ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
እስኪ ልጠይቃችሁ ሀገር ማለት ምን ማለት ነው? ህዝብ መንግስት ምንድነው? ባህል፣ ወግ፣ ስርዓት ይሄስ ከየት መጣ? ሀገር የቤተሰብ ነጸብራቅ ናት። ቤተሰብ የሀገር መሰረት ነው። ኢትዮጵያን እኔና እናተ ነን የሰራናት። ሀገር የእኔና የእናንተ የአስተሳሰብ ውጤት ናት። የሀገርና ህዝብ ጠንካሬ ከቤተሰብ ጥንካሬ የሚመጣ ነው። ጣታችሁን ወደ ማንም አትቀስሩ ሀገራችን ልክ አይደለችም ካላችሁ በመጀመሪያ እናንተ ልክ አልነበራችሁም ማለት ነው።
ማህበረሰባችን ልክ አይደለም ካላችሁ ቤተሰቦቻችሁ ሲያሳድጓችሁ ልክ አልነበሩም ማለት ነው። በሀገራችን ጉዳይ የምንመሰገነውም የምንወቀሰውም እኛ ልጆቿ ነን። የድሮዋ ኢትዮጵያ የድሮ አባቶቻችን አስተሳሰብ ነበረች። የዛሬዋ ደግሞ የእኛ ሆና እየኖረች ነው። በእኛ አስተሳሰብም ትቀጥላለች። የሁሉም ነገር መሰረት ቤተሰብ ነው..አስተዳደግ። ልጆች የቤተሰቦቻቸው የእጅ ስራ ውጤቶች ናቸው። ወላጆች ልጆቻቸውን እንደፈለጉ አድርገው መስራት ይችላሉ አጣማችሁ፣ አቃንታችሁ የመስራት ስልጣኑ የእናንተ ነው።
በጥሩ ቤተሰብ ያደገ ልጅ ነገ ላይ ለሀገር የሚበጅ ጥሩ ዜጋ ይሆናል። በተቃራኒው ሃላፊነት በጎደላቸው ወላጆች እጅ ፍቅር አጥቶ ያደገ ልጅ ነገ ላይ ሀገር ከሚያፈርሱት ጋር ስለማበሩ ተጠራጣሪ የለም። ወላጆች ለልጆቻቸው አስተማሪዎች ናቸው..ልጆች ከወላጆቻቸው የነገ ህይወታቸውን ብሩህ ሊያደርግ በሚችል መልካም አስተሳሰብ ውስጥ ማደግ አለባቸው። አስተዳደግ በማናችንም ህይወት ላይ ይሄ ነው የማይባል የበረታ ተጽዕኖ አለው። የሁላችንም ተጽዕኖ ማረፊያ ደግሞ ሀገርና ህዝብ ነው።
ለዚህም ነው ሀገር የቤተሰብ ውጤት ናት ስል ያወራሁት። ሀገራችንን የተሻለች ሀገር ለማድረግ በመጀመሪያ እኛ የተሻለ አስተሳሰብ፣ የተሻለ ስብዕናን፣ የተሻለ የስራ ባህልን ማዳበር አለብን። እኛ ሳንስተካከል የሚስተካከል ሀገርና ህዝብ የለንም። እኛ ሳንለወጥ የሚለወጥ ምንም ነገር የለም። ሁሉም ነገር በእኔና በእናንተ ለውጥ ውስጥ ያለ ነው። እኛ ስለተበላሸን ነው ሀገራችን አንል ላይ የተበላሸችው። እኛ እንዳንበላሽ ደግሞ አሳዳጊዎቻችን ከፍተኛውን ሀላፊነት ይወስዳሉ። ለምንም ነገር መሰረቱ ቤተሰብ ነው።
ቤተሰብ ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ወጣቶች የሚፈሩበት ተቋም እንደሆነ ነው የማስበው። ሁላችንም አሁን የቆምንበት ቦታ ላይ የተገኘነው በቤተሰቦቻችንና በእኛ በግል እሳቤ ታግዘን ነው። እዚህ ዓለም ላይ በህይወት ለመኖር ከሚደረግ ትግል ቀጥሎ ሁለተኛው ከባድ ነገር ልጅ ማሳደግ ነው እላለሁ። መውለድ ደግሞ በተቃራኒው ቀላል።
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የምትሆነን ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት። ለልጆች የሚሆን ምንም ነገር በሌላት ሀገር ላይ ነን። መውለድ እንጂ ማሳደግ አንችልበትም። የወለድናቸውን በወጉ አሳድገን ለቁም ነገር ሳናበቃ በልጅ ላይ ልጅ በመጨመር ከአፍሪካ የሚወዳደረን አጥተናል። ማሳደግን ለማያውቅ ማህበረሰብ መውለድ በህመም ላይ ህመምን ከመጨመር ባለፈ የሚፈይደው አንዳች ነገር አለ ብዬ አላስብም። መውለድ ትርጉም የሚኖረው፣ ወላጅነት ደስ የሚለው ለወለድናቸው ልጆች ሀላፊነት ሲሰማን ብቻ ነው።
በህዝብ ቁጥራችን መቶ ሚሊዮንን አልፈን። ከድህነት በቀር ለሀገርም ለህዝብም የጠቀምነው ነገር የለም። ዓለም ላይ በትንሽ የህዝብ ቁጥር የዓለምን ኢኮኖሚ በቀዳሚነት የሚመሩ በርካታ ሀገራትን አውቃለሁ። ስልጣኔ መውለድ ሳይሆን የወለዱትን ለቁም ነገር ማብቃት ነው። የሰለጠኑት ሀገራት ለልጆች የሚሆን ብዙ ነገር አላቸው። ከእርግዝና ጀምሮ የልጆችን አስተዳደግ ስነልቦና የሚከታተል ስርዓት አላቸው።
የዛሬው የሀገራችን ክስረት ከአስተዳደግ ችግር የመነጨ ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። ከመውለድ ባለፈ ጥሩ አስተዳደግን ባህል እስካላደረግን ድረስ የነገውም የሀገራችን ክስረት በወለድናቸው ልጆቻችን በኩል እንደሚመጣ ጥርጥር የለኝም። የወለድናቸው ልጆች ሀገርና ህዝብ ከመጥቀም ባለፈ ስቃይ እየሆኑብን ባለበት በዚህ ዘመን አብዛኛው የኢትዮጵያዊ አብራክ ከመውለድ አልነጠፈም። አብዛኞቻችን ለመውለድ የቸኮልን ለማሳደግ ግን የዘገየን ነን።
በእውቀት ከመኖር ይልቅ በዘልማድ መኖርን በመረጠ ማህበረሰብ ውስጥ ነን። ለመውለድ ያለንን ፍላጎት ያክል ለአስተዳደግ ቢኖረን ዛሬ ላይ በሁሉ ነገሯ የከሰረችን ሀገር አናይም ነበር። ወላጆች ልጆቻችሁን እንዴት እያሳደጋችኋቸው እንደሆነ ቆም ብላችሁ አስቡ። ልጆች እንዴት እያደጋችሁ እንደሆነ ለአንድ ጊዜ ራሳችሁን ጠይቁ። ወላጆች ለልጆቻችሁ መሰረት መሆን ካልቻላችሁ በመውለዳችሁ እፈሩ እንጂ እንዳትደሰቱ። ለልጆቻችሁ ጥሩ ቤተሰብ መሆን ካልቻላችሁ በህይወት ውስጥ ለማያባራ መከራና ስቃይ እንደፈጠራችኋቸው ልብ በሉ። ለልጆቻችሁ መልካም ወላጅ ለመሆን ካልቻላችሁ ስቃይ እየሆናችሁባቸው እንደሆኑ አስቡ።
በየቦታው ህጻናት ተጥለው አይተናል። ወልዶ መጣል ብርቃችን አይደለም። ጎዳና የተወለዱ ህጻናት ሞልተውናል። ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ተጥለው ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ካለ ቤተሰብ ያደጉ ልጆች ሞልተውናል። እንዲህ እየወለድን..እንዲህ ተወልደን እያደግን ለሀገር ስጋት ከመሆን ሌላ ምን ጥቅም ሊኖረን ይችላል? ሀገራችንን እኛው ነን ያበላሸናት። በእኛው አስተሳሰብ፣ በእኛው አመለካከት ነው ወደ ኋላ የቀረችው። እኔና እናተ ለልጆቻችን ጥሩ ወላጆች እስካልሆንን ድረስ የሀገራችን ህመም አይሽርም። ልጆቻችሁ እናንተን ናቸው።
አብዛኞቹ ወላጆች ልጆቻቸው ስለሚበሉትና ስለሚጠጡት ስለሚለብሱትም ተራ ነገር የሚጨነቁ ናቸው። አስተሳሰባቸውን ገለው በሰው ፊት ጥሩ ለብሰው እንዲታዩላቸው የሚለፉ ናቸው። አብዛኛው የኢትዮጵያዊ ወላጅ ልጁ ጥሩ እንዲለብስ እንጂ ጥሩ እንዲያስብ ሲጨነቅ አላየሁም። ከሰው እንዳያንሱ በሚል አጉል አመለካከት አካላዊ በሆኑ አላቂ ነገሮች ላይ ጊዜና ገንዘባቸውን የሚያፈሱ ናቸው። ልጆች ጥሩ ሆነው እንዲያድጉ ልብስ ሳይሆን የአእምሮ ግንባታ ነው የሚያስፈልጋቸው። ከሰው እንዳያንሱ በሚል አመለካከት በሌለን አቅም የማንችለውን ከማድረግ ይልቅ ባላቸው ነገር እንዲኮሩ፣ የሌላውን እያሰቡ የበታችነት እንዳይሰማቸው ታላቅ አስተሳሰብን ልንሞላባቸው ነው የሚገባን።
አእምሮው ያልተገነባ ልጅ የቻይና እቃ ነው። ወርቅ በሚመስል አርቴፊሻል ነገር ተሽሞንሙኖ ገበያ የሚወጣ። ግን አገልግሎት የሌለው..ግን ቶሎ የሚሰበር፣ ግን ጥቅም የሌለው። አእምሮው ያልተገነባ ትውልድ የሀገር ስጋት ነው። አሁን ላይ ሀገር እያፈረሱ ያሉ ጥሩ የለበሱ የእንጀራ ጠርዝ ጣታቸውን የሚቆርጣቸው ባለ ጸዐዳ እጆች ናቸው። ብሩህ ነገ ይኖረን ዘንድ በአእምሮ መሰራት አለብን።
ልብስ ለአካል ነው የተሰራው፣ ልብስ ከብርድ ነው የሚከላከለው የአእምሮን ስብራት አይጠግንም። ልብስ የአእምሮን ጎደሎነት አይሞላም። የአእምሮ ጎደሎነት የሚሞላው በአስተሳሰብ ነው። የህዝቦች ጥያቄ የሚመለሰው በእውቀት ነው። ለዛም ነው ዓለም ልታልፍ ጥቂት ጊዜ ብቻ በቀራት ስልጡን ዘመን ላይ ቆመን ወደ ኋላ የምናስበው። ለዛም ነው አማኝ በሆነች ሀገር ላይ ተፈጥረን ለፈጣሪ ቦታ አጥተን በነውር የምንኖረው። ለዛም ነው ከሀሳብ የበላይነት ይልቅ በማይጠቅሙን ተራ በሆኑ ነገሮች የምንጋፋው። ለዛም ነው ፖለቲከኛና አክቲቪስት ነን በማለት ሀገር የምንረብሸው። በአእምሮ መበልጸግ እንዲህ አይደለም።
በአእምሮ ያደገ፣ በስነልቦና የበለጸገ ማህበረሰብ በልዩነት ውስጥ ተስማምቶ የሚኖር ነው። እነርሱ በሀሳብ የበላይነት የሚያምኑ፣ በውይይትና በመነጋገር የበለጸጉ ናቸው። ስለዚህም ለልጆቻችሁ እውነት በመሆን የወላጅነት ግዴታችሁን እንድትወጡ አደራ እላችኋለሁ። ልጆቻችሁ እናንተን ናችው። በመልካቸው ላይ መልካችሁ አለ። በነፍሳቸው ላይም ነፍሳችሁ አጎንቁሏል። በሳቃቸው ላይ ሳቃችሁ ተስሏል። በሀዘናቸው ላይም ሀዘናችሁ ተቀምጧል። ላትሞቱ በላያቸው ላይ ለሁልጊዜም አላችሁ። ከደም ከአጥንታችሁ ተቀይጠው የስጋችሁን ወዘና ለብሰው እናንተን ሆነው ከእናንተ ተፈጥረዋል። ዘለአለማዊ ሳቃችሁ ከነሱ ውስጥ ይፈልቃል። በልጆቻችሁ ዳግም እየኖራችሁ እንደሆነ አስቡ…እነርሱ አምላክ እናንተን በወርቅ ቀለም የጻፈበት ቀለሙ ናቸው። ከዚህ ሁሉ በላይ ህልምና ራዕዮቻችሁ ናቸው..ነጋችሁን በነሱ በኩል ነው የምታዩት። ልጆቻችሁ በብዙ ነገር ያስፈልጓችኋል። የእውነት ልታሳድጓቸው ይገባል። የእውነት ሰው ልታደርጓቸው ግድ ይላችኋል። የእውነት ወላጅ ልትሆኗቸው ግዴታ አለባችሁ።
አብዛኞቻችን ከቤተሰብ በወረስንው ዘልማዳዊ መንገድ ነው ልጆቻችንን እያሳደግን የምንገኘው። ልጅ ማሳደግ ጥበብ ይጠይቃል። እንዲያውም ልጅ ወልዶ እንደማሳደግ ጥበብ አለ ብዬ አላስብም። ይሄ እውነት ስላልገባን ነው ዛሬ ላይ ለሀገር ሸክም ሆነን የተገኘነው። ይሄ እውነት ስላልገባን ነው በተጋባን በማግስቱ ልጆቻችንን በየቆሻሻ ገንዳው የምንጥለው። አብዛኞቹ ልጆች በምክንያት ሳይሆን ስሜት በወለደው መኝታ ወደዚህ ዓለም የመጡ ናቸው። ስንጋባ በምክንያት እንደሆነ ሁሉ ለመውለድም ምክንያት ያስፈልገናል። ምክንያታችን ግን ዝም ብሎ መሆን የለበትም። በእውቀትና በመረጃ ላይ የተገነባ ሳይንሳዊ እንዲሆን ግድ ይላችኋል።
እንደዚሁም ደግሞ አብዛኛው ወላጅ ልጁን በሚሄድበት የሚመራ ነው። ልጆች የራሳቸው መንገድ የራሳቸው እውነት አላቸው በዛ መንገድ ላይ እንዲሄዱ አግዟቸው እንጂ በራሳችሁ እውነት ላይ እንዲቆሙ አታስገድዷቸው። አንድ ልጅ ተወልዶ ለአቅመ ማሰብ እስኪደርስ ድረስ በአካል፣ በአእምሮ፣ በስነ ልቦና መገንባት አለበት። ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። በዚህ ሁኔታ ያደጉ ልጆች እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ የሀገር ባለውለታ ናቸው። ወላጅነት ደብተርና እስክርቢቶ ገዝቶ ትምህርት ቤት መላክ የሚመስለን ብዙዎች ነን። ወላጅነት የረቀቀ ምስጢር ረቀቀ ተፈጥሯዊ ሀቅ ነው። ወላጅነት ፍጹማዊ ደስታችሁን የምታገኙበት ስፍራችሁ ነው። ጥሩ ወላጅ ስትሆኑ ደግሞ ደስታው እጥፍ ድርብ ነው የሚሆነው። ለልጆቻችሁ ድከሙ። የምትመሰገኑባቸው ልጆች ፍጠሩ።
የነገዋ ኢትዮጵያ በልጆቻችሁ አስተሳሰብ ልክ የምትፈጠር ናት። ልጆቻችሁ ደግሞ በእናንተ እጅ ውስጥ ናቸው። እናንተ የእናት የአባቶቻችሁ ውጤቶች እንደሆናችሁ ሁሉ ልጆቻችሁም የእናንተ አስተሳሰብ ናቸው። ነገ ላይ መልካምና ለሀገር ጠቃሚ ዜጋ አድርጋችሁ የምትፈጥሯቸው እናንተ ናችሁ። ነገ ላይ እንኳንም የነሱ ሆንኩ ብለው በአደባባይ በኩራት የሚናገሩላችሁን ልጆች ወልዳችሁ አሳድጉ።
ደግሜ እላችኋለሁ ዛሬ ላይ ሀገራችን የተበላሸችው በወጉ ባላደጉ ልጆች ነን። መሰረቱ የተበላሸ ፍጻሜው አያምርም። ልጆቻችሁ ላይ ትጉ..ከዛም በሁሉ ነገሩ የተስተካከለ አዲስ ትውልድ ታያላችሁ። ለራሳችሁም ለሌላውም ስትሉ ለልጆቻችሁ ጥሩ ወላጅ ሁኑ። ወላጅ ለመሆን በሚያስችል ቁመና ላይ ብቻ ስትሆኑ ውለዱ። ለመጣል አትውለዱ፣ ስለልብስና ጫማ እንድትጨነቁላቸው አትውለዱ። ልጆቻችሁ መጠሪያዎቻችሁ ናቸው። መደነቂያ መወቀሻዎቻችሁም። መከበሪያ መሸማቀቂያዎቻችሁም። ክብርና ውርደታችሁ ናቸው። በሌላችሁበት በልጆቻችሁ ትመዘናላችሁ። ምን አይነት ቤተሰብ ቢያሳድገው (ቢያሳድጋት) ነው እየተባላችሁ በሌላችሁበት ትከበራላችሁ አሊያም ትናቃላችሁ።
በቤተሰብ ውስጥ ያለ ነገር ነው ወደ ውጪ የሚወጣው ቤተሰቦቻችን አጠንክረው ካበጁን ዓለም አያሸንፈንም። ከሁሉም በፊት ወላጆች የጥሩ ስብዕና ባለቤቶች መሆን አለባቸው። ልጆች የቤተሰቦቻቸው ነጸብራቆች ናቸው። የእነዚህ ነጸብራቆች ስብስብ ሀገር ይፈጥራል። ሀገር ደግሞ የሁላችንም የመጨረሻ እውነት ናት።
በልጆቻችሁ ነፍስ ፤ ላይ ሰውነትን ትከሉ። የተማሩ ሳይሆን፣ ዶክተርና ፕሮፌሰር እንዲሆኑ ሳይሆን መልካም ሰው ሆነው እንዲያድጉ ስሯቸው። ታዋቂ ሳይሆን አዋቂ እንዲሆኑ ፍጠሯቸው። ስለገንዘብ ሳይሆን ስለ ስራ፣ ስለ ጉልበት ሳይሆን ስለትህትና እየነገራችሁ አበልጽጓቸው። ስለ ጥላቻ ሳይሆን ስለ ፍቅር፣ ስለመለያየት ሳይሆን ስለአንድነት አስጠኗቸው።
ለሰው ልጅ ሁሉ የሚራሩ፣ ለፈጣሪ የተመቹ አድርጋችሁ አብቅሏቸው እመኑኝ ውሎ ሳያድር ፍሬውን ትበላላችሁ። ሀገር እኔና እናንተ ነን። ሀገር የእኔና የእናንተ ትላንትና ናት። እኔና እናንተ በሆነው በምንሆነው ልክ ትወሰናለች። የእስካሁኑ አበሳዋ በእኔና በእናንተ በኩል ያገኘችው ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የእያንዳንዳችን አስተዳደግ፣ የእያንዳንዳችን አስተሳሰብ ሀገርና ህዝባችን ላይ አሉታዊም አዎንታዊም ተጽዕኖ አለው። ነጋችንን በአዲስ አስተሳሰብ እንጀምር። ከነበርንበት ወጥተን በአዲስነት አዲሷን ኢትዮጵያ በጋራ እንገንባ ስል እያሳሰብኩ ላብቃ። ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013