መልካምስራ አፈወርቅ
አንድ ቤት ሲገነባ ጥብቅ መሰረት እንደሚያሻው ሁሉ ታላቅ ጉዳይ ሲወጠንም አስቀድሞ ማሰብ የግድ ይላል:: አንዳንዴ ነገሮችን በቸልተኝነት እናልፋለን:: አንዳንዴ ደግሞ በ ‹‹ይደርሳል›› ልማድ ተዘናግተን ከእጃችን የገባውን መልካም ዕድል እንበትናለን ፤ እናኮላሻለን :: እንዲህ በሆነ ጊዜ ለእኛም ሆነ ለሀገር፣ ብሎም ለትውልዱ የሚያስከፍለን ዋጋ ቀላል የሚባል አይሆንም::
እነሆ! ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተቃርቧል:: በኢትዮጵያ ዕውን ከሆነው ታላቅ የፖለቲካ ለውጥ በኋላም ይህ ምርጫ የሚካሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው:: በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት መልከ ብዙ ምርጫዎች ተካሂደዋል:: በርካቶች እንደሚያምኑበት የአብዛኞቹ ሂደት የህዝብ ድምጽን ያላማከለ፣ የገዥውን ፓርቲ ፍላጎት የከወነና ኢ – ፍትሀዊ የሚባል ነበር::
በሀገራችን የምርጫ ታሪክ በርካቶች የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉበትን ምርጫ 1997ን ጨምሮ ትውልድና ታሪክ የማይዘነጋቸው ክፉ አጋጣሚዎች ታልፈዋል:: መብት ሲጣስ፣ ህዝብ ሲበደል፣ ነጻነት ሲገፈፍ ፣ያስተዋሉ የህዝብ ልጆች ባነሱት ጥያቄም ግፍና ስቃይ ተፈጽሞባቸዋል::
ወደቀደመው ነገሬ ልመለስ:: በቸልተኝነታችን ስለምንከፍለው ያልተገባ ዋጋ ጉዳይ:: ይህን አበይት ርዕሰ ያለምክንያት ላነሳ አልወደድኩም:: የጊዜንና የዋጋ መክፈልን እውነት ልነካካ የፈለግሁት በምክንያት ነው:: ምክንያቴ ደግሞ አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት አገራዊው ምርጫና የመራጮች ምዝገባ ካርድን ይመለከታል::
በየትኛውም አገር ቢሆን ምርጫን ለማካሄድ ሲታሰብ ህግና ደንቡ በሚፈቅደው አግባብ የቅድመ- ምርጫ መሰናዶዎች ይካሄዳሉ:: ከነዚህ ቅድመ ዝግጅቶች መካከልም የመራጮች ምዝገባን ማካሄድ፣ ድምጽ የሚወሰንበት ካርድን መስጠትና መቀበል ዋንኛው ይሆናል::
በሀገራችን እስከዛሬ በተካሄዱ የምርጫ ሂደቶችም እነዚህን መሰል ዝግጅቶች አስቀድመው ሲከወኑ ቆይተዋል:: ዛሬም ቢሆን የተለያዩ ማዕከላት በቂ የሰው ሃይል፣ ተመድቦላቸውና የጊዜ ገደብ ተበጅቶላቸው ካርድ የሚወስዱ መራጮችን እየተጠባበቁ ነው::
የምርጫ ካርድ የመውሰድ ሂደቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል:: ይሁን እንጂ በርካታው ድምጽ ሰጪ የታሰበውን ያህል ካርድ አለመውሰዱ ተረጋግጧል:: ብዘዎች ባለፉት የምርጫ ሂደቶች ካሳረፉባቸው ጥቁር አሻራዎች በመነሳት የራሳቸውን ግምት ያስቀምጣሉ:: በተለይም በምርጫ 97 በህዝቡ ላይ የሆነውን ክፉ አጋጣሚ በማስታወስ በመጪው ምርጫም ላይ የሚኖረውን አመኔታ አሳንሰው አኮስሰው ይስሉታል::
እውነት ነው! በዛን ዘመን ብዘዎች ለሀቅ ታግለዋል ፣ ስለእውነት በነበራቸው ተጋድሎም ታስረው ተገርፈዋል፣ ከሀገር ተሰደዋል:: ከዚህም አልፎ ክቡር ህይወታቸውን ተነጥቆ ፣ሙሉ አካላቸው ጎድሏል::
በምርጫ ካርዳቸው ድምጽ የሰጡ ብዙሃን ኮሮጆ ተገልብጦ፣ ቆጠራው ተዛብቶ የነበረው እንዳልነበር ቢሆን፣ በካርድ ያጡትን ድምጽ በአደባባይ አሰምተዋል:: ይህ መሆኑ ያስቆጣቸው የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናትም እነዚህን ዜጎች አንገላተው በማፈን ሀቁን ለመደበቅ አሲረዋል::
ይህን ያወቁ እንደ ‹አና ጎሜዝ›› የመሰሉ የውጭ አገራት ታዛቢዎች ስለምን ባሉ ብዙ ተብለዋል:: በአይናቸው ያዩትን ሀቅ መላው ዓለም አውቆ ፣ ሚዛናዊ ፍርዱን እንዳይሰጥም ስማቸው በአደባባይ ጎድፏል:: ማንነታቸውን ጥላሸት በመቀባት ትክክለኛው ገጽታ እንዳይገለጥና የህዝቡ ዕንባና ደም እንደይጠረግ ብዙ ተደርጓል፡፤
እነሆ! አሁን ያንን አስከፊ ዘመን ተሻግረናል:: የግፈኞች፣ ብረት ድልድይ ተሰብሮም ከሌላው መንገድ ላይ ቆመናል:: ህዝቡ የራሱን ወኪል በራሱ ድምጽ ይወስን ዘንድ ደግሞ የምርጫው ካርድ ተዘጋጅቶለታል::
ምርጫ የዘመናዊ ህዝብ መገለጫ ነው:: ሂደቱ ፍትሀዊና ሚዛናዊ ሲሆን ደግሞ መራጩ የእኔ ያለውን ተወካዩን እንዲለይና በሚሰጠው ትክክለኛ ድምጽ ውሳኔውን እንዲያሳልፍ ዕድል ይሰጣል:: ይህ ይሆን ዘንድም ወቅቱን የጠበቀ፣ ጊዜውን የዋጀ የምርጫ ካርድ በእጁ ይኖረው ዘንድ የግድ ይላል:: ዘንድሮ የሚካሄደውን ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ለተመዝጋቢው ከሌሎች ጊዜያት የበለጠ አማራጮች ተቀምጠዋል::
በነዋሪነት መታወቂያና መሰል ጉዳዮች ሳቢያ ክፍተት እንዳይፈጠር የሚያስችል አሰራር በመኖሩም ሁሉንም ዜጋ ተሳታፊ የሚያደርግ የምዝገባ ሂደት ተመቻችቷል :: የቀበሌ ፣መታወቂያ ያላቸውን ጨምሮ ብዙሃኑ በሚሳተፉበት የምዝገባ መስመር ሰበብ የሚፈጥር ፣ ምክንያት የሚያስነሳ ጉዳይ ሳይኖር ሁሉም ዜጋ መብቱን ተጠቅሞ ድምጹን የሚሰጥበት አግባብ ዕውን ሆኗል::
ተደጋግሞ እንደተገለጸው ግን በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ድምጽ ሰጪዎች የታሰበውን ቁጥር ያህል አልተመዘገቡም:: አልያም የተዘጋጁ ካርዶችን አልወሰዱም:: የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃም በመላው አገሪቱ የሚገኙና የጸጥታ ችግር የሌለባቸው ክልሎች ያሉ መራጮች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መሰረት የታሰበውን ያህል ካርዶችን አልወሰዱም::
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ ሶስት መቶ ሺህ የማይሞሉ ነዋሪዎች ብቻ ካርድ ሲወስዱ በሚሊዮን የሚገመተውና ድምጽ ይሰጣል ተብሎ የሚገመተው በርካታው ህዝብ ከምርጫ ጣቢያዎች ደጃፍ አልተገኘም::
በእርግጥ አብዛኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች በራሳቸው የህይወት መስመር ሲሮጡ የሚውሉ ባተሌዎች ናቸው:: ከዚሁ ጋር ተያይዞም ብዙሃኑ የምርጫ ካርድ ላለመውሰዳቸው የሚሰጡት ምክንያት ይህንኑ ሰበብ ያጣቀሰ ነው:: የጊዜ ማጣት፣ የቦታ አለመመቻቸትና መሰል ጉዳዮች ለምክንያቶቻቸው እንደ መነሻ ይሆናሉ::
አንዳንዶች ደግሞ ወቅታዊውን የኑሮ ውድነት ከምርጫው መከሰት ጋር አያይዘው ትኩረታቸውን አንድ አቅጣጫ ላይ ብቻ ያደርጋሉ :: ባይገባቸው እንጂ እንዲህ አይነቱን መሰል ችግር ‹‹እቀርፋለሁ›› ለሚል የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ መስጠት፣ መፍትሄ አመላካችና መላ ፈጣሪ ይሆን ነበር::
ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በሀገራችን እየሆነ ያለውን የጸጥታ መናጋት እያሰቡ በመጪው አገራዊ ምርጫ ተስፋ ሲቆርጡ ይታያሉ:: እነሱም ቢሆኑ የተወዳዳሪ ፓርቲዎችን የሰላምና ጸጥታ አጀንዳ በመቃኘት ለዚህ አሳሳቢ ችግር መፍትሄ የሚሆነውን ዕጩና ድርጅት ከወዲሁ ለማወቅ ይቻላቸዋል::
ብዙ ጊዜ በርካቶች የምርጫን ጉዳይ የአንድ ወገን እሳቤና የፖለቲካ አጀንዳ ሲደርጉት ይስተዋላል:: ስለምርጫ ጥቅምና ውጤት በአግባቡ ሳይረዱም በዚህ ሂደት ማለፉ ብቻ የማይፈልጉትን ፖለቲከኛ የመባል ስያሜ እንደሚያሰጣቸው ይገምታሉ:: ይህ የተሳሳተ ግምትም ጥቅማቸውን አሳልፎ በምርጫ ካርዳቸው ድምጽ እንዳይሰጡ ዕንቅፋት ሆኖ ይዘልቃል::
እያንዳንዱ ዜጋ ከራሱ እሳቤና ምናብ በመነሳት የሚያስቀምጠው ግምት ልክ አይደለም ማለት አይቻልም:: ማንም ቢሆን በግሉ አስተሳሰብ የመመራትና ሀሳቡን የማንሸራሸር ዴሞክራሲያዊ መብት ተሰጥቶታል:: ይሁን እንጂ በምርጫው ሂደት ከታሰበው ጥግ ለመድረስ አንዱና ብቸኛው አማራጭ የምርጫ ካርድን በወቅቱና በጊዜው ከእጅ ማስገባት ብቻ ይሆናል::
ይህን እውነት በዚህ ገጽ ላይ ሳሰፍር ለክፍተቱ መፈጠር ተጠያቂው መራጩ ዜጋ ብቻ ይሁን አልልም:: የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና የሚመለከታቸው አካላትም በቂ ግንዛቤና ዕወቀት በመፍጠር በኩል ለህብረተሰቡ የሚገባውን ሁሉ የማድረስ ሃላፊነትን በብቃት ተወጥተዋል የሚል ግምት የለኝም::
አሁንም ቢሆን በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ በቀሩት ጊዜያት ህብረተሰቡን ተደራሽ የሚያደርጉ አሰራሮች ሊተገበሩ ይገባል:: የካርድ መውሰጃ ቀኑን በማራዘምና ከቀድሞው በበለጠ ፣ ፈጣን እንቅስቃሴ በማድረግም ወደ መራጩ ህዝብ የሚያደርሱ አቋራጭ መንገዶች ሊተገበሩ ግድ ይላል:: ይህም ብቻ አይደለም:: ሰሞኑን በአንዳንድ ካርድ መስጫ ጣቢያዎች የምርጫ ካርዶች ጨርሰናል የሚሉ ምክንያቶችም መፍትሄ ሊበጅላቸው ያስፈልጋል::
እኔ ግን አሁንም ደግሜ ደጋግሜ እንዲህ እላለሁ:: ድምጽ ለመስጠትና ለመንፈግ ታላቁ የምርጫ መፍትሄ በእጆቻችን የምናስገባቸው ካርዶቻችን ወሳኝ ይሆናሉ :: ጊዜ ካለፈ በኋላ ‹‹ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ….›› ይሉት ተረት ተምሳሌት እንዳንሆን ወሳኞቹን የምርጫ ካርዶች በመያዝ ዕጩዎቻችን ከወዲሁ እናስብ የግል መልዕክቴ ነው:: እንዲህ መባሉንም አንርሳው::
ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሸቀዳድሞ
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ ::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013