ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ምርጫ በአንድ ሀገር ላይ የዘመናዊነትና የስልጣኔ ምልክት ነው:: በተለይ በሀሳብ ብልጫ ሲሆን በዛች ሀገር ላይ ያሉ ማህበረሰቦች ይበልጥ ተጠቃሚ የመሆን እድላቸው የሰፋ ይሆናል:: ምርጫ የራስንም የሀገርንም መጻኢ እድል የምንወሰንበት መሳሪያችን ነው:: አስተዋይና ልባም ዜጎች የሚበጃቸውን መሪ ለመምረጥ ይጠቀሙበታል:: በሀሳብ የበላይነት የሚመራ ካልሆነ ምርጫ ብቻውን ትርጉም አለው ብዬ አላምንም::
፡ ለዚህ ማሳያ እንዲሆነን ያለፉትን የሀገራችንን አምስት ምርጫዎች ማየት በቂ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የምርጫ ስርአት ታውቁታላችሁ.. የዘንድሮውን ሳንቆጥር እስካሁን ድረስ በሀገራችን አምስት ምርጫዎች ተካሂደዋል:: ሁሉም ምርጫዎች ግን ህገ መንግስቱ በሚፈቅደውና በሚያዘው መሰረት የተከናወኑ አልነበሩም:: የይስሙላ ምርጫ ታውቃላችሁ? ልክ እንደዛ ነበር::
የአንድ ፓርቲ የበላይነት የገነነበት፣ የህዝቦች ተሳትፎ ያልታየበት፣ በብዙ ውሸትና በብዙ ማጭበርበር የተሞላ ነበር:: እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ነበረ ብዬ አላስብም ፤ምክንያቱም ብዙሃኑ መራጭ ከሚፈልገው ይልቅ የማይፈልገውን እንዲመርጥ የሚገደድበት ስርዓት ስለነበር ነው:: ምርጫ ማለት ህዝብ የሚፈልገውን ፓርቲ ካለምንም ተጽዕኖ በነጻነት መምረጥ ሲችል ነው:: ምርጫ ማለት የህዝቦች ነጻ ተሳትፎ ነው::
በርካታ ሀሳቦች ተፈጥረው ከነዛ በርካታ ሀሳቦች መካከል በህዝብ የበላይነት አንዱ አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ያኔ ምርጫ ተካሄደ ማለት እንችላለን:: ምርጫ ወቅቱን የጠበቀ፣ ተአማኚነት ያለውና የብዙሃን ተሳትፎ የተረጋገጠበት ሲሆን ነው ህጋዊ የሚሆነው:: ባለፉት ምርጫዎች ደግሞ ይሄ አልነበረም:: ጥቂት ግለሰቦች፣ ጥቂት የመንግስት ካድሬዎች ራሳቸው ጀምረውት ራሳቸው የሚጨርሱት ‹‹ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ›› አይነት የህጻን ጨዋታ ነበር::
ሰሚ በሌላቸው በሚያልጎመጉሙ በታፈኑ ድምጾች በርካታ ዓመታትን በዚህ ሁኔታ አሳልፈናል:: ምርጫ አስተሳሰብ ነው…አስተሳሰብ ስላችሁ የወረደ አስተሳሰብ ማለቴ አይደለም:: ከምንም በላይ የሰላ..አስተሳሰብ ማለቴ ነው::
ህዝብ ያልመረጠው፣ በህዝብ ይሁንታን ያላገኘ ፓርቲና መንግስት ሀገር ቢመራ ትርፉ ኪሳራ ነው የሚሆነው:: ነገም ዛሬም ሁሌም ህዝብን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ያስፈልገናል:: ህዝብ ምን እንደሚፈልግ ያወቀ ፓርቲ ሁሌም አሸናፊ ነው ::
ቅሉ ግን አንዳችንም ህዝብ ምን እንደሚፈልግ አለማወቃችን ነው:: እንዳውም እላለሁ አብዛኞቻችን ከህዝብ በተቃራኒ የቆምን ነን:: ለየትኛውም ህዝብ ፓርቲው ምን ይዞ መጥቷል የሚለው ቀዳሚ ጥያቄው ነው:: የዘንድሮው ምርጫ ለብዙዎቻችን የተስፋ ጮራን የፈነጠቀ ነው…ዜጎች ከመምረጣቸው በፊት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በሀሳብ የበላይነት ማመን መቻል አለባቸው:: በሀሳብ የበላይነት የማያምን ዜጋ ምርጫን እንደ ነውጥ እንጂ እንደ ለውጥ አያየውም:: በመሰረቱ ምርጫ የለውጥ ጅማሬ ነው::
ዜጎች ፍትህ የሚያገኙበት፣ ከጭቆና የሚወጡበት፣ የተሻለ ነገን የሚያዩበት አዲስ ምዕራፍ ነው:: ምርጫ በብዙ አስተሳሰቦች መሀል የሚያልፍ በስተመጨረሻም በአንድ ሀሳብ የበላይነት የሚጠናቀቅ የህዝቦች የውሳኔ ፍጻሜ ነው:: የተለያዩ ሀሳቦች፣ የተለያዩ አመለካከቶች የሚንሸራሸሩበት የህዝቦች የዳኝነት ውጤት ነው:: በዚህም ሀገራችን ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ልታካሂድ ሽር ጉድ ላይ ናት::
እንደነገርኳችሁ ምርጫ በአንድ ሀገር ላይ የራሱ የሆነ ትልቅ ሚና አለው:: ለሀገርም ሆነ ለማህበረሰብ የሚጠቅም ምርጫ በሀሳብ ብልጫ የበላይነት ያገኘ እንጂ በማጨበርበር የሆነ አይደለም:: በየትም ቦታ ላይ ህዝብ ታላቅ ሚና አለው:: ለምንም ነገር የህዝብ ድምጽ መሰማት አለበት:: ህዝብ ይሁንታ ያልሰጠው መንግስትና ስርዓት ወደ ስልጣን ቢመጣ እንኳን ጨቋኝና አምባገነን ከመሆን ውጪ ጥቅም የለውም::
ያለፉት አምስት የኢትዮጵያ ምጫዎች ግለሰብን እንጂ ህዝብን መሰረት ያደረጉ አልነበሩም:: በምንም ነገር ላይ ህዝብ መቅደም አለበት:: የአንድ ፓርቲ ምርጥነት የሚለካው በአስተሳሰቡ ውስጥ ህዝብ ሲኖር ነው:: ህዝብ የሌለበት ሀሳብና ራዕይ ፍጻሜው መሸነፍ ነው:: ከእንግዲህ ባለው ዘመናችን እና ከእንግዲህ በምትፈጠረው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ እንዲቀድም ያስፈልጋል:: ህዝብ የሌለበት ሀሳብ የመከነ ነው::
ምርጫ የሚደረገው እኮ ህዝብ ለማስተዳደር ነው:: የምረጡኝ ቅስቀሳ የምናደርገው እኮ ህዝብ በሀሳባችን አምኖ እንዲመርጠን ነው:: የወጣንው እኮ ከህዝብ አብራክ ነው..ህዝብን ረስተን የምንፈጥረው ተአምር የለም:: መጀመሪያ ሁላችንም ወደ ህዝብ መመለስ አለብን ብዬ አስባለሁ:: መጀመሪያ የምንመራውን ህዝብ ማወቅ አለብን::
ያለፉት ምርጫዎች የብዙሃን ድምጽ የማይሰማባቸው ህዝብ አልባ ነበሩ:: ለዛም እኮ ነው የአንድ ፓርቲ የበላይነት የገነነው:: ለዛም እኮ ነው ተአማኚነት የጎደለው ምርጫ ሲካሄድ የቆየው::
ምርጫ ህዝብን ከማወቅና ከመረዳት የሚጀምር ነው:: በሀሳብ ብልጫ የተቃኘ ተአማኝነት ያለው ምርጫ እንዲኖር ህዝብን ያከበረ ሀሳብ ያስፈልጋል ባይ ነኝ:: መነሻችን ህዝብ እንደሆነ ሁሉ መድረሻችንም ህዝብ ነው::
ከህዝብ አብራክ በቅለን ህዝብ የምንዋሽበት ምንም ምክንያት አይታየኝም:: ያለፉት ምርጫዎች ብዙ ነገር ያስተማሩን ሆነው ያለፉ ናቸው:: በዚህም መጪው ስድስተኛ ምርጫ ብዙዎቻችን እንደምንናፍቀው በሀሳብ የበላይነት ተጀምሮ እንደሚጠናቀቅ እናምናለን:: ወደፊት ለምትፈጠረው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ድንቅ ሀሳብ ነው የሚያስፈልጋት:: እስካሁን ድረስ በከሰሩ ሀሳቦች ከስረን ኖረናል::
ከእንግዲህ ግን ለሀገርም ለህዝብም በሚጠቅሙ ትውልድ አሻጋሪ ሀሳቦች መመራት አለብን:: የዘንድሮው ምርጫ ብዙ መልካም ነገሮችን ያሳየናል ብዬ አምናለሁ:: ህዝብ የሚፈልገውን ፓርቲ በነጻነት የሚመርጥበት ከሁሉ የተሻለ መልካም እድል ይዞ መጥቷል ብዬ አምናለሁ:: ህዝብን ያገናዘበ፣ ህዝብን መሰረት ያደረገ የፓርቲ ስብስብ የታየበት ስለመሆኑም እምነት አለኝ:: እንዳለፉት ምርጫዎች በውሸትና በማጭበርበር ሳይሆን በሀሳብ ልዕልና የሚመራ ሆኖ መጠናቀቅም ይኖርበታል::
ትላንት አልፏል:: ዛሬ አዲስ ቀን ነው:: በዚህ አዲስ ቀን ላይ አዲስ አስተሳሰብን እንሻለን:: ከዘመኑ ጋር የዘመነ፣ ለትውልዱ የሚመጥን አሻጋሪ ሀሳብ ያስፈልገናል:: ቀደም ሲል እንዳልኳችሁ መነሻችንም መድረሻችንም ሀገርና ህዝብ መሆን አለበት:: የአሁኑ ምርጫ ከግለሰባዊነት ወጥተው ለሀገርና ህዝብ የሚሆን የነጠረ ሀሳብ ላላቸው ፓርቲዎች የተሻለ እድል አለው ብዬ አምናለሁ:: በሀሳብ ላይ የበረቱ፣ መቼም የትም ህዝብን መሰረት ያደረጉ እነርሱ ለሁላችን ያስፈልጋሉ:: እንዳለፈው ጊዜ በውሸትና በማጭበርበር የሚሆን ነገር የለም::
ስልጣን የህዝብ ነው:: ዜጎች በዚህ እድል ተጠቅመው የነገ መሪያቸውን መምረጥ ይኖርባቸዋል:: ሁላችንም የምንፈልገውን ለመምረጥ ይሄን መልካም አጋጣሚ መጠቀም አለብን:: ለምንፈልጋት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ድምጻችን ዋጋ አለው:: እንዳውም ስህተት የምንሰራው በዚህ ምርጫ ላይ መሳተፍ ካልቻልን ነው እላለሁ::
ኢትዮጵያ..ኢትዮጵያ ለምንል ሀገር ወዳዶች ሁሉ ይህ ጊዜ ከሁሉ የተሻለ ምቹ ጊዜ ነውና ድምጻችሁን ለምትፈልጉት ፓርቲ በመስጠት ሀገር ወዳድነታችሁን ማሳየት አለባችሁ እላለሁ:: እድላችሁን ተጠቅማችሁ ካልመረጣችሁ ነገ ላይ ሌሎች በመረጡት ፓርቲ እየተገዛችሁ እንደሆነ አስቡት:: እድላችሁን ተጠቅማችሁ ዛሬ ካልመረጣችሁ ነገ በሌሎች አስተሳሰብ ስር እንደሆናችሁ እንዳትረሱት:: ይህ እንዳይሆን እድላችሁን ተጠቀሙ::
የእያንዳንዳችን ድምጽ ዋጋ አለው:: እንዳለፈው ጊዜ ምርጫ በጥቂቶች ድምጽ የብዙሃኑ እጣ ፈንታ የሚወሰንበት እንዳይሆን ሁላችሁም አሻራችሁን አሳርፉ:: ከምንም በላይ የህዝብ የበላይነት የገነነበት ምርጫ ያስፈልገናል:: የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በፈለግናት ልክ እንድትፈጠር ከህዝብ ለህዝብ የሆነ ፓርቲ ያስፈልገናል::
ለዚህም የእያንዳንዳችን ድምጽ ወሳኝነት አለው:: ነገ ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያለው ምርጫ ነው:: በዚህ ምቹ ጊዜ ላይ በንቃት መሳተፍ ያልቻለ ሀገሬን እወዳለሁ ቢል ውሸት ነው የሚሆነው:: ሀገር መውደድ እኮ በሀገር ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ነው:: ከፊታችን ያለው ምርጫ ደግሞ ሀገራችንን ለመውደዳችን አንዱ ማሳያ ነው::
ከድሮነት መውጣት አለብን ዘመኑ የሚመጥነውን ሀሳብ ለህዝባችን ማድረግ አለብን:: ከዚህ በፊት እንደነበሩት ምርጫዎች ህዝብ የሚወናበድበት ስርዓት አይኖርም:: ብዙ አይኖች እውነትን ማየት ናፍቀዋል:: ብዙ ጆሮዎች እስከ ዛሬ ሰምተው የማያውቁትን እውነት መስማት ሽተዋል:: ብዙ ልቦች..ብዙ ነፍሶች በኢትዮጵያ ታሪክ በሀሳብ የበላይነት የሚመራን ምርጫ ናፍቀው እየጠበቁ ነው::
እርግጠኛ ነኝ እኔም እናንተም ናፍቀናል:: እኔና እናንተ ብቻ አይደለንም በቀጣዩ ምርጫ መልካም ነገር ለማየትም ሆነ ለመስማት ያሰፈሰፉ ብዙ ናቸው:: ይሄ ሁሉ የሚሆነው ግን እያንዳንዳችን የመምረጥ መብታችንን ተጠቅመን መምረጥ ስንችልና ጥፋት ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ራሳችንን ስናቅብ ነው:: ምርጫን በተመለከተ ብዙ ሀላፊነትን ለመንግስት ሰጥተን ተመልካች የሆንን ብዙዎች ነን:: ምርጫ የሀገር ጉዳይ እስከሆነ ድረስ የእያንዳንዳችን ንቁ ተሳትፎ ወሳኝነት አለው::
ካለው ኢፍትሀዊነት አንጻር በኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ተስፋ ቆርጠን የነበርን ብዙዎች ነን፤ በዛው ልክ በአዲስ ተስፋ በአዲስ አስተሳሰብ ቀጣዩ ምርጫ የኢትዮጵያ የአዲስነት ምዕራፍ የሚጀምርበት እንደሆነ በማመንም ነገን የምንጠብቅ ሞልተናል:: የሆነው ሆኖ ግን ከትላንት የተሻለ ምርጫ እንጠብቃለን::
ህዝብ የሚደመጥበት፣ ሀገር የቀደመችበት፤ ብሄርተኝነትና ተረኝነት የማይሰሙበት፣ እኔነትና መሰል ነቀርሳዎቻችን የሻሩበት አዲስ ቀን እንናፍቃለን:: በሀሳብ የበላይነት የምትመራ፣ በአንድነትና በእኩልነት የምትደነቅ ቀዳማይት በኩር ሀገር ህልማችን ናት:: ለጋራ ጥቅም የተባበሩ ክንዶች የበረቱባት፣ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት የተመቸች ልዕለ ሀያል ኢትዮጵያን እንሻለን::
ይህ እንዲሆን መንግስት ብቻ ሳይሆን እኛም እናስፈልጋለን:: ይህ እንዲሆን ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዳችን ግድ ይለናል:: የእስካሁኗ ኢትዮጵያ በጥቂት ሀገር ወዳድ ዜጎች የቆመች ናት:: ብዙዎቻችን በምን ያገባኛል ህመሟን ሳንታመም፣ ስቃይዋን ሳንሰቃይ ኖረናል:: ከእንግዲህ ለምትፈጠረው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ግን ሁላችንም እናስፈልጋለን:: በጥቂቶች የምትፈጠር ሀገር የለችም:: በጥቂቶች የምትለማ ሀገር የለችም::
በጥቂቶች የሚበለጽግ ህዝብ የለም:: ለምንም ነገር የሁላችንም ድምጽ ያስፈልጋል:: ህልማችን በብዙ ነገሯ የምትደነቅ ሀገርን መፍጠር ከሆነ መጀመሪያ ሁላችንም ሀገራችንን በተመለከተ አንድ አይነት ህልም ማለም ይኖርብናል::
በጎ የሆነ አንድ አይነት ሀሳብ ማሰብ ግድ ይለናል:: አንዱ እየጠላ አንዱ እየወደደ፣ አንዱ እየገነባ ሌላው እያፈረሰ የምትፈጠር ምርጥ ሀገር የለችም:: ምርጥ ሀገር ለመፍጠር ከሁሉ በፊት እኛ ምርጥ እንሁን::
ምርጥ ትውልድ ለመፍጠር ከሁሉ አስቀድመን እኛ በሀሳብ የበላይነት የምናምን እንሁን:: ከሁሉ ትልቁን ፍቅርን እንወቅ:: በጋለ የሀገር ፍቅር ስሜት ከፊታችን ባለው ወሳኝ ምርጫ ላይ እንሳተፍ:: መንግስት ምርጫው ተአማኝነት ያለው እንዲሆን እየሰራ ነው፤ እኛም የምንፈልገውን በመምረጥ ሀላፊነታችንን እንወጣ:: አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በምናደርገው ሂደት የሁላችንም አስተዋጽኦ ወሳኝነት አለው::
በአባቶቻችን ስርዓት ወደፊት እንሂድ.. አዲሷ ኢትዮጵያ ከፊት ነው ያለችው:: ህልማችን ውብ ሀገር ከሆነ፣ ህልማችን ስልጡን ህዝብ ከሆነ እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን እንወጣ:: በፍቅር በአንድነት የምንመኛትን ኢትዮጵያ በተባበረ ክንድ እንስራት እያልኩ ላብቃ:: ቸር ሰንብቱ::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013