ጌትነት ተስፋማርያም
የኮሮና በሽታ ወደኢትዮጵያ ከገባ ዓመት ከአንድ ወር አስቆጥሯል። ጊዜውን ጠብቆ በወርሃ መጋቢት ዳግም ያገረሸው የበሽታው ስርጭት በየቀኑ የብዙሃኑን ህይወት ወደመቅጠፍ ተሸጋግሯል። በዚህ አሳሳቢ የጤና ወቅት ደግሞ እያንዳንዱ ግለሰብ እራሱንና አገሩን ከአደጋ ለመከላከል ጥንቃቄ የተሞላበት የህይወት ዘይቤን መከተል እንዳለበት በርካታ የጤና ባለሙያዎችም በየቀኑ እየመከሩ ይገኛል።
እኛም የበሽታው ስርጭት እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን የኮቪድ መከላከያ መመሪያ አተገባበር በተመለከተ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለበሽታው ያለውን መዘናጋት እና መፍትሄዎችን፤ እንዲሁም የክትባቱ ስርጭት እና ፍትሃዊነትን በተመለከተ በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ምላሽ አስተባባሪ ከሆኑት ዶክተር ሚዛን ኪሮስ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ የኮቪድ ጥንቃቄ መመሪያ ፕሮቶኮልን ከመተግበር አኳያ ክፍተት እንዳለ ይታያል፤ መመሪያው በአግባቡ እንዲተገበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ምን መሰራት አለበት?
ዶክተር ሚዛን፦ የኮቪድ ምላሽ በመስጠት ረገድ ከአመት በፊት የተለያዩ ተቋማትን ባሳተፈ መልኩ ሰፊ ስራ ተከናውኗል። በዚህም ምክንያት ሊደርስ ይችላል ተብሎ የተሰጋውን ጉዳት በብዙ መንገድ መቀነስ ተችሏል። ከጊዜ ወደጊዜ ግን የኮቪድ ምላሽ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ላይ ቸልተኝነት ተስተውሏል።
ባለፉት ስድስት ወራት በማህበረሰብ ደረጃ፣ በተቋም ደረጃ እና በግለሰብ ደረጃም ጭምር የታየው ቸልተኝነት እና በሽታውን አሳንሶ የማየት ችግር ነበር። ይህን ቸልተኝነት ተከትሎ ደግሞ የበሽታው ስርጭት አሁን እንደምናየው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል። አዲስ አበባ ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም የሌሎች መከላከያ ግብአቶች አጠቃቀም መልካም የነበረና ለሌችም ተሞክሮ የሚሰጥ ቢሆንም በኋላ ላይ መዘናጋቱ ስርጭቱን አጉልቶታል።
የበሽታው ስርጭት በሀገር ደረጃ አሳሳቢ በመሆኑ ቀድሞ የነበረውን የጥንቃቄ እርምጃ ከፍ ማድረግ ተገቢ ነው። ጤና ሚኒስቴርም በየወቅቱ ከበሽታው ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለህዝብም ሆነ ለሚመለከታቸው አካላት እያሳወቀ ይገኛል። ኮቪድ ሀገራዊ ስጋት መሆኑን መረዳት እና ከሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮች ጋር አጣምሮ የመከላከል ስራውን ማከናወኑ አስፈላጊ ነው። ለዚህም የሚመለከታቸውን አመራሮች ስለበሽታው የተለየ ትኩረት እንዲሰጡ ስንጠይቅ ቆይተናል።
የኮቪድ መመሪያ 30 የተሰኘ መስከረም ላይ ወጥቶ ነበር። በመሪያው መሰረት ክልከላዎቹን ብንፈጽም ወረርሽኙን በከፍተኛ ሁኔታ መከላከል እንደምንችልና ሀገራዊ ስጋቱንም መቀነስ እንችላለን የሚል እምነት ስላለ መመሪያው ድጋሚ ወደስራ እንዲገባ ተደርጓል። መመሪያውን መሰረት በማድረግ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ከፖሊስ፣ ጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች ተቋማትን በማካተት የተለያዩ ግብረ ሃይሎች ተቋቁመው ስራዎች እየተከናኑ ይገኛል።
ከመጋቢት መጨረሻዎቹ ቀናት ጀምሮ ህዝብ ስለበሽታው የሚያደርገውን መከላከል እና ጥንቃቄ እንዲያጠናክር የማስተዋወቅ እና የማስገንዘብ ስራ ተከናውኗል። አብዛኛው ሰው አዲስ መመሪያ የወጣ ነው የመሰለው። ስለዚህ የመመሪያው ግንዛቤ ላይ ክፍተት እንዳለ ስለተረዳን መመሪያውን ህዝብ እና ተቋማት በአግባቡ እንዲረዱት የማድረጉ ስራ በስፋት ተከናውኗል።
በዚያው ልክ ደግሞ የህግ ማስከበር ስራው መጠናከር አለበት በሚል በተለይ አዲስ አበባ ላይ ቁጥጥር እና ቅጣት የመጣል ስራ ተጀምሯል። ሆቴሎች፣ ህብረሰተቡ ፣ ተቋማት እና የስብሰባ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ጭምር ለኮቪድ ምላሽ ተገቢውን ጥንቃቄ ወደ ማድረግ ተሸጋግረዋል። ይህም የመረጃ ልውውጡ በአግባቡ መከናወኑን ያሳያል። ስለዚህ እንደሀገር አሳሳቢ የሆነውን በሽታ ለመከላከል ህብረተሰቡ የኮቪድ መመሪያዎችን በይበልጥ እያከበረ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴው ላይ እንዲሳተፍ ጥረት ማድረግ እና መቆጣጠር ያስፈልጋል።
ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችም በመመሪያው አተገባበር እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ላይ ያሳዩት በጎ ተግባር ለውጤታማነቱ አስፈላጊ ነውና ይበልጥ ህብረተሰቡ እነዲጠነቀቅ የሚረዱ የመከላከል እርምጃዎችን ማሳየት ይኖርባቸዋል። ይሁንና በእያንዳንዱ ቦታ እና ግለሰብ ደረጃ ጠባቂ አቁሞ ክትትል ማድረግ አይቻልም። ዋነኛው ስራ ህዝብ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ በማድረግ ለእራሱ ጤና ሃላፊነቱን እንዲወስድ ማድረግ ያስፈልጋል። ነዋሪዎችም አስፈላጊውን የመከላከያ ግብአቶች በመጠቀም እና እርቀታቸውን በመጠበቅ የበሽታውን ስርጭት መቀነስ መቻል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፦ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም የጥንቃቄ ግብአቶች ከመጠቀም አንጻር የታየው መዘናጋት ምን ድረስ እንደሆነ በመረጃ አስደግፋችሁ ያጠናችሁት መረጃ ምን ውጤት ያሳያል?
ዶክተር ሚዛን፦ የመከላከያ ግብአቶች አጠቃቀም ላይ መዘናጋቱ እንዳለ ነው። ለአብነት አዲስ አበባ ላይ ቀደም ብሎ የነበረው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀም ከ79 እስከ 81 በመቶ ነው። ይሄ ቁጥር ካደጉ ሀገራት ጥንቃቄ እርምጃ ጋር ሊወዳደር የሚችል በጎ ውጤት ነበር።
ከዚህ አንጻር ጠንካራ እርምጃ ይወስዳሉ ተብለው ከሚጠቀሱ እና ከኮቪድ በፊትም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የማድረግ ባህል ያላቸው የኤዥያ ሀገራት በተለይ ቻይና እና ጎረቤት ሀገራቶቿ ላይ የኮቪድ ጥንቃቄን በተመለከተ በመንገድ እና ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ከ90 እስከ 95 በመቶ ህዝባቸው የአፍና አፍንጫ መከላከያ ያደርጋሉ።
ነገር ግን ከሌሎች ያደጉ ሀገራት ላይ ካለው የጥንቃቄ እርምጃ አኳያ የአዲስ አበባው የተሻለ የሚባል ነበር። ትልቅ ስራ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም ባለፈው ግማሽ አመት የታየው መቀዛቀዝ ግን ጥንቃቄውን አውርዶታል። የአሁኑ የኮቪድ ንቅናቄ እስኪጀመር በአዲስ አበባ የነበረው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀም ከ49 እስከ 54 በመቶ ወርዶ ይዋዥቅ ነበር።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ልምዱ ቀንሶ ባለበት ወቅት ደግሞ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል። የሁለቱ መስተጋብር ማለትም የጥንቃቄው ማነስ እና የመስተጋብሮች ማደግ የኮቪድ በሽታ ዳግም አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል። አሁን ላይ ሰዎች ህዝብ የተሰበሰበበት ለቅሶ መሄዳቸውን ቀጥለዋል፤ ሰርግ እና የተለያዩ ድግሶች ላይ በርካታ ህዝብ ይገኛል።
ስብሰባዎች በየቦታው መደረጋቸው እና መጠጥ ቤቶች በሰዎች መሞላታቸው ሳያንስ ይባስ ብሎ ሰዎቹ ማስክ ያላደረጉ መሆኑ በሽታውን አስፋፍቶታል። የኮቪድ መከላከያ መመሪያ ፕሮቶኮልን ድጋሚ ወደስራ ለማስገባት የተጀመረውን ንቅናቄ ተከትሎ በሽታውን በመከላከል ረገድ በጎ ለውጦች አሉ። መሻሻሎቹን ግን ያሳዩትን ውጤት የምንለካው በየሳምንቱ በሚቀርቡ ጥናቶች ነው።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር 15 ዋና ዋና ከተሞችን መርጠን የአካላዊ ንጽህና እና አካላዊ ርቀትን እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀምን በተመለከተ መረጃ እየሰበሰብን ይገኛል። ይህን መረጃ እያየን ምን ያክል የኮቪድ መከላከል የጥንቃቄ እርምጃ እየተተገበረ ነው የሚለውን በቁጥር አስደግፈን መናገር እንችላለን። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ኮቪድ በመገናኛ ብዙሃን ረገድ ያገኘው ትኩረት የበሽታውን አሳሳቢነት ባገናዘበ መልኩ ከፍ ብሏል።
ህብረሰተቡም እኛ ላወጣነው ግን ተገዥ እስከሆንን ድረስ ተቀብሎ ለመተግበር ችግር እንደሌለበት ታይቷል። በሌላ በኩል ከሁለት ሺህ እስከ አስር ሺህ ሰዎች ሊገኙባቸው የነበሩ እና በስታዲየም ደረጃ ከ20ሺህ ሰው በላይ ሊታደምባቸው የነበሩ ትላልቅ ስብሰባዎች እንዲሰረዙ ተደርጓል።
እንዲሻሻሉ ተደርገው በአነስተኛ መጠን የተካሄዱ ስብሰባዎችም አሉ። ሆቴሎችም ፍቃድ ካልተገኘ ስብሰባዎችን አናስተናግድም ወደማለት መምጣታቸው በሽታውን ከመከላከል አኳያ እንደ ትልቅ ለውጥ ተደርጎው ይወሰዳሉ። እኛም ሆነ የእኛ ባለሙያዎች መሬት ወርደው በሚያደርጉት ቅኝት ግን አንጻራዊ ለውጦች እየታዩ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በገበያ ቦታ፣ ትራንስፖርትና የሃይማኖት ቀብር ማስፈጸሚያ ቦታዎች ላይ የኮቪድ ጥንቃቄ በመቀነሱ የኮቪድ መመሪያ ሲተገበር አይስተዋልምና ምን አይነት ልዩ ስራ ያስፈልጋል።
ዶክተር ሚዛን፦ በትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ ከተፈቀደው ልክ በላይ ይጭናሉ፤ ማስክ ያላደረጉ ሰዎችም ይሳፈራሉ። በገበያ ቦታዎች፣ በየምግብ ቤቱ እና መዝናኛ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ይሰበሰባል አሁንም።
አሁንም መፍትሄው ግን አንድና አንድ መጠንቀቅ ነው። በዘላቂነት በሽታውን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ የችግሩን መጠን ልክ እንዲረዳው ማድረግ ነው። የተግባቦት ዘዴዎቻችንን በመቀያየር ህብረተሰቡ ስለጥንቃቄው ያለውን ትኩረት ከፍ እንዲያደርገ ማድረግ ይገባል።
አንድ አካል ጤና ሚኒስቴር ብቻ መረጃ የሚያስተላልፍ ከሆነ፤ አንድ አይነት መረጃ ይሆንና ህብረተሰቡ ይሰለቻል፤ መረጃውንም መስማት ሊያቆም ይችላል። ስለዚህ በበሽታው ምክንያት ጉዳቱ የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፤ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች፤ ችግሩን በደንብ የተረዱ ባለሙያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ተከታይ ያላቸው ሰዎች የኮቪድን መረጃ ለህብረተሰቡ በማዳረስ ረገድ በንቃት ሊሳተፉ ይገባል። ህብረተሰቡም አይ እውነትም ይህ ነገር ያሰጋኛል ብሎ በዘላቂነት እንዲጠነቀቅ የተለያዩ የተግባቦት አማራጮችን በተለያዩ አካላት ማስተላለፍ ያስፈልጋል።
ስለኮቪድ የሚመጥን ፍርሃት ማለትም ያላነሰም ያልበዛም ልከኛ ፍርሃት በመፍጠር ህብረተሰቡ በገበያ ቦታ፤ በትራንስፖርት አገልግሎትም ሆነ ሌሎች ክንውኖች ላይ አካላዊ እርቀቱን እንዲጠብቅና መከላከያ ግብአቶችን እንዲጠቀም ማድረግ ይቻላል። ለዚህም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው በእጅጉ መጠናከር ያለበት ነው።
ህብረተሰቡም የአፍና የአፍንጫ መከላከያ ማድረጉ እና ርቀቱን መጠበቁ ለህይወቱ አዲስ የኑሮ ዘይቤ እንደሆነ አድርጎ ማየት ያለበት መሰረታዊ ጉዳይ እስኪሆን ተግባቦት እና ግንዛቤ የማሳደግ ስራው መቀጠል አለበት። ይሁንና የግንዛቤ ስራውን ከህግ ማስከበር ስራው ጋር ማስተሳሰር ደግሞ የግድ ይላል።
ከኮቪድ ጋር ተያይዞ እንደሀገር መደረግ የሚችለው እና የማይቻለው ነገር በግልጽ ከተቀመጠ መፈጸም ግዴታ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ህግ ተግባራዊ ሲደረግ ደግሞ እያንዳንዱ ቦታ ላይ የጸጥታ አካል ማቆም ባይቻልም ተቆጣጣሪ ተቋማት የእራሳቸውን ድርሻ ወስደው እንዲሰሩ ማድረግ ግን ያስፈልጋል።
ተቋማት ለቁጥጥር የዘረጉትን ሥርዓት ለኮቪድ መከላካልም መተግበር አለባቸው። ለአብነት የንግድ ተቋማትን የሚቆጣጠሩ አካላት የገበያ ቦታዎችን የኮቪድ ጥንቃቄ እርምጃ መከታተል ይችላሉ።
በተመሳሳይ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ አካላትም በታክሲ እና አውቶብሶች ላይ ያለውን ጉዳይ መመልከት ይችላሉ። ስለዚህ የተለያዩ ሴክተሮች በስራቸው ባሉ አገልግሎት መስጫዎች ላይ ከሚሰሩት ስራ ጎን በኮቪድ ላይ ምን እየተሰራ ነው የሚለውን መከታተል ይኖርባቸዋል። የትራንስፖርትን ጉዳይ የትራንስፖርት ባለስልጣን ፣ የንግዱን የንግድ ሚኒስቴር፣ በየሆቴሉ ያለውን ጉዳይ ደግሞ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በየፊናቸው ቁጥጥር የማድረግ እና እርምጃ የመውሰድ ስራቸውን በበላይነት መምራት አለባቸው።
የእምነት ተቋማትም በበኩላቸው በስራቸው ለሚከናወኑ ሁነቶች ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ ይኖርባቸዋል። ወጣቶችን በብዛት በበጎ ፈቃደኝነት በማሰማራት ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። አንድ ተቋም ብቻ በሚያከናውነው ተግባር ኮቪድን መከላካል ስልማይቻል የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል። ሁሉም ተቋማት የአሰራር ሥርዓታቸውን ከኮቪድ አንጻር መቃኘት አለባቸው። ቅንጅታዊ አሰራርን በሁሉም ተቆጣጣሪ አካላት በኩል ማከናወን ሲቻል በገበያ ቦታም ሆነ በትራንስፖርት አገልግሎት እና በቀብር እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ተገቢው የኮቪድ ጥንቃቄ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ ጥንቃቄው ላይ መዘናጋቱ እየከፋ ከሄደ እንደ ሃገር ሊደርስ የሚችልው ጉዳት እስከምን ድረስ ሊሆን እንደሚችል ተገማች ነው?
ዶክተር ሚዛን፦ የኮቪድን ጥንቃቄ በተገቢው መንገድ ካልተገበርን እንደ ሃገር አደጋውም ከፍ ይላል። ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኖ ከጨመረ ብዙዎች ወደ ህክምና ጣቢያ መሄድ ሳይችሉ ለከፋ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ፤ ብዙ የምንወዳቸውን ቤተሰቦቻችንን በሙት እናጣለን። መዘናጋቱ ካለ ኮቪድ መባባሱ ስለማይቀር የስስኳር፤ የልብ እና ሎች በሽታዎች ህክምና እና መሰረታዊ የህክምና ክትትሎች አገልግሎት በአግባቡ ላይሰጡ ይችላል።
ጥንቃቄው ከጎደለ እና ከአቅም በላይ ከተባባሰ በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎችም ጠንከር እያሉ እንደሚመጡ ማሰብ ይገባል። ለአብነት የተከፈቱ ንግድ ቦታዎችም ሆነ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ዳግም ለዚጉ ይችላሉ። ቀድሞ ወደነበርንበት እንቅስቃሴ ገደብ (ሎክ ዳውን) ልንሄድ እንችላለን። ይህ ደግሞ የእያንዳንዳችንን ህይወት ሊነካ የሚችል እና ከኢኮኖሚ አንጻርም አሉታዊ ተጽእኖ በግለሰብም ሆነ በሀገር ላይ የሚያደርስ ነው።
በሽታውን ለመከላከል የምናደርገው ጥንቃቄ ከተጓደለ እና ነገሩ ከአቅም በላይ ከሆነ ነገ ላይ እንደማህበረሰብ በፖለቲካም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚከተሉ እቀባዎች ህይወታችንን ይጎዱታል። ስለዚህ እንደማህበረሰብ እዛ ደረጃ ሳንደርስ በሽታውን ስለመግታት ማሰብ አለብን፤ ለመግታት ደግሞ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት። ውጥንቅጥ ውስጥ ሳንገባ በእጃችን ያለውን የኮቪድ ጥንቃቄ እድል ብንጠቀም ከጥፋት እንድናለን።
አዲስ ዘመን፦ የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ መሆን ኢትዮጵያ ካላት የጤና አገልግሎት አቅም በላይ ሆኗል የሚል ሃሳብ ይነሳል፤ ከዚህ አንጻር የታካሚዎች መርጃ መሳሪያዎች እጥረት ምን ደረጃ ላይ ነው?
ዶክተር ሚዛን፦ የበሽታው ስርጭት ሲጨምር የጤና ተቋማት ላይ የሚያደርሰው ጫና መጨመሩ አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በሽታው ሲስፋፋ ለታካሚዎች የሚሆን መርጃ መሳሪያ እጥረት ማጋጠሙ አይቀርም። ባለፈው ሳምንት እንኳን ለአብነት ማንሳት ቢቻል የጽኑ ህሙማን ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር 892 ነበር። ነገር ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ የጽኑ ህሙማንን ማስተናገድ የሚችለው የህክምና አቅም 652 አካባቢ ነው።
ከዚህ ልዩነት የምንረዳው 150 ሰዎች የጽኑ ህክምና እያስፈለጋቸው ህክምናውን አለማግኘታቸውን አሊያም አልጋ አለማግኘታቸውን ነው። አልጋ ቢያገኙ እንኳን ሌሎች የጽኑ ህሙማን እስካልወጡ ድረስ የሚያስፈልገውን የጽኑ ህክምና እርዳታ አያገኙም ማለት ነው። ይህም በየቀኑ ከዛሬ ነገ አልጋ ይለቀቃል ብለው የሚጠብቁ ጽኑ ህሙማን በየቤታቸው ወይም በጤና ተቋማት መኖራቸውን ያሳያል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ችግር በከተሞች ደረጃ ስናየው ደግሞ አንዳንዶቹ ቦታዎች ላይ የከፋ ይሆናል። አዲስ አበባ ላይ 450 በላይ የጽኑ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ባለፈው ሳምንት ላይ ነበሩ። በመዲናዋ ያለው የጽኑ ህክምና አቅም ግን 180 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ብቻ ነው። ፍላጎቱ ከአቅሙ በሶስት እጥፍ በልጧል።
በአዲስ አበባ ሲዳማ ክልል ፣ ሃረር ከተማ ላይ ያለው የጽኑ ህሙማን ቁጥር ካላቸው የህሙማን ማስተናገጃ አቅም በላይ አልፏል። ኦሮሚያን ጨምሮ ሌሎች ክልሎችም ወደዚያው አሳሳቢ ደረጃ እየተጠጉ ይገኛል።
እንደእኛ ውስን ሃብት ባለበት ሀገር ውስጥ ግን የቱንም ያክል ገንዘብ ኢንቨስት ይደረግ ቢባል በሽታው አሁን ካለበት ደረጃ በላይ የሚጨምር ከሆነ የጤና ተቋማት ላይ የሚደረግ የማስፋፊያ ስራ የህብረተሰቡን ፍላጎት ሊያሟላ አይችልም። የኮቪድ የጽኑ ህክምና ፍላጎት በጨመረ ቁጥር ደግሞ የሌሎች ጤና አገልግሎት ፍላጎት የሚውሉ መሳሪያዎችም እጥረት ያጋጥማል።
ለኮቪድ ታማሚዎች የኦክሲጅን እጥረት አጋጠመ ሲባል ለኮቪድ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ህመም ታካሚዎችም ጭምር ነው ችግሩ የሚፈጠረው። እጥረቱ ሲባባስ የቀዶ ጥገናዎች ሊሰረዙ ይችላሉና ችግሩ ተያያዥ ነው።
በአጠቃላይ የበሽታው ስርጭት እንደ ሃገር ካለው የህክምና አቅም ጋር ሲነጻጸር እየጨመረ ነው። ይህ ሲሆን የአልጋ ቁጥር፤ የኦክስጅን መተንፈሻ እና ሌሎች የህክምና ግብአቶችን ቁጥር ለመጨመር የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል።
ካለፈው ሶስት ሳምንት በፊት የኦክስጂን እጥረት አጋጥሞ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ በጊዜያዊነት ችግሩ ተቃሏል። ከውጭ የመጡ መሳሪያዎች ወደስራ እንዲገቡ በመደረጉ እና አነስተኛ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን በማሰራት አገልግሎቱ እንዲጨምር ተደርጓል። ኢትዮጵያው ውስጥ ያሉ ኦክስጅን አምራቾችም ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት የውጭ ምንዛሬ በማቅረብ እን ልዩ ድጋፍ በማድረግ ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል።
በሀገር ውስጥ ካሉት ኦክስጂን አምራቾን ውስጥ 93 በመቶው የግል ተቋማት ናቸው ፤ ተቋማቱ ለብረታ ብረት ፣ ለምግብ እና ለተለያየ አላማ የሚያመርቱ ቢሆኑም በተደረገ ድርድር አማካኝነት በምሽትና ሌሎች ሽፍቶች የህክምና ኦክስጂን እንዲያመርቱና ለጤና ተቋማት እንዲያቀርቡ ተደርጓል። በዚህ አጋጣሚ ህክምናውን የሚያግዙ ተቋማትን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ይህን በማድረጋችን ባለፉት ሶስት ሳምንታት የኦክስጅ ምርት ላይ ሁለት ሺህ ሲሊንደር ተጨማሪ አቅም መፍጠር ተችሏል።
የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ የሆነውን መካኒካል ቬንትሌተርን በተመለከተ ኮቪድ ከተከሰተ በኋላ 180 ተገዝቶ ወደጤና ተቋማት እነዲሰራጭ ተደርጓል። መሳሪያው እጅግ ውድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሀገር የመጨመር አቅሙ እምብዛም ነው። ይሁንና የተለያየ ሃብት በማሰባሰብ በርካታ የህክምና ግብአቶችን ለማሟላት የሚደረግ ጥረት አልተቋረጠም።
በመሰረቱ መካኒካል ቬንትሌተር ደረጃ የደረሰ የኮቪድ ታካሚ የመትረፍ እድሉ ከአምስት በመቶ በላይ አይደለም። 100 ሰዎች መካኒካል ቬንትሌተር እስኪገጠምላቸው የሚያደርስ ችግር ካጋጠማቸው የሚተርፉት ከአምስት አይበልጡም ማለት ነው።
የመሳሪያው እጥረት ከመኖሩ ባለፈ እዛ ደረጃ የሚደርሱ ሰዎችም ለሞት የሚጋለጡ በመሆናቸው ትልቁ ስራ መሆን ያለበት ዛሬም ነገም በሽታውን መከላከሉ ላይ ነው። የበሽታው ስርጭት አሁን ካለበት እየጨመረ ከሄደ የህክምና ጣቢያዎች አቅም የማይችለው ጫና ስልሚፈጠር ከወዲሁ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ የተሞላበት የህይወት ልምዱን ማጠናከር ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ ኮቪድ መስፋፋቱ በዚሁ ከቀጠለ ከትምህርት ጋር ተያይዞ በቀጣይ ሊያደርስ የሚችለው ተጽእኖ በማየት ታሳቢ የሚሆንን እርምጃ ይኖራል?
ዶክተር ሚዛን፦ ትምህርት ቤት ላይ የኮቪድ ጥንቃቄ እየተሰራ አይደለም የሚለውን አይተናል። ልጆች ተቃቅፈው አብረው የሚሄዱበት እና በወሬ ደረጃ የምንሰማው ጣፋጭ በረዶ እንኳን እየተቀባበሉ የሚመጡበት ሁኔታ እንዳለ ተረድተናል። በመጀመሪያ ትምህርት በቤት ከመዝጋት በፊት የኮቪድ መመሪያ በትምህርት ቤት መተግበር ላይ ነው የምናተኩረው።
በሌሎችም ዘርፎች በተመሳሳይ ነው። አንድ ተቋም መመሪያውን እንዲተገበር ሳያደርግ ሰራተኞቹ እና ደንበኞች ለኮቪድ ካጋለጠ በህግም ይጠየቃል። ለዚህም ሁሉም ሰራተኛውም አሰሪውም፤ ተማሪውም መምህራኑን ሃላፊነት እንዳለባቸው መገንዘብ ይገባል። መንግስትም የየዘርፉን ተቋማት ሳይዘጉ ችግሮቻቸውን ማስተካከል እንችላለን የሚል እምነት ነው ያለው።
ስለዚህ ትምህርት ቤቶች ላይ ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ የኮቪድ ስርጭትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባል። ትምህርት በኮቪድ ምክንያት ሳይቋረጥ ልጆች ዕውቀት የሚያገኙበትን መንገድ አጠናክሮ መሄድ ያስፈልጋል።
አንደኛው ጉዳይ ከሆነ የሚል (ሃይፖተቲካል) ነገር ነው የምናወራው፤ ነገሮች ከቀጠሉ በትምህርት ስርዓት ላይ ሊፈጠር የሚችልውን ነገር እናያለን። ከዚህ አንጻር በሌሎች ዓለም የተደረገ እና እኛም ሀገር ተግብረነው የምናውቀው እርምጃ አለ።
ነገሮች አሁን ባሉበት ከቀጠሉና በሽታው ስርጭቱ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ እንደመንግስት ህዝብን ለማዳን ማንኛውም እርምጃ ሊወሰድ ይችላል። ይህ ሲባል ግን በቀጣይ ትምህርት በሙሉ ይዘጋል ማለት አይደለም።
አሁን ያለን አካሄድና መመሪያ ትምህርት የመዝጋት አዝማሚያ የለውም። ከዚያ በፊት ልንከላከላቸው የምንችላቸው ችግሮችን ስለመቅረፍ ነው የምንሰራው። እኛ እያልን ያለነው ሰዎች አትገናኙ አትሰብሰቡ ሳይሆን ከተቻለ በቴክኖሎጂ እገዛ ይወያዩ በአካል ከተገናኙም ግን ርቀታቸውን ጠብቀው እና ማስክ አድርገው ይሁን ነው።
ከ50 በታች ይሁን ስብሰባዎች ሲባል የግድ ከሃምሳ በታች ይሁን ሳይሆን ከዛም በላይ ከሆነ ተገቢው ጥንቃቄ እርምጃ እንዳይለያቸው ትኩረት ማድረግ ይገባል እንላለን። ትምህርት ላይም ተገቢውን የንጽህና፣ የርቀት እና ማስክ አጠቃቀም እየተከተሉ እንዲቀጥል ነው።
አዲስ ዘመን፦ የኮቪድ በሽታ ክትባት ወደ ሃገር ውስጥ ከገባ በኋላ ስርጭቱ ደካማ መሆኑ ታይቷል፤ ለዚህ ምንድን ነው ችግሩ ቀጣይ መፍትሄውስ ምን መሆን አለበት
ዶክተር ሚዛን፦ ክትባቱ ከታሰበለት አንጻር የሄደበት ፍጥነት ስናየው በምንፈልገው መንገድ ሄዶልናል ብለን አናምንም። የክትባቱ ስርጭት ፍጥነት በተወሰነ ደረጃ ዘግይቷል የሚል እምነት በእኛም ዘንድ አለ። በመሰረታዊነት ማየት ያለብን ነገር ግን በዓለም ብዙ ድርድር ተደርጎ ከፍተኛ ባለስልጣናትም ተሳትፈውበት ቅድሚያ ካገኙ ሀገራት መካከል ሆነናል። ክትባቱ ግን አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ ትግበራ ለማዋል የሚከናወኑ ትላልቅ ስራዎች አሉ።
የጤና ባለሙያዎች ስለክትባቱ አሰጣጥ በቂ ግንዛቤ ማግኘት አለባቸው። ክትባቱን ስለሚወስደውን ሰው ምን አይነት መረጃ መያዝ እንዳለባቸው እና ምን አይነት ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው ማሳወቅ ይገባል። ለክትባቱ ተፈጻሚነት የሚያስፈልጉ ቅጻ ቅጾች በየተቋማቱ ማድረስ እና ክትባቱን እራሱ ወደተለያዩ ቦታዎች ማጓጓዝ የሚወስደው ሰፊ ጊዜ አለ።
እንደሀገር ዝግጁ አይደለንም ብለን ክትባቱ እንዳይመጣ ከማድረግ ይልቅ ክትባቱ እየገባ ጎን ለጎን ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። ሂደቶቹን ማየት ከተቻለ እውነት ለመናገር ስራዎች ስላልተሰሩ ሳይሆን ሁኔታው የሚያድስገድድ በመሆኑ ክትባቱ መዘግየቱን መረዳት ይቻላል። በቀሩት ቀናት ግን የመጣውን 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ክትባት ሙሉ በሙሉ ከትቦ ለመጨረስ እድቅ ተይዟል።
ይህን ስራ የሚያስተባብረው ሌላ ቡድን ቢሆንም እስከ ሚያዚያ አጋማሽ ክትባቱን ከትቦ ለመጨረስ ነው ዝግጅት ያደረገው። ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች ክትባቶችን ሰጥታ የምታውቅ ሀገር በመሆኗ ለዚህ ልምዱ አለን። ስለዚህ አሁን ላይ ክልሎች ላይም ስልጠናውን ስለጨረሱ እና ግብአቱም ስለደረሰላቸው እስከሚያዚያ አጋማሽ ድረስ በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ክትባት ይዳረሳል ተብሎ ይጠበቃል። ስለዚህ የስርጭቱ ጉዳይም በቅርቡ መፍትሄ ያገኛል።
አዲስ ዘመን፦ ከክትባቱ ፍትሃዊ ክፍፍል ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ይነሳሉ ለዚህ ምን ምላሽ አለዎት?
ዶክተር ሚዛን፦ የክትባቱ ዋና ዓላማ እንግዲህ የተከተቡ ሰዎች በሽታው ቢይዛቸው እንኳን በፀና ታመው ለሞት የመዳረግ እድላቸው ለመቀነስ ነው። ይህን ከማሳካት አንጻር በኢትዮጵያ የተወሰዱ መረጃዎች እነደሚያሳዩት በየትኛውም እድሜ ላይ ያሉ ሰዎች በበሽታው የሞቱ ቢሆንም በዋናነት ግን በሽታው ክንዱን ያበረታው እድሜያቸው የገፉ እና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ላይ መሆኑን ማወቅ ይገባል።
ስለዚህ ለክትባቱ እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ናቸው ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መደረጉ ምክንያታዊነት አለው። በሌላ በኩል ለበሽታው ተጋላጭነት ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው ክትባቱን ቅድሚያ የሚያገኙት። ከተጋላጭነት አንጻር ደግሞ ከሁሉም በላይ ቁጥር አንድ ተጋላጭ በየትኛውም ዓለም ቢሆን የጤና ባለሙያ ነው ፤ ከዚያ ቀጥሉ ትራንስፖርት ላይ አሊያም ጸጥታ ማስከበር ላይ የሚሰሩ፤ መምህራን እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው ተጋላጭ የሆኑት።
ከክትባቱ ፍትሃዊነት አንጻር እነማንን በመጀመሪያ መከተብ አለብን የሚለው ለማን መሰጠት አለበት የሚለው ግልጽ በሆነ መንገድ መስፈርት ተቀምጦለት እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንም መሰረት አድርጎ ነው የሚሰራበት።
ቅድሚያ ባለስልጣናት የተከተቡበት መንገድ እና የጤና ባለሙያዎች መጀመሪያ ክትባቱን የወሰዱበት መንገድ ህብረተሰቡ ስለክትባቱ ያለውን አመኔታ ለመጨመር ታስቦ የተደረገ ነው።
በቀጣይ በሚሊዮኖች ክትባቶቹ መስፈርቱን በተከተለ መንገድ ለህብረተሰቡ እንዲዳረስ ይደረጋል። ስለዚህ ፍትሃዊነቱን በተመለከተ ችግር ይኖራል ብሎ መስጋት አይገባም። በሌላ በኩልም እድሜው የገፋ እና የሚታወቅ የህክምና ችግር ያለበት ሰው ክትባቱን የማግኘት መብት አለው። ለኮቪድ ተጋላጭ ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ እድሜውም ከ55 ዓመት በላይ ከሆነ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይም ሆነ ሌሎች ተቋማት ላይ የሚሰራ መከተብ ይችላል።
በአንጻሩ ግን ትራንስፖርት ላይ የሚሰራ ወጣት ከሆነ ለኮቪድ ተጋላጭነት ቢኖረውም በበሽታው ተይዞ የመሞት እድሉ ዝቅተኛ ስለሚሆን ቅደሚያ እድሜያቸው ለገፉ እና ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው እንዲሰጥ መደረጉ ፍትሃዊነቱ ላይ ችግር እንደሌለው ያሳያል።
እንደ አጠቃላይ ካየነው ግን አቅማችን ስለማይፈቅድ ነው እንጂ ክትባቱ ለሁሉም ዜጋ መድረስ ያለበት ነው። በፈረንጆቹ እስከ 2021 ማለቂያ ድረስ 22 ሚሊዮን ሰዎች በኢትዮጵያ የኮቪድ ክትባትን ያገኛሉ የሚል እቅድ ተይዟል። ስለዚህ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ሁሉ እስከ 2014 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ከትቦ የመጨረስ ውጥን መኖሩን ህብረተሰቡ ቢገነዘብ መልካም ነው ለማለት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን መልካም ቆይታ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሚዛን፦ እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013