ኢትዮጵያ መላው ጥቁር ሕዝቦች ለነፃነትና እኩልነት የሚያደርጉትን ትግል ከፊት ሆና መርታለች፡፡ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ የሆነውም ሀገሪቱ የአፍሪካውያን የነፃነትና እኩልነት ትግል ፊት አውራሪ በመሆኗ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን ነፃነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋዕት ለሆኑ ጀግኖች ክብር ሲባል የተሰጠ ገፀ በረከት ነው፡፡
አፍሪካውያንም በ32ኛው የህብረቱ ጉባዔ የነጻነቱን ጎህ በቀደደችው ኢትዮጵያ ምድር ላይ ለአንድ አህጉራዊ ዓላማ ለመምከር ሲመክሩ ቀናትን አሳልፈዋል፡፡ አጋፋሪዋ አዲስ አበባም እንግዶቿን ተቀብላ እስከ መሸኘት ቁርጠኛ አቋሟን ስታሳይ ቆይታለች፡፡ የተሰጣትን ኃላፊነት እየተወጣች ያለችው አዲስ አበባ ከየአገራቱ በመጡ ተሳታፊዎች ሙገሳ ቀርቦለታል፡፡
ግብፃዊቷ ጋዜጠኛ ማይ ታረክ አል ጂብሊ በጉባኤው የመጨረሻ ቀን የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ መረጃን ለአገሯ ህዝብ ልታደርስ ማልዳ ተገኝታለች፡፡ ተሰብሳቢዎችና ሌሎች አካላት ገብተው ጉባዔው እስኪጀመር በአዲስ አበባ ስለነበራት ቆይታ እንድትነግረኝ ራሴን አስተዋውቄ ‹‹አዲስ አበባ በአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ ያላትን ሚና እንዴት ታይዋለሽ?›› የሚል ጥያቄዬን አስቀደምኩላት፡፡
‹‹መቀመጫው አዲስ አበባ በሆነውና ሁሉን አፍሪካ አንድ በሚያደርገው የአፍሪካ ህብረት በመሰብሰብ ስለ አህጉራዊ ጉዳይ ከማሰብ በተጓዳኝ ለጉባዔው ስኬት አዲስ አበባ ግንባር ቀደም ናት›› ትላለች፡፡
‹‹አህጉሩ ላይ ያሉት ዜጎች እንዲህ ባለ መንገድ ተደራጅተው የራሳቸውን የአንድነት አጀንዳ ለማካሄድ ሁነኛ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ እድለኛ ናት፡፡ ትልቅ አህጉር የመገንባት ሚና የሚጫወተው የአፍሪካ ህብረት መቀመጫው አዲስ አበባ መሆኑም በበጎ መልክ የሚታይ ነው›› በማለት ለአዲስ አበባ ያላትን የከፍታ አመለካከት ማይ ታረክ ገልጻለች፡፡
ማይ እንደምትለው፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን የመሳሰሉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን ማዘጋጀት በመቻሏ በእርግጥም የአፍሪካ መዲና መባሏ ይገባታል፡፡ በተለይ አሁን ላይ እየተሠራበት ያለው ‹‹የቪዛ ሲስተሙ›› ከተማዋን ብሎም ከሌሎች አገራት ጋር ለማስተሳሰርና አፍሪካውያን የሚኖራቸውን የእርስ በእርስ ግንኙነት በቀላሉ ማጠናከር ይችላል፡፡
በጉባዔው ለመሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ የከተመው የኬፕ ቨርዴ ተወላጅ አንቶኒዮ ዲዎስ እንደሚለው፤ ኢትዮጵያውያንና ኬፕቨርዲያውያን በደም የተሳሰሩ ያህል ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ማንኛውም ኬፕቨርዲያው ሰው አዲስ አበባ ቢመጣ አገሩ እንዳለ ነው የሚያስበው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በተፈጥሮ ከመመሳሰሉ በላይ አዲስ አበባ የሁሉም አፍሪካዊ መሰብሰቢያ መሆኗ ነው፡፡
ይህ ስሜት በሁሉም ላይ መጋራት አለበት፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ባለውለታ መሆኗና እንግዶች እንደልባቸው ተዘዋውረው ያሻቸውን ማድረጋቸው ምስክርነት ነው፡፡ ነዋሪዎቿ ከሁሉም አገራት የሚመጡትን እኩል በመቀበል እኩል ያስተናግዳሉ፡፡ በእንግዳ ተቀባይነቷ ሌላውን መስበክ የሚችል ተወዳጅ ህዝብ ያለባት አዲስ አበባ በአጋጣሚ ብቻ ሳይሆን አዘውትረው ቢመላለሱባት የማትጠገብ ናት ሲል ያብራራል፡፡
ሌላኛዋ የህብረቱ ጉባዔ ተሳታፊ ካሜሮናዊቷ ሲሳኮ ታምኮ በበኩሏ፤ ‹‹ያለ ምንም ክርክር አዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና ከተማ ስለመሆኗ አገሪቷ በአፍሪካ ውስጥ ያላትን ታሪክ መውሰድ በቂ ነው›› በማለት አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና የሆነችው በአጋጣሚ አለመሆኗንም ገልጻለች፡፡ ‹‹እኔ ከካሜሮን ወጥቼ አዲስ አበባ ስመጣ እንደ አገሬ ዋና ከተማ ነው የማያት፡፡›› ስትል ለመዲናዋ ያላትን ክብር ገልጻለች፡፡
‹‹እንዲህ አይነት አህጉራዊ ጉባዔዎች ሲካሄዱ ሰዎች መረጃን በቀላሉ ሊያገኙ የሚችሉባቸው እድሎች በከተማዋ ሊኖሩ ይገባል›› የምትለው ሲሳኮ፤ በተለይ በከተማዋ ያሉት የህትመት ሚዲያዎች ይህንን በትኩረት ቢሠሩ አሁን ካለው አድናቆት በላይ የሚያስመሰግን ታሪክ ሊኖራት እንደሚችልም ነው ያስገነዘበችው፡፡
ሲሳኮ ይህንን ያለችው ጉባዔው በሚካሄድበት የአፍሪካ ህብረት አካባቢ የየእለቱን የህብረቱ ውሎ የሚገልጽ የጋዜጣም ሆነ የመጽሔት ስርጭቶች አለመኖራቸውን በመታዘብ ነው፡፡ የከተማዋን ኃያልነት ሊያመለክቱ የሚችሉ ብዙ ጉዳዮች እንዳሉና እነዚህም በተለያዩ የመረጃ ድርሳናት ተከትበው በቀላሉ ሊገኙ እንደሚገባም ነው ሲሳኮ የምታሳስበው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
በአዲሱ ገረመው