ራስወርቅ ሙሉጌታ
በምስራቋ ኮከብ በጸሀይ መውጫዋ ድሬዳዋ ከተማ ወይዘሮ አሰገደችን የማያውቅ አለ ማለት ዘበት ነው። ወይዘሮ አሰገደች አስፋው አንዳንድ ጊዜ በተረት ብቻ የምንሰማቸው የሚመስሉንን ደግ ስራዎች ሲያከናውኑ ያለፉትን ከአርባ ዓመታት በላይ አሳልፈዋል።
ወይዘሮ አሰገደች እንዲህ አይነቱን ምግባረ ሰናይ የጀመሩት ገና በልጅነታቸው በእናትና አባታቸው ቤት ሳሉ ነበር። በዛም ወቅት ለሳቸውና ለቤተሰብ የተዘጋጀውን ምግብ ለተራበ በማብላት የታመመን በቤት ውስጥ በማስተኛትና የእናት አባታቸውን ልብስ ሳይቀር ለተቸገሩት እየወሰዱ በማልበስ ይታወቃሉ።
ታዲያ የዚያን ጊዜ ዕብድና የኔ ቢጤ እየሰበሰብሽብን ችግር ታመጪያለሽ በሚል የማዘጋጃ ቤት ጥበቃ ይሰሩ በነበሩት አባታቸውና ሌሎች ቤተሰቦችም ቅጣት ይደርስባቸው ነበር፡፡ ባል አግብቶ ልጆች ካፈሩም በኋላ ይህንን ተግባራቸውን በመቀጠል በመኖሪያ ቤታቸው ከየቤተ-ክርስቲያኑ ደጅ የወደቁትን በመሰብሰብ በዕቃ ቤታቸው ውስጥ በማሳረፍ በመመገብ፣ የታመሙትንም ወደ ህክምና ማዕከል እየወሰዱ ሲያሳክሙ ኖረዋል፡፡
በአንድ ወቅት ሹፌር የነበሩት ባለቤታቸውን ልብስ ለተቸገረ መቸራቸውን ባለቤታቸው ያወቁት መንገድ ላይ አለኝ ያሉትን ልብስ ተመጽዋች ለብሶት ሲያዩ ነበር። በወቅቱ ከባለቤታቸው በላይ ልጆቻቸው ተበሳጭተውባቸው እንደ ነበር ያስታውሳሉ። በእምነታቸው የሚያዘክሯቸውን በዓላት አስታከው በየቤተክርስቲያኑ የወደቁትን ሲደግፉ ኑረዋል ታዲያ ወይዘሮ አሰገደች ሰው ሁሉ እኩል ነው የሚለውን መርህ ይተገብሩ ስለነበር ለእኔ ቢጤዎቹም የተረፋቸውን ሳይሆን እነሱን አስበው ለእነሱ አዘጋጅተው ይመግቡ ነበር።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ድሬዳዋ እብድ ማሰሪያ የሚባለው አካባቢ በመሄድ የተቸገሩትን ያበሉ ያጠጡም የነበረ ሲሆን እዚያ ሲሄዱ በአካባቢው ባህልና አኗኗር መሰረት ለሙስሊሙም ለክርስቲያኑም አዘጋጅተው ነበር የሚሄዱት። የመንግስትንም ችግር ይካፈሉ የነበሩት ወይዘሮ አሰገደች በአንድ ወቅት ድል ጮራ የሚባለው ሆስፒታል በገጠመው ችግር ለታካሚዎች ምግብ ማቅረብ የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ስለነበር ወይዘሮ አሰገደች በየቀኑ ያገኙትን እህል በመያዝ እጅ ያጠራቸው ጊዜ ደግሞ በሶ በጥብጠው ህመምተኞችን ይጠይቁ ነበር። እንዲህ እያደረጉ ታማሚዎችን እየተመላለሱ ሲጠይቁ ያዩት የበድል ጮራ ሆስፒታል ሰራተኞች እኚህ ሴትዮ ልጆቻቸው ውጪ አገር ሆነው የሚልኩላቸውን ገንዘብ ቁጭ ብለው እንደመብላት ለምንድን ነው እንዲህ የሚያደርጉት ይሏቸው ነበር፡፡
ታዲያ ልግስናቸው ለሚበላ ለሚጠጣው ብቻ አልነበረም መውደቂያ ያጣ ያመመውም ከመጣ በራቸውን ከፍተው ያኖሩ ነበር። ይህን ሲያደርጉ ደግሞ እሳቸው መሬት ላይ አየተኙ ነበር ይህን ያየ ዘመድም ደጋፊም ፍራሽና የሚለበስ ሲያመጣላቸውም አሳልፈው ለባሰበት ይሰጣሉ። ጎረቤቶቻቸውም ግቢውን አቆሸሹት ሰዎቹ፤ ሽታ አላቸው ወዘተ እያሉ ስራቸውን እንዲያቆሙ ደጋግመው መክረዋቸው ቢመክሯቸውም እሳቸው ግን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም።
በተለይ በአንድ ወቅት የሳንባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ ስለነበርና እሳቸው በቤታቸው ከሚያስታምሟቸው መካከል በበሽታው የተያዙ ስለነበሩ የጎረቤትም የዘመድም ስጋት አይሎ ወይዘሮ አሰገደች ላይ ጫና ቢፈጠርም እሳቸው ግን ማንንም ሳይሰሙ ስራቸውን ይቀጥላሉ። ይህም ሆኖ አንደኛዋ ልጃቸው ስትናገር የዘጠኝ ዓመት ሳለች በሣንባ ነቀርሳ ታማ ሀኪም ቤት ስትሄድ የተነገራት እቤት ውስጥ ካሉት የኔ ቢጤዎች እንደተላለፈባት ነበር፡፡ በእንደዚህ አይነት መሰዋአትነት የተጀመረው ምግባረ ሰናይ መጠናከርና ዘላቂ መሆን ስለነበረበት በአስራ ዘጠኝ ሰማኒያ ሁለት ዓ.ም «አሰገደች አስፋው ድሬዳዋና አካባቢዋ አረጋውያን መንከባከቢያና ማቆያ ማእከል» ተብሎ ለመመስረት ይበቃል።
ዛሬ የአሰገደች አስፋው ድሬዳዋና አካባቢዋ አረጋውያን መንከባከቢያና ማቆያ ማእከል ከመግቢያው ጠባብ መስሎ በሚታየው ሰፊ ግቢ ከተንበሬውን አልፈው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ከስፋቱ በላይ ለአይን ብቻ ሣይሆን ለህሊናም እረፍትን በሚያመጡ ትእይንቶች የተሞላ ለመሆን በቅቷል። በአጫጭሮቹ የበርሃ ዛፎችና የፍራፍሬ ተክሎች አቅራቢያ የሚታዩት ከብቶችና ሌሎች የቤት እንስሳት ግቢውን የበረሃ ገነት ያስመሠሉት ሲሆን በግቢው በስተቀኝና በስተግራ በተሠሩት ሰርቪስ ቤቶች በረንዳ ላይ የተሰባሰቡት አዛውንቶች ሰብሰብ፤ ሰብሰብ ብለው የሞቀ ጨዋታ ይዘዋል።
ከሁሉም ፊት ላይ የዘመን አሻራ ያረፈበት ትዝታን ወደ ኋላ የሚያስቃኝ ድባብ ይነበባል። በኮሮና ምክንያት ወደ ግቢው የሚገባውም ሆነ በግቢው ውስጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ ፍጹም ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። በስተቀኝ ከወንዶች ማደሪያ ቤት በረንዳ ላይ ከተቀመጡት መካከል ሞላ ያለ ሠውነት ያላቸውን ጠይም አባት ጠጋ ብዬ ያሉበትን ሁኔታ እንዲነግሩኝ ጠየቅኳቸው ፈቃደኛ ሆነው የሚከተለውን አጫወቱኝ።
አቶ እምሬ ባይለየኝ ይባላሉ፤ በ1933 ዓ.ም ነበር በደቡብ ጎንደር ደብረታቦር እስቴ የምትባል አካባቢ የተወለዱት። በወቅቱ እስከ ስምንተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ወደ ኤርትራ ክፍለ ሀገር በማቅናት ደቀ መሀሪ የሚባል ቦታ ላይ ለሀገራቸው ወታደራዊ አገልግሎት ሲሰጡ ይቆያሉ። ከዓመታት በኋላ የሶማሊያ ጦር በኢትዮጵያ ላይ የመጀመሪያውን ወረራ በፈጸመበት በቀዳማዊ ኃይለ ሰላሴ ዘመነ መንግስት ከሶማሊያ ጦር ጋር ገጥመው ሀገራቸውን ከወራሪ ለመታደግ ድንበራቸውን ለማስከበር በቅተዋል።
ከዛ በኋላ በሌላ ግዳጅ ላይ እያሉ በጥይት በመመታታቸው በደረሰባቸው ጉዳት ሁለተኛ በወታደርነት ለማገልገል የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠርና ጡረታቸውን በመያዝ በድሬዳዋ ከተማ የተለያዩ የግል ስራዎችን እየሰሩ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ። አቶ እምሬ ትዳር መስርተው ቤት ሰርተው ቤተሰብም አፍርተው የሰባት ልጆች አባት ለመሆን የበቁም ነበሩ። ነገር ግን ትዳራቸው ሳይሳካ ይቀርና ቤተሰባቸውም ተበትኖ እሳቸውም በጤና እክል ምክንያት ራሳቸውን ሊያስተዳድሩ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ቀን ቀንን እየወለደ ሲመጣ ደግሞ ነገሮች ሁሉ መስመር እየሳቱና እየተወሳሰቡ መጥተው የአቶ እምሬ ባይለየኝ ህይወት የሚደግፋት ካጣች መጨረሻዋ ጎዳና ለመሆን ይቃረባል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነበር የዛሬ አስራ አንድ ዓመት የእድሜያቸውን እኩሌታ አብረው ያሳለፏቸው ጎረቤታቸው ወደሆኑትና በመላው ድሬዳዋ ለተቸገረ በመድረስ ወደሚታወቁት ወይዘሮ አሰገደች ያመሩት። ወይዘሮ አሰገደችም እንኳን ለሚያውቁት በስማ በለው እከሌ ተቸግሯል የሚባል ወሬም ከሰሙ ተኝተው አያድሩምና አቶ እምሬን ሁሉን አሟልተው ቤታቸው ያስገቧቸዋል። አቶ እምሬ ያለፈውን አስራ አንድ ዓመት እንዲህ ያስታውሱታል።
«ወይዘሮ አሰገደችን ከአርባ ዓመት በላይ አውቃቸዋለሁ፤ ስራ ሲሰሩ የነበረው ሰው ለመርዳት ሳይሆን ነግዶ ለማትረፍ ይመስል ነበር፤ ራሳቸው ሲሚንቶ ያቦካሉ ድንጋይ ይሸከማሉ፤ ከብቶችን የሚንከባከቡት እሳቸው ናቸው፤ አታክልቶችን የሚንከባከቡትም እሳቸው ናቸው።
በተጨማሪ እቤት የሚሰበስቧቸውን ያበላሉ ያጠጣሉ ቤተ-ክርስቲያን የወደቁትን ሄደው ይረዳሉ፤ ቢያቁዋቸውም ባያውቋቸውም ሆስፒታል ሄደው የታመመ ይጠይቃሉ፤ ሁሌም እንቅልፍ የላቸውም። ሳቃቸው ጀምሮ ይሄ የዘወትር ስራቸው ነው ይኸው ዛሬ ደግሞ ተሳክቶላቸው እኔን ጨምሮ የብዙዎችን ስቃይ ለመታደግ እንባችንንም ለማበስ በቅተዋል፤ ይላሉ አቶ እምሬ።»
በሌላው ጎን ውሃ የሚጠጡበትን ኮዳ እያጠቡ ያገኘናቸው ወይዘሮ አድና ዘመነ ደግሞ ትውልዳቸው በወሎ ክፍለ ሀገር ሲሆን በልጅነታቸው ነበር ሀገራቸውን በመልቀቅ ኑሯቸውን ከአክስታቸው ጋር አዲስ አበባ ያደረጉት። አክስታቸው በሞት ሲለዩዋቸው ደግሞ ሌላ ዘመድ ስላልነበራቸው «የተሻለ ስራም የተሻለ ህይወትም እንሞክር» ብላ አንድ ጓደኛቸው ይዛቸው ወደ ድሬደዋ ትመጣለች። ዓመተ ምህረቱን እሳቸው በውል ባያስታውሱትም በደርግ ዘመን መሆኑን ግን ያውቃሉ። ከዛን ጊዜ አንስቶ ከቤት ሰራተኝነት ጀምሮ የቻሉትንና ያገኙትን ሁሉ ሲሰሩ ዓመታትን አሳልፈዋል።
ከአምስት ዓመት በፊት ግን ምንም ባላወቁት ሁኔታ ሁለመናቸውን ቅስፍ አድርጎ ይይዛቸውና እጃቸውም እግራቸውም አፋቸውም ይያያዛል። ይህ ከመከሰቱ ከወራት በፊት መንግስት በአካባቢ ጽዳት አደራጅቷቸው ሲሰሩ ስለነበር የቆጠቧትን ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ብር ተቀብለው ወደ አዲስ አበባ በማቅናት የረር የሚባል አካባቢ ጸበል ሲጠመቁ ቆይተው የተወሰነ መንቀሳቀስና መናገር ይጀምራሉ። ነገር ግን ጨርሶ ከመዳናቸው በፊት ብራቸው ስላለቀ የሚያውቁት ዘመድም ስላልነበራቸው ወደ ድሬዳዋ ይመለሳሉ።
ነገር ግን ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስና መናገር ቢጀምሩም ስራ መስራት የሚያስችላቸው ሁኔታ ውስጥ አልነበሩም፤ ሰው ቤት በሚሰሩበት ጊዜ ሳይታሰብ የወለዷት አንዲት ልጅ ብትኖርም በአቅም ምክንያት ልትደግፋቸው አልቻለችም። በመሆኑም ጎረቤቶቻቸው ወደ አሰገደች የአረጋውያን መጦሪያ እንዲገቡ ያደርጓቸዋል። ወይዘሮ አድና ከዛን ጊዜ አንስቶ እስካሁን በማእከሉ እየኖሩ ሲሆን ወይዘሮ አሰገደችንም እንዲህ ይገልጿቸዋል።
«ወይዘሮ አሰገደች የሚቆጡ ሰው የሚተቹ እናት አይደሉም ግን ለእኛ በማሰብ ስንመገብ አብረውን ይሆናሉ እናም አንዳንድ ጊዜ እንጀራ ለምን ታሳሳላችሁ ብለው ሰራተኞችን ይናገሩ ነበር። ልብሳችንን ንጹህ መሆኑን ሳይቀር እየዞሩ ይከታተሉ ያጸዱልንም ነበር። ከሁሉም በላይ ከወይዘሮ አሰገደች ስራ ከአእምሮዬ የማይጠፋው የፈጣሪ ስራ ሆኖ ከመካከላችን ሰው ሲያልፍ የሚገንዙት እሳቸው ብቻ ናቸው። ምንም ቢቆይ እስከ ቀበር እህል አይቀምሱም ከአስክሬኑም አይለዩም፤ በመኪና ተጭኖ ሲሄድ እንኳን ከፊት ጋቢና ግቡ ሲባሉ እሺ አይሉም አስክሬኑ አጠገብ ተቀምጠው አስቀብረው ይመለሳሉ።»
ሌላዋ ተጧሪ ወይዘሮ አሰገደች ገብሩ የተወለዱት ሂርና በምትባል ከተማ አካባቢ ነው። በልጅነታቸው አውራ ጎዳና ይሰራ የነበረ ሰው አግብተው፤ ባለቤታቸውን እየተከተሉ ኦጋዴ፤ ጎደዴ፤ ሸዋ፤ ወለጋ ኑረዋል። በዚህ ግዜም ሁለት ልጆችን ለማፍራት የበቁ ቢሆንም አንደኛው ልጃቸው ገና በህጻንነቱ ያለፈ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ካደገና ውትድርና ዘምቶ ከመጣ በኋላ ታሞ ሞቶባቸዋል። ባላቸውንም ልጆቻቸውንም ካጡ በኋላ ራሳቸውን ያስተዳድሩ የነበረው የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን በተለይ ብዙውን ጊዜ እንጀራ በመጋገር ነበር።
ከጊዜ በኋላ ግን እያመማቸው ይመጣና እንጀራ መጋገሩም እየከበዳቸው ቤት ኪራይ የሚከፈለውም የሚበላውም እየታጣ ሲመጣ መንገድ ላይ ያገኙትን ሰው ጠይቀው ወደ አሰገደች የአረጋውያን መጦሪያ ያቀናሉ። ወይዘሮ አሰገደችም እንደመጡ «ሞክሼዬ» በማለት ተቀብለው ያስገቧቸውና ኑሯቸውን ይጀምራሉ። ትንሽ ከቆዩና ካረፉ በኋላ ደግሞ ጤናቸው ፋታ ሲሰጣቸው ወይዘሮ አሰገደች «ይሄ መቼም ብመጣ በሩ የማይዘጋብኝ ቤቴ ነው ለምን ወጣ ብዬ አቅሜ እስከፈቀደ አልሰራም» ብለው ለወይዘሮ አሰገደች ይነግሩና ወጥተው ስራ አፈላልገው መስራት ይጀምራሉ።
ሁኔታዎች ይሳኩላቸውና ለዘጠኝ ዓመታትም የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ ራሳቸውን ችለው ከቆዩ በኋላ አቅማቸው እየደከመና እያመማቸው ሲመጣ የማይዘጋውን በር በማስከፈት ተመልሰው የወይዘሮ አሰገደችን የአረጋውያን መጦሪያ ተቀላቅለው አሁን ሶስተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል።
በተመሳሳይ ወይዘሮ ሮማን ታደሰ ትውልዳቸው ሂርና የምትባል ከተማ ሲሆን በልጅነታቸው ጀምሮ ይኖሩ የነበረው ግን በድሬዳዋ ከተማ ከቤት ሰራተኝነት ጀምሮ የተለያዩ የጉልበት ስራ በመስራት ነበር። ከዛሬ አስራ አራት ዓመት በፊት ነበር አንድ አይናቸውን እንደ ቀልድ ያማቸውና እየፈዘዘች የሚያዩትን ሁሉ እየጋረደቻቸው መምጣት ትጀምራለች። ወደ ህክምናው ቢሄዱም ሳይሳካ ይቀርና ውላ ስታድር ደግሞ ጭራሽ ትጠፋለች። በአቅማቸው ሀክምና ሲከታተሉ ቢቆዩም ሳይሳካ ይቀርና ከጊዜ በኋላ አንደኛዋም አይናቸው መድከም ትጀምርና ከጊዜ በኋላ እሷም ስራዋን ታቆማለች።
ከዚህ በኋላ ሙሉ አካል ይዞም ይከብድ የነበረው ህይወት ለወይዘሮ ሮማን ጭራሽ የተወሳሰበ ይሆናል፤ እናም መጨረሻቸውን በወይዘሮ አሰገደች አረጋውያን ማቆያ ለማድረግ ይገደዳሉ። ወይዘሮ ሮማን እዚህ ባይገቡ ኖሩ ይገጥማቸው የነበረውን ነገር እንዲህ ይገለጹታል። «ፈጣሪ ይመስገን ዓመት ሁለት ዓመት አልሰነብትም ያልኩት ዛሬ አስራ አራት ዓመት አድርጌያለሁ፤ የአንድ ልጅ እድሜ ማለት ነው። ወይዘሮ አሰገደች ባይኖሩ አይን የለኝ የሚመራኝ የለ፤ ለምኜ ልብላ ብለም አይሆንልኝም፤ እዚህ ባልመጣ ኖሮ ርቦኝ ወይንም ታምሜ መሞቴ አይቀርም ነበር። የምበላው ባላጣ እንኳን አንድ ቀን ምን አልባትም የጅብ ራት እሆን ነበር።»
እኛ ለምልከታችን ያህል እነዚህን አነሳን እንጂ የወይዘሮ አሰገደች ግቢ በርካታ የሀገር ባለውለታዎችን በእንክብካቤ አቅፎ የሚገኝ ማእከል ነው። አረጋውያኑም በየአጋጣሚው ለወይዘሮ አሰገደች ብቻ ሳይሆን የእሳቸውን ፈለግ ተከትለው አየተንከባከቧቸው ላሉ ልጆቻቸውም ረጅም እድሜን ሲለምኑ ይውላሉ።
ልጃቸው ኤልሳቤጥ መኮንን ያለፉትን ሰላሳ ሁለት ዓመታት በውጪ ሀገር ከኖረች በኋላ ወደ ሀገሯ ስትመለስ ያልጠበቀችው ነገር ይገጥማታል፤ ወትሮም የተቸገረ ይሰበስቡ የነበሩት እናቷ በርካታ አዛውንቶችን የጤና እክል ያለባቸውን ጨምሮ ሰብስበው ሲኖሩ ታገኛቸዋለች። የሚበሉት አይለይም፣ የሚጠጡት አይለይም፣ የሚተኙት መሬት ላይ ከእርሳቸው ጋር ነበር። እናም በጣም አዝና ነገሮችን ለማስተካከል ብትሞክርም ሳይሳካ ይቀራል።
በተመሳሳይ ሌላዋ ልጃቸው ወይዘሮ እመቤት መኮንን ከውጪ መጥታ ያለውን ነገር ትመለከትና ድሮ በወጣትነትሽ እየሩሳሌም ሄደሽ መሳለም ትፈልጊ ነበር፤ አሁን እኔ ጋር ካናዳ ልውሰድሽና በዛው እየሩሳሌም ተሳልመሽ ትመለሺያለሽ ይሏቸዋል። እሳቸውም እየሩሳሌምን ስመኝ የነበረው ያኔ ነበር፤ ዛሬ ያለሁት ገነት ውስጥ ነው፤ ይህንን ትቼ የትም አልሄድም ይሏታል። ነገሩን ላይመለሱ እንደ ጀመሩት የተረዱት ልጆቻቸው ዛሬ ከጎናቸው በመሆን በግቢያቸው ለገቢ ማስገኛና ለሌሎች አገልግሎቶችም የሚውል ባለ አራት ወለል ህንጻ እያሰሩላቸው ይገኛሉ። ወይዘሮ እመቤት በአሁኑ ወቅት ከአስራ አምስት ዓመት በላይ የኖሩበትን የካናዳ ኑሯቸውን ትተው ድሬዳዋ በመከተም እናታቸውንም አረጋውያኑንም በመንከባከብ ላይ ይገኛሉ።
እድሜያቸውን አንዴ ዘጠና አንዴ ሰማኒያ የሚሉት ወይዘሮ አሰገደች የሶስት ሴትና የሁለት ወንዶች እናት ሲሆኑ ለሰሩት በጎ ስራ ከተሰጧቸው በርካታ እውቅናዎች መካከል የመጀመሪያ የክብር ዲግሪያቸውን ከአለማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛውን የክብር ዶክትሬት ደግሞ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸው ይጠቀሳል። የእሳቸውን ፈለግ የተከተሉ የከተማዋ ተማሪዎች በየወቅቱ እየመጡ ለአረጋውያኑ የሚያደርጉት እንክብካቤ ለሌሎችም ትልቅ አርአያ የሚሆን ነው።
ወይዘሮ አሰገደች ዛሬ እንደ ድሮው ተሯሩጠው ሰማኒያ የሚደርሱትን አረጋውያን የሚቀልቡበት ብሎም ሃያ በየቤታቸው ተቀምጠው የእሳቸውን ድጋፍ የሚጠብቁና በርካታ ተመላላሽ የምግብ አገልግሎት የሚሰጣቸውን የሚንከባከቡበት አቅም የላቸውም። ይህም ሆኖ ሁሌም ከአንደበታቸው የማትለይ ምክር አዘል ምርቃታቸውን ለመጣው ሁሉ እንዲህ በማለት ያደርሳሉ። «ለሀገራችን ሠላም ይስጥልን፣ ከስደት ያድነን፣ ኢትዮጵያ ሀገራችን እኮ ሀብታም ነች፤ እኛ ግን ሥራ አንሰራም፤ ሰነፍ ነን እንጂ
ይላሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013