ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ gechoseni@gmail.com
የንባብ ማዋዣ፤
ለሟቹ የዘመነ ደርግ “የነፍስ ምህረት ባንማጠንም” የታሪካች አንዱ ክፋይ ስለሆነ ደጋግመን ማስታወሳችን አይቀርም። በዚሁ ወለፌንድ የሶሻሊስት ብካይ ዓመታት ለሥርዓቱ ዘለዓለማዊነት “ይደልዎ!” (ይገባዋል እንደማለት ነው) እያሉ ይቀኙለት ከነበሩት “ፍቅረኛሞች” መካከል አንዱ አለቃ ዕንባቆም ቃለ ወልድ በቀዳሚነት ይታወሳሉ።
እኒህ ጎምቱ ካህን በወቅቱ በነበሩት ብዙኃን መገናኛዎች አማካይነት ለሥርዓቱ የአድናቆት “ቅኔ” በማዥጎድጎድ ያለመታከት አድናቆታቸውን ይገልጹ ነበር። የግል አመለካከታቸውንና እምነታቸውን በሚገባ ማክበሬ እንደተጠበቀ ሆኖ እርሳቸው “ቅኔያት” እያሉ ያነቧቸው ከነበሩት ግጥሞችና ከሌሎች ብዕረኞች ጋር ከታተሙላቸው ሥራዎቻቸው መካከል (ጽጌሬዳ ብዕር፤ 1977 ዓ.ም) በወቅቱ በዝነኛነታቸው ብዙ ከተባለላቸው መካከል ለንባብ ማዋዣነት እንዲረዳ ጥቂት ስንኞችን መዝዤ ላስታውስ።
እነግዛው ንዳው ጌቶች እንዳይሰሙ፣
የዛሬው ፋሲካ ወንድም በወንዱሙ።
በዘውድ አቆጣጠር የትላንቱ ዜሮ፣
ሠርቶ አደር ገበሬ ሚሊዮን ዘንድሮ።
ያምሳ ዘመን በላይ ተረት እንቆቅልሽ፣
ብዝበዛ ዘረፋ ዛሬ ምን አውቅልሽ።
በዚህ ዐምደኛ እምነት እነዚን መሰል አወዳሽም ይሁኑ ነቃፊ የብዕር ጭማቂ ውጤቶች በትናንትና ጀንበር ተለስነው የሚቀሩ ብቻ ሳይሆኑ ዘመን የመሸጋገር አቅማቸውም በእጅጉ የበረታ ነው። አነሳሴ የአለቃ ዕንባቆምን ግጥሞችን ይዘት እየነቀስኩ ለመኄስና ለመተንተን ሳይሆን “ቅኔያት” ብለው ከዘረዘሯቸው የላይኞቹ ስንኞች መካከል አንድ ሁለቱን ተውሼ ከዛሬው ዐውድ ጋር ሊያስተምሩም ሆነ ሊያስፈግጉ ይቻላሉ ብዬ በብእሬ እግረ መንገድ ጠቅሼ ለማለፍ ስለፈለግሁ ብቻ ነው። ዳሩ “ቅኔ” የሕዝብ ሀብት ነው ይባል የለ? ስለዚህም የተውሶ ስንኞቼ የጊዜያችንን ጠረን እንዲጋሩ በማሰብ እንዲህ በማለት አውገርግሬያቸዋለሁ።
“በኢህአዴግ ዘመን የትናንቱ ዜሮ፣
“መቶ ቤት” ደፈነ ምርጫችን ዘንድሮ።”
የቱ ምርጫ? ተብዬ ብጠየቅ “የትናንቱን” መቶ በመቶ ማለቴን ልብ ይሏል። የዛሬውስ? ከተባለ አጀማመሩን ለመቃኘት ካልሆነ በስተቀር መልሱን የምናገኘው ከወር በኋላ ይሆናል። መቼም ነገር ማዋዣያና የምግብ ማባያ አዋዜ የሚያገለግሉት የምግብ ፍላጎትን (አፒታይት) ለመቀስቀስ እንጂ እንዲያጠግቡ ታስቦ ስለማይሆን እኔም ለመንደርደሪያነት የመረጥኩትን የንባብ አፒታይት መቀስቀሻ እዚሁ ላይ ገትቼ ወደ ኮስታራው የዛሬው ምርጫ ነክ ቁዘማዬ አዘግማለሁ።
የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን የባዶነት መገለጫዎች፤
ለስድስተኛ ጊዜ ሊደረግ ሽር ጉድ የሚባልለት የዘመነ ብልፅግናው ብሔራዊ የፖለቲካ ምርጫ ጉዳይ ከአጀማመሩ ለብዙ ትዝብቶች እየተዳረገ እንደሆነ እያስተዋልን ነው። “ፖለቲካ ይሉት ጨዋታ በአፍንጫዬ ይውጣ!” እያሉ በአደባባይና በየሚዲያው እየወጡ ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ በርካታ ሰዎች ድንገት ገልበጥ ብለው “ማንም ሰው ከፖለቲካ ውጭ አይደለም።
ሊሆንም አይችልም” በሚል የማምለጫ አመክንዮ የቀዳሚውን አቋማቸውን አለሳልሰው ከምርጫ የውድድር ሜዳ በአሸናፊነት ተወጥተው “የሥልጣን ዋንጫውን” ለመጎንጨት ሲሟሟቁ ስናስተውል “ድሮውንስ ባይሸነግሉን ምን ነበረበት” በማለት እንድንታዘባቸው በር ከፍተውልናል። የፖለቲካ ታዛ መርጦ የመጠለል አቋማቸውን ማክበራችን እንደተጠበቀ ሆኖ ለምን ሲያጃጅሉን ከረሙ ብለን ቅሬታ ቢገባን አያስወቅሰንም። ለማንኛውም “የምርጫውን መንገድ ጨርቅ ያድርግላቸው” ብለን እንመርቃቸዋለን።
በምርጫው አተገባበር ዙሪያ በአንዳንድ ክልሎች ችግሮች ከፊት ለፊታችን የተራራ ያህል ገዝፈው መገሸራቸውን ስናስተውል ሥጋት እንደሚያጭርብን ብንሸሽግ አያምርብንም። ዜጎች ነንና ምርጫውን ተከትሎ “ሳይወድ ከእኛው ለተፈጠረው ትውልድ ነግ ተነግወዲያ ምን ይገጥመው ይሆን!?” እያልን ብንቃትትና ብንጨነቅ ተፈጥሯዊ ስለሆነ ሊያስወቅሰን አይገባም። እኛ ዕድሜውን ያደለን እንኳን በየዘመኑ የችግር ዲሪቶ እየደረብን መከራው ስለሞቀን ለምደነዋል። ይብላኝ እኛው በፈጠርነው ዳፋ አሳሩን እንዲበላ ለፈረድንበት ከጉልበታችን ለወጣው ትውልድ።
በውሎ አምሽቷችን የምናደምጣቸውና የምናስተውላቸው ኮምጣጣ ክስተቶችና ዜናዎችም በምርጫው አፈጻጸም ላይ መሰናክል ሆነው እንቅፋት ይፈጥሩብን ይሆን? በማለት በፍርሃት ቆፈን ብንንዘረዘርም ልንተችና “እምነተ ቢሶች” ልንባል አይገባም። እነዚህ ሁሉ ንብርብር ችግሮቻችን ምክንያት ሆነው ሥረ ነገሩ ባልተብራራ ሁኔታ እስካሁን ለምርጫው የተመዘገበው “የሕዝበ ኢትዮጵያ” ቁጥር ከተገመተው በታች ማሽቆልቆሉም ልባችን እንዲከብድ ምክንያት ሆኗል።
የተፎካካሪ ተብዬ ፓርቲዎች የአደባባይና የጎዳናዎች ላይ ቅስቀሳም “ጭር” ማለቱ “እንዴት ነው ነገሩ!?” ብለን እንድንጠይቅ ሰበብ ሆኗል። እነዚህ ሁሉ “እፍኝ ሙሉ” ችግሮች በሚስተዋሉበት ሁኔታ ተጨማሪ ግራ አጋቢ ክስተቶችም በስሜታች ላይ መርግ መጫናቸው አልቀረም። ጥቂት ማሳያዎችን ላመላክት።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ስኬት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለቅስቀሳ እንዲጠቀሙባቸው በብሮድካስቱ ሥር የሚመደቡትን የቴሌቪዥንና የሬዲዮ እና የህትመት ውጤቶችንም አክሎበት ምርጫውን ከሚያስፈጽመው ቦርድ ጋር በመቀናጀት የአየርና የጋዜጣ ዐምዶችን በመደልደል ማከፋፈሉ ይታወቃል።
ይህ ዓይነቱ አሰራር ለይስሙላም ሆነ ለምር “እንዳያማህ ጥራው፤ እንዳይበላህ ግፋው” ይሉት ብጤ ቢሆንም ባለፉት ምርጫዎችም ይደረግ እንደነበር እናስታውሳለን።
በዚህ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫም ይሄው አሰራር ተሻሽሎ መተግበሩ ተደጋግሞ ተነግሮናል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ፓርቲዎች የተሰጣቸውን የጋዜጣ ዐምድ፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ የአየር ሰዓት በአግባቡ መጠቀም ተስኗቸው ባዶ ሲሆኑ እያስተዋልን ነው።
ይህ ጸሐፊ ለዓመታት የቅርብ ቤተኛ የሆነበትና በሚያከብረው በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይም ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ሊስተናገዱ የሚችሉባቸው ዐምዶች “ይህ ቦታ…. ለተሰኘው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የተመደበ ቢሆንም ጽሑፍ ስላላቀረበ ቦታው ክፍት ሆኗል” (ለአብነት፡- አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1፣2፣3 ቀን 2013 ዓ.ም) በሚል ማስታወሻ ሁለትና ሦስት ዐምዶች እንዲሁ መለመላቸውን ቦዶ ሆነው ጋዜጦቹ እየታተሙ መሆናቸው ያሰቅቃልም ያሳፈራልም። “ተጠቃሚዎቹ መጡም አልመጡ እኛ ግን ዐምዶቹን ደልድለን ሰጥተን ነበር” በሚል ምክንያት “ከደሙ ንጹሕ መሆንን” ታሳቢ ተደርጎ ከሆነም አግባብ አይሆንም።
በሬዲዮ የአየር ሞገድም ሆነ በቴሌቪዥን መስኮቶችም እንዲሁ “የእከሌ ፓርቲ ተወካዮች ሊገኙልን ስላልቻሉ” እየተባለ ውዱ የአየር ሰዓት እየባከነ መሆኑን ማስተዋል እንደ አንድ የዘርፉ ባለሙያ ከማስቆጨትም አልፎ በእጅጉ ያስገርማል።
ይክፋም ይልማ “የሕዝብ ንብረት ናቸው” በሚል ቅጥያ የምንሸነገልባቸው የጋዜጣ ዐምዶችና የብሮድካስት የአየር ሰዓቶች በንዝህላል ፓርቲ ተብዬዎች በከንቱ ሲባክኑ ሃይ የሚላቸው ተቆጣጣሪ አካል መጥፋቱ ግራ እያጋባ ነው። ለመሆኑ አብዛኞቹ ብሔራዊ የመንግሥት ሚዲያዎች የሚተዳደሩት ርሃቡን ለማስታገስና መጠለያ ብርቅ ከሆነበት ዜጋ ጉሮሮ በግብር ስም ከሚነጠቀው ሃብት አይደለምን?
ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ፓርቲ ተብዬዎች፣ አስፈጻሚዎቹና ፈጻሚዎቹ በምን ቸገረኝነትና “እንዳፈቀደው” በሚል ዳተኝነት በሕዝብ ሃብት ማላገጣቸውን እንደ ዋዛ የሚመለከቱ ከሆነ ውሎ አድሮ “የጦሱ ዶሮ” ከደጃፋቸው ድረስ ቀርቦ መጠየቃቸው የሚቀር አይመስለንም።
ጋዜጦቹስ ቢሆኑ ገና ለገና ከተጠያቂነት ለመዳን ብለው በጥቂት ቃላት “ይህ ዐምድ የተመደበለት የፖለቲካ ፓርቲ እድሉን ሊጠቀምበት ስላልቻለ ገጹ ለሌላ ርዕሰ ጉዳይ ውሏል” ብሎ ለመጠቀም ለምን አልተቻለም? ለሬዲዮና ለቴሌቪዥኑስ ቢሆን አየሩን ከማዝረክረክ ይልቅ የመጠባበቂያ (Backlog) መያዙ አይበጅም ነበር። ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትስ ኃላፊነቱን ለመወጣት ምን እርምጃ ወስዷል? ወይም ይወስድባቸዋል? ሕዝብ መገዛት ብቻም ሳይሆን ገዢውን መሞገትም መብቱ ስለሆነ ይግባኛችን ለሚገባው ክፍል ይድረስልን።
ይህን ጸሐፊ እጅግ ከገረሙት ጉዳዮች መካከል አንዱ በቅርብ ቀናት ውስጥ አንድ ፓርቲ ለክርክር የመደባቸው ግለሰብ ለምን እዚያ የሚዲያ ማዕከል እንዳልተገኙ ኃላፊዎችን ሲጠይቅ የተሰጠው መልስ “የሰው ኃይል እጥረት ስላለብን ነው!” የሚል መልስ ነበር። አይ ፓርቲ! አይ ፖለቲካ! ሕዝብን ብቻ ሳይሆን ሚሊዮን አባላትን አፍርቻለሁ በማለት እየፎከሩና እያስፎከሩ “ሰው አጠረኝ” ማለት ሕዝብን መናቅ እንጂ ሌላ ምን ስም ይሰጠዋል። ወይንም ምክንያቱን በቅንነት እነቀበል ከተባለም እንደነዚህ ዓይነት “ፓርቲ ተብዬዎች” የተቋቋሙት በሁለትና በሦስት ግለሰቦች ስብስብ ስለሆነ “የሰው እጥረት ቢገጥማቸው አይፈረድባቸውም።
የሰሞኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርም በርካታ ጉዳዮችን እንድንታዘብ ምክንያት ሆኖናል። አንዳንድ ፓርቲ ተብዬ ተከራካሪዎች እንኳን ሕዝብን የሚመጥን ፖሊሲ ሊኖራቸው ቀርቶ ሃሳባቸውን እንኳን ወግ ባለው ቋንቋ ማስተላለፍ ተስኗቸው ሲያንቧችሩ ተመልክተን “የዴሞክራሲ ዕድገታችን” የውሃ ልክ ምን ድረስ እንደሆነ በሚገባ ተረድተናል። “የየጁ ደብተራ ቅዳሴው ሲያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት” እንዲሉ የመወዳደሪያ ፖሊሲ ድህነታቸውን በስድብና በመዘላለፍ ሲገልጡ ተመልክትን “አድሮ ቃሪያነታቸውን” በማስተዋል ተሸማቀናል።
አንዳንዱም እንኳን ለንግግሩና ለሚያስተላልፈው መልእክት ቀርቶ ለአለባበሱ እንኳን መጠንቀቅ እንዳለበት ዘንግቶ ወይንም በእብሪት ተኮፍሶ እንደተዝረከረከ የስቱዲዮውን ክብር ዝቅ በማድረግ “አረፋ እየደፈቀ” ሲፎገላ ተመልክተን ለእርሱ ወይንም ለእነርሱ እኛ አፍረናል። ይብላኝ ለሀገሬ! ይብላኝ ለምስኪኑ ሕዝብ! እንኳን ሀገርን ያህል ሸክም ይቅርና የራሱን ቤተሰብ እንኳን በወጉ መምራት የተሳነው የፖለቲካ ዋልጌ አደባባይ ላይ ወጥቶና የክብር ወንበር ተሰጥቶት “አንቱ!” እየተባለ መወደሱ ያማል፣ ይጠዘጥዛል፣ ይጓጉጣል።
የሀገሬ የፖለቲካ ካንሰር መቼና በየትኛው ትውልድ ታክሞ እንደሚፈወስ ለመገመትም ሆነ ለመተንበይ በእጅጉ ያዳግታል። የዴሞክራሲ ግብሩን ሳይሆን ስሙን አንጠልጥሎ ብቻ ሕዝብንና ሀገርን ከለላ በማድረግ ተዋርዶ ማዋረድ “ግዴለም ዴሞክራሲው ሥር ሲሰድ ችግሩ ይቀረፋል!” እየተባለ ብቻ በሽንገላ ሊታለፍ አይገባውም። በተዋረደ ማንነቱ ሕዝብንና ሀገርን የሚያዋርደውን “የፖለቲካ ቁማርተኛ” በአደባባይና በግላጭ በሕግ ይሁን በማኅበረሰቡ የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት ቅጣት ተላልፎበት ሊታረም ይገባል።
ጠቢቡ ሰለሞን በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ሲል ይመክረናል። “በሦስት ነገሮች ምክንያት [ሀገር] ትንቀጠቀጣለች፤ ልትታገስም አትችልም። እንዲያውም አራት ናቸው። ከንቱ ሰው በነገሠ ጊዜና ቦዘኔ ሲጠግብ” (ምሳሌ ምዕራፍ 30 ቁጥር 21 አዲሱ መደበኛ ትርጉምን ይመልከቱ።) ለጊዜው የጠቀስኩት ሦስቱን ሀገር አንቀጥቀጥ ምክንያቶች ዘልዬ አንደኛውንና ቀዳሚው ብቻ ነው። ካስፈለገ በይደር ያስተላለፍካቸውን ሁለቱን ወይንም ሦስቱን ጊዜው ሲፈቅድ ልመለስባቸው እችላለሁ። ነገሬን እዚሁ ላይ ልግታና በማዋዣው ክፍል የጠቀስኩትን የአለቃ ዕንባቆምን ሁለት ስንኞች ለሁለተኛ ጊዜ እንደተመቸኝ አሻሽዬ ሃሳቤን ልደምድም።
“በኢህአዴግ ዘመን የትናንቱ ዜሮ፣
ኔጌቲቭ እንዳይሆን ምርጫችን ዘንድሮ።”
አይሁንብን! አሜን! የሰላም በረከት ተመኘሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013