ዳግም ከበደ
በአገራችን ባህል “ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ” ይባላል። አባቶቻችን ይህን ሲሉ ምክንያት ነበራቸው። አንድም ሃሳብና ትችትን እንዲያው በደረቁ ከመሰንዘር ይልቅ እያዋዙ በጨዋታና በተለያዩ አዝናኝ ምሳሌዎች ለማስረዳት ባላቸው ብልሃት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሥነ ሥርዓትን አዋቂነትን፣ ባህልና ወግ ጠባቂነትን ስለሚያመላክት ነው።
ስለምሳሌና ነገር ላወራ አስቤ አይደለም ይህን ማለቴ። ላቀርብ የፈለኩትን ሃሳብና ትችት በዚህ ወግ መሰረት ለማቅረብ ወድጄ ነው በማረፊያ አምድ ላይ የተከሰትኩት። እስቲ አንድ ታሪክ ላጋራችሁ። ጥሞናችሁ አይለየኝ!
ይህ ታሪክ አንድ አባትና ልጅ ያደረጉትን አስደሳች ውይይት ይተርክልናል። ልጅ አባቱን ከራሱ አስበልጦ ይወዳል። የአባት ወጉም አይደል! ልጅም ምንም ሲያስፈልጋት የአባቷን እርዳታ ትጠይቃለች። በእርሱ ጥበቃና ጥላ ስር ህይወትን ታጣጥማለች። ደግና ክፉውን ትለያለች።
ታዲያ አንድ ወቅት ላይ ልጅ የአባቷን ድጋፍ ፈለገች። ተጨንቃ ነበር። በእርሷ አቅምና ብልሃት የማይፈታ ጉዳይ ገጠማት። እንግዲያውስ ምን ገዷት የገጠማት እንቅፋት ምንም ከባድ ቢሆን አባት አንድ መላ አያጣም። እርሱ ዘንድ ቀረበች። እንዲህም ስትል የልብ መጨነቋንና መፍትሄ መሻቷን አስረዳችው።
“አባቴ ሁልጊዜ የሚያጋጥመኝን ችግር መቋቋም አልቻልኩም። አንዱን ፈታሁት ስል ሌላኛው መጥቶ ድቅን ይላል፤ ለዚህኛውም መፍትሄ አገኘሁለት ስል ደግሞ ያልታሰበ ሌላ ፈተና ይገጥመኛል። አሁንስ ትክት ብሎኛል። ህይወት እየከበደኝ ነው። ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም” አለችው።
አባት በልጁ መጨነቅ ቢያዝንም አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት ማድረግ እንዳለበት ገብቶታል። አንድ ልጁ የህይወት ፈተናን እንዴት መቋቋም እንደሚኖርባት ክህሎቱን ማስተማር አለበት። በህይወት ውስጥ ሁሌም ፈተና አለ ታዲያ ፈተናውን ለማለፍ የምንወስደው እርምጃን የማወቅና ያለማወቅ ጉዳይ ነው ዋናው። አባትም ይሄ ስለገባው በምሳሌ ልጁን በቀላል መንገድ ማስረዳት ጀመረ።
አባት ልጁን በመኖሪያ ቤቱ በሚገኝ የምግብ ማብሰያ ክፍል ይዟት ሄደ። ይህ ሰው በሙያው ምግብ አብሳይ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ አስደናቂ ነገርና የህይወት ልምድን አግኝቷል አሁን ደግሞ ልጁን ይህን ጥበቡን ሊያስተምራት ፈልጓል።
አባት በሶስት ድስቶች ውስጥ ውሃ ሞልቶ ሁሉንም በተለያየ ምድጃ ላይ ጣዳቸው። ከፍተኛ እሳት እንዲነድባቸውም አደረገ። ልጁ ይህን ሁኔታ በጥሞና እንድትከታተል ነገራት። ውሃው መፍላት ሲጀምር በአንደኛው ድስት ውስጥ ድኝች በሁለተኛው እንቁላል በሶስተኛው ላይ ደግሞ የቡና ዱቄት ጨመረባቸው። ልጅ ሁኔታውን በግርምት እየተከታተለች ነው። አባቷ ምን ሊያሳያት እየሞከረ እንደሆነ ግን አልገባትም ነበር።
ይህ ሂደት ለሃያ ደቂቃ ቀጠለ። የተጣዱት ድኝችና እንቁላል በሚገባ አበሰላቸው። ቡናውንም እንዲሁ በሚገባ አፈላው። ይህን ሲረዳ አባት እሳቱን አጠፋው። ድንቹን እና እንቁላሉን ከፈላው ውሃ ውስጥ አውጥቶ ሰሃን ላይ አስቀመጠ። ቡናውን ደግሞ በብርጭቆ ቀድቶ አስቀመጠ። የሚሆነውን ለመመልከት ልጅቷ ጉጉቷ በእጅጉ ጨመረ።
አባት ስራውን እንደ ጨረሰ ወደ ልጁ ዞሮ “አሁን በዚህ ጠረጴዛ ላይ ምን ትመለከቻለሽ” ሲል ጠየቃት። ልጅም እንቁላል፣ ድኝችና ቡና ስትል መለሰችለት። አባትም “በደንብ ቀረብ ብለሽ ተመልከች” ሲል በድጋሚ እያየች ያለችውን ነገር ጠየቃት። ድንቹንም እንድትነካው አዘዛት። ቡናውንም እንድትጠጣው ፣ እንቁላሉንም ሰብራው ውስጡ ያለውን እንድታወጣው አደረገ። ድንቹ ሙክክ ብሎ በስሏል። እንቁላሉም በደንብ በስሏል። ቡናውም ፈልቷል።
ልጅ ግን በሁኔታው ግራ ተጋባች እንጂ አባት ሊያስረዳት ያሰበው ነገር አልገባትም። በዚህ ጊዜ “ምንድነው? ምንም አልገባኝም” ስትል ሁኔታውን ግልፅ እንዲያደርግላት፣ እሷ እያጋጠማት ካለው ችግር ጋር ምን እንደሚያገናኘውም ጠየቀችው።
አባት ልጁ ከዚህ በላይ ግራ እንድትጋባ አልፈለገም። ስለ ጉዳዩ ያስረዳት ጀመረ። “ልጄ እንደምታይው ሶስቱንም ነገሮች በተመሳሳይ የፈላ ውሃ ውስጥ ከተናቸው ነበር። ሶስቱም ግን በዚህ ፈታኝ የፈላ ውሃ ውስጥ ሲገቡ ያሳዩት ባህሪ የተለያየ ነው። ድንቹ መጀመሪያ ጠንካራና ለመፈርከስ የሚያስቸግር ነበር። የፈላ ውሃ ውስጥ ሲገባ ግን ሙክክ ብሎ በሰለ ፤ በቀላሉ የሚፈረካከስ ሆነ።
እንቁላሉ ምንም እንኳን በቅርፊት ቢከለልም ፈሳሽ ነበር። በተመሳሳይ በዚህ የፈላ ውሃ ውስጥ ሲገባ ፈሳሽነቱ ቀርቶ ይበልጥ ጠንካራ ሆነ።
ቡናውም እንደምታይው ነው፤ በዚህ በከፍተኛ ሁኔታ የፈላ ውሃ ውስጥ ስንከተው የውሃውን መልክ ቀይሮ የራሱን መልክ እንዲይዝ አደረገው” አላት። ሁኔታውን ሲያብራራላትም ይበልጥ እየተገለጠላት መጣ፤ ተገረመች።
አባት ቀጠለናም “ ልጄ ታዲያ ከድንቹ፣ ከእንቁላሉና ከቡናው አንቺ የትኛውን ነው መሆን የምትፈልጊው? ልጅ በመገረም ለመናገር እንኳን ቃል አጠራት። በላይዋ ላይ አድሮ የነበረው ጭንቀትና ችግር ብን ብሎ ሲጠፋ ታወቃት።
በዚህ ጊዜ አባት መልሶ “በህይወት ውስጥ ችግር፣ ፈተና፣ እንቅፋት የማይጠፉና ሁሌም የሚኖሩ ነገሮች ናቸው። እነርሱን የምንፈታበትንና የምንጋፈጥበትን መንገድ መፈለግ ግን ዋናው ቁልፍ መሳሪያ ነው። ስለዚህ ልጄ ማንኛውም ፈተና ሲገጥምሽ እንደ ድንቹ ሙሽሽ አትበይ፤ ይልቁኑ እንደ እንቁላሉ ይበልጥ ፈተናው እያጠነከረሽ ይሂድ። እንደ ቡናው ችግርሽን በራስሽ ፍላጎት መልኩን ቀይሪው። በምትፈልጊው መንገድ አስኪጂው” በማለት ፈታላት ፤ይህን በማድረግም ልጁን ታላቅ የህይወት መርህና ጥበብ አስታጠቃት።
ታዲያ እኛስ አሁን እየገጠሙን ባሉ የግል፣ የማህበረሰብ፣ የህዝብ እንዲሁም የአገር ችግሮች የትኛውን መሆን ነው ያለብን? እንቁላሉን፣ ድንቹን ወይስ ቡናውን? ኢትዮጵያን ሀገራችንን ክፉዎችና ራስ ወዳዶች እያደረሱባት ካለው ጥፋት በብልሃትና በፅናት አንድ ሆነን በመቆም እንታደጋት። ይሄን የምናደርገው ግን ፅናትን እንደ እንቁላሉ፣ ብልሃትን እንደ ቡናው ተላብሰን ይሁን። እኔም ሃተታ ምሳሌዬን እዚህ ላይ ልደምድም። ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይባርክ። ሰላም !
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013