መርካቶ ባህር ነው ፤ መርካቶን ዘርዝረን አይደለም በጨረፍታም አንጨርሰውም።ባንጨርሰውም በጨረፍታ እንመልከተው፡።መርካቶ የተመሠረተው በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።ጣሊያኖች የራሳቸውን መገበያያ እና መዝናኛ ሥፍራ ፒያሳ አድርገው ፤ ኢትዮጵያውያን በመርካቶ ውስጥ እንዲገበያዩ ያዘጋጁት ቦታ ነው።
አገር ከየጎራው ወጥቶ
አንቺን ብሎ ነቅሎ መጥቶ
ግሣንግሡን ጓሱን ሞልቶ
ኁልቆ መሣፍርትሽ ፈልቶ
ባንቺ ባዝኖ ተንከራቶ
እንደባዘቶ ተባዝቶ
ተንጠራውዞ ዋትቶ ዋትቶ
አይ መርካቶ
የምድረ ዓለም የእንጀራ እናት
ላንዱ ርካሽ ለሌላ እሳት
ላንዱ ፍትፍት ላንዱ ምትሃት
ላንዱ ሲሳይ ላንዱ ፍርሃት
ላንዱ ተስፋ ላንዱ ሥጋት
ላንዱ የሆይታ ቋት
አይ መርካቶ
ነፍስሔር ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ከአርባዎቹ ዓመታት በፊት አይ መርካቶ በሚል ርእስ ከጻፉት ግጥም ቀንጭበን የወሰድናቸው ስንኞች ናቸው።በመርካቶ ያለው የህዝብ ለህዝብ ትርምስ፣ የሻጩ የሸማቹ የጫኙ የአውራጁ ሁካታ፣ የአህዮችና የተሽከርካሪዎች የደላላው የሌባውንና የአጭበርባሪውን የለማኙ ግፊያና ግርግር እልልታና ኡኡታ የፖሊሱንና የደንብ አስከባሪው ስንጠቅሰው አሁንም በዘመናችን ስንመለከተው ግጥሙን የበለጠ ህያው አድርጎ ያሳየናል፡፡
መርካቶን የሚያደምቀው ግርግሩ ነው።የደላላው የነጋዴው የጫኙ የአውራጁ ጩኸት የመርካቶ ሕይወትና ድምቀት ነው። መርካቶ ግርግር ቢኖረውም ይስማማል፤ ይደምቃል፤ ግርግሩ ለመርካቶ ውበትና ድምቀት ነው።ጎዳናዎቹ ግርግር ይወዳሉ፤ የሰዎች ጩኸት ግርግር ወከባው ግፊያው የመኪናው ጡሩምባ ቢበዙም ለመርካቶ ግን ሕይወቷና ድምቀቷ ነው።
በሰንበት እና በበዓላት ቀን መርካቶን ያየ ይደነግጣል።የተወረረ ከተማ የሚባለውን ትመስላለች ።ለወትሮው መተላለፍ የማይቻልባቸው መንገዶች አደባባይ መስለው ይታያሉ።መርካቶ የሚኖሩ ይመስሉኛል በሰንበትና በአላት ቀናት በጎዳናዎቹ ላይ ኳስ ይጫወታሉ።የመንገዶቹን ሰው አልባ መሆን የተመለከተ ቢደነግጥ አይገርምም ፡፡
መርካቶ የአፍሪካ ትልቁ ክፍት የገበያ ሥፍራ በመባል ይታወቃል፤ ይህ እውነታ ግን አሁን አሁን እየተቀየረ ይመስላል።ነጋዴዎች በአክሲዮን ተደራጅተው በርካታ ህንፃዎችን እየገነቡ በመሆናቸው መርካቶ ህንፃ በህንፃ እየሆነች ፒያሳን እያስናቀች ነው።ትላልቅ የገበያ ማእከላት / ሞሎች የሚባሉት አይነት/ ተፈጥረዋል።
በፊት በአመዴ ገበያና በአዳራሽ ገበያ ከዚያም በጣና ህንፃ ባለህንጻ የነበረችው መርካቶ ፣አሁን የህንፃ አይነት የሚቆጠርባት ለመሆን በቅታለች።የራጉኤል አካባቢ በራጉኤል ህንፃዎች፣ ይርጋ ኃይሌ ህንፃ .፣የሳጥን ተራ ፣ ሚሊታሪ ተራ፣ ዱባይ ተራ በህንፃዎች ደምቀዋል።የአሜሪካ ግቢ ህንጻዎች እውን ሲሆኑ ደግሞ መርካቶ የቀድሞ ስሟን ከአሁኑም በላይ ትቀይራለች።ይህ ስፍራ ለልማት በሚል ከፈረሰ አመታት ቢቆጠሩም ከሚገነቡት ህንጻዎች ዲዛይን ብዙም የሚታይ የህንጻ ግንባታ አይስተዋልም።
መርካቶ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኝ የገበያ ሥፍራ ነው።ክልሉ ከዚህ እስከዚህ ነው የሚል መረጃ ባላገኝም ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ ጀምሮ ጎጃም በረንዳ ጨው በረንዳ አውቶቡስ ተራ መናኸሪያ በመሳለሚያ እህል በረንዳ የመሳሰሉትን ሁሉ ያካትታል ።በሰባተኛ በኩልም እስከ አብነት አደባባይ እና ምናለሽ ተራ ጎማ ተራ በርበሬ ተራን አካቶ በተክለሃይማኖት አደባባይ ሲዳሞ ተራ እና አሜሪካ ግቢን ጨምሮ ተመልሶ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ መጥቶ በአንዋር መስጊድ ቁጭራ ባንክና ይርጋ ሀይሌ ህንፃን የሚያካትት ነው።
በጠቀስኳቸው አካባቢዎች የንግድ አገልግሎት ብቻ አይደለም ሲካሄድ የነበረው፤በርካታ ነዋሪዎችም ይኖሩበት ነበር።ነዋሪዎቹ የቀበሌ ቤታቸውን ቁልፍ ለነጋዴዎች በጥሩ ገንዘብ እየሸጡ ፣ በወቅቱ ለነበሩ የቀበሌ ሹማምንትም እየሸጓጎጡ ወደ ሌላ ቦታ ኮብልለዋል።የመኖሪያ ቤታውን ወደ ሱቅ ቀይረው እየነገዱ ወደ ባለሀብትነት ጎራ የተቀላቀሉ በርካታ ናቸው።መኖሪያ ቤታቸውን ሙሉ ለሙሉ አንዳንዶችም በከፊል ለነጋዴዎች አከራይተው የገቢ ምንጭ እያፈሩ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ነጋዴ ቤታቸውን አከራይተው የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
በተለያዩ ሙያዎች መርካቶ ውስጥ ሱቅ ሳይኖራቸው የሚሠሩም በርካታ ናቸው።አናፂዎች፣ በወንበር ተራ ቆዳ ጫማ ሠራተኞች በሸራ ተራ የኤሌክትሪክና ቧንቧ ሠራተኞች በቧንቧ የመጋረጃና ሶፋ ወንበር አልባሳት ሠራተኞች በሚሊተሪ ተራ ታገኛላችሁ።የሻይ ቡና ማሽን የቴሌቪዥንና ፍሪጅ ጥገና ሠራተኞችን በጎጃም በረንዳ ታገኛላችሁ፡፡
ምን አለሽ ተራን የት ተውከው እንዳትሉኝ።እርግጥ ነው፤ ምን አለሽ ተራ የሚገርም አካባቢ ነው።እዚህ አካባቢ የማይገኝ ያገለገለ እና አዲስ እቃ የለም።የምን አለሽ ተራ መደብሮች ጣሪያቸው መጋዘንም ነው።ጣሪያቸው ያልተሸከመው የፕላስቲክና የመሳሰሉት ቁሳቁስ የለም።ያገለገለ እቃ የሚፈልጉ ከሆነ የትም የትም እንዳይሉ ፤ በቀጥታ ምን አለሽ ተራ ይሂዱ።የአዲስ አበባ መልሶ ልማት ለምን አለሽ ተራ ትልቅ አዱኛ ይዞለት የመጣ ይመስለኛል።ትእግስቱ ኖሮት አንድ ሰው ዱሮ የነበረውን እቃ ቢጠይቅ ሊያገኘው ይችላል።
ማህበራዊ ሃላፊነትን በመወጣት በኩልም ብዙም አይታዩም ።ዕድሮች መንገድና ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች ሲያሠሩ የመርካቶ ነጋዴዎች የሥራ ቦታቸውን እንኳ ለማሰማመር ብዙም ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም።በክረምት ዶሮ ተራ በርሜል ተራ ብትሄዱ መንገዱ በሰውና በተሽከርካሪ ተጨናንቆና ተጨማልቆ የት ነው የገባሁት ትላላችሁ።
ከአሥር ዓመት በፊት ሸራ ተራ አጎራባች 14 የሚደርሱ ወፍጮ ቤቶች ነበሩ።በወቅቱ ተሳቢ የጭነት መኪና በርበሬ አምጥቶ አስፈጭቶ ወደ ተለያዩ የገጠሪቱ አካባቢዎች ይወስድባቸዋል ፡፡የበርበሬ ወፍጮ ቤቶች ከሥራቸው ብዛት በማለዳ ተከፍተው እስከ ምሽቱ ስድስት ሰዓት አንዳንዴም ከቀን እስከ አዳር ሙሉ ይፈጭባቸዋል።የወፍጮ ቤቶቹን ገቢና አቅም ገምቱ፡፡
የሚያሳዝነው በዚህ አቅማቸው ከወንበር ተራ እንጨት መሰንጠቂያ ቤቶች ሰጋቱራ ( ዱቄት የሆነ የእንጨት ፍቅፋቂ እየገዙ) ከሌላም አካባቢዎች ቀይ አፈርና ሸክላ አምጥተው እያደቀቁ የበርበሬውን ዱቄት ቀላቅለው ሲሸጡ መያዛቸውን አስታውሳለሁ።ንፁኅ ሆነው የተገኙት ሁለት ወፍጮ ቤቶች ብቻ ነበሩ።በወቅቱ በፖሊስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም እሰራ ስለነበር ጉዳዩን አስታውሳለሁ።ሠፈሬ ስለሆነም አልተገረምኩም፤ ተቀጥተው ወደ ስራ ሲመለሱ ግን ቀኑን ሙሉ ሊፈጩ ቀርቶ ግማሽ ቀን የሚፈጩበት ገበያና ገቢ ብን ብሎ ጠፋ።
መርካቶ አሁንም ብዙ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደርግበት ስፍራ ነው።የአገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ በመዳፋቸው ውስጥ ያረጉ አስመጪዎችና አከፋፋዮች የሚገኙት በዚሁ ስፍራ ነው።ገበያውን እንዳሻቸው ያረጉታል።ህዝብ ብቻ ሳይሆን መንግስትም በእዚህ ህገወጥ ንግድ ተማሯል።ለእዚህም በዚህ አመት ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት አንዱ ምንክንያት በመርካቶ ያለው ግብይት መሆኑ በመንግስት ታምኖበት የንግድ እንቅስቃሴውን ስርአት ለማስያዝ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013