ታምራት ተስፋዬ
የዓለም ባንክ በየዓመቱ ከየአገሮች በሚሰበሰቡ የተለያዩ መለኪያ አስር መስፈርቶች ላይ መሠረት በማድረግ የቢዝነስ ሥራ ምቹነት (Ease of Doing Business) የደረጃ ሪፖርት ያወጣል:: ሪፖርቱም አገሮች ያሏቸው አሠራሮች ምን ያህል ለቢዝነስ ምቹ እንደሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር እያነጻጸረ ያመላከታል:: ከቢዝነስ ሥራ ምቹነት በተጨማሪም ለንብረት የሚሰጥ ጥበቃንም ከግምት ያስገባል::
መስፈርቱም አዲስ ቢዝነስ ለመጀመር ያለው አመቺነት፣ብድር ከማግኘት፣ ለአነስተኛ ባለሀብቶች ጥበቃ በማድረግ፣ ግብር በመክፈል እና በሀገሪቱ የትኛውም ስፍራ ለመነገድ ባለው አመቺነት፣ ከግንባታ ፍቃድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የንብረት ምዝገባ፣ የውሎች ተፈጻሚነትና ኪሳራን ከመከላከል እና መፍትሄ ከመስጠት አንጻር ይቃኛል::
የኢትዮጵያ መንግስት ለኢኮኖሚ ሁለንተናዊ እድገት በተለይም የኢንቨስትመንት ፍሰት እና አቅም ግንባታ ቅድሚያ ትኩረት የሰጠው ሀገሪቱን ለቢዝነስ ሥራ የምታመች ለማድረግ ነው:: በዚህ ሂደትም ፈርጀ ብዙ ገጽታ ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን አመችነትን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀየር የኢትዮጵያን የእድገት ደረጃ በአጭር ጊዜ በማሻሻል ሰፊና አፋጣኝ የሪፎርም ስራዎችን መስራት ተገቢ እንደሆነ ታምኖበታል።
ለዚህም ውጥኔ ስኬትም የተለያዩ ሕጎችን በማሻሻልና የአሠራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ኢትዮጵያን ከ100 አገሮች ተርታ ለማሰለፍ እየሠራ ይገኛል:: እነዚህ ማሻሻያዎች በንግድ ምዝገባ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድና ቢሮክራሲ ላይ ያተኮሩ ናቸው::
እኤአ በ2019 የወጣ ሪፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ190 አገራት ኢትዮጵያ 159 ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመላክቷል::በዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን አነጋግረናል::
አስተያየታቸውን ከጠየቅናቸው የምጣኔ ሃብት ምሁራን መካከልም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ አንዱ ናቸው:: ኢንቨስተሮች በአንድ አገር በተለያየ ዘርፍ ላይ መዋእለ ነዋያቸውን ፈሰስ ከማድረጋቸው አስቀድሞ ውጤታማ መሆን የሚያስችላቸውን በርካታ መመዘኛዎችን እንደሚያስቀምጡ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለ አገራቱ ያወጡትን ሪፖርት እንደሚቃኙ ይጠቁማሉ::
ይህ በሆነበት አገራት ኢንቨስትመንት እና ኢንቨስተሮችን ለማሰብ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን አመቺ ማድረግ የግድ እንደሚላቸው አፅእኖት የሚሰጡት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ይህን ማድረግም የኢትዮጵያን የእድገት ደረጃ በአጭር ጊዜ ለማሻሻል ወሳኝ ስለመሆኑ ይናገራሉ::
ቀደም ሲል በነበረው የመንግስት አስተዳደር የኢንቨስትመንት ምቹነትን ለማጎልበት የግሉን ዘርፍ ተዋናዮች ለማበረታታ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን የሚያስታውሱት ዶክተሩ፣ ከዚህ በአንፃሩ የግል ሴክተሩ ኪራይ ሰብሳቢ የሚል ታርጋ ተለጥፎለት፣ ቀማኛ እና ሙሰኛ ተብሎ ከተሳትፎው ገሸሽ እንዲል ተደርጓል። በተለያዩ ዘርፍ የመንግስት ሚና ከፍተኛ እንዲሆን መደረጉን ያስታውሳሉ::
‹‹ይህ አሁን ላይ ተቀይራል፣ የግል ሴክተሩ ይበልጥ እንዲንቀሳቀስ ሆኗል›› የሚሉት ዶክተር ቆስጠንቀጢኖስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡም ለኢኮኖሚ ሁለንተናዊ እድገት በተለይም የኢንቨስትመንት ፍሰት እና አቅም ለማጎልበት ቅድሚያ ትኩረት ይሠጣቸዋል ካላቸው አጀንዳዎች አንዱ ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ስራ የምትመች ማድረግ፤ ዝቅተኛ ደረጃዋን መቀየር መሆኑን ያስታውሳሉ:: ይህን እሳቤ ተፈፃሚ ለማድረግ እና የአገሪቱን ደረጃዋን ለማሻሻልም የሚያስችሉ አሰራሮችን ለማቀላጠፍ በኮሚቴ ደረጃ ባለድርሻ አካላት መቋቋማቸውን ይጠቁማሉ::
እንደ ዶክተሩ ገለፃ፣ የቢዝነስ ሥራ ምቹነት (Doing Business) መሻሻል በፈቃድ አሰጣጥ፣ የፋይናንስ በተለይ የባንኮች አሰራር ቅልጥፍና፣ የገቢ እና የታክስ ጉዳዮች ወሳኝ ናቸው:: ኢንቨስተሮች ጉዳያቸው በቀላሉ መፈፀም መቻላቸው ደግሞ ሁሉንም ይጠቅማል:: ስለዚህ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከተማ እና ክልል እንዲሁም ፌደራል ደረጃ የሚዘልቅ መሆኑን የሚያስረዱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ስራ የተሻለ በሆነ መልኩ እየተከናወነ ስለመሆኑ መናገር የሚቻለው ግን በፌደራል መስሪያ ቤቶች ብቻ ነው ይላሉ::
የኢንቨስትመንት እና ኢንቨስተሮችን ጉዳይ የመከታተል እንዲሁም ጥያቄም ሆነ ፍላጎታቸውን የማስፈፀም ትልቁ ስራ ወረዳ ላይ ስለመሆኑ አፅእኖት የሚሰጡት ዶክተሩ፣ በወረዳ ደረጃ ያለው የስራ አፈፃፀም ሲቃኝ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ::ችግሩም ለኢንቨስተሮቹ ምሬት እና ተስፋ መቆረጥ በአጠቃላይ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ሁነኛ ማነቆ መሆኑን ያሰምሩበታል::
በህዝብ አስተዳደር፣ በልማት አስተዳደር የሠለጠኑ ወጣቶች በብዛት ከዩኒቨርሲቲ ይወጣሉ:: እነሱን በዚህ ቦታ መድቦ ስራውን ማቀላጠፍ የሚቻልበትን መንገድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል::
የቢዝነስ ሥራ ምቹነት በማሻሻል የኢንቨስትመንት ፍሰት እና አቅም ለማጎልበት ሲታሰብ ሌላው ልዩ ትኩረት እና መፍትሄ ሊሰጠው የሚገባ አገሪቱ ውስጥ ስር ሰዶ የሚገኘው ግዙፍ የሙስና ወንጀል መከላከል እና ማስቆም መሆኑንም ይጠቁማሉ:: ኢንቨስተሮች ጉዳዮቻቸው በተቀላጠፈ መልኩ እንዲፈፀምላቸው ከሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ገንዘብ ዋነኛው ነው:: ሁሉም በሚባል መልኩ ለስራቸው እንቅፋት፣ ምሬት እና ተስፋ መቁረጥ ዋነኛ ምክንያት ሙስና ነው ሲሉ ይደመጣሉ ::
ሙስናን መቆጣጠር አለመቻል በኢንቨስመንት ፍሰት እና በኢንቨስተሮች ስነ ልቦና ላይ ከባድ ጫናን እንደሚፈጥር አፅእኖት ሰጥተው የሚያስገነዝቡት ዶክተሩ፣ በመሆኑን ችግሩን ለመከላከል መንግስት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ፣ የመገናኛ ብዙሃን በተለይ የምርመራ ስራዎች በማቅረብ ሙስናን በማጋለጥ ረገድ ጉልህ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል:: ለዚህ ደግሞ ተገቢውን ጊዜ መስጠት ብሎም ባለሙያዎችን በስልጠና ማብቃት ያስፈልጋል›› ይላሉ::
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ሌላው ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ያሉት የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ነው:: እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ለኢንቨስትመንት መጎልበት የመሰረተ ልማት አቅርቦት እና ተደራሽነት የግድ ነው::ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገነቡ ሃይል፣ ውሃ እና መንገድ ያስፈልጋቸዋል:: በተለይ የሃይል አቅርቦት እጅግ ወሰኝ ነው:: መንግስትም ባለፉት ዓመታት ግድቦችን የገነባው እና የተገነቡትን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የሚታትረው እንዲሁም ከፍተኛና የሃይል ማሰራጫ ጣቢያዎችን ለማስፋፋት የሚሮጠው ይህን ጠንቅቆ በመረዳት ነው::
የዓለም ባንክ የ“ቢዝነስ አመቺነት የደረጃ ሰንጠረዥ ለማውጣት እንዲያስችለው ካስቀመጣቸው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ምቹነት መለኪያዎች ውስጥ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አንዱ እና ዋነኛው ነው። በመሰረተ ልማት አቅርቦት እና ተደራሽነት ረገድ በተለይ የዓመታት የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንቱ እድገቱ ማነቆ ሆኖ የቆየው የሃይል አቅርቦት መሆኑንም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይስማሙበታል:: ችግሩ ስር የሰደደን መፍትሄ የራቀው በመሆኑ አንዳንድ ኢንቨስተሮች የሚፈልጉትም ሃይል ለማግኘት መንግስትን ከመጠበቅ ይልቅ በራሳቸው አቅም ግንባታ ማካሄዳቸውን ይስታውሳሉ::
የኤሌክትሪክ አቅርቦትን እንደ አንድ የቢዝነስ አመችነት ወይም የንግድ እና ኢንቨስትመንት ምቹነት መለኪያነቱ ችግር ለመሻገር በሚደረግ ጥረት እና ርብርብ ከፊት ለፊት ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን እና ታላቁ የህዳሴ ግድብም መጠናቀቅ ለኢንቨስተሮቹ የዓመታት ጥያቄ መልስ የመስጠት አቅሙ ከፍተኛ ስለመሆኑ ነው ያስገነዘቡት::
መንግስት የግድቡ ግንባታ በቶሎ ተጠናቆ ማበርከት የሚገባውን ሚና እንዲሰጥ ቁርጠኛ አቋም መያዙም የሚደነቅ መሆኑን አውስተው፣ ግድቡን በፍጥነት መጠናቀቁ አይቀሬ እንደሆነ እና በአሁኑ ወቅትም ግንባታው ሳይሆን ቀሪው እና ሊታሰብበት የሚገባው ተግባር ግብፅ እና ሱዳንን በዲፕሎማሲ ማሳመን መሆኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም::
በአጠቃላይ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን አመቺ በማድረግ ቀልብን በመሳብ ከዘርፉ ትሩፋት ለመቋደስ ልዩ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ አብይት ተግባራትን በሚመለከት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በሰጡት ምክረ ሃሳብ፣ የአገሪቱን ፖለቲካ ማረጋጋት ቀዳሚ መፍትሄ አድርገውታል::
ከዚህ ባሻገር ኢንቨስትመንቱ የሚመጥኑ ሰራተኞችን ማቅረብ፣ ከወረዳ እስከ ፌደራል ኢንቨስትመንት ላይ የሚመደቡ የስራ ሃላፊዎችን አቅም መከታተል እና ማጎልበት የግድ ይላል:: ኢንቨስትመንት እና ኢንቨስተሮች ከባንክ በተለይም ብድር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው በመሆኑም አገሪቱ ውስጥ ምን ያህል ባንኮች አሉ፣ ምን ያህል የማበደር አቅም አላቸው፣ የሚሉትን መቃኘትና ማስተካከል ያስፈልጋል::
የአገሪቱ የፋይናንስ ፖሊሲ መስተካከል ይኖርበታል:: በተለይም ሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የካፒታል ገበያን ለመመስረት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ በቶሎ እንዲፀድቅ ማድረግ ያስፈልጋል:: ይህም የውጭ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት እድል ያጎለብታል::መሰል ችግሮችን መሻገር ከተቻለም አገሪቱ ከፍተኛ አቅም እና የመበልፀግ ተስፋ እንዳላት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሳያስገነዝቡ አላለፉም::
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህር ፍሬዘር ጥላሁን በበኩላቸው፣ ኢትዮጰያ በሁሉ ረገድ ባላት ሃብት ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሻሻል እና ኢንቨስተሮችን ቀልብ ለመቆጣጠር እንደማትቸገር ያስረዳሉ::
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ አስር ሚሊየን በላይ ህዝብ በላይ ያላት አገር ናት:: ይህ ከፍተኛ ፍላጎት እና ገበያ እንዳለ ማረጋገጫን የሚሰጥ ነው:: ይህ ደግሞ ሌሎችን ሳይጨምር አገሪቱ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ገበያ እንዳላት ይመሰክራል::
ኢንቨስተሮችም ኢትዮጵያ ላይ መዋእለ ነዋያቸው ፈሰስ ለማድረግ ሲያስቡም የገበያ አዋጭነት፣ የደንበኞች ቁጥር፣ የግብአት እንዲሁም የመሰረተ ልማት አቅርቦትን እና ተደራሽነት መጠንን ይቃኛሉ:: ከዚህም በላይ ግን የፖለቲካ መረጋጋት የሰላም እና የፀጥታ ደህንነት መረጋገጥ ያሳስባቸዋል:: የቢዝነስ አመቺነት ‹‹Ease of Doing Business››ን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋማት የሚወጡ መረጃንም ያማትራሉ::
ኢትዮጵያ በቢዝነስ አመቺነት ስትቃኝ መሻሻሎችን ብታሳይም መሆን ከሚገባት ደረጃ ላይ እንዳልሆነች የሚጠቁሙት አቶ ፍሬዘር፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ከትርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ከሁሉ በላይ የተቋማት አቅም መጎልበት በተለይ ህግ እና ስርአትን በአግባቡ መተግበር የግድ መሆኑን ይናገራሉ ::
እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ገለፃ፣ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛ እንቅፋት ሙስና እና ሌብነት ነው:: ይህም አገሪቱ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የምትደርገውን ጥረት በእጅጉ የሚፈታተን ነው::
ከፍተኛ ሙስና በሚስተዋልባቸው አገራት ጉዳዩ የሚያልቀው በእጅ እንጂ በእግር በመሄድ አይደለም::በ20 ሰከንድ አሊያም ደቂቃ ሊያልቅ የሚችል ስራ 20 ቀን ሊወስድ ይችላል:: በዚህም ችግር ኢንቨስትመት በእጅጉ ይፈተናል:: ኢንቨሰተሮችም ወደ ስራ ለመጋባት አይፈልጉም:: ገበያውም ጤናማ አየር ለመተንፈስ እጅጉን ይቸገራል::
‹‹በማንኛውም አገር ሙስና ፣ አድሎአዊነት እና ዘረኝነት ካልተወገዱ ኢንቨስትመንት ወይንም የቢዝነስ አመቺነት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም›› የሚሉት አቶ ፍሬዘር፣ ከሁሉ በላይ የየቢሮው የሚስተዋሉ የሙስና እንቅስቃሴዎች መወገድ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት::
እያንዳንዱ ተቋማት ሙስናን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ጠንካራ እና የጋራ አቋም መያዝ እንዲሁም ህግ እና ስርአትን የማስከበር ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አፅኖት ሰጥተውታል::፡
‹‹ሙስንና ከመፋለም በተጓዳኝ ሰላምን በማስፈን ማንኛውም ኢንቨስተር በነፃነት ተንቀሳቅሶ ኢንቨስት ማድረግ እንዲቻል ማድረግ ነው:: ከጎጃም የመጣው ባሌ ላይ ከባሌ የመጣው ጎጃም ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይኖርበታል:: ይህን መተግበር ካልተቻለም የቢዝነስ አመቺነት የሚባል ነገር አይኖርም ›› ይላሉ::
ሌላኛው የመስፈር አከል የመሰረተ ልማት አቅርቦት እና ተደራሽነትም እጅግ መጎልበት እንዳለበት ይገልፃሉ:: እንደ እሳቸው ገለጻም፣ የኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ ኢንቨስትመንቶች የሚካሄዱት መሃል አገር ነው:: ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑ ኢንቨስትመንቶች ምርጫና መገኛ አዲስ አበባ ዙሪያ ነው:: ይህ የሆነው የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲሁም ትራንስፖርት አቅርቦት እና ተደራሽነት ውስንነት በመኖሩ ነው:: ምርቶች ጀብቲ ወደብ አልፈው መሃል አገር እስኪደርስ አሊያም ከመሃል አገር ተነስተው ወደብ እስኪደርሱ ያለው ሂደት ረጅም፣ አድካሚ እና ጊዜን የሚሻማ መሆኑ ለዚህ በቂ ምስክር ይሰጣል:: ችግሩም የአገሪቱ ኢንቨስትመንት መሮጥ ባለበት ልክ እንዳይሮጥ ከፍተኛ ማነቆ ይሆናል::
ይህን ችግር ለመሻገርም ፈጣን ባቡርን ጨምሮ ሌሎችም የትራንስፖርት አማራጮችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ ያመላከቱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፣ መንግስትን ለዚህ ችግር መፍትሄ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል:: በአጠቃላይ የቢዝነስ አመቺነትን ማሻሻል ከኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ከማህበራዊ መስተጋብር ብሎም ከፖለቲካ ትርጉሙ ጭምር መቃኘት እንዳለበትም አፅእኖት ሰጥተውታል::
ከ60 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየውን የንግድ ሕጉ መሻሻል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የንግድ ሥራ አመቺነት ከማሻሻል ባለፈ ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት ተደራሽነትና የካፒታል ፍሰትን የሚያመጣ ነው::ማሻሻያው በተለይ አገሪቱ ለዓመታት የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የምታደርገውን ጉዞ ለማሳለጥ፣ ንግዱ ዘርፍ የሚታዩ ሕገወጥ አሠራሮችን ለማሻሻልና ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል::
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013