– በ25 ተማሪዎች ላይ የዲስፕሊን እርምጃ ወስዷል፤
– 14 የስታፍ አባላትንም ለይቶ ለዲስፕሊን የማቅረብ ሂደት ጀምሯል፤
አዲስ አበባ፡- የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በዳግም ቅበላ ተማሪዎቹን ማስተማር መጀመሩን ገለጸ፡፡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይማሩ በማድረጉ ሂደት ተሳትፎ ባላቸው 25 ተማሪዎች ላይ የዲስፕሊን እርምጃ መውሰዱን እና 14 የስታፍ አባላትንም ለይቶ ለዲስፕሊን የማቅረብ ሂደት መጀመሩን ገልጿል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ እየኖሩ ነገር ግን ለረዥም ጊዜ ክፍል ሳይገቡ መቆየታቸውን ተከትሎ ለአንድ ሴሚስተር እንዲቀጡ ሴኔቱ በወሰነው መሰረት ከጊቢ እንዲወጡ ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ተማሪዎች ከሄዱ በኋላ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተማሪዎች ከጊቢ በወጡበት ጊዜ ውስጥ መሰራት በሚገባቸው ዘጠኝ ያህል ነጥቦችን ለይቶ ቀንና ሌሊት ሲሰራ በመቆየቱ ለአንድ ወር ከ15 ቀን የነበረውን ከጊቢ ውጪ ቆይታቸውን ወደ ሦስት ሳምንት እንዲያጥር ተደርጓል፡፡ አብዛኛው ተማሪም ፒቲሺን ፈርሞ ይቅርታ ጠይቋል፡፡
እንደ ዶክተር ለሚ ገለጻ፤ ተማሪዎች ከጊቢ ውጭ በነበሩበት ጊዜ ከዩኒቨርሲቲው በቅርብ ርቀት ያሉ ወላጆችን በማወያየት ቤተሰብም ያላቸውን ጥያቄዎች አንስተው መልስ ተሰጥቶ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህም ተማሪዎቹ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እድል እንዲሰጣቸውና የሴሚስተር ቅጣቱ ቀርቶላቸው፤ አጥፊ ተማሪዎች ግን ተለይተው እርምጃ እንዲወሰድና ሌሎች ተማሪዎች በይቅርታ እንዲመለሱ መስማማት ተችሏል፡፡ ቤተሰብም ልጆቻቸውን እንደሚመክሩ ቃል ገብተው በሄዱት መሰረት የሴሚስተሩ ቅጣት በሴኔቱ ውሳኔ መሰረት እንደገና ተነስቶላቸው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
እንደ ዶክተር ለሚ ገለጻ፤ ከወላጆች ጋር በነበረው ውይይት ልጆቻችን ትምህርት እንዳይገቡ የሚያስፈራሩ አካላት አሉ፤ በጥቂት ተማሪዎች ተጽዕኖ ስር ወድቀዋልናም እርምጃ ሊወሰድ ይገባል የሚል ጥያቄ ከወላጆች ቀርቦ ነበር፡፡ ይሄንና ሌሎች መረጃዎችን መነሻ በማድረግም እርምጃ መውሰድ የተጀመረ ሲሆን፤ አጥፊና አስተባባሪ የሚባሉ ተማሪዎችን ለይቶ ለዲስፕሊን የማቅረብ ስራ እንዲከናወን፤ ከአካዳሚክ ስታፉም ሆነ ከአስተዳደር አካሉ በዚህ ላይ የተሳተፈ ፤ ተማሪዎች ወደክፍል እንዳይሄዱ የሚመክርና የሚያስተባብር ካለ፤ እነዚህን ለይቶ እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ይህ የእርምጃና የልየታ ስራ ተጠናቅቆ 25 ተማሪዎች የዲሲፕሊን ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡ 5 የአካዳሚክ ስታፍና 9 የአስተዳደር ስታፍ አባላትም ተለይተው ለዲስፕሊን እንዲቀርቡ እየተደረገ ሲሆን፤ ተጨማሪ መረጃዎችን የማሰባሰብ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
ከዚህ በኋላ ሰኞ እና ማክሰኞን ዳግም ምዝገባው ተካሂዶ ዕረቡ ዕለት ትምህርት መጀመሩን የገለጹት ዶክተር ለሚ፤ መመዝገብ ከሚገባቸው ተማሪዎች ውስጥ 93ነጥብ5 በመቶዎቹ ተመዝግበው ትምህርታቸውን መከታተል እንደቻሉና፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱም ጥሩ በሚባል ደረጃ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ቀሪዎቹም በተመሳሳይ ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንደሚጀምሩ ያላቸውን እምነት በመጠቆምም፤ ተማሪዎች ባለው ጊዜ ውስጥ የሁለቱንም ሴሚስተር ትምህርት እንዲከታተሉ በሚያስችል መልኩ የትምህርት መርሃ ግብሩ እንደሚከለስም ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም የዲስፕሊን እርምጃ የተወሰደባቸው ተማሪዎች ካልተመለሱ ክፍል አንገባም የሚሉ ጥቂት ተማሪዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ ዓላማቸው መማር እንደመሆነና ወክለው የመጡትም ራሳቸውን መሆኑን ተገንዝበው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መክረዋል፤ ይሄን የሚያራምዱ ጥቂት ተማሪዎችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡ ሆኖም ይሄን በመዘንጋት ዳግም ወደሌላ ችግር ለመግባት የሚታትሩ ተማሪዎች ካሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ወላጆችም ይሄን ተገንዝበው ልጆቻቸውን ሊመክሩና መስመር ሊያሲይዙ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
እንደ ዶክተር ለሚ ገለጻ፤ ተማሪዎች ጥያቄ ማንሳትና ጥያቄዎቻቸውን በሕግና በስርዓት ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበው መልስ የማግኘት መብታቸው ነው፡፡ ይሄን ሲያደርጉ ግን እየተማሩና የመጡበትን ዓላማ እየከወኑ መሆን እንዳለበት መረዳት አለባቸው፡፡ በዚህ ላይም ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት ያለበት ሲሆን፤ በተለይ ቤተሰብ ከፍተኛ ሚና ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ወላጅ ልጁን ልኮ መቀመጥ ብቻ ሳይሆን የልጁን የትምህርት አቅምና ባህሪ በተለያየ አግባብ መከታተል ይኖርበታል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ እና የተማሪዎችን ባህሪና ስነምግባር ለመከታተል የሚያስችሉ የተለያዩ ሰነዶች የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችን ልምድ በመውሰድ ተዘጋጅተዋል፤ አሰራሮችም ተዘርግተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አስካሁን ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች ባይኖሩም፤ ለወደፊት መልኩን ቀይሮ ችግሩ እንዳይመጣ በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከጸጥታም ሆነ ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ካሉም እየተፈተሹ ክፍተቶች እንዳይኖሩ እየተሰራ ነው፡፡ ለአብነት ከጊቢ ጸጥታ ጋር በተያያዘ የጊቢውን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ ወደ 200 የሚሆኑ የጸጥታ ሰራተኞቹን ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ጠንካራ ስልጠና እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም በዩኒቨርሲቲው ከመምህራን ባሻገር ከተማሪዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩ ፕሮክተሮች፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የላይበራሪ አገልግሎት የሚሰጡና ሌሎችም አካላት ጋርም ሰፊ ውይይትና ግምገማ ተደርጎ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም ተቀምጧል፡፡
ተማሪዎችን ለማነጽ ዋናው ጉዳይም በጭንቅላት ላይ መስራት እንደመሆኑ አነቃቂ ንግግሮችና ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እየተደረገ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ወደ 600 ለሚሆኑ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የቦርድ ሰብሳቢው አነቃቂ ንግግር አቅርበውላቸዋል፡፡ ለቀጣይ ቅዳሜም ዶክተር ምህረት ደበበ ተጋብዘዋል፡፡ ይሄን መሰል ሥራ ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚሰራ ሲሆን፤ ተማሪውና ማህበረሰቡ እንዲዋሃድ፣ አንዱም አንዱን እንዲረዳ የሚደረግ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ወንድወሰን ሽመልስ