ዳግም ከበደ
በዓለማችን ላይ እልፍ ሁነቶች ይከሰታሉ። አንዳንዶቹ እንዲያውም ከተለመደው መንገድ ወጣ ይሉና እንደ ክስተት የሚታዩበትም አጋጣሚ አይጠፋም። ያልተለመዱ ድርጊቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የፈጠራ ውጤቶች፣ አዝናኝ አሊያም ልብን የሚሰብሩ ክንውኖች ምድራችን በየጊዜው ታስተናግዳለች።
ይሄን ኡደት ደግሞ እኛ ለውጥ እንለዋለን። በዛሬው የእለተ ሰኞ የማረፊያ አምዳችን ላይ እናንተ አንባቢዎቻችን ብትመለከቷቸውና ብታውቋቸው አንድም እውቀትን ትገበዩበታላችሁ ሁለትም ትዝናኑበታላችሁ ብለን በማሰባችን አንዳንድ ጉዳዮችን ከዚህ እንደሚከተለው አንድ ሁለቱን እናቀርብላችኋለን።
ሮቦት የአእምሮ ዝግመት
ላለባቸው ህጻናት
የአእምሮ እድገት ውስንነት በበፊት ስያሜው `የአእምሮ ዝግመት` ያላቸው የሚባሉት የአእምሮ ብስለት ውጤታቸው (Intelligence quotient score) ሰባ እና ከሰባ ያነሰ ሲሆን እንዲሁም ራስን ችሎ ለመኖር አስፈላጊ ናቸው ከሚባሉት ዋና ዋና አስሩ ክህሎቶች መካከል ቢያንስ ሁለቱን ማድረግ ሲሳናቸው ነው። ለአእምሮ ብስለት እንደ መለኪያ ከምንጠቀማቸው ውስጥ (የማመዛዘን ችሎታ፤ ችግር የመፍታት አቅም፤ እቅድ ማውጣት፤ ውሳኔ መስጠት እና መማር) የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። የአእምሮ ብስለት መለኪያ ጥያቄዎችም ከላይ የጠቀስናቸውን መመዘኛዎችን መሰረት አድርጎ የሚዘጋጁ ናቸው።
ስለዚህ ጉዳይ በመግቢያችን ላይ ያነሳንላችሁ ወደን አይደለም ፤ በቅርቡ ከወደ ሆንክ ኮንግ ይህን ችግር ይቀርፋል የተባለ የአንድ ፕሮፌሰር የቴክኖሎጂ ውጤትና ጥረትን ልናጋራችሁ ወደን ነው።
ከአገረ ሆንግ ኮንግ የአእምሮ ውስንነት ያለባቸው ህፃናትን ማህበራዊ ክህሎት እንዲያዳብሩ ያግዛል የተባለለት ሮቦት ይፋ ተደርጓል። ይሄ የቴክኖሎጂ ውጤት ትግበራ ላይ እንዲውል በምርምር ግኝታቸው ያስተዋወቁት ደግሞ አንድ ፕሮፌሰር ናቸው።
በሆንክ ኮንግ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በስነልቦና የትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ካትሪን ሶ “የአእምሮ ውስንነት ያለባቸው ህፃናት ከሌሎች ጋር ለመግባባት ዝቅተኛ ተነሳሽነት እና በአካባቢያቸው ላሉት ነገሮች ቁጡና ስስ ስሜት ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው። ስለዚህ ጭንቀታቸውን ለመቀነስ በሮቦቶቹ አማካኝነት ማህበራዊ ክህሎቶችን ለማስተማር እንጠቀምባቸዋለን” ይላሉ። በዚህም ሮቦቶች ልጆቹን በተጫዋችነት እና በቃላት መስተጋብር እንዲያሳትፉና ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ያግዛሉ ብለዋል።
በአንድ አነስተኛ ክፍል ልጆች በጠረጴዛ ላይ ማህበራዊ ግንኙነቶችን ለማዳበር ታልመው ከተሰሩ ሁለት ትናንሽ ሮቦቶች ጋር ይቀመጣሉ። ሮቦቶቹም ልጆቹ እንደ ንዴት ወይም ጩኸት ባሉ ተገቢ እና ተቀባይነት በሌላቸው ባህሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት እንዲመለከቱ ይረዳቸዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆነችው ሙሴ ዎንግ አንድ የ5 ዓመት ታዳጊ በፕሮግራሙ ውስጥ ለሰባት ወራት እንደቆየችና ማህበራዊና የግንኙነቷና ክህሎቶቿ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻላቸውን ተናግራለች። ዎንግ እንዳለችው “በተወሰነ ደረጃ ታዳጊዋ የማኅበራዊ ሕይወትን በመላመድ መኖር ጀምራለች” ልጆቹ ከሮቦቶች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የተማሩትን ማህበራዊ ክህሎቶች ከሰው ሞግዚት ጋር እንዲሞክሩ ይበረታታሉ።
ይህ ፕሮጀክት ውጤት እያሳየ በመምጣቱ በሆንግ ኮንግ እና በማካው ውስጥ ባሉ መንግስታት እና በመንግስት ትምህርት ቤቶች የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው ከ20 በላይ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ቡድኖች መሰል የሮቦት ማህበራዊ ክህሎት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ጀምረዋል። ስለዚህ ፕሮጀክቱ መገለልን ለመዋጋት እንደሚረዳ ተስፋ አለው። “ሮቦቶቹ ጋር የተገናኘው ፕሮግራም በአእምሮ ውስንነት የተያዙ ህፃናት ማህበራዊ እና ስነምግባር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳል። እንዲሁም በምላሹም የህይወታቸውን ጥራት ያጠናክራል” ብለዋል የዚህ ፕሮጀክት አባላት። ምንጭ «ሮይተርስ»
በመርፌ ከመቀጣት ይልቅ ጥይትን የመረጠው ወንጀለኛ
በአሜሪካዋ ግዛት ኔቫዳ በግድያ ወንጀል ሞት የተፈረደበት ፍርደኛ ገዳይ መርፌ ከምወጋ ይልቅ በአልሞ ተኳሽ ልገደል ሲል መጠየቁን የቢቢሲ የዜና ምንጭ አስታውቋል። በኔቫዳ ግዛት ወንጀለኛ በሞት የተቀጣው ከ15 ዓመታት በፊት ነበር።
ዛኔ ማይክል ፍሎይድ የሚባለው ፍርደኛው በመርፌ ተወግቶ ከመሞት ይልቅ በጥይት ተመትቶ መሞትን የመረጠው ‘ሕመሙ አነስተኛ” በመሆኑ ነው ተብሏል። አሶሺዬትድ ፕሬስ ተመለከትኩት ባለው የፍርድ ቤት ሰነዶች ውስጥ የሕግ ባለሙያዎች ዘዴው የተመረጠው ሕመሙ አነስተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ሰኔ ወር ላይ የሚፈጸምበትን የሞት ፍርድ እየተጠባበቀ የሚገኘው ፍርደኛ ጠበቆች ደንበኛቸው ይህን ጥያቄ ያቀረበው የተላለፈበትን የፍርድ ውሳኔ ለማዘግየት አቅዶ አይደለም ይላሉ። አሜሪካ ውስጥ በአልሞ ተኳሾች የሞት ቅጣትን ማስፈፀም እምብዛም አልተለመደም።
ዕቅዱ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚፈልግ ወገን አማራጭ ዘዴ እንዲያቀርብ ይጠየቃል። የፍሎይድ ጠበቃ ጥይት “እጅግ ሰብዓዊ መንገድ” ነው። በአሜሪካ በጥይት መገደል ተግባራዊ የሚደረግባቸው በሦስት ግዛቶች ብቻ ነው። በሚሲሲፒ፣ ኦክላሆማ እና ዩታ። ይህም ቢሆን ከ2010 ወዲህም ተግባራዊ አልተደረገም።
በቀጣዩ ወር ፍሎይድ ላይ የሞት ፍርዱ እንዲፈጸም የሚጠይቅ ማመልከቻ ለማስገባት ዓቃቤ ህጎች እየተሰናዱ ነው። በእቅዱ መሰረት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ ይደረጋል። ፍሎይድ ከጎርጎሮሳዊያኑ 2006 ጀምሮም ኔቫዳ ውስጥ በሞት የተቀጣው የመጀመሪያው ግለሰብ ይሆናል።
ፍሎይድ 45 ዓመቱ ነው። በ1999 ላስ ቬጋስ በሚገኝ ሱፐርማርኬት አራት ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ተኩሶ ገድሏል። አንድ ግለሰብ ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ ጥፋተኛ ተብሏል።
እአአ 2000 ላይ ዓመት ጥፋተኛነቱን ከተቀበለ በኋላ በሞት እንዲቀጣ ተወሰነበት። ፍሎይድ በተደጋጋሚ ይግባኝ ቢልም ጥያቄዎቹ ውድቅ ተደርገውበታል።
የኔቫዳ ግዛት የታችኛው ምክር ቤት አባላት በግዛቱ የሞት ቅጣት እንዲቆም የቀረበውን ረቂቅ በቅርቡ ደግፈዋል። ይህን ተከትሎም ፍሎይድ በድጋሚ ይግባኝ ሲል ጠይቋል። የኔቫዳ ሴኔት ውሳኔውን በአብላጫ ድምፅ ካሳለፈ የግዛቲቱ የሞት ፍርዶች ተሽረው አመክሮ ወደሌለው የዕድሜ ልክ እስራት ይቀየራሉ።
ኔቫዳ ውስጥ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው 70 ሰዎች አሉ። ግዛቲቱ የሞት ቅጣት ከሚፈጸምባቸው 27 ግዛቶች አንዷ መሆኗን የአሜሪካ ዴዝ ፔናሊቲ ኢንፎርሜሽን ሴንተር ገልጿል። ከ1976 ወዲህ ግዛቲቱ ምህረት የሰጠችው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013