በሶስት ሜትር ዝቅ የማድረግና መሃል ላይ ያለው የውሃ ማስኬጃ አሁን የሚፈስበት ማለት ነው እሱን ነጻ ለማድረግ በሶስት ሜትር ወደታች ዝቅ ለማድረግ ነው። የኮንክሪቱ 560 ሜትር ላይ ነው ያለው፤ ያንን በሶስት ሜትር ዝቅ ስናደርግ ከኮንክሪቱ ጫፍ 557 ሜትር ላይ ይሆናል ማለት ነው። ያ ሶስት ሜትር ኮንክሪቱን ለሚሰሩ ሰዎች አርማታውን ለሚያስገቡ ሰዎች የስራ ቦታ ይሰጣቸዋል ማለት ነው።
ስለዚህ ግብጽና ሱዳን ግድቡ ጉዳት ያደርስብናል የሚሉት ነገር ቴክኒካዊ መሰረት የሌለው ነው። የአፍሪካንም ሚና ሁለቱ አገሮች ወደሌላው የመውሰዱ አግባብነት የሌለው ነው። እንደሚታወቀውም ግድቡ የዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ሰላም የሚያናጋ አይደለም። ምክንያቱም ወደተባበሩት መንግስታት የሚወሰዱ ነገሮች ጸጥታን የሚያናጉ ጉዳዮች ሲሆኑ ነው። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን በጀመርነው የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካ መድረክ ነው የምናቀርበውና ውጤት አያመጣም ማለቱ ተገቢ አይሆንም።
በቅርቡ ማለትም ወደነሐሴ መጨረሻ አካባቢ እንደተባለው ወይም ከዚያ በኋላ እንደግንባታው ሂደት ሁለቱ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ይጀምራሉ። ስለዚህ ጊዜ በማንኛውም ጊዜ ቀደም ብለው የሚያገኙትን ውሃ ወይም ደግሞ ከዚያ ከፍ ያለ ውሃ የበታች አገሮች ያገኛሉ ማለት ነው። ስለዚህ ተጽዕኖ ያደርስብናል የሚለው አባባል ቴክኒካዊ መሰረት የለውም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በሃገር ውስጥ እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?
ኢንጂነር ጌድዮን፡- እኔ በግሌ እንደማንኛውም ኢትዮጵያ በውስጥ ያለን አለመረጋጋት ለሁላችንም እንደስጋት የምንቆጥረውና ሁላችንም ተባብረን ማቆም እንዳለብን ይሰማኛል።
በማንኛውም መልኩ የውጭ ኃይልን ለመቋቋም የሚቻለው የውስጥ ጥንካሬና አንድነት ሲኖር ነው። የውስጥ ጥንካሬና አንድነት በሌለበት ሁኔታ በተለያየ መልክ ኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ ተቋውሞዎችን ለመቋቋም በጣም አስቸጋሪ ነው። እናም ኢትዮጵያ እንደህዳሴ ግድብ ያሉ ሌሎችንም ትልልቅ ፕሮጀክቶች በምትሰራበት ወቅት ይህንንም በሌሎች ተፋሰሶች ለማስፋፋት ሌሎችን ፕሮጀክቶችን መስራት ባለብን ወቅት ምልክቱ ይህንን ትልቅ ግድብ መስራታችን ነው። ሌሎቹ ከዚያ ያነሱ ነው የሚሆኑት። እነዚያን ለመስራት የውስጥ ጥንካሬ ያስፈልገዋል። እናም በውስጣችን አለመረጋጋት መኖሩ በጣም የሚያሳስብ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ቅድሚያ የሚሰጠውና መስጠትም ያለበት ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደህንነት ነው። እያዳንዱ ኢትዮጵያዊ በህገ መንግስቱ ውስጥም እንዳለው በህይወት የመኖር መብት ነው። የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ህይወት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ ካልቻልን ሌላ ትልቅ ነገር ለመስራት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው የሚፈጠረው።
ሁላችንም ላይ ያለው አሳሳቢ ሁኔታ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ያሉ ኢትዮጵያውያን ደህንነት በመጀመሪያ መጠበቅ መቻል ነው፤ ምክንያቱ መቅደም ያለበት በመጀመሪያ ደህንነት ነው። በመጀመሪያ ሰው በህይወት የመኖር ተስፋ ሊኖረው ይገባል። ምክንያቱም ሰው በህይወት የመኖር ተስፋ ሲኖረው ነው ልማቱ ትርጉም የሚኖረው።
የውጪን ተጽዕኖ ለመቋቋም በመጀመሪያ የውስጡን ማረጋጋትና አሁን ያለውን ሁኔታ መለወጥ ያስፈልጋል። ይህ የግሌ አስተያየት ነው፤ ደግሞም የሁሉም ሰው አስተያየት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ መቀየር አለብን።
በልማት በኩል ያለው ነገር ጥሩ ጅማሮ ሆኖ ሳለ ነገር ግን በሰው ደህንነትና በህይወት የመኖር ተስፋ የሚያጨልሙ ሁኔታዎችን መቀየር ያለብን ይመስለኛል። እንደሱ ካልሆነ የምንሰራው ልማት ትርጉም አይኖረውም።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ ምሁራን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ነው፤ በዚህ ላይ ድርድር ማድረግ ተገቢ አይደለም፤ ስለዚህ ከመነሻም ለድርድር እድል መሰጠት አልነበረበትም ይላሉ፤ ለመሆኑ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሚኖር አለም አቀፍ ስምምነት ከዚህ አንጻር ምን ይላል?
ኢንጂነር ጌድዮን፡– የዓለም አቀፍ ህግ ኢትዮጵያ ሀብቷን እንዳትጠቀም የሚከለክል ሁኔታ የለም። ኢትዮጵያ አይደለችም ማንኛውም አገር በሉዓላዊ ክልሉ ማልማት የሚከለክል ህግ የለም። ይህን ደግሞ በአይናችን የምናየው ነው። ለምሳሌ ሱዳን ውስጥ የሚደረገውን ልማት እናያለን። እንዲሁም ግብጽ ውስጥ የሚደረገውንም ልማት እናያለን። በግብጽ ውስጥ የዛሬ 50 እና 60 ዓመት ገደማ የተገነባው ግድብ ከእኛ የበለጠ ነው። ግብጽ ውስጥ ወደ አራት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት አልምተዋል።
ከአባይ ተፋሰስ ውጭ ወደ ቶሺካ ወንዙን አስወጥተው በረሃማ ወደሆነው ስፍራ ወስደው ብዙ ሐይቆች ሰርተዋል። አባይን ከተፈጥሮ ተፋሰሱ ውጭ በቀይ ባህር ስር አሾልከው ወደሲናይ በረሃ ወስደው አልምተዋል። በተመሳሳይም ሱዳኖችም አምስት ስድስት ያህል ግድቦችን ሰርተዋል። እነሱም ቢሆኑ ከሁለት ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ አልምተዋል። ይህ ደግሞ በአይን የሚታይ ነውና ኢትዮጵያ ከእነሱ ሊጠጋጋ የሚችል ልማት ቀርቶ ገና ምንም አላለማችም። በተለይ በመስኖ በኩል።
አባይ እነሱ ብሉ ናይል በሚሉት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ የሚለማ አለ። ባሮ አኮቦም ተከዜም እንዲሁ እና በሌሎችም ተፋሰሶች መስኖ ለማልማት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ስላሉ እነሱን ማልማት ነው፤ እነሱን አታልሙ የሚል ህግ የለም።
ናይል የእኛ ነው ብለው መቶ በመቶ ተስማምተው ለመውሰድ ሲሞክሩ የዓለም አቀፍ ህብረተሰቡም ዝም ብሎ ማየቱ ብሎም አለማውገዙ በእጅጉ ይገርመኛል። እንዴት 86 በመቶ ውሃ እያዋጣን የሚገባችሁ ዜሮ ነው ብለው ለሚከራከሩ ወገኖች ድጋፍ ሲሰጡ ምንድን ነው ያለው ሁነት፤ ይህ የማይታይ ሆኖ ነው ወይ? ይህ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ምስጢር ነው?
ለምሳሌ አሜሪካ ኮሎራዶ ውስጥ ሜክሲኮና አሜሪካ ውሃ ይከፋፈላሉ። አሜሪካ እንደበላይ አገር 95 በመቶውን ወስዳ ከአምስት እስከ 10 በመቶ የሚሆነውን ነው ለሜክሲኮ የምትለቀው። ወደቱርክና ወደሌሎች አገሮች ብንሄድ የበላይ አገር ሆነው የውሃ ባለቤት ሆነው ውሃ የላችሁም የሚባልበት ኢትዮጵያና የናይል ወንዝ ብቻ ነው። ሁሉ ነገር ግልጽ ሆኖ እያለ የዓለም አቀፍ ህብረተሰቡስ ይህንን ማውገዝ እንዴት አቃተው? የዓለም አቀፍ ትልልቅ ሚዲያዎች በተቃራኒው ቆመው ስለግብጽ ህዝብ መጎዳት ብቻ ሲያወሩ ነው የሚሰማው። በመሆኑም ያለው ሁኔታ አሳዛኝም ነው። ሞራልም የሌለበት ነው። ስለሆነም ይህን አይነቱን አካሄድ መፍቀድ የለብንም፤ በያዝነው አቋም መጽናት አለብን። ህዝብም ይህንን መብቱን ማስከበር መቻል አለበት። ተደራዳዎችም ይህንን ትልቅና ቀይ መስመር የሆነውን ጉዳይ ማለፍ የለባቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብ በወንዞቹ የአሁኑ ትውልድና የሚመጣው ትውልድ የመጠቀም መብቱን ማስከበር ትልቅ ዓላማና ትልቅ አቋም ነው፤ ይህንን ይዞ መሄድ ያስፈልጋል። ይህ ያልተስተካከለና ፍትሃዊ ያልሆነውን አካሄድ ጠንክሮ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ማስረዳትና የያዙትን አቋም እንዲለውጡ ማድረግ ያስፈልጋል። መሄድ ያለብን በዚያ መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በአለም ላይ ከ250 በላይ ድንበር ተሸጋሪ ወንዞች አሉ፤ ለመሆኑ በነዚህ ላይ የተካሄዱ የልማት ስራዎችም ሆኑ በተጋሪ ሃገራቱ መካከል ሲደረጉ የነበሩ የድርድር ሂደቶች ምን ይመስላሉ?
ኢንጂነር ጌድዮን፡– በወሰን አለፍ ወንዞች ላይ የሚደረጉ ድርድሮች የትም አካባቢ ብንሄድ ረጅም ጊዜ ይፈጃሉ። ምክንያቱም አገሮቹ የየራሳቸውን ጥቅም አሳልፈው ላለመስጠት ብዙ እሰጣገባ ውስጥ መገባቱ አይቀርም። ይህ ሁሉ ማለትም በሕንድ፣ በፓኪስታንና በሌሎችም የወሰን አለፍ ወንዞች ባሉበት ሁሉ ካናዳ-አሜሪካ፣ አሜሪካ-ሜክሲኮ እንዲሁም በአፍሪካም አገሮች በተለያዩ አገሮች እንዲህ አይነቱ ነገር ያጋጥማል። ነገር ግን መጨረሻቸው ጦርነት አይደለም።
በግብጽና በሱዳን በኩል ወደጦርነት እንሄዳለን የሚለው ጩኸት መቼም ቢሆን የአንድን የበላይ አገር በኃይል አስገድዶ የውሃ መብትን ማስከበር አይቻልም። ይህ ግልጽ የሆነ ሁኔታ በመሆኑ መረዳት ያለባቸው ይመስለኛል። በየትም በኩል የበላይ አገርን ቅኝ ግዛት አድርጎ ለማስገደድ ካልሆነ በስተቀር በምንም መልኩ በኃይልና በጦርነት እንዲሁም የሰው ግድብ በማፍረስ በዚህ አይነት የሚከበር የውሃ መብት የለም። የትምም ተደርጎ አይታወቅም። ስለዚህ ከእንዲህ ያለ ቅስቀሳ እና ከእንዲህ ያለ አቋም መቆጠብ ያለባቸው ይመስለኛል።
ምክንያቱም በአንድ አገር በራሱ ሀብት ላይ ጥቃት ሲደርስበት የመከላከል መብቱ የተጠበቀ ነው። ይህንን ማወቅ አለባቸው፤ ማንም ቢሆን የራሱን ህዝብ ውሃ እያስጠማ ለሌላው የሚቆምበት ሞራልም የለውም። በሌላም አገር እንዲህ ያለ ነገር የለም።
እናም በዚህ በዲፕሎማሲና በሚዲያ ጩኸት ብዛት የአንድን አገር መብት ለመንጠቅ የሚደረገው አካሄድ አይበጀንም። ለሶስቱ አገሮች የሚበጃቸው ተባብረንና አንዱ የሌላውን መብት አክብሮ ልማት ለማካሄድ እንችላለን የሚለውን ማየት ነው።
ይህ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ለሶስቱም አገሮች ይጠቅማል፤ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ኢነርጂ ሲያያዝና ሲቀናጅ አንዱ ዘንድ በማያስፈልግበት ጊዜ ወደሌላው፣ ከሌላው ወደሌላ እየተባለ ነው የሚከናወነው። አውሮፓ ውስጥም የምናየው ይኸው ነው። ከአንዱ የሚመነጨው ኃይል በማያስፈልግበት ጊዜ ወደሌላ ይሄዳል። ይህ አይነቱ አካሄድ የኢነርጂንም ዋጋ ይቀንሳል። እንዲሁም እንዳይቆራጥ ያደርጋል። አንዱ ዘንድ ያለው አመቺ ሁኔታ ለሌላው ጥቅም የሚሰጥበት ሁኔታ አለ። ስለዚህም ተባብሮ መሥራቱ ላይ ነው ጥቅም ያለው እንጂ አንተ መብት የለህም የሚባለው ክርክር የሚያዋጣ አይደለም። ይህ በዓለም አቀፍም ህግ የሚደገፍ ስላልሆነ ኢትዮጵያ መጠቀሟን ትቀጥላለች፤ ታለማለችም። መስኖም ታለማለችና ለምን ኢትዮጵያ ታለማለች የሚለው ክርክራቸው የሚገርም ክርክር ነው።
የእኛ ህዝብ በአባይ መነሻ ላይ በ80ዎቹ በመጣው ረሃብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። በዚያን ጊዜ ግን አንድም ግብፃዊም ሆነ ሱዳናዊ አልሞተም። በግድቦቻቸው የማጠራቀም ችሎታ ነበራቸው። ስለዚህ ያንን አስከፊ ረሃብ አንድም ሰው ሳይሞትባቸው ነው የተሻገሩት። ይህንን እያየን አትልሙ የሚለው ነገር በጣም አስገራሚ ነው። የሚያሳዝንም ነው፤ ነገር ግን ማልማታችን ይቀጥላል። ይህንን ምንም አይነት ኃይል ሊያቆመው አይችልም። መተባበሩ ነው ለሶስቱም አገሮች የሚጠቅመው።
መቼም ሰው ሶሪያ፣ የመንና ሊቢያን እያየ ወደእዚያ እንግባ ማለቱ ከበድ ይላል፤ ምክንያቱም የግጭት እሳቱ የሚለበልበው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነው። ስለዚህ ይህ አጥፍቶ የመጥፋትና ህዝብ ላይ ጉዳት የማድረስ የእልህ አካሄድ ለህዝብም ለአገራትም አይጠቅምም። ስለዚህም አገር የሚመሩ ሁሉ ህዝባቸውን ወደስምምነት የመግፋት እንጂ በኃይል ልማትን እናስቆማለን የሚለው አካሄድ አዋጭ አይደለምና ከዚያ መቆጠቡ ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚነሱት የ1902 እና የ1959 የሱዳንና የግብፅ ስምምነቶች ናቸው፤ እውን እነዚህ ስምምነቶች ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ናቸው ማለት እንችላለን? ስለምን ድርቅ ብለው መሞገት ፈለጉ?
ኢንጂነር ጌድዮን፡– ቅድም እንዳልኩት እኮ ነው። በግርማዊ አጼ ምኒልክ ጊዜ ከእንግሊዝ ጋር የተፈረመ ውል ነው። በእርግጥ እኔ የህግ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን በዚያ ውል ውስጥ እንዳነበብኩት ኢትዮጵያ በውሃው አትጠቀም የሚል ነገር የለም።
ግድቦችም ከዳር እስከዳር ውሃውን አቋርጠው የሚያቆዩ አይደለም፤ ግድብ ውሃ ያጠራቅማል እንጂ የናይልን ፍሰት ያቆማል ማለት አይደለም። ውሃው መፍሰሱ አይቀርም። ስለዚህ ያ ውለታ ልማታችንን የሚያግድ ውለታ አይደለም። በዚያ ውለታ ውስጥ ኢትዮጵያ ውሃውን አትጠቀምም የሚል አንድም አንቀጽ የለም። እ.ኤ.አ የ1902ቱም ቢሆን ማለት ነው።
የ1959ኙ አይመለከተንም፤ በሁለቱ አገሮች የተፈረመ ነው። የሁለቱ አገሮች ውለታ ነው። ያን ውለታ እኛን በሚመለከት ሊጠቅሱም አይችሉም። እነርሱም አይሉም። ነገር ግን በሌላ መንገድ አሁን በምናደርገው ድርድር ውስጥ በተለያዩ አንቀጾች ውስጥ ያንን እንድንቀበል የሚያደርጉ ሁኔታዎችን አሾልኮ የማስገባት ነገር ስለምናይ አስገዳጅ ስምምነት እያሉ ይጮሃሉ። የኢትዮጵያን የውሃ መጠቀም መብት የሚያግድ ነገር በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የሚሉት እሱ ነው። እሱ ግን የሚሆን ነገር አይደለም። ስለሙሌቱ ስለሆነ የምንደራደረው ስለሙሌቱ መፈራረም እንችላለን። ስለዓመታዊ ኦፕሬሽኑም ቢሆን መደራደርም ይቻላል። ሁለቱ አገሮች የተፈራረሙት አስገዳጅ ነው። የሚያስጮኸን ነገር አይደለም። የሚያስማማን ነገር ላይ ሁለት አገሮች በመንግስት የተወከሉ ኃላፊዎች ሲፈርሙ በሶስት አገሮች መሃል የፀና ነው፤ አስገዳጅም ነው። በዓለም አቀፍ ህግም የሚያጠያይቅ ነገር አይደለም፤ የሚያጠያይቀው አስገዳጅ የሚሉት ነገር በእነዚህ ውለታዎች ውስጥ ሾልከው የገቡ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነኩ ነገሮች አስገዳጅ ሆነው እንዲወጡ ስለሚፈልጉ ነው። እሱ ግን አይሆንም። በግልጽም ተነግሯል። እንደሱ ያለ ውለታ ኢትዮጵያ አትፈርምም። ስለዚህ ያለፉ ውለታዎች የኢትዮጵያን ልማት የሚያስሩ አይደሉም፤ ሊያስሩም አይችሉም።
አዲስ ዘመን፡– ኢንጂነር ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ ላመሰግንዎ እወዳለሁ።
ኢንጂነር ጌድዮን፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013