ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
በተለያየ ጽሑፌ ላይ ስለ ህይወትና ሰውነት አውርቻችኋለሁ። ወደዚህ ዓለም ለአንድ ጊዜ መጥተናል..በማይደገም ህላዊ ውስጥ ነን ስል ነግሬአችኋለው። በማስተዋልና በጥበብ እንጂ በዘልማድ የሚመራ የህይወት ቅንጣት እንደሌለ ይሄንንም ሹክ ብያችኋለሁ። ታዲያ ለኮሮና የሚሆን እውቀት ስለምን አጣችሁ? ኮቪድ ሲገድለን፣ ብዙ አገራዊ ኪሳራዎችን ሲያደርስብን ምነው ዝም አላችሁ? ለመከላከል የሚሆን የጥንቃቄ እውቀት ስለምን አጣችሁ? የዓለም ሕዝብ ግራ በተጋባበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት ላይ ቆመን፣ በዚህ እጅግ አስፈሪ በሆነ የሞት ጊዜ ላይ ሆነን መዘናጋታችንና እየሆንን ያለነው ነገር ግራ ግብት ቢለኝ ስትሞቱ ላለማየት ስል ዳግመኛ ብዕሬን ከልሙጥ ሉኬ ጋር ሞሽሬ መጣሁ።
ቆይ ለእናንተ ህይወት ማለት ምን ማለት ነው? መኖር ማለት ትርጉሙ ምንድን ነው? ስለምን ለህይወታችሁ ዋጋ መስጠት አቃታችሁ? ስለምን ዓይናችሁ እያየ ወደ ሞት መሄድን መረጣችሁ? ቆይ ምን እየሆንን ነው? ቸልተኝነታችን ዋጋ እያስከፈለን ነው። የፈራነው ደርሷል..በሩቅ የሰማነው..አውሮፓና እስያ መንደር ሲሆን ያየነው ዛሬ ቤታችን እየገባ ነው። የቧልታችንን..የቸልተኝነታችንን ፍሬ እየበላን ነው። ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሽታው እያጠቃን ይገኛል። በየቀኑ ብዙ ሞትና ሰምተን የማናውቀውን የተጠቂ ቁጥር እያደመጥን ነው። በጣም የሚገርመው ደግሞ ዛሬም ድረስ ከእንቅልፋችን አለመንቃታችን ነው። በጣም የሚገርመው ደግሞ ዛሬም ድረስ በሽታው እንደሌለ ማሰባችን ነው። በጣም የሚገርመው እየሞትን፣ እየታመምን ያለ መፍትሔ ቆመን ለበሽታው አጋላጭ በሆነ መንገድ ላይ መገኘታችን ነው። ቆይ መቼ ነው የሚገባን? ቆይ መቼ ነው በእውቀትና በማስተዋል የምንኖረው?
የምታውቁትን ነው የምነግራችሁ፣ ከራሴ የጨመርኩት አንዳች ነገር የለም…አሁን ላይ በሽታው ከመስፋፋቱም በተጨማሪ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ላይ ብዙዎችን እያጠቃ ይገኛል። ለብዙዎችም ስጋትና ፍርሀት ሆኖ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በመሰራጨት ላይ ነው። የሟቾችን ቁጥር ለመስማት ጆሮአችንን ከማቆም ባለፈ በሽታውን ለመግታት ምንም አይነት ጥረት ስናደርግ አንታይም። ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ የተለያዩ የክልል ከተሞችን የማየት እድል ገጥሞኝ ነበር። ያየሁት ነገር ግን እጅግ የሚያስደነግጥ ነገር ነው። የአፍና የፊት መሸፈኛ የሚያደርግ አንድም ሰው የለም። አንድ ጊዜ አንድ ጓደኛዬ ምናለኝ መሰላችሁ ከአዲስ አበባ ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች ለሥራም ሆነ ቤተሰብ ጥየቃ ስሄድ ከተማው ውስጥ ማስክ አድርጌ የምታየው እኔ ብቻ ነኝ ብሎኝ ነበር። እውነቱን ነው፤ ትላልቅ የክልል ከተሞች ላይ ሄዳችሁ መታዘብ ትችላላችሁ፤ አብዛኛው ሰው ማስክ አያደርግም። አብዛኛው ሰው እየሞተ በግዴለሽነት ህይወቱን መግፋት መርጧል ። በእርግጠኝነት እነግራችኋለሁ ኮሮናን በመከላከል ማህበረሰባችን እያደረገ ያለው ጥረት በጣም ውስን ነው። ሁላችንም ጆሮ ዳባ ብለን አጋላጭ በሆነ መንገድ የምንቀሳቀስ ነን።
ከአዲስ አበባ ከተማ በቀር አብዛኞቹ የክልል ከተሞች በሽታውን በመከላከል እያሳዩ ያሉት ትብብር ደካማ ነው። ቆይ ስልጣኔ ምንድነው? መማር..ማወቅ ጥቅሙ ምንድነው? ማወቅ እኮ መለወጥ ነው፣ ሥልጣኔ እኮ የባህሪ ለውጥ ማምጣት ነው። ማወቃችን..መማራችን ለህይወታችን ካልበጀ እውቀታችን ትርጉም አለው ብዬ አላስብም። ብዙዎች እንደ ቅጠል ሲረግፉ እያየንና እየሰማን አሸወይና ማለታችን ሊገባኝ አልቻለም። የምንወዳቸውን በሞት እየተነጠቅን፣ እዛም እዚም ሀዘን በዝቶ እያየን የእኛ መዘናጋት ከየት የመጣ እንደሆነ እንጃ። ለአንድ ጊዜ ብቻ እኮ ነው ሰው የሆንነው..ድጋሚ እኮ በሰውነት ወደዚህ ዓለም አንመጣም ።እንዴት ለአንድ ራሳችን ማሰብና መሆን ያቅተናል። ስለምን በቀላሉ በምንከላከለው በሽታ ውድ ህይወታችንን እናጣለን። በየቀኑ..የሞትና የመከራ ዜና እየሰማን እንኳን አንለወጥም። ትንሹንና ቀላሉን የመከላከያ ዘዴ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንኳን አናደርግም። ከመንግሥት ባለስልጣናት ጀምሮ እስከ ታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ድረስ ተቃቅፎ የሚሄድ ነው። አንዳንድ ሰዎችና ሳይ ግርም ይለኛል…ከግዴለሽነታቸው ብዛት በሽታውን ለመከላከል ሳይሆን ለማሰራጨት ሆን ብለው የሚንቀሳቀሱ ነው የሚመስሉት። ሁላችሁም እንደምታውቁት የበሽታው ባህሪ አንድና ሁለት ሰው በተጠነቀቀ የሚሆን አይደለም፤ በሽታውን ለመቆጣጠር የሁላችንም ጥንቃቄ ወሳኝነት አለው። እናትና አባት ተጠንቅቀው ልጆች የማይጠነቀቁ ከሆነ ዋጋ የለውም። በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በመዝናኛ ቦታ በሁሉም የህይወት መስክ ላይ የጋራ ጥንቃቄ ያሻናል። አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው ግዴለሽ ሰዎች አሉ…ለራሳቸውም ለሌሎችም ግድ የማይሰጣቸው፣በራሳቸውም በሌሎች ህይወት ላይም የሚቀልዱ ።
ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለብን ኮሮና ለአንድ ዓመት ያክል አሰቃይቶናል፣ በህይወታችን ድጋሚ እንዲመጣ የማንፈልገውን ክፉ ጊዜ አሳልፈናል። አሁን ግን ካሳለፍንው ሁሉ በከፋ ሁኔታ የምንጎዳበት ጊዜ ላይ ነን። ይሄ እንዳይሆን የሁላችንም የጋራ ድምጽ፣ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል። ከላይ እንዳልኳችሁ በመንግስት ጥረት ብቻ፣ በታዋቂ ሰዎች ጩኸት ብቻ የሚቆም አይደለም። አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ኮሮናን ለመዋጋት በጋራ የምንቆምበት ጊዜ ነው። ብዙ የሞት መርዶዎችን እየሰማን ነው። ብዙ አስደንጋጭ ነገሮችን እያየን ነው። ከትላንት ይልቅ ዛሬ የከፋ ነው። ከዚህ የባሰ እንዳይመጣብን ራሳችን ለራሳችን አስተማሪዎች እንሁን። ማስክ አድርጉ ተብለን የምንገደድበት ጊዜ አልፏል። እጃችሁን ታጠቡ፣ ርቀታችሁን ጠብቁ የምንባልበት ጊዜ ላይ አይደለንም ።ሁላችንም በጋራ የምንተጋበት ሰዓት ላይ ነን። ጎልቶ የሚሰማ ድምጽ የለም ።ሁላችንም በሽታውን ለመከላከል መጮህና ዘብ መቆም አለብን። የትላንት ቀልዳችን ዛሬ ላይ ውድ ዋጋ እያስከፈለን ነው።
ቆይ ከሞት ወዲያ ምን ሊያስተምረን ነው? የሚሞተውን የታማሚ ቁጥር፣ የሚያዘውን የሰው አኀዝ እያየንና እየሰማን ከዚህ በላይ እኛን ለማስተማር ምን ሊመጣ ይችላል? ነው ወይስ ካልሞትን አናምንም ነው? እርግጥ ነው የብዙዎቻችን አስተሳሰብ እንደዛ ነው.. ባይሆንማ እየሆነ ያለው ሞትና መከራ እኛን ለማስተማርና ለመለወጥ ከበቂ በላይ ነበር። ባይሆንማ ወዳጆቻችንን ከጎናችን እያጣን ባልተሳለቅን ነበር። ብታምኑም ባታምኑም በኮሮና ለመሞትም ሆነ በሽታውን ለመከላከል የመጨረሻው ሰዓት ላይ እንገኛለን። በዚህ ሰዓት ላይ ወረርሽኙን ለመከላከል በጋራ ከመቆም ባለፈ የምናደርገው እውቀት ላይ ያልተመሰረተ ነገር ይዞን ነው የሚጠፋው። ለመሞትም ሆነ ለመዳን ትክክለኛው ጊዜ ላይ ነን። በቀልዳችን የምንቀጥል ከሆነ እመኑኝ ከእንግዲህ ነገ የለንም። ራዕያችንን ውሀ ይበላዋል..ከህልማችን ሳንገናኝ እንቀራለን። ደግሜ እላችኋለሁ ለመሞትም ሆነ በህይወት ለመቆየት ጊዜው አሁን ነው። መንግስትን መስማት በዚህ ሰዓት ነው። ከጤና ጥበቃ የሚወጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተግባራዊ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን።
በዚሁ ከቀጠልን ነገን ማሰብ ፈራሁ…የእያንዳንዳችን ነገ ዛሬ በምናደርገው የጥንቃቄ ልክ የተቀመረ ነው። ምንም ሰበብ አያስፈልገውም ፤የተጠነቀቀ ይተርፋል ያልተጠነቀቀ ደግሞ የእጁን ያገኛል፤ ይሄ እንዳይሆን የሁላችንም ኃላፊነት ያስፈልጋል። ከጥንቃቄ አንጻር ኃላፊነት የጎደላቸውን ብዙ ሰዎችን ለመታዘብ ችያለሁ። በጣም እኮ ነው የሚገርመው…ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰው እየሞተና እየተያዘ ጥንቃቄያችን ግን የወረት ነው። በፊት የሽማግሌ በሽታ ነው እንል ነበር ፤እንዳይደለና ብዙ ወጣቶችን እንደገደለ እያወቅንም እንኳን ግዴለሾች ነን። በነገራችን ላይ በአሁኑ ሰዓት እየተያዙና ህይወታቸውን እያጡ የሚገኙት ወጣቶች ናቸው። ይሄን ደግሞ ወደ ኮቪድ ማዕከላት ጎራ በማለት ማረጋገጥ ትችላላችሁ። ወጣት አይዝም ስንል ኖረን በምትኩ የበሽታው ሰለባ ወጣቶች እየሆኑ ነው። በሽታው ዘር፤ ቀለም የማይለይ የሰውን ልጅ ሁሉ የሚያጠቃ ስለመሆኑ ከኔ በላይ እውቀቱ አላችሁ ብዬ አምናለሁ። በየቀኑ የምንሰማቸው የሞት ዜናዎች ማህበረሰቡን እንዲጠነቀቅ እያደረገው አይደለም። ለጥንቃቄ ከማበርታት ይልቅ ቀልድ እየመሰሉን የመጡበት ሁኔታ ነው ያለው። በሞት ካልፈራን በሌላ በምን እንደምንፈራ አላውቅም።በፊት ባለማወቅ ነው አሁን ግን ተነግሮናል ፤ተምረናል፤ ለአንድ አመት ያክል ተሰቃይተንበታል ፤ታዲያ ስለምን ትላንትን ለመድገም እንሽታለን።
ስለበሽታው መሰረት አልባ የሆኑ በርካታ አሉባልታዎችን ሰምተናል እየሰማንም ነው። መንግስት ያመጣው የሚመስላቸው አሉ። የፖለቲካ ጨዋታ ነው ኮሮና የሚባል የለም የሚሉም አድምጫለሁ..እያደመጥኩም ነው። ጉንፋን ነው..በትኩስ ነገር እናባርረዋለን…ኢትዮጵያውያንን አይዝም የሚሉ እጅግ የተሳሳቱ በዚህ ዘመን ከሚኖር ዘመነኛ ወጣት የማይጠበቁ የውሸት ወሬዎችን ከትላንት እስከዛሬ ሰምተናል በመስማት ላይም እንገኛለን። እውነቱ ግን ለሁላችሁም ግልጽ ነው። ኮሮና ከትላንት እስከዛሬ ድረስ ብዙዎችን ያስጨነቀ፣ ኃያላንን ያዋረደ በሽታ ነው። አይደለም ለእንደኛ አይነቶቹ ድሀ ሀገራት ቀርቶ በኢኮኖሚ አቅማቸው ከምድር አልፈው ጨረቃ ላይ ለወጡት እንኳን ራስ ምታት ከሆነ እነሆ አንድ አመት አልፎታል። ዛሬም እያስጨነቀ ነው ብዙዎች በበሽታው ሕይወታቸውን አጥተዋል። ብዙዎችም በከባድ ስቃይ ህክምና ላይ ናቸው። በእውቀት እንጂ በአሉባልታ የሚሸነፍ በሽታ አይደለም።
መጀመሪያ በሽታው ወደ ሀገራችን ሲገባ የነበረው የጥንቃቄ ሁኔታ መመለስ አለበት። በወጣን በገባን ቁጥር ማስክና ሳኒታይዘር የምንይዝበት፣ ርቀታችንን ጠብቀን በታላቅ ጥንቃቄ የምንቀሳቀስበት ያጊዜ ዳግመኛ መምጣት አለበት እላለሁ። ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈሪ ጊዜ ላይ ነን ። አይደለም ቀልደን ተጠንቅቀን እንኳን በማንወጣበት እጅግ አስፈሪ የወረርሽኝ ጊዜ ላይ ነን። ነጋችንን እናይ ዘንድ መኖር አለብን። የምንኖረው ደግሞ በጥንቃቄአችን ሞትን ማሸነፍ ስንችል ብቻ ነው።
ይሄን እየጻፍኩ ባለሁበት ማለዳ ላይ የሰማሁት የሞትና የተያዥ ቁጥር እውነት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው የሆነብኝ። ባለንበት ቦታ ሁሉ ጥንቃቄ ያስፈልገናል። ኮሮና አሁንም እየገደለ ነው..ከመቼውም ጊዜ በላይ እያስጨነቀን ነው። በመኖርና ባለመኖር ቀጭን መስመር ላይ እንገኛለን። ቀልድና ቧልት ጊዜ አልፎባቸዋል። ዛሬ በትላንት የተበላሸ ቀናችንን መልካም ለማድረግ የምንበረታበት ሰዓት ነው። ነገን መልካም ለማድረግ መጠንቀቅ አለብን። ህልማችንን ለማሳካት በጤንነት መኖር አለብን። በተገኘው መድኃኒት ተስፋ ቢኖረንም ብዙ ባለጸጋና ራስ ወዳድ ሀገራት ባሉበት ሁኔታ መድኃኒቱን ገዝቶ ወደ ሀገር ማስገባት ለድሀ ሀገር እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነው። በጊዜ ሂደት ነገሮች መልካም እስኪሆኑ ድረስ አማራጫችን መጠንቀቅ ብቻ ነው። የምንማረው፣ የምንሰራው፣ የምንለፋው ነገን ብሩህ ለማድረግ አይደል? በልባችን ውስጥ ብዙ ተስፋዎች አሉ፣ ከዛሬ የተሻሉ ነገዎችን የምንጠብቅ ብዙዎች ነን። ወልደን ከብደን ጥሩ ቤተሰብ ለማፍራት የምንመኝም ብዙዎች ነን ሁሉም የሚሆነው ግን ጤንነት ሲኖር ነው። ጤና ከሌለን ያለን ሁሉ አይጠቅመንም። ህልም ፤ራዕይ ያለ ጤና ምንም ነው። የልባችሁን ፍሬ ትበሉ ዘንድ ራሳችሁን ከኮሮና ወረርሽኝ ጠብቁ። ህልማችሁን ኮሮና እንዳይነጥቃችሁ በታላቅ ጥንቃቄ ተራመዱ። የእናተ እንዝህላልነት ለሌሎች እንዳይተርፍ ስትኖሩ ሌሎችን እያሰባችሁ ይሁን። ይሄን ክፉና አስጨናቂ ጊዜ በጋራ እናልፍ ዘንድ የሁላችንም ጥንቃቄ ወሳኝ እንደሆነ በማሳሰብ ላብቃ። ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 8/2013