
በየሱፍ እንድሪስ
አዲስ አበባ- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ዝግጅት ላይ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ከሚጠበቅባቸው ኃላፊነት አንፃር አነስተኛ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ገለፁ።
መልካም አስተዳደር ለአፍሪካ-ምስራቅ አፍሪካ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ዘሪሁን ሙሐመድ ፣ ቀጣዩ ምርጫ ከሃገር አቀፍ አልፎ በቀጠናው እና በአህጉር ደረጃ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ኩነት ነው ።
ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል መጥፎ አጋጣሚን ለመቀነስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ያሉትዶክተር ዘሪሁን ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ከፍተኛ የሆነ አቅም እንዳላቸው የገለፁት ኃላፊው ፣ይህንን አቅማቸውንም መጠቀም እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጅማ ደሊቦ በበኩላቸው ፤አዲሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ከፀደቀ በኋላ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንደጨመረ ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ በምርጫ ሂደቱ ላይ የተለየ ተሳትፎ እያደረጉ ባለመሆኑ በቀጣይ ቀሪ ጊዜያት አቅማቸውን በማጠናከር እና ሕግን መሠረት በማድረግ ተሳትፏቸውን እንዲያሻሽሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከምርጫ ጋር በተያያዘ የስራ ፈቃድ ወስደው ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ያረጋገጡት ዳይሬክተሩ፤ መሰረታዊ የሚባሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስነ ምግባርን እየተከታተሉ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል።
በውይይቱ ከተገኙ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር
ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፣ በዚህ ምርጫ ሂደት አብዛኞች የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ የሚጠይቁ በመሆናቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፏቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።
የጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ቁጥር ዝቅተኛ በመሆኑ የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቱን እና የመራጮች ምዝገባ ላይ
ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ከወዲሁ ለማስቀረት ወይም ከተከሰቱ በኋላ የጉዳት መጠንን ለመቀነስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከወዲሁ አቅማቸውን ማጠናከር እንዳሚገባቸውም አሳስበዋል።
ከዚህ ቀደም ከምርጫ ጋር ተያይዞ በተከሰቱ ችግሮች ምን ያህል የሰው ሕይወት እንደጠፋ እናውቃለን።
የተረጋጋች ሀገር እና የተሻለ ዴሞክራሲ ለመገንባት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ እና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያለው ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
መድረኩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በቀጣዩ ምርጫ ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና እና የአጋር አካላት ተሳትፎ በሚል የተካሄደ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013