መላኩ ኤሮሴ
በሀገራችን የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ ሁሉም የመንገድ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው ቢሆንም የአንዳንድ የመንገድ ፕሮጀክቶች ፋይዳ ከሌሎቹ ላቅ ያለ እንደሚሆን አያጠያይቅም።በግንባታ ላይ የሚገኙት ሶዶ- ዲንኬ ሎት 2 እና ዲንኬ-ሳውላ- ሸፊቴ የመንገድ ፕሮጀክቶች የአካባቢውን እና የሀገሪቱን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን የማቀላጠፍ አቅም ካላቸው የሀገራችን የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የወላይታን ዞን ከጋሞ እና ጎፋ ዞን ጋራ በቅርበት ከማስተሳሰራቸው ባሻገር በዞኖቹ መካከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን በመፍጠር የትራንስፖርት እንቅስቃሴን እንደሚያስፋፋ ተስፋ የተጠለባቸው ናቸው።ከዚያ በተጨማሪ ሀገሪቱ በብዙ ወጪ የገነባቻቸው እና ተስፋ የምትጥልባቸው የኦሞ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት አማራጭ መንገድ ይሆናሉ፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በአካባቢው በስፋት ፍራፍሬዎች እንዲሁም የቀንድ ከብቶችና በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ በማድረስ አምራቹንና ሸማቹን የሚያስተሳስሩ ናቸው።የቱሪስት መዳረሻ የሆነውን የማዜ ፓርክን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ሀገሪቱ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪ የምታገኘውን የውጪ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ተስፋ የተጣለበት ነው፡፡
ሁለቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ ሲሆን ሶዶ-ዲንኬ ሎት 2 ግንባታ ግንቦት 2010 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በአራት ዓመት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል።86.22 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በገጠር 10 ሜትር፤ በወረዳ 12 ሜትር እና በዞን 26 ሜትር የጎን ስፋት ይኖረዋል።የግንባታው ወጪ አንድ ቢሊዮን ሃምሳ አራት ሚሊዮን ሶስት ሺህ ብር ሲሆን ወጪውም በኢትዮጵያ መንግስትና በአፍሪካ ልማት ባንክ እየተሸፈነ ይገኛል።ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ቻይና ሬልዊይ ሰቨን ግሩፕ ኤልቲዲ ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ጃቪ ነውቲች ኮንሰልቲንግ ግሩፕ ከነት ኮንሰልቲንግ ኢንጂነሪግ ፒኤልሲ ጋር በመሆን ነው፡፡
በኮንትራቱ ውሉ መሰረት የመንገድ ግንባታው በአራት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ክፍት እንደሚሆን እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ከአጠቃላይ የመንገድ ግንባታው ስራ እስካሁን ድረስ ማጠናቀቅ የተቻለው 41 ነጥብ 34 በመቶ መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የሶዶ-ዲንኬ መንገድ አካል የሆነውና 75.9 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ዲንኬ-ሳውላ- ሸፊቴ የመንገድ ፕሮጀክት 12 ድልድዮችን ያካተት ነው።ግንባታው ጥር 2011 ዓ.ም የተጀመረ የመንገድ ፕሮጀክት በአጠቃላይ የሚኖረው የጎን ስፋትም የመንገድ ትከሻን ጨምሮ በዞን 26 ሜትር፣ በቀበሌ 12፣ በገጠር 10 ሜትር የጎን ስፋት ይኖረዋል፡፡
የግንባታ ወጪው አንድ ቢሊየን 20 ሚሊየን 177 ሺህ ብር በላይ የሚፈጅ ሲሆን ወጪው በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት በጋራ የሚሸፈን ይሆናል።የግንባታ ስራውን ቤጂንግ አርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ ካምፓኒ እያከናወነው ሲሆን በአራት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ማጠናቀቅ የተቻለው 30 ከመቶ ብቻ ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከእቅዱ አንጻር መጓተት ይስተዋልባቸዋል።በአራት ዓመት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ የነበረው የሶዶ ዲንኬ ሎት 2 ግንባታ በሁለት ዓመት ከ11 ወር ውስጥ 41 ነጥብ 34 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን በተመሳሳይ በአራት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የተያዘው የዲንኬ-ሳውላ- ሸፊቴ መንገድ ፕሮጀክት በሁለት ዓመት ከሁለት ወር ውስጥ 30 በመቶ ብቻ ነው መፈጸም የተቻለው።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ ኤልያስ ተክለወልድ፤ በአካባቢው ከነበረው አስቸጋሪ ሁኔታዎች አንጻር ፕሮጀክቶቹ መልካም የሚባል አፈጻጸም እየታየባቸው መሆኑን ያነሳሉ።ፕሮጀክቱ ከዚህ በላይ እንዲፈጥን ይፈለግ ነበር። ሆኖም በጣት በሚቆጠሩ ችግሮች ምክንያት ፕሮጀክቱን አሁን ካለው በላይ ማፋጠን አልተቻለም፡፡
ግንባታው እየተካሄደ ያለበት አካባቢ በተለይ በክረምት ወቅት የተራዘመ ዝናብ የሚጥልበት በመሆኑ ግንባታውን ለማካሄድ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል የሚሉት አቶ ኤልያስ፤ በአሁኑ ወቅትም በዝናብ ምክንያት የግንባታ ስራው ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው።አካባቢው ዝናባማ ባይሆን ግንባታውን ከዚህ በላይ ማፋጠን ይቻል እንደነበር አንስተዋል፡፡
ፕሮጀክቱን አሁን ካለው በላይ ማፋጠን እንዳይቻል ያደረገው ሌላኛው ምክንያት የብዙ ፕሮጀክቶች ችግር የሆነው የወሰን ማስከበር ችግር መሆኑን ያነሱት አቶ ኤልያስ፤ የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለመቅረፍ ሲደረግ የነበረው ጥረት የግንባታ ጊዜን ወስዷል ይላሉ። ሁለቱ ችግሮች ባያጋጥሙ የበለጠ ማፋጠን ይቻል ነበር፡፡
አቶ ኤልያስ እንዳሉት፤ ሰሞኑን የመንገዶች ባለስልጣን እና የትራንስፖርት ባለስልጣን የስራ ሀላፊዎች ፕሮጀክቶቹን ጎብኝተዋል።በዚሁ ወቅት የመንገድ ግንባታውን እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተዋል።ያሉ የወሰን ማስከበር እና የግብዓት እጥረት እንዲፈታ እና የአካባቢው መስተዳድር ድጋፍ አድርጎ ግንባታው በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።ፕሮጀክቶቹን በታቀደላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ መግባባት ላይ ከመድረስ ባሻገር የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ይሻሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013