ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
በውሸት፣ በማስመሰል ያልተማረረ እዚች አገር ላይ ማን አለ? እኔ በበኩሌ ምርር ብሎኛል። መሽቶ በነጋ ቁጥር የምሰማው፣ የማነበው ሁሉ ውሸት ነው። በየማህበራዊ ሚዲያው ላይ የህዝቦችን አንድነት የሚያላላ የጠብ ቁርሾ ማንበብ ሰልችቶኛል። ዋሽቶ ማስታረቅ እያለ ዋሽተው የሚያጣሉ የበዙበት ዘመን ላይ ቆመናል።
እዛም እዚም መሰረተ ቢስ የውሸት ትርክቶችን መስማት ጆሯችን ሰልችቶታል። አገር የሚያቆም ጠፍቶ ሀገር ለማፍረስ መሽቀዳደም የብዙዎቻችን አላማ ሆኗል። ከአገር በላይ፣ ከህዝብ በላይ ምን ደስታ እንዳለን አላውቅም፡፡
የተማረውም ያልተማረውም በየፊናው ነገር ሲፈትል፣ የሀሰት ወሬ ሲፈጥር የሚውል ነው። አብዛኞቻችን ከአገር ግንባታ ይልቅ እውቀታችንን ለአገር መከራ እያዋልነው ነው። ለክፋትና ለተንኮል የምንጠቀምበትን አእምሮ ሀገር ሊለውጥ በሚችል ተግባር ላይ ብናውለው ይሄኔ የት ባደረስን ነበር።
ሰው እንዴት ሀገር ለማፍረስ ይማራል? ሰው እንዴት አገር ለመጉዳት ይሰለጥናል? ለዚች አገር በአንድነት የምንቆመው መቼ ነው? ከክፋት ወጥተን ለጽድቅ ስራ የምንተጋው መቼ ነው? እያንዳንዳችን እኮ የቆምነው በአባቶች ደምና አጥንት በተገነባች አገር ላይ ነው።
ዛሬ ላይ እንደፈለግን የምንሆነው እኮ ለእኛ ሲሉ በተሰዉ ታማኝ ነፍሶች ነው።እስኪ ከግለሰብነት ወጥታችሁ እንደ ህዝብ አስቡ። እስኪ እንደ አገር እናስብ። እናንተ ባይርባችሁ ብዙ የተራቡ ህዝቦች ያሉባት አገር ናት። እናንተ ባትቸገሩ ብዙ ችግረኛ ወገኖች ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉባት አገር ናት። እስኪ ህይወትን ካለ መልካምነት ለአፍታ አስቧት? ህይወት እኮ ያለ ጥሩነት ምንም ናት።
እኛ በአባቶቻችን እንደኮራን ሌሎችም በእኛ የሚኮሩበትን እድል እንፍጠር። እስካሁን ድረስ አገራችን በውሸታሞች ወሬ ብዙ ነገር ደርሶባታል። እየደማች..እየቆሰለች ዘመናት አልፏታል። ህዝባችንን በተሳሳተ ትርክት ፍቅሩን፣ አንድነቱን ያጣበት ጊዜ ብዙ ነው።የእኛን ጨምሮ የብዙዎቻችን ህይወት በምንናገረው ቃል ልክ የተሰፈረ ነው። ቃላት በእያንዳንዳችን ህይወት ላይ ገዳይና አዳኝ ሆነአሉ።አጼ ምንሊክ በክተት አውጀው ህዝቡን ለዘመቻ ጠርተው አድዋን የሚያክል ታላቅ ድል ተፈጥሯል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በአመስጋኝና በመራቂ ቃላቸው በህዝቦች መካከል ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥረዋል። ቃላት እንዳደረግናቸው ናቸው። የቃልን ሀይል በሚገባ የተረዳ ሰው በህይወቱ ምንም ፈልጎ የሚያጣው አይኖርም። ሁሉ ነገራችን በምንናገረው ቃል ልክ የእኛ የሚሆን ነው።ቃልን በትክክለኛው ቦታ በአግባቡ መጠቀም ከቻልን ፈልገን የምናጣው ምንም ነገር አይኖርም።
አብዛኞቻችን ግን ከመልካም ምላስ ጎለን በእርግማንና በትችት በወቀሳም የምንኖር ነን።በእስካሁኑ ህይወታችን ሳይሳኩ የቀሩ ነገሮች ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከምንናገራቸው ቃላት ጋር ግንኙነት ያላቸው ስለሆኑ ነው።
የፖለቲካ ሰዎችን፣ የእምነት አባቶችን፣ የንግድ ሰዎችን ስለ ቃል ብትጠይቋቸው በደንብ አድርገው ይነግሯችኋል። ፖለቲከኞች ህዝቡን እንዳሻቸው የሚዘውሩት በቃል ነው። የእምነት አባቶች በፈጣሪና በተፈጣሪ መካከል ያለውን የእምነት ድልድይ የገነቡት በቃል ነው።ስለ ቃላት ኃይል ካላወቃችሁ ምንም ናችሁ።
ሰው ማንን ይመስላል ንግግሩን የሚል ሀገረኛ አባባል አለ።መልካም ቃላት አብረዋችሁ እስካሉ ድረስ ሁሌም አሸናፊዎች ናችሁ። አብዛኞቹ ስኬታማ ሰዎች በመልካም ቃል የተሞሉ ናቸው። የሚንቀሳቀሱት ምላሳቸው ላይ አመስጋኝና መራቂ ቃላቶችን ይዘው ነው።
ሁሉም ነገር ተለዋዋጭ በሆነበት ዓለም ላይ እየኖራችሁ ልትተማመኑበት የሚያስችላችሁ አንድ ነገር ቢኖር መልካም ምላስ ነው። መልካም ምላስ ከያዛችሁ በየትኛውም ዘመን ላይ ከየትኛውም ማህበረሰብ ጋር ተግባብታችሁ መኖር ትችላላችሁ። አንድን ሰው በጥሩ ቃል ልታሸንፉት ካልቻላችሁ በሌላ በምንም አታሸንፉትም። ዓለም ለመልካም ሰዎች በሯን የከፈተች ናት።
ብዙዎቻችን በክፋት በእርግማን ተሞልተን በተዘጋች ዓለም ላይ ቆመን የማይከፈትን በር የምንቆረቁር ነን።በሮቻችን የሚከፈቱት በመልካም ቃል ነው።ህልማችን የሚሳካው ለሌላው የሚሆን መልካም ነገር ሲኖረን ነው። ወደፊት የምንሄደው ሌሎች እንዲሄዱ መፍቀድ ስንችል ነው። ስለራሳችን ብቻ እያሰብን፣ እኔን ብቻ እያልኩ የምከፍተው በር፣ የምፈጥረው ተዐምር የለም።
ሁሉም ነገር በልባችን ውስጥ ባለው ቅንነት ልክ ወደ እኛ የሚመጣ ነው። በአሁኑ ሰዓት ስለ ቃላት ሀይል የሚያውቁ ጥቂቶች ናቸው። እነርሱም ራሳቸውን ባርከው፣ በብዙ ፍቅር፣ በብዙ ደስታ የሚኖሩ ሆነው ከፊታችን የቆሙ ናቸው። እ ነርሱ በእያንዳንዱ የህይወት መስክ ላይ ተሳክቶላቸው የምናያቸው ወይኔ እነሱን ባረገኝ ስንል የምንቀናባቸው ናቸው።
ብዙዎቻችን ቃል መግባቢያ ብቻ ይመስለናል እውነቱ ግን ሌላ ነው ቃል ወደምንፈልገው ቦታ ለመሄድና ለመድረስ መንገድ የሚጠርጉልን ኃይላችን ናቸው። ቃላት ከመግባቢያነት ባለፈ የእያንዳንዳችንን እጣ ፈንታ የመወሰንም አቅም አላቸው።የዚህ ዓለም ተአምራቶች ያሉት በምንናገራቸው ቃላቶች ውስጥ ነው።ባጠቃላይ ቃላት የደስታ ሁሉ ምንጮች ናቸው ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡
በልባችሁ ላይ መራቂና አወዳሽ ቃላት ከሌሉ ጥሩ ነገራችሁን ለማጣት እየተዘጋጃችሁ እንደሆነ አስቡት። ራዕያችሁ እየመከነ፣ ተስፋችሁ እየሞተ እንደሆነ ቁጠሩት። መተማመኛ የሚሆን ምንም ነገር ሊኖራችሁ ይችላል። ሀይል እንዳለው ቃል የሚጠቅማችሁ ግን ምንም ነገር የለም።የሚያስፈልጋችሁ ነገር ሁሉ በምትናገሩት ቃላት ላይ የተቀመረ ነው፡፡ አንዳንንድ ሰዎች ሁሉ ኖሯቸው እንዴትና ምን መናገር እንዳለባቸው ሳያውቁ ድሀ ሆነው ይኖራሉ። አንዳንዶች ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል ምንም ሳይኖራቸው በሚናገሩት ቃል ብቻ ሁሉን አግኝተው በሙልአት ይኖራሉ።
ቃላት የንግስና በትር፣ የሹመት ካባ ናቸው። ዘወትር መልካምና ለሌላው ክብርና ፍስሀ መሆን የሚችሉ ቃላትን ተናገሩ።ጥቂት ውብ ቃላትን፣ ጥቂት የጥንካሬ ቃላትን፣ አነቃቂ የሆኑ መልካም ንግግሮችን በመናገር በህይወታችሁ ላይ የሚመጣውን ለውጥ እስኪ አስተውሉት። እየተራገማችሁ፣ እየናቃችሁ፣ እየወቀሳችሁ በውሸት ሀገርና ህዝብ እየጎዳችሁ ከመክሰር ባለፈ የምትፈጽሙት ጀብድ የለም።
ከመጉደል ባለፈ የምትሞሉት የህይወት ክፍል አይኖራችሁም። በህይወታችሁ ሞልታችሁ የምትፈሱት በመልካም ቃላቶቻችሁ በኩል ነው።ሰዎች እንደፈለጉ ሊናገሯችሁ ይችላሉ፤ ከእናንተ የሚወጣው ቃል ግን ነገሩን ሊያባብሰውም፤ ሊያበርደውም ይችላል።መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች የሚለው ሀገረኛ አባባል በእያንዳንዳችን ህይወት ላይ ልክ ሆኖ ይገኛል። እኛ የምንናገረውን ቃል ነን።አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ በተቆጣና በተናደደ ስሜት እየጮኸ ሊናገራችሁ ይችላል።ቁጣው ላይ ውሀም ሆነ ቤንዚል የምታርከፈክፉት እናንተ ናችሁ።የተቆጣን ሰው በመልካም ምላስ ማረጋጋት ጥበብ ነው።
ተናዶ ቡጢ ሊሰነዝር የመጣን ሰው በጥሩ ንግግር አረጋግቶ እንደመመለስ አስተውሎት የለም።ብዙዎቻችን ሰዎችን እንዳመጣጡ የምንመልስ ነን። ከተናደደው ጋር መናደደድ፣ ከተቆጣው ጋር የምንቆጣ፣ ካበደው ጋር የምናብድ ነን።ከብዙ አይነት ሰዎች ጋር የምንኖር ነን።ማህበራዊነት ብዙ ነገር ነው። ከሰዎች ጋር ለመግባባት አይቶ ማለፍ፣ ሰምቶ መቻል ያስፈልጋል። ድንጋይ ለወረወረባችሁ ሁሉ ድንጋይ የምትወረውሩ ከሆነ፣ የሰደባችሁን ሁሉ የምትሰድቡ ከሆነ በመኖር ውስጥ የምታርፉት ምንም አይኖራችሁም።አንዳንድ አስተዋይ ሰዎች የተወረወረባቸውን ድንጋይ ከመወርወር ይልቅ በተወረወረባቸው ድንጋይ የሚያምር ጡብ የሚሰሩ ናቸው።
ታግሎ በመጣል ሳይሆን፣ በመሳደብ፣ በማንቋሸሽ ሳይሆን፣ በእርግማን በነገር በእንደዚህም ሳይሆን በመልካም ስብዕና፣ በመልካም ንግግር ሰዎችን ማሸነፍን ልመዱ። በአሁኑ ሰዓት የሀገራችንን አንድነት እየበረዙ ያሉት ከከፉ አንደበት የሚወጡ እኩይ ቃላቶች ናቸው። ቃላት በወጉ ካልተጠቀምንባቸው ጉዳት የማድረስ ኃይላቸው ከፍተኛ ነው። ሩዋንዳ ውስጥ ያን ሁሉ የንጹሀንን እልቂት ያስከተለው ቃል ነው።
ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ዛሬም ድረስ እንደ ምክንያት የሚነሳው ቃል ነው።ቃላት የጥቅማቸውን ያክል ጉዳታቸውም የከፋ ነው።በአሁኑ ሰዓት አገራችን ውስጥ እዛም እዚም የምንሰማቸው መሰረተ ቢስ የጥላቻ ንግግሮች አሉ።በየማህበራዊ ሚዲያው የምንለቃቸው መልዕክቶች አገር የማፍረስ ሀይል ያላቸው ናቸው።
ቃላትን ስንጠቀም ተጠንቅቀን መሆን አለበት።መናገር የሚኖርብኝ በኔ ንግግር ሌላው እንደማይጎዳ እርግጠኛ ስሆን ብቻ ነው። ከዛ ባለፈ የኔ ንግግር፣ የእኔ ቃል ሌሎችን ከማስደሰትና ከመባረክ ባለፈ ለሌሎች የሀዘን ምክንያት ከሆነ ጥቅም እየሰጠሁ አይደለም ማለት ነው።
ህዝብን ከህዝብ፣ ሀይማኖትን ከሀይማኖት፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት ስራዬ ብለው የተሳሳቱ መልዕክቶች የሚያሰራጩ ራስ ወዳድ የሆኑ ጥቅመኛ ግለሰቦች በየቦታው አሉ። በህዝቦች መከፋፈል የግል ጥቅማቸውን ለማስፈጸም ውሸት ፈብርከው፣ ያልሆነና ያልተደረገ ነገር እንደሆነና እንደተደረገ በማስመሰል ህዝብ የሚያወናብዱ ብዙዎች አሉ።
አሁን ላይ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የእኛን አብሮነት የእኛን አንድነት የምትፈልግበት ጊዜ ነው።ስሜታዊነት ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም። ነገሮችን የምናይበት የሰከነ ልቦና ያስፈልገናል። በተሳሳተ ወሬ ተመርተን ጥቂት ራስ ወዳድ የሆኑ ግለሰቦች በሚለቁት የተሳሳተ መልዕክት ከመደናገርና ለጥፋት ከመቸኮል ይልቅ መልዕክቱን በሰከነ ልብ ማየቱ የተሻለ ነው ብዬ አስባለው።መልካም ቃላት ወደፊት የሚያራምዱ ምርኩዝ ናቸው። እኩይ ቃላት ደግሞ ወደ ፊት እንዳንሄድ የሚያደናቅፉ እንቅፋቶች ናቸው። ከእንግዲህ ጥሩ ሰው ሁኑ።ለሀገራችሁ የሚበጅ መልካም ቃላትን አመንጩ።
ዋሽታችሁ ከማጣላት ይልቅ ዋሽቶ ማስታረቅን ባህል አድርጉ።እስካሁን በተሳሳቱ ወሬዎች ብዙ ነገር ሆነናል።አሁን ግን በማሰብ የምንኖርበት ጊዜ እንዲሆን እፈልጋለሁ።ፕሮፌሰር ኬሊ ጃሚሰን ስለ ቃላት ሲናገር ‹ስለ ቃላት ያላችሁ ግንዛቤ ከፍ ባለበት ቅጽበት በራስ ተነሳሽነት የምታደርጉት ጉዞ ጀመረ ማለት ነው።ይህ ሲሆን ለስኬት ራሳችሁን ታነሳሳላችሁ። ድካማችሁ ተለውጦ ግርማ ሞገስን ትላበሳላችሁ።
ቃላት የወደፊት ጉዟችሁን ለማቃናት እንዲረዷችሁ የተዘጋጁ ናቸው።ይህ የሚሆንበት ጊዜ ደግሞ አሁን ነው።ቃላቶቻችሁ ከበድ ያሉ አሳማኝና ለሰዎች የሚጠቅሙ ከሆኑ ደግሞ ራሳችሁን ለምትፈልጉት ነገር እያዘጋጃችሁ እንደሆነ እርግጠኛ ሁኑ ነበር ያለው።እመኑኝ መልካምና አስደሳች ቃላትን ተናግራችሁ የምታጡት ነገር የለም።መጥፎ ነገሮች ሁሉ የተቀመጡት ለመጥፎ ተናጋሪዎች ነው።
የምታሸንፉት ጀግና ስለሆናችሁ አሊያም ደግሞ ስለበረታችሁ አይደለም ሰዎች መስማት ስለሚፈልጉት ነገር ስታወሩ ብቻ ነው። ይሄ እውነት በየትኛውም የህይወት መስክ ላይ የሚሰራ ነው። ጥሩ ነገር ሰርታችሁ ሀገራችሁን መጥቀም ባትችሉ እንኳን ሀገርና ህዝብ የሚጎዱ መጥፎ የውሸት ተረት ባለማሰራጨት የበኩላችንን መወጣት ይኖርብናል። እንዳልኳችሁ ቃላትን መጠቀም ያለባችሁ ለበጎ ነገር ብቻ ነው።
ቃላትን ለክፉ ነገር መጠቀም ያጠፋል። የሀገሬ ሰው ወሬ ምን ያክል አስከፊ እንደሆነ ሲገልጽ ‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው› ይላል። በሰዎች ልብ ውስጥ ሀሴትን ለመሙላት ካልሆነ በስተቀር አፋችሁን ለሀጢያት አትክፈቱ።ምላስ አጥንትን የመስበር ጉልበት አለው። ዛሬ የተናገርነው እያንዳንዱ ነገር በተለያየ ሚዲያ ላይ መልኩን ቀይሮ የሚወራበት ዘመን ላይ ነን።ለሁላችንም ስንል አንደበታችንን አላስፈላጊ ከሆኑ ንግግሮች፣ ወቀሳዎች መቆጠብ ይኖርብናል እያልኩ ላብቃ።ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 14/2013