ግርማ መንግሥቴ
የአፍሪካ ጉዳይ በተለያዩ ጎኖቹ ታሪኩ ብዙ ነው። ከነጮች ቅርምት እስከ በአፓርታይድ መገዛት፤ ከመሀይምነት እስከ ኋላ ቀርነት፤ የተፈጥሮ ሀብትን ከመታደል እስከ መጠቀም አለመቻል፤ ከአምባገነኖች መፈልፈያነት እስከ ሙሰኞች መቀፍቀፊያነት (በ2018 የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ “አፍሪካ በሙስና በዓመት 148 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች” ተብሎ መገለፁን፤ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የጥናት ግኝቱን “ተስፋ የሚያስቆርጥ” እንደሆነ መግለፁን ያስታውሷል)፤ ከሰላምና ደህንነት መታጣት እስከ የእርስ በእርስ መተላለቅ፤ ከፍልሰት እስከ ስደት፤ ከመሰረተ ልማት እጥረት እስከ ቴክኖሎጂ ድርቀት፤ ከስራ አጥነት እስከ ነፍስ ወከፍ ገቢ ድቀት ወዘተ ወዘተ ድረስ ተቆጥሮ የማያልቅ ብሶትና መከራ፤ ግዞትና ሰቆቃ ያለበት አህጉር ነው።
እነዚህና ሌሎች እዚህ ያልጠቀስናቸው በርካታ ስር የሰደዱ ችግሮች ምንጭ ደግሞ (የባእዳኑ እጅ እንዳለ ሆኖ) እራሳቸው አፍሪካዊያን፤ በተለይም ከበፊት እስከ አሁኑ 21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ያሉትና እየተፈራረቁ የገዙት መሪዎች ሲሆኑ ህዝቡም እነዚህን አምባገነኖች ዞር በሉ፤ በቃችሁ ማለት እየተገባው ተሸክሞ በመኖሩ ለችግሮቹ ከተጠያቂነት አያመልጥም።
በተለያዩ ዓለም አቀፍ እውቅና ባላቸው አፍሪካዊያን የተጠናውና በ2010 ለህትመት የበቃው፤ በ2011 በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ በነፃም የተሰራጨው SHARED VALUES, CONSTITUTINALISM AND DEMOCRACY IN AFRICA መጽሐፍ (በተለይም በፕሮፌሰር Crlson Anyagwe የቀረበው ምእራፍ 2) የአፍሪካን ጓዳ ጎድጓዳ፤ ጓጥ ስርጓጉጥ ሁሉ ፈትሾ ችግሮቿን አይን ከሰበከት እያገላበጠ ያሳየ በመሆኑ እሱን መመልከቱ በእጅግ ጠቃሚ ነው።
አፍሪካ ከላይ በነካካናቸውና መሰል ችግሮች ትታወቅ እንጂ የዛኑም ያህል ተጠቃሽ ስኬቶች አሏት፤ አንዱም ከነጭ አገዛዝ ነፃ መውጣቷና የአፓርታይድ አገዛዝን መገርሰሷ ነው። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ደግሞ የዲፕሎማሲው ጉዳይ አለና እሱን ከታላቋ ሩሲያ አንፃር እንመለከታለን።
የቀድሞውን በእግረ መንገድ እናድርገውና ከ2019 ጀምሮ፤ ማለትም ከተቋረጠ ከዘመናት በኋሏ በፕሬዝዳንት ፑቲን አሳሳቢነትና ጥሪ መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በ2019 በሩሲያዋ ታሪካዊት ከተማ (ሶሺ) የመጀመሪያው (“First ever Russia-Africa Summit”) ውይይት አካሄዱ፤ ዓመቱም “The year of 2019 is the Year of Africa in Russia” ተብሎ የክብር መዝገብ ቦታውን ያዘ። በውይይቱም የሩሲያው ፑቲን ተገኙ።
በንግግራቸውም አፍሪካ የፖለቲካም ሆነ ሌለ ተፅእኖ ንክች እንደማያደርጋት ቃል ገቡ፤ ለዚህም ጠንክረው በጋራ እንደሚሰሩ ተናገሩ። ተጨበጨበ – ኮምጨጭ እንዳሉ። ሰላምና ፀጥታን የተመለከተና 13 ነጥቦችን የያዘ የመግባቢያ ሰነድ (MOU) ም ተፈራረሙ። ሂደቱም በበርካታ አስተያየት ሰጪዎች ከቻይና ቀጥሎ . . . (ወይም ጎን ለጎን) መሆኑ ከበቂ በላይ ተተነተኑ፤ ጉዳዩ በርካታ አስተያየቶችንም አስተናገደ። ሁለተኛው ጉባኤም በማርች 24 – 25 2021 ይካሄድ ዘንድ አፅድቀው ተለያዩ፤ ተካሄደ። ከወዲያኛው ዓለም በኩል ጉዳዩ የጎሪጥ ቢታይም።
ሩሲያና አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ያላቸውን ፍላጎት በተመለከተ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች በርካታ ቢሆኑም በምእራቡ ዓለም የሚናፈሰው የሩሲያ ፍላጎት ሀይል (ሀይድርፓወር)ና ተፅእኖ መፍጠር፤ የአሜሪካ ፍላጎት ደግሞ በአህጉሩ ዲሞክራሲን ለመገንባት፣ ሰላምና ብልፅግናን ለማምጣት መሆኑን የሚሰብኩ ሲሆን አንዱም የPAUL STRONSKI አስተያየት ነው።
በሌላ በኩል በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በቀናነት የሚያዩና መልካምነቱን የሚያመላክቱ ወገኖች “በጋራ እሴት ላይ የተመሰረተ” በማለት ያወደሱት ሲሆን እሴቶቹ (በተለይ Afro-optimism እና Afro-intellectualism)ንም በጋራ ተግባራዊ ለማድረግ ማሰባቸውን ያሳያል በማለት ያስረዳሉ።
አስቀድሞም ከአፍሪካ ጋር በቅርብ በመስራት የምትታወቀው ሩሲያ በኮንጎ ዲሞክራቲክ፤ ምዕራብ ሳራዊ፤ ኮትዲቯር፤ ደቡብ ሱዳንና ሊቢያ የሰላም አስከባሪ ሀይል በመላክም የማትረሳ ሲሆን በተለያዩ የአፍሪካ አገራትም የአዲስ አበባውን “ፑሽኪን” መሰል የባህል ተቋማት አሏት።
ሩሲያን ከተቀሩት ለየት የሚያደርጋት “ለአፍሪካዊያን አጀንዳ አፍሪካዊ መፍትሄ ነው የሚያስፈልገው” በሚል ጠንካራና ያልተዛነፈ አቋሟ ያፀናች መሆኗ ሲሆን፤ ይህም ልክ እንደ ቻይና ሁሉ ትጋቷ ለአፍሪካ አጋርነትና የጋራ ጥቅም እንጂ ግለኝነት እንዳልሆነ መስካሪዎች ብዙ ናቸው።
በዓለማችን ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛ ትልቋ የጦር መስሪያ አቀራቢ የሆነችው፤ እስከዛሬ ከአፍሪካ ሀገራት ጋራ ከ20 በላይ (በ2019 የተገኘ መረጃ ነው) የሚሆኑ የጦር ስምምነት ህብረት ፊርማ ያላት ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ግንኙነቷ እንደገና (“ተፈረካከሰች” ከተባለ ወዲህ) ለማደስ ስታስብና የአፍሪካ መሪዎችንም ስታማክር ያገኘችው መልስ ተቀባይነት ከማግኘቱም በላይ ዛሬ ከአንድም ሁለተኛ ጉባኤያቸውን አካሂደው በሁለተኛው የጋራ ጉባኤም ተሳታፊዎች ከ800 ቢሊዮን ሩብል በላይ የሚያስፈልጋቸውን ከ50 በላይ ስምምነቶችን በመፈራረም አጠናቀዋል።
ይህ በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሳይቀር ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን ያገኘው የሩሲያ-አፍሪካ ዳግም ወዳጅነት (ህዳሴ) በነፃ ገበያ አራማጆች ዘንድ “ተወዷል/ አልተወደደም” የሚለው እራሱን የቻለና ሌላ ጊዜን የሚጠይቅ ሲሆን የአፍሪካ-ሩሲያ ግንኙነት ግን ለአፍሪካ ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ስለመሆኑ ብዙዎች ከሚሰጡት አስተያየት መረዳት ይቻላል። በቅርቡ የተካሄደው የሩሲያና አፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጉባኤ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቪዲዮ ያስተላለፉት መልእክትም ይህንኑ በደማቁ ከስሩ የሚያሰምር ነው።
የቀድሞዋ ራሽያ ፌዴሬሽን የአሁና ሩሲያ አፍሪካዊያን ለነፃነት ሲያደርጉ የነበሩትን ትግል በመደገፍ (በኢትዮ ሶማሌ ጦርነትም ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም) ያበረከተችው አስተዋጽኦ በአብዛኛው አፍሪካዊ ልብ ውስጥ ተፅፏል።
በበርካታ ምሁራንም ሆነ ጥናቶች እንደሚስማሙት ለአፍሪካ ፍቱን መድኃኒት ልማታዊ መንግስትና የሶሻሊስት (ኮሙዩኒዝም) አስተሳሰብ (ርእዮት) ናቸው። ለዚህ ደግሞ የሚያቀርቧቸው ማስረጃዎች አህጉሪቷ በተለያዩ የችግር ማጦች ውስጥ ተዘፍቃ የምትገኝ ሲሆን ከዚህ ማጥ ውስጥ ለመውጣትም ሆነ ያሉባትን ችግሮች ለማራገፍ የሚያስችላት በርካታ የትግል ስልቶችንና አማራጭ ሀሳቦችን፤ እንዲሁም መፍትሄዎችን የሚያመላክተው የማርክስ ንድፈ ሀሳብና ፍልስፍና እንጂ የደልቃቆቹ ኒዮ ሊበራሊዝም (ካፒታሊዝም) አይደለም የሚል ነው። የፈጠራ/ኪነጥበብ ስራዎች ሳይቀሩ አፍሪካን ቀስፎ ከያዛት ውስብስብ ችግር የምትወጣበትን አቅጣጫና መፍትሄ ማሳየት እንጂ እንደደላቸው አገራት ዳንኪራ ላይ ማተኮር አይገባቸውም። ከዚህ አንፃር የሩሶ-አፍሪካ ስምምነትም ሆነ አብሮ የመስራት ፍላጎት መኖር ለሁለቱም በተለይም ለአፍሪካ መልካም እድልና ጥሩ አጋጣሚ ሂደቱንም “ህዳሴ” ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013