አዲስ አበባ፦ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባደረገው የታሪፍ ማሻሻያ አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከአቅማቸው በላይ መሆኑንና በክፍያው መማረራቸውን ገለጹ።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ድንጋይ ጣቢያ አካባቢ እንደምትኖር የምትናገረው ወይዘሮ ረድኤት ታደሰን ያገኘናት ቸርቸር አካባቢ ባለው የቅድመ አገልግሎት ክፍያ ጣቢያ ነው። የቅድመ ክፍያ ስትፈፅም ያገኘናት ረድኤት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የምትከፍለው ወጪ እንዳማረራት ትናገራለች።
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ረድኤት፤ በሳምንት አንድ ጊዜ እንጀራ እንደምትጋግርና አንድ የማብሰያ ምድጃ ብቻ የምትጠቀም ቢሆንም ከታሪፍ ማስተካከያው በፊት እና አሁን እየታየ ያለው ልዩነት በጣም ከፍተኛ ነው ትላለች።
መንግሥት የኤሌክትሪክ ዋጋን ማስተካከያ ሲያደርግ ያለውን የኑሮ ውድነትና በወር ደመወዝ የሚተዳደረውን ደሃ ህብረተሰብ ከግምት አላስገባም፤ የምትለው ረድኤት፤ ከታሪፍ ማሻሻያው በፊት የ300 ብር ካርድ ሞልቼ አንድ ወር እጠቀም የነበረ ቢሆንም፣ በአሁን ሰዓት 300 ብር 15 ቀን እንኳን አያደርሰኝም፤ በወር ውስጥ 600 እና 700 ብር እንደምትከፍልና ማሻሻያው በእጥፍ እንደጨመረባት አማርራ ትናገራለች።
በዚሁ አካባቢ ያገኘናት ሌላኛዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኛ አዜብ ኢርኮ ትባላለች። አዜብ በቅድመ ክፍያ አገልግሎት በካርድ የምትጠቀም ባይሆንም በቀጥታ መስመር በቆጣሪው ንባብ መሰረት ለሁሉ የአገልግሎት የክፍያ ጣቢያ ላይ እንደምትከፍል የምትናገረው አዜብ የቤተሰብ ብዛት የለብኝም፤ ከምጣድና ከምድጃ የተለየም የኤሌክትሪክ አገልግሎት አልጠቀምም። ይሁን እንጂ የተደረገው ማሻሻያ ከዚህ በፊት ከምከፍለው ዋጋ ጋር ሲነጻፀር በእጥፍ ጨምሯል። ለምሳሌ፤ ከዚህ በፊት ስከፍል የነበረው ቢበዛ 100 ብር የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን እስከ 700 ብር ድረስ እየከፈልኩ ነው። ይህ ደግሞ ከአቅሜ በላይ እየሆነ ነውና መንግሥት አንድ ነገር ቢለን ጥሩ ነው፤ የአሰራር ችግርም ካለ ቢፈተሽ መልካም ነው ትላለች።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ፊት ለፊት በሚገኘው ለሁሉ የክፍያ ጣቢያ ከፍለው ሲወጡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ውቢት ይመር ናቸው። ወይዘሮዋ አንድ አምፖል ብቻ የሚጠቀሙና ሌላ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያለመሆናቸውን በመናገር፤ ከዚህ በፊት አራት ብርና አምስት ብር እከፍል ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አስር ብርም አስራ አምስት ብርም እየከፈልኩ ነው ይላሉ። በዕለቱም አስራ አንድ ብር የከፈሉበትን ደረሰኝ ማየት ችለናል።
እነዚህንና መሰል የህብረተሰቡን እሮሮና ጥያቄዎች በመያዝ ወደ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስልክ በመደወል የታሪፍ ማስተካከያውን አስመልክቶ ያለውን ሁኔታ እንዲያስረዱን ጠይቀናል። በጥያቄው መሰረትም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለማሟላት እንቅፋት ከሆኑባቸው ተግዳሮቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የፋይናንስ እጥረት መሆኑን፤ በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ግብዓቶችንም በሚፈለገው መጠን ለማስገባት አሁንም ፋይናንስ ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አሁን የተደረገው ጭማሪ ሳይሆን የታሪፍ ማስተካከያ ነው። ይህም ማለት ደግሞ እስከ 50 ኪሎ ዋት ሰዓት በየወሩ የሚጠቀሙ ደንበኞች ከዚህ በፊት እንደሚከፍሉት የሚከፍሉና ምንም ዓይነት ጭማሪ ያልተደረገባቸው ናቸው ይላሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ እስከ 100 ኪሎ ዋት በሰዓት የሚጠቀሙ ደንበኞች 75 በመቶ እንዲደጎሙ በማድረግ 25 በመቶ የታሪፍ ማስተካከያ እንዲከፍሉ ተደርጓል። እስከ 200 ኪሎ ዋት በሰዓት ለሚጠቀሙ ደንበኞች ደግሞ የታሪፍ ማስተካከያውን 25 በመቶ እንዲደጎሙ በማድረግ 75 በመቶው ጭማሪ ይከፍላሉ። ከ200 ኪሎ ዋት በላይ በሰዓት የሚጠቀሙ ከፍተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በዋነኛነት ማጠቢያ ማሽኖችንና የተለያዩ ግብዓቶችን የሚጠቀሙና ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ጥገኛ ናቸው ተብለው ስለሚታሰብ ሙሉ በሙሉ እንዲከፍሉ ተደርጓል ብለዋል።
አሁን የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ከየትኛውም የኃይል አማራጭ በታች መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡ እስካሁን እየከፈለ የነበረው ከዛሬ 12 ዓመት በፊት በነበረው ታሪፍ በመሆኑ አሁን ያለውን ማሻሻያ ለመቀበል ዝግጁ ባለመሆኑ እንጂ ከዚህ ቀደም ይከፍል ከነበረው መቶ በመቶ ተጨምሮ አሊያም፤ ህብረተሰቡን የሚያማርር ጭማሪ ተደርጎ አይደለም ይላሉ።
የማሻሻያው ሂደትም በአንድ ጊዜ ሳይሆን በአራት ዓመት የሚጠናቀቅ ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ አጠቃቀሙን ማሻሻል አለበት። ተቋሙ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚያቀርብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እያንዳንዱ ህብረተሰብ በተጠቀመው ልክ ፍትሐዊ የሆነ ክፍያ እንዲፈጽም የተደረገ ማስተካከያ እንጂ መቶ በመቶ የተጨመረ ጭማሪ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በመጨረሻም ህብረተሰቡ በወቅቱ ቆጣሪውን ማስነበብና ካልተነበበም እንዲነበብለት መጠየቅና በየወሩ ሳያሳልፍ ክፍያ ሊፈፅም ይገባል። ይህ ካልሆነና በአንድ ወር 100 ኪሎ ዋት በሰዓት የተጠቀመ ሰው በወቅቱ ሳይነበብለትና ሳይከፍል ወደ ቀጣይ ወር ቢገባ የቀጣዩን ፍጆታ ጨምሮ 200 ኪሎ ዋት በሰዓት ይገባና በተጠቀመው ልክ በእጥፍ እንዲከፍል ይገደዳል። ስለዚህ ህብረተሰቡ ይህን ግንዛቤ ወስዶ ክፍያውን በወቅቱ ሊከፍልና ካልተነበበለትም በአካባቢው ወዳለ ተቋም በመሄድ እንዲነበብለት ማድረግና ቆጣሪ ሊያነቡ ለሚመጡ ሠራተኞችም ተባባሪ በመሆን ግዴታውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
ፍሬህይወት አወቀ