አዲስ አበባ፡- የሐረሪ ክልል ህገ መንግሥት ላይ ጥያቄ ከተነሳ የራሱ የሆነ ሂደት ስላለው ሂደቱን ጠብቆ ሊሻሻል እንደሚችል የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ጠቆሙ፡፡
የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲ በድሪ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት፤ ክልሉ በዋነኛነት በከተማው ውስጥ ያለው የሐረሪ ሕብረተስብ እና በገጠሩም አካባቢ ያለው የኦሮሞ ብሔረሰብ በጋራ አቋቁመውታል፡፡ የክልሉ ሕገ መንግሥቱ የሐረሪ ሕዝብ የክልሉ የሥልጣኑ ባለቤት ነው የሚለው ክልሉ በዋናነት ሲቋቋም የሐረሪን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ስለሆነ ነው፡፡
በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ረገድ ውስንነት ይታያል፣ አንዳንዶች ጫና ተደርጎብናል ይላሉ ለሚለው ጥያቄ አቶ ኦርዲ በሰጡት ምላሽ፤ ሁሉንም ያቀፈ አካሄድ መከተል እንዳለብን ለመግለጽ የተለያዩ የሕዝብ መድረኮችን ስናካሂድ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ ብለዋል፡፡
‹‹ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከሥልጣን ክፍፍል አኳያ በእኛ ክልል ሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች በኃላፊነት ደረጃ እንዲመደቡ ተደርገዋል፡፡ በተለይ እነዚህን ጥያቄዎች በተመለከተ ለውጡ ከተጀመረ በኋላ የበለጠ ፍትሐዊ ለመሆን እየሞከርን ነው›› ያሉት አቶ ኦርዲ፤ ሕገ መንግሥቱ ላይ ጥያቄ ካለ ሕዝቡ ውሳኔ የሚሰጥበት የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው፡፡ በዚህ መልኩ ታይቶ ሕብረተሰቡ ተወያይቶ በሚመለከታቸው አካላት ሂደቱን ጠብቆ የሚሻሻልበት ሥርዓት ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
በወንድወሰን መኮንን